ደስታ ሊጨበጥ አልቻለም
ቁጣ፣ ስጋትና የመንፈስ ጭንቀት ለረዥም ዘመናት ሳይንሳዊ ምርምር ሲደረግባቸው ቆይቷል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ሳይንቲስቶች የምርምር አቅጣጫቸውን በሚያንጸውና በሰዎች ዘንድ እጅግ ተፈላጊ በሆነው ደስታ ላይ አዙረዋል።
ሰዎችን የበለጠ ደስተኞች እንዲሆኑ ሊያደርጋቸው የሚችለው ነገር ምንድን ነው? ወጣት፣ ሃብታም፣ ጤናሞች፣ ረጃጅሞች ወይም ቀጭኖች መሆናቸው ነውን? እውነተኛ ደስታ የሚገኝበት ቁልፍ ምንድን ነው? አብዛኞቹ ሰዎች ለዚህ ጥያቄ መልስ ማግኘት ተስኗቸዋል። እንዲያውም አንዳንዶች ደስታ ለማግኘት የሚደረጉት ጥረቶች በአብዛኛው መና ሆነው መቅረታቸውን በማሰብ ደስታ ለማግኘት ቁልፍ ያልሆኑት ነገሮች ምን እንደሆኑ መናገሩ ይበልጥ ቀላል ሆኖ አግኝተውታል።
የታወቁ የስነልቦና ሐኪሞች በራስ ፍላጎት ላይ ብቻ ማተኮር ደስታ የሚገኝበት ቁልፍ እንደሆነ ለረዥም ዘመናት ሲናገሩ ቆይተዋል። ደስታ ያጡ ሰዎች ደስታ ማግኘት እንዲችሉ የግል ፍላጎታቸውን በማርካት ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ አበረታተዋል። “ራስህን ሁን፣” “ውስጣዊ ስሜትህን ተገንዘብ፣” እና “ማንነትህን እወቅ” የሚሉትን የመሰሉ ስሜት የሚስቡ ሐረጎች በሳይኮቴራፒ ሕክምና ተሠርቶባቸዋል። ሆኖም ይህን አስተሳሰብ ሲያራምዱ የነበሩ አንዳንድ ጠበብት እንዲህ የመሰሉ ግላዊ አስተሳሰብ ላይ ያተኮሩ ዝንባሌዎች ዘላቂ የሆነ ደስታ እንደማያመጡ ተገንዝበዋል። ራስን ብቻ መውደድ ሥቃይና ሐዘን ማምጣቱ የማይቀር ነው። ራስ ወዳድነት ደስታ የሚገኝበት ቁልፍ አይደለም።
ለደስታ ማጣት ምክንያት የሆነው ነገር
ተድላን በማሳደድ ደስታ ለማግኘት የሚጣጣሩ ሁሉ ፍለጋቸው የተሳሳተ አቅጣጫን የተከተለ ነው። የጥንቱ እሥራኤል ንጉሥ የነበረውን ጠቢቡ ሰሎሞንን እንደ ምሳሌ አድርገን እንውሰድ። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በመክብብ መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ዓይኖቼንም ከፈለጉት ሁሉ አልከለከልኋቸውም፤ ልቤም በድካሜ ሁሉ ደስ ይለው ነበርና ልቤን ከደስታ ሁሉ አላራቅሁትም፤ ከድካሜም ሁሉ ይህ እድል ፈንታዬ ሆነ።” (መክብብ 2:10) ሰሎሞን ለራሱ ቤቶች ሠራ፤ ወይን ተከለ፣ ለራሱ የሚሆን የአትክልት ቦታና መናፈሻ እንዲሁም የውኃ ማጠራቀሚያዎች አዘጋጀ። (መክብብ 2:4-6) እንዲያውም አንድ ጊዜ “ከእኔ ይበልጥ የበላና የጠጣ ማን አለ?” በማለት ጠይቋል። (መክብብ 2:25 NW) ዝና ባተረፉ ሙዚቀኞችና ዘፋኞች ይዝናና ነበር፤ እንዲሁም በምድሪቱ ከነበሩት እጅግ ውብ የሆኑትን ሴቶች በወዳጅነት ይዞ ነበር።—መክብብ 2:8
እዚህ ላይ ሊተላለፍ የተፈለገው ነጥብ ሰሎሞን እርካታ በሚሰጡ እንቅስቃሴዎች ከመካፈል ወደ ኋላ አለማለቱን ነው። በሕይወቱ ውስጥ እርካታ የሚሰጡ ብዙ ነገሮችን ካከናወነ በኋላ ምን መደምደሚያ ላይ ደረሰ? እንዲህ አለ:- “እጄ የሠራቻትን ሥራዬን ሁሉ የደከምሁበትንም ድካሜን ሁሉ ተመለከትሁ፤ እነሆ፣ ሁሉ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነበረ፣ ከፀሐይ በታችም ትርፍ አልነበረም።”—መክብብ 2:11
ጠቢቡ ንጉሥ የደረሰበት መደምደሚያ ዛሬም ቢሆን እውነት ነው። ሃብታም አገር የሆነችውን ዩናይትድ ስቴትስን እንደ ምሳሌ አድርገን እንውሰድ። ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ አሜሪካውያን እንደ መኪናና ቴሌቪዥን ያሉት ቁሳዊ ሃብቶቻቸው ቁጥር በሁለት እጥፍ ከፍ ብሏል። ሆኖም የአእምሮ ጤና ሕክምና ጠበብት እንደተናገሩት ከሆነ አሜሪካውያን ምንም ዓይነት የተሻለ ደስታ የላቸውም። አንድ ጽሑፍ እንደ ዘገበው “በእነዚሁ ዓመታት የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ላይ አሻቅቧል። የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉ በአሥራዎቹ እድሜ የሚገኙ ወጣቶች ቁጥር በሦስት እጥፍ አድጓል። ፍቺ በእጥፍ ጨምሯል።” ተመራማሪዎች በቅርቡ በተለያዩ 50 አገሮች በሚኖሩ ሰዎች ላይ በገንዘብና በደስታ መካከል ያለውን ተዛምዶ ከመረመሩ በኋላ ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። በቀላል አነጋገር ደስታን መግዛት አትችልም።
እንዲያውም በተቃራኒው ሃብትን ማሳደድ ደስታ የሚያሳጣ ነገር ነው ተብሎ በትክክል ሊገለጽ ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፣ አንዳንዶችም ይህን ሲመኙ፣ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ” በማለት አስጠንቅቋል።—1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10
ሃብት፣ ጤና፣ ወጣትነት፣ መልክ፣ ሥልጣንም ሆነ የእነዚህ ነገሮች ጥምረት ለዘላቂ ደስታ ዋስትና አይሆንም። ለምን? ምክንያቱም መጥፎ ነገሮች እንዳይከሰቱ የማገድ ኃይል የለንም። ንጉሥ ሰሎሞን “ሰውም ጊዜውን አያውቅም፤ በክፉ መረብ እንደ ተጠመዱ ዓሣዎች፣ በወጥመድም እንደ ተያዙ ወፎች፣ እንዲሁ የሰው ልጆች በክፉ ጊዜ በድንገት ሲወድቅባቸው ይጠመዳሉ” በማለት ጉዳዩን በትክክል አስቀምጦታል።—መክብብ 9:12
ሊጨበጥ ያልቻለ ግብ
የትኛውም ዓይነት የሳይንስ ምርምር ደስታን ለማስገኘት የሚያስችል ሰው ሰራሽ ደንብ ወይም ዘዴ ሊፈጥር አይችልም። ሰሎሞን “እኔም ተመለስሁ፣ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፣ ሰልፍም ለኃያላን፣ እንጀራም ለጠቢባን፣ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፣ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና ዕድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል” በማለት አክሎ ተናግሯል።—መክብብ 9:11
ከላይ ከተጠቀሱት ቃላት ጋር የሚስማሙ ብዙ ሰዎች እውነተኛ ደስታ የሞላበት ሕይወት ለማግኘት መናፈቅ የሕልም እንጀራ ነው ብለው ደምድመዋል። አንድ የታወቁ አስተማሪ “ደስታ አእምሮ የወለደው ሐሳብ ነው” ብለዋል። ሌሎች ደግሞ ደስታ የሚገኝበት ቁልፍ ሊፈታ የማይችል ምሥጢር እንደሆነና ምሥጢሩን የመፍታቱ ችሎታ ረቂቅ ነገሮችን ለመፍታት ተሰጥኦ ላላቸው ለጥቂት አዋቂ ሰዎች የተወሰነ እንደሆነ አድርገው ያምናሉ።
እንዲህም ሆኖ ሰዎች ደስታ ለማግኘት በሚያደርጉት ፍለጋ የተለያዩ ዓይነት የአኗኗር ዘይቤዎችን መሞከራቸውን ቀጥለዋል። ከእነሱ በፊት የኖሩት ሰዎች ሳይሳካላቸው የቀረ ቢሆንም በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ለሐዘናቸው ፈውስ ለማግኘት ሃብትን፣ ሥልጣንን፣ ጤንነትን ወይም እርካታ የሚሰጡ ነገሮችን ያሳድዳሉ። ብዙ ሰዎች ዘላቂ ደስታ እንዲያው አእምሮ የወለደው ሐሳብ እንዳልሆነ ጠንካራ እምነት ስላላቸው ይህን ደስታ ለማግኘት ፍለጋ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። ደስታ የሕልም እንጀራ እንዳልሆነ ያምናሉ። አንተም ‘ታዲያ ደስታን እንዴት ማግኘት እችላለሁ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።