የዘመናዊው የገና በዓል አመጣጥ
በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ገና የሚከበርበት ጊዜ እጅግ አስደሳች የሆነ ወቅት ነው። ታላቅ ግብዣ የሚደረግበት፣ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ባህል የሚከበርበትና ቤተሰቦች አንድ ላይ የሚሰባሰቡበት ጊዜ ነው። በተጨማሪም የገና በዓል ጓደኛሞችና ዝምድና ያላቸው ሰዎች ካርዶችንና ስጦታዎችን የሚለዋወጡበት ጊዜ ነው።
ይሁን እንጂ ገና ከ150 ዓመታት በፊት ከዚህ ፍጹም የተለየ በዓል ነበር። የታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ስቲቨን ኒሰንቦም ዘ ባትል ፎር ክሪስማስ በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ገና . . . የሰዎችን ባህርይ ይቆጣጠሩ የነበሩት መመሪያዎች ለጊዜው ወደኋላ ገሸሽ ተደርገው በታኅሣሥ ወር እንደሚከበረው ማርዲ ግራ ‘ለፌስታ’ ሲባል ያለ ልክ የሚጠጡበት ጊዜ ነበር።”
ገናን እንደ ቅዱስ አድርገው ለሚመለከቱ ሰዎች ይህ መግለጫ ግራ የሚያጋባ ነው። የአምላክን ልጅ ልደት ለማስታወስ ተብሎ የሚከበርን በዓል ሰዎች ለምን ያረክሱታል? መልሱ ያስገርምህ ይሆናል።
ብልሹ ጅምር
የገና በዓል መከበር ከጀመረበት ከአራተኛው መቶ ዘመን አንስቶ ብዙ ውዝግብ ተካሄዶበታል። ለምሳሌ ያህል የኢየሱስን የልደት ቀን አስመልክቶ ጥያቄ ተነስቶ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቶስ የተወለደበትን ቀንም ሆነ ወር ለይቶ የማይገልጽ በመሆኑ ክርስቶስ ተወልዶባቸዋል ተብለው የሚታሰቡ የተለያዩ ቀናት ሲጠቀሱ ቆይተዋል። በሦስተኛው መቶ ዘመን ግብጻውያን የሆኑ የሃይማኖት ምሁራንን ያቀፈ አንድ ቡድን ኢየሱስ የተወለደበት ቀን ግንቦት 20 ነው ሲል ሌሎች ደግሞ እንደ መጋቢት 28፣ ሚያዝያ 2 ወይም ሚያዝያ 19 የመሳሰሉትን ቀደም ያሉ ቀናት ጠቅሰዋል። በ18ኛው መቶ ዘመን የኢየሱስ ልደት በዓመት ውስጥ ከሚገኘው ከእያንዳንዱ ወር ጋር ተያይዞ ነበር! ታዲያ በመጨረሻ ታኅሣሥ 25 ሊመረጥ የቻለው እንዴት ነው?
ታኅሣሥ 25ን የኢየሱስ የልደት ቀን አድርጋ የሰየመችው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንደሆነች በርካታ ምሁራን ይስማማሉ። ለምን? ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ “ይህ የሆነበት ምክንያት የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች ቀኑ አረማውያን የነበሩ ሮማውያን ‘የማትበገረው ፀሐይ የልደት ቀን’ ብለው ያከብሩት ከነበረው በዓል ጋር አንድ ቀን ላይ እንዲውል በመፈለጋቸው ሳይሆን አይቀርም” ብሏል። ይሁን እንጂ ከሁለት መቶ ተኩል ለሚበልጡ ዓመታት ከአረማውያን ከፍተኛ ስደት ይደርስባቸው የነበሩት ክርስቲያኖች በድንገት ለአሳዳጆቻቸው የተንበረከኩት ለምንድን ነው?
የአረማውያን ትምህርት ሰርጎ ገባ
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሐዋርያው ጳውሎስ “ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች” ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ሾልከው እንደሚገቡና ብዙዎችን እንደሚያስቱ ለጢሞቴዎስ አስታውቆታል። (2 ጢሞቴዎስ 3:13) ሐዋርያት ሞተው ካለቁ በኋላ ይህ ታላቅ ክህደት ጀመረ። (ሥራ 20:29, 30) በአራተኛው መቶ ዘመን ቆስጠንጢኖስ ወደ ክርስትና ተለወጠ ከተባለ በኋላ በርካታ ቁጥር ያላቸው አረማውያን በወቅቱ ሰፍኖ ወደነበረው ስመ ክርስትና መጉረፍ ጀመሩ። ውጤቱስ ምን ሆነ? ኧርሊ ክርስቺያኒቲ ኤንድ ፓጋኒዝም የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ ጥቂት የነበሩት እውነተኛ አማኞች ከፍተኛ ቁጥር በነበራቸው ክርስቲያን ነን ባዮች ተዋጡ።”
የጳውሎስ ቃላት በእርግጥም ትክክል ነበሩ! እውነተኛ ክርስትና በአረማውያን ትምህርት የተዋጠ ያህል ነበር። ይህ ብክለት ይበልጥ ግልጽ ሆኖ የሚታየው በተለይ በበዓላት አከባበር ላይ ነው።
እንደ እውነቱ ከሆነ ክርስቲያኖች እንዲያከብሩ የታዘዙት የጌታን እራት ብቻ ነው። (1 ቆሮንቶስ 11:23-26) የሮማውያን በዓላት ከጣዖት አምልኮ ጋር ግንኙነት ስለነበራቸው የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች በእነዚህ በዓላት አይካፈሉም ነበር። በዚህም ምክንያት በሦስተኛው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ አረማውያን ክርስቲያኖችን እንዲህ እያሉ ይነቅፏቸው ነበር:- “ኤግዚቢሽኖችን አትጎበኙም፣ ለሕዝብ ለሚቀርቡ ትርኢቶች ግድ የላችሁም፤ ሕዝባዊ የእራት ግብዣዎች ላይ አትገኙም እንዲሁም የተቀደሱ ግጥሚያዎችን ትጠላላችሁ።” በሌላ በኩል ደግሞ አረማውያን “አማልክትን የምናመልከው በደስታ፣ በግብዣ፣ በዘፈንና በጨዋታዎች ነው” በማለት ጉራቸውን ይነዙ ነበር።
በአራተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ አረማውያን ያሰሙት የነበረው ተቃውሞ ጋብ አለ። ይህ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው? አስመሳይ ክርስቲያኖች ቀስ በቀስ ወደ ቡድኑ እየገቡ ሲሄዱ የክህደት አስተሳሰቦች ተባዙ። ይህም አቋማቸውን በማላላት ከሮማውያኑ ዓለም ጋር ስምምነት መፍጠር እንዲጀምሩ አደረጋቸው። ዘ ፓጋኒዝም ኢን አወር ክርስቺያኒቲ የተባለው መጽሐፍ ይህን በተመለከተ እንደሚከተለው ብሏል:- “ባህሉ በሕዝቡ ዘንድ ተወዳጅ ያደረጋቸውን አረማዊ በዓላት ክርስቲያናዊ ትርጉም እንዲኖራቸው ማድረግ የክርስትና ልማድ ሆኖ ነበር።” አዎን፣ ታላቁ ክህደት ሥር እየሰደደ ነበር። እነዚህ ክርስቲያን ተብዬዎች አረማዊ በዓላትን ለማክበር ያሳዩት ፈቃደኝነት በማኅበረሰቡ ዘንድ በተወሰነ ደረጃ ተቀባይነትን አስገኘላቸው። ብዙም ሳይቆይ እንደ አረማውያን ሁሉ ክርስቲያኖችም የሚያከብሯቸው ዓመታዊ በዓላት በጣም ተበራከቱ። ከእነዚህም በዓላት ውስጥ ገና ግንባር ቀደሙን ሥፍራ መያዙ ምንም አያስደንቅም።
ዓለም አቀፋዊ በዓል
ጎልቶ ይታይ የነበረው ስመ ክርስትና በአውሮፓ ሲስፋፋ ገናን የሚያከብሩ ሰዎች ቁጥር የዚያኑ ያህል እየጨመረ መጣ። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የኢየሱስን የልደት ቀን በማሰብ አስደሳች በዓል መከበሩ መቀጠል አለበት የሚል አቋም ያዘች። በዚህ መሠረት በ567 እዘአ የቱር ምክር ቤት “ከገና እስከ ጥምቀት ያሉትን 12 ቀናት ቅዱስና የበዓል ቀናት ብሎ ሰየማቸው።”—ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ ፎር ስኩል ኤንድ ሆም
ብዙም ሳይቆይ ገና በሰሜን አውሮፓ ይከበሩ ከነበሩት ዓለማዊ የመከር በዓላት በርካታ ሥርዓቶችን ወረሰ። በዓሉን የሚያከብሩት ሰዎች ያለ ልክ የሚበሉና የሚጠጡ በመሆናቸው ከሃይማኖተኛነት ይልቅ ፈንጠዝያ የተለመደ ነገር ሆነ። ቤተ ክርስቲያን ልቅ የሆነውን ይህን ሥነ ምግባር ከማውገዝ ይልቅ ደገፈችው። (ከሮሜ 13:13ና ከ1 ጴጥሮስ 4:3 ጋር አወዳድር።) በ601 እዘአ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ግሪጎሪ አንደኛ በእንግሊዝ ሚስዮናዊ ሆኖ እንዲያገለግል ለላኩት ለሜሊተስ በጻፉት ደብዳቤ ላይ “ጥንታዊ የሆኑ አረማዊ በዓላት እንዳይከበሩ ከማድረግ ይልቅ በዓላቱ ያላቸውን አረማዊ ትርጉም ቀይሮ ክርስቲያናዊ ትርጉም እንዲኖራቸው በማድረግ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ውስጥ ይጨመሩ” በማለት ነግረውታል። ከላይ ያለውን ሪፖርት ያቀረቡት የግብጽ መንግሥት የጥንታዊ ቅርሶች ኢንስፔክተር ጄኔራል የነበሩት አርተር ዋይጎል ናቸው።
በመካከለኛው ዘመን የነበሩ የተሃድሶ ለውጥ አራማጆች እንዲህ ያለውን ከልክ ያለፈ ነገር ማውገዝ እንደሚገባ ተሰምቷቸው ነበር። “በገና በዓል የሚፈጸሙ አግባብነት የሌላቸው ነገሮችን” በመቃወም ያሳለፏቸውን በርካታ ውሳኔዎች አሰራጩ። ዶክተር ፔኒ ሬስታድ ክሪስማስ ኢን አሜሪካ—ኤ ሂስትሪ በተባለው መጽሐፋቸው እንዲህ ብለዋል:- “አንዳንድ ቀሳውስት ፍጽምና የጎደለው የሰው ዘር በክርስቲያናዊ ቁጥጥር ጥላ ሥር እስከሆነ ድረስ ተፈጥሯዊ ስሜቶቹን ያለ ገደብ የሚያረካበት ወቅት ያስፈልገዋል ሲሉ ጠበቅ አድርገው ተናግረዋል።” ይህ አስተሳሰብ የተፈጠረውን ግራ መጋባት አባብሶታል። ይሁን እንጂ ይህ እምብዛም ለውጥ አላመጣም፤ ምክንያቱም አረማዊ ልማዶች ቀድሞውኑ ከገና ጋር ጥብቅ ትስስር ስለነበራቸው ብዙ ሰዎች ሊተዉአቸው ፈቃደኞች አልሆኑም። ትሪስትረም ኮፊን የተባሉት ጸሐፊ “ብዙሃኑ ሕዝብ የሥነ ምግባር ደንቦችን መከተል አለብን የሚሉ ሰዎች ለሚያቀርቡት ክርክር እምብዛም ትኩረት ሳይሰጥ ሁልጊዜ ያደርግ የነበረውን ነገር መፈጸሙን ቀጠለ” በማለት ሁኔታውን ገልጸውታል።
አውሮፓውያኑ በሰሜንና በደቡብ አሜሪካ መስፈር በጀመሩበት ጊዜ ገና ታዋቂ የሆነ በዓል ነበር። ይሁንና የገና በዓል በቅኝ ግዛቶቹ ዘንድ ወዲያውኑ ተቀባይነት አላገኘም። የፑሪታን የተሃድሶ ለውጥ አራማጆች በዓሉ አረማዊ ነው በማለት ከ1659 እስከ 1681 ባሉት ዓመታት በማሳቹሴትስ ከተማ እንዳይከበር አግደው ነበር።
እገዳው ከተነሳ በኋላ በቅኝ ግዛቶቹ ሁሉ፣ በተለይም በደቡባዊው ኒው ኢንግላንድ ገናን የሚያከብሩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጣ። ይሁን እንጂ የበዓሉን የቀድሞ ታሪክ ስንመለከት አንዳንድ ሰዎች ይበልጥ የሚያሳስባቸው ነገር ለአምላክ ልጅ ክብር መስጠት ሳይሆን አስደሳች የሆነ ጊዜን ማሳለፍ መሆኑ ምንም አያስገርምም። ይበልጥ አዋኪ የሆነው አንዱ የገና ልማድ በእንግሊዝኛ ዋሴይሊንግ የሚባለው [የሆያ ሆዬ ዓይነት ጭፈራ] ነው። ጋጠወጥ ወጣቶች ተሰባስበው በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ሀብታም ሰው ቤት በመግባት የሚበሉትና የሚጠጡት ነገር እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ። የቤቱ ባለቤት ለመስጠት ፈቃደኛ ካልሆነ ብዙውን ጊዜ ይረግሙታል፤ አሊያም አንዳንድ ጊዜ በንብረቱ ላይ ጉዳት ያደርሱበታል።
ይህ ሁኔታ በ1820ዎቹ በጣም ከመባባሱ የተነሳ “በገና ጊዜ የሚታየው ረብሻ ለኅብረተሰቡ እጅግ የሚያሰጋ” ሆኖ ነበር ሲሉ ፕሮፌሰር ኒሴንቦም ተናግረዋል። እንደ ኒው ዮርክና ፊላደልፊያ በመሳሰሉ ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ከበርቴ ባለርስቶች ንብረታቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ዘበኞችን መቅጠር ጀመሩ። ሌላው ቀርቶ የኒው ዮርክ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ የፖሊስ ኃይል ያደራጀው በ1827/28 የገና ወቅት የተነሳውን ከፍተኛ ረብሻ ለማስቆም ታስቦ እንደሆነ ይነገራል!
የገናን በዓል በአዲስ መልክ ማደራጀት
አሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን የሰው ዘር ከዚህ በፊት አይቶት የማያውቀውን ለውጥ አመጣ። የመንገዶችና የባቡር ሃዲዶች መስፋፋት ሰዎች፣ እቃዎችና የዜና ዘገባዎች በፍጥነት እንዲጓዙ በር ከፈተ። የኢንዱስትሪው አብዮት ከፍተኛ የሥራ እድል ፈጠረ፤ እንዲሁም ፋብሪካዎች ሸቀጣ ሸቀጦችን ያለማቋረጥ በብዛት ማምረት ጀመሩ። የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ውሎ አድሮ በገና አከባበር ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩ አዲስና የተወሳሰቡ ማኅበራዊ ችግሮችንም አስከትሏል።
ሰዎች ከረዥም ጊዜ ጀምሮ የቤተሰብን ትስስር ለማጎልበት በበዓላት ይጠቀሙ ነበር። የገናንም በዓል ቢሆን በዚሁ መልኩ ተጠቅመውበታል። የበዓሉ አራማጆች ቀደም ሲል የነበሩ አንዳንድ የገና ልማዶችን በማሻሻል፣ መረን የለቀቀና ሕዝባዊ የነበረውን በዓል በመቀየር በቤተሰብ ደረጃ የሚከበር በዓል አደረጉት።
እንደ እውነቱ ከሆነ በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ ገና ዘመናዊው የአሜሪካ ሕይወት ለተጠናወተው ችግር መፍትሔ እንደሆነ ተደርጎ መታየት ጀመረ። ዶክተር ሬስታድ “ከበዓላት ሁሉ የገና በዓል ሃይማኖትና ሃይማኖታዊ ስሜት በየቤቱ እንዲሰፍን ለማድረግና በሕዝቡ ዘንድ የሚታየውን ልቅ የሆነ ሥጋዊ ፍላጎትን የማርካት ስሜትና ጉድለት ለማረም የሚያስችል ትክክለኛው መሣሪያ ነበር” ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል:- “ስጦታ መለዋወጥ፣ ምጽዋት ማድረግ፣ ሌላው ቀርቶ በበዓሉ ጊዜ የመልካም ምኞት መግለጫ መለዋወጥና የእንግዳ መቀበያ ክፍልን ወይም የሰንበት ትምህርት ቤት አዳራሽን ቅጠሉ በማይደርቅ ዛፍ በማስጌጥ መደሰት፣ እያንዳንዱን የቤተሰብ አባል እርስ በርሱ፣ ከቤተ ክርስቲያንና ከኅብረተሰቡ ጋር አስተሳስሯል።”
በተመሳሳይም ዛሬ ብዙዎች ገናን የሚያከብሩት አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር ለመግለጽና የቤተሰብ አንድነትን ጠብቆ ለማቆየት ሲሉ ነው። እርግጥ ሳይጠቀስ ሊታለፍ የማይገባው ነገር ቢኖር መንፈሳዊው ገጽታ ነው። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ገናን የሚያከብሩት የኢየሱስን ልደት ለማስታወስ ሲሉ ነው። በቤተ ክርስቲያን በሚከናወኑ ልዩ የቅዳሴ ሥነ ሥርዓቶች ላይ ይገኙ ይሆናል፤ በቤታቸው የክርስቶስን ልደት የሚያንጸባርቁ ነገሮችን ያደርጋሉ፤ ወይም ለራሱ ለኢየሱስ የምስጋና ጸሎት ያቀርባሉ። ይሁን እንጂ አምላክ ይህን ሁኔታ እንዴት አድርጎ ይመለከተዋል? እነዚህ ድርጊቶች በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት አላቸውን? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በተመለከተ ምን እንደሚል ተመልከት።
“እውነትንና ሰላምን ውደዱ”
ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ ተከታዮቹን “እግዚአብሔር መንፈስ ነው፣ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 4:24) ኢየሱስ ያደረጋቸው ነገሮች ከእነዚህ ቃላት ጋር የሚስማሙ ናቸው። ሁልጊዜ እውነትን ይናገር ነበር። “የእውነት አምላክ” የሆነውን አባቱን ፍጹም በሆነ መንገድ መስሎታል።—መዝሙር 31:5፤ ዮሐንስ 14:9
ይሖዋ ሁሉንም ዓይነት የማታለል ድርጊት እንደሚጠላ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ግልጽ አድርጓል። (መዝሙር 5:6) ከዚህ አንፃር ስናየው ከገና ጋር የተያያዙ ብዙ ነገሮች ከውሸት ጋር ቁርኝት ያላቸው አይደሉምን? ለምሳሌ ያህል ስለ ሳንታ ክሎዝ የሚነገረውን ተረት ተመልከት። በብዙ አገሮች እንደሚታመነው ሳንታ በበር ሳይሆን በጭስ ማውጫ በኩል አድርጎ ለመግባት ለምን እንደሚመርጥ ለአንድ ትንሽ ልጅ ለማስረዳት ሞክረህ ታውቃለህን? እንዲሁም ሳንታ በአንድ ምሽት ብቻ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ቤቶችን የሚጎበኘው እንዴት እንደሆነ ለማስረዳት ሞክረህ ታውቃለህ? ስለ በራሪው አጋዘንስ? አንድ ትንሽ ልጅ ሳንታ የሚባል ሰው አለ ብሎ እንዲያምን የተደረገው በውሸት መሆኑን ሲገነዘብ በወላጆቹ ላይ እምነት አያጣምን?
ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ “ገና አረማዊ ልማዶችን . . . ወርሷል” በማለት በግልጽ ይናገራል። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና ሌሎች የሕዝበ ክርስትና ቤተ ክርስቲያኖች ክርስቲያናዊ መሠረት የሌላቸው ልማዶች ያቀፈውን በዓል ማክበራቸውን የቀጠሉት ለምንድን ነው? ይህ አረማዊ ትምህርቶችን ችላ ብለው ማለፋቸውን አያመለክትምን?
ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሰዎች እሱን እንዲያመልኩት አላበረታታም። ኢየሱስ ራሱ “ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 4:10) በተመሳሳይም ኢየሱስ ሰማያዊ ክብሩን ከተጎናጸፈ በኋላም ቢሆን አንድ መልአክ ለሐዋርያው ዮሐንስ “ለእግዚአብሔር ስገድ” ብሎ በመናገር ይህ ሁኔታ አለመለወጡን አመልክቷል። (ራእይ 19:10) ይህ ደግሞ ኢየሱስ በገና በዓል ወቅት ለአባቱ ሳይሆን ለእሱ የሚቀርብለትን አምልኮታዊ ፍቅር ሁሉ ይቀበለዋልን? የሚል ጥያቄ ያስነሳል።
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ዘመናዊውን የገና በዓል በተመለከተ ያሉት እውነታዎች ጥሩነቱን የሚገልጹ አይደሉም። ገና ባመዛኙ የሰዎች ፈጠራ ሲሆን ከማስረጃዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው ደግሞ ጥንታዊ ታሪኩ ብልሹ የሆነ በዓል ነው። በመሆኑም በሚልዮን የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች በጥሩ ሕሊና ተገፋፍተው ገናን ላለማክበር ወስነዋል። ለምሳሌ ያህል ራያን የተባለ አንድ ወጣት የገናን በዓል አስመልክቶ እንዲህ ብሏል:- “የቤተሰብ አባላት አንድ ላይ የሚሰባሰቡባቸውና ሁሉም የሚደሰቱባቸውን በዓመት ውስጥ የሚውሉ ሁለት የበዓላት ቀናትን ሰዎች እንደ ልዩ ነገር አድርገው ይመለከቷቸዋል። ይሁን እንጂ ከሌላው ጊዜ ልዩ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው? ወላጆቼ ዓመቱን በሙሉ ስጦታዎችን ይሰጡኛል!” 12 ዓመት የሆናት አንዲት ሌላ ወጣት ደግሞ “የቀረብኝ ነገር እንዳለ ሆኖ አይሰማኝም። ሰዎች የግድ ስጦታ መግዛት እንደሚኖርባቸው በሚሰማቸው አንድ ልዩ ቀን ላይ ብቻ ሳይሆን ዓመቱን በሙሉ ስጦታ ይመጣልኛል” ብላለች።
ነቢዩ ዘካርያስ ‘እውነትንና ሰላምን እንዲወዱ’ መሰል እስራኤላውያንን አበረታቷቸዋል። (ዘካርያስ 8:19) ልክ እንደ ዘካርያስና በቀድሞ ዘመን ይኖሩ እንደነበሩ ሌሎች የታመኑ ሰዎች ‘እውነትን የምንወድ’ ከሆነ ‘ሕያውና እውነተኛውን አምላክ’ የማያስከብሩ የሐሰት ሃይማኖታዊ በዓላትን ልናስወግድ አይገባንምን?—1 ተሰሎንቄ 1:9
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“የቀረብኝ ነገር እንዳለ ሆኖ አይሰማኝም። ዓመቱን በሙሉ ስጦታ ይመጣልኛል”