የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w97 7/15 ገጽ 8-13
  • ብልግና በሞላበት ዓለም ውስጥ በጎ ሆኖ መኖር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ብልግና በሞላበት ዓለም ውስጥ በጎ ሆኖ መኖር
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በብልግና የተሞላው የሮማውያን ዓለም
  • ዛሬ ያለው በብልግና የተሞላ ዓለም
  • ከዓለም ብልግና ራቁ
  • በጎነትን እየተከታተላችሁ ነውን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • በጎነትን ማዳበር የምንችልበት መንገድ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • በእምነታችን ላይ በጎነትን መጨመር የምንችለው እንዴት ነው?
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • የፆታ ስነ ምግባር ምክንያታዊ መስሎ ይታይሃልን?
    ወጣትነትህን በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
w97 7/15 ገጽ 8-13

ብልግና በሞላበት ዓለም ውስጥ በጎ ሆኖ መኖር

“በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጒሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ።”​ —⁠ፊልጵስዩስ 2:​14, 15

1, 2. አምላክ ከነዓናውያን ጨርሰው እንዲጠፉ የፈለገው ለምን ነበር?

የይሖዋ ትእዛዛት ምንም የማያወላዱ ናቸው። እስራኤላውያን በነቢዩ ሙሴ አማካኝነት “አምላክህ እግዚአብሔር እንዳዘዘህ ኬጢያዊውን አሞራዊውንም ከነዓናዊውንም ፌርዛዊውንም ኤዊያዊውንም ኢያቡሳዊውንም ፈጽመህ ታጠፋቸዋለህ” የሚለውን ትእዛዝ ሲቀበሉ ወደ ተስፋይቱ ምድር ሊገቡ የቀራቸው ጥቂት ጊዜ ብቻ ነበር።​—⁠ዘዳግም 7:​2፤ 20:​17

2 ይሖዋ መሐሪ አምላክ ሆኖ ሳለ የከነዓን ምድር ነዋሪዎች ፈጽሞ እንዲጠፉ የፈለገው ለምን ነበር? (ዘጸአት 34:​6) አንዱ ምክንያት ‘ከነዓናውያን ለአማልክቶቻቸው ያደረጉትን ርኩሰት ሁሉ ያደርጉ ዘንድ እስራኤላውያንን እንዳያስተምሩአቸውና በአምላካቸው በይሖዋ ላይ ኃጢአት እንዳይሠሩ’ ነበር። (ዘዳግም 20:​18) በተጨማሪም ሙሴ “እነዚህን አሕዛብ ስለ ኃጢአታቸው እግዚአብሔር ከፊትህ ያወጣቸዋል” ሲል ተናግሯል። (ዘዳግም 9:​4) ከነዓናውያን ብልግና ክፉኛ የተጠናወታቸው ሰዎች ነበሩ። ልቅ የጾታ ብልግናና ጣዖት የአምልኳቸው መለያ ነበር። (ዘጸአት 23:​24፤ 34:​12, 13፤ ዘኁልቁ 33:​52፤ ዘዳግም 7:​5) በቅርብ ዘመዳሞች መካከል የጾታ ብልግና መፈጸም፣ ግብረ ሰዶምና እንስሳትን በጾታ መገናኘት ‘የከነዓን ምድር ሰዎች ሥራ’ ነበር። (ዘሌዋውያን 18:​3-25) ምንም የማያውቁ ጨቅላ ሕፃናት ጭካኔ በሞላበት መንገድ ለሐሰት አማልክት መሥዋዕት ሆነው ይቀርቡ ነበር። (ዘዳግም 18:​9-12) ይሖዋ የእነዚህ ብሔራት ሕልውና ብቻ እንኳ ለሕዝቦቹ አካላዊ፣ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ደህንነት አደገኛ እንደሆነ አድርጎ መመልከቱ ምንም አያስደንቅም!​—⁠ዘጸአት 34:​14-16

3. ከነዓናውያን ነዋሪዎችን በተመለከተ እስራኤላውያን አምላክ የሰጣቸውን ትእዛዝ ሙሉ በሙሉ ሳይፈጽሙ መቅረታቸው ምን አስከትሏል?

3 እስራኤላውያን አምላክ የሰጠውን ትእዛዝ ሙሉ በሙሉ ሳይፈጽሙ በመቅረታቸው የተስፋይቱን ምድር ለመያዝ ከወሰዱት የጥቃት እርምጃ ብዙ የከነዓን ምድር ነዋሪዎች በሕይወት ተርፈዋል። (መሳፍንት 1:​19-21) ውሎ አድሮ የከነዓናውያኑ መሰሪ ተጽዕኖ ወደ እስራኤል ብሔር ተዛመተ፤ በእርግጥም እንደሚከተለው ብሎ መናገር ይቻል ነበር:- “[እስራኤላውያንም] ሥርዓቱንም [የይሖዋንም ሥርዓት] ከአባቶቻቸውም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን፣ ያጸናላቸውንም ምስክሩን ናቁ፤ ከንቱ ነገርንም ተከተሉ፣ ምናምንቴዎችም ሆኑ፣ እግዚአብሔርም እንደ እነርሱ እንዳይሠሩ ያዘዛቸውን በዙሪያቸው ያሉትን አሕዛብን ተከተሉ።” (2 ነገሥት 17:​15) አዎን፣ ብዙ እስራኤላውያን አምላክ ከነዓናውያኑን እንዲያጠፋ ያስገደደውን ብልግና ለረጅም ዘመናት ሲፈጽሙ ኖረዋል። ጣዖት አምልከዋል፣ መረን የለቀቀ የጾታ ተግባር ይፈጽሙ ነበር፣ ከዚህም ሌላ ልጆቻቸውን ሳይቀር መሥዋዕት አድርገው አቅርበዋል!​—⁠መሳፍንት 10:​6፤ 2 ነገሥት 17:​17፤ ኤርምያስ 13:​27

4, 5. (ሀ) ከሃዲዋ እስራኤልና ይሁዳ ምን ደርሶባቸዋል? (ለ) በፊልጵስዩስ 2:​14, 15 ላይ ምን ጥብቅ ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል? ምን ጥያቄዎችስ ተነሥተዋል?

4 በመሆኑም ነቢዩ ሆሴዕ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ፣ እውነትና ምሕረት እግዚአብሔርን ማወቅ በምድር ስለሌለ እግዚአብሔር በምድሩ ላይ ከሚኖሩ ጋር ክርክር አለውና የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። እርግማንና ሐሰት ግዳይና ስርቆት ምንዝርናም ወጥተዋል፤ ደምም ወደ ደም ደርሶአል። ስለዚህ ምድሪቱ ታለቅሳለች፣ በእርስዋም የሚቀመጡ ሁሉ ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች ጋር ይደክማሉ፤ የባሕሩም ዓሦች ያልቃሉ።” (ሆሴዕ 4:​1-3) ብልሹ የነበረው የሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት በ740 ከዘአበ በአሦራውያን ተደመሰሰ። አንድ መቶ ዓመት ከሚያክል ጊዜ በኋላ ደግሞ ከሀዲ የነበረው የደቡባዊው የይሁዳ መንግሥት በባቢሎናውያን ተደምስሷል።

5 እነዚህ ታሪኮቸ በብልግና እንድንዋጥ መፍቀድ ምን ያህል አደገኛ ሊሆን እንደሚችል በግልጽ ያሳያሉ። አምላክ ዓመፃን ይጸየፋል፤ በሕዝቦቹ መካከል እንዲህ ዓይነት ነገር ሲፈጸም እያየም ዝም አይልም። (1 ጴጥሮስ 1:​14-16) እርግጥ ነው የምንኖረው እያደር ብልሹ እየሆነ በሚሄደው ‘በአሁኑ ክፉ ዓለም’ ውስጥ ነው። (ገላትያ 1:​4፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​13) ሆኖም ግን የአምላክ ቃል ሁሉም ክርስቲያኖች ‘በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የአምላክ ልጆች በመሆን በዓለም እንደ ብርሃን’ መመላለሳቸውን እንዲቀጥሉ አጥብቆ ያሳስባል። (ፊልጵስዩስ 2:​14, 15) ይሁን እንጂ ብልግና በሞላበት ዓለም ውስጥ በጎነታችንን ጠብቀን መኖር የምንችለው እንዴት ነው? በእርግጥ ይህንን ማድረግ ይቻላልን?

በብልግና የተሞላው የሮማውያን ዓለም

6. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በጎ ሆነው በመመላለስ ረገድ ፈታኝ ሁኔታ የገጠማቸው ለምን ነበር?

6 የሮማውያኑ ማኅበረሰብ በማንኛውም ዘርፍ በብልግና ተጥለቅልቆ ስለነበር በመጀመሪያ መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች በጎነታቸውን ጠብቀው ለመኖር ፈታኝ ሁኔታ ገጥሟቸው ነበር። ሮማዊው ፈላስፋ ሴኔካ በዘመኑ ስለነበረው ትውልድ እንዲህ ብሏል:- “ሰዎች ከክፋት ጋር ብርቱ ትንቅንቅ ገጥመዋል። በየዕለቱ ኃጢአት የመፈጸም ምኞት እያደገ ሲሄድ ኃጢአትን መፍራት እየተመናመነ ሄዷል።” ሴኔካ የሮማውያኑን ማኅበረሰብ ከ“ዱር አራዊት” ጋር አመሳስሎታል። በመሆኑም ሮማውያኑ ጭካኔ በተሞላበት የግላዲያተር ግጥሚያና የጾታ ብልግና በሚታይባቸው ተውኔቶች ለመዝናናት መምረጣቸው ምንም አያስገርምም።

7. ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ የነበሩ ብዙዎቹ ስለሚፈጽሟቸው የብልግና ድርጊቶች የገለጸው እንዴት ነው?

7 ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ የጻፈው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ሰዎች ወራዳ ምግባር በማሰብ ሊሆን ይችላል:- “ስለዚህ እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ፤ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ።” (ሮሜ 1:​26, 27) የረከሱ የሥጋ ምኞቶችን ለመከተል ቆርጦ የተነሳው የሮማውያኑ ማኅበረሰብ በብልግና ውስጥ ተዘፍቆ ነበር።

8. በግሪካውያንና በሮማውያን ኅብረተሰብ ውስጥ ልጆችን ለእኩይ ተግባር ይጠቀሙባቸው የነበረው እንዴት ነው?

8 በሮማውያን ዘንድ ግብረሰዶም ምን ያህል ተስፋፍቶ እንደነበር ታሪክ የሚገልጸው ነገር የለም። ይሁን እንጂ ከእነርሱ በፊት የነበሩት ግሪካውያን ተጽዕኖ እንዳደረጉባቸው ምንም ጥርጥር የለውም፤ በግሪካውያኑ ዘንድ ግብረሰዶም በእጅጉ ተስፋፍቶ ነበር። ብዙውን ጊዜ በዕድሜ ከፍ ያሉ ወንዶች ወጣት ወንዶችን ለማስተማር ብለው በኃላፊነት ከወሰዱ በኋላ በሥነ ምግባር ያበላሿቸዋል። ይህም ልጆቹን ወደ ወራዳ የጾታ ብልግና ይመራቸዋል። ከዚህ ብልግናና በልጆች ላይ ከሚፈጸም በደል በስተጀርባ ያሉት ሰይጣንና አጋንንቱ መሆናቸውም ምንም አያጠያይቅም።​—⁠ኢዩኤል 3:​3፤ ይሁዳ 6, 7

9, 10. (ሀ) 1 ቆሮንቶስ 6:​9, 10 የተለያዩ ዓይነት ብልግናዎችን ያወገዘው እንዴት ነው? (ለ) በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ የነበሩት አንዳንዶቹ ምን ዓይነት ድርጊቶች ይፈጽሙ ነበር? ምን ዓይነት ለውጥስ አደረጉ?

9 ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት ሲጽፍ እንዲህ ብሏል:- “ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፣ ተቀድሳችኋል፣ ጸድቃችኋል።”​—⁠1 ቆሮንቶስ 6:​9-11

10 ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈው ደብዳቤ “ዝሙት የሚሠሩ” “የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” በማለት የጾታ ብልግናን አውግዟል። ሆኖም ጳውሎስ በርከት ያሉ የብልግና ድርጊቶችን ከዘረዘረ በኋላ “ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን . . . ታጥባችኋል” ሲል ተናግሯል። ኃጢአተኛ የነበሩት ሰዎች በአምላክ እርዳታ በፊቱ ንጹሕ መሆን ችለው ነበር።

11. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ዙሪያቸውን በከበባቸው መጥፎ ሁኔታ ውስጥ ቢኖሩም ምን አድርገዋል?

11 አዎን፣ ብልግና በሞላበት የመጀመሪያው መቶ ዘመን እንኳን ክርስቲያናዊ በጎነት አብቦ ታይቷል። አማኞች ‘በልባቸው መታደስ ተለውጠው’ ነበር። (ሮሜ 12:​2) ‘ፊተኛ ኑሯቸውን ትተው አእምሮአቸውን በሚያንቀሳቅሰው ኃይል ታድሰዋል።’ በዚህ መንገድ ከዓለም ብልግና ርቀው ‘እንደ አምላክ ፈቃድ በእውነተኛ ጽድቅና ታማኝነት የተፈጠረውን አዲሱን ሰው’ ለብሰዋል።​—⁠ኤፌሶን 4:​22-24 NW

ዛሬ ያለው በብልግና የተሞላ ዓለም

12. ከ1914 ወዲህ በዓለም ላይ ምን ዓይነት ለውጥ ተከስቷል?

12 ስለ ዘመናችንስ ምን ማለት ይቻላል? የምንኖርበት ዓለም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ብልግና የገነነበት ሆኗል። በተለይ ከ1914 ወዲህ በምድር ዙሪያ ከፍተኛ የሥነ ምግባር ማሽቆልቆል ይታያል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5) ብዙ ሰዎች በባሕላቸው እንደ ጥሩ ነገር ተደርገው ይታዩ የነበሩትን በጎነትን፣ መልካም ምግባርን፣ ሌሎች ሰዎችን ማክበርንና ግብረገብነትን ወደጎን ገሸሽ በማድረግ በራስ ወዳድነት አስተሳሰብ ከመዋጣቸውም በላይ ‘የሥነ ምግባር ስሜታቸው ጨርሶ ደንዝዟል።’ (ኤፌሶን 4:​19) ኒውስዊክ የተባለው መጽሔት “የምንኖረው ጥሩ ሥነ ምግባር እንደየሰዉ ሁኔታ ይለያያል የሚል ፈሊጥ በነገሠበት ጊዜ ላይ ነው” ከማለቱም ሌላ ዛሬ የሰፈነው የሥነ ምግባር ሁኔታ “ትክክል እና ስህተት የሆኑት ነገሮች በግል ምርጫና ስሜት ወይም እንደ ባሕሉ ሁኔታ እንዲወሰኑ እንዳደረገ” ገልጿል።

13. (ሀ) ዛሬ ያለው አብዛኛው መዝናኛ ብልግናን የሚያራምደው እንዴት ነው? (ለ) ተገቢ ያልሆነ መዝናኛ በግለሰቦች ላይ ምን ዓይነት መጥፎ ውጤት ሊያስከትል ይችላል?

13 እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ ዛሬም ወራዳ መዝናኛዎች ተስፋፍተዋል። ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮ፣ ሲኒማዎችና የቪዲዮ ፊልሞች ከጾታ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ነገሮች ያዥጎደጉዳሉ። ብልግና ወደ ኮምፒዩተር ኔትወርኮች ሳይቀር ዘልቆ ገብቷል። የወሲብ ስሜትን ለመቀስቀስ ታስበው የሚዘጋጁ ነገሮች በዛሬዎቹ የኮምፒዩተር ኔትወርኮች እየተስፋፉ የመጡ ሲሆን በተለያየ የዕድሜ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች በቀላሉ የሚያገኟቸው ሆነዋል። ታዲያ ይህ ሁሉ ነገር ያስከተለው ውጤት ምንድን ነው? አንድ የጋዜጣ አምድ አዘጋጅ እንዳሉት “ደም መፋሰስና ጭካኔ እንዲሁም ርካሽ የጾታ ብልግና ተወዳጅ ባሕላችንን ሲበክለው ደም መፋሰሱንም፣ ጭካኔውንም ሆነ ርካሽ የጾታ ድርጊቱን ሁሉ እንለምደዋለን። ደንዝዘን እናድጋለን። የሚፈጸመው የሥነ ምግባር ብልግና እምብዛም የማያስደነግጠን መሆኑ ድርጊቶቹን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተላመድናቸው እንደመጣን ያሳያል።”​—⁠ከ1 ጢሞቴዎስ 4:​1, 2 ጋር አወዳድር።

14, 15. በዓለም ዙሪያ የጾታ ሥነ ምግባር እንዳሽቆለቆለ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

14 ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ መጽሔት ላይ የወጣውን የሚከተለውን ሪፖርት ልብ በል:- “ከ25 ዓመታት በፊት አጸያፊ እንደሆነ ተደርጎ ይታይ የነበረው ነገር ዛሬ ተቀባይነት ያገኘ አኗኗር ሆኗል። [በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ] ከመጋባት ይልቅ እንዲሁ ከተቃራኒ ጾታ ጋር አብሮ መኖር የሚመርጡ ሰዎች ቁጥር ከ1980 እስከ 1991 ባሉት ዓመታት ውስጥ 80 በመቶ አሻቅቧል።” ይህ በሰሜን አሜሪካ ውስጥ ብቻ የሚታይ ነገር አይደለም። ኤዢያዊክ የተባለው መጽሔት እንዲህ በማለት ሪፖርት አድርጓል:- “በመላዋ [እስያ] በሚገኙ አገሮች ውስጥ በባሕል ላይ የሚደረገው እሰጥ አገባ ተጧጡፏል። ክርክሩ በጾታ ነጻነትና በባሕላዊ ሥነ ምግባሮች መካከል ሲሆን ለውጥ እንዲካሄድ የሚደረገው ግፊት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።” አኃዛዊ መረጃዎቹ እንደሚያሳዩት በብዙ አገሮች ውስጥ ምንዝርና ከጋብቻ በፊት የሚፈጸም የጾታ ግንኙነት እያደር ተቀባይነት እያገኙ መጥተዋል።

15 መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን ሰይጣናዊ ድርጊቶች እንደሚበራከቱ አስቀድሞ ተናግሯል። (ራእይ 12:​12) እንግዲያውስ ብልግና በአስደንጋጭ ሁኔታ እየተስፋፋ መሄዱ ሊያስገርመን አይገባም። ለምሳሌ ያህል ልጆችን ለወሲብ ተግባር መጠቀም እንደ ወረርሽኝ ተስፋፍቷል።a የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት እንዲህ ሲል ሪፖርት አድርጓል:- “ሕፃናትን በጾታ ተግባር አሠማርቶ የገንዘብ ማግኛ ማድረግ በልጆች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነው፤ ይህ ችግር ያልዳሰሰው የዓለም ክፍል የለም ለማለት ይቻላል።” በየዓመቱ “በዓለም ዙሪያ ከ1 ሚልዮን የሚበልጡ ልጆች ለሕፃናት ዝሙት አዳሪነት ይዳረጋሉ፣ ለወሲብ ተግባር ይሸጣሉ እንዲሁም ዕርቃንን የሚያሳዩ የወሲብ ሥዕሎችን ለማዘጋጀት ይጠቀሙባቸዋል።” ግብረሰዶምም የተለመደ ነገር ሆኗል፤ እንዲያውም አንዳንድ ፖለቲከኞችና የሃይማኖት መሪዎች ግብረሰዶምን “እንደ አማራጭ የኑሮ ዘይቤ” አድርገው በመከተል ረገድ ግንባር ቀደም ሆነዋል።

ከዓለም ብልግና ራቁ

16. የይሖዋ ምሥክሮች የጾታ ሥነ ምግባርን በተመለከተ ምን አቋም ይወስዳሉ?

16 የይሖዋ ምሥክሮች የጾታ ሥነ ምግባርን በተመለከተ ልቅ የአቋም ደረጃ የሚያራምዱትን ሰዎች አይደግፉም። ቲቶ 2:​11, 12 እንዲህ ይላል:- “ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይህም ጸጋ፣ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፣ . . . ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል።” አዎን፣ ከጋብቻ በፊት የሚፈጸም የጾታ ብልግናን፣ ዝሙትንና ግብረሰዶምን ለመሳሰሉት የብልግና ድርጊቶች ጠንካራ ጥላቻ ለማዳበርና እነዚህን ነገሮች ለመጸየፍ እንጥራለን።b (ሮሜ 12:​9፤ ኤፌሶን 5:​3-5) ጳውሎስ “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከዓመፅ ይራቅ” ሲል አጥብቆ መክሯል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 2:​19

17. እውነተኛ ክርስቲያኖች ለአልኮል መጠጦች ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው?

17 እውነተኛ ክርስቲያኖች ዓለም አቅልሎ ከሚያያቸው ብልግናዎች ይርቃሉ። ለምሳሌ ያህል ዛሬ ብዙ ሰዎች የአልኮል መጠጦችን ከልክ በላይ መጠጣትን እንደ ጨዋታ ያዩታል። የይሖዋ ሕዝቦች ግን በኤፌሶን 5:​18 ላይ ያለውን ምክር ይከተላሉ:- “መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና።” አንድ ክርስቲያን ለመጠጣት ቢመ​ርጥ እንኳን የሚጠጣው በልክ ነው።​—⁠ምሳሌ 23:​29-32

18. የይሖዋ አገልጋዮች ከቤተሰብ አባሎቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት የሚመሩት እንዴት ነው?

18 ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን በትዳር ጓደኛና በልጆች ላይ በቁጣ መጮህ ወይም እነርሱን መሳደብ ምንም ስህተት የለበትም የሚለውን አንዳንድ የዓለም ሰዎች ያላቸውን አመለካከት አንቀበልም። ክርስቲያን ባሎችና ሚስቶች የበጎነትን ጎዳና ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ ጳውሎስ የሰጠውን ምክር በተግባር ለማዋል ተባብረው ይሠራሉ:- “መራርነትና ንዴት ቊጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፣ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ።”​—⁠ኤፌሶን 4:​31, 32

19. ብልግና በንግዱ ዓለም ምን ያህል ተስፋፍቷል?

19 በዛሬው ጊዜ እምነት ማጉደል፣ ማጭበርበር፣ ውሸት፣ በሌላው ጉሮሮ ላይ ከመቆም ተለይተው የማይታዩ የንግድ ስልቶችና ስርቆት ጭምር በሰፊው ተለምደዋል። ሲ ኤፍ ኦ በተባለው የንግድ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ እንዲህ ብሏል:- “በ4,000 ሠራተኞች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው . . . ጥናቱ ከተካሄደባቸው ሰዎች መካከል 31 በመቶ የሚያክሉት ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ‘ከበድ ያለ እኩይ ተግባር’ ሲፈጸም ተመልክተዋል።” ይህም ውሸትን፣ መዛግብት መደለዝን፣ ጾታዊ ጥቃትንና ስርቆትን የሚጨምር ነበር። በይሖዋ ዓይን በሥነ ምግባር ንጹህ ሆነን እንድንታይ ከፈለግን እንዲህ ዓይነቶቹን ድርጊቶች አስወግደን በምናደርጋቸው ገንዘብ ነክ ግንኙነቶች ሁሉ ሐቀኞች መሆን ይኖርብናል።​—⁠ሚክያስ 6:​10, 11

20. ክርስቲያኖች ‘ገንዘብን ከመውደድ’ መራቅ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?

20 በንግዱ ዓለም ገብቶ በአጭር ጊዜ ቢከብር ለአምላክ አገልግሎት የሚያውለው ተጨማሪ ጊዜ ሊያገኝ እንደሚችል የተሰማው አንድ ሰው ምን እንደገጠመው ተመልከት። ስለሚገኘው የወደፊት ትርፍ ከልክ በላይ በማጋነን ሌሎችም በእርሱ የኢንቨስትመንት ሕልም ውስጥ እንዲገቡ አደረገ። ያሰበው ነገር ሊሳካ ባለመቻሉ የተዘፈቀበትን ከፍተኛ ዕዳ ለመክፈል ሲል በእጁ ላይ ከነበረው ገንዘብ ይሠርቃል። ባደረጋቸው ነገሮችና የንስሐ ዝንባሌ ባለማሳየቱ ምክንያት ከክርስቲያን ጉባኤ ተወገደ። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው የሚከተለው ምክር እውነት ነው:- “ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፣ አንዳንዶችም ይህን ሲመኙ፣ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ።”​—⁠1 ጢሞቴዎስ 6:​9, 10

21. በዓለም ውስጥ በሥልጣን ላይ ባሉት ሰዎች ዘንድ ባብዛኛው የሚታየው ባሕርይ የትኛው ነው? ይሁን እንጂ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ወንዶች እንዴት መመላለስ ይገባቸዋል?

21 በዓለም ውስጥ ሥልጣንንና ተደማጭነትን ያገኙ ሰዎች ብዙውን ጊዜ በጎነት የላቸውም፤ ይህም ‘ሥልጣን ያባልጋል’ የሚለው ምሳሌ እውነት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። (መክብብ 8:​9) በአንዳንድ አገሮች ጉቦና ሌሎች የምግባረ ብልሹነት ድርጊቶች በዳኞች፣ በፖሊሶችና በፖለቲካ ሰዎች ዘንድ የተለመዱ ነገሮች ሆነዋል። ሆኖም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ቀዳሚ ሆነው የሚያገለግሉት ወንዶች በጎነትን የሚከተሉ እንጂ በሌሎች ላይ የሚገዙ ሊሆኑ አይገባም። (ሉቃስ 22:​25, 26) ሽማግሌዎችም ሆኑ የጉባኤ አገልጋዮች የሚያገለግሉት ‘መጥፎውን ረብ በመመኘት’ አይደለም። ወደፊት የሚያገኙትን ብልጽግና በማሰብ የሚያደርጉትን ውሳኔ ለማጣመም ወይም ለማስተካከል ከመሞከር መራቅ ይኖርባቸዋል።​—⁠1 ጴጥሮስ 5:​2፤ ዘጸአት 23:​8፤ ምሳሌ 17:​23፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:​21

22. በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ የሚብራራው ነገር ምንድን ነው?

22 በጥቅሉ ሲታይ ክርስቲያኖች ዛሬ ባለው ብልግና በሞላበት ዓለም ውስጥ የሚገጥማቸውን በጎ ሆኖ የመኖር ፈታኝ ሁኔታ በተሳካ ሁኔታ እየተቋቋሙት ነው። ይሁን እንጂ በጎነት ከክፋት በመራቅ ብቻ አይወሰንም። የሚቀጥለው ርዕስ በጎነትን መኮትኮት ምን ነገር እንደሚጠይቅ ያብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ጥቅምት 8, 1993 የእንግሊዝኛ ንቁ! መጽሔት እትም ላይ የወጣውን “ልጆቻችሁን ጠብቁ!” የሚለውን ተከታታይ ርዕስ ተመልከት።

b ከአሁን ቀደም ግብረሰዶም ይፈጽሙ የነበሩ ሰዎች በመጀመሪያው መቶ ዘመን አንዳንዶች እንዳደረጉት የባሕርይ ለውጥ ሊያደርጉ ይችላሉ። (1 ቆሮንቶስ 6:​11) በመጋቢት 22, 1995 ንቁ! (የእንግሊዝኛው) ገጽ 21-23 ላይ ጠቃሚ ሐሳብ ወጥቷል።

የክለሳ ነጥቦች

◻ ይሖዋ ከነዓናውያን ጨርሰው እንዲጠፉ ያዘዘው ለምንድን ነበር?

◻ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ተስፋፍተው የነበሩት የብልግና ድርጊቶች የትኞቹ ናቸው? ክርስቲያኖችስ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ምን አድርገዋል?

◻ ዓለም ከ1914 ወዲህ ለተከሰተው የሥነ ምግባር ውድቀት የዓይን ምሥክር እንደሆነ የሚሳይ ምን ማረጋገጫ አለ?

◻ የይሖዋ ሕዝቦች ሊርቋቸው የሚገቡ የተለመዱ የብልግና ድርጊቶች ምንድን ናቸው?

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ብልግና በሞላበት ዓለም ውስጥ ቢኖሩም በጎዎች ነበሩ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብልግና ወደ ኮምፒዩተር ኔትወርኮች እንኳ ሳይቀር ዘልቆ ገብቷል፤ ይህም ብዙ ወጣቶችንና ሌሎችንም የወሲብ ስሜትን ለመቀስቀስ ታስበው ለሚዘጋጁ ነገሮች አጋልጧቸዋል

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያኖች የሌሎችን የማጭበርበሪያ ዘዴ ከመኮረጅ በመራቅ በጎነታቸውን ጠብቀው ሊኖሩ ይገባል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ