ታስታውሳለህን?
በቅርብ ጊዜ ከወጡት የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ተግባራዊ ጠቀሜታ አግኝተህባቸዋልን? እንግዲያው ምን ያህል እንደምታስታውስ በሚከተሉት ጥያቄዎች ለምን ራስህን አትፈትንም?
◻ አርማጌዶን ምን ይመስል ይሆን? (ራእይ 16:14, 16)
አርማጌዶን የኑክሌር እልቂት ወይም የሰው ልጅ የሚያመጣው ጥፋት አይደለም። አርማጌዶን ጦርነትንና ጦርነቶቹን የሚያራምዱትን ሰዎች ጨርሶ የሚያወድምና ሰላም ወዳድ ለሆኑ ሁሉ እውነተኛ ሰላም ለማምጣት የሚደረግ የአምላክ ጦርነት ነው። አይዘገይም። (ዕንባቆም 2:3)—4/15፣ ገጽ 17
◻ ይሖዋን የሚያስከብር ሠርግ ምን ዓይነት ነው?
አንድ ሠርግ ከዓለማዊ ልማዶች ይልቅ መንፈሳዊ ነገሮች ጎልተው የሚታዩበት ከሆነ በእርግጥም ይሖዋን ያስከብራል። ክርስቲያኖች ወራዳ የሆኑ ዓለማዊ ባህሎችንና አጉል እምነቶችን እንዲሁም አባካኝነትን ካስወገዱ፣ ሠርጉ ለመደበኛ የቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ዕንቅፋት እንዲሆን ካልፈቀዱና ከይታይልኝ መንፈስ ይልቅ ልከኝነትን ካንጸባረቁ በግብዣው ይደሰታሉ።—4/15፣ ገጽ 26
◻ የአቋም ጽናት ያለው ሰው በምን ተለይቶ ይታወቃል?
የጸና አቋም ያለው አንድ ሰው በሌሎች ሰዎች ዘንድ ብቻ ሳይሆን ይበልጡኑ በአምላክም ፊት እምነት የሚጣልበት ሆኖ ይገኛል። የልብ ንጽሕናው በሚያደርገው ነገር ይንጸባረቃል። ግብዝነት የለበትም። አጭበርባሪ ወይም ምግባረ ብልሹ አይደለም። (2 ቆሮንቶስ 4:2)—5/1፣ ገጽ 6
◻ ኤርምያስ “ሰው በታናሽነቱ ቀንበር ቢሸከም መልካም ነው” ሲል የተናገረው ለምንድን ነው? (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:27)
አንድ ሰው በወጣትነቱ ችግሮችን እንዴት መቋቋም እንደሚችል መማሩ በጉልምስና ዕድሜው የሚያጋጥሙትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመጋፈጥ ዝግጁ እንዲሆን ይረዳዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) ታማኝነት የሚያስገኘው ጥቅም አቋምን ማላላት ሊያመጣ ከሚችለው ከማናቸውም ጊዜያዊ እፎይታ በጣም የላቀ ነው።—5/1፣ ገጽ 32
◻ ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ በተለወጠበት ጊዜ ሙሴና ኤልያስ መታየታቸው ምን የሚያመለክት ነበር?
ኢየሱስ በተዓምራዊ ሁኔታ በተለወጠበት ጊዜ የታዩት ሙሴና ኤልያስ የኢየሱስን ቅቡዓን ወንድሞች በትክክል ያመለክታሉ። ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር “በክብር” መታየታቸው ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሰማያዊ መንግሥት ዝግጅት ውስጥ ከኢየሱስ ጋር ‘ክብር እንደሚጎናጸፉ’ የሚያመለክት ነው። (ሉቃስ 9:30, 31፤ ሮሜ 8:17፤ 2 ተሰሎንቄ 1:10)—5/15፣ ገጽ 12, 14
◻ የአምላክ “ቅዱስ ምሥጢር” ምንድን ነው? (1 ቆሮንቶስ 2:7)
የአምላክ “ቅዱስ ምሥጢር” በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያተኮረ ነው። (ኤፌሶን 1:9, 10) ይሁን እንጂ ይህ ቅዱስ ምሥጢር ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ መሆኑን ብቻ የሚያመለክት አይደለም። አንድን ሰማያዊ መንግሥት ማለትም የአምላክን መሲሐዊ መንግሥትና ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተውን ሚና ይጨምራል።—6/1፣ ገጽ 13
◻ አንድ ክርስቲያን የእድሜ መግፋትንና ሕመምን እንዴት ሊመለከታቸው ይገባል?
የሚደርስበትን ፈተና ለይሖዋ የሚያቀርበውን አገልግሎት እንደሚገድብበት አድርጎ ከመመልከት ይልቅ በእርሱ ላይ ያለውን ትምክህት ለማሳደግ የሚያስችል አጋጣሚ አድርጎ ሊመለከተው ይገባል። በተጨማሪም የአንድ ክርስቲያን ዋጋማነት የሚለካው በሚያከናውናቸው ነገሮች ብቻ ሳይሆን በእምነቱና በፍቅሩ ጥልቀት መጠን መሆኑን ማስታወስ አለበት። (ማርቆስ 12:41-44)—6/1፣ ገጽ 26
◻ ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን ከመላእክት ይልቅ ሰዎች እንዲጽፉ ማድረጉ ጥበቡ ታላቅ እንደሆነ የሚያሳየው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምንም ዓይነት ሰብዓዊ ለዛ ባይኖረው ኖሮ መልእክቱን መረዳት ሊቸግረን ይችል ነበር። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን ሰዎች መጻፋቸው ልባዊ ስሜት የተንጸባረቀበት፣ የተለያየ አቀራረብ ያለውና የሚስብ እንዲሆን አድርጎታል።—6/15፣ ገጽ 8
◻ የቤተሰብ ደስታ የሚገኝበት ምሥጢር ምንድን ነው?
ምስጢሩ ያለው የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስና በውስጡ በሚገኙት እንደ ራስን መግዛት፣ የራስነትን ሥርዓት መቀበል፣ ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግና ፍቅር የመሳሰሉትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በማድረግ ላይ ነው።—6/15፣ ገጽ 23, 24
◻ ኢየሱስ ያከናወነው ፈውስ በዛሬው ጊዜ የመፈወስ ኃይል አለን በሚሉ ሰዎች ከሚፈጸሙ የተለመዱ ድርጊቶች የሚለየው እንዴት ነው?
በሕዝቡ መካከል ኃይለኛ የስሜት ግንፋሎት አልታየም፤ ኢየሱስም ቢሆን በስሜት እየተወራጨ ልዩ እንቅስቃሴ አላሳየም። በተጨማሪም ኢየሱስ የሰጣችሁት መዋጮ በቂ አይደለም ወይም እምነት ጎድሏችኋል የሚል ሰበብ በማቅረብ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ሳይፈውስ የቀረበት ጊዜ የለም።—7/1፣ ገጽ 5
◻ ይሖዋ ሕዝቦቹን ከስሙና ከመንግሥቱ ጋር በተያያዘው መለኮታዊ ዓላማ ውስጥ ቦታ እንዲኖራቸው የረዳቸው እንዴት ነው?
አንደኛ ይሖዋ እውነትን ለሕዝቦቹ በአደራ የሰጠ ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ ቅዱስ መንፈሱን ሰጥቷል። በሦስተኛ ደረጃም ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነትና እጅግ አስደሳች የሆነ የይሖዋ ድርጅታዊ የአምልኮ ዝግጅት አለን።—7/1፣ ገጽ 19, 20
◻ በጎነት ምንድን ነው?
በጎነት ጥሩ ሥነ ምግባር፣ መልካም ጠባይ፣ ትክክለኛ ድርጊትና አስተሳሰብ ነው። በጎነት ድርጊት አልባ ባሕርይ ሳይሆን የሚያንቀሳቅስና ገንቢ ባሕርይ ነው። በጎነት ከኃጢአት በመቆጠብ ብቻ አይወሰንም፤ መልካም የሆነውን ነገር መከታተልን ይጨምራል። (1 ጢሞቴዎስ 6:11)—7/15፣ ገጽ 14
◻ ወላጆች ለልጆቻቸው ሊሰጧቸው የሚችሉት ከሁሉ የላቀ ዋጋ ያለው ውርሻ ምንድን ነው?
በጣም ውድ የሆነው ውርስ የወላጆች የራሳቸው ለሌሎች ፍቅርን የማሳየት ምሳሌነት ነው። ከሁሉም በላይ ወላጆቻቸው በሚያደርጉት በማንኛውም ነገር ለአምላክ ያላቸውን እውነተኛ ፍቅር ሲገልጹና ሲያሳዩ ልጆቻቸው ማየትና መስማት አለባቸው።—7/15፣ ገጽ 21
◻ ውጤታማ ለሆነ የቤተሰብ ጥናት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ አንዳንድ ጠቃሚ ነገሮች ምንድን ናቸው?
የቤተሰብ ጥናት ቋሚ መሆን አለበት። ለጥናቱ የሚሆን ‘ጊዜ መዋጀት’ አለባችሁ። (ኤፌሶን 5:15-17) መጽሐፍ ቅዱስ ሕያው ሆኖ እንዲታያቸው በማድረግ የጥናቱን ክፍለ ጊዜ ለልጆች አስደሳች አድርጉት። ልጆች በጥናቱ እንዲደሰቱ ለማድረግ ተሳታፊ መሆን እንዳለባቸው ማወቅ ይኖርባቸዋል።—8/1፣ ገጽ 26, 28