በአዲሱ ቃል ኪዳን በኩል የሚገኙ የላቁ በረከቶች
‘ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን መካከለኛ ሆኗል።’ —ዕብራውያን 8:6
1. በኤደን ተስፋ የተሰጠበት ‘የሴቲቱ ዘር’ ማን ሆኖ ተገኘ? ‘ሰኮናው የተቀጠቀጠውስ’ እንዴት ነው?
አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ በኋላ ይሖዋ፣ ሔዋንን ባሳሳታት በሰይጣን ላይ እንዲህ በማለት ብያኔውን አሳልፏል:- “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ።” (ዘፍጥረት 3:15) ኢየሱስ በ29 እዘአ በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀ ጊዜ በኤደን ቃል የተገባለት ዘር በመጨረሻ ተገለጠ። በ33 እዘአ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሲሞት ይህ ጥንታዊ ትንቢት በከፊል ፍጻሜውን አገኘ። ሰይጣን የዘሩን ‘ሰኮና ቀጠቀጠ።’
2. ኢየሱስ ራሱ እንደተናገረው የእርሱ ሞት የሰውን ዘር የሚጠቅመው እንዴት ነው?
2 የደረሰበት ጉዳት ከባድ ስቃይ የሚያስከትል ቢሆንም ዘላቂ አለመሆኑ ደስ ይላል። ኢየሱስ የማይጠፋ መንፈሳዊ አካል በመልበስ ከሞት ተነሥቶ ወደ ሰማያዊ አባቱ በመሄድ “ለብዙዎች ቤዛ” እንዲሆን የፈሰሰውን የደሙን ዋጋ አቅርቧል። በዚህ መንገድ ራሱ የተናገራቸው የሚከተሉት ቃላት በትክክል ተፈጽመዋል:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው . . . የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል። በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 3:14-16፤ ዕብራውያን 9:12-14) አዲሱ ቃል ኪዳን በኢየሱስ ትንቢት ፍጻሜ ውስጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።
አዲሱ ቃል ኪዳን
3. አዲሱ ቃል ኪዳን ሥራውን የጀመረው መቼ ነው?
3 ኢየሱስ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ የፈሰሰው ደሙ ‘የአዲስ ኪዳን ደም’ እንደሆነ ለተከታዮቹ ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 26:28፤ ሉቃስ 22:20) ወደ ሰማይ ካረገ ከአሥር ቀናት በኋላ 120 ደቀ መዛሙርቱ በኢየሩሳሌም በሚገኝ አንድ ሰገነት ላይ ተሰብስበው ሳሉ መንፈስ ቅዱስ መፍሰሱ አዲሱ ቃል ኪዳን ሥራውን እንደጀመረ የሚያሳይ ነበር። (ሥራ 1:15፤ 2:1-4) እነዚህ 120 ደቀ መዛሙርት ወደ አዲሱ ቃል ኪዳን መግባታቸው “ፊተኛው” ማለትም የሕጉ ቃል መሻሩን ያመለክታል።—ዕብራውያን 8:13
4. አሮጌው ቃል ኪዳን ጉድለት ነበረበት ማለት ነውን? አብራራ።
4 አሮጌው ቃል ኪዳን ጉድለት ነበረበት ማለት ነውን? በፍጹም። እርግጥ ነው፣ ይህ ቃል ኪዳን በሌላ ስለተተካ ሥጋዊ እስራኤላውያን የአምላክ ልዩ ሕዝቦች የመሆናቸው ጉዳይ አክትሞለታል። (ማቴዎስ 23:28) ይሁን እንጂ ይህ የሆነው እስራኤላውያን ባለመታዘዛቸውና የይሖዋን ቅቡዕ ለመቀበል አሻፈረኝ በማለታቸው ነው። (ዘጸአት 19:5፤ ሥራ 2:22, 23) ነገር ግን ሕጉ ከመተካቱ በፊት ብዙ ነገሮችን አከናውኗል። ለብዙ መቶ ዘመናት ወደ አምላክ ለመቅረብና ከሐሰት ሃይማኖት ጥበቃ ለማግኘት የሚያስችል መንገድ ሆኖ አገልግሏል። የአዲሱን ቃል ኪዳን ገጽታዎች ከወዲሁ ያመላከተ ከመሆኑም ሌላ በተደጋጋሚ ጊዜ መሥዋዕት ማቅረብን የሚጠይቅ መሆኑ የሰው ልጅ የግድ ከኃጢአትና ከሞት የሚቤዠው እንደሚያስፈልገው የሚያሳይ ነበር። በእርግጥም ሕጉ ‘ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ ሞግዚት ነበር።’ (ገላትያ 3:19, 24፤ ሮሜ 3:20፤ 4:15፤ 5:12፤ ዕብራውያን 10:1, 2) ይሁን እንጂ ለአብርሃም ቃል የተገባለት በረከት ሙሉ በሙሉ እውን የሚሆነው በአዲሱ ቃል ኪዳን አማካኝነት ነው።
አሕዛብ በአብርሃም ዘር በኩል ተባርከዋል
5, 6. በአብርሃም ቃል ኪዳን ዋነኛው መንፈሳዊ ፍጻሜ መሠረት የአብርሃም ዘር ማን ነው? በእርሱ አማካኝነትስ በረከት ለማግኘት የመጀመሪያ የሆነው ብሔር የትኛው ነው?
5 ይሖዋ ለአብርሃም “የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ [“ራሳቸውን ይባርካሉ፣” NW]” ሲል ቃል ገብቶለታል። (ዘፍጥረት 22:18) በአሮጌው ቃል ኪዳን ሥር ገር ልብ የነበራቸው ብዙ መጻተኞች በብሔር ደረጃ የአብርሃም ዘር ከነበሩት እስራኤላውያን ጋር በነበራቸው ቅርርብ ተባርከዋል። ይሁን እንጂ በተስፋው ዋነኛ መንፈሳዊ ፍጻሜ መሠረት የአብርሃም ዘር አንድ ፍጹም ሰው ነው። ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ይህን ጉዳይ ገልጾታል:- “ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ። ስለ ብዙዎች እንደሚነገር:- ለዘሮቹም አይልም፤ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን:- ለዘርህም ይላል፣ እርሱም ክርስቶስ።”—ገላትያ 3:16
6 አዎን፣ ኢየሱስ የአብርሃም ዘር ነው። በእርሱ አማካኝነትም አሕዛብ ከሥጋዊ እስራኤላውያን ሊያገኙት ከሚችሉት እጅግ የላቀ በረከት ያገኛሉ። ይህን በረከት ለማግኘት የመጀመሪያ አጋጣሚ የተከፈተለት የእስራኤል ብሔር እንደነበረ ግልጽ ነው። በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት በኋላ ብዙም ሳይቆይ ጴጥሮስ አንድ ላይ ለተሰባሰቡ አይሁዳውያን እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “እናንተ የነቢያት ወራሾች ናችሁ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር ለአብርሃም ‘በምድር ላይ ያሉ ሕዝቦች ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ’ ብሎ ከአባቶቻችን ጋር የገባው ቃል ኪዳን ወራሾች ናችሁ። ስለዚህ እግዚአብሔር ልጁን የላከው በመጀመሪያ ለእናንተ ነበር፤ ይህንንም ያደረገው እያንዳንዳችሁን ከክፉ መንገዳችሁ በመመለስ እንዲባርካችሁ ነው።”—ሥራ 3:25, 26 የ1980 ትርጉም
7. የአብርሃም ዘር በሆነው በኢየሱስ አማካኝነት የተባረኩት አሕዛብ የትኞቹ ናቸው?
7 ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በረከቱ ለሳምራውያን ቀጥሎም ለአሕዛብ ተዘረጋ። (ሥራ 8:14-17፤ 10:34-48) ከ50 እስከ 52 እዘአ ገደማ ባለው ጊዜ መሐል ጳውሎስ በትንሿ እስያ ለነበሩት የገላትያ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፎላቸዋል:- “መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ:- በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ። እንደዚህ ከእምነት የሆኑት ካመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ።” (ገላትያ 3:8, 9፤ ዘፍጥረት 12:3) በገላትያ የነበሩት ብዙዎቹ ክርስቲያኖች ‘ከአሕዛብ ወገን’ ቢሆኑም በእምነታቸው ምክንያት በክርስቶስ አማካኝነት ተባርከዋል። በምን መንገድ?
8. በጳውሎስ ዘመን ለነበሩት ክርስቲያኖች በአብርሃም ዘር አማካኝነት መባረክ ምን ነገር የሚያስገኝ ነበር? የዚህ በረከት ተቋዳሽ የሚሆኑት ጠቅላላ ቁጥርስ ስንት ነው?
8 ጳውሎስ ትውልዳቸው ምንም ይሁን ምን በገላትያ ለነበሩት ክርስቲያኖች በጠቅላላ ሲናገር “የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ” ብሏል። (ገላትያ 3:29) ለእነዚያ የገላትያ ሰዎች በአብርሃም ዘር በኩል የሚገኘው በረከት የአዲሱ ቃል ኪዳን ተካፋዮችና ከኢየሱስ ጋር ተባባሪ ገዥዎች በመሆን ከኢየሱስ ጋር የአብርሃም ዘር ክፍል የመሆንን መብት የሚያስገኝላቸው ነበር። የጥንቱ የእስራኤል ብሔር ምን ያህል የሕዝብ ብዛት እንደነበረው አናውቅም። የምናውቀው ነገር ቢኖር “እንደ ባሕር አሸዋ ብዛት ብዙ” እንደነበሩ ብቻ ነው። (1 ነገሥት 4:20) ከኢየሱስ ጋር ተባባሪ መንፈሳዊ ዘር የሚሆኑት ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር ግን ስንት እንደሆነ እናውቃለን፤ 144,000 ነው። (ራእይ 7:4፤ 14:1) እነዚህ 144,000 ሰዎች ከሰው ዘር ‘ነገድ፣ ቋንቋ፣ ወገን፣ ሕዝብ ሁሉ’ የተውጣጡ ሲሆኑ እነርሱም በተራቸው ከአብርሃም ቃል ኪዳን የሚገኙትን በረከቶች ለሌሎች በማዳረሱ ሥራ ይካፈላሉ።—ራእይ 5:9
ፍጻሜውን ያገኘ አንድ ትንቢት
9. በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የታቀፉት ሰዎች የይሖዋ ሕግ በውስጣቸው ተጽፏል ለማለት የምንችለው ለምንድን ነው?
9 ኤርምያስ ስለ አዲሱ ቃል ኪዳን ትንቢት ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፣ ይላል እግዚአብሔር፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፣ በልባቸውም እጽፈዋለሁ።” (ኤርምያስ 31:33) ይሖዋን በፍቅር ተገፋፍቶ ማገልገል በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የታቀፉት ሰዎች ባሕርይ ነው። (ዮሐንስ 13:35፤ ዕብራውያን 1:9) የይሖዋ ሕግ የተጻፈው በልባቸው ውስጥ ሲሆን ፈቃዱን ለማድረግ ልባዊ ምኞት አላቸው። በጥንቷ እስራኤል ውስጥም የይሖዋን ሕግ በጣም የሚወዱ አንዳንድ የታመኑ ግለሰቦች እንደነበሩ አይካድም። (መዝሙር 119:97) ነገር ግን ብዙዎቹ እንዲህ ዓይነት ፍቅር አልነበራቸውም። ሆኖም የብሔሩ ክፍል ሆነው ቀጥለዋል። በአዲሱ ቃል ኪዳን ግን የአምላክ ሕግ በልቡ ካልተጻፈለት በቀር ማንም ቢሆን በቃል ኪዳኑ ሥር ሊቆይ አይችልም።
10, 11. በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ለታቀፉት ሰዎች ይሖዋ ‘አምላካቸው የሚሆነው’ በምን መንገድ ነው? ሁሉም የሚያውቁትስ እንዴት ነው?
10 ይሖዋ በአዲሱ ቃል ኪዳን ሥር ስለሚኖሩት ሰዎች ጨምሮ ሲናገር “እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል” ብሏል። (ኤርምያስ 31:33) በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ብዙዎች የአሕዛብን አማልክት እያመለኩ እስራኤላውያን ሆነው ይቀጥሉ ነበር። ይሖዋ በአዲሱ ቃል ኪዳን መሠረት ሥጋዊ እስራኤላውያንን ለመተካት አንድ መንፈሳዊ ብሔር ማለትም ‘የአምላክን እስራኤል’ አዘጋጅቷል። (ገላትያ 6:16፤ ማቴዎስ 21:43፤ ሮሜ 9:6-8) ይሁን እንጂ ማንኛውም ሰው ይሖዋን ብቻ ማምለኩን ካቆመ የዚህ አዲስ መንፈሳዊ ብሔር ክፍል ሆኖ ሊቀጥል አይችልም።
11 በተጨማሪም ይሖዋ “ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ያውቁኛል” ብሏል። (ኤርምያስ 31:34) በእስራኤል ውስጥ የነበሩ ብዙዎች “እግዚአብሔር መልካምን አያደርግም፣ ክፉም አያደርግም” ብለው ችላ ያሉት ያክል ነበር። (ሶፎንያስ 1:12) ይሖዋን ችላ የሚል ወይም ደግሞ ንጹሕ አምልኮውን የሚበርዝ ማንኛውም ሰው የአምላክ እስራኤል ክፍል ሆኖ አይቀጥልም። (ማቴዎስ 6:24፤ ቆላስይስ 3:5) መንፈሳዊ እስራኤላውያን “አምላካቸውን የሚያውቁ ሕዝብ” ናቸው። (ዳንኤል 11:32) ‘ብቻውን እውነተኛ ስለሆነው አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ትክክለኛ እውቀት’ በማግኘታቸው ይደሰታሉ። (ዮሐንስ 17:3) ከዚያ በፊት ሆኖ በማያውቅ መንገድ ስለ ‘አምላክ የተረከው’ ኢየሱስ ስለሆነ ስለ እርሱ ማወቅ ስለ አምላክ ያላቸው እውቀት እንዲያድግ ይረዳቸዋል።—ዮሐንስ 1:18፤ 14:9-11
12, 13. (ሀ) ይሖዋ በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የታቀፉትን ሰዎች ኃጢአት ይቅር የሚለው ምንን መሠረት በማድረግ ነው? (ለ) የኃጢአት ይቅርታን በተመለከተ አዲሱ ቃል ኪዳን ከአሮጌው ቃል ኪዳን የሚበልጠው በምን መንገድ ነው?
12 በመጨረሻም ይሖዋ እንዲህ ሲል ቃል ገብቷል:- “በደላቸውን እምራቸዋለሁና፣ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና።” (ኤርምያስ 31:34) የሙሴ ሕግ በመቶ የሚቆጠሩ በጽሑፍ የሰፈሩ መመሪያዎችን የያዘ ሲሆን እስራኤላውያን እነዚህን መመሪያዎች እንዲታዘዙ ተነግሯቸው ነበር። (ዘዳግም 28:1, 2, 15) ሕጉን የሚተላለፉ ሁሉ ኃጢአታቸውን ለመሸፈን መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር። (ዘሌዋውያን 4:1-7፤ 16:1-31) ብዙ አይሁዳውያን በሕጉ መሠረት በገዛ ሥራቸው ሊጸድቁ እንደሚችሉ ያምኑ ነበር። ይሁንና ክርስቲያኖች በራሳቸው ሥራ ፈጽሞ ጻድቅ ሆነው ሊቆጠሩ እንደማይችሉ ይገነዘባሉ። ከኃጢአት ሙሉ በሙሉ ነጻ ሊሆኑ አይችሉም። (ሮሜ 5:12) በአዲሱ ቃል ኪዳን ሥር በአምላክ ፊት የጽድቅ አቋም ማግኘት የሚቻለው በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት ብቻ ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው አቋም ስጦታ ማለትም ይገባናል የማንለው የአምላክ ፍቅራዊ ደግነት ነው። (ሮሜ 3:20, 23, 24) ይህም ቢሆን ይሖዋ አገልጋዮቹ ታዛዥ እንዲሆኑ ይፈልግባቸዋል። ጳውሎስ በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የታቀፉት ሰዎች “በክርስቶስ ሕግ በታች” እንዳሉ ተናግሯል።—1 ቆሮንቶስ 9:21
13 ለክርስቲያኖችም ቢሆን የኃጢአት መሥዋዕት ይቀርባል፤ ይሁን እንጂ ይህ መሥዋዕት በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር ይቀርቡ ከነበሩት መሥዋዕቶች እጅግ የላቀ ዋጋ ያለው ነው። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “[በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር ያሉት] ሊቀ ካህናትም ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሞአል፤ እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ።” (ዕብራውያን 10:11, 12) በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የታቀፉት ክርስቲያኖች በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ እምነት ስላላቸው ይሖዋ እንደ ጻድቅ ማለትም ኃጢአት እንደሌለባቸው አድርጎ በመቁጠር መንፈሳዊ ልጆቹ ሆነው ለመቀባት የሚያስችል አቋም እንዳላቸው አድርጎ ይቀበላቸዋል። (ሮሜ 5:1፤ 8:33, 34፤ ዕብራውያን 10:14-18) በሰብዓዊ አለፍጽምና ምክንያት ኃጢአት ሲፈጽሙ የይሖዋን ይቅርታ መጠየቅ ይችላሉ፤ ይሖዋም በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ ያላቸውን እምነት መሠረት በማድረግ ይቅር ይላቸዋል። (1 ዮሐንስ 2:1, 2) ይሁን እንጂ ሆነ ብለው የኃጢአትን ጎዳና ለመከተል ቢመርጡ የጽድቅ አቋማቸውንና የአዲሱ ቃል ኪዳን ተካፋዮች የመሆን መብታቸውን ያጣሉ።—ዕብራውያን 2:2, 3፤ 6:4-8፤ 10:26-31
አሮጌውና አዲሱ ቃል ኪዳን
14. የሕጉ ቃል ኪዳን ምን ዓይነት ግርዘት እንዲከናወን ይጠይቅ ነበር? አዲሱ ቃል ኪዳንስ?
14 በአሮጌው ቃል ኪዳን ሥር የነበሩት ወንዶች በሕጉ ሥር መሆናቸውን ለማሳየት ይገረዙ ነበር። (ዘሌዋውያን 12:2, 3፤ ገላትያ 5:3) የክርስቲያን ጉባኤ ሥራውን ከጀመረ በኋላም አንዳንዶች አይሁዳዊ ያልሆኑ ክርስቲያኖች ሊገረዙ ይገባቸዋል የሚል አቋም ይዘው ነበር። ይሁን እንጂ ሐዋርያትና በኢየሩሳሌም የነበሩት ሽማግሌዎች በአምላክ ቃልና በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ይህ ነገር አስፈላጊ እንዳልሆነ ተገነዘቡ። (ሥራ 15:1, 5, 28, 29) ከጥቂት ዓመታት በኋላ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በግልጥ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ አይደለምና፣ በግልጥ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና፤ ዳሩ ግን በስውር አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው፣ መገረዝም በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በመጽሐፍ አይደለም።” (ሮሜ 2:28, 29) በሥጋ አይሁዳዊ ለሆኑት እንኳ ሳይቀር በሥጋ የሚደረግ መገረዝ ከዚያ በኋላ በይሖዋ ፊት ምንም ዓይነት መንፈሳዊ ጠቀሜታ አልነበረውም። በአዲሱ ቃል ኪዳን ሥር የነበሩት ሰዎች የሚያስፈልጋቸው የልብ መገረዝ እንጂ የሥጋ መገረዝ አልነበረም። ይሖዋን የሚያሳዝን ወይም በፊቱ ንጹሕ ያልሆነው አስተሳሰባቸው፣ ምኞታቸውና ዝንባሌያቸው ሁሉ ሊወገድ ይገባው ነበር።a ዛሬ መንፈስ ቅዱስ በዚህ መንገድ የሰዎችን አስተሳሰብ የመለወጥ ኃይል እንዳለው የሚያሳዩ ብዙ ሕያው ምሥክሮች አሉ።—1 ቆሮንቶስ 6:9-11፤ ገላትያ 5:22-24፤ ኤፌሶን 4:22-24
15. ንጉሣዊ አገዛዝን በተመለከተ ሥጋዊ እስራኤልንና የአምላክ እስራኤልን ማነጻጸር የሚቻለው እንዴት ነው?
15 በሕጉ ቃል ኪዳን ዝግጅት ውስጥ የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ይሖዋ ሲሆን ከጊዜ በኋላም በኢየሩሳሌም ለሚቀመጡ ሰብዓዊ ነገሥታት ሥልጣኑን በውክልና በመስጠት አስተዳድሯል። (ኢሳይያስ 33:22) ይሖዋ የአምላክ እስራኤል ማለትም የመንፈሳዊ እስራኤላውያንም ንጉሥ ነው፤ ከ33 እዘአ አንስቶ ደግሞ ‘በሰማይና በምድር ሁሉ ሥልጣንን ባገኘው’ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት እየገዛ ነው። (ማቴዎስ 28:18፤ ኤፌሶን 1:19-23፤ ቆላስይስ 1:13, 14) ዛሬ የአምላክ እስራኤል ኢየሱስ በ1914 የተቋቋመው የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ እንደሆነ ይቀበላሉ። ኢየሱስ እንደ ሕዝቅያስና ኢዮስያስ ካሉትና ከሌሎቹም የጥንቷ እስራኤል የታመኑ ነገሥታት እጅግ የላቀ ንጉሥ ነው።—ዕብራውያን 1:8, 9፤ ራእይ 11:15
16. የአምላክ እስራኤል ክህነት ምን ዓይነት ነው?
16 የእስራኤል ብሔር መንግሥት ከመሆኑም በተጨማሪ ቅቡዕ ካህናት ነበሩት። በ33 እዘአ የአምላክ እስራኤል የሥጋዊ እስራኤላውያንን ብሔር በመተካት የይሖዋ ‘ባሪያ’ እንዲሁም የእርሱ ‘ምሥክር’ ሆኗል። (ኢሳይያስ 43:10) ከዚያ በኋላ ይሖዋ እስራኤልን በሚመለከት የተናገራቸው በኢሳይያስ 43:21 እና በዘጸአት 19:5, 6 ላይ የሚገኙት ቃላት ለአምላክ መንፈሳዊ እስራኤል አገልግለዋል። አዲሱ የአምላክ መንፈሳዊ ብሔር ‘የይሖዋን በጎነት የመናገር’ ኃላፊነት የተጣለበት “የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን” ሆኗል። (1 ጴጥሮስ 2:9) ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በአምላክ እስራኤል ውስጥ የታቀፉት ሁሉ አንድ የካህናት ቡድን ይሆናሉ። (ገላትያ 3:28, 29) በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሱ የአብርሃም ዘር እንደመሆናቸው መጠን “እናንተ አሕዛብ ሆይ፣ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ” ይላሉ። (ዘዳግም 32:43) ከመንፈሳዊ እስራኤል መካከል በምድር ላይ የቀሩት “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሆነዋል። (ማቴዎስ 24:45-47) ለአምላክ ተቀባይነት ያለው ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ የሚቻለው ከእነርሱ ጋር በመተባበር ብቻ ነው።
የአምላክ መንግሥት—የመጨረሻ ፍጻሜው
17. በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ያሉ ሰዎች ይወለዳሉ ሲባል ምን ማለት ነው?
17 ከዘአበ ከ1513 በኋላ የተወለዱት እስራኤላውያን የሕጉ ቃል ኪዳን ክፍል የሆኑት በውልደት ነበር። ይሖዋ ወደ አዲሱ ቃል ኪዳን የሚያስገባቸውም ሰዎች ቢሆኑ እንዲሁ መወለድ አለባቸው፤ ይሁን እንጂ የእነርሱ መንፈሳዊ ውልደት ነው። ኢየሱስ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ለፈሪሳዊው ኒቆዲሞስ እንዲህ ሲል ነግሮታል:- “እውነት እውነት እልሃለሁ፣ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም።” (ዮሐንስ 3:3) ፍጽምና ከጎደላቸው የሰው ልጆች መካከል ይህን አዲስ ውልደት ለማግኘት የመጀመሪያ የሆኑት በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ተሰብስበው የነበሩት 120 ደቀ መዛሙርት ናቸው። በአዲሱ ቃል ኪዳን ሥር እንደ ጻድቅ በመቆጠር የንጉሣዊ ርስታቸው “መያዣ” የሆነውን መንፈስ ቅዱስ ተቀብለዋል። (ኤፌሶን 1:14) የአምላክ ልጆች ለመሆን ‘ከመንፈስ ተወልደዋል፤’ ይህም የኢየሱስ ወንድሞች በመሆን ከክርስቶስ ጋር ‘አብረው የመውረስ’ መብት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። (ዮሐንስ 3:6፤ ሮሜ 8:16, 17) ‘ዳግም መወለዳቸው’ ድንቅ የሆኑ ተስፋዎችን እንዲያገኙ በር ከፍቶላቸዋል።
18. በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ላሉት ሰዎች ዳግም መወለድ የትኞቹን ድንቅ ተስፋዎች እንዲያገኙ በር ይከፍትላቸዋል?
18 ኢየሱስ ለአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ ሆኖ ባገለገለበት ጊዜ እንዲህ በማለት ከተከታዮቹ ጋር ተጨማሪ ቃል ኪዳን ገብቷል:- “አባቴ ከእኔ ጋር የመንግሥት ቃል ኪዳን እንዳደረገ እኔም ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን አደርጋለሁ።” (ሉቃስ 22:29 NW) ይህ የመንግሥት ቃል ኪዳን በዳንኤል 7:13, 14, 22, 27 ላይ የተገለጸው አስገራሚ ራእይ ፍጻሜውን እንዲያገኝ መንገድ የሚጠርግ ነው። ዳንኤል “የሰው ልጅ የሚመስል” ‘በዘመናት በሸመገለው’ በይሖዋ አምላክ ፊት ቀርቦ ንጉሣዊ ሥልጣን ሲቀበል ተመልክቷል። ከዚያም ዳንኤል ‘የልዑሉ ቅዱሳን መንግሥቱን ሲወርሱ’ አይቷል። “የሰው ልጅ የሚመስል” የተባለው በ1914 ሰማያዊ መንግሥቱን ከይሖዋ አምላክ የተቀበለው ኢየሱስ ነው። “ቅዱሳኑ” ከእርሱ ጋር በዚያች መንግሥት የሚካፈሉት በመንፈስ የተቀቡት ደቀ መዛሙርቱ ናቸው። (1 ተሰሎንቄ 2:12) እንዴት?
19, 20. (ሀ) ይሖዋ ለአብርሃም የገባው ቃል በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ለታቀፉት ሰዎች ምን የመጨረሻና ክብራማ ፍጻሜ ይኖረዋል? (ለ) ልንመረምረው የሚገባን ተጨማሪ ጥያቄ የትኛው ነው?
19 እነዚህ ቅቡዓን ከሞት ከተነሡ በኋላ እንደ ኢየሱስ የማይጠፋ መንፈሳዊ ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት በመሆን ከእርሱ ጋር ሰማያዊ ነገሥታትና ካህናት ሆነው ያገለግላሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:50-53፤ ራእይ 20:4, 6) እንዴት ያለ ክብራማ ተስፋ ነው! በከነዓን ምድር ብቻ ሳይሆን በመላዋ ‘ምድር ላይ ይነግሣሉ።’ (ራእይ 5:10) ‘የጠላቶቻቸውን ደጅ ይወርሱ’ ይሆን? (ዘፍጥረት 22:17) አዎን፣ የጠላትነት ዝንባሌ ያላትን የሃይማኖታዊቷን ጋለሞታ የታላቂቱ ባቢሎንን ጥፋት በዓይናቸው ሲመለከቱና እነዚህ ትንሣኤ ያገኙት ቅቡዓን ‘አሕዛብን በብረት በትር’ በመግዛቱና የሰይጣንን ራስ በመቀጥቀጡ ሥራ ከኢየሱስ ጋር ሲካፈሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የጠላቶቻቸውን ደጅ ይወርሳሉ። በዚህ መንገድ በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተገለጸው ትንቢት የመጨረሻ ፍጻሜውን እንዲያገኘ በማድረግ ተካፋይ ይሆናሉ።—ራእይ 2:26, 27፤ 17:14፤ 18:20, 21፤ ሮሜ 16:20
20 አሁንም ቢሆን የአብርሃም ቃል ኪዳንና አዲሱ ቃል ኪዳን የሚያቅፉት እነዚህን 144,000 የታመኑ ነፍሶች ብቻ ነውን? የሚል ጥያቄ ልናነሣ እንችላለን። የለም፣ በሚቀጥለው ርዕስ እንደምንመለከተው በቀጥታ በእነዚህ ቃል ኪዳኖች ውስጥ ያልታቀፉ ሌሎችም ይባረካሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግን እና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (በእንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ገጽ 470 ተመልከት።
ታስታውሳለህን?
◻ አዲሱ ቃል ኪዳን ሥራውን የጀመረው መቼ ነው?
◻ አሮጌው ቃል ኪዳን ምን ነገር አከናውኗል?
◻ ዋነኛው የአብርሃም ዘር ማን ነው? በዚህ ዘር አማካኝነት አሕዛብ የተባረኩበት ቅደም ተከተልስ ምን ይመስላል?
◻ የአብርሃም ቃል ኪዳንና አዲሱ ቃል ኪዳን በ144,000ዎቹ ላይ የሚኖራቸው የመጨረሻ ፍጻሜ ምንድን ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኃጢአት ይቅርታ በአሮጌው ቃል ኪዳን ውስጥ ከታቀፉት ሰዎች ይልቅ በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ለታቀፉት ሰዎች የበለጠ ጥልቅ ትርጉም አለው