“ፍቅራዊ ደግነትህ ከሕይወት ይሻላል”
ካልቪን ኤች ሆልምዝ እንደተናገረው
ጊዜው ታኅሣሥ 1930 ነው፤ አባቴ በአቅራቢያችን ያለውን ጎረቤታችንን ጠይቆ ሲመጣ ገና ላሞቹን አልቤ መጨረሴ ነበር። “ዋይማን ያዋሰኝ መጽሐፍ ይኸውልህ” አለና ከኪሱ አንድ ሰማያዊ መጽሐፍ አውጥቶ አሳየኝ። በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀ ዲሊቨረንስ የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ ነበር። ማንበብ የሚባል ነገር እምብዛም የማይወደው አባባ እስከ ሌሊት ድረስ ቁጭ ብሎ መጽሐፉን አነበበው።
ከዚያም ላይት እንዲሁም ሪኮንሲሊዬሽን እንደሚሉ ያሉትን በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የተዘጋጁ መጻሕፍት ተውሶ አነበበ። የእናቴን አሮጌ መጽሐፍ ቅዱስ ፈለገና እስከ ሌሊት ድረስ ቁጭ ብሎ በኩራዝ ብርሃን ያነብብ ነበር። አባቴ ትልቅ ለውጥ አሳየ። በዚያ የክረምት ወቅት እናቴ፣ ሦስቱ እህቶቼና እኔ አንድ ላይ ከአሮጌዋ የእንጨት ማንደጃችን ዙሪያ እንሰበሰብና ለሰዓታት ያነጋግረን ነበር።
አባባ እነዚህን መጻሕፍት የሚያሳትሙት ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እንደሚባሉና እነርሱ እንደሚሉት ከሆነ ዛሬ የምንኖረው ‘በመጨረሻዎቹ ቀናት’ ውስጥ እንደሆነ ነገረን። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) በዓለም መጨረሻ ምድር አትጠፋም፤ ከዚህ ይልቅ በአምላክ መንግሥት ሥር ወደ ገነትነት ትለወጣለች እያለ አስረዳን። (2 ጴጥሮስ 3:5-7, 13፤ ራእይ 21:3, 4) ይህ ነገር በጣም ሳበኝ።
አባባ፣ ሥራችንን አንድ ላይ ሆነን ስንሠራም ይነግረኝ ጀመር። የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ የነገረኝ ቁጭ ብለን በቆሎ ስንሸለቅቅ እንደነበር ትዝ ይለኛል። (መዝሙር 83:18 NW) በዚህ መንገድ በ14 ዓመቴ በ1931 የጸደይ ወቅት ከይሖዋና ከመንግሥቱ ጎን ለመቆም ቆረጥኩ። ከቤታችን ኋላ ከነበረው አንድ ያረጀ የፖም ተክል በስተጀርባ ሆኜ ወደ ይሖዋ በመጸለይ እስከ ዘላለሙ ድረስ እንደማገለግለው ቃል ገባሁ። ልቤ ድንቅ በሆነው አምላካችን ፍቅራዊ ደግነት ተነክቶ ነበር።—መዝሙር 63:3 NW
የምንኖረው በዩ ኤስ ኤ ከሴንት ጆሴፍ ሚዙሪ ክፍለ ግዛት 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከካንሳስ ሲቲ ደግሞ ከ65 ኪሎ ሜትር በሚያንስ ርቀት ላይ በሚገኝ የእርሻ ቦታ ነበር። አባቴ የተወለደው ቅድመ አያታችን በ19ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በእርሻ ቦታው ላይ በሠራው የእንጨት ቤት ውስጥ ነበር።
ለአገልግሎት መሠልጠን
በ1931 የበጋ ወር በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ጆሴፍ ራዘርፎርድ በኮሎምበስ ኦሃዮ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የሰጠው “የዓለም ተስፋ የሆነው መንግሥት” የሚለው ንግግሩ በራዲዮ ሲተላለፍ ሰማን። ንግግሩ ልቤን አነሳሳው፤ ከአባቴ ጋር ይህን በጣም ጠቃሚ የሆነ ንግግር የያዘውን ቡክሌት ለምናውቃቸው ሰዎች ማሠራጨት በመቻሌ ተደሰትኩ።
በ1932 የጸደይ ወር ለመጀመሪያ ጊዜ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። ጆርጅ ድራፐር የተባለ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ የበላይ ተመልካች በሴንት ጆሴፍ የሚሰጠውን ንግግር እንድናዳምጥ ጎረቤታችን እኔንና አባባን ጋበዘን። እዚያ ስንደርስ ስብሰባው ተገባዷል፤ ደንደን ካለው ጄ ዲ ድራየር ጀርባ አንድ ቦታ አገኘሁና ቁጭ አልኩ። ድራየር በእኔ ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ሚና የተጫወተ ሰው ነው።
በመስከረም 1933 ካንሳስ ሲቲ ውስጥ በተደረገ አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ከአባባ ጋር ተገኘሁ፤ ለሕዝብ በሚሰጠው ምሥክርነት ለመጀመሪያ ጊዜ የተካፈልኩት በዚህ ጊዜ ነበር። አባባ ሦስት ቡክሌቶችን ሰጠኝና ምን እንደምል አስጠናኝ:- “የአምላክን መንግሥት ምሥራች ከሚሰብኩት የይሖዋ ምሥክሮች አንዱ ነኝ። ጀጅ ራዘርፎርድ በራዲዮ ሲናገር እንደሰሙት አያጠራጥርም። እርሱ የሚያቀርባቸው ንግግሮች በየሳምንቱ ከ300 በሚበልጡ የራዲዮ ጣቢያዎች ይሠራጫሉ።” ከዚያም አንድ ቡክሌት አበረከትሁ። የዚያን ዕለት ምሽት ወደ እርሻ ከተመለስኩም በኋላ ላሞቹን እያለብኩ ይህ ቀን በሕይወቴ ውስጥ ፈጽሞ ከማልረሳቸው ቀናት አንዱ እንደሚሆን አስብ ነበር።
ወዲያው የክረምቱ ቅዝቃዜ ስለጀመረ ብዙም ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ አልቻልንም። ይሁን እንጂ ወንድም ድራየርና ባለቤቱ ቤታችን መጡና ቅዳሜ ዕለት ምሽት ቤታቸው ሄጄ ከእነርሱ ጋር እንዳድር ጠየቁኝ። ወደ እነድራየር ቤት ያደረግሁት አሥር ኪሎ ሜት የሚፈጅ የእግር ጉዞ ምንም አልቆጨኝም፤ ምክንያቱም በሚቀጥለው ቀን አብሬያቸው ለማገልገልና በሴንት ጆሴፍ በሚደረገው የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ ለመገኘት ችዬ ነበር። ከዚያ ጊዜ ወዲህ እሁድ እሁድ አገልግሎት ሳልካፈል የቀረሁባቸው ጊዜያት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ወንድም ድራየር የሰጠኝ ሥልጠናና ምክር እጅግ ጠቅሞኛል።
በመጨረሻ መስከረም 2, 1935 ዕለት በካንሳስ ሲቲ በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን በጥምቀት ማሳየት ቻልኩ።
የዕድሜ ልክ ሥራ መጀመር
በ1936 መጀመሪያ ላይ አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ለመሆን አመለከትኩና የአቅኚነት ጓደኛ ከሚፈልጉት መካከል ተመዘገብኩ። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በዋዮሚንግ አርቫዳ ከሚገኘው ኤድዋርድ ስቴድ ደብዳቤ ደረሰኝ። የተሽከርካሪ ወንበር ቁራኛ እንደሆነና በአቅኚነት ለማገልገል እርዳታ እንደሚፈልግ ገለጸልኝ። ወዲያው ግብዣውን ተቀበልኩና ሚያዝያ 18, 1936 አቅኚ ሆኜ ተሾምኩ።
ከወንድም ስቴድ ጋር ለማገልገል ከመሄዴ በፊት እናቴ ለብቻዬ ጠርታ አነጋገረችኝ። “የእኔ ልጅ፣ እርግጠኛ ነህ ይህን ሥራ መሥራት ትፈልጋለህ?” ስትል ጠየቀችኝ።
“ያለዚያማ ሕይወት ትርጉም አይኖረውም” ስል መለስኩላት። የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ከምንም ነገር እንደሚበልጥ ተገንዝቤ ነበር።
እኛ ቴድ እያልን ከምንጠራው ከወንድም ስቴድ ጋር በአቅኚነት ማገልገል ግሩም ሥልጠና ማግኘት ነበር። ከፍተኛ ቅንዓት ያለውና የመንግሥቱን መልእክት በጣም ማራኪ በሆነ መንገድ የሚያቀርብ ወንድም ነበር። ይሁን እንጂ ቴድ ማድረግ የሚችለው ነገር ቢኖር መጻፍና መናገር ብቻ ነበር፤ መገጣጠሚያዎቹ ሁሉ ሩማቶይድ አርትራይተስ በተባለ በሽታ ተሳስረው ነበር። በጠዋት ተነስቼ አጥበዋለሁ፣ ጺሙን እላጭለታለሁ፣ ቁርስ አዘጋጅቼ አበላዋለሁ። ከዚያም ልብሱን አለብሰውና ለአገልግሎት አዘጋጀዋለሁ። በዚያ የበጋ ወር ማታ ማታ ከቤት ውጭ እያደርን ዋዮሚንግና ሞንታና ውስጥ በአቅኚነት አገልግለናል። ቴድ በዕቃ መጫኛ መኪናው ላይ በተሠራችለት ልዩ መጠለያ ውስጥ ሲያድር እኔ ደግሞ መሬት አድር ነበር። ትንሽ ቆይቶ በዚያው ዓመት በቴነሲ፣ በአርካንሳስና በሚሲሲፒ በአቅኚነት ለማገልገል ወደ ደቡብ ሄድኩ።
በመስከረም 1937 በኮሎምበስ ኦሃዮ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። ያን ያህል ብዙ ተሰብሳቢ ባለበት የአውራጃ ስብሰባ ላይ ስገኝ ይህ የመጀመሪያዬ ነበር። በዚያ አካባቢ የምሥክርነቱን ሥራ በሸክላ ማጫወቻዎች አማካኝነት ለማስፋፋት ዝግጅቶች ተደርገው ነበር። የሸክላ ማጫወቻውን የተጠቀምንበትን እያንዳንዱን ጊዜ ሴትአፕ ብለን እንጠራው ነበር። አንደኛው ወር ከ500 በላይ ሴትአፕ አድርጌ የነበረ ሲሆን ከ800 በላይ ሰዎች አዳምጠዋል። በምሥራቃዊ ቴነሲ፣ በቨርጂኒያ እንዲሁም በምዕራብ ቨርጂኒያ በሚገኙ ብዙ ከተሞች ውስጥ ከመሠከርኩ በኋላ በልዩ አቅኚነት እንዳገለግል አዲስ ምድብ ተሰጠኝ። ይህም የዞን አገልጋይ ይባሉ ከነበሩት ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ጋር በመቀናጀት ለመሥራት የሚያስችለኝ ምድብ ነበር።
በምዕራብ ቨርጂኒያ የሚገኙ ጉባኤዎችንና በገለልተኛ ቦታዎች ያሉ ቡድኖችን የጎበኘሁ ሲሆን ከእያንዳንዳቸው ጋር ከሁለት እስከ አራት ሳምንት አብሬያቸው በመቆየት በአገልግሎት ግንባር ቀደም ሆኜ እሠራ ነበር። ከዚያም በጥር 1941 የዞን አገልጋይ ሆኜ ተሾምኩ። በዚህ ጊዜ እናቴና ሦስቱ እህቶቼ ማለትም ክላራ፣ ሎይስ እና ሩት ከአምላክ መንግሥት ጎን ተሠልፈው ነበር። በመሆኑም በዚያ የበጋ ወር ሴንት ሉዊስ በተደረገው ትልቅ የአውራጃ ስብሰባ ላይ መላው ቤተሰባችን ተገኝቶ ነበር።
ከዚህ የአውራጃ ስብሰባ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የዞን አገልጋዮች በኅዳር 1941 ላይ የዞን ሥራ እንደሚያቆም ተነገራቸው። በቀጣዩ ወር ዩናይትድ ስቴትስ ወደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ገባች። ከዚያም ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ፤ ይህም በወር 175 ሰዓት ባገልግሎት ማሳለፍን የሚጠይቅ ነበር።
ልዩ የአገልግሎት መብቶች
በሐምሌ 1942 በባሕር ማዶ ለማገልገል ፈቃደኛ መሆኔን የሚጠይቅ ደብዳቤ ደረሰኝ። የአዎንታ መልስ ከሰጠሁ በኋላ በብሩክሊን ኒው ዮርክ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ዋና መሥሪያ ቤት ማለትም ወደ ቤቴል ተጠራሁ። በዚያ ጊዜ ልዩ ሥልጠና እንዲሰጣቸው የተጠሩት 20 የሚያክሉ ነጠላ ወንድሞች ነበሩ።
በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ወንድም ናታን ኤች ኖር የስብከቱ እንቅስቃሴ እንደቀነሰ ከገለጸልን በኋላ ጉባኤዎችን በመንፈሳዊ ለማበርታት የሚያስችል ሥልጠና እንደሚሰጠን ነገረን። “ማወቅ የምንፈልገው በጉባኤዎቹ ውስጥ ያለውን ችግር ብቻ ሳይሆን እናንተ ችግሩን ለመፍታት ምን እንዳረጋችሁ ጭምር ነው” አለን።
ከወንድም ኖር ቀጥሎ በ1977 የማኅበሩ ፕሬዚዳንት የሆነው ፍሬድ ፍራንዝ ቤቴል እያለን ንግግር ሲሰጥ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ሁለተኛው የዓለም ጦርነት አብቅቶ ታላቅ የስብከት ሥራ የሚሠራበት በር ይከፈታል። ገና በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ይሖዋ ድርጅት እንደሚሰበሰቡ ምንም አያጠራጥርም!” ይህ ንግግር ሙሉ በሙሉ አመለካከቴን ቀየረው። ምድባችን ሲነገረን በቴነሲ እና በኬንተኪ የሚገኙትን ጉባኤዎች በሙሉ እንደምጎበኝ አወቅሁ። የወንድሞች አገልጋይ ተብለን እንጠራ የነበር ሲሆን በኋላ የወረዳ የበላይ ተመልካች በሚል ስያሜ ተቀይሯል።
ጥቅምት 1, 1942 ጉባኤዎችን ማገልገል ስጀምር ዕድሜዬ ገና 25 ዓመት ነበር። በዚያ ጊዜ ወደ አንዳንዶቹ ጉባኤዎች መሄድ የሚቻለው በእግር አለዚያም በፈረስ ነበር። አንዳንድ ጊዜ በእንግድነት ከተቀበለኝ ቤተሰብ ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ አድር ነበር።
በሐምሌ 1943 ቴነሲ የሚገኘውን የግሪንቪል ጉባኤ በማገልገል ላይ እያለሁ በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ሁለተኛ ክፍል እንድሳተፍ ግብዣ ቀረበልኝ። በጊልያድ እያለሁ ‘ለሰማነው ነገር አብልጠን እንጠንቀቅ’ እንዲሁም ‘የጌታ ሥራ የበዛልን እንሁን’ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ተምሬያለሁ። (ዕብራውያን 2:1፤ 1 ቆሮንቶስ 15:58) በትምህርት ቤቱ ውስጥ የምንቆይባቸው አምስት ወራት ሳናስበው አልቀው ጥር 31, 1944 የምንመረቅበት ቀን ደረሰ።
ወደ ካናዳ ከዚያም ወደ ቤልጂየም
የተወሰንነው በቅርቡ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ከዕገዳ ነፃ ወደ ሆነባት ወደ ካናዳ ሄደን እንድናገለግል ተመደብን። እኔ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት እንዳገለግል ተመደብኩ፤ ይህም በአንዳንድ ጉባኤዎች መካከል ከፍተኛ ርቀት መጓዝን ይጠይቅ ነበር። ከአንዱ ጉባኤ ወደ ሌላው ስጓዝ ሥራችን በካናዳ በእገዳ ሥር እንዴት ይካሄድ እንደነበር ተሞክሮዎችን መስማት እጅግ የሚያስደስት ነበር። (ሥራ 5:29) ብዙዎቹ በአንድ ሌሊት ከአንዱ የካናዳ ጫፍ እስከሌላው ድረስ በእያንዳንዱ ቤት በር ላይ አንድ አንድ ቡክሌት በማስቀመጥ ስላደረጉት ዘመቻ ነግረውኛል። በግንቦት 1945 በአውሮፓ ይደረግ የነበረው ጦርነት እንዳበቃ መስማት ምሥራች ነበር!
በዚያ የበጋ ወር በኦሳጅ ሳስካጄዋን በሚገኝ አንድ ጉባኤ እያገለገልኩ እያለ ከወንድም ኖር እንዲህ የሚል ደብዳቤ ደረሰኝ:- “ወደ ቤልጂየም የመሄድ መብት እንዳገኘህ ልገልጽህ እወዳለሁ። . . . በዚህች አገር ብዙ የሚሠራ ሥራ አለ። ጦርነት ያደቀቃት አገር ስለሆነች ወንድሞቻችን እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። እነዚህ ወንድሞች የሚያስፈልጋቸውን እርዳታና ማጽናኛ እንዲያገኙ አንድ ወንድም ከአሜሪካ መላካችን የተገባ ይሆናል።” ይህን የአገልግሎት ምድብ መቀበሌን በመግለጽ ወዲያው ምላሽ ሰጠሁ።
በኅዳር 1945 ወደ ብሩክሊን ቤቴል ሄድኩና የአልሳስ ተወላጅ ከሆነው አረጋዊ ከቻርለስ አይከር ጋር ፈረንሳይኛ መማር ጀመርኩ። በተጨማሪም የቅርንጫፍ ቢሮ አሠራርን በሚመለከት ፈጣን ሥልጠና ተሰጠኝ። ወደ አውሮፓ ከመሄዴ በፊት በሴንት ጆሴፍ ሚዙሪ የሚገኙትን ቤተሰቦቼንና ወዳጆቼን ሄጄ ጠየቅኋቸው።
ታኅሣሥ 11 ከኒው ዮርክ ኩዊን ኤልዛቤት ተብላ በምትጠራው መርከብ ተሳፍሬ ከአራት ቀን ጉዞ በኋላ እንግሊዝ ሳውዝሃምፕተን ገባሁ። በብሪታንያ ቅርንጫፍ ቢሮ ለአንድ ወር ያህል ቆይቼ ተጨማሪ ሥልጠና ተሰጠኝ። ከዚያ በኋላ ጥር 15, 1946 የእንግሊዝን የባሕር ወሽመጥ አቋርጬ ወደ ቤልጂየም ኦስተንድ ወደብ ደረስሁ። ከዚህ በባቡር ተሳፍሬ ወደ ብራስልስ ስገባ መላው የቤቴል ቤተሰብ ባቡር ጣቢያ ድረስ መጥቶ ተቀበለኝ።
ከጦርነቱ በኋላ የተፋጠነው እንቅስቃሴ
ኃላፊነቴ በቤልጂየም የሚሠራውን የመንግሥቱን ሥራ በበላይነት መቆጣጠር ነበር፤ ይሁንና ቋንቋውን ገና መናገር እንኳ አልችልም። ወደ ስድስት ወር በሚጠጋ ጊዜ ውስጥ ለመግባባት የሚያስችለኝን ያህል ፈረንሳይኛ አወቅሁ። በአምስት ዓመቱ የናዚ ወረራ ጊዜ ሕይወታቸውን ሳይቀር አደጋ ላይ ጥለው የስብከቱን ሥራ ሲያካሂዱ ከነበሩ ወንድሞች ጋር አብሮ መሥራት ትልቅ መብት ነበር። አንዳንዶቹም ከማጎሪያ ካምፖች ገና መውጣታቸው ነበር።
ወንድሞች ሥራው ተደራጅቶ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የተጠሙትን ሰዎች ለመመገብ ተቻኩለው ነበር። ስለዚህ ትላልቅ ስብሰባዎች የሚደረጉበትና ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ጉባኤዎችን የሚጎበኙበት ዝግጅት ተደረገ። በተጨማሪም በብሩክሊን ከሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት በየጊዜው የመጡት ወንድም ናታን ኖር፣ ሚልተን ሄንሸል፣ ፍሬድ ፍራንዝ፣ ግራንት ሱተር እና ጆን ቡዝ አበረታች ጉብኝቶችን አድርገውልናል። በእነዚያ የመጀመሪያ ዓመታት የወረዳ የበላይ ተመልካች፣ የአውራጃ የበላይ ተመልካችና የቅርንጫፍ ቢሮ የበላይ ተመልካችም ሆኜ አገልግያለሁ። ታኅሣሥ 6, 1952 ማለትም ቤልጂየም ውስጥ ለ7 ዓመታት ካገለገልሁ በኋላ በዚያው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ታገለግል የነበረችውን ኢሚሊያ ቫኖፕስላውክን አገባሁ።
ከጥቂት ወራት በኋላ በሚያዝያ 11, 1953 በአካባቢው ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ተጠራሁና የእኔ በአገሪቱ መቆየት ለቤልጂየም ደህንነት አስጊ እንደሆነ ተነገረኝ። ጉዳዩ ለይግባኝ ወደ መንግሥት ምክር ቤት ቀርቦ እስኪታይልኝ ድረስ ወደ ሉክሰምበርግ ሄድኩ።
በየካቲት 1954 የቤልጂየም የመንግሥት ምክር ቤት የእኔ በአገሪቱ መቆየት ለአገሪቱ አደገኛ እንደሆነ በመስማማት የመጀመሪያውን ውሳኔ አጸደቀ። የቀረበው ማስረጃ እኔ ቤልጂየም ከገባሁ ጀምሮ በአገሪቱ ያሉት ምሥክሮች ቁጥር በእጅጉ መጨመሩ፣ ይኸውም በ1946 ከነበረው ከ804 ተነስቶ በ1953 ወደ 3,304 ከፍ ማለቱ ሲሆን ብዙ ወጣቶች ክርስቲያናዊ ገለልተኛነትን በሚመለከት ጥብቅ አቋም እየወሰዱ በመሆናቸው የቤልጂየም ደህንነት አደጋ ላይ ወድቋል የሚል ነበር። በመሆኑም ሚኢሊያና እኔ ስዊዘርላንድ ውስጥ በፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ክልል በወረዳ ሥራ እንድናገለግል ተመደብን።
ለክርስቲያን ሽማግሌዎች ተጨማሪ ሥልጠና ለመስጠት ሲባል የተዘጋጀው የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት በ1959 በኒው ዮርክ ሳውዝ ላንሲንግ ውስጥ ተጀመረ። በአውሮፓ የሚካሄዱትን የዚህን ትምህርት ቤት ክፍሎች ለማስተማር የሚያስችለኝን ሥልጠና እንዳገኝ ወደ ኒው ዮርክ እንድሄድ ተጋበዝኩ። ዩናይትድ ስቴትስ እንደሄድኩ በሴንት ጆሴፍ ሚዙሪ የሚገኙትን ቤተሰቦቼን ጎበኘኋቸው። ውዷን እናቴን ለመጨረሻ ጊዜ ዓይኗን ያየኋት በዚህ ጊዜ ነበር። ከዚያ በኋላ በጥር 1962 ሞተች፤ አባቴ በ1955 ቀደም ብሎ ሞቶ ነበር።
በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ የሚካሄደው የመንግሥት አገልግሎታችን ትምህርት ቤት መጋቢት 1961 ሲከፈት ኢሚሊያም አብራኝ ሄደች። በትምህርት ቤቱ ለመካፈል የአውራጃ የበላይ ተመልካቾች፣ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች፣ የጉባኤ የበላይ ተመልካቾችና ልዩ አቅኚዎች ከፈረንሳይ፣ ከቤልጂየምና ከስዊዘርላንድ ይመጡ ነበር። ለቀጣዮቹ 14 ወራት ይህን የአራት ሳምንታት ርዝማኔ ያለው ኮርስ ለ12 ክፍሎች ሰጥቻለሁ። ከዚያም በሚያዝያ 1962 ኢሚሊያ ነፍሰ ጡር መሆኗን ተገነዘብን።
ከሁኔታዎች ጋር ራስን ማስተካከል
ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ስለነበረን ወደ ጄኔቫ ስዊዘርላንድ ተመልሰን ሄድን። ይሁን እንጂ ከፍተኛ የቤት እጥረት ስለነበር መኖሪያ ቤት ማግኘት ቀላል አልነበረም። ሥራም ማግኘት ቢሆን እንዲሁ ቀላል አልነበረም። በመጨረሻ ጄኔቫ መሃል ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ ትልቅ የንግድ ድርጅት ውስጥ ሥራ አገኘሁ።
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት 26 ዓመታት ስላሳለፍኩ አዲሱ ሁኔታችን ትልቅ ማስተካከያ ማድረግን የሚጠይቅ ነበር። በዚህ የንግድ ድርጅት ውስጥ በሠራሁባቸውና ሎይስና ዩንስ የተባለቱን ሁለቱን ሴቶች ልጆቻችንን በማሳደግ ባሳለፍናቸው 22 ዓመታት በሙሉ ቤተሰባችን የመንግሥቱን ፍላጎቶች በማስቀደም ተመላልሷል። (ማቴዎስ 6:33) በ1985 ከሰብዓዊ ሥራዬ ጡረታ ከወጣሁ በኋላ ተተኪ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ ማገልገል ጀመርሁ።
ኢሚልያ ጤና እያጣች ብትመጣም በአገልግሎቱ የምትችለውን ያክል ትካፈላለች። ሎይስ ለአሥር ዓመታት አቅኚ ሆና አገልግላለች። በ1993 በበጋ ወር በሞስኮ በተካሄደው ድንቅ የሆነ ዓለም አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከእርሷ ጋር የሚያስደስት መንፈሳዊ ጊዜ አሳልፈናል! ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በአፍሪካ ወደምትገኘው ሴኔጋል ለሽርሸር ሄዳ እያለ በውቅያኖስ ውስጥ ስትዋኝ ሕይወቷ አለፈ። በቀብር ስነ ሥርዓቷ ላይ ለመገኘት ወደ ሴኔጋል በሄድኩበት ጊዜ በአፍሪካ የሚገኙት ወንድሞቻችንና ሚስዮናውያን ያሳዩኝ ፍቅርና ደግነት ትልቅ ማጽናኛ ሆኖልኛል። ሎይስን በትንሣኤ ላገኛት እጅግ እናፍቃለሁ!—ዮሐንስ 5:28, 29
ከአራት አሥርተ ዓመታት ለሚበልጡ ጊዜያት በታማኝነት የምትደግፈኝ አፍቃሪ ጓደኛ በማግኘቴ አመስጋኝ ነኝ። በእርግጥም ችግርና መከራ ቢገጥመኝም የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት አስደሳች ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ሕይወቴንም ይበልጥ ትርጉም ያለው አድርጎልኛል። አምላካችንን ይሖዋን በሚመለከት ልቤ መዝሙራዊ እንደተናገረው ለማለት ይገፋፋኛል:- “ፍቅራዊ ደግነትህ ከሕይወት ይሻላልና ከንፈሮቼ ያመሰግኑሃል።”—መዝሙር 63:3 NW
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የስብከቱን ሥራ በሸክላ ማጫወቻዎች አስፋፍተናል
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወላጆቼ በ1936
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1948 በቤልጂየም የመንገድ ላይ ምሥክርነት ስሰጥ