የአምላክ ልጆች በቅርቡ ክብራማ ነፃነት ይጎናጸፋሉ
“ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና፣ በተስፋ ስላስገዛው ነው . . . ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው።”—ሮሜ 8:20, 21
1. የኢየሱስ መሥዋዕት በስርየት ቀን በጥላነት የተገለጸው እንዴት ነበር?
ይሖዋ አንድያ ልጁን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ መስጠቱ 144,000 ሰዎች ሰማያዊ ሕይወት እንዲያገኙና የቀረው የሰው ዘር ደግሞ ዘላለማዊ የሆኑ ምድራዊ ተስፋዎችን እንዲጨብጥ በር ከፍቷል። (1 ዮሐንስ 2:1, 2) በፊተኛው ርዕስ እንደተገለጸው ኢየሱስ በመንፈስ ለተወለዱት ክርስቲያኖች ያቀረበው መሥዋዕት የእስራኤል ሊቀ ካህናት በዓመታዊው የስርየት ቀን ለራሱ፣ ለቤተሰቡና ለሌዊ ነገድ ኃጢአት በሚያቀርበው ወይፈን በጥላነት ተገልጿል። የክርስቶስ መሥዋዕት የቀሩትን የሰው ልጆች በአጠቃላይ እንደሚጠቅም ሁሉ ሊቀ ካህናቱ በዚያው ዕለት ለሌሎቹ እስራኤላውያን የሚሆን የኃጢአት መሥዋዕት ያቀርብ ነበር። በምሳሌያዊ መንገድ የሕዝቡን የጋራ ኃጢአት ተሸክሞ እንዲሄድ ሲባል አንድ ፍየል ከነሕይወቱ ወደ በረሃ ይለቀቅ ነበር።a—ዘሌዋውያን 16:7-15, 20-22, 26
2, 3. በሮሜ 8:20, 21 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት የጳውሎስ ቃላት ትርጉም ምንድን ነው?
2 ሐዋርያው ጳውሎስ ሰማያዊ ‘የአምላክ ልጆች’ የሚሆኑት ሰዎች ያላቸውን ተስፋ ከገለጸ በኋላ እንዲህ ብሏል:- “የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና። ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና፣ በተስፋ ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም፤ ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው።” (ሮሜ 8:14, 17, 19-21) የዚህ አባባል ትርጉሙ ምንድን ነው?
3 አባታችን አዳም ሲፈጠር ፍጹም ሰው የነበረ ከመሆኑም ሌላ “የእግዚአብሔር ልጅ” ነበር። (ሉቃስ 3:38) ኃጢአት በመሥራቱ ምክንያት ‘በጥፋት ባርነት’ ሥር የወደቀ ሲሆን ይህንኑ ሁኔታ ለመላው የሰው ዘር አውርሷል። (ሮሜ 5:12) አምላክም ሰዎች በወረሱት አለፍጽምና ምክንያት ‘ከንቱነት’ ከፊታቸው ተጋርጦባቸው እንዲወለዱ ፈቅዷል፤ ይሁን እንጂ “ዘር” ተብሎ በተጠቀሰው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ተስፋ ሰጥቷቸዋል። (ዘፍጥረት 3:15፤ 22:18፤ ገላትያ 3:16) ራእይ 21:1-4 ‘ሞት፣ ኃዘን፣ ጩኸትና ስቃይ የማይኖርበት’ ጊዜ እንደሚመጣ ይገልጻል። ይህ ‘ለሰው ዘር’ የተሰጠ ተስፋ በመሆኑ በመንግሥቱ ግዛት ሥር የሚኖረው አዲስ ምድራዊ የሰው ዘር ማኅበረሰብ ሙሉ አእምሯዊና አካላዊ ጤንነት የሚላበስበትና በምድር ላይ ‘የአምላክ ልጆች’ በመሆን የሚኖሩበት ጊዜ እንደሚመጣ ማረጋገጫ ይሆነናል። በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ‘ከጥፋት ባርነት ነፃ’ ይወጣሉ። በመጨረሻው ፈተና ወቅት ለይሖዋ ያላቸውን ታማኝነት ካረጋገጡ በኋላ ከወረሱት ኃጢአትና ሞት ለዘላለም ነፃ ይሆናሉ። (ራእይ 20:7-10) ከዚያ በኋላ በምድር ላይ የሚኖሩት ሰዎች ‘የአምላክን ልጆች ክብራማ ነፃነት ይጎናጸፋሉ።’
“ና” እያሉ ነው
4. ‘የሕይወትን ውኃ በነፃ መውሰድ’ ማለት ምን ማለት ነው?
4 ከሰው ዘር ፊት የተዘረጋው ተስፋ እንዴት ድንቅ ነው! በምድር ላይ ያሉት በመንፈስ የተወለዱ ክርስቲያኖች ስለዚህ ተስፋ ለሌሎች በቅንዓት በማወጅ ረገድ ግንባር ቀደም ሆነው መገኘታቸው አያስገርምም! ቅቡዓን ቀሪዎቹ ክብር የተቀዳጀው የበጉ የኢየሱስ ክርስቶስ “ሙሽራ” ክፍል እንደመሆናቸው መጠን በሚከተሉት ትንቢታዊ ቃላት ፍጻሜ እየተካፈሉ ነው:- “መንፈሱና ሙሽራይቱም:- ና ይላሉ። የሚሰማም:- ና ይበል። የተጠማም ይምጣ፣ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ።” (ራእይ 21:2, 9፤ 22:1, 2, 17) ከኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚገኘው ጥቅም ለ144,000 ቅቡዓን ብቻ የተወሰነ አይደለም። የአምላክ መንፈስ “ና” እያሉ ባሉት በምድር በቀሩት የሙሽራይቱ ክፍል አባላት በኩል መሥራቱን ይቀጥላል። ለጽድቅ ተጠምቶ ጥሪውን የሚሰማ ሰው ይሖዋ ባደረገው ታላቅ የመዳን ዝግጅት በመጠቀም “ና” እንዲል ተጋብዟል።
5. የይሖዋ ምሥክሮች እነማን በመካከላቸው በመገኘታቸው ይደሰታሉ?
5 የይሖዋ ምሥክሮች፣ አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ባደረጋቸው የሕይወት ዝግጅቶች ላይ እምነት አላቸው። (ሥራ 4:12) ስለ አምላክ ዓላማ ለመማርና ፈቃዱን ለማድረግ የሚጓጉ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በመካከላቸው በመገኘታቸው ይደሰታሉ። የመንግሥት አዳራሾቻቸው በዚህ ‘የፍጻሜ ዘመን’ ‘የሕይወትን ውኃ በነፃ ለመውሰድ’ ለሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ክፍት ናቸው።—ዳንኤል 12:4
ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የተከናወኑ ለውጦች
6. በተለያዩ ወቅቶች የአምላክ መንፈስ በይሖዋ አገልጋዮች ላይ የሠራው በምን መንገድ ነው?
6 አምላክ ዓላማውን የሚፈጽምበት ጊዜ አለው፤ ይህ ደግሞ ከሰዎች ጋር የሚኖረውንም ግንኙነት ይነካል። (መክብብ 3:1፤ ሥራ 1:7) የአምላክ መንፈስ በቅድመ ክርስትና ዘመን በነበሩት የአምላክ አገልጋዮች ላይ ቢወርድም መንፈሳዊ ልጆቹ ሆነው አልተወለዱም። ይሁን እንጂ ይሖዋ ከኢየሱስ ጀምሮ ራሳቸውን የወሰኑ ወንዶችና ሴቶች በመንፈሱ አማካኝነት ለሰማያዊ ውርሻ መንፈሳዊ ልጆች ሆነው እንዲወለዱ የሚያደርግበት ጊዜ ደርሶ ነበር። ስለእኛ ዘመንስ ምን ለማለት ይቻላል? ይኸው መንፈስ በኢየሱስ “ሌሎች በጎች” ላይ ይሠራል፤ ይሁን እንጂ የሰማያዊ ሕይወት ተስፋና ምኞት በውስጣቸው አያሳድርባቸውም። (ዮሐንስ 10:16) አምላክ የሰጣቸው ተስፋ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም መኖር ስለሆነ በአሮጌው ዓለምና ጽድቅ በሰፈነበት የአምላክ አዲስ ዓለም መካከል ባለው በዚህ የሽግግር ዘመን ቅቡዓኑን በምሥክርነቱ ሥራ በደስታ ይረዷቸዋል።—2 ጴጥሮስ 3:5-13
7. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ያተኮሩት የትኛውን መከር በመሰብሰቡ ላይ ነበር? ይሁን እንጂ ስለ ገነት ምን ነገር ተገንዝበው ነበር?
7 አምላክ ‘ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ማምጣት’ የጀመረው በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስን በማፍሰስ ሲሆን ጠቅላላ ቁጥራቸው 144,000 የሆነው መንፈሳዊ ‘የአምላክ እስራኤል’ መሰብሰብ የሚያበቃበትንም ጊዜ እንደወሰነ ግልጽ ነው። (ዕብራውያን 2:10፤ ገላትያ 6:16፤ ራእይ 7:1-8) ከ1879 አንስቶ በዚሁ መጽሔት ላይ የቅቡዓን ክርስቲያኖችን መከር ስለመሰብሰብ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ (ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለዋል) ቅዱሳን ጽሑፎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዳለ እንደሚገልጹም ተገንዝበው ነበር። ለምሳሌ ያህል የሐምሌ 1883 መጠበቂያ ግንብ እትም እንዲህ ብሎ ነበር:- “ኢየሱስ መንግሥቱን ሲያቋቁም፣ ክፋትን ሲደመስስና ሌሎች እርምጃዎችን ሲወስድ ይህች ምድር ገነት ትሆናለች፤ . . . በመቃብር ያሉ ሁሉ ተነሥተው ይኖሩባታል። ሕጎቿን በመታዘዝ ለዘላለም ሊኖሩባት ይችላሉ።” ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የቅቡዓኑ መከር እየቀነሰ መጣና ሰማያዊ ተስፋ የሌላቸው ሰዎች ወደ ይሖዋ ድርጅት መሰብሰብ ጀመሩ። ይህ በእንዲህ እንዳለ አምላክ ለቅቡዓን አገልጋዮቹ ማለትም ዳግም ለተወለዱት ክርስቲያኖች ድንቅ ማስተዋል ሰጣቸው።—ዳንኤል 12:3፤ ፊልጵስዩስ 2:15፤ ራእይ 14:15, 16
8. ስለ ምድራዊ ተስፋ የነበረው ግንዛቤ በ1930ዎቹ መጀመሪያ ላይ የዳበረው እንዴት ነው?
8 በተለይ ከ1931 ወዲህ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር ሲተባበሩ ቆይተዋል። በዚያ ዓመት ይሖዋ በመንፈስ ለተወለዱት ክርስቲያን ቀሪዎች የእውቀት ብርሃን ስለፈነጠቀላቸው ሕዝቅኤል ምዕራፍ 9 የሚናገረው ወደ አዲሱ ዓለም በሕይወት ስለሚያልፉት ምልክት የተደረገባቸው ሰዎች እንደሆነ አስተዋሉ። በ1932 ዛሬ ያሉት በግ መሰል ሰዎች ከኢዩ ጋር የተባበረው ዮናዳብ (ኢዮናዳብ) ጥላ የሆነላቸው ሰዎች መሆናቸው ታወቀ። (2 ነገሥት 10:15-17) በ1934 ‘የኢዮናዳብ’ ክፍል የሆኑት ሰዎች ለአምላክ “የተለዩ መሆን” ወይም ራሳቸውን ለእርሱ መወሰን እንደሚገባቸው ተገለጸ። ቀደም ሲል በሰማይ የክርስቶስን ሙሽራ ‘የሚያጅቡ’ ሁለተኛ ደረጃ ያላቸው የመንፈሳዊ ጥሪ ተካፋዮች ተደርገው ይታሰቡ የነበሩት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሌሎች በጎች መሆናቸው ታወቀ። (ራእይ 7:4-15፤ 21:2, 9፤ መዝሙር 45:14, 15) በተለይ ከ1935 ወዲህ ቅቡዓኑ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር የሚናፍቁትን ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በመፈለግ ረገድ ግንባር ቀደም ሆነው ሲሠሩ ቆይተዋል።
9. ከ1935 ወዲህ አንዳንድ ክርስቲያኖች በጌታ እራት ላይ ከምሳሌያዊዎቹ ቂጣና ወይን መካፈል ያቆሙት ለምንድን ነበር?
9 ከ1935 በኋላ በጌታ እራት ላይ ከቂጣውና ከወይኑ ይካፈሉ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች መካፈላቸውን አቆሙ። ለምን? ተስፋቸው ሰማያዊ ሳይሆን ምድራዊ እንደሆነ ስለተገነዘቡ ነበር። በ1930 የተጠመቀች አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች:- “በዚያን ጊዜ በተለይ ቀናተኛ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ከሆኑ [ከቂጣና ወይኑ መካፈላቸው] ተገቢ እንደሆነ ተደርጎ ቢቆጠርም ሰማያዊ ተስፋ አለኝ የሚል እምነት ፈጽሞ አልነበረኝም። ከዚያ በ1935 በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው እጅግ ብዙ ሰዎች እየተሰበሰቡ እንዳሉ ግልጽ ተደረገልን። ብዙዎቻችን ከእነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች መካከል መሆናችንን ስንረዳ እጅግ ተደስተን የነበረ ሲሆን ከምሳሌያዊዎቹ ቂጣና ወይን መካፈላችንንም አቆምን።” የክርስቲያናዊ ጽሑፎችም ይዘት ተለውጧል። ቀደም ባሉት ዓመታት የሚወጡት ጽሑፎች በዋነኛነት የሚዘጋጁት በመንፈስ የተወለዱትን የኢየሱስ ተከታዮች በማሰብ የነበረ ሲሆን ከ1935 ወዲህ ግን መጠበቂያ ግንብም ሆነ ‘ታማኝና ልባም ባሪያ’ የሚያዘጋጃቸው ሌሎቹ ጽሑፎች ለቅቡዓኑና ምድራዊ ተስፋ ላላቸው ተባባሪዎቻቸው የሚጠቅሙ መንፈሳዊ ምግቦችን ይዘው መውጣት ጀመሩ።—ማቴዎስ 24:45-47
10. የታመነ ሆኖ ያልተገኘ አንድ ቅቡዕ በሌላ የሚተካው እንዴት ሊሆን ይችላል?
10 አንድ ቅቡዕ የታመነ ሆኖ ሳይገኝ ቀረ እንበል። ይህ ሰው በሌላ ይተካልን? ጳውሎስ ስለ ምሳሌያዊው የወይራ ተክል ሲናገር በሌላ እንደሚተካ የሚጠቁም ሐሳብ ገልጿል። (ሮሜ 11:11-32) አንድን በመንፈስ የተወለደ ሰው በሌላ መተካት ካስፈለገ አምላክ ለብዙ ዓመታት ለእርሱ ቅዱስ አገልግሎት በማቅረብ ምሳሌ የሚሆን እምነት ላሳየ ሌላ ሰው ሰማያዊውን ጥሪ እንደሚያቀርብ ግልጽ ነው።—ከሉቃስ 22:28, 29፤ 1 ጴጥሮስ 1:6, 7 ጋር አወዳድር።
አመስጋኝ የምንሆንባቸው ብዙ ምክንያቶች
11. ተስፋችን ምንም ይሁን ምን ያዕቆብ 1:17 ስለ ምን ነገር ማረጋገጫ ይሰጠናል?
11 የትም ይሁን የት ይሖዋን የታመንን ሆነን እስካገለገልነው ድረስ የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ ያሟላልናል፤ በጎ ምኞቶቻችንንም ይፈጽምልናል። (መዝሙር 145:16፤ ሉቃስ 1:67-74) እውነተኛ ሰማያዊ ተስፋ ያለንም ሆንን ምድራዊ ተስፋ ያለን አምላክን ለማመስገን የሚያስችሉ ብዙ ምክንያቶች አሉን። ሁልጊዜ የሚያደርጋቸው ነገሮች እርሱን ለሚያፈቅሩት ሰዎች የሚጠቅሙ ናቸው። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፣ . . . ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ” ሲል ተናግሯል። (ያዕቆብ 1:17) እስቲ ከእነዚህ ስጦታዎችና በረከቶች መካከል አንዳንዶቹን እንመልከት።
12. ይሖዋ ለእያንዳንዱ የታመነ አገልጋዩ ድንቅ ተስፋ ሰጥቷል ልንል የምንችለው ለምንድን ነው?
12 ይሖዋ ለእያንዳንዱ የታመነ አገልጋዩ ድንቅ ተስፋ ሰጥቷል። አንዳንዶችን ለሰማያዊ ሕይወት ጠርቷቸዋል። ይሖዋ በቅድመ ክርስትና ዘመን ለኖሩት ምሥክሮቹ ትንሣኤ አግኝተው በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ዕጹብ ድንቅ ተስፋ ሰጥቷቸዋል። ለምሳሌ ያህል አብርሃም በትንሣኤ ተስፋ ላይ እምነት ስለነበረው “መሠረት ያላትን” ከተማ ማለትም ለምድራዊ ሕይወት ትንሣኤ የሚያገኝበትን ሰማያዊ መንግሥት ይጠባበቅ ነበር። (ዕብራውያን 11:10, 17-19) አምላክ በዚህ የመጨረሻ ዘመንም በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም የመኖርን ተስፋ ሰጥቷል። (ሉቃስ 23:43፤ ዮሐንስ 17:3) ይሖዋ እንዲህ ዓይነት ታላቅ ተስፋ የሰጣቸው ሁሉ ከልባቸው አመስጋኝ መሆን እንደሚገባቸው ግልጽ ነው።
13. የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በሕዝቦቹ ላይ የሚሠራው እንዴት ነው?
13 ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን በስጦታ መልክ ለሕዝቦቹ ያፈስሳል። ሰማያዊ ተስፋ የተሰጣቸው ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ ይቀባሉ። (1 ዮሐንስ 2:20፤ 5:1-4, 18) ይሁንና ምድራዊ ተስፋ ያላቸው የአምላክ አገልጋዮችም የመንፈሱን እርዳታና አመራር ያገኛሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ ሙሴ ነበር፤ እርሱን እንዲረዱት እንደተሾሙት 70 ሰዎች ሁሉ የይሖዋ መንፈስ በላዩ ነበር። (ዘኁልቁ 11:24, 25) ባስልኤል በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ በእስራኤል የመገናኛ ድንኳን ሥራ ውስጥ የተካነ የእጅ ሙያተኛ ሆኖ አገልግሏል። (ዘጸአት 31:1-11) ጌዴዎን፣ ዮፍታሄ፣ ሳምሶን፣ ዳዊት፣ ኤልያስ፣ ኤልሳዕና ሌሎችም እንዲሁ የአምላክ መንፈስ ነበራቸው። እነዚህ በጥንት ዘመን የኖሩ ግለሰቦች ወደ ሰማያዊ ክብር ይመጣሉ ማለት ባይሆንም ዛሬ እንዳሉት የኢየሱስ ሌሎች በጎች የመንፈስ ቅዱስን እርዳታና አመራር አግኝተዋል። እንግዲያውስ መንፈስ ቅዱስ አለን ማለት የሰማያዊ ጥሪ ተካፋዮች ነን ማለት አይደለም። ይሁንና የአምላክ መንፈስ አመራር ይሰጠናል፣ እንድንሰብክም ሆነ ሌሎች አምላካዊ ሥራዎቻችንን እንድናከናውን ይረዳናል፣ ከወትሮው የበለጠ ኃይል ይሰጠናል እንዲሁም እንደ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የዋሃትና ራስን መግዛት የመሳሰሉትን ፍሬዎች እንድናፈራ ያስችለናል። (ዮሐንስ 16:13፤ ሥራ 1:8፤ 2 ቆሮንቶስ 4:7-10፤ ገላትያ 5:22, 23) ለዚህ የአምላክ የደግነት ስጦታ አመስጋኞች ልንሆን አይገባንምን?
14. ከአምላክ የእውቀትና የጥበብ ስጦታዎች የምንጠቀመው እንዴት ነው?
14 እውቀትና ጥበብ ከአምላክ ያገኘናቸው ስጦታዎች ናቸው። ተስፋችን ሰማያዊም ይሁን ምድራዊ ስለ እነዚህ ስጦታዎች አመስጋኝ ልንሆን ይገባናል። ስለ ይሖዋ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ‘የሚሻለውን ነገር ፈትነን እንድናውቅ’ እንዲሁም ‘በነገር ሁሉ ይሖዋን ደስ ለማሰኘት ለእርሱ እንደሚገባ’ ሆነን እንድንመላለስ ያስችለናል። (ፊልጵስዩስ 1:9-11፤ ቆላስይስ 1:9, 10) አምላካዊ ጥበብ በሕይወታችን ውስጥ ጥበቃና መመሪያ ይሆንልናል። (ምሳሌ 4:5-7፤ መክብብ 7:12) እውነተኛ እውቀትና ጥበብ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ሲሆን በቁጥር ጥቂት የሆኑትን ቅቡዓን በተለይ የሚስባቸው ስለ ሰማያዊ ተስፋ የሚናገረው ነገር ነው። ይሁን እንጂ ለአምላክ ቃል ፍቅር ያለን መሆናችንና ስለ ቃሉ ጥሩ ግንዛቤ ማግኘታችን አምላክ ለሰማያዊ ሕይወት እንደጠራን የሚያሳይ ማረጋገጫ አይደለም። እንደ ሙሴና ዳንኤል ያሉት ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ክፍል ሳይቀር ጽፈዋል፤ ይሁን እንጂ ወደፊት የሚያገኙት ትንሣኤ ምድራዊ ነው። ተስፋችን ሰማያዊም ይሁን ምድራዊ ሁላችንም የይሖዋን ሞገስ ባገኘው “ታማኝና ልባም ባሪያ” አማካኝነት መንፈሳዊ ምግብ ይቀርብልናል። (ማቴዎስ 24:45-47) ሁላችንም በዚህ መንገድ ለምናገኘው እውቀት ምንኛ አመስጋኞች ነን!
15. ከአምላክ ታላላቅ ስጦታዎች መካከል አንዱ ምንድን ነው? እንዴትስ ትመለከተዋለህ?
15 ከአምላክ ታላላቅ ስጦታዎች መካከል አንዱ የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ሲሆን ተስፋችን ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ ሁላችንም የዚህ ፍቅራዊ ዝግጅት ተጠቃሚዎች ነን። አምላክ የሰውን ዘር ዓለም እጅግ ከመውደዱ የተነሣ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ . . . አንድያ ልጁን” ሰጥቷል። (ዮሐንስ 3:16) ኢየሱስም በፍቅር ተገፋፍቶ “ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ” ሰጥቷል። (ማቴዎስ 20:28) ሐዋርያው ዮሐንስ እንደገለጸው ኢየሱስ ክርስቶስ “የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፣ ለኃጢአታችንም [ለቅቡዓኑ] ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።” (1 ዮሐንስ 2:1, 2) በመሆኑም ሁላችንም የዘላለምን ሕይወት መዳን እንድናገኝ ለተደረገልን ለዚህ ፍቅራዊ ዝግጅት ከልብ አመስጋኞች መሆን ይገባናል።b
አንተም ትገኝ ይሆን?
16. ሚያዝያ 11, 1998 ቀን ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የሚታሰበው የትኛው ጉልህ ክንውን ነው? በዚያስ እነማን መገኘት ይኖርባቸዋል?
16 አምላክ በልጁ በኩል ላደረገው የቤዛ ዝግጅት ያለን አመስጋኝነት የይሖዋ ምሥክሮች ሚያዝያ 11, 1998 ቀን ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የክርስቶስን ሞት ለማስታወስ በሚሰበሰቡባቸው የመንግሥት አዳራሾች ወይም ሌሎች ቦታዎች ለመገኘት ሊያነሳሳን ይገባል። ኢየሱስ ምድር ላይ ባሳለፋት የመጨረሻ ምሽት ከታመኑ ሐዋርያቱ ጋር ሆኖ ይህን በዓል ባቋቋመበት ጊዜ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ብሏል። (ሉቃስ 22:19, 20፤ ማቴዎስ 26:26-30) በምድር ላይ የቀሩት ጥቂት ቅቡዓን የኢየሱስን ኃጢአት የለሽ ሰብዓዊ አካል ከሚወክለው ያልቦካ ቂጣና ለመሥዋዕት የፈሰሰውን ደሙን ከሚያመለክተው ምንም ማጠናከሪያ ያልተቀላቀለበት ቀይ ወይን ይካፈላሉ። ከዚህ መካፈል የሚገባቸው በመንፈስ የተወለዱት ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው፤ ምክንያቱም በአዲሱ ቃል ኪዳንና በመንግሥት ቃል ኪዳን ውስጥ የታቀፉት እንዲሁም ተስፋቸው ሰማያዊ እንደሆነ የሚያረጋግጥ አስተማማኝ የመንፈስ ቅዱስ ምሥክርነት ያላቸው እነርሱ ብቻ ናቸው። ለዘላለም ሕይወት በር ከከፈተው የኢየሱስ መሥዋዕት ጋር በተያያዘ መንገድ አምላክና ክርስቶስ ላሳዩት ፍቅር አመስጋኞች የሆኑ ሌሎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሥነ ሥርዓቱን ለመመልከት በአክብሮት ይገኛሉ።—ሮሜ 6:23
17. በመንፈስ መቀባትን በተመለከተ ልናስታውስ የሚገባን ነገር ምንድን ነው?
17 አንዳንዶች ቀድሞ በነበራቸው ሃይማኖታዊ አመለካከት፣ የሚወዱት ሰው መሞቱ የሚያሳድርባቸው ጠንካራ ስሜት፣ ዛሬ በምድር ላይ ያለው ሕይወት በመከራ የተሞላ መሆኑ ወይም ደግሞ ከይሖዋ የተለየ በረከት አግኝቻለሁ የሚለው ሐሳብ የሰማያዊ ሕይወት ጥሪ እንዳላቸው አድርገው በስህተት እንዲያስቡ ያደርጋቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ቅዱሳን ጽሑፎች ለክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ያለንን አድናቆት ለማሳየት ስንል በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚቀርቡት ምሳሌያዊ ቂጣና ወይን እንድንካፈል እንደማያዝዙ ሁላችንም ልናስታውስ ይገባል። ከዚህም በተጨማሪ በመንፈስ መቀባት ‘ለወደደ ወይም ለሮጠ ሳይሆን’ ኢየሱስ መንፈሳዊ ልጁ ሆኖ እንዲወለድ ካደረገውና ሌሎች 144,000 ልጆችን ብቻ ወደ ክብር ከሚያመጣው ‘ከአምላክ ነው።’—ሮሜ 9:16፤ ኢሳይያስ 64:8
18. ዛሬ ይሖዋን በማገልገል ላይ ያሉት አብዛኞቹ ሰዎች ከፊታቸው የሚጠብቃቸው በረከት ምንድን ነው?
18 በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት አምላክን በማገልገል ላይ ከሚገኙት አብዛኞቹ ሰዎች ፊት የተዘረጋው ተስፋ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም መኖር ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) በቅርቡም ይህን ዕጹብ ድንቅ ገነት ይወርሳሉ። በዚህ ጊዜ መሳፍንት በሰማያዊ አመራር ሥር ሆነው ምድራዊ ጉዳዮችን ያከናውናሉ። (መዝሙር 45:16 NW) የምድር ነዋሪዎች ከአምላክ ሕግ ጋር ተስማምተው ስለሚመላለሱና ስለ ይሖዋ መንገዶች ተጨማሪ ነገሮችን ስለሚማሩ ሰላማዊ ሁኔታ ይሰፍናል። (ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ራእይ 20:12) ቤቶችን በመገንባትና ምድርን በመግዛት ረገድ ብዙ የሚሠራ ሥራ ይኖራል። (ኢሳይያስ 65:17-25) ሙታን ወደ ሕይወት ተመልሰው ቤተሰቦች እንደገና ሲዋሃዱ የሚኖረውን ደስታ እስቲ አስቡት! (ዮሐንስ 5:28, 29) ከመጨረሻው ፈተና በኋላ ክፋት የሚባል ነገር በሙሉ ተጠራርጎ ይጠፋል። (ራእይ 20:7-10) ከዚህ በኋላ ምድር ለዘላለም ‘ከጥፋት ባርነት ነፃ ወጥተው የአምላክን ልጆች ክብር በተጎናጸፉ’ ፍጹማን ሰዎች ትሞላለች።
[የግርጌ ማስታወሻ]
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ‘የሕይወትን ውኃ በነፃ መውሰድ’ ማለት ምን ማለት ነው?
◻ ተስፋችን ሰማያዊም ይሁን ምድራዊ አምላክን የምናመሰግንባቸው ምን ምክንያቶች አሉን?
◻ ሁላችንም በየትኛው ዓመታዊ በዓል ላይ መገኘት ይኖርብናል?
◻ ለአብዛኞቹ የይሖዋ ሕዝቦች የወደፊቱ ጊዜ ምን ተስፋ ይዞላቸዋል?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ‘የሕይወትን ውኃ በነፃ’ መውሰድ ጀምረዋል። አንተስ ከእነርሱ አንዱ ነህን?