ወጣቶች በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ?
አስቀድመህ ለመስማት የምትፈልገው የትኛውን ነው? መልካሙን ዜና ወይስ መጥፎውን? ብዙ ሰዎች ይህ ጥያቄ ሲቀርብላቸው መልካሙ ዜና በአእምሯቸው ውስጥ ተቀርጾ እንዲቆይ ሲሉ አስቀድመው መጥፎውን ዜና ለመስማት ይመርጣሉ።
ወጣቶች የሚገኙበትን ሁኔታ በምንመረምርበት ጊዜ በቅድሚያ አሁን ያለውን ሁኔታ ማጤን ያስፈልጋል። አረጋውያን በአጠቃላይ ዛሬ ያሉ ወጣቶች ከድሮዎቹ ወጣቶች የተለዩ መሆናቸውን ይናገራሉ። በአንጻሩ ደግሞ ወጣቶች ቀደም ሲል የነበረውን የአቋም ደረጃ አያሟሉም የሚለው አባባል አይዋጥላቸውም። የሆኖ ሆኖ ሰብዓዊውን ኅብረተሰብ በንቃት የሚከታተሉ ታዛቢዎች የዛሬዎቹ ወጣቶች የተለዩ እንደሆኑ ይናገራሉ።
የተለዩ የሆኑት እንዴት ነው?
ወጣቶች፣ መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው፣ ኃላፊነት የሚሰማቸውና ለሌሎች አክብሮት ያላቸው መሆን እንደሚኖርባቸው በአብዛኞቹ ሰዎች የሚታመን ቢሆንም እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው። በለንደኑ ዚ ኢንዲፔንደንት ጋዜጣ ላይ ታትሞ የወጣ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ወጣቶች “እንደጠበቁት ሆኖ ያላገኙትን ዓለም በመቃወም ‘አዲስ የዓመፅ መንፈስ’ እያዳበሩ ናቸው።” ዛሬ ራሳቸውን “አስተዋይና ኃላፊነት የሚሰማቸው” አድርገው የሚመለከቱ ወጣቶች በጣም ጥቂት መሆናቸውን አንድ ጥናት ያመለከተ ሲሆን በጥናቱ ላይ ይበልጥ የተንጸባረቀው ይህ “አዲስ የዓመፅ መንፈስ” ነው። እነዚህ ወጣቶች “ስድና የማይጨበጡ” ሆነው ቢታዩ ይመርጣሉ።
ለምሳሌ ያህል በብሪታንያ በአብዛኛው በወጣቶች የተፈጸሙ ለመንግሥት ሪፖርት የተደረጉ ወንጀሎች ቁጥር ከ1950 እስከ 1993 ባለው ጊዜ ውስጥ በአሥር እጅ ጨምሯል። አደንዛዥ ዕፆችን የሚወስዱና አልኮልን አላግባብ የሚጠቀሙም ቁጥራቸው የዚያኑ ያህል ጨምሯል። በተመሳሳይ ሁኔታ የለንደኑ ዘ ታይምስ መጽሔት በሁሉም ያደጉ አገሮች ውስጥ ማለት ይቻላል፣ “ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በወጣቶች ላይ የሚታየው ሥነ ልቦናዊና ማኅበራዊ ቀውስ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን” ዘግቧል። በወንጀል ድርጊቶች ላይ ጥናት የሚያካሄዱት ፕሮፌሰር ዴቪድ ጄ ስሚዝ እነዚህ ቀውሶች “ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ከማጣት ወይም ሀብት ከማካበት ጋር የተቆራኙ አይደሉም” ብለዋል። በወጣቶችና በአረጋውያን መካከል ትልቅ ልዩነት መኖሩን ጥናቶች ያረጋግጣሉ።
በአሁኑ ጊዜ ልጆችና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ በሚሄድ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ይገኛሉ። ራሳቸውን ለመግደል ሙከራ ስላደረጉ ወይም ተሳክቶላቸው ራሳቸውን ለህልፈተ ሕይወት ስለዳረጉ ወጣቶች መስማት የተለመደ ነገር ሆኗል። የስኮትላንዱ የግላስጎ ሄራልድ ጋዜጣ ራሳቸውን የመግደል ሙከራ የሚያደርጉ ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ቁጥር ከአሥር ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በእጥፍ መጨመሩን ሪፖርት አድርጓል። ትልልቅ ልጆች፣ ተስፋ መቁረጥ ተመሳሳይ የሆነ ነገር እንዲፈጽሙ ያደርጋቸዋል። ጋዜጣው እንዲህ ብሏል:- “እነዚህ ራስን ለመግደል የሚደረጉ ሙከራዎች ወጣቶች ያሉባቸው ሥነ አእምሯዊ ችግሮች የሚያስከትሏቸው ውጤቶች ናቸው። እነዚህ ችግሮች ደግሞ እንዲህ ላሉት ወጣቶች ከሚሰጠው እርዳታ በልጠው እንዳይገኙ ያሰጋል።”
ተወቃሹ ማን ነው?
ወጣቶች ያላቸው አመለካከት “በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን አስተሳሰብ የሚጻረር” በመሆኑ አዋቂዎች ወጣቶችን ተወቃሽ ማድረግ ይቀናቸዋል። ይሁን እንጂ እውነቱን ለመናገር ዛሬ ወጣቶች ለሚገኙበት ሁኔታ ዋነኛ ተወቃሾች አዋቂዎች አይደሉምን? ብዙውን ጊዜ ምክንያት ተደርገው የሚጠቀሱት ነገሮች ከእኩዮቻቸው የሚደርስባቸው ተጽእኖ፣ የወላጆች ቸልተኛ መሆን፣ ወጣቶች ምሳሌ ሊሆናቸው የሚችል የሚተማመኑበት ሰው ማጣት ናቸው። የብሪታንያ ሜዲካል ሪሰርች ካውንስል ቻይልድ ሳይኪያትሪ ዩኒት ኃላፊ የሆኑት ፕሮፌሰር ሰር ማይክል ራተር “በሰፊው ሕዝብ ዘንድ ያለው የመንፈስ ጭንቀት የዛሬ 30 ዓመት ከነበረው ጋር ተመሳሳይ ነው” ብለዋል። አክለውም “ይሁን እንጂ በአሥራዎቹ ዕድሜ በሚገኙ ልጆችና በወጣቶች ዘንድ እጅግ ተበራክቷል። . . . የቤተሰብ መፈራረስ ለዚህ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ምንም አያጠራጥርም፤ ይህም ፍቺን ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በአዋቂዎች መካከል የሚኖረውን አለመግባባትና ግጭት ይጨምራል።”
አንዲት ተመራማሪ ወጣቶች “ባህላዊውን የሥነ ምግባር ደንብ እየተዉት መጥተዋል” ብለዋል። ለምን? “ምክንያቱም ባህላዊው የሥነ ምግባር ደንብ ለእነሱ የሚሠራ ሆኖ አልተገኘም።” የጾታን ሚና በተመለከተ በመለወጥ ላይ ያለውን አመለካከት እንደ ምሳሌ አድርገህ ውሰድ። ብዙ ወጣት ሴቶች የወንዶችን የጠብ አጫሪነትና የዓመፀኝነት መንፈስ ሲኮርጁ በአንጻሩ ደግሞ ወጣት ወንዶች ሴት የሚያስመስላቸውን ነገር ያደርጋሉ። በቀድሞ ዘመን ከነበረው ባህል እንዴት የተለየ ነው!
በአሁኑ ጊዜ ይህን የመሰለ ሥር ነቀል ለውጥ የምናየው ለምንድን ነው? እንዲሁም በጊዜያችን ያሉትን ወጣቶች በተመለከተ ምን መልካም ዜና ሊኖር ይችላል? አስተማማኝ የሆነ የወደፊት ተስፋ ሊኖራቸው የሚችለው እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕሳችን በእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ላይ ያተኩራል።