ፍትሕ የሰፈነበት ዓለም ሕልም አይደለም!
የታወቁት የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣን ዳንኤል ዌብስተር “በምድር ላይ የሰው ልጅ ጽኑ ፍላጎት ፍትሕን ማግኘት ነው” ሲሉ ተናግረዋል። መጽሐፍ ቅዱስም “እግዚአብሔር ፍርድን [“ፍትሕን፣” NW] ይወዳልና” በማለት ይገልጻል። (መዝሙር 37:28) የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት በአምላክ መልክ ስለተፈጠሩ የፍትሕ ስሜትን ጨምሮ መለኮታዊ ባሕርያት ነበሯቸው።—ዘፍጥረት 1:26, 27
ቅዱሳን ጽሑፎችም ‘ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ከባሕርያቸው የሕግን ትእዛዝ እንደሚያደርጉ’ ይናገራሉ። ይህም በመሆኑ “እነርሱም ሕሊናቸው ሲመሰክርላቸው፣ አሳባቸውም እርስ በርሳቸው ሲካሰስ ወይም ሲያመካኝ በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ።” (ሮሜ 2:14, 15) አዎን ሰዎች ትክክልና ስህተት የሆነውን ከሚለይ ሕሊና ከተባለ ውስጣዊ የማመዛዘን ስጦታ ጋር ተፈጥረዋል። ሰዎች በተፈጥሯቸው ፍትሕን እንደሚፈልጉ ግልጽ ነው።
መዝሙር 106:3 “ፍርድን [“ፍትሕን፣” NW] የሚጠብቁ፣ ጽድቅንም ሁልጊዜ የሚያደርጉ ምስጉኖች [“ደስተኞች፣” NW] ናቸው” ስለሚል የሰው ልጅ ፍትሕን ለማግኘት ካለው ፍላጎት ጋር ቅርብ ትስስር ያለው ደስታን ለማግኘት የሚያደርገው ፍለጋ ነው። ታዲያ የሰው ልጅ ፍትሕ ያለበት ዓለም ለማስገኘት ያልቻለው ለምንድን ነው?
የሰው ልጅ ያልተሳካለት ለምንድን ነው?
የሰው ልጅ ፍትህ የሰፈነበት ዓለም ለማምጣት የሚያደርገው ጥረት ያልተሳካበት ዋናው ምክንያት ከመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ከአዳምና ከሔዋን በወረስነው እንከን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ” በማለት ያብራራል። (ሮሜ 5:12) ይህ ከአዳምና ከሔዋን የተወረሰው እንከን ኃጢአት ነው። አዳምና ሔዋን ምንም እንኳ ያለ አንዳች እንከን የተፈጠሩ ቢሆንም በአምላክ ላይ ለማመፅ በመምረጣቸው ራሳቸውን ኃጢአተኞች አደረጉ። (ዘፍጥረት 2:16, 17፤ 3:1-6) በዚህም ምክንያት የኃጢአተኝነትን መጥፎ ዝንባሌዎች ለልጆቻቸው አወረሱ።
እንደ ስስትና መሠረተቢስ ጥላቻ የመሳሰሉት የሰዎች ባሕርያት የኃጢአተኝነት ዝንባሌ ውጤቶች አይደሉምን? እነዚህ ባሕርያት በዓለም ላይ ላለው የፍትሕ መጓደል አስተዋጽኦ አያደርጉምን? እያወቁ ተፈጥሮን ያለ አግባብ መጠቀምና የኢኮኖሚ ጭቆና መንስኤያቸው ስስት ነው! ከጎሳ ግጭትና ከዘር መድልዎ በስተጀርባ መሠረተቢስ ጥላቻ መኖሩ የተረጋገጠ ነው። እንዲህ ዓይነቶቹ ባሕርያት ሰዎች እንዲሰርቁ፣ እንዲያጭበረብሩና ሌሎችን የሚጎዱ ነገሮችን እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል።
ፍትሕን ለማስፈንና ጠቃሚ የሆነ ነገር ለማድረግ በጥሩ ውስጣዊ ግፊቶች የሚደረጉ ጥረቶችም በኃጢአተኝነት ዝንባሌዎች ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ መና ይቀራሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ራሱ ሳይሸሽግ እንዲህ ብሏል:- “የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም።” ከዚያም የሚያደርገውን ትግል ሲያብራራ “እንግዲያስ መልካሙን አደርግ ዘንድ ስወድ በእኔ ክፉ እንዲያድርብኝ ሕግን አገኛለሁ። በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፣ ነገር ግን በብልቶቼ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ” ብሏል። (ሮሜ 7:19-23) በዛሬው ጊዜ እኛም ተመሳሳይ የሆነ ትግል ይገጥመናል። ለዚህም ነው ብዙ ጊዜ የፍትሕ መዛባት የሚታየው።
ሌላው በዓለም ላይ ፍትሕ እንዳይሰፍን ያደረገው ነገር የሰው ልጅ የአገዛዝ ሥርዓት ነው። በማንኛውም አገር ሕግና ሕግ አስከባሪ ኃይሎች አሉ። ዳኞችና ፍርድ ቤቶች መኖራቸውም የታወቀ ነው። አንዳንድ በመልካም ምግባር የታነፁ ሰዎች የሰው ልጆችን መብት ለማስከበርና ሁሉም እኩል ፍትሕ እንዲያገኝ ለማድረግ መሞከራቸው አይካድም። ቢሆንም ጥረቶቻቸው በአመዛኙ መክነዋል። ለምን? ኤርምያስ 10:23 እንዳይሳካላቸው አስተዋጽኦ ያደረጉትን የተለያዩ ምክንያቶች ጠቅለል አድርጎ ሲያስቀምጥ እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “አቤቱ፣ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም።” የሰው ልጅ ከአምላክ ተነጥሎ ጽድቅና ፍትሕ የሰፈነበት ዓለም ማቋቋም በጭራሽ አይችልም።—ምሳሌ 14:12፤ መክብብ 8:9
የሰው ልጅ ፍትሕ የሰፈነበት ዓለም ለመገንባት ለሚያደርገው ጥረት ትልቁ መሰናክል ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ዓመፀኛው መልአክ ሰይጣን የመጀመሪያው “ነፍሰ ገዳይ” እና “ሐሰተኛ” መሆኑንና “ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ” በግልጽ ይናገራል። (ዮሐንስ 8:44፤ 1 ዮሐንስ 5:19) ሐዋርያው ጳውሎስ “የዚህ ዓለም አምላክ” በማለት የእርሱን ማንነት ገልጿል። (2 ቆሮንቶስ 4:3, 4) ሰይጣን ጽድቅን የሚጠላ ስለሆነ ክፋትን ለማስፋፋት የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። ሰይጣን ዓለምን መቆጣጠሩን እስካላቆመ ድረስ በሰው ዘር ላይ ብዙ ዓይነት ግፍ መፈጸሙና ከዚህም የተነሳ ወዮታ መኖሩ አይቀርም።
ታዲያ እንዲህ ሲባል በሰብዓዊው ኅብረተሰብ ውስጥ ፍትሕ ማስፈን ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው ማለት ነውን? ፍትሕ የሰፈነበት ዓለም ፈጽሞ እውን ሊሆን የማይችል ሕልም ነውን?
ፍትሕ የሰፈነበት ዓለም እውን የሚሆነው እንዴት ነው?
ፍትሕ የሰፈነበት ዓለም እውን እንዲሆን ከተፈለገ የሰው ልጅ ለፍትሕ መጓደል መንስኤ የሆኑትን ነገሮች ሙሉ በሙሉ ሊያስወግድ ወደሚችል አንድ አካል ዞር ማለት አለበት። ነገር ግን ኃጢአትን ከሥሩ ነቅሎ ለመጣልና ሰይጣንንና የእርሱን አገዛዝ ለማንኮታኮት የሚችል ማን አለ? ይህ ማንኛውም ሰው ወይም ሰው ሠራሽ ድርጅት ሊያከናውነው የሚችለው ነገር እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ይህን ማድረግ የሚችለው ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው! መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እርሱ ሲናገር “እርሱ አምላክ ነው፤ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱ ሁሉ የቀና [“ፍትሕ፣” NW] ነው፤ የታመነ አምላክ፣ ክፋትም የሌለበት፣ እርሱ እውነተኛና ቅን ነው” ይላል። (ዘዳግም 32:4) ይሖዋ ‘ፍትሕን የሚወድ’ እንደመሆኑ መጠን ሰዎች ፍትሕ በሰፈነበት ዓለም ውስጥ በሕይወት እንዲደሰቱ ይፈልጋል።—መዝሙር 37:28 NW
አምላክ ፍትሕ የሰፈነበት ዓለም ለማምጣት ያለውን ዝግጅት አስመልክቶ ሲናገር ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል:- “ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።” (2 ጴጥሮስ 3:13) “አዲስ ሰማይ” የተባለው አዲስ ግዑዝ ሰማይ ማለት አይደለም። አምላክ ግዑዙን ሰማይ ፍጹም አድርጎ ስለሠራው ለእርሱ ውዳሴ ያስገኝለታል። (መዝሙር 8:3፤ 19:1, 2) ‘አዲሱ ሰማይ’ በምድር ላይ የሚሰፍነው አዲስ አገዛዝ ነው። ባሁኑ ጊዜ ያለው “ሰማይ” ሰው ሠራሽ መስተዳድሮችን ያቀፈ ነው። በቅርቡ የአምላክ ጦርነት በሆነው በአርማጌዶን ይህ ሰማይ የአምላክ መንግሥት ወይም መስተዳድር ለሆነው ‘ለአዲሱ ሰማይ’ ቦታውን ይለቃል። (ራእይ 16:14-16) የዚህ መንግሥት ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የሰውን አገዛዝ ለዘለቄታው በማስወገድ ይህ መስተዳድር ላልተወሰነ ጊዜ ይገዛል።—ዳንኤል 2:44
ታዲያ “አዲሱ ምድር” ምንድን ነው? አምላክ ምድርን ለሰው ልጆች መኖሪያነት ፍጹም ተስማሚ አድርጎ ስለሠራትና ለዘላለምም እንድትኖር ፈቃዱ ስለሆነ፤ አዲስ ፕላኔት ማለት አይደለም። (መዝሙር 104:5) “አዲስ ምድር” የሚያመለክተው አዲስ የሰዎችን ኅብረተሰብ ነው። (ዘፍጥረት 11:1፤ መዝሙር 96:1) የሚጠፋው “ምድር” ራሳቸውን የዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ክፍል ያደረጉ ሰዎችን ያቀፈ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:7) እነርሱን የሚተካው “አዲስ ምድር” ክፋትን ከሚጠሉና ጽድቅንና ፍትሕን ከሚወዱ እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች የተዋቀረ ይሆናል። (መዝሙር 37:10, 11) በዚህ መንገድ የሰይጣን ዓለም ያከትምለታል።
ሆኖም ሰይጣንስ ምን ይጠብቀዋል? ሐዋርያው ዮሐንስ እንደሚከተለው ሲል ተንብዮአል:- “የጥልቁንም መክፈቻና ታላቁን ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ [ኢየሱስ ክርስቶስ] ከሰማይ ሲወርድ አየሁ። የቀደመውንም እባብ ዘንዶውን እርሱም ዲያብሎስና ሰይጣን የተባለውን ያዘው፣ ሺህ ዓመትም አሰረው፣ ወደ ጥልቅም ጣለው አሕዛብንም ወደ ፊት እንዳያስት ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በእርሱ ላይ ዘግቶ ማኅተም አደረገበት።” (ራእይ 20:1-3) በጨለማ ክፍል ውስጥ የታሰረ እስረኛ ምንም ነገር ማድረግ እንደማይችል ሁሉ በሰንሰለት የታሰረው ሰይጣንም በሰው ዘሮች ላይ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ አይኖረውም። ፍትሕ ወደሰፈነበት ዓለም ለሚገቡት ሰዎች ይህ እንዴት ያለ እፎይታ ይሆናል! ከዚያም በሺው ዓመት መጨረሻ ሰይጣን ከሕልውና ውጭ ይደረጋል።—ራእይ 20:7-10
የተወረሰው ኃጢአትስ ምን ይሆናል? ኃጢአትን ከስሩ ለመመንገል የሚያስችለውን መሠረት ይሖዋ አስቀድሞ አዘጋጅቷል። ‘የሰው ልጅ [ኢየሱስ ክርስቶስ] . . . ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ መጣ።’ (ማቴዎስ 20:28) “ቤዛ” የሚለው ቃል አንድን እስረኛ ለማስለቀቅ የሚከፈለውን ዋጋ ያመለክታል። የሰውን ዘር ነፃ ለማውጣት ኢየሱስ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ከፍሏል።—2 ቆሮንቶስ 5:14፤ 1 ጴጥሮስ 1:18, 19
የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አሁንም ቢሆን ይጠቅመናል። በቤዛው ላይ እምነት በማሳደር በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋም በማግኘት መደሰት እንችላለን። (ሥራ 10:43፤ 1 ቆሮንቶስ 6:11) በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ስር ቤዛው የሰው ዘር ከኃጢአት ሙሉ በሙሉ እንዲላቀቅ ያስችላል። የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ከአምላክ ዙፋን ስለሚወጣ ምሳሌያዊ “የሕይወት ውኃ ወንዝ” እና ከወንዙ ወዲያና ወዲህ “ለሕዝብ መፈወሻ” የሚሆኑ ቅጠሎች ስላሏቸው ምሳሌያዊ ፍሬያማ ዛፎች ይገልጻል። (ራእይ 22:1, 2) መጽሐፍ ቅዱስ እዚህ ላይ በስዕላዊ መንገድ የገለጸው ነገር በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት የሰው ዘር ከኃጢአት የሚላቀቅበትን የፈጣሪን አስደናቂ ዝግጅት ያመለክታል። ይህ ዝግጅት ሙሉ በሙሉ በሥራ ላይ ሲውል ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ያወጣቸዋል።
ፍትሕ በሰፈነበት ዓለም ውስጥ የሚኖረው ሕይወት
በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ስር ሕይወት ምን ሊመስል እንደሚችል እስቲ አስብ። ወንጀልና ዓመፅ ያከትማል። (ምሳሌ 2:21, 22) የኢኮኖሚ ችግር አይኖርም። (መዝሙር 37:6፤ 72:12, 13፤ ኢሳይያስ 65:21-23) ማንኛውም ዓይነት የብሔር፣ የዘርና የጎሳ ልዩነቶች ጨርሶ ይወገዳሉ። (ሥራ 10:34, 35) ጦርነቶችና የጦር መሣሪያዎች ፈጽሞ አይኖሩም። (መዝሙር 46:9) በሚልዮን የሚቆጠሩ ሙታን ፍትሕ በሰፈነበት ዓለም ውስጥ ለመኖር ወደ ሕይወት ይመለሳሉ። (ሥራ 24:15) እያንዳንዱ ሰው ፍጹምና የተሟላ ጤንነት ይኖረዋል። (ኢዮብ 33:25፤ ራእይ 21:3, 4) “[ኢየሱስ ክርስቶስ] በታማኝነት ለሰው ዘር ሁሉ ፍትሕን ያስገኛል” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል።—ኢሳይያስ 42:3 የ1980 ትርጉም
እስከዚያ ድረስ ግፍ ሊፈጸምብን ይችላል፤ ሆኖም እኛም በአጸፋው ግፈኞች መሆን የለብንም። (ሚክያስ 6:8) የሚደርስብንን ግፍ በትዕግሥት መቻል በሚኖርብን ጊዜም ገንቢ አመለካከት እንያዝ። በተስፋ የምንጠባበቀው ፍትህ የሰፈነበት ዓለም በቅርቡ እውን ይሆናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ 2 ጴጥሮስ 3:11-13) ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ተናግሯል፤ የተናገረው ደግሞ “እንዲሁ ይሆናል።” (ኢሳይያስ 55:10, 11) አምላክ የሚፈልግብንን ነገሮች በመማር ፍትሕ በሰፈነበት ዓለም ውስጥ ለመኖር የምንዘጋጅበት ጊዜ አሁን ነው።—ዮሐንስ 17:3፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ምንም ዓይነት የፍትሕ መጓደል አይኖርም