ተአምራዊ ፈውሶች በአሁኑ ጊዜም ይሠራሉ?
“ኢየሱስን ተቀበል ትፈወሳለህ!” እንዲህ ዓይነቱ አባባል አሌክሳንደር የተባለ አንድ የኢቫንጄሊካል ቤተ ክርስቲያን አባል ለሕመሙ መድኃኒት መውሰድ እምነት እንደጎደለው የሚያሳይ ድርጊት ሆኖ እንዲሰማው አድርጎታል። እምነቱ ብቻውን የሚያስፈልገውን ተአምራዊ ፈውስ እንደሚያስገኝለት አምኖ ተቀብሎ ነበር። ቤነዲት የተባለች አጥባቂ የካቶሊክ አማኝ በብራዚል አገር በሳኦ ፖሎ ግዛት አፓርሲድ ድ ኖርት በተባለ መቅደስ ውስጥ ስለሚከናወነው ተአምራዊ ፈውስ ስትሰማ ስሜቷ በጥልቅ ተነክቶ ነበር። አክስቷ ያስተማረቻትን አንዳንድ የድግምት ቃላት በመጠቀም ቤነዲት የታመሙትን ለመፈወስ የሚያስችለውን ኃይል ለማግኘት ለእመቤታችን አፕሬሲዳ፣ ለአንቶኒ እና ለሌሎች “ቅዱሳን” ጸለየች።
አሁን ባለንበት በ20ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ እንኳ ብዙ ሰዎች በተአምራዊ ፈውስ ያምናሉ። ግን ለምን? አንዳንድ ሰዎች በሚወዱት ሰው በተለይም በልጆቻቸው የሚደርሰውን በሽታ፣ ሕመምና ሥቃይ ለማስታገስ ሐኪሞች ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ሲያዩ ተስፋ መቁረጣቸው የማይቀር ነው። ሥር በሰደደ በሽታ እየተሠቃዩ ያሉ ሰዎች ዘመናዊው ሕክምና ከሚያስወጣው ከፍተኛ ወጪ አንፃር ሲታይ የእምነት ፈውስ ወደሚደረግበት ቦታ ቢያቀኑ ምንም ጉዳት እንደሌለው አድርገው ሊሰማቸው ይችላል። አንዳንዶች የተለያዩ ቤተ ክርስቲያኖችና ግለሰቦች ኤድስን፣ የመንፈስ ጭንቀትን፣ ካንሰርን፣ የአእምሮ ሕመምን፣ ከፍተኛ የደም ግፊትንና ሌሎች ብዙ ሕመሞችን ሲፈውሱ በቴሌቪዥን ይመለከታሉ። በእነዚህ አባባሎች እርግጠኞች ሆኑም አልሆኑ እርዳታ ለማግኘት ወደ እነርሱ ዘንድ ይሄዳሉ። በክፉ መናፍስት አማካኝነት እንደታመሙ የሚያምኑ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ዘመናዊ ሕክምና እነርሱን የማዳን ኃይል እንደሌለው አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ።
በሌላው በኩል ደግሞ የሞቱ “ቅዱሳን” ወይም በሕይወት ያሉ ፈዋሾች በተአምር ያድናሉ የሚለውን ሐሳብ አጥብቀው የሚቃወሙ እንዲያውም የሚያወግዙ ሰዎችም አሉ። ጆርናል ዳ ታርዴ የተባለው ጋዜጣ እንደጠቀሰው ሰውነት ያለውን በሽታን የመከላከል ችሎታ የሚያጠኑት (ኢሚዩኖሎጂስት) ድራዩስዩ ቫሬል በተአምራታዊ ፈውስ ማመን “ባልጠረጠረና ተስፋ በቆረጠ ሰው አእምሮ ውስጥ የተሳሳተ እምነት ያሳድራል” ብለው እንደሚያስቡ ዘግቧል። አክለውም “በእነዚህ አታላዮች የተነሳ ብዙዎች በተአምራት ላይ ተስፋ በመጣላቸው በጣም አስፈላጊ የሆነ ሕክምና ሳያደርጉ ሊቀሩ ይችላሉ።” እንዲሁም ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ የሚከተለውን ማብራሪያ ይሰጣል:- “በጥንት ጊዜ እንግዳ የሆነ ፈውስ ከቅዱስ ቦታዎችና ከሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ጋር የተያያዘ ነበር። የሕክምና ሳይንስ ደግሞ እነዚህ ሁሉ ፈውሶቸ ምቹ ሁኔታዎችን ተጠቅሞ አእምሮን በማፍዘዝ ሊፈጸሙ የሚችሉ እንግዳ ያልሆኑ ድርጊቶች ናቸው የሚል አቋም አለው።” ሆኖም አሁንም በተአምራዊ መንገድ እንደተፈወሱ የሚያምኑ ብዙ ሰዎች አሉ። በእነሱ አመለካከት ፈውሱ ሠርቶላቸዋል!
ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ትውውቅ ያላቸው ሰዎች ኢየሱስ በተለያዩ ወቅቶች የታመሙ ሰዎችን እንደፈወሰ ይህንንም ያደረገው “በአምላክ ኃይል” እንደሆነ ያውቃሉ። (ሉቃስ 9:42, 43 NW) በዚህም የተነሳ ‘በዛሬው ጊዜ የአምላክ ኃይል እየሠራና ተአምራዊ ፈውሶችን እያከናወነ ነውን?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናሉ። የሚሠራ ከሆነ ለመፈወስ የሚደረጉት ሙከራዎች ተስፋ የተደረገውን ውጤት ሳያስገኙ የሚቀሩት ለምንድን ነው? ይህ የሆነው ሕመምተኛው በቂ እምነት ስለ ሌለው ነው ወይስ የሚሰጠው መዋጮ በቂ ስላልሆነ? አንድ ክርስቲያን የሚያሠቃይ ሕመም ወይም ምናልባትም የማይድን በሽታ በሚይዘው ጊዜ ተአምራዊ ፈውስ ለማግኘት ቢሞክር ተገቢ ይሆናል? እንዲሁም ኢየሱስ ያከናወነው ዓይነት እውነተኛ ተአምራዊ ፈውስ በድጋሚ ይፈጸም ይሆን? ለእነዚህ አንገብጋቢ ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ላይ መልስ ማግኘት ትችላለህ።