የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
አምላክ በአላስካ የተዘራው ዘር እንዲያድግ እያደረገ ነው
በበረዶ ተሸፍና ያለች አንዲት ትንሽ ዘር ሥር ሰድዳ የምታድግበትን ጊዜ እየተጠባበቀች ነው። ለሦስት ወር ብቻ በሚቆየው የአላስካ አጭር የበጋ ወቅት ሦስት ሚሊ ሜትር ስፋት ያላት አንዲት የጎመን ዘር እስከ 40 ኪሎ ግራም ድረስ ታድጋለች! አዎን፣ በአንድ ወቅት በብዙዎች ዘንድ እንደ ጠፍ እና ምንም ጥቅም እንደሌለው ይታሰብ የነበረው ይህ ምድር የተትረፈረፈ ምርት ሊሰጥ ይችላል።
ይህ አባባል በአላስካ ላለው መንፈሳዊ መስክ ይበልጥ ይሠራል። የክረምቱ ወራት ረዥም በሆነበት በዚያ አገር የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥቱን ዘር መዝራታቸውን ቀጥለዋል። እንደሌሎቹ የምድር ክፍሎች ሁሉ አምላክ ለም በሆነ ልብ ውስጥ ዘሩ እንዲያድግ ያደርጋል።—1 ቆሮንቶስ 3:6, 7
● ትምህርት ቤት በሚያደርሳቸው አውቶቡስ ተሳፍረው በሚሄዱበት ጊዜ ቨኔሰ የተባለች ወጣት ምሥክር አብራት የምትማር አን የምትባል አንዲት ወጣት ሁልጊዜ ለብቻዋ እንደምትቀመጥ አስተዋለች። አን ያዘነች ትመስላለች። ስለዚህ ቨኔሰ፣ አን አብራት እንድትቀመጥ ጋበዘቻት። አን ማዘንዋ ምንም አያስደንቅም! እናትዋ በልብ ድካም የሞተችባት ሲሆን ከዚያ ብዙም ሳይቆይ አባቷ ደግሞ በካንሰር በሽታ ሞቶባታል። አን ከዘመዶችዋ ጋር በአላስካ የምትኖረው በዚህ ምክንያት ነው።
አንድ ቀን ቅዳሜ ዕለት ቨኔሰ በመስክ አገልግሎት ላይ ሳለች በቅርብ የተዋወቀቻት ጓደኛዋ ቤት ጎራ አለችና አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን? የተባለውን ብሮሹር ሰጠቻት። በሚቀጥለው ሰኞ ትምህርት ቤት ውስጥ አን ወጣትዋን ምሥክር ትፈልጋት ጀመር። አን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች ነበሯት፤ ቨኔሰ ጥያቄዎችዋን ሁሉ መለሰችላት። ከዚያም አን “የጸሎት ቤታችሁ የት ነው?” ብላ ጠየቀቻት። አን በዚያው ዕለት ምሽት ለመጀመሪያ ጊዜ በመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው ስብሰባ ላይ ተገኘች።
ይህች ወላጆቿን በሞት ያጣች የ17 ዓመት ወጣት ኢየሱስ ቃል በገባው መሠረት ብዙ ‘አባቶች’ እና ‘እናቶች’ ለማግኘት ረዥም ጊዜ አልወሰደባትም። (ማቴዎስ 19:29) “የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ደስተኛዋና ፈገግታ የተላበሰችው አን ራስዋን ለይሖዋ መወሰኗን በውኃ ጥምቀት ስታሳይ መመልከት ምንኛ የሚያስደስት ነበር!
● ሰፊ በሆነው የአላስካ አርክቲክ ክልል ውስጥ ራቅ ብለው በሚገኙት አካባቢዎች (መንደሮቹ በመቶዎች በሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች በጣም ተራርቀው ይገኛሉ) የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ንብረት የሆነችው ባለ ሁለት ሞተር አውሮፕላን ከ150 በላይ በሚሆኑት መንደሮች ውስጥ የመንግሥቱን ዘር ለመዝራት ስታገለግል ቆይታለች። ሆኖም ቋሚ በሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት ሰዎች መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ርዳታ የሚያገኙት ደብዳቤ በመጻጻፍ ነው። ደብዳቤ መጻፍ ለብዙዎች አዳጋች ሥራ ስለሆነ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ የተማሪውን ፍላጎት ሕያው አድርጎ ለማቆየት እንዲችል መላ መፍጠር ይኖርበታል። ይህን ማከናወን የሚቻለው እንዴት ነው?
ምንም እንኳ ካቲ እና ኢድነ በ600 ኪሎ ሜትሮች ተራርቀው ቢኖሩም ካቲ ከኢድነ ጋር ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መርታለች። ካቲ ለማስጠናት ከምትጠቀምበት መጽሐፍ ጥያቄዎቹን ወስዳ ደብዳቤው ላይ እንዳለ ከመገልበጥ ይልቅ ከመጽሐፉ የተወሰዱትን ጥያቄዎች የያዘ ሌላ ወረቀት ታዘጋጅና የመልስ መጻፊያ ቦታ ትተዋለች። ኢድነ መልሱን ሠርታ ከላከችላት በኋላ ካቲ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘችው አንድን ነጥብ ለማብራራት ተጨማሪ ሐሳቦች በማከል የመልስ ደብዳቤ ትጽፋለች። ካቲ እንዲህ በማለት ትገልጻለች:- “ረቡዕ ምሽትን ‘ለጥናታችን’ መደብኩ፤ ለሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቀጠሮ እንደማከብር ሁሉ ይህንንም ፕሮግራም ለማክበር ጥሬአለሁ። ኢድነ መልሳ የምትልክበት አድራሻዬ የተጻፈበትና ቴምብር የተለጠፈበት ኤንቨሎፕ ከደብዳቤዬ ጋር ጨምሬ እልክላት ነበር። ደብዳቤው እስኪደርስ ሁለት ሳምንት ስለሚወስድ በደብዳቤ አማካኝነት የሚደረግ ጥናት ትንሽ ጎታታ ይመስላል።”
ደብዳቤ በመጻጻፍ ለአሥር ወራት ያክል ካጠኑ በኋላ በአንኮሬጅ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ካቲ እና ኢድነ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገናኙ የተሰማቸውን ደስታ እስቲ ገምቱ! በአላስካ ገለልተኛ በሆኑ በርካታ መንደሮች ውስጥ የሚኖሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችና ሌሎች ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በስብሰባው ላይ በመገኘታቸውም ምሥክሮቹ ተደስተው ነበር።
ምንም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ጭማሪው አዝጋሚ ቢመስልም አንዳንድ “ቡቃያዎች” ለእውነት ብርሃን በሚጋለጡበት ጊዜ በፍጥነት ያድጋሉ። በአላስካ በየዓመቱ በአማካይ ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ ይሖዋን የሚያወድሱ አዳዲሶች ይጠመቃሉ። የተዘራው ዘር እንዲያድግ በማድረጉ “ይሖዋ እናመሰግንሃለን” እንላለን።