አረጋውያን ወላጆችን ማክበር የሚያስገኛቸው በረከቶች
እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች ለአረጋውያን ወላጆቻቸው ከፍተኛ ፍቅር ስላላቸው በጥንቃቄ ይይዟቸዋል፣ ያከብሯቸዋል እንዲሁም ይጦሯቸዋል። ይህ የአምልኮታቸው ክፍል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “እነርሱ [ልጆች ወይም የልጅ ልጆች] አስቀድመው ለገዛ ቤተ ሰዎቻቸው እግዚአብሔርን መምሰል ያሳዩ ዘንድ፣ ለወላጆቻቸውም ብድራትን ይመልሱላቸው ዘንድ ይማሩ፤ ይህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና የተወደደ ነውና” በማለት ይገልጻል። (1 ጢሞቴዎስ 5:4፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) ወጣትም ሆንን በዕድሜ የገፋን ለወላጆቻችንና ለአያቶቻችን “ብድራት” መመለሳችን የተገባ ነገር ነው። እንዲህ በማድረግ እነሱ ለረዥም ዓመታት ላሳዩን ፍቅር፣ ለድካማቸውና ላደረጉልን እንክብካቤ አድናቆታችንን እናሳያለን። እንዲያውም ወደ ሕልውና የመጣነው በእነሱ ምክንያት ነው!
ለወላጆችና ለአያቶች ተገቢ የሆነውን ብድራት መክፈል “በእግዚአብሔር ፊት መልካምና የተወደደ” እንደሆነ አስተውሉ። ‘ለአምላክ ከማደራችን’ ጋር የተያያዘ ነገር አለው። ስለዚህ አምላክን ደስ የሚያሰኘውን ነገር እያደረግን እንዳለን ስለምናውቅ ይህን ምክር ተግባራዊ በማድረጋችን እንባረካለን። ይህ ደግሞ ደስታ ያመጣልናል።
ለሌሎች በመስጠት በተለይም ደግሞ በለጋስነት ሲሰጡን ለነበሩት ሰዎች በመስጠት ደስታ ይገኛል። (ሥራ 20:35) “አባትህንና እናትህን ደስ አሰኛቸው፣ አንተንም የወለደች ደስ ይበላት” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለስ ትልቅ በረከት ያስገኛል!—ምሳሌ 23:25
የወላጆቻችንንና የአያቶቻችንን ብድራት ልንመልስ የምንችለው እንዴት ነው? በሦስት መንገዶች ማለትም በቁሳዊ፣ በስሜታዊና በመንፈሳዊ ነው። ሦስቱም መንገዶች በረከት ያስገኛሉ።
ቁሳዊ ነገሮችን መስጠት
አምላክን የሚያገለግሉ ሁሉ ለቅርብ የቤተሰብ አባላት ቁሳዊ ነገሮችን ማቅረብ አስፈላጊ እንደሆነ ያውቃሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ “ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፣ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው” በማለት አጥብቆ አሳስቧል።—1 ጢሞቴዎስ 5:8
ቱንጂ እና ጆይ የሚኖሩት በምዕራብ አፍሪካ ነው። የገንዘብ ችግር ቢኖርባቸውም በዕድሜ የገፉትን የጆይ ወላጆች ከእነርሱ ጋር እንዲኖሩ አደረጉ። አባትየው ታመሙና ከጊዜ በኋላ ሞቱ። ቱንጂ እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “አባባ ሲሞት እማማ ባለቤቴን እቅፍ አድርጋ ‘ሰው ሊያደርገው የሚችለውን ነገር ሁሉ አድርገሻል። በአባትሽ ሞት ምንም የምትጸጸችበት ምክንያት የለም’ አለቻት። አባባን በማጣታችን ብናዝንም የሚያስፈልገውን ጥሩ መድሃኒት እንደገዛንለት እናውቃለን፤ እንዲሁም ያልተረሳና ተፈላጊ እንደሆነ እንዲሰማው ሁልጊዜ ጥረት እናደርግ ነበር። አምላክ የሰጠንን ኃላፊነት ለመፈጸም የተቻለንን ሁሉ አድርገናል። እንዲህ ማድረጋችን እርካታ አስገኝቶልናል።”
እርግጥ ነው ሁሉም ሌሎችን በቁሳዊ ነገሮች ለመርዳት የሚያስችል አቅም አይኖረውም። አንድ በናይጄርያ የሚኖር ሰው “አንድ ሰው ራሱን መርዳት ካልቻለ ሌላውን ሰው እንዴት አድርጎ መርዳት ይችላል?” በማለት ተናግሯል። በብዙ አገሮች ያለው ሁኔታ ወደፊት የበለጠ እየከፋ ሊሄድ ይችላል። በአንድ የተባበሩት መንግሥታት ትንበያ መሠረት በአፍሪካ ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች ከሚኖረው ሕዝብ ግማሹ ወደፊት በጣም ለከፋ የድህነት ኑሮ ይዳረጋል።
አንተም በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ውስጥ የምትገኝ ከሆነ ስለ አንዲት ደሃ መበለት ከሚናገረው እውነተኛ ታሪክ ማጽናኛ ልታገኝ ትችላለህ። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ አንዲት መበለት በቤተ መቅደሱ መዝገብ ውስጥ ጥቂት መዋጮ ስትከት ተመለከተ። ያደረገችው መዋጮ ‘ሁለት ሳንቲሞችን’ ብቻ ነበር። ኢየሱስም ያለችበትን ሁኔታ በመገንዘብ “እውነት እላችኋለሁ፣ ይህች ድሀ መበለት ከሁሉ ይልቅ አብልጣ ጣለች፤ እነዚህ ሁሉ ከትርፋቸው ወደ እግዚአብሔር መዝገብ ጥለዋልና፤ ይህች ግን ከጒድለትዋ የነበራትን ትዳርዋን ሁሉ ጣለች” በማለት ተናግሯል።—ሉቃስ 21:1-4
እኛም በተመሳሳይ ኢኮኖሚያችን ዝቅተኛ ቢሆንም እንኳ ወላጆቻችንን ወይም አያቶቻችንን በቁሳዊ ነገሮች ለመንከባከብ የተቻለንን ሁሉ ካደረግን ይሖዋ ይመለከታል እንዲሁም ያደንቃል። ማድረግ ከምንችለው በላይ እንድናደርግ አይጠብቅብንም። ምናልባት ወላጆቻችንም ሆኑ አያቶቻችን ሁኔታውን በተመሳሳይ መንገድ ሊመለከቱት ይችላሉ።
ስሜታዊ ድጋፍ መስጠት
ለወላጆቻችንና ለአያቶቻችን የምናደርግላቸው ነገር የሚያስፈልጓቸውን ቁሳዊ ነገሮቸ በማቅረብ ብቻ የሚወሰን አይደለም። ሁላችንም ስሜታዊ ፍላጎቶች አሉን። ሁሉም ሰው በእድሜ የገፉትም ጭምር በሌሎች ዘንድ የመወደድ፣ ተፈላጊ የመሆንና ጠቃሚ የቤተሰብ አባል የመሆን ፍላጎት አለው።
ኬንያ የምትኖረው ማሪ አረጋዊ አማቷን ለሦስት ዓመታት ጦራለች። ማሪ ስትናገር “የሚያስፈልጋትን ቁሳዊ ነገሮች ከማቅረብም በላይ ሁልጊዜ እንጨዋወት ነበር። እማማ እቤት ውስጥ እንደ ልብ መንቀሳቀስ አትችልም። ሆኖም እንጫወታለን እንዲሁም የቅርብ ጓደኛሞች ሆንን። አንዳንድ ጊዜ ስለ አምላክ እናወራለን፤ አንዳንዴ ደግሞ ከዚህ ቀደም አብረውን ይኖሩ የነበሩ ሰዎችን እያስታወስን እናወራለን። ዕድሜዋ ከ90 ዓመት በላይ ቢሆንም የማስታወስ ችሎታዋ በጣም ጥሩ ነው። ከ1914 በፊት በነበሩት ጊዜያት ትንሽ ልጅ ሆና ያሳለፈችውን ሕይወት አስታውሳ ትናገራለች።”
በመቀጠልም ማሪ “ያረጁ ሰዎችን መጦር ቀላል አይደለም። ሆኖም እሷ ከእኛ ጋር መሆኗ ብዙ በረከት አስገኝቶልናል። በቤተሰብ ውስጥ ሰላምና ስምምነት አለን። ለእሷ ቸርነት ማድረጌ ሌሎቹ የቤተሰቡ አባላትም ለሌሎች የመስጠት መንፈሳቸውን አነሳስቷል። ባለቤቴ ለእኔ ከፍተኛ አክብሮት አለው። እማማ ማንም ሰው እኔን በክፉ ቃል ሲናገር ከሰማች ቶሎ ብላ ትቆጣቸዋለች። እርሷ ካለች ማንም ሰው ደፍሮ ክፉ ቃል አይናገረኝም!’
በመንፈሳዊ ድጋፍ መስጠት
ቁሳዊና መንፈሳዊ ነገሮችን መስጠት ለሰጪው በረከት እንደሚያስገኝለት ሁሉ በመንፈሳዊ መስጠትም በተመሳሳይ መንገድ በረከት ያስገኛል። ሐዋርያው ጳውሎስ ሮም ለሚገኘው የክርስቲያን ጉባኤ “ትጸኑ ዘንድ መንፈሳዊ ስጦታ እንዳካፍላችሁ ላያችሁ እናፍቃለሁና፤ ይህንም ማለቴ በመካከላችን ባለች በእናንተና በእኔ እምነት አብረን በእናንተ እንድንጽናና ነው” በማለት ጽፏል።—ሮሜ 1:11, 12
በተመሳሳይም አምላክን ለሚያገለግሉ አረጋውያን መንፈሳዊ ነገሮችን መስጠት ብዙውን ጊዜ ለእነሱ ብቻ ሳይሆን ለእኛም ማበረታቻ ያስገኛል። ናይጄርያ የሚኖረው ኦሰንዱ እንዲህ በማለት ይተርካል:- “አያቶቼን በሚመለከት ከሁሉም በላይ የሚያስደስተኝ ስላለፈው ጊዜ እውቀት እንዲኖረኝ የሚነግሩኝ ነገር ነው። አያቴ ፊቱ ፈገግ ብሎ በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ ዓመታት የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆኖ ስለ ሠራባቸው የአገልግሎት ክልሎች ይናገራል። በአሁኑ ጊዜ ያለውን የጉባኤ አሠራር እሱ የይሖዋ ምሥክር በሆነበት ጊዜ ከነበረው ጋር ያወዳድራል። እነዚህ ተሞክሮዎች አቅኚ ሆኜ በማገለግልበት ጊዜ ጠቅመውኛል።”
በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ሌሎችም ለአረጋውያን በመስጠት በኩል እርዳታ ሊያበረክቱ ይችላሉ። ቀደም ብሎ የተጠቀሰው ቱንጂ በጉባኤው ውስጥ ምን ነገር እንደተፈጸመ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “የሕዝብ ንግግር እንዲያቀርብ የተመደበ አንድ አቅኚ ወንድም ንግግሩን በሚዘጋጅበት ጊዜ ከአባባ ጋር አብሮ ለመዘጋጀት የንግግሩን አስተዋጽኦ ይዞ መጥቷል። በተጨማሪም የመጠበቂያ ግንብ ጥናት መሪው ወደ አባባ መጥቶ ‘አንተ ተሞክሮ አለህ። እድገት እንዳደርግ ምን ትመክረኛለህ’ በማለት ጠየቀው። አባባ ለእዚያ ሽማግሌ አንዳንድ ተግባራዊ ምክሮችን መስጠት ችሎ ነበር። ወንድሞች በጉባኤ ውስጥ ጸሎት በሚያቀርቡበት ጊዜ ደጋግመው የአባባን ስም ይጠቅሱ ነበር። ይህ ሁሉ የተጣለ ሆኖ እንዳይሰማው ረድቶታል።”
ጥሩ ምግባር ሰዎች ወደ አምላክ እንዲቀርቡ ያደርጋል
አንዳንድ ጊዜ አክብሮትና ፍቅር ለወላጆቻችንና ለአያቶቻችን ባሳየን መጠን ሰዎች ወደ አምላክ እንዲቀርቡ እናደርጋለን። ሐዋርያው ጴጥሮስ “ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ፣ ክፉ እንደምታደርጉ በዚያ እናንተን በሚያሙበት ነገር፣ በሚጐበኝበት ቀን እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን” በማለት ጽፏል።—1 ጴጥሮስ 2:12
በምዕራብ አፍሪካ የሚኖር አንድሩ የተባለ አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ አማኝ ያልነበረውን አባቱን ለመንከባከብ በሳምንት ሁለት ጊዜ 95 ኪሎ ሜትር ይጓዝ ነበር። እንዲህ በማለት ይናገራል:- “የይሖዋ ምሥክር በሆንኩበት ወቅት አባቴ አጥብቆ ተቃውሞኝ ነበር። ይሁን እንጂ ታሞ በነበረበት ወቅት እንዴት እንከባከበው እንደነበር ሲመለከት ታናናሽ ወንድሞቼንና እህቶቼን ‘የወንድማችሁን ሃይማኖት መያዝ አለባችሁ!’ በማለት አጥብቆ ያሳስባቸው ጀመር። ይህም እነርሱን ስላነሳሳቸው አሁን የአባቴ ዘጠኝ ልጆች በሙሉ የይሖዋ ምሥክር ሆነዋል።”
አረጋዊ ወላጆቻችንን ማክበርና መጦር በተለይ ደግሞ የኢኮኖሚ ችግር ሲኖር ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች እንዲህ ለማድረግ ሲጣጣሩ የድካማቸውን ዋጋ ያገኛሉ። ከሁሉም በላይ “የሁሉም አባት” የሆነውን ይሖዋ አምላክን እያስደሰቱ እንዳሉ በማወቅ ከሚገኘው እርካታ ጋር በመስጠት የሚገኘውን ደስታ ይቀምሳሉ።—ኤፌሶን 4:6
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ለተጧሪዎችና ለጧሪዎች የሚሆን አምላካዊ ምክር
አበረታች ሁኑ:- “እያንዳንዳችን እንድናንጸው እርሱን ለመጥቀም ባልንጀራችንን ደስ እናሰኝ።”—ሮሜ 15:2
ጸንታችሁ ቁሙ:- “ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት።”—ገላትያ 6:9
ትሑት ሁኑ:- “ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፣ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቊጠር።”—ፊልጵስዩስ 2:3
መልካሙን የምታደርጉ ሁኑ:- “እያንዳንዱ የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ አንድ ስንኳ የራሱን ጥቅም አይፈልግ።”—1 ቆሮንቶስ 10:24
ምክንያታዊ ሁኑ:- “ገርነታችሁ [“ምክንያታዊነታችሁ፣” NW] ለሰው ሁሉ ይታወቅ።” —ፊልጵስዩስ 4:5
ሩኅሩኅ ሁኑ:- “እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፣ . . . ይቅር ተባባሉ።”—ኤፌሶን 4:32
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወጣት ሽማግሌዎች በዕድሜ የገፉ ትልልቅ ሰዎች ካካበቱት ተሞክሮ ሊጠቀሙ ይችላሉ