የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
“ዋጋዋ እጅግ የበዛ አንዲት ዕንቁ” አገኘ
“መንግሥተ ሰማያት መልካምን ዕንቁ የሚሻ ነጋዴን ትመስላለች፤ ዋጋዋም የበዛ አንዲት ዕንቁ በአገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ገዛት።” ኢየሱስ በእነዚህ ቃላት በመጠቀም የአምላክ መንግሥትን ከፍተኛ ዋጋ ገልጿል። (ማቴዎስ 13:45, 46) የመንግሥቲቱን ዋጋማነት የተገነዘቡ ሰዎች እሷን ለማግኘት ሲሉ ብዙ ጊዜ በግላቸው ትልልቅ መሥዋዕቶችን ይከፍላሉ። ከታይዋን ከፒንጁ ግዛት የተገኘው የሚከተለው ተሞክሮ ይህን ያሳያል።
አቶ ሊን እና ባለቤቱ በ1991 ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ይጀምራሉ። በከተማው የሚገኝ አንድ ቄስ ይህን በሚያውቅበት ጊዜ እነሱን የእርሱ ቤተ ክርስቲያን አባላት እንዲሆኑ ለማድረግ ይሞክራል። ሊንና ቤተሰቡ በከተማው በሚገኘው ገበያ የአሳማና የዳክዬ ደም ይሸጡ ስለነበር ቄሱ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን አመለካከት ሊጠይቁት ወሰኑ። ቄሱም “አምላክ የሠራው ማንኛውም ነገር ለሰው ምግብ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል” በማለት መለሰ። በሌላ በኩል ግን ምሥክሮቹ የአምላክ ቃል ምን እንደሚል እንዲመረምሩ አበረታቷቸው። “የአንድ ፍጡር ሕይወት ደም ስለሆነ” ይሖዋ አምላክ ደምን ቅዱስ አድርጎ እንደሚመለከተው ተማሩ። (ዘሌዋውያን 17:10, 11፣ ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) ስለዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘ከደም መራቅ’ ይኖርባቸዋል። (ሥራ 15:20) የሊን ቤተሰብ ቅዱሳን ጽሑፎች ይህን ርዕስ በተመለከተ ምን እንደሚሉ ከመረመሩ በኋላ ዋነኛው የገቢ ምንጫቸው ቢሆንም እንኳን ደም መሸጣቸውን ለማቆም ወሰኑ። ይሁን እንጂ ምንም ያህል ሳይቆዩ ከዚህ የሚበልጥ ሌላ ፈተና አጋጠማቸው።
የሊን ቤተሰብ እውነትን ከማጥናታቸው በፊት በማሳቸው ውስጥ ያለሟቸው 1,300 የቢተል ነት ተክሎች ነበሯቸው። ምንም እንኳ ተክሎቹ አድገው ትርፍ እስኪያስገኙ ድረስ አምስት ዓመት የሚፈጅ ቢሆንም አንድ ጊዜ ሙሉ ምርታቸውን መስጠት ከጀመሩ በኋላ ግን የሊን ቤተሰብ በዓመት 77,000 ዶላር ለማግኘት ይችል ነበር። መጀመሪያ የደረሰው ቢተል ነት የሚሰበሰብበት ወቅት ሲቃረብ የሊን ቤተሰብ አንድ አስፈላጊ እርምጃ መውሰድ ነበረበት። ክርስቲያኖች እንደ ሲጋራ ማጨስ፣ በዕፅ አለአግባብ መጠቀም እና ቢተል ነት ማኘክ በመሳሰሉ ርኩስ ልማዶች ከመጠቀምም ሆነ ከማስፋፋት በመራቅ “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ” ራሳቸውን ማንጻት እንዳለባቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው ተምረው ነበር። (2 ቆሮንቶስ 7:1) ምን አድርገው ይሆን?
አቶ ሊን ሕሊናው እረፍት ስለነሳው ጥናቱን ለማቆም ወሰነ። ይህ በእንዲህ እንዳለ የአቶ ሊን ባለቤት ቀደም ሲል ተክለዋቸው ከነበሩ ዛፎች ጥቂት ቢተል ነቶችን በመሸጥ ከ3,000 ዶላር በላይ ትርፍ አገኘች። ይህ ደግሞ ተክሎቹ እንዲያድጉ ከተተዉ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚያስገኙትን ትርፍ የሚያመላክት ነበረ። ሆኖም አቶ ሊን ሕሊናው እረፍት ሊሰጠው አልቻለም።
በጉዳዩ ላይ ካወጣና ካወረደ በኋላ አንድ ቀን በከተማው የሚገኙትን ምሥክሮች የቢተል ተክሎቹን እንዲቆርጡለት ጠየቃቸው። ምሥክሮቹ ይህን ለማድረግ የወሰነው እሱ ስለሆነ ተክሎቹን ራሱ በመቁረጥ ‘የገዛ ራሱን ሸክም መሸከም’ እንዳለበት ገለጹለት። (ገላትያ 6:4, 5) ምሥክሮቹ በ1 ቆሮንቶስ 10:13 ላይ የሚገኙትን “ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፣ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል” የሚሉትን ተስፋ ያዘሉ ቃላት እንዲያስታውስ አበረታቱት። በተጨማሪም ምሥክሮቹ “እኛ ዛፎቹን ቆርጠን ብናጠፋቸው ምናልባት ይጸጽትህና ለዛፎቹ መጥፋት እኛን ተወቃሽ ታደርገን ይሆናል” በማለት በምክንያት አስረዱት። ከጥቂት ጊዜያት በኋላ የመጋዝ ድምፅ የአቶ ሊንን ባለቤት ከጠዋት እንቅልፏ ይቀሰቅሳታል። ባለቤቷና ልጆቿ የቢተል ዛፎቹን እየቆረጧቸው ነበር!
አቶ ሊን ይሖዋ የገባውን ቃል የሚፈጽም መሆኑን ተገንዝቧል። ንጹህ ሕሊና እንዲኖረው የሚያስችለውን ሥራ ስላገኘ የይሖዋ አወዳሽ ለመሆን ችሏል። በሚያዝያ 1996 በተደረገ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች የወረዳ ስብሰባ ላይ ተጠምቋል።
አዎን፣ አቶ ሊን ቃል በቃል “ያለውን ሁሉ ሸጦ፣ ዋጋዋ እጅግ የበዛ አንዲት ዕንቁ” ገዝቷል። በአሁኑ ወቅት አቶ ሊን ከይሖዋ አምላክ ጋር የግል ዝምድና የመመሥረትና ስለ አምላክ መንግሥት የመናገር ውድ መብት አግኝቷል።