የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 1/15 ገጽ 23-28
  • በአምላክ ቃል ላይ ያለንን እምነት ማጠንከር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በአምላክ ቃል ላይ ያለንን እምነት ማጠንከር
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአምላክ ቃል እውነት ነው —⁠የእምነታችን መሠረት ነው
  • “የእምነታችንን ፈጻሚ” ምሰሉት
  • በእምነት ኑሩ
  • ይሖዋ በገባው ቃል ላይ እምነት እንዳላችሁ በተግባር አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
  • በእርግጥ በምሥራቹ ታምናለህ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • በእውነት ላይ የተመሠረተ እምነት አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • “እምነት ጨምርልን”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 1/15 ገጽ 23-28

በአምላክ ቃል ላይ ያለንን እምነት ማጠንከር

መጽሐፍ ቅዱስን ከማንኛውም ሌላ መጽሐፍ ይበልጥ ብዙ ሰዎች አንብበውታል። ይሁን እንጂ በመልእክቱ ላይ እምነት እንዳላቸው ያሳዩት ስንቶቹ ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ‘እምነት ለሁሉም አይደለም’ በማለት ይናገራል። (2 ተሰሎንቄ 3:​2) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው እምነት አብሮን የሚወለድ ነገር አይደለም። ሊዳብር የሚገባው ነገር ነው። ሌላው ቀርቶ የተወሰነ እምነት ያላቸው ሰዎች እንኳ ባላቸው እምነት መኩራራት አይኖርባቸውም። እምነት ሊመናመንና ጨርሶ ሊሞት ይችላል። በመሆኑም “በእምነት ጤናሞች” ሆነን ለመኖር ጥረት ይጠይቃል።​—⁠ቲቶ 2:​2

ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል በ1997/98 ለሚደረጉ ተከታታይ የአውራጃ ስብሰባዎች “በአምላክ ቃል ማመን” የሚል ጭብጥ መምረጡ ምክንያታዊ ነበር። በሚልዮን የሚቆጠሩ ምሥክሮችና ሌሎች ሰዎች በአምላክ ቃል ላይ ያላቸውን እምነት ለማጎልበት አንድ ላይ የመሰብሰብ መብት አግኝተው ነበር።

የአምላክ ቃል እውነት ነው —⁠የእምነታችን መሠረት ነው

ይህ የአውራጃ ስብሰባው የመጀመሪያ ቀን ጭብጥ ነበር። ስብሰባው የጀመረው በዚያ የተገኙትን በማመስገን ነበር። በአውራጃ ስብሰባው ላይ መገኘታቸው ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት እንዳላቸው ያሳያል። ሆኖም የእምነታችንን ጥራት አስመልክቶ ሊጤኑ የሚገባቸው ጥያቄዎች ቀርበዋል:- ‘የአምላክን ቃል እንደ ባለ ሥልጣን በመጥቀስ ስለ እምነታችን ማስረዳት እንችላለን? መጽሐፍ ቅዱስን፣ የጉባኤ ስብሰባዎችን እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን አቅልለን ባለመመልከት ለመንፈሳዊ ምግብ አድናቆት እንዳለን እናሳያለን? በፍቅር፣ በትክክለኛ እውቀትና በማስተዋል እድገት እያደረግን ነው?’ ተናጋሪው “ይህ ‘በአምላክ ቃል ማመን’ የተሰኘው የአውራጃ ስብሰባ ራሳችንን በጥንቃቄ እንድንመረምርና እያንዳንዳችን በግላችን ያለንን እምነት ጥንካሬና ጥራት እንድንገመግም የተዘጋጀ መሆኑን” በመግለጽ ሁሉም በትኩረት እንዲያዳምጡ አበረታቷል።

የጭብጡ ቁልፍ ንግግር “በማየት ሳይሆን በእምነት መመላለስ” የሚል ነበር። (2 ቆሮንቶስ 5:​7) ተናጋሪው “የይሖዋ ምሥክሮች የሚሆኑ ሰዎች እምነት፣ በየዋህነት ላይ የተመሠረተ ጭፍን እምነት አይደለም” በማለት ተናግሯል። ይህ እንዴት እውነት ነው! ትክክለኛ እምነት ጭፍን አይደለም። በተጨባጭ ነገሮች ላይ የተመሠረተ ነው። ዕብራውያን 11:​1 “እምነትም ተስፋ ስለ ምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፣ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው” ይላል። ተናጋሪው “በእርግጥ በእምነት ለመመላለስ የምንፈልግ ከሆነ ጠንካራ መሠረት ያለው እምነት ሊኖረን ይገባል” ብሏል። በማየት ሳይሆን በእምነት ስለምንመላለስ ይሖዋ የዓላማውን እያንዳንዱን ዘርፍ እንዴትና መቼ እንደሚፈጽም የሚገልጽ ማብራሪያ አያስፈልገንም። አስቀድመን ስለ እሱ ያወቅናቸው ነገሮች የገባውን ቃል በፍቅርና በጽድቅ የመፈጸም ኃይል እንዳለው ፍጹም ማረጋገጫ ይሰጡናል።

“ክርስቲያን ወጣቶች​—⁠በጉባኤ ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ” የሚለው ንግግር ወጣቶች በይሖዋ ዘንድ ምን ያህል ውድ እንደሆኑ አስገንዝቧቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር እንደ ማንበብና ራስን ወደ መወሰንና ወደ ጥምቀት የሚያደርሱ ብቃቶችን እንደ ማሟላት የመሳሰሉ ግቦችን በመከታተል በመንፈሳዊ እንዲያድጉ ተበረታተዋል። ተጨማሪ ትምህርት መከታተል ከወላጆች ጋር የሚወሰን የግል ጉዳይ ነው። ይሁን እንጂ ተጨማሪ ትምህርት ለመከታተል ከተፈለገ ምንጊዜም ዓላማው አምላክን ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማገልገል እንድንችል ማስታጠቅ ሊሆን ይገባል። ከእምነታችን ጋር በተዛመደ መንገድ ‘ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ምን እንደሆነ ፈትነን’ የምንለይ ከሆነ ዓለማዊ ትምህርት ጠቃሚ ለሆነ ዓላማ ሊያገለግል ይችላል።​—⁠ፊልጵስዩስ 1:​9, 10

ቀጥሎ የቀረበው “የምትከተሉት ማን ያወጣውን መስፈርት ነው?” የሚል ጭብጥ ያለው ሦስት ንግግሮችን የያዘ ሲምፖዚየም ነበር። በአምላክ ቃል ላይ ያለን እምነት ከመጽሐፍ ቅዱስ መስፈርቶች ጋር ተጣብቀን እንድንመላለስ ይገፋፋናል። ክርስቲያኖች የይሖዋን ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች ይታዘዛሉ። ለምሳሌ ያህል ቅዱሳን ጽሑፎች ጸያፍ የሆነ የስድብ ንግግር ከአፋችን እንዳይወጣ ያስጠነቅቁናል። (ኤፌሶን 4:​31, 32) ተናጋሪው “በምትበሳጩበት ወይም በምትናደዱበት ጊዜ በሚስቶቻችሁ ወይም በልጆቻችሁ ላይ እየጮኻችሁ የስድብ ቃላት ታዥጎደጉዳላችሁ?” በማለት ጠይቋል። እንዲህ ማድረግ ክርስቲያናዊ ባሕርይ አይደለም። በተጨማሪም አምላክ በአለባበስና በሰውነት አያያዝም ረገድ የራሱ መስፈርት አለው። ክርስቲያኖች የሚለብሱት ልብስ ‘ሥርዓታማና ልከኛ’ መሆን ይኖርበታል። (1 ጢሞቴዎስ 2:​9, 10) “ልከኛ” የሚለው ቃል ለራስና ለሌሎች አክብሮት ማሳየትን፣ አሳቢ መሆንንና ጭምት የመሆንን ሐሳብ ያስተላልፋል። የሚገፋፋን ለሌሎች ያለን ፍቅር ሲሆን የምንመራው በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ትክክል ስለሆነው ነገር ባለን ግንዛቤ ነው።

ተከታዮቹ ሁለት ንግግሮች ዕብራውያን 3:​7-15ና 4:​1-16 ጥቅስ በጥቅስ የተብራሩባቸው ነበሩ። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ‘ኃጢአት ባለው የማታለል ኃይል’ እንዳንደነድን ያስጠነቅቁናል። (ዕብራውያን 3:​13) ከኃጢአት ጋር በምናደርገው ውጊያ አሸናፊ ለመሆን የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ይረዳናል። በእርግጥም “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፣ የሚሠራም፣ . . . ነው፣ . . . የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል።”​—⁠ዕብራውያን 4:​12

በአውራጃ ስብሰባው የመጀመሪያ ቀን ማብቂያ ላይ የቀረበው ንግግር “ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ” የሚል ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስን ሐቀኛነት፣ ትክክለኛነትና ተግባራዊ ጠቀሜታ የሚያጎላ ነበር። ተናጋሪው ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ! የተባለ አዲስ ባለ 32 ገጽ ብሮሹር መውጣቱን ሲያስታውቅ መስማት እንዴት የሚያስፈነድቅ ነበር። ይህ አዲስ ጽሑፍ በተለይ የተዘጋጀው የተማሩ ቢሆኑም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በቂ እውቀት የሌላቸውን ሰዎች ለመርዳት ታስቦ ነው። ንግግሩ ያበቃው በሚከተሉት ቃላት ነው:- “ሰዎች የአምላክን ቃል በግላቸው መመርመር ያስፈልጋቸዋል። ሌሎች የሚሉትን ከመስማት አልፈው ራሳቸው ቢመረምሩት ይህ በዓይነቱ ብቸኛ የሆነ መጽሐፍ ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ መሆኑን እንደሚገነዘቡ እርግጠኞች ነን!”

“የእምነታችንን ፈጻሚ” ምሰሉት

ይህ የአውራጃ ስብሰባው ሁለተኛ ቀን ጭብጥ “የእምነታችን ፈጻሚ” በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያተኮረ ነበር። ‘ፍለጋውን በቅርብ መከተል’ አለብን። (ዕብራውያን 12:​2፤ 1 ጴጥሮስ 2:​21 NW) በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉ ብዙዎች ‘በጌታ በኢየሱስ እመኑ ትድናላችሁ!’ ተብሎ ይነገራቸዋል። ይሁን እንጂ እምነት ማለት ይኸው ብቻ ነውን? መጽሐፍ ቅዱስ “ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው” ይላል። (ያዕቆብ 2:​26) ስለዚህ በኢየሱስ ከማመን ጋር ጎን ለጎን እሱ ያደርጋቸው የነበሩ ሥራዎችን መፈጸም ይገባናል። በተለይ ይህ የአምላክ መንግሥት ምሥራችን መስበክን ይጨምራል።

የጠዋቱ ፕሮግራም በአብዛኛው ያተኮረው በወንጌላዊነቱ ሥራ ላይ ነበር። ልክ እንደ ጳውሎስ የመዳንን ምሥራች ለማወጅ ቅንዓት ሊኖረን ይገባል። (ሮሜ 1:​14-16) ኢየሱስ ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ሰብኳል። ከቤት ወደ ቤት የምናደርገው ቋሚ አገልግሎት ፍሬ እያስገኘ ቢሆንም ብዙ ሰዎችን በቤታቸው አናገኛቸውም። (ሥራ 20:​20) ብዙዎች ትምህርት ቤት፣ ሥራ ወይም ገበያ ሄደዋል፤ ወይም በጉዞ ላይ ናቸው። ስለዚህ በሕዝብ ማዘውተሪያ ስፍራዎችና ሰዎች በሚገኙባቸው ቦታዎች ሁሉ መስበክ አለብን።

“በእውነት ውስጥ ሥር ሰዳችሁና ጸንታችሁ ቁሙ” የሚለው ንግግር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አዳዲስ ደቀ መዛሙርት እየተጠመቁ መሆኑን አስታውሶናል። በቀን በአማካይ ከ1,000 ሰዎች በላይ ይጠመቃሉ! እነዚህ አዳዲስ ሰዎች በእምነት ሥር የሰደዱና የጸኑ መሆናቸው የግድ አስፈላጊ ነው። (ቆላስይስ 2:​6, 7) ተናጋሪው የአንድ ተክል ሥሮች ውኃና ምግብ ለመምጠጥና ተክሉን ቀጥ አድርጎ ለመያዝ ወይም ደግፎ ለማቆም እንደሚያገለግሉ ገልጿል። በተመሳሳይም አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ጥሩ የጥናት ልማድ በማዳበርና የሚያንጽ ቅርርብ በመፍጠር በእውነት ውስጥ ጸንተው ሊቆሙ ይችላሉ።

ይህ ምክር በተለይ ለእጩ ተጠማቂዎች ተገቢ ነበር። አዎን፣ በአውራጃ ስብሰባው ሁለተኛ ቀን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አዳዲስ ደቀ መዛሙርት የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ተጠምቀዋል። “በአምላክ ቃል ማመን ወደ ጥምቀት ይመራል” የሚለው ንግግር ውኃው ውስጥ ሙሉ በሙሉ መጥለቅ ቀደም ሲል በራስ ወዳድነት ይመላለሱበት ለነበረው አኗኗር መሞታቸውን የሚያሳይ ትክክለኛ መግለጫ መሆኑን ለእጩ ተጠማቂዎቹ አሳስቧል። ከውኃው ውስጥ መውጣታቸው ደግሞ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ሕያው መሆናቸውን ያመለክታል።

“ለእምነት በብርቱ ተጋደሉ” የሚለው ንግግር የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በይሁዳ መጽሐፍ ላይ የተመሠረተ ነበር። እንደ ሥነ ምግባር ብልግና፣ በሥልጣን ላይ ማመፅና ክህደት የመሳሰሉትን ጎጂ ተጽእኖዎች በመቋቋም እምነታችንን እንድንከላከል ተበረታተናል። ቀጥሎ “ቤተሰባችሁ የሚያስፈልጉትን ነገሮች አቅርቡ” በሚለው ንግግር ላይ ወላጆች በተለይም አባቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው ነበር። ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን መንፈሳዊ፣ ሥጋዊና ስሜታዊ ፍላጎቶች ማሟላት ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 5:​8) ይህም ጊዜን፣ ሐሳብ ለሐሳብ መግባባትንና መቀራረብን ይጠይቃል። ይሖዋ አምላክ ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን በእውነት ውስጥ ለማሳደግ በሚያከናውኑት ትጋት የተሞላበት ሥራ እንደሚደሰት የተረጋገጠ ነው።

“ወደ ይሖዋ ቤት እንሂድ” የሚለው ተከታዩ ሲምፖዚየም ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ያለንን አድናቆት የገነባ ነበር። ከዚህ ዓለም ጭንቀቶች እፎይታ የምናገኝባቸው ቦታዎች ናቸው። በስብሰባዎች ላይ እርስ በርስ ለመበረታታት አጋጣሚውን ከማግኘታችንም በላይ ለመሰል አማኞች ያለንን ፍቅር ለመግለጽ እንችላለን። (ዕብራውያን 10:​24, 25) በተጨማሪም ስብሰባዎች የማስተማር ችሎታችንን እንድንስልና ስለ አምላክ ዓላማ ያለን ማስተዋል ጥልቀት እንዲኖረው ይረዱናል። (ምሳሌ 27:​17) ራሳችንን ከጉባኤው ማግለል ፈጽሞ አይኖርብንም። “ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት እናስታውስ።​—⁠ማቴዎስ 18:​20

የዕለቱ የመጨረሻ ንግግር “የእምነታችሁ ጥንካሬ​—⁠ዛሬ ይፈተናል” የሚል ነበር። ያልተፈተነ እምነት ምንም ዓይነት የተረጋገጠ ፋይዳ አይኖረውም፤ ጥንካሬውም አይታወቅም። ገና እንዳልተመነዘረ የገንዘብ ቼክ ነው። በላዩ ላይ የሠፈረውን ገንዘብ ማስገኘቱ የተረጋገጠ ነውን? በተመሳሳይም እምነታችን ጥሩ መሠረትና ጥንካሬ ያለው መሆኑ እንዲረጋገጥ ከፈለግን መፈተን ይኖርበታል። (1 ጴጥሮስ 1:​6, 7) ተናጋሪው እንዲህ ብሏል:- “አንዳንድ ጊዜ መገናኛ ብዙሐንና ባለ ሥልጣኖች በቀሳውስትና በከሃዲዎች ተገፋፍተው ክርስቲያናዊ እምነታችንንና አኗኗራችንን በተሳሳተ መንገድ በመተርጎም በሐሰት ይወነጅሉናል። . . . ሰይጣን ያሳወራቸው ሰዎች እንዲያስፈራሩንና ወኔያችንን እንዲሰልቡ በመፍቀድ በምሥራቹ እናፍራለን? ስለ እውነት በሚነገሩ ውሸቶች ምክንያት አዘውትረን ከመሰብሰብና በስብከት ሥራ ከመሳተፍ ወደኋላ እንላለን? ወይስ ጸንተን በመቆምና ደፋሮች በመሆን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ስለ ይሖዋና ስለ መንግሥቱ የሚገልጸውን እውነት ለማወጅ ቆርጠን እንነሳለን?”

በእምነት ኑሩ

የአውራጃ ስብሰባው ሦስተኛ ቀን ጭብጥ “ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎአልና ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንዳይጸድቅ ግልጥ ነው” በሚሉት የጳውሎስ ቃላት ላይ የተመሠረተ ነበር። (ገላትያ 3:​11) “ኢዩኤል ስለ ዘመናችን የተናገራቸው ትንቢታዊ ቃላት” የሚለው ሲምፖዚየም በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ከቀረቡት ዋና ዋና ንግግሮች አንዱ ነበር። የኢዩኤል መጽሐፍ ጊዜያችንን በማመልከት “የእግዚአብሔር ቀን ቀርቧልና ለቀኑ ወዮ! እርሱም ሁሉን ከሚችል ከአምላክ ዘንድ እንደ ጥፋት ይመጣል” በማለት በጥድፊያ ስሜት ተናግሯል። (ኢዩኤል 1:​15) ከምሕረት የለሾቹ አንበጦች ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ቅቡዓን ክርስቲያኖቹም በዚህ የመጨረሻ ቀን ላይ መንግሥቱን ከማወጅ ምንም ነገር እንዲያግዳቸው አልፈቀዱም።

በተጨማሪም የኢዩኤል መጽሐፍ “የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” የሚል ተስፋ ይሰጣል። (ኢዩኤል 2:​32) ይህ የይሖዋን ስም ከመጠቀም የበለጠ ነገርን ይጨምራል። ከልብ ንስሐ መግባት ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ ለመጥፎ ድርጊት ጀርባችንን መስጠትን ይጨምራል። (ኢዩኤል 2:​12, 13) ይሖዋ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮሳፍጥ ዘመን በሞዓብ፣ በአሞንና በሴይር ተራራ ላይ እንዳደረገው ሁሉ በቅርቡ በብሔራት ላይ የፍርድ እርምጃ ስለሚወስድ አሁን ወደኋላ የምንልበት ጊዜ አይደለም።​—⁠2 ዜና መዋዕል 20:​1-30፤ ኢዩኤል 3:​2, 12

“ይሖዋን በትዕግሥት በመጠባበቅ እምነት አሳዩ” በሚለው ንግግር ሁሉም ሰው ተበረታቷል። ወደ ፍጻሜው ዘመን ጠልቀን በገባንበት በአሁኑ ጊዜ ከዚህ በፊት ይሖዋ በገባው ቃል መሠረት የተፈጸሙትን ብዙ ተስፋዎች ወደ ኋላ መለስ ብለን ለመመልከት እንችላለን፤ እንዲሁም ገና ወደፊት የሚፈጸሙትን ሌሎች ነገሮችም በትዕግሥት እንጠባበቃለን። የይሖዋ ሕዝቦች አምላክ ቃል የገባላቸው ነገሮች በሙሉ እንደሚፈጸሙ በማስታወስ በትዕግሥት መቀጠል አለባቸው።​—⁠ቲቶ 2:​13፤ 2 ጴጥሮስ 3:​9, 10

የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ የተደመደመው “ዓይናችሁ ቀና ይሁን” በሚለው ድራማ ነበር። ይህ እውነታውን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ድራማ ስለ ቁሳዊ ነገሮች ያለንን አመለካከት እንድንመረምር አበረታቶናል። የትም እንኑር የት ሕይወታችን ከጭንቀት ነፃ እንዲሆን ከፈለግን ኢየሱስ ዓይናችን ቀና እንዲሆን የሰጠውን ምክር በመከተል በአምላክ መንግሥት ላይ ማተኮር አለብን።​—⁠ማቴዎስ 6:​22

የሕዝብ ንግግሩ “እምነትና የወደፊት ዕጣችሁ” የሚል ትኩረት የሚስብ ርዕስ ነበረው። ንግግሩ ሰብዓዊ ገዥዎች የዓለምን ችግሮች ለመፍታት ችሎታ እንደሌላቸው የሚያሳይ ማስረጃ አቅርቧል። (ኤርምያስ 10:​23) የሰው ልጅ ታሪክ በመጠኑም ሆነ በአውዳሚነቱ አቻ በሌለው ሁኔታ ራሱን አየደገመ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን ይሰማቸዋል? የታመኑ ሆነው የተገኙ የሰው ልጆች በአምላክ መንግሥት ሥር ብሩህ የሆነ የወደፊት ተስፋ እንደሚኖራቸው እናምናለን። (ማቴዎስ 5:​5) “እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፣ ቀርቦም ሳለ ጥሩት” በማለት በሚመክረው ቃሉ ላይ እምነት ለሚያሳድሩ ሰዎች ጥቅም ሲል አምላክ የገባውን ቃል ይፈጽማል።​—⁠ኢሳይያስ 55:​6

ኢየሱስ የእኛን ዘመን በአእምሮው በመያዝ አንድ ዐቢይ ጥያቄ አንስቶ ነበር። “የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?” በማለት ጠይቋል። (ሉቃስ 18:​8) የመደምደሚያው ንግግር የአውራጃ ስብሰባውን ፕሮግራም በመከለስ የምንኖረው እምነት በጠፋበትና ሥጋዊ አስተሳሰብ በተጠናወተው ዓለም ውስጥ ቢሆንም ዛሬም በአምላክ ቃል ላይ እምነት እንዳለ ጠንካራ ማረጋገጫ ያገኘንበት ስብሰባ እንደነበር ገልጿል።

አሁንም ቢሆን ‘በአምላክና በቃሉ ላይ የማይናወጥ እምነት ካላቸው ሰዎች መካከል ነኝን?’ በማለት በግለሰብ ደረጃ ራሳችንን ልንጠይቅ እንችላለን። “በአምላክ ቃል ማመን” የተሰኘው የአውራጃ ስብሰባ ለዚህ ጥያቄ አዎን የሚል ምላሽ እንድንሰጥ ረድቶን መሆን ይኖርበታል። ይሖዋ በእሱና በመንፈሱ ባስጻፈው በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለንን እምነት ስላጠነከረልን እጅግ እናመሰግነዋለን!

[በገጽ 24 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በሺህ የሚቆጠሩ እንግዶችን በማስተናገዱ ሥራ በርካታ ፈቃደኛ ሠራተኞች በደስታ ተካፍለዋል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ኤል ኤ ስዊንግል አዲሱ ብሮሹር መውጣቱን ሲያስታውቅ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዓለም ዙሪያ እንደዚህ የመሳሰሉ ታላላቅ ስታዲዮሞች ለስብሰባው አገልግለዋል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙዎች ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን በጥምቀት አሳይተዋል

[በገጽ 27 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የስብሰባው ተካፋዮች የመንግሥቱን መዝሙሮች በደስታ ዘምረዋል። ከውስጥ ያለው ሥዕል:- “ዓይናችሁ ቀና ይሁን” የሚለው ድራማ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ