የይሖዋን ፈቃድ ፈጽመዋል
የራስን ጥቅም የመሰዋትና በታማኝነት የመጣበቅ ምሳሌ
ኤልሳዕ የተባለ አንድ ወጣት ገበሬ አንድ ቀን በዘወትር የእርሻ ሥራው ላይ ተሰማርቶ ሳለ በሕይወቱ ውስጥ ፈጽሞ ያልጠበቀው ነገር ገጠመው። እርሻውን እያረሰ ባለበት ወቅት የእስራኤል ዋነኛ ነቢይ የሆነው ኤልያስ ድንገት ሊጠይቀው መጣ። ‘ምን ፈልጎ ይሆን ሊጠይቀኝ የመጣው?’ ብሎ ሳያስብ አይቀርም። መልስ ለማግኘት ብዙ መጠበቅ አላስፈለገውም። ኤልያስ የነቢይነት ልብሱን ኤልሳዕ ላይ በመጣል አንድ ቀን ኤልሳዕ የእርሱ ተተኪ እንደሚሆን ጠቆመው። ኤልሳዕ ጥሪውን አቅልሎ አልተመለከተውም። ኤልሳዕ ወዲያው እርሻውን ትቶ የኤልያስ አገልጋይ ለመሆን ሄደ።—1 ነገሥት 19:19-21
ከስድስት ዓመታት ገደማ በኋላ ኤልያስ የሚሄድበት ጊዜ ደረሰ። ኤልያስ ከኤልሳዕ ስለተለየበት ሁኔታ የሚገልጸው ዘገባ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከሚገኙት “እጅግ አስደናቂ ከሆኑት ትረካዎች አንዱ” እንደሆነ ይነገርለታል።
ኤልያስ ለመሄድ ተዘጋጀ
ኤልያስ ለመጨረሻ ጊዜ ቤቴልን፣ ኢያሪኮንና ዮርዳኖስን ለመጎብኘት ፈለገ። ይህ ደግሞ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን በእግር መጓዝ፣ እንዲያውም የተወሰነው መንገድ አቀበትና ቁልቁለት መውጣት መውረድ የሚጠይቅ ነበር። በእያንዳንዱ የጉዞ ጣቢያ ኤልያስ ኤልሳዕን እዚያው እንዲቀር ያበረታታው ነበር። ኤልሳዕ ግን ከጌታዬ ፈጽሞ አልለይም አለ።—2 ነገሥት 2:1, 2, 4, 6
በቤቴልና በኢያሪኮ በነበሩበት ወቅት “የነቢያት ልጆች” ወደ ኤልሳዕ ቀርበው “እግዚአብሔር ጌታህን ከራስህ ላይ ዛሬ እንዲወስደው አውቀሃልን?” ብለው ጠየቁት።a “አዎን፣ አውቄአለሁ፤ ዝም በሉ” ብሎ መለሰላቸው።—2 ነገሥት 2:3, 5
በመቀጠልም ኤልያስና ኤልሳዕ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ አቀኑ። ዮርዳኖስ ወንዝ በደረሱ ጊዜ 50 የሚያክሉ የነቢያት ልጆች ከርቀት እየተመለከቱት፣ ኤልያስ ተአምር አደረገ። “ኤልያስም መጎናጸፊያውን ወስዶ ጠቀለለው፣ ውኃውንም መታ፣ ወዲህና ወዲያም ተከፈለ፤ ሁለቱም በደረቅ ተሻገሩ።”—2 ነገሥት 2:8
ከተሻገሩ በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን “ከአንተ ሳልወሰድ አደርግልህ ዘንድ የምትሻውን ለምን” አለው። ኤልሳዕ የኤልያስን “ሁለት እጥፍ” መንፈስ እንዲሰጠው ጠየቀ። ይህ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ በኩር ለሆነ ወንድ ልጅ የሚሰጠውን ሁለት እጥፍ ድርሻ ያመለክታል። በእርግጥም ኤልሳዕ አንድ በኩር ልጅ አባቱን የሚያከብረውን ያህል ኤልያስን አክብሮታል። ከዚህም በላይ የኤልያስ ተተኪ በመሆን በእስራኤል የይሖዋ ነቢይ ለመሆን ተቀብቷል። ስለዚህ የእርሱ ጥያቄ ራስ ወዳድነትን የሚያንጸባርቅ ወይም ደግሞ ተገቢ ያልሆነ ጥያቄ አልነበረም። የሆነ ሆኖ ይህን ጥያቄ ሊያሟላ የሚችለው ይሖዋ ብቻ መሆኑን በመገንዘብ “አስቸጋሪ ነገር ለምነሃል” በማለት ኤልያስ በትህትና መልሷል። አክሎም “ከአንተ ዘንድ በተወሰድኩ ጊዜ ብታየኝ ይሆንልሃል፤ አለዚያ ግን አይሆንልህም” አለው።—2 ነገሥት 2:9, 10፤ ዘዳግም 21:17
ኤልሳዕ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጌታውን የሙጥኝ ብሎ ለመቀጠል እንደወሰነ ምንም ጥርጥር የለውም። በኋላም “የእሳት ሰረገላና የእሳት ፈረሶች” መጡ። የኤልሳዕ ዓይኖች በመገረም አፍጥጠው እንዳሉ ኤልያስ ተአምራዊ በሆነ ሁኔታ በዐውሎ ነፋስ ወደ ሌላ ቦታ ተወሰደ።b ኤልሳዕ የኤልያስን የነቢይነት ልብሱን ከወደቀበት አንስቶ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ተመለሰ። “የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው?” በማለት ውኃውን መታ። ኤልሳዕ የኤልያስ ተተኪ ለመሆን መለኮታዊ ድጋፍ ማግኘቱን ግልጽ ማረጋገጫ በመስጠት ውኃው ተከፈለ።—2 ነገሥት 2:11-14
ለእኛ የሚሆኑ ትምህርቶች
ከኤልያስ ጋር እንዲሠራ ለልዩ አገልግሎት ግብዣ በቀረበለት ጊዜ ኤልሳዕ የእስራኤልን ዋነኛ ነቢይ ለማገልገል እርሻውን ወዲያውኑ ትቶ ሄደ። “በኤልያስ እጅ ላይ ውኃ ያፈስስ የነበረው” ተብሎ ይታወቅ ስለነበር አንዳንድ ሥራዎቹ ዝቅተኛ እንደነበሩ ከሁኔታው ለመረዳት ይቻላል።c (2 ነገሥት 3:11) የሆነ ሆኖ ኤልሳዕ ሥራውን እንደ መብት ቆጥሮታል፤ ከኤልያስ ጎንም በታማኝነት ተጣብቋል።
በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ የአምላክ አገልጋዮች ተመሳሳይ የሆነ የራስን ጥቅም የመሰዋት መንፈስ ያሳያሉ። አንዳንዶች ራቅ ባሉ ክልሎች ምሥራቹን ለመስበክ ወይም የቤቴል ቤተሰብ አባል ሆነው ለማገልገል ሲሉ “እርሻቸውን” ማለትም የሚተዳደሩበትን ሥራ ትተዋል። ሌሎች ደግሞ በማኅበሩ የግንባታ ፕሮጀክቶች ለመሥራት ወደ ባዕድ አገሮች ሄደዋል። ብዙዎች ዝቅተኛ ሥራዎች ሊባሉ የሚችሉትን በፈቃደኝነት ተቀብለዋል። ሆኖም ይሖዋን የሚያገለግል ማንኛውም ሰው የሚያከናውነው አገልግሎት ፈጽሞ አይናቅም። ይሖዋ በፈቃደኝነት እርሱን የሚያገለግሉትን ያደንቃል፤ የራስን ጥቅም የመሰዋት መንፈሳቸውንም ይባርካል።—ማርቆስ 10:29, 30
ኤልሳዕ እስከመጨረሻው ድረስ ኤልያስን የሙጥኝ ብሏል። ኤልሳዕ በእድሜ የሚበልጠው ነቢይ ከእርሱ እንዲለይ በጠየቀው ጊዜ እንኳ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። ከኤልያስ ጋር የነበረው የጠበቀ ዝምድና እንዲህ ባለው ታማኝ ፍቅር እንዲደሰት እንዳስቻለው ምንም አያጠራጥርም። ዛሬም የአምላክ አገልጋዮች ከአምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድና ለማጠናከርና ወደ እምነት ጓደኞቻቸው ይበልጥ ለመቅረብ ይጥራሉ። የጠበቀ አንድነታቸው ይባረካል፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ሲናገር “ከታማኝ ሰው ጋር ታማኝ ሆነህ ትገኛለህ” ይላል።—2 ሳሙኤል 22:26 NW
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a “የነቢያት ልጆች” የሚለው አጠራር ለዚህ ሥራ የተጠሩት ስልጠና የሚያገኙበትን ትምህርት ቤት ወይም የነቢያትን የመረዳጃ ማኅበር ሊያመለክት ይችላል።
b ለይሁዳ ንጉሥ ለኢዮራም የተላከው የኤልያስ መልእክት ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ የተጻፈ ነበር።—2 ዜና መዋዕል 21:12-15
c አንድ አገልጋይ፣ በተለይ ከምግብ በኋላ የጌታውን እጅ ማስታጠቡ የተለመደ ነበር። ይህ ልማድ የእንግዳ ተቀባይነት፣ የአክብሮትና በአንዳንድ ግንኙነቶችም የትህትና ድርጊት ከሆነው እግርን ከማጠብ ጋር ተመሳሳይ ነበር።—ዘፍጥረት 24:31, 32፤ ዮሐንስ 13:5