የመከር በዓላት አምላክን ያስደስታሉን?
ጣፋጭ ፍራፍሬዎች፣ አስደሳች ቅጠላ ቅጠሎችና ዛላዎቻቸው የሚያማምሩ የእህል ነዶዎች አንድ ላይ ሲከመሩ ማራኪ የሆነ እይታን ይፈጥራሉ። በመከር ወቅት በእንግሊዝ አገር በሚገኙ ቤተ ክርስቲያኖች ውስጥ ያሉ መሠዊያዎችና አትራኖሶች እነዚህን በመሳሰሉ ነገሮች ያጌጣሉ። በሌሎች ቦታዎች እንደሚደረገው ሁሉ በአውሮፓም በመከር ወቅት መጀመሪያና ማብቂያ ላይ የሚከበሩ ብዙ በዓላት አሉ።
በተለይ በግብርና የሚተዳደሩ ሰዎች መሬቱ ምርታማ ሲሆን በጣም ይደሰታሉ። እርግጥ አምላክ የጥንቱን የእስራኤል ሕዝብ ከመከር ጋር በቅርብ የተዛመዱ ሦስት ዓመታዊ በዓላትን እንዲያከብሩ ይፈልግባቸው ነበር። በጸደይ ወራት መግቢያ ላይ የቂጣ በዓል በሚከበርበት ጊዜ እስራኤላውያን ከገብስ መከር በኩራት አንድ ነዶ ለአምላክ ያቀርቡ ነበር። በጸደይ ወራት መገባደጃ በሚከበረው የሳምንታቱ በዓል (ወይም ጰንጠቆስጤ) ላይ ከስንዴ መከር በኩራት የተጋገሩ ቂጣዎችን አቅርበዋል። በበልግ ወቅት የእስራኤልን የእርሻ ዓመት ማብቃት የሚጠቁመው የመከር በዓል ይመጣል። (ዘጸአት 23:14-17) እነዚህ በዓላት ‘የተቀደሱ ጉባኤዎች’ እና የደስታ ጊዜያት ነበሩ።—ዘሌዋውያን 23:2፤ ዘዳግም 16:16
በዘመናችን በመከር ወቅት ስለሚከበሩ በዓላትስ ምን ለማለት ይቻላል? እነዚህ በዓላት አምላክን ያስደስታሉን?
ከአረማዊ ልማዶች ጋር ንክኪ ያላቸው
በእንግሊዝ አገር በኮርንዎል ከተማ ይኖር የነበረ አንድ የአንግሊካን ቄስ ዓለማዊ መልክ የነበረው ባህላዊው የመከር ወቅት ግብዣና በዓሉን ምክንያት በማድረግ የሚታየው ስካር ስላላስደሰተው በ1843 በመካከለኛው ዘመን የነበረው የመከር ወቅት ልማድ እንዲያንሰራራ ለማድረግ ወሰነ። ከታጨደው አዝመራ ከበኩሩ ጥቂት ወስዶ በቤተ ክርስቲያኑ ለሚደረገው ሥርዓተ ቁርባን የሚውል ቂጣ አድርጎ ጋገረው። ይህን በማድረግ አንዳንዶች ከቀድሞው የሴልቲክ አምላክ ከሆነው ከሉክ አምልኮ የመነጨ ነው የሚሉትን ላማስ የተባለው “ክርስቲያናዊ” በዓል ተጠብቆ እንዲቆይ አድርጓል።a ስለዚህ ዘመናዊው የአንግሊካን የመከር በዓል አረመኔያዊ መሠረት አለው።
በመከር ወቅት ማብቂያ ላይ ስለሚከበሩ ሌሎች በዓላትስ ምን ለማለት ይቻላል? ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንደገለጸው እነዚህን በዓላት የሚያመለክቱት ብዙዎቹ ልማዶች የመነጩት “ከእህል መንፈስ ወይም ከእህል እናት መናፍስታዊ አምልኮ” ነው። በአንዳንድ አካባቢ የሚኖሩ ገበሬዎች በመጨረሻ በሚታጨደው የእህል ነዶ ላይ አንድ መንፈስ ያርፋል ብለው ያምናሉ። ይህን መንፈስ ለማባረር እህሉ ሙልጭ ብሎ እስኪረግፍ ድረስ በእንጨት ይመቱታል። በሌሎች ቦታዎች ደግሞ ከእህሉ ጥቂት ዛላዎችን ወስደው አንድ ላይ በመጎንጎን “ኮርን ዶሊ” በመሥራት እስከሚቀጥለው ዓመት የዘር ወቅት ድረስ ለ“ዕድል” ይሆናል በማለት በደኅና ቦታ ያስቀምጡታል። ከዚያም አዲሱን ሰብል ይባርከዋል ብለው ተስፋ በማድረግ መልሰው ማሳው ውስጥ ይበትኑታል።
አንዳንድ አፈ ታሪኮች የመከርን ወቅት ኢሽታር የተባለችው የመራባት አምላክ ባል ከሆነው ከባቢሎናውያን አምላክ ከተሙዝ አምልኮ ጋር ያያይዙታል። በደንብ የደረሰውን የእህል ዛላ መቁረጥን ከተሙዝ ያለጊዜው መሞት ጋር ያመሳስሉታል። ሌሎች አፈ ታሪኮች የመከርን ወቅት ሰዎችን መሥዋዕት ከማድረግ ልማድ ጋር ያገናኙታል፤ ይህ ደግሞ ይሖዋ አምላክ በጣም የሚጠላው ድርጊት ነው።—ዘሌዋውያን 20:2፤ ኤርምያስ 7:30, 31
የአምላክ አመለካከት ምንድን ነው?
አምላክ ከጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ ጋር የነበረው ግንኙነት ፈጣሪና የሕይወት ምንጭ የሆነው ይሖዋ አምላኪዎቹ ለእሱ ብቻ የተወሰነ አምልኮ እንዲያቀርቡለት እንደሚፈልግባቸው በግልጽ ያሳያል። (መዝሙር 36:9፤ ናሆም 1:2) በነቢዩ ሕዝቅኤል ዘመን ተሙዝ ለተባለው አምላክ የማልቀስ ልማድ በይሖዋ ዓይን ‘እጅግ የተጠላ ነገር’ ነበር። በዚህና በሌሎችም ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ግንኙነት ባላቸው ድርጊቶች ምክንያት አምላክ የእነዚያን የሐሰተኛ አምላኪዎች ጸሎት ላለመስማት ጆሮውን እንዲዘጋ አድርጎታል።—ሕዝቅኤል 8:6, 13, 14, 18
ይህን ሁኔታ ይሖዋ አምላክ ከመከር ጋር በተያያዘ መንገድ እስራኤላውያን እንዲጠብቁት ካዘዛቸው ነገር ጋር አነጻጽር። በመከር በዓል ጊዜ እስራኤላውያን ትልቅ ስብሰባ በማድረግ ወጣትና አረጋዊ እንዲሁም ሀብታምና ድሃ ሳይባል ከለምለም የዛፍ ቅጠሎች በተሠሩ ጊዜያዊ ዳሶች ውስጥ ይኖሩ ነበር። ይህ ለእነሱ ታላቅ የደስታ ጊዜ የነበረ ብቻ ሳይሆን አምላክ ቅድመ አያቶቻቸውን ከግብጽ እንዴት ነጻ እንዳወጣቸው የሚያሳይ ነበር።—ዘሌዋውያን 23:40-43
በእስራኤላውያን በዓላት ወቅት መሥዋዕቶች የሚቀርቡት ብቻውን እውነተኛ አምላክ ለሆነው ለይሖዋ ነበር። (ዘዳግም 8:10-20) ከላይ የተገለጹት መናፍስታዊ እምነቶች እንደሚሉት መጽሐፍ ቅዱስ በየትኛውም ቦታ ላይ ቢሆን እንደ ስንዴ ነዶዎች ያሉ ምርቶች ነፍስ እንዳላቸው አድርጎ አይገልጽም።b እንዲሁም ቅዱሳን ጽሑፎች ጣዖታት ግዑዝ የሆኑና ለመናገር፣ ለማየት፣ ለመስማት ለመዳሰስ ወይም ለአምላኪዎቻቸው እርዳታ ለመስጠት እንደማይችሉ በግልጽ ያሳያሉ።—መዝሙር 115:5-8፤ ሮሜ 1:23-25
ዛሬ ክርስቲያኖች አምላክ ከቀድሞው የእስራኤል ሕዝብ ጋር ገብቶት በነበረው የሕግ ቃል ኪዳን ሥር አይደሉም። በእርግጥ አምላክ ‘ሕጉን በኢየሱስ የመከራ እንጨት ላይ ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል።’ (ቆላስይስ 2:13, 14) በዘመናችን የሚገኙት የይሖዋ አገልጋዮች “የክርስቶስን ሕግ” ይታዘዛሉ እንዲሁም አምላክ ለሚሰጣቸው ማንኛውም ነገር አድናቆታቸውን ይገልጻሉ።—ገላትያ 6:2
ሐዋርያው ጳውሎስ የአይሁዳውያን በዓላት “ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፣ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (ቆላስይስ 2:16, 17) ከዚህ ጋር በመስማማት እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚከተለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማብራሪያ ይቀበላሉ:- “ነገር ግን አሕዛብ የሚሠዉት ለአጋንንት እንዲሆን እንጂ ለእግዚአብሔር እንዳይሠዉ እላለሁ፤ . . . የጌታን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ ልትጠጡ አትችሉም።” (1 ቆሮንቶስ 10:20, 21) ከዚህም በላይ ክርስቲያኖች ‘ርኵስ የሆነውን ነገር አትንኩ’ የሚለውን መመሪያ ይከተላሉ። በአካባቢህ የሚከበሩ የመከር በዓላት ከአረማዊ ትምህርቶች ወይም ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ንክኪ አላቸውን? ይህ ከሆነ እውነተኛ ክርስቲያኖች በማንኛውም የተበከለ አምልኮ ለመሳተፍ ባለመፍቀድ ይሖዋን ከማስከፋት ሊርቁ ይችላሉ።—2 ቆሮንቶስ 6:17
አንድ አድናቂ የሆነ ልጅ ከአባቱ ስጦታ ቢቀበል የሚያመሰግነው ማንን ነው? በፍጹም የማያውቀውን እንግዳ ሰው ወይስ ወላጁን? አምላክን የሚያመልኩ ሰዎች ከልብ በመነጨ ጸሎት አማካኝነት የሰማዩ አባታቸው ይሖዋን ለተትረፈረፈው ለጋስነቱ ያመሰግኑታል።—2 ቆሮንቶስ 6:18፤ 1 ተሰሎንቄ 5:17, 18
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a “ላማስ” የሚለው ቃል “ሎፍ-ማስ” የሚል ትርጉም ካለው ከአንድ የቆየ የእንግሊዝኛ ቃል የተገኘ ነው።
b ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “አትክልቶች ደም ስለሌላቸው ነፈሽ (ነፍስ) የሚለው ቃል ከአትክልቶች መፈጠር ጋር ተያይዞ በሦስተኛው የፍጥረት ‘ቀን’ (ዘፍ 1:11-13) ላይም ሆነ ከዚያ በኋላ አልተሠራበትም።”—ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።