የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w97 6/1 ገጽ 29-31
  • የአምላክ ቃል ተማሪዎችን ማስመረቅ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የአምላክ ቃል ተማሪዎችን ማስመረቅ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ለአዲሶቹ ሚስዮናውያን የተሰጠ ወቅታዊ ማበረታቻ
  • ቃለ ምልልሶች
  • ከጎበዝ ተማሪነት ወደ ውጤታማ ሚስዮናዊነት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • “እውነተኛ ሚስዮናውያን” የሆኑት የጊልያድ ምሩቃን
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • የፈቃደኝነት መንፈስ ለጊልያድ ያበቃል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • ጊልያድ ሚስዮናውያንን ‘እስከ ምድር ዳር ድረስ’ ይልካል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
w97 6/1 ገጽ 29-31

የአምላክ ቃል ተማሪዎችን ማስመረቅ

የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ የሚታወቁት እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ከበር ወደ በር እየሄዱ በመስበካቸው ነው። ጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የ102ኛ ክፍል ተማሪዎቹን ሲያስመርቅ በቀረበው የመግቢያ ንግግር ላይ ይህ ሥራ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል።

የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል የሆነው አልበርት ሽሮደር መጋቢት 1, 1997 በተከናወነው በዚህ ፕሮግራም ላይ በቅርቡ ለ ፑወ በተባለው የፈረንሳይኛ ጋዜጣ ላይ የወጣውን አንድ ርዕስ ጠቅሶ ነበር። ጋዜጣው የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ኢጣልያ ውስጥ ከቤት ወደ ቤት ሄዶ ለመስበክ ስላወጣችው ዕቅድ ዘግቧል። ጋዜጣው እንዲህ ይላል:- “[የቫቲካን ሚስዮናውያን] በይሖዋ ምሥክሮች መስክ ገብተው ሲሠሩ ወንጌሉን ከበር ወደ በር ‘በማዳረስ’ በኩል ከተካኑት [የይሖዋ ምሥክሮች] ጋር መገናኘታቸው ስለማይቀር ባዶ እጃቸውን እንዳይሄዱ ስትል ቫቲካን የቅዱስ ማርቆስን ወንጌል እስከ አንድ ሚልዮን ቅጂዎች ድረስ አሳትማለች።”

አርባ ስምንቱ ተመራቂዎች ኢየሱስ የአምላክን ቃል ለማሠራጨት የተጠቀመባቸውን የተዋጣላቸው የስብከት ዘዴዎች የተከተሉ ሰዎች ናቸው። በፓተርሰን ኒው ዮርክ ወደሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል የመጡት ከስምንት የተለያዩ አገሮች ነው። በትምህርት ቤቱ ባሳለፏቸው አምስት ወራት መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር አጥንተዋል። የወሰዱት ኮርስ የአምላክን ድርጅት ታሪክና የሚስዮናውያንን ሕይወት አንዳንድ ተግባራዊ ገጽታዎች እንዲሁም የአምላክን መንፈስ ፍሬዎች የሚዳስስ ነበር። የዚህ ሁሉ ትምህርት ዓላማው አንድ ነው፤ ይኸውም በሚላኩባቸው 17 አገሮች ውስጥ ለሚጠብቃቸው የሚስዮናዊነት ሥራ እነርሱን ማዘጋጀት ነበር። በተመረቁበት ወቅት 5,015 የሚያክሉ ከየአገሩ የተውጣጡ አድማጮች የደስታው ተካፋዮች ሆነዋል። እነዚህ የጊልያድ ተማሪዎች በመጨረሻ ምን ተግባራዊ ምክር ተሰጥቷቸው ይሆን?

ለአዲሶቹ ሚስዮናውያን የተሰጠ ወቅታዊ ማበረታቻ

ከሊቀ መንበሩ የመክፈቻ ንግግር ቀጥሎ የአስተዳደር አካል ፐርሶኔል ኮሚቴ ረዳት ሆኖ የሚያገለግለው ራልፍ ዎልስ ለአዲሶቹ ሚስዮናውያን የሚሆን ተግባራዊ ምክር ያዘለውን የመጀመሪያውን አጠር ያለ ንግግር አቀረበ። ጭብጡ “አፍቃሪ መሆንን አትዘንጉ” የሚል ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ በ2 ጢሞቴዎስ ምዕራፍ 3 ላይ ዓለም እያደር ፍቅር የለሽ እየሆነ እንደሚሄድ አስቀድሞ እንደተናገረ ገለጸ። ከዚያም በ1 ቆሮንቶስ 13:​1-7 ላይ ፍቅርን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መግለጫ በማስመርኮዝ ለአዲሶቹ ሚስዮናውያን የሚከተለውን ወቅታዊ ማሳሰቢያ ሰጥቷል:- “ሚስዮናውያን እንደመሆናችሁ መጠን ከሚፈለግባችሁ የሰዓት ግብ በላይ ታገለግሉ ይሆናል። ከጊልያድ ሥልጠናችሁ ያካበታችሁት ከፍተኛ እውቀት ይኖራችሁ ይሆናል። ወይም በተመደብንበት የቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በቅንዓት ትርፍ ሰዓት ሳይቀር እናገለግል ይሆናል። ይሁን እንጂ አፍቃሪ መሆንን ከዘነጋን ይህ ሁሉ ጥረታችንና የምንከፍለው መሥዋዕትነት ሁሉ ከንቱ ነው።”

በመቀጠል “ይሖዋ ወደ ድል እየመራን ነው” የሚል ጭብጥ ይዞ የቀረበው የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ካሪ ባርበር ነበር። ይሖዋ የታመኑ አገልጋዮቹን በዚያ ሁሉ ስደት መሐል ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከነበራቸው አነስተኛ ጅምር አንስቶ የመንግሥቱን ምሥራች በማወጅ ረገድ ለድል አብቅቷቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ (ይህ በዚያን ጊዜ የሚታወቁበት መጠሪያ ነበር) በ1931 የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን ስም መጠቀም የጀመሩ ሲሆን ይህ ለሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት የግር እሳት ሆኖባቸዋል። ወንድም ባርበር “ከጊልያድ ሰልጥነው የወጡ የ102ኛው ክፍል ሚስዮናውያን የተቻለውን ያህል ብዙ ሰዎች ስለዚህ ቅዱስ ስም ማወቅ የሚችሉበትን አጋጣሚ በመስጠት በኩል ከፍተኛ ድርሻ የሚያበረክቱበት ታላቅ መብት ከፊታቸው ተዘርግቷል” ሲል ተናገረ። እነዚህ ተመራቂዎች የአምላክን ቃል የመስበኩ ሥራ በ1943 ከነበረበት ከ54 አገሮች ዛሬ ወደ 233 አገሮች እንዲያድግ ከረዱት በጊልያድ ትምህርት ቤት ሠልጥነው የወጡ 7,131 ሚስዮናውያን ጋር ይቀላቀላሉ።

የሚቀጥለው ተናጋሪ የአስተዳደር አካል አባል የሆነውና ከ11ኛው የጊልያድ ክፍል ተመርቆ በጃፓን ለ25 ዓመታት በሚስዮናዊነት ያገለገለው ወንድም ሎይድ ባሪ ነበር። ‘በእነዚህ ነገሮች ጽኑ’ የሚል ጭብጥ ያለው ማበረታቻ ሰጥቷል። “ደስታ ማግኘታችሁ በአብዛኛው የተመካው በምታሳዩት ጽናት ላይ ነው” ሲል ለተማሪዎቹ ተናግሯል። በሚስዮናዊነት ሥራም ሆነ በማንኛውም ቲኦክራሲያዊ የሥራ ምድብ በመጽናት የሚገኘው ወሮታ ምንድን ነው? “በመጀመሪያ ደረጃ መጽናታችን የይሖዋን ልብ ደስ ያሰኛል። . . . በፈተና ወቅት ጽኑ አቋም ይዘን መገኘታችን ከፍተኛ እርካታ ያመጣልናል። . . . የሚስዮናዊነት አገልግሎታችሁን የዕድሜ ልክ ሥራችሁ አድርጋችሁ ያዙት . . . ‘መልካም’ አደረጋችሁ የሚል ሞቅ ያለ ምስጋና ያስገኝላችኋል።” (ማቴዎስ 25:​21፤ ምሳሌ 27:​11) ወንድም ባሪ በንግግሩ መደምደሚያ ላይ የሚስዮናዊነት አገልግሎት መላ ሕይወታቸው እንዲሆን ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ ‘በእነዚህ ነገሮች እንዲጸኑ’ ለአዲሶቹ ሚስዮናውያን ልባዊ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።​— 1 ጢሞቴዎስ 4:​16

ብዙ የጊልያድ ክፍሎችን በማስተማር የተካፈለው ካርል አዳምስ ያቀረበው ጥያቄ “ዓይናችሁ የሚያርፈው ምን ላይ ይሆን?” የሚል ነበር። ሚስዮናውያኑ በምድብ ቦታቸው የሚያዩት ነገር በሰብዓዊ ዓይናቸው ላይ ብቻ ሳይሆን በልባቸውም ዓይን ጭምር የተመካ እንደሆነ ተናገረ። (ኤፌሶን 1:​18) ይህንንም እስራኤላውያኑ ሰላዮች የተስፋይቱን ምድር ሲገመግሙ ያዩትን ነገር በምሳሌነት በመጥቀስ አስረድቷል። ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር 12ቱም ሰላዮች ያዩት ተመሳሳይ ነገር ነበር፤ ይሁን እንጂ የተስፋይቱን ምድር በአምላክ ዓይን ያዩት ሁለቱ ሰዎች ብቻ ነበሩ። ሚስዮናውያንም ነገሮችን በተለያየ ዓይን ሊመለከቱ ይችላሉ። በሚያገለግሉባቸው አንዳንድ አገሮች ውስጥ ድህነት፣ ሕመምና ተስፋቢስነት ያጋጥማቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ አሉታዊ አስተሳሰብ ብቻ በመያዝ ምድባቸውን ጥለው መሄድ የለባቸውም። ወንድም አዳምስ በቅርቡ ከተመረቁት ክፍሎች መካከል በአንዱ ውስጥ የነበረች ሚስዮናዊት “እነዚህ ተሞክሮዎች እዚሁ መቆየት እንዳለብኝ አስገንዝበውኛል። እነዚህ ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ አንድ ተስፋ መጨበጥ ያስፈልጋቸዋል። ሕይወታቸው እንዲሻሻል ልረዳቸው እፈልጋለሁ” ስትል እንደተናገረች ጠቅሷል። ወንድም አዳምስ አዲሶቹ ሚስዮናውያን የሚመደቡበትን አገር ይሖዋ ወደፊት የሚያመጣው ምድር አቀፍ ገነት አካል ሊያደርገው እንዳሰበ አድርገው እንዲያዩትና ሰዎቹንም የአዲሱ ዓለም ኅብረተሰብ እጩ አባላት እንደሆኑ አድርገው እንዲመለከቱአቸው በማበረታታት ንግግሩን ደምድሟል።

የዚህኛውን ክፍል የመጨረሻ ንግግር ያቀረበው የጊልያድ አስተማሪ ከመሆኑ በፊት በሚስዮናዊነት ለበርካታ ዓመታት ያገለገለው ዋላስ ሊቨራንስ ነበር። ጭብጡ “የአምላክን ድንቅ ሥራዎች እያስተዋላችሁ ተመላለሱ” የሚል ነበር። በማስተዋል መመላለስ በብልህነት፣ በጥበብና በተፈጥሮ እውቀት መመላለስን ይጠይቃል። የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሳኦል የተሳነው ነገር ይህ ነበር።​— 1 ሳሙኤል 13:​9-13፤ 15:​1-22

በማስተዋል መመላለሳችንን ከምናሳይበት መንገድ አንዱ ከአዲስ ዓይነት አኗኗር ጋር ራስን ማስተካከል የሚያስከትለውን ፈታኝ ሁኔታ መቀበል ሲሆን ይህም አዲስ ቋንቋ መማርና ከሕዝቦቹ ጋር መተዋወቅን ይጨምራል። ኢያሱና ካሌብ አምላክ የሰጣቸውን ምድር ድል አድርገው በያዙ ጊዜ ብርታት እንዳገኙ ሁሉ ሚስዮናውያንም ፈታኝ ሁኔታዎችን በመጋፈጥና እንቅፋቶችን በመወጣት ረገድ የሚያገኙት ተሞክሮ መንፈሳዊ ጥንካሬ ይሰጣቸዋል።

ቃለ ምልልሶች

ተከታዩ የፕሮግራሙ ክፍል ደግሞ ተከታታይ ቃለ ምልልሶችን ያካተተ ነበር። ሃሮልድ ጃክሰን የጊልያድ ትምህርት ቤት ሬጂስትራር እንዲሁም አስተማሪ ሆኖ ለረጅም ጊዜ ካገለገለውና የ85 ዓመት ዕድሜ ካለው ከዩሊሰስ ግላስ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል። አሁንም በመስኩ የተሠማሩት ብዙ ሚስዮናውያን ትምህርትና ሥልጠና በመስጠት በታማኝነት ያሳለፋቸውን ዓመታት ያስታውሳሉ። በመቀጠልም ቀደም ሲል ከአገሩ ውጭ በአፍሪካ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ያገለገለው የጊልያድ አስተማሪ ማርክ ኒውሜር መጣ። በአምስቱ ወር የትምህርት ወቅት ስላከናወኑት አገልግሎት ከተማሪዎች ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል። የተናገሯቸው ተሞክሮዎች በዚያ አካባቢ አሁንም ለአምላክ ቃል ፍላጎት ያላቸው ሰዎች እንዳሉ በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው።

ከዚያም ሮበርት ሲራንኮና ቻርልስ ሞሎሃን ለቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት በፓተርሰን እየተሰጠ ባለው ኮርስ ላይ ለመካፈል ከመጡት ተሞክሮ ያላቸው ወንዶች ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። ለተመራቂው ክፍል የሰጡት ምክር ትሑት የመሆንንና ለጉባኤው አንድነት አስተዋጽኦ የማድረግን አስፈላጊነት ያካተተ ነበር። ተመራቂዎቹ በሚስዮናዊነት ሥራቸው ምን እንደሚገጥማቸው አስቀድመው ከመደምደም ይልቅ የሚያጋጥማቸውን ነገር ሁሉ ለመቀበል ፈቃደኛ እንዲሆኑ ተናግረዋል። አዲሶቹ ሚስዮናውያን ይህንን ምክር ሥራ ላይ ማዋላቸው የአምላክ ቃል አስተማሪዎች የመሆን ሥራቸውን ለመፈጸም እንደሚረዳቸው ምንም አያጠራጥርም።

በመጨረሻም የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ቴዎዶር ጃራዝ “ምን በማን ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው?” በሚል ርዕስ ለአድማጮች ንግግር አቅርቧል። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን የአምላክን መንፈስ ፍሬዎች ስናንጸባርቅ በሌሎች ላይ በጎ ተጽእኖ እንደምናሳድር ገልጿል። “የይሖዋ ድርጅት የላካቸው ሚስዮናውያን በሰዎች ላይ በመንፈሳዊ ነገሮች ረገድ በጎ ተጽዕኖ በማሳደር በኩል የሚያስመሰግን ውጤት አስመዝግበዋል” ሲል ተናገረ። በመቀጠልም የሚስዮናውያን መልካም ምሳሌነት አምላክን እንዲያገለግሉ የረዳቸው ሰዎች የሰነዘሯቸውን አንዳንድ አስተያየቶች ጠቅሷል። “የይሖዋ ሕዝቦች ያተረፉትን ስም የምታንጸባርቁና በተመደባችሁበት ቦታ ምሥራቹ የሚገባቸውን ሰዎች ለማግኘት ማንኳኳታችሁን የምትቀጥሉ ያድርጋችሁ። . . . ትክክለኛና ንጹህ በሆነው አኗኗራችሁ የዓለምን መንፈስ ተቋቋሙ፤ ለይሖዋ ውዳሴና ክብር በሚያመጣ መንገድ በሌሎች ላይ በጎ ተጽዕኖ የምታሳድሩ ሁኑ” በማለት ንግግሩን ደመደመ።

በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ላይ ሊቀ መንበሩ ከቅርብና ከሩቅ የተገኙትን ሰላምታዎች ከተናገረ በኋላ ዲፕሎማዎችን በመስጠት ሚስዮናውያኑ የተመደቡባቸውን ቦታዎች ተናግሯል። ከዚያም ከተመራቂዎቹ መካከል አንዱ ክፍሉ ላገኘው ትምህርት ያቀረበውን ምስጋና የሚገልጽ ደብዳቤ አነበበ። የ102ኛው ክፍል የምረቃ ፕሮግራም በዚያ የተገኙት ሁሉ የአምላክን ቃል በማወጅ ረገድ ከበፊቱ የበለጠ ቆራጥ አቋም እንዲኖራቸው እንዳደረገ ምንም ጥርጥር የለውም።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የተመረቁ የ102ኛው ክፍል ተማሪዎች

ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ለእያንዳንዱ ረድፍ ተራ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደ ኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው።

(1) ደፊ ሲ፣ አሌክሲስ ዲ፣ ሃርፍ አር፣ ሊ ጄ፣ ኮሪ ቪ፣ ኖርተም ቲ፣ ሞራ ኤን፣ ጆርኔት ኤፍ (2) ዩፕቪክ ኤል፣ ሲንግ ኬ፣ ሃርት ቢ፣ ከርኮርያን ኤም፣ ሊ ኤስ፣ ራስተል ኤስ፣ ዙለን ኬ፣ ኮሌት ኬ (3) ሲንግ ዲ፣ ፒትሉ ጄ፣ ፒትሉ ኤፍ፣ ቦኮክ ኤን፣ ቶርመ ሲ፣ መስሎ ኤ፣ ሪቻርድሰን ሲ፣ ኖርተም ዲ (4) ሃርፍ ጄ፣ ጆርኔት ኬ፣ ባርበር ኤ፣ ሎቤርቶ ጄ፣ ሎቤርቶ አር፣ መስሎ ኤም፣ ሞራ አር፣ ሃርት ኤም፣ (5) ቶርመ ኤስ፣ ራስተል ኤ፣ ዲያዝ አር፣ ዲያዝ ኤች፣ ዋይዘር ኤም፣ ዋይዘር ጄ፣ ከርኮርያን ጂ፣ ዙለን ኤ (6) አሌክሲስ አር፣ ባርበር ዲ፣ ዩፕቪክ ኤች፣ ደፊ ሲ፣ ኮሌት ቲ፣ ሪቻርድሰን ኤም፣ ቦኮክ ኤስ፣ ኮሪ ጂ፣

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ