መጨረሻው ቀርቧል፤ “ጤናማ አስተሳሰብ” ይኑራችሁ
“የነገሮች ሁሉ መጨረሻ ቀርቧል። ስለዚህ ጤናማ አስተሳሰብ ይኑራችሁ።” —1 ጴጥሮስ 4:7 NW
1. “ጤናማ አስተሳሰብ” መያዝ ምን ማለት ነው?
ከላይ ያሉት የሐዋርያው ጴጥሮስ ቃላት በክርስቲያኖች አኗኗር ላይ ትልቅ ሚና ሊኖራቸው ይገባል። ይሁን እንጂ ጴጥሮስ ይህን ያለው አንባቢዎቹ ከሌሎች ኃላፊነቶቻቸውና የኑሮ ጉዳዮች እንዲሸሹ ወይም ደግሞ በጣም ቀርቦ የነበረውን ጥፋት በማሰብ ብርክ እንዲይዛቸው አልነበረም። ከዚያ ይልቅ “ጤናማ አስተሳሰብ ይኑራችሁ” ሲል አጥብቆ አሳስቧል። “ጤናማ አስተሳሰብ” መያዝ ደግሞ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታን፣ አስተዋይና ልባም መሆንን እንዲሁም በንግግርና በድርጊት ምክንያታዊ መሆንን ይጠይቃል። እንዲሁም የአምላክ ቃል አስተሳሰባችንንና ድርጊታችንን እንዲቆጣጠረው መፍቀድ ማለት ነው። (ሮሜ 12:2) የምንኖረው “በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል” በመሆኑ ችግሮች ውስጥ ከመዘፈቅ ለመዳን ጤናማ አስተሳሰብ እንዲኖረን ያስፈልጋል።—ፊልጵስዩስ 2:15
2. የይሖዋ ትዕግሥት ዛሬ ያሉትን ክርስቲያኖች የሚጠቅማቸው እንዴት ነው?
2 “ጤናማ አስተሳሰብ” ስለ ራሳችንም ቢሆን ልከኛና ያልተጋነነ አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል። (ቲቶ 2:12፤ ሮሜ 12:3) በ2 ጴጥሮስ 3:9 ላይ ከሚገኙት ቃላት አንጻር ስናየው ይህ የግድ አስፈላጊ ነው:- “ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፣ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።” ይሖዋ የሚታገሠው አማኝ ላልሆኑት ሰዎች ሲል ብቻ ሳይሆን “ስለ እናንተ” ማለትም ስለ ክርስቲያን ጉባኤ አባላትም ጭምር እንደ ሆነ ልብ በሉ። ለምን? “ማንም እንዳይጠፋ” ሲል ነው። ምናልባት አንዳንዶች ለዘላለም ሕይወት ለመብቃት ገና አንዳንድ ለውጦችና ማስተካከያዎች ማድረግ ያስፈልጋቸው ይሆናል። እንግዲያውስ አንዳንድ ለውጦች ማድረግ ሊያስፈልግ የሚችልባቸውን ዘርፎች እንመልከት።
ከሌሎች ጋር ባለን የግል ግንኙነት “ጤናማ አስተሳሰብ” መያዝ
3. ወላጆች ልጆቻቸውን በሚመለከት ራሳቸውን ምን ብለው ሊጠይቁ ይችላሉ?
3 ቤት ሰላም የሰፈነበት ቦታ ሊሆን ይገባል። ይሁን እንጂ የአንዳንዶች ቤት ‘ጥልና ክርክር የበዛበት ይሆናል።’ (ምሳሌ 17:1 የ1980 ትርጉም) የእናንተስ ቤተሰብ እንዴት ነው? ቤተሰባችሁ ‘ከቁጣ፣ ከጩኸትና ከስድብ’ ነፃ ነውን? (ኤፌሶን 4:31) ልጆቻችሁስ? እንደምታፈቅሯቸውና እንደምታደንቋቸው ይሰማቸዋል? (ከሉቃስ 3:22 ጋር አወዳድር።) እነርሱን ለማስተማርና ለማሠልጠን ጊዜ ትመድባላችሁ? በንዴትና በቁጣ ሳይሆን ‘በጽድቅ ትገስጿቸዋላችሁ?’ (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ልጆች ‘የይሖዋ ስጦታ’ እንደመሆናቸው መጠን ይሖዋ ስለሚደረግላቸው አያያዝ በጥልቅ ያስባል።—መዝሙር 127:3
4. (ሀ) አንድ ባል ሚስቱን በአግባቡ አለመያዙ ምን ሊያስከትል ይችላል? (ለ) ሚስቶች ከአምላክ ጋር ሰላም ሊፈጥሩና በመላው ቤተሰብ ውስጥ ደስታ እንዲሰፍን ሊያደርጉ የሚችሉት እንዴት ነው?
4 ስለ ትዳር ጓደኛችንስ ምን ማለት ይቻላል? “እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፣ ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለ ሆንን፣ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት፣ ይመግበዋል ይከባከበውማል።” (ኤፌሶን 5:28, 29) ተሳዳቢ፣ አምባ ገነን ወይም ምክንያታዊነት የጎደለው ወንድ ቤተሰቡን ሰላም ከመንሳቱም በላይ ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና አደጋ ላይ ይጥላል። (1 ጴጥሮስ 3:7) ሚስቶችስ? እነርሱም በተመሳሳይ ‘ለጌታ እንደሚገዙ ለባሎቻቸው ሊገዙ’ ይገባል። (ኤፌሶን 5:22) አንዲት ሚስት ጌታን እንዴት ደስ እንደምታሰኝ የምታስብ ከሆነ የባሏን ድክመቶች ሳትቆጥር ያለ ቅሬታ እንድትገዛለት ይረዳታል። አንዳንድ ጊዜ ሚስት የተሰማትን ለመናገር ትገደድ ይሆናል። ምሳሌ 31:26 ስለ ጥሩ ሚስት ሲናገር እንዲህ ይላል:- “አፍዋን በጥበብ ትከፍታለች፤ የርኅራኄም ሕግ በምላስዋ አለ።” ባልዋን በደግነትና አክብሮት በተሞላበት መንገድ በመያዝ ከአምላክ ጋር ያላትን ሰላም ጠብቃ ከመኖሯም ሌላ መላው ቤተሰብ ደስተኛ እንዲሆን ታደርጋለች።—ምሳሌ 14:1
5. ወጣቶች ለወላጆቻቸው በሚኖራቸው አመለካከት ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር መከተል የሚገባቸው ለምንድን ነው?
5 እናንተ ወጣቶች ለወላጆቻችሁ ያላችሁ አመለካከት ምን ዓይነት ነው? ብዙውን ጊዜ በዓለም ውስጥ እንደቀላል የሚታየውን ዓይነት የሽሙጥና አክብሮት የጎደለው ንግግር ትናገራላችሁን? ወይስ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው ሲል የሚሰጠውን ምክር ትከተላላችሁ:- “ልጆች ሆይ፣ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፣ ይህ የሚገባ ነውና። መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር፤ እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት።”—ኤፌሶን 6:1-3
6. ከመሰል አማኞች ጋር ባለን ግንኙነት ሰላምን መሻታችንን የምናሳየው እንዴት ነው?
6 በተጨማሪም ከመሰል አማኞች ጋር ባለን ግንኙነት ‘ሰላምን ስንሻና ስንከተል’ “ጤናማ አስተሳሰብ” እንዳለን እናሳያለን። (1 ጴጥሮስ 3:11) አልፎ አልፎ አለመጣጣምና አለመግባባት ይፈጠራል። (ያዕቆብ 3:2) ጥላቻ እንዲነግሥ ከፈቀድንለት የጠቅላላው ጉባኤ ሰላም አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል። (ገላትያ 5:15) እንግዲያውስ አለመግባባቱን ሳይውል ሳያድር ፍቱት፤ ሰላማዊ መፍትሔ ለማግኘት ተጣጣሩ።—ማቴዎስ 5:23-25፤ ኤፌሶን 4:26፤ ቆላስይስ 3:13, 14
“ጤናማ አስተሳሰብ” እና የቤተሰብ ኃላፊነቶች
7. (ሀ) ጳውሎስ የዕለት ተዕለት ኑሮን ስለሚመለከቱ ጉዳዮች “ጤናማ አስተሳሰብ” መያዝን ያበረታታው እንዴት ነው? (ለ) ክርስቲያን ባሎችና ሚስቶች በቤት ውስጥ ያሉባቸውን ኃላፊነቶች በተመለከተ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?
7 ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች “ጤናማ አስተሳሰብ” ይዘው እንዲኖሩ መክሯል። (ቲቶ 2:12 NW) ጳውሎስ ከዚህ ጥቅስ ዙሪያ ሴቶች “ባሎቻቸውን የሚወዱ፣ ልጆቻቸውን የሚወዱ፣ ራሳቸውን የሚገዙ [“ጤናማ አስተሳሰብ ያላቸው፣” NW] ንጹሖች፣ በቤት የሚሠሩ” እንዲሆኑ ማሳሰቡ ትኩረት የሚስብ ነው። (ቲቶ 2:4, 5) ጳውሎስ ይህንን የጻፈው የአይሁድ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ከመምጣቱ ትንሽ ቀደም ብሎ ማለትም ከ61-64 እዘአ ባሉት ዓመታት መሀል ነው። ሆኖም ይህ እንደ ቤት ውስጥ ሥራ ያሉትን የዕለት ተዕለት ኑሮን የሚመለከቱትን ጉዳዮች አስፈላጊነት አይቀንሰውም። እንግዲያውስ ባሎችም ሆኑ ሚስቶች “የእግዚአብሔር ቃል እንዳይሰደብ” በቤት ውስጥ ስላሏቸው ኃላፊነቶች ጤናማና አዎንታዊ አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል። በአንድ ወቅት አንድ የቤተሰብ ራስ ሊጠይቃቸው የመጣውን እንግዳ ቤታቸው ምስቅልቅል ብሎ ስለነበር ይቅርታ ይጠይቀዋል። ሁሉም ነገር እንደዚህ የተዘበራረቀው እርሱ “አቅኚ ስለነበረ” እንደሆነ ገለጸለት። ለመንግሥቱ ሥራ ስንል መሥዋዕትነት መክፈላችን የሚያስመሰግን ነው፤ ይሁን እንጂ የቤተሰባችንን ደህንነት መሥዋዕት እንዳናደርግ መጠንቀቅ ይኖርብናል።
8. የቤተሰብ ራሶች ቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ነገር በሚዛናዊነት ማሟላት የሚችሉት እንዴት ነው?
8 መጽሐፍ ቅዱስ ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን የማሟላት ኃላፊነቱን ሳይወጣ የቀረን ሰው “ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው” በማለት አባቶች ለቤተሰቦቻቸው ቅድሚያ እንዲሰጡ አጥብቆ ያሳስባል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) በዓለም ዙሪያ ያለው የኑሮ ደረጃ የተለያየ ነው፤ ለቁሳዊ ነገሮች ያለንን ፍላጎት ልከኛ ማድረጉ ጥሩ ነው። የምሳሌ 30:8 ጸሐፊ “ድህነትንና ባለጠግነትን አትስጠኝ” ሲል ጸልዮአል። ይሁን እንጂ ወላጆች ልጆቻቸው የሚያስፈልጓቸውን ቁሳዊ ነገሮች ችላ ሊሉ አይገባም። ለምሳሌ ያህል በቲኦክራሲያዊ መብቶች ለማገልገል ሲባል ሆነ ብሎ ቤተሰቡ ለሕይወት የሚያስፈልጉትን መሠረታዊ ነገሮች ሳያሟሉ መቅረት ጥበብ ይሆናልን? ይህ ልጆችን ሊያስመርር አይችልምን? በአንጻሩ ደግሞ ምሳሌ 24:27 “በስተ ሜዳ ሥራህን አሰናዳ፣ ስለ አንተ በእርሻ አዘጋጃት። ከዚያ በኋላ ቤትህን ሥራ” ይላል። አዎን፣ ስለ ቁሳዊ ነገሮች በአግባቡ ማሰቡ ተገቢ ቢሆንም ‘ቤትን’ በመንፈሳዊና ስሜታዊ ነገሮች ‘መገንባቱ’ የግድ አስፈላጊ ነው።
9. የቤተሰብ ራሶች ሊሞቱ ወይም ሊታመሙ እንደሚችሉ ማሰባቸው ጥበብ የሚሆነው ለምንድን ነው?
9 በአጋጣሚ ብትሞት ቤተሰብህ የሚያስፈልገውን ነገር ማግኘት የሚችልበትን ዝግጅት አድርገሃልን? ምሳሌ 13:22 “ጻድቅ ሰው ለልጅ ልጆቹ ያወርሳል” ይላል። ወላጆች ለልጆቻቸው ስለ ይሖዋ ያገኙትን እውቀትና ከእርሱ ጋር ያላቸውን ዝምድና ከማውረስም አልፈው የሚያስፈልጋቸውን ቁሳዊ ዝግጅት ያደርጋሉ። በብዙ አገሮች የቤተሰብ ራሶች የቁጠባ ሒሳብ ለመክፈት፣ ንብረታቸውን በሕግ ለመናዘዝ ወይም ኢንሹራንስ ለመግባት ይሞክራሉ። የአምላክ ሕዝቦችም ቢሆኑ ‘ጊዜና ያልታሰበ አጋጣሚ’ ከሚያመጣው ነገር ነፃ አይደሉም። (መክብብ 9:11) ገንዘብ “ጥላ” ይሆናል፤ ጥንቃቄ የተሞላበት ዕቅድ ማውጣት ደግሞ ችግርን ሊያስቀር ይችላል። (መክብብ 7:12) መንግሥት የሕክምና ወጪዎችን በማይሸፍንባቸው አገሮች አንዳንዶች ለሕክምና የሚሆን ገንዘብ ለማስቀመጥ ወይም የሕክምና ወጪያቸውን የሚሸፍኑበት ሌላ መንገድ ለማዘጋጀት ይጥራሉ።a
10. ክርስቲያን ወላጆች ለልጆቻቸው ‘የሚያከማቹት’ እንዴት ሊሆን ይችላል?
10 ቅዱሳን ጽሑፎችም “ወላጆች ለልጆች እንጂ ልጆች ለወላጆች ገንዘብ ሊያከማቹ አይገባቸውምና” በማለት ይናገራሉ። (2 ቆሮንቶስ 12:14) በዓለም ውስጥ ወላጆች ልጆቻቸው የተሳካ ጅምር እንዲኖራቸው ሲሉ ለልጆቻቸው የወደፊት ትምህርት እና ትዳር በማሰብ ገንዘብ ማጠራቀማቸው የተለመደ ነገር ነው። እናንተስ፣ ለልጃችሁ የወደፊት መንፈሳዊ ሁኔታ አስባችሁበታል? ለምሳሌ ያህል የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ የገባ አንድ ትልቅ ልጅ አለ እንበል። የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሌሎች ጥገኛ ወይም የሰው እጅ የሚጠብቁ መሆን ባይኖርባቸውም አፍቃሪ ወላጆች ልጃቸው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲቀጥል ለመርዳት ሲሉ ‘በሚያስፈልገው ለማካፈል’ ሊወስኑ ይችላሉ።—ሮሜ 12:13፤ 1 ሳሙኤል 2:18, 19፤ ፊልጵስዩስ 4:14-18
11. ስለ ገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ እምነት እንደጎደለን ያሳያልን? አብራራ።
11 ስለ ገንዘብ ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት መያዝ የሰይጣን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ መቅረቡን በሚመለከት እምነት እንደጎደለን አያመለክትም። ይህ “ተግባራዊ ጥበብ” የማሳየትና ጤናማ ውሳኔ የማድረግ ጉዳይ ነው። (ምሳሌ 2:7፤ 3:21 NW) በአንድ ወቅት ኢየሱስ በገንዘብ አጠቃቀማቸው ረገድ “የዚህ ዓለም ልጆች . . . ከብርሃን ልጆች ይልቅ ልባሞች ናቸው” ብሏል። (ሉቃስ 16:8) በመሆኑም አንዳንዶች የቤተሰባቸውን ፍላጎት ይበልጥ በተሻለ መንገድ ለማሟላት ይችሉ ዘንድ ንብረታቸውን በሚጠቀሙበት መንገድ ላይ ማስተካከያ ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው ማስተዋላቸው ምንም አያስገርምም።
ለትምህርት ባለን አመለካከት “ጤናማ አስተሳሰብ” መያዝ
12. ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር ራሳቸውን እንዲያስተካክሉ ያስተማራቸው እንዴት ነው?
12 ‘የዚህች ዓለም መልክ ተለዋዋጭ ነው።’ መጠነ ሰፊ ኢኮኖሚያዊ ለውጦችና የቴክኖሎጂ መሻሻሎች በከፍተኛ ፍጥነት በመካሄድ ላይ ናቸው። (1 ቆሮንቶስ 7:31 NW) ይሁን እንጂ ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ከሁኔታዎች ጋር ተስማምተው እንዲሄዱ አስተምሯቸዋል። ለመጀመሪያው የስብከት ዘመቻ ሲልካቸው እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “ወርቅ ወይም ብር ወይም ናስ በመቀነታችሁ፣ ወይም ለመንገድ ከረጢት ወይም ሁለት እጀ ጠባብ ወይም ጫማ ወይም በትር አታግኙ፤ ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና።” (ማቴዎስ 10:9, 10) ይሁንና ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ “አሁን ግን ኮረጆ ያለው ከእርሱ ጋር ይውሰድ፣ ከረጢትም ያለው እንዲሁ” ሲል ተናግሯል። (ሉቃስ 22:36) ምን የተለወጠ ነገር ነበር? ሁኔታዎቹ ተለውጠው ነበር። ሃይማኖታዊው ክፍል ይበልጥ ተቃዋሚ ሆኖ ስለነበር የራሳቸውን ዝግጅት ማድረግ አስፈልጓቸው ነበር።
13. የትምህርት ዋነኛ ዓላማው ምንድን ነው? ወላጆችስ በዚህ ረገድ ልጆቻቸውን ሊደግፏቸው የሚችሉት እንዴት ነው?
13 ዛሬም በተመሳሳይ ወላጆች ዛሬ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ ያህል ልጆቻችሁ በቂ ትምህርት የሚያገኙበትን ዝግጅት ታደርጋላችሁን? የትምህርት ዋነኛው ዓላማ ወጣቶች ውጤታማ የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ ማስታጠቅ ሊሆን ይገባዋል። ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው የትምህርት ዓይነት ደግሞ መንፈሳዊ ትምህርት ነው። (ኢሳይያስ 54:13) በተጨማሪም ወላጆች ልጆቻቸው ራሳቸውን በገንዘብ መደገፍ መቻላቸውም ያሳስባቸዋል። እንግዲያውስ ለልጆቻችሁ መመሪያ ስጧቸው፤ ተገቢውን የትምህርት ዓይነት እንዲመርጡ እርዷቸው፤ እንዲሁም ተጨማሪ ትምህርት መከታተሉ ጥበብ ይሁን አይሁን አወያዩአቸው። እንዲህ ያሉትን ውሳኔዎች ማድረግ ያለበት ቤተሰቡ ነው፤ ቤተሰቡ የወሰደውን እርምጃ ሌሎች ሊነቅፉ አይገባም። (ምሳሌ 22:6) ወላጆች ልጆቻቸውን ቤት ውስጥ ለማስተማር ቢመርጡስ?b ብዙዎች በዚህ ረገድ የተዋጣላቸው ቢሆንም አንዳንዶች ይህ ነገር ካሰቡት ይበልጥ ከባድ ሆኖባቸው ልጆቻቸው ተገቢውን ትምህርት ሳያገኙ ቀርተዋል። ስለዚህ ልጆቻችሁን በቤት ለማስተማር የምታስቡ ከሆነ ችሎታውም ሆነ እስከ መጨረሻው ድረስ ለመግፋት የሚያስፈልገው ጽናት ያላችሁ ስለመሆኑ ከሐቁ ሳትርቁ ራሳችሁን በመገምገም ወጪያችሁን አስሉ።—ሉቃስ 14:28
‘ታላቅን ነገር አትፈልጉ’
14, 15. (ሀ) ባሮክ መንፈሳዊ ሚዛኑን ያጣው እንዴት ነው? (ለ) ‘ታላቅን ነገር መፈለጉ’ ሞኝነት የነበረው ለምንድን ነው?
14 አንዳንዶች የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ እስካሁን ድረስ ባለመምጣቱ ዓለም የሚሰጠውን ነገር ይኸውም የሚያስከብር ሙያ፣ ብዙ ትርፍ የሚያስገኝ ሥራና ሀብት ለማግኘት ወደ መጣጣር ሊያዘነብሉ ይችላሉ። የኤርምያስ ጸሐፊ የነበረውን የባሮክን ምሳሌ ተመልከቱ። “እግዚአብሔር በሕመሜ ላይ ኀዘንን ጨምሮብኛልና ወዮልኝ! በልቅሶዬ ጩኸት ደክሜአለሁ፣ ዕረፍትንም አላገኘሁም” ብሏል። (ኤርምያስ 45:3) ባሮክ ብዙ ደክሞ ነበር። የኤርምያስ ጸሐፊ ሆኖ ማገልገል አስቸጋሪና የሚያስፈራ ሥራ ነበር። (ኤርምያስ 36:14-26) ፍርሃቱ ማብቂያ ያለው አይመስልም ነበር። ኢየሩሳሌም ሳትጠፋ 18 ዓመታት አልፈዋል።
15 ይሖዋ ባሮክን እንዲህ አለው:- “እነሆ የሠራሁትን አፈርሳለሁ፣ የተከልሁትንም እነቅላለሁ፤ ይኸውም በምድር ሁሉ ነው። ለራስህ ታላቅን ነገር ትፈልጋለህን? . . . አትፈልገው።” ባሮክ ሚዛኑን ስቶ ነበር። ምናልባት ሀብት፣ ዝና ወይም አስተማማኝ ንብረት ለማግኘት ሳይሆን አይቀርም ‘ታላቅን ነገር መፈለጉን’ ተያይዞት ነበር። አምላክ ‘ምድሪቱን እንኳን ሳይቀር ሊነቅል’ ነበር፤ እርሱ እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች ማሳደዱ ምን ትርጉም ነበረው? በመሆኑም ይሖዋ፣ ባሮክ ልብ እንዲገዛ ያደረገውን ይህን ማሳሰቢያ ሰጠው:- “በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ፣ እነሆ፣ ክፉ ነገርን አመጣለሁና . . . በምትሄድበት ስፍራ ሁሉ ነፍስህን እንደ ምርኮ አድርጌ እሰጥሃለሁ።” ቁሳዊ ንብረት በኢየሩሳሌም ላይ ከሚመጣው ጥፋት ሊተርፍ አይችልም ነበር! ይሖዋ ዋስትና የሰጠው ‘ነፍሱ እንደ ምርኮ’ ሆና እንደምትተርፍ ብቻ ነበር።—ኤርምያስ 45:4, 5
16. ዛሬ ያሉት የይሖዋ ሕዝቦች ከባሮክ ተሞክሮ ምን ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ?
16 ባሮክ የይሖዋን እርማት በመቀበሉ ልክ ይሖዋ እንዳለው በሕይወት ተርፏል። (ኤርምያስ 43:6, 7) ይህ ዛሬ ላሉት የይሖዋ ሕዝቦች እንዴት ያለ ትልቅ ትምህርት ነው! ይህ ለራሳችን ‘ታላቅ ነገርን’ የምንፈልግበት ጊዜ አይደለም። ለምን? ምክንያቱም “ዓለምም ምኞቱም ያልፋሉ።”—1 ዮሐንስ 2:17
የቀረውን ጊዜ ከሁሉ በተሻለ መንገድ መጠቀም
17, 18. (ሀ) የነነዌ ሰዎች ንስሐ ሲገቡ ዮናስ ምን ተሰማው? (ለ) ይሖዋ ዮናስን ምን ነገር አስተምሮታል?
17 እንግዲያውስ የቀረውን ጊዜ ከሁሉ በተሻለ መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው? ከነቢዩ ዮናስ ተሞክሮ ተማሩ። “ወደ ነነዌ ሄደ . . . ነነዌ በአርባ ቀን ውስጥ ትገለበጣለች ብሎ ዐወጀ።” ይግረምህ ብሎ የነነዌ ሰዎች ንስሐ በመግባት ለመልእክቱ ምላሽ ሰጡ! ይሖዋም ከተማዋን ከማጥፋት ታቀበ። ዮናስ ምን ተሰማው? “አሁንም፣ አቤቱ፣ ከሕይወት ሞት ይሻለኛልና እባክህ፣ ነፍሴን ከእኔ ውሰድ አለው።”—ዮናስ 3:3, 4 የ1980 ትርጉም፤ 4:3
18 ከዚያም ይሖዋ ዮናስን አንድ በጣም ጠቃሚ ትምህርት አስተማረው። ይሖዋ “ቅል አዘጋጀ፣ . . . በራሱ ላይ ጥላ እንድትሆን በዮናስ ላይ ከፍ ከፍ አደረጋት፤ ዮናስም ስለ ቅሊቱ እጅግ ደስ አለው።” ይሁን እንጂ የዮናስ ደስታ ለረጅም ጊዜ አልዘለቀም፤ ምክንያቱም ተክሏ ወዲያው ደረቀች። ዮናስ ከደረሰበት የሚያስከፋ ነገር የተነሣ ‘እጅግ ተቆጣ።’ ከዚያም ይሖዋ ሊያስተምረው የፈለገውን ነገር አስታወቀው:- “አንተ . . . [ለ]ቅል አዝነሃል እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሃያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ነነዌ አላዝንምን?”—ዮናስ 4:6, 7, 9-11
19. ማስወገድ የሚኖርብን የትኛውን ዓይነት የራስ ወዳድነት አስተሳሰብ ነው?
19 ዮናስ ያቀረበው ምክንያት ምንኛ ራስ ወዳድነት የተጠናወተው ነበር! ለአንዲት ተክል ሲያዝን በመንፈሳዊ ሁኔታ ‘በቀኝና በግራቸው መካከል ያለውን ልዩነት ለማያውቁት’ የነነዌ ሰዎች ግን ቅንጣት ታክል እንኳን ርኅራኄ አልነበረውም። እኛም በተመሳሳይ የዚህ ዓለም ጥፋት እንዲመጣ እንጓጓ ይሆናል፤ ደግሞም መጓጓታችን ተገቢ ነው! (2 ተሰሎንቄ 1:8) ይሁን እንጂ እስከዚያው ድረስ በመንፈሳዊ ሁኔታ ‘ቀኛቸውን ከግራቸው ለይተው የማያውቁትን’ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የመርዳት ኃላፊነት አለብን። (ማቴዎስ 9:36፤ ሮሜ 10:13-15) የቀረውን አጭር ጊዜ የቻላችሁትን ያክል ብዙ ሰዎች ውድ የሆነውን የይሖዋን እውቀት እንዲያገኙ ለመርዳት ትጠቀሙበታላችሁን? አንድ ሰው ሕይወት እንዲያገኝ በመርዳት ከሚገኘው ደስታ ጋር ሊተካከል የሚችል ምን ሥራ ይኖራል?
“ጤናማ አስተሳሰብ” ይዛችሁ መኖራችሁን ቀጥሉ
20, 21. (ሀ) ከፊታችን ባሉት ቀናት “ጤናማ አስተሳሰብ” እንዳለን ማሳየት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው? (ለ) “ጤናማ አስተሳሰብ” ይዞ መኖር ምን በረከቶችን ያስገኛል?
20 የሰይጣን ሥርዓት በፍጥነት ወደ ጥፋት እየገሰገሰ መሄዱን በቀጠለ መጠን አዳዲስ ፈታኝ ሁኔታዎች እንደሚገጥሙን አያጠራጥርም። ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 3:13 “ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች፣ እያሳቱና እየሳቱ፣ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ” በማለት ይተነብያል። ይሁን እንጂ ‘በነፍሳችሁ ዝላችሁ አትድከሙ።’ (ዕብራውያን 12:3) ብርታት ለማግኘት በይሖዋ ላይ ተደገፉ። (ፊልጵስዩስ 4:13) ስላለፈው ጊዜ ከማውጠንጠን ይልቅ እየከፉ ከሚሄዱት ሁኔታዎች ጋር ራሳችሁን ማለማመድን ተማሩ። (መክብብ 7:10) “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚሰጠውን መመሪያ በመከተል ተግባራዊ ጥበብ ተጠቀሙ።—ማቴዎስ 24:45-47
21 ካሁን በኋላ የቀረው ጊዜ ምን ያህል እንደሆነ አናውቅም። ይሁን እንጂ በእርግጠኛነት “የነገሮች ሁሉ መጨረሻ ቀርቧል” ብለን መናገር እንችላለን። ይህ መጨረሻ እስኪመጣ ድረስ እርስ በርስ ባለን ግንኙነትም ሆነ ለቤተሰቦቻችን ባለን አያያዝ እንዲሁም በሌሎች ኃላፊነቶቻችን ረገድ “ጤናማ አስተሳሰብ” ይዘን እንኑር። እንዲህ ካደረግን በመጨረሻ ሁላችንም “ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆነን በሰላም” እንደምንገኝ ትምክህት ሊኖረን ይችላል!—2 ጴጥሮስ 3:14
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ለምሳሌ ያህል በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ቢሆንም ብዙዎቹ የጤና ኢንሹራንስ ይገባሉ። ቤተሰቡ የሕክምና ኢንሹራንስ ያለው ከሆነ አንዳንድ ዶክተሮች ያለ ደም ሕክምና ለማድረግ ይበልጥ ፈቃደኛ ሆነው እንደሚገኙ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክር ቤተሰቦች ተገንዝበዋል። ብዙ የሕክምና ባለ ሙያዎች ውስን የሆነውን የኢንሹራንስ ክፍያ ወይም መንግሥት የሚከፍልለትን የገንዘብ መጠን ተቀብለው ያክማሉ።
b አንድ ሰው ልጁን ቤት ውስጥ ማስተማር ወይም አለማስተማር በግሉ የሚያደርገው ውሳኔ ነው። “የቤት ውስጥ ትምህርት—ለአንተ የሚሆን ምርጫ ነውን?” የሚለውን በሚያዝያ 8, 1993 (እንግሊዝኛ) ንቁ! መጽሔት ላይ የወጣውን ርዕስ ተመልከት።
ለክለሳ የቀረቡ ነጥቦች
◻ በግል ግንኙነቶቻችን “ጤናማ አስተሳሰብ” እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
◻ የቤተሰብ ኃላፊነታችንን በመወጣት ረገድ ሚዛናዊነትን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
◻ ወላጆች ስለልጆቻቸው ሰብዓዊ ትምህርት ማሰብ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?
◻ ከባሮክና ከዮናስ ምን ትምህርት እናገኛለን?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባልና ሚስት አንዳቸው ሌላውን በአግባብ የማይዙ ከሆነ ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና አደጋ ላይ ይጥላሉ
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወላጆች ስለ ልጆቻቸው ትምህርት ሊያስቡ ይገባል