አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈስ አነሳሽነት ያስጻፈው እንዴት ነው?
የመገናኛው መስክ ከየትኛውም የታሪክ ወቅት ይበልጥ ዛሬ አስገራሚ ደረጃ ላይ ደርሷል። ስልክ፣ የፋክስ መሣሪያዎችና ኮምፒዩተሮች ተፈልስፈዋል፤ ከዓመታት በፊት በየትኛውም የምድር ክፍል ለሚኖሩ ሰዎች ቅጽበታዊ በሆነ መንገድ መልእክት ማስተላለፍ የሚቻልበት ጊዜ ይመጣል ብሎ የሚያስብ ማን ነበር?
ይሁን እንጂ ከዚህ ሁሉ ይበልጥ አስገራሚ የሆነውን የመገናኛ ዘዴ ሰው ሊደርስበት አይችልም፤ ይህም በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት መልእክት ማስተላለፍ የሚቻልበት መንገድ ነው። ይሖዋ በጽሑፍ የሰፈረውን ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ለማዘጋጀት 40 የሚያክሉ ሰዎች በእርሱ መንፈስ አነሳሽነት እንዲጽፉ አድርጓል። ሰዎች ብዙ የመገናኛ ዘዴዎች እንዳሏቸው ሁሉ ይሖዋም ቅዱሳን ጽሑፎችን በመንፈስ አነሳሽነት ለማስጻፍ በርካታ ዘዴዎችን ተጠቅሟል።
የቃል ጽሕፈት። አምላክ ከጊዜ በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገብ ውስጥ የሰፈሩትን የተወሰኑ መልእክቶች ቀጥተኛ በሆነ መንገድ አስተላልፏል።a ለምሳሌ ያህል በሕጉ ቃል ኪዳን ውስጥ የተካተቱትን መመሪያዎች ተመልከት። ይሖዋ ለሙሴ “በእነዚህ ቃሎች መጠን ከአንተና ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና እነዚህን ቃሎች ጻፍ” ብሎታል። (ዘጸአት 34:27) ‘በመላእክት አማካኝነት የተላለፉትን’ እነዚያን ‘ቃላት’ የገለበጠው ሙሴ ሲሆን ዛሬ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዘጸአት፣ በዘሌዋውያን፣ በዘኁልቁና በዘዳግም መጻሕፍት ውስጥ ተመዝግበው ይገኛሉ።— ሥራ 7:53
ኢሳይያስን፣ ኤርምያስን፣ ሕዝቅኤልን፣ አሞጽን፣ ናሆምንና ሚክያስን ጨምሮ ሌሎች ብዙ ነቢያት በመላእክት አማካኝነት ስለተወሰነ ነገር የሚገልጹ መልእክቶችን ከአምላክ ተቀብለዋል። እነዚህ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ መልእክታቸውን “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” በሚል ሐረግ ጀምረዋል። (ኢሳይያስ 37:6፤ ኤርምያስ 2:2፤ ሕዝቅኤል 11:5፤ አሞጽ 1:3፤ ሚክያስ 2:3፤ ናሆም 1:12) ከዚያም አምላክ የተናገረውን ነገር በጽሑፍ ያሰፍራሉ።
ራእይ፣ ሕልምና ተመስጦ። ራእይ አንድ ሰው ሳያንቀላፋ ነቅቶ እያለ ባልተለመደ መንገድ ወደ አእምሮው የሚመጣለት ሐሳብ፣ ምስል፣ ወይም መልእክት ነው። ለምሳሌ ያህል ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ “ነቅተው” እያሉ ኢየሱስ በተዓምራዊ ሁኔታ የተለወጠበትን ራእይ ተመልክተዋል። (ሉቃስ 9:28-36፤ 2 ጴጥሮስ 1:16-21) አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በሕልም ወይም በሌሊት ራእይ አማካኝነት ተቀባዩ ሰው አንቀላፍቶ እያለ መልእክቱ በግለሰቡ ውስጠ ሕሊና ይቀረጻል። በዚህ ምክንያት ዳንኤል “የራሴ ራእይ በአልጋዬ ላይ” ሲል ጽፏል፤ ወይም ተርጓሚው ሮናልድ ኤ. ኖክስ እንዳስቀመጡት “ተኝቼ በሕልም ስመለከት” ብሏል።— ዳንኤል 4:10
ይሖዋ ተመስጦ ውስጥ ያስገባው ሰው ምንም እንኳ በከፊል ንቁ ቢሆንም በጣም በሐሳብ ይዋጣል። (ከሥራ 10:9-16 ጋር አወዳድር።) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ተመስጦ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል (ኤክስታሲስ) ትርጉሙ ‘ማስወጣት ወይም ቦታን ማስለቀቅ’ ማለት ነው። አእምሮ ከነበረበት የተለመደ ሁኔታ ወጣ እንዲል ማድረግ የሚል መልእክት ያስተላልፋል። በመሆኑም በተመስጦ ውስጥ ያለ ሰው ራእይውን ሲቀበል በዙሪያው ያለውን ነገር ሙሉ በሙሉ ይረሳል። ሐዋርያው ጳውሎስም ‘ወደ ገነት የተነጠቀውና ሰውም ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውንም ቃል የሰማው’ በእንዲህ ዓይነት ተመስጦ ውስጥ ሆኖ ሳይሆን አይቀርም።— 2 ቆሮንቶስ 12:2-4
ከአምላክ በቃል መልእክት ተቀብለው ካሰፈሩት ሰዎች በተቃራኒ ራእይ ወይም ሕልም ያዩት አለዚያም በተመስጦ አማካኝነት መልእክት የተቀበሉት ሰዎች ያዩትን ነገር በራሳቸው አባባል ለመግለጽ የተወሰነ ነጻነት ይኖራቸዋል። ዕንባቆም እንደሚከተለው ተብሎ ነበር:- “የምገልጥልህን ራእይ ጻፍ፤ በቀላሉ እንዲነበብም አድርገህ በሰሌዳ ላይ ቅረጸው።”— ዕንባቆም 2:2 የ1980 ትርጉም
ይህ ማለት ግን እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በቃል ጽሕፈት የሰፈሩትን ያህል ሙሉ በሙሉ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ አይደሉም ማለት ነውን? ፈጽሞ አይደለም። ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት በእያንዳንዱ ጸሐፊ አእምሮ ውስጥ መልእክቱን በግልጽ አስቀምጧል፤ በመሆኑም ያስተላለፉት ሐሳብ የሰው ሳይሆን የአምላክ ነው። ይሖዋ ተስማሚውን ቃላት እንዲመርጥ ለጸሐፊው ነፃነት ቢሰጥም በጣም አስፈላጊ የሆነው እውቀት ሳይጠቀስ እንዳይቀር እንዲሁም መልእክቱ በሰዎች ዘንድ እንደ ሰው ቃል ሳይሆን እንደ አምላክ ቃል ተደርጎ እንዲታይ ሲል የጸሐፊውን ልብና አእምሮ ይመራ ነበር።— 1 ተሰሎንቄ 2:13
በመለኮታዊ መንፈስ የተገለጠ። መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ማለትም ከመፈጸማቸው በፊት የተገለጡ ወይም የተጻፉ ታሪኮችን የያዘ ነው፤ ይህን ማድረግ ከሰው ልጅ አቅም በላይ ነው። አንዱ ምሳሌ ‘የግሪኩ ንጉሥ’ የታላቁ እስክንድር መነሣትና መውደቅ ሲሆን ይህ ትንቢት የተነገረው ከመፈጸሙ ከ200 ዓመታት በፊት ነበር! (ዳንኤል 8:1-8, 20-22) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆች ያላዩአቸውን ክስተቶች ይዘግባል። አንዱ ምሳሌ የሰማይና የምድር መፈጠር ነው። (ዘፍጥረት 1:1-27፤ 2:7, 8) ከዚህም ሌላ በኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ዓይነት በሰማይ ውስጥ የተከናወኑ ውይይቶችን ይገልጻል።— ኢዮብ 1:6-12፤ 2:1-6
አምላክ መጽሐፉን ለጻፈው ሰው በቀጥታ አልገለጠለትም ብንል እንኳ እነዚህ ነገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እስኪመዘገቡ ድረስ በቃል የሚነገሩ ወይም በጽሑፍ የሰፈሩ ታሪኮች ሆነው ከአንዱ ትውልድ ወደ ሌላው እንዲተላለፉ ሲል አምላክ ለአንድ ሰው አሳውቆታል ማለት ነው። (ገጽ 7 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) በዚህም ሆነ በዚያ የዚህ ሁሉ መረጃ ምንጭ ይሖዋ እንደሆነና ዘገባው እንዳይዛባ፣ እንዳይጋነን ወይም በአፈ ታሪክ እንዳይበረዝ ጸሐፊዎቹን እየመራ እንዳስጻፋቸው እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ጴጥሮስ ትንቢትን በሚመለከት “ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ” ሲል ጽፏል።b— 2 ጴጥሮስ 1:21
ከፍተኛ ጥረት ጠይቋል
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎቹ ‘በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው’ ቢጽፉም ጥንቃቄ የተሞላበት ጥረት ማድረግ አስፈልጓቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል ሰሎሞን ‘ብዙ ምሳሌዎችን መርምሮና ፈላልጎ አስማምቷል። ያማረውን በቅንም የተጻፈውን እውነተኛውን ቃልም መርምሮ ለማግኘት ጥሯል።’— መክብብ 12:9, 10
አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች መልእክታቸውን ለማስፈር ከፍተኛ ምርምር ማድረግ አስፈልጓቸዋል። ለምሳሌ ያህል ሉቃስ የራሱን የወንጌል ዘገባ በሚመለከት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ከመጀመሪያው አንሥቼ ሁሉን ነገር በጥንቃቄ ከመረመርኩ በኋላ ታሪኩን በቅደም ተከተል” ጽፌያለሁ። እርግጥ ነው አስተማማኝ ታሪካዊ መረጃዎችን እንዲያገኝ በማድረግ እንዲሁም በሕይወት የነበሩትን ደቀ መዛሙርት የመሳሰሉ እምነት የሚጣልባቸውን የዓይን ምሥክሮችና ምናልባትም የኢየሱስን እናት ማርያምን እንዲያነጋግር በማነሳሳት መንፈስ ቅዱስ ሉቃስ ያደረገውን ጥረት እንደባረከለት የተረጋገጠ ነው። ከዚያም የአምላክ መንፈስ ሉቃስ ያገኘውን መረጃ በትክክል እንዲመዘግብ ረድቶታል።— ሉቃስ 1:1-4 የ1980 ትርጉም
ከሉቃስ ወንጌል በተቃራኒ ዮሐንስ በዓይኑ ያየውን ነገር በወንጌሉ ውስጥ አስፍሯል። ይህ ወንጌል የተጻፈው ኢየሱስ ከሞተ ከ65 ዓመታት ገደማ በኋላ ነው። ዮሐንስ ከጊዜ ብዛት የተፈጸሙትን ነገሮች እንዳይረሳ የይሖዋ መንፈስ ጥሩ የማስታወስ ችሎታ እንደሰጠው ምንም ጥርጥር የለውም። ይህ ኢየሱስ ለተከታዮቹ ከገባው ቃል ጋር ይስማማል:- “አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።”— ዮሐንስ 14:26
አንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የዓይን ምሥክሮች ከዘገቧቸውና ቀደምት ታሪክ ጸሐፊዎች ካሰፈሯቸው ነገሮች አንዳንድ ሐሳቦችን አጠናቅረዋል፤ ከእነዚህ ምንጮች መካከል አንዳንዶቹ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ አይደሉም። ኤርምያስ የአንደኛና ሁለተኛ ነገሥት መጻሕፍትን በአብዛኛው ያጠናቀረው በዚህ መንገድ ነው። (2 ነገሥት 1:18) ዕዝራ አንደኛና ሁለተኛ ዜና መጻሕፍትን ለመጻፍ ‘የንጉሡን የዳዊትን መዝገብ’ እንዲሁም ‘የይሁዳና የእሥራኤል ነገሥታትን መጽሐፍ’ ጨምሮ በመንፈስ አነሳሽነት ያልተጻፉ ቢያንስ 14 የሚሆኑ የመረጃ ምንጮችን አገላብጧል። (1 ዜና መዋዕል 27:24፤ 2 ዜና መዋዕል 16:11) ሙሴም ቢሆን ‘ከእግዚአብሔር የጦርነት መጽሐፍ’ ጠቅሷል፤ ይህ መጽሐፍ የአምላክ ሕዝቦች ያደረጓቸውን ጦርነቶች የሚገልጽ አስተማማኝ መዝገብ ሳይሆን አይቀርም።— ዘኁልቁ 21:14, 15
በእነዚህ ሁኔታዎች ጸሐፊዎቹ አስተማማኝ ነጥቦችን ብቻ እንዲመርጡ በማድረግ በኩል መንፈስ ቅዱስ የጎላ ድርሻ አበርክቷል፤ በኋላም እነዚህ ሐሳቦች በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሆነዋል።
ጠቃሚ ምክር—ከማን?
መጽሐፍ ቅዱስ አስተዋይነት በተሞላባቸው የግለሰብ ግንዛቤዎች ላይ የተመሠረቱና ጠቃሚ የሆኑ በርካታ ምክሮችን ይዟል። ለምሳሌ ያህል ሰሎሞን እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ለሰው ከሚበላና ከሚጠጣ በድካሙም ደስ ከሚለው በቀር የሚሻለው ነገር የለም፤ ይህም ደግሞ ከእግዚአብሔር እጅ እንደ ተሰጠ አየሁ።” (መክብብ 2:24) ጳውሎስ ትዳርን በተመለከተ የሰጠውን ሐሳብ ‘እንደ ራሱ ምክር’ አድርጎ ቢገልጽም “እኔም ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ያለ ይመስለኛል” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 7:25, 39, 40) ጳውሎስ በእርግጥም የአምላክ መንፈስ ነበረው፤ ምክንያቱም ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደገለጸው ጳውሎስ የጻፈው “እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን” ነበር። (2 ጴጥሮስ 3:15, 16፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) በዚህ መንገድ በአምላክ መንፈስ በመመራት የራሱን ሐሳብ ሰጥቷል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች እነርሱ በጽኑ የሚያምኑበትን እንዲህ የመሰለውን ሐሳብ የሚሰጡት በእጃቸው የነበሩትን ቅዱሳን ጽሑፎች በማጥናትና በሥራ ላይ በማዋል ካገኙት ተሞክሮ ተነሥተው ነው። የጻፉት ነገር ከአምላክ ሐሳብ ጋር እንደሚስማማ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። እነርሱ የመዘገቡት ነገር ዛሬ የአምላክ ቃል ክፍል ሆኗል።
እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ የተሳሳተ አስተሳሰብ የነበራቸው አንዳንድ ሰዎች የተናገሩትንም ሐሳብ አስፍሯል። (ኢዮብ 15:15ን ከ42:7 ጋር አወዳድር።) በተጨማሪም የአምላክ አገልጋዮች የተሰማቸውን ውስጣዊ ጭንቀት የሚገልጹ ጥቂት ሐሳቦች ይዟል፤ ይሁንና እነዚህ ሐሳቦች ለምን እንደዚያ እንደተሰማቸው ቁልጭ አድርገው አይገልጹም።c ጸሐፊው እንዲህ ዓይነት የግል ሐሳቦችን ሲያሰፍር የአምላክ መንፈስ ትክክለኛውን ነገር እንዲመዘግብ ረድቶታል፤ ይህ ነገር መመዝገቡም የተሳሳቱ ሐሳቦችን ለይቶ ለማወቅና ግልጽ ለማድረግ ረድቷል። ከዚህም በተጨማሪ ምክንያታዊ ለሆኑ አንባብያን ከጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ራሱ የጸሐፊው ሐሳብ ተቀባይነት ያለው መሆንና አለመሆኑን ያስረዳል።
ለማጠቃለል ያህል መላው መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ መልእክት ለመሆኑ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። በእርግጥም ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው እያንዳንዱ ነገር ከዓላማው ጋር የሚስማማና እርሱን ለማገልገል ለሚፈልጉ ሰዎች በጣም አስፈላጊ የሆነውን መመሪያ የሚሰጥ እንዲሆን አድርጓል።— ሮሜ 15:4
ሰብዓዊ ጸሐፊዎች—ለምን?
ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን ሰዎች እንዲጽፉ ማድረጉ ጥበቡ ታላቅ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። እስቲ አስበው:- አምላክ ይህንን ሥራ ለመላእክት ሰጥቶ ቢሆን ኖሮ መጽሐፍ ቅዱስ አሁን ያለውን ዓይነት ይዘት ይኖረው ነበርን? መላእክት ከእነርሱ አመለካከት አንጻር ስለ አምላክ ባሕርያትና ስላደረጋቸው ነገሮች የገለጹትን ነገር ማንበባችን ስሜት ቀስቃሽ ሆኖ እንደምናገኘው አይካድም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም ዓይነት ሰብዓዊ ለዛ ባይኖረው ኖሮ መልእክቱን መረዳት ሊቸግረን ይችል ነበር።
ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ንጉሥ ዳዊት ምንዝር እንደፈጸመና ነፍስ እንዳጠፋ በመጨረሻም ንስሐ እንደገባ ብቻ ባጭሩ ሊገልጽልን ይችል ነበር። ይሁንና ድርጊቱ ያስከተለበትን የመንፈስ ስብራት እንዲሁም የይሖዋን ይቅርታ እንዴት እንደለመነ የሚገልጹትን የራሱን የዳዊትን ቃላት ማንበብ ምንኛ የተሻለ ነው! “ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነው” ሲል ጽፏል። “የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም።” (መዝሙር 51:3, 17) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን ሰዎች መጻፋቸው ልባዊ ስሜት የተንጸባረቀበት፣ የተለያየ አቀራረብ ያለውና የሚስብ እንዲሆን አድርጎታል።
አዎን፣ ይሖዋ ቃሉን ለእኛ ለማስተላለፍ ከሁሉ የተሻለውን ዘዴ ተጠቅሟል። ምንም እንኳ ይሖዋ የተጠቀመባቸው ሰዎች የራሳቸው ድክመት የነበረባቸው ቢሆኑም በጽሑፋቸው ውስጥ ምንም ዓይነት ስህተት እንዳይገኝ የጻፉት ‘በአምላክ መንፈስ እየተነዱ’ ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ጥቅም እጅግ ከፍተኛ ነው። ምክሩ መሬት ጠብ አይልም፤ ወደፊት በምድር ላይ የሚመጣውን ገነት በተመለከተ የሚናገረውም ትንቢት አስተማማኝ ነው።— መዝሙር 119:105፤ 2 ጴጥሮስ 3:13
ታዲያ ከአምላክ ቃል በየዕለቱ የተወሰነ ክፍል ማንበብን ለምን ልማድህ አታደርገውም? ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ።” (1 ጴጥሮስ 2:2) ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ በመሆኑ “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፣ . . . የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር” ደግሞ የሚጠቅም ሆኖ ታገኘዋለህ።— 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ቢያንስ በአንድ አጋጣሚ ይኸውም አሥርቱ ትእዛዛት ሲሰጡ መልእክቱ በቀጥታ ‘በአምላክ ጣት’ ተጽፏል። ከዚያ በኋላ ሙሴ ያደረገው ነገር ቢኖር እነዚያን ቃላት በጥቅልሎች ወይም ሌሎች ነገሮች ላይ መገልበጥ ነው።— ዘጸአት 31:18፤ ዘዳግም 10:1-5
b “ተነድተው” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ፌሮ የሚል ሲሆን በሥራ 27:15, 17 ላይ በነፋስ የተወሰደችን መርከብ ለማመልከት በሌላ መልክ ተሠርቶበት እናገኘዋለን። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎቹን ‘እየተቆጣጠረ መርቷቸዋል’ ማለት ነው። የተዛቡ መረጃዎችን እየተዉ ትክክለኛ የሆኑትን ብቻ እንዲያሰፍሩ አድርጓቸዋል።
c ለምሳሌ ያህል 1 ነገሥት 19:4ን ከቁጥር 14 እና 18 ጋር አወዳድር፤ ኢዮብ 10:1-3፤ መዝሙር 73:12, 13, 21፤ ዮናስ 4:1-3, 9፤ ዕንባቆም 1:1-4, 13
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሙሴ መረጃውን ያገኘው ከየት ነው?
የዘፍጥረትን መጽሐፍ የጻፈው ሙሴ ነው። ይሁን እንጂ የመዘገባቸው ነገሮች በሙሉ የተከናወኑት እርሱ ከመወለዱ ከረጅም ዘመን በፊት ነው። ታዲያ እንዲህ ያለውን መረጃ ያገኘው ከየት ነው? አምላክ በቀጥታ ገልጾለት ሊሆን ይችላል፤ ወይም ደግሞ አንዳንዶቹ ክንውኖች ከአንዱ ትውልድ ወደ ሌላው በቃል ሲተላለፉ የቆዩ ሊሆኑ ይችላሉ። ቀደም ባሉት ጊዜያት የኖሩት ሰዎች ዕድሜያቸው ረጅም በመሆኑ ሙሴ በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ከመዘገበው ነገር መካከል አብዛኛው በአዳምና በሙሴ መካከል ባሉ አምስት ሰዎች ተዋረድ ብቻ ማለትም ከአዳም ለማቱሳላ፣ ከማቱሳላ ለሴም፣ ከሴም ለይስሐቅ፣ ከይስሐቅ ለሌዊ፣ ከሌዊ ለአምራም ከዚያም ከአምራም ወደ ሙሴ ደርሶ ሊሆን ይችላል።
ከዚህም በተጨማሪ ሙሴ የጽሑፍ መዛግብትን አገላብጦ ሊሆን ይችላል። በዚህ ረገድ ሙሴ የእያንዳንዱን ግለሰብ ታሪክ ከመግለጹ በፊት “የ . . . ታሪክ ይህ ነው” እያለ መጀመሩን ልብ ልንለው ይገባል። (ዘፍጥረት 6:9 የ1980 ትርጉም፤ 10:1 NW፤ 11:10, 27 NW፤ 25:12, 19 NW፤ 36:1, 9 NW፤ 37:2 NW) አንዳንድ ምሁራን እዚህ ላይ “ታሪክ” ተብሎ የተተረጎመው ቶህሌዶዝ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል የሚያመለክተው ሙሴ ለጽሑፉ ምንጭ አድርጎ የተጠቀመበትን ቀደም ብሎ የተዘጋጀ የታሪክ መዝገብ ነው ይላሉ። እርግጥ እንደዚያ ብሎ በእርግጠኛነት መደምደም አይቻልም።
በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው መረጃ የተሰባሰበው ከላይ በተጠቀሱት በሦስቱም ዘዴዎች አማካኝነት ሊሆን ይችላል። ይህም ማለት አንዳንዶቹ በቀጥታ ከአምላክ ተገልጠውለት፣ አንዳንዶቹ በቃል በተላለፈ ታሪክ እንዲሁም አንዳንዶቹ ደግሞ ቀደም ሲል ከተጻፉ መዛግብት ሊሆን ይችላል። ዋናው ነገር ሙሴ የጻፈው በይሖዋ መንፈስ መሪነት መሆኑ ነው። በመሆኑም ያሠፈረው ሐሳብ በትክክል እንደ አምላክ ቃል ተደርጎ የሚታይ ነው።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲጽፉ በመንፈሱ ያነሳሳቸው በተለያየ መንገድ ነው