የአምላክ ወዳጅ ነህን? ጸሎቶችህ ምን ያረጋግጣሉ
ሁለት ሰዎች ሲነጋገሩ የሚያወሩት ነገር ድንገት ጆሮህ ውስጥ ጥልቅ ብሎ ያውቃል? ሰዎቹ በጣም የሚቀራረቡ ጓደኛሞች ይሁኑ የማይተዋወቁ ወይም ደግሞ በሩቅ ብቻ የሚተዋወቁ ይሁኑ ወይም የሚተማመኑ ወዳጆች ለመለየት ብዙ ጊዜ እንዳልፈጀብህ የታወቀ ነው። በተመሳሳይም ጸሎቶቻችን ከአምላክ ጋር ያለንን ግንኙነት ያንጸባርቃሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ “ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (ሥራ 17:27) እንዲያውም አምላክ ራሱ እንድናውቀው ይጋብዘናል። ወዳጆቹም መሆን እንችላለን። (መዝሙር 34:8፤ ያዕቆብ 2:23) ከእርሱ ጋር በጣም የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት እንችላለን! (መዝሙር 25:14) በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ለእኛ፣ ፍጹማን ላልሆነው ሰዎች ከአምላክ ጋር ወዳጅነት ከመመሥረት የሚበልጥ ውድ ነገር አይኖርም። ይሖዋም ከእኛ ጋር ያለውን ወዳጅነት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። ከእርሱ ጋር ያለን ወዳጅነት የተመሠረተው ለእኛ ሲል ሕይወቱን በሰጠው አንድያ ልጁ ላይ ባለን እምነት መሆኑ ራሱ ለዚህ ማስረጃ ይሆናል።— ቆላስይስ 1:19, 20
በመሆኑም ጸሎቶቻችን ለይሖዋ ያለንን ጥልቅ ፍቅርና አድናቆት የሚያንጸባርቁ ሊሆኑ ይገባል። ይሁንና ጸሎቶችህ አክብሮት የተሞላባቸው ቢሆኑም ከልብህ ፈንቅለው የወጡ እንዳልሆኑ ተሰምቶህ ያውቃልን? ይህ አዲስ ነገር አይደለም። ይህንን ለማሻሻል ቁልፉ ምንድን ነው? ከይሖዋ አምላክ ጋር ያለህን ወዳጅነት ማጎልበት ነው።
ለጸሎት ጊዜ መመደብ
ከሁሉ በፊት ወዳጅነትን ለማጎልበትና ለማጠንከር ጊዜ ይጠይቃል። በየዕለቱ ከብዙ ሰዎች ጋር ማለትም ከጎረቤቶችህ፣ አብረውህ ከሚሠሩ፣ ከአውቶቡስ ሹፌሮችና ከባለሱቆች ጋር ሰላምታ ትለዋወጥ ብሎም ትወያይ ይሆናል። ያም ሆኖ ግን ከእነዚህ ሰዎች ጋር ወዳጅ ነህ ማለት አይቻልም። ከአንድ ሰው ጋር ብዙ በተነጋገርህ መጠን ወዳጅነትህ እያደገ ይሄዳል፤ እንዲሁ ላይ ላዩን ብቻ ከሚደረግ ውይይት አልፈህ ውስጣዊ ስሜትህንና ሐሳብህን መግለጽ ትጀምራለህ።
በተመሳሳይም ጸሎት ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ ይረዳናል። ይሁን እንጂ ይህ በቂ ጊዜ ሊሰጠው ይገባል፤ ምግብ ልትበላ ስትል የምታቀርበው አጭር የምስጋና ጸሎት ብቻ በቂ ሊሆን አይችልም። ከይሖዋ ጋር ብዙ በተነጋገርህ መጠን የዚያኑ ያህል የራስህን ስሜት፣ ውስጣዊ ዝንባሌና ድርጊት መመርመር ትችላለህ። የአምላክ መንፈስ በቃሉ ውስጥ ያሉትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሲያስታውስህ ከባድ ለሆኑ ችግሮች መፍትሔው ግልጽ ሆኖ እየታየህ ይመጣል። (መዝሙር 143:10፤ ዮሐንስ 14:26) ከዚህም በተጨማሪ ስትጸልይ ይሖዋ ይበልጥ እውን ሆኖ ይታይሃል፤ ለአንተ ያለውን ፍቅራዊ አሳቢነትና ተቆርቋሪነትም ይበልጥ ትገነዘባለህ።
በተለይ ለጸሎቶችህ መልስ በምታገኝበት ጊዜ ይህን አባባል እውነት ሆኖ ታገኘዋለህ። እንዲያውም ይሖዋ “ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ሊያደርግ” ይችላል! (ኤፌሶን 3:20) ይህ ማለት ግን ይሖዋ ተአምር ያደርግልሃል ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ በተጻፈው ቃሉ፣ ታማኝና ልባም ባሪያ በሚያዘጋጃቸው ጽሑፎች ወይም አፍቃሪ በሆኑ ወንድሞችና እህቶች አማካኝነት የሚያስፈልግህን ምክርና መመሪያ ሊሰጥህ ይችላል። አለዚያም ደግሞ አንድን ፈታኝ ሁኔታ በጽናት ለማለፍ ወይም ለመቋቋም የሚያስችልህን ብርታት ሊሰጥህ ይችላል። (ማቴዎስ 24:45፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:17) እንዲህ ያሉት አጋጣሚዎች ልባችን ለሰማያዊው ወዳጃችን ባለን አድናቆት እንዲሞላ ያደርጋሉ!
በመሆኑም አንድ ሰው ለጸሎት ጊዜ ሊመድብ ይገባል። በእነዚህ ውጥረት በበዛባቸው ቀናት ውስጥ ጊዜ እንደ ልብ እንደማይገኝ እሙን ነው። ይሁን እንጂ ከልብ ከምትወደው ሰው ጋር የምታሳልፈው ጊዜ አታጣም። ዳዊት ስለ ራሱ ምን እንዳለ ልብ በል:- “ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ፣ አቤቱ እንዲሁ ነፍሴ ወደ አንተ ትናፍቃለች። ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች፤ መቼ እደርሳለሁ? የአምላክንስ ፊት መቼ አያለሁ?” (መዝሙር 42:1, 2) አንተስ ከአምላክ ጋር ለመነጋገር እንደዚህ ትናፍቃለህን? እንግዲያውስ ይህንን ለማድረግ የሚያስችልህን ጊዜ ዋጅ!— ከኤፌሶን 5:16 ጋር አወዳድር።
ለምሳሌ ያህል ለመጸለይ የሚያስችልህን ፀጥ ያለ ጊዜ ለማግኘት ጠዋት በማለዳ ለመነሳት ልትሞክር ትችል ይሆናል። (መዝሙር 119:147) ሌሊት እንቅልፍ አጥተህ የምታሳልፋቸው ጊዜያት አሉ? እንግዲያው ልክ እንደ መዝሙራዊው ይህን አጋጣሚ የሚያሳስቡህን ነገሮች ለአምላክ ለመንገር ልትጠቀምበት ትችላለህ። (መዝሙር 63:6) ወይም በቀን ውስጥ በርከት ያሉ አጫጭር ጸሎቶችን ልታቀርብ ትችላለህ። መዝሙራዊው “አቤቱ፣ ቀኑን ሁሉ ወደ አንተ እጮኻለሁ” ሲል ለአምላክ ተናግሯል።— መዝሙር 86:3
የጸሎቶቻችንን ይዘት ማሻሻል
አንዳንድ ጊዜ የጸሎቶችህንም ርዝማኔ ማሳደጉን ጠቃሚ ሆኖ ታገኘው ይሆናል። ጸሎትህ አጭር ከሆነ ጥልቀት ስላላቸው ነገሮች ለመጥቀስ አይጋብዝህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ረዘም ያሉና ጥልቀት ያላቸው ጸሎቶች በምታቀርብበት ጊዜ የበለጠ ሐሳብህንና ውስጣዊ ስሜትህን ለመግለጽ ትነሳሳለህ። ኢየሱስ ቢያንስ በአንድ አጋጣሚ ሙሉ ሌሊት ሲጸልይ አድሯል። (ሉቃስ 6:12) ሳትቸኩል በምትጸልይበት ጊዜ የራስህ ጸሎቶች ይበልጥ ጥልቀትና ትርጉም ያላቸው ሆነው እንደምታገኛቸው ጥርጥር የለውም።
ይህ ማለት ግን ብዙም የምትናገረው ነገር ሳይኖርህ የባጥ የቆጡን ማውራት ወይም አላስፈላጊ ድግግሞሽ ማብዛት ማለት አይደለም። ኢየሱስ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል:- “አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደ እነርሱ በከንቱ አትድገሙ። ስለዚህ አትምሰሉአቸው፤ ሳትለምኑት አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃልና።”— ማቴዎስ 6:7, 8
ስለ ምን ጉዳይ እንደምትጸልይ አስቀድመህ ካሰብክበት ጸሎትህ ይበልጥ ትርጉም ያለው ይሆናል። ልትጸልይባቸው የምትችላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ብዙ ናቸው። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያክል በአገልግሎት የምናገኘው ደስታ፣ ድካምና መተላለፋችን፣ ቅር የተሰኘንበት ነገር፣ የኢኮኖሚ ጭንቀት፣ በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት የሚገጥመን ተጽዕኖ፣ የቤተሰባችን ደህንነት እንዲሁም የጉባኤያችን መንፈሳዊ ሁኔታ ይገኙበታል።
አንዳንድ ጊዜ ስትጸልይ አእምሮህ ወደ ሌላ ሐሳብ ይሄድብሃልን? ከሆነ ሐሳብህን ለመሰብሰብ ተጨማሪ ጥረት አድርግ። ይሖዋ እንኳ ‘ጩኸታችንን ለማዳመጥ’ ፈቃደኛ ሆኖ የለምን? (መዝሙር 17:1) ታዲያ እኛ ለራሳችን ጸሎት ትኩረት ለመስጠት ልባዊ ጥረት ማድረግ አይገባንም? አዎን፣ ‘አእምሮህ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር አድርግ፤’ ሽርሽር እንዲሄድ አትፍቀድለት።— ሮሜ 8:5
ይሖዋን የምናነጋግርበት መንገድ ራሱ ሊታሰብበት ይገባል። እንደ ወዳጃችን አድርገን እንድናየው የሚፈልግ ቢሆንም እንኳ የምንነጋገረው ከአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ጋር እንደሆነ መርሳት የለብንም። በራእይ ምዕራፍ 4 እና 5 ላይ የተገለጸውን አስፈሪ ግርማ የተንጸባረቀበት ትዕይንት አንብብና አሰላስልበት። ዮሐንስ በዚህ ራእይ ውስጥ በጸሎት የምናነጋግረው አምላክ ያለውን ዕጹብ ድንቅ ግርማ ተመልክቷል። “በዙፋኑ ላይ በተቀመጠው” ፊት መቅረብና ከእርሱ ጋር መነጋገር መቻላችን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! የምንናገራቸው ቃላት የተናቁና አክብሮት የጎደላቸው እንዲሆኑ አንፈልግም። ይልቁንም ‘የአፋችን ቃልና የልባችን ሐሳብ ለይሖዋ ደስ የሚያሰኝ’ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይገባናል።— መዝሙር 19:14
ይሁንና የይሖዋን ልብ መማረክ የምንችለው የተራቀቁ ቃላት በመጠቀም እንዳልሆነ አስታውስ። የተጠቀምንበት መግለጫ የቱንም ያህል ቀላል ቢሆን እርሱን የሚያስደስተው አክብሮት ያለውና ከልባችን የመነጨ መሆኑ ነው።— መዝሙር 62:8
በችግራችን ጊዜ የሚያጽናናንና ስሜታችንን የሚረዳልን ማግኘት
ብዙውን ጊዜ እርዳታና ማጽናኛ ሲያስፈልገን የሚደግፈንና ሐዘናችንን የሚጋራን ሰው ለማግኘት ወደ ቅርብ ወዳጃችን እንሄዳለን። እንደ እውነቱ ከሆነ ከይሖዋ ይበልጥ በቅርብ ልናገኘው የምንችለው ወዳጅ የለም። እርሱ “ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው።” (መዝሙር 46:1) “የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” እንደመሆኑ መጠን ከማንኛውም ሰው በተሻለ መንገድ የገባንበትን ችግር ይረዳልናል። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4፤ መዝሙር 5:1፤ 31:7) በችግር ለተቆራመዱ ሰዎች የአዘኔታና የርኅራኄ ስሜት ያሳያል። (ኢሳይያስ 63:9፤ ሉቃስ 1:77, 78) ይሖዋን ችግራችንን እንደሚረዳልን ወዳጅ አድርገን የምናየው ከሆነ እርሱን ከልባችን ለማነጋገር ነፃነት ይሰማናል። በልባችን ውስጥ የተተከለውን ፍርሃትና ጭንቀት ለእርሱ አውጥተን ለመንገር እንገፋፋለን። በዚህ መንገድ ‘ይሖዋ የሚሰጠው ማጽናኛ እንዴት ነፍስን ደስ እንደሚያሰኝ’ እንቀምሳለን።— መዝሙር 94:18, 19
አንዳንድ ጊዜ በሠራነው ኃጢአት ምክንያት ወደ አምላክ ለመቅረብ እንደማንበቃ ሆኖ ይሰማን ይሆናል። ይሁን እንጂ አንድ በጣም የምትቀርበው ወዳጅህ ቢበድልህና ይቅር እንድትለው ቢለምንህ ምን ታደርጋለህ? እርሱን ለማጽናናትና ለማረጋጋት አትገፋፋምን? ታዲያ ይሖዋ እንዲህ አያደርግም ብለህ የምትጠብቅበት ምን ምንክያት አለ? በሰብዓዊ አለፍጽምና ምክንያት ኃጢአት የሚሠሩ ወዳጆቹን በልግስና ይቅር ይላል። (መዝሙር 86:5 NW፤ 103:3, 8-11) ይህንን ስለምናውቅ በደላችንን ነፃነት ተሰምቶን ለእርሱ ከመናዘዝ ወደ ኋላ አንልም፤ ስለ ፍቅሩና ምሕረቱ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። (መዝሙር 51:17) በፈጸምነው በደል ምክንያት ከተጨነቅን 1 ዮሐንስ 3:19, 20 ላይ ባሉት ቃላት ልንጽናና እንችላለን:- “ልባችንም በእኛ ላይ በሚፈርድበት ሁሉ፣ ከእውነት እንደ ሆንን በዚህ እናውቃለን በፊቱም ልባችንን እናሳርፋለን፣ እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉንም ያውቃል።”
ሆኖም የአምላክን ፍቅራዊ አሳቢነት ለመቅመስ የግድ ችግር ውስጥ መግባት አያስፈልገንም። ይሖዋ መንፈሳዊና ስሜታዊ ደህንነታችንን የሚያናጋ ማንኛውም ነገር ያሳስበዋል። አዎን፣ ስሜቶቻችንና ሐሳቦቻችን በጸሎት ሊጠቀሱ የማይገባቸው ተራ ነገሮች ናቸው ብለን ፈጽሞ ልናስብ አይገባንም። (ፊልጵስዩስ 4:6) ከቅርብ ወዳጅህ ጋር ስትገናኝ የምታወራው በሕይወትህ ውስጥ ስለሚያጋጥሙህ ከፍተኛ ቁም ነገሮች ብቻ ነውን? በአንጻራዊ ሁኔታ ጥቃቅን የሆኑ ነገሮችንም አንስተህ ትወያይ የለምን? በተመሳሳይም እርሱ ‘ስለ አንተ እንደሚያስብ’ እርግጠኛ በመሆን ስለ ማንኛውም የሕይወትህ ዘርፍ ከይሖዋ ጋር ለመወያየት ነፃነት ሊሰማህ ይገባል።— 1 ጴጥሮስ 5:7
እርግጥ ስለ ራስህ ብቻ የምታወራ ከሆነ ወዳጅነትህ ላይዘልቅ ይችላል። በተመሳሳይም ጸሎቶቻችን በራሳችን ጥቅም ላይ ብቻ ያተኮሩ መሆን አይገባቸውም። ለይሖዋና ለዓላማዎቹ ያለንን ፍቅርና ተቆርቋሪነት መግለጽ ይገባናል። (ማቴዎስ 6:9, 10) ጸሎት ከአምላክ እርዳታ የሚጠየቅበት ብቻ ሳይሆን ለእርሱ ምስጋናና ውዳሴም ለማቅረብ የሚቻልበት አጋጣሚ ነው። (መዝሙር 34:1፤ 95:2) ቋሚ በሆነ የግል ጥናት አማካኝነት ‘እውቀት መሰብሰብ’ ይበልጥ ከይሖዋና ከመንገዶቹ ጋር እንድንተዋወቅ ስለሚያስችለን በዚህ ረገድ ጠቃሚ ሆኖ እናገኘዋለን። (ዮሐንስ 17:3) በተለይ የመዝሙር መጻሕፍትን ማንበብህና ሌሎች የታመኑ አገልጋዮች ለይሖዋ ባቀረቡት ጸሎት ውስጥ ስለምን ነገር እንደገለጹ ማወቅህ ይጠቅምሃል።
በእርግጥም ከይሖዋ ጋር ያለን ወዳጅነት ውድ ስጦታ ነው። ጸሎቶቻችን ይበልጥ ጥልቀት ያላቸው፣ ልባዊና የውስጥ ስሜታችን የተንጸባረቀባቸው እንዲሆኑ በማድረግ ይህንን ስጦታ እንደምናደንቅ እናሳይ። እንዲህ ካደረግን እንደሚከተለው ሲል የተናገረው መዝሙራዊ የነበረውን ዓይነት ደስታ እናገኛለን:- “የመረጥኸውና ወደ አንተ እንዲቀርብ ያደረግኸው ደስተኛ ነው።”— መዝሙር 65:4 NW
[በገጽ 28 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ቀኑን ሙሉ አጋጣሚውን ባገኘን ቁጥር ወደ አምላክ መጸለይ እንችላለን