ሕሊና ጸጋ ነው ወይስ ሸክም?
‘ሕሊናዬ እየረበሸኝ ነው!’ ሁላችንም ማለት ይቻላል፣ አልፎ አልፎ ሕሊናችን ያሠቃየናል። እንዲህ ዓይነቱ ስሜት ደረጃው የተለያየ ሲሆን ከቀላል የአእምሮ መረበሽ አንስቶ እስከ ከፍተኛ የስሜት ሥቃይ ሊደርስ ይችላል። የሕሊና መረበሽ የመንፈስ ጭንቀት ወይም ከባድ የሆነ የከንቱነት ስሜት ሊያስከትልም ይችላል።
እንግዲያው ከዚህ አንጻር ሲታይ ሕሊና ሸክም አይደለምን? አንዳንዶች ሸክም እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። ቀደም ባሉት ዘመናት የነበሩት ትውልዶች በአብዛኛው ሕሊናን በተፈጥሮ የተገኘ ስጦታ አድርገው ይመለከቱት ነበር። ብዙዎች አምላክ ራሱ በቀጥታ ለሰው ልጆች የሰጠው የሥነ ምግባር መምሪያ እንደሆነ ይሰማቸው ነበር። በመሆኑም ሕሊና “በሰው ውስጥ ያለ አምላክን የሚወክል ነገር፣” “በቀጥታ በተፈጥሮ የተገኘ ውርስ፣” አልፎ ተርፎም “የአምላክ ድምፅ” ተብሎ ተጠርቷል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ሕሊና በአብዛኛው ወላጆችና ማኅበራዊ ሁኔታዎች በሚያሳድሩት ተጽዕኖ ከጊዜ በኋላ የሚገኝ ችሎታ ነው የሚለው አስተሳሰብ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ የሥነ ልቦና ምሁራን ሕሊና ብለን የምንጠራው ነገር የሚያመለክተው ከወላጆቻችን የቀሰምናቸውን የግል እሴቶችና እምነቶች ብቻ ነው የሚል እምነት ስላላቸው አንድ ልጅ መጥፎ ከሆነ ድርጊት የሚቆጠብበት ዋነኛው ምክንያት ቅጣትን ስለሚፈራ ነው ብለው ይከራከራሉ። ሌሎች ደግሞ ኅብረተሰቡ በአጠቃላይ እሴቶችንና የሥነ ምግባር ሥርዓቶችን በማስተላለፍ ረገድ የሚጫወተውን ሚና ይጠቅሳሉ። አንዳንዶች የሕሊና ሥቃይ የሚመጣው መሥራት በምንፈልገው ነገርና አንድ ጨቋኝ ኅብረተሰብ እንድናደርገው በሚፈልግብን ነገር መካከል በሚፈጠረው ግጭት ብቻ ነው የሚል አስተሳሰብ አላቸው!
ስለ ሕሊና እነዚህን የመሰሉ አስተያየቶች ቢሰነዘሩም ሰዎች ወላጆቻቸው፣ ቤተሰቦቻቸውና መላው ኅብረተሰብ የሚያደርጉባቸውን ተጽእኖ ሁሉ ተቋቁመው ሕሊናቸው ያዘዛቸውን ነገር እንዳደረጉ በተደጋጋሚ ታይቷል። እንዲያውም አንዳንዶች ሕሊናቸውን ለመታዘዝ ሲሉ ሕይወታቸውን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኞች እስከ መሆን ደርሰዋል! በተጨማሪም በዓለም ውስጥ ያሉት ባሕሎች በጣም የተለያዩ ቢሆኑም እንኳ ነፍስ ግድያ፣ ስርቆት፣ ምንዝር፣ ውሸት፣ በቅርብ ዘመዳሞች መካከል የሚፈጸም የጾታ ግንኙነትና እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች ድርጊቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ማለት ይቻላል፣ የሚወገዙ ነገሮች ናቸው። ይህ ሁኔታ ሕሊና በተፈጥሮ የሚገኝ ስጦታ እንደሆነ አያስገነዝብምን?
ሕሊና—የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
ይህን ርዕሰ ጉዳይ በተመለከተ ከማንም በላይ ትክክለኛውን ማብራሪያ መስጠት የሚችለው ይሖዋ አምላክ ነው። ደግሞም ‘የሠራን አምላክ እንጂ እኛ አይደለንም።’ (መዝሙር 100:3) አፈጣጠራችንን ጠንቅቆ ያውቃል። የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ሰው በአምላክ ‘መልክ’ እንደተሠራ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 1:26) ሰው የተፈጠረው ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር እንዲለይ ተደርጎ ነው፤ ከመጀመሪያው አንስቶ ሕሊና የሰው ልጅ በተፈጥሮ ያገኘው ነገር ነው።—ከዘፍጥረት 2:16, 17 ጋር አወዳድር።
ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ለሮሜ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ይህን አረጋግጧል:- “[የአምላክ] ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ከባሕርያቸው [“በተፈጥሮአቸው፣” የ1980 ትርጉም] የሕግን ትእዛዝ ሲያደርጉ፣ እነዚያ ሕግ ባይኖራቸው እንኳ ለራሳቸው ሕግ ናቸውና፤ እነርሱም ሕሊናቸው ሲመሰክርላቸው፣ አሳባቸውም እርስ በርሳቸው ሲካሰስ ወይም ሲያመካኝ በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ።” (ሮሜ 2:14, 15) ብዙዎች ለአይሁዳውያን በተሰጠው መለኮታዊ ሕግ ተኮትኩተው ያላደጉ ቢሆንም እንኳ በአምላክ ሕግ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንደተከተሉ ልብ በል፤ ይህን ያደረጉት በማኅበራዊ ተጽእኖ ሳይሆን “በተፈጥሮአቸው” ነው!
እንግዲያው ሕሊና ሸክም ሳይሆን መለኮታዊ ስጦታ ወይም ጸጋ ነው። ጭንቀት ሊያስከትልብን እንደሚችል አይካድም። ሆኖም በሚገባ ስንታዘዘው ደግሞ ጥልቅ የእርካታ ስሜትና ውስጣዊ ሰላም በመስጠት ሊክሰን ይችላል። ሊመራን፣ ሊጠብቀንና ለሥራ ሊያንቀሳቅሰን ይችላል። ዚ ኢንተርፕሬተርስ ባይብል የሚከተለውን ሐሳብ ይሰጣል:- “አንድ ግለሰብ የአእምሮና የስሜት ጤንነቱ ሊጠበቅ የሚችለው በሚያደርገው ነገርና ማድረግ እንዳለበት በሚሰማው ነገር መካከል ያለውን ክፍተት ለመዝጋት ከሞከረ ብቻ ነው።” አንድ ሰው ይህን ክፍተት መዝጋት የሚችለው እንዴት ነው? ሕሊናችንን መቅረጽና ማሰልጠን ይቻላልን? እነዚህ ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራሉ።