በክርስትና ጎዳና ራስን ሲወስኑ ከገቡት ቃል ጋር ተስማምቶ በነፃነት መኖር
“የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ።”—2 ቆሮንቶስ 3:17
1. የይሖዋ ምሥክሮች ራሳቸውን የወሰኑት ለማን ነው? ሕጋዊ ማኅበራትንስ የሚጠቀሙት ለምንድን ነው?
የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታቸው ለዘላለም እንደሚዘልቅ ያምናሉ። በመሆኑም አምላክን ለዘላለም “በእውነትና በመንፈስ” ለማገልገል ተስፋ ያደርጋሉ። (ዮሐንስ 4:23, 24) እነዚህ ክርስቲያኖች ነፃ ምርጫ ያላቸው ፍጡራን እንደመሆናቸው መጠን ያለ ገደብ ራሳቸውን ለይሖዋ አምላክ ከመወሰናቸውም ሌላ ከዚሁ ውሳኔያቸው ጋር ተስማምተው ለመመላለስ ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። ይህንኑ ከዳር ማድረስ ይችሉ ዘንድ የሚደገፉት በአምላክ ቃልና በእርሱ ቅዱስ መንፈስ ላይ ነው። ምሥክሮቹ አምላክ የሰጣቸውን ነፃነት ተጠቅመው ለአምላክ ራሳቸውን የወሰኑበትን ክርስቲያናዊ ጎዳና በሙሉ ልብ ሲከተሉ የመንግሥት ‘ባለ ሥልጣኖች’ ላላቸውም ቦታ ተገቢውን አክብሮት በማሳየት ሕጋዊነት ባላቸው መንገዶችና ዝግጅቶች ይጠቀማሉ። (ሮሜ 13:1፤ ያዕቆብ 1:25) ለምሳሌ ያህል ምሥክሮቹ ሌሎች ሰዎችን በተለይ በመንፈሳዊ ነገሮች ለመርዳት ሲሉ በተለያዩ አገሮች ከሚገኙት ቢሮዎች መካከል አንዱ የሆነውን የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቢሮን እንደ ሕጋዊ መሣሪያ አድርገው ይጠቀማሉ። ይሁን እንጂ ምሥክሮቹ ራሳቸውን የወሰኑት ለአምላክ ነው እንጂ ለማንኛውም ሕጋዊ ማኅበር አይደለም፤ ራሳቸውን ለይሖዋ በመወሰን የገቡት ቃልም እስከ ዘላለም የሚዘልቅ ነው።
2. የይሖዋ ምሥክሮች የመጠበቂያ ግንብ ማኅበርና ሌሎች መሰል ሕጋዊ ማኅበራት የሚሰጡትን አገልግሎት በእጅጉ የሚያደንቁት ለምንድን ነው?
2 የይሖዋ ምሥክሮች ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ አገልጋዮቹ እንደመሆናቸው መጠን ኢየሱስ “አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ሲል የሰጠውን መመሪያ የመከተል ግዴታ አለባቸው። (ማቴዎስ 28:19, 20) ኢየሱስ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” በማለት ስለተናገረ ይህ ሥራ እስከዚህ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ድረስ ይቀጥላል። (ማቴዎስ 24:3, 14) በየዓመቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ማተሚያዎችና ሌሎች መሰል ሕጋዊ ማኅበራት በምድር ዙሪያ ለሚካሄደው የስብከት እንቅስቃሴ የሚያገለግሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ መጽሐፍ ቅዱሶችን፣ መጻሕፍትን፣ ብሮሹሮችንና መጽሔቶችን ለይሖዋ ምሥክሮች ያዘጋጃሉ። በመሆኑም እነዚህ ሕጋዊ ማኅበራት ራሳቸውን የወሰኑት የአምላክ አገልጋዮች ከውሳኔያቸው ጋር ተስማምተው እንዲቀጥሉ በመርዳት ረገድ የሚያበረክቱት ድርሻ ወደር የለውም።
3. የይሖዋ ምሥክሮች “ማኅበሩ” የሚለውን ስያሜ ቀደም ሲል ይጠቀሙት የነበረው ከምን አንጻር ነበር?
3 አንድ ሰው ምሥክሮቹ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር (እንዲያውም ብዙውን ጊዜ “ማኅበሩ” ብቻ ይላሉ) የሚለውን መጠሪያ የሚጠቀሙበት መንገድ ሲታይ እንደ ሕጋዊ ማኅበር ብቻ አድርገው እንደማያዩት ያመለክታል ብሎ ይከራከር ይሆናል። የአምልኮ ጉዳዮችን በተመለከተ የመጨረሻው ባለ ሥልጣን እንደሆነ አድርገው አይመለከቱትምን? የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ ይህን ጉዳይ እንዲህ በማለት ግልጽ አድርጎታል:- “መጠበቂያ ግንቡ [የሰኔ 1, 1938] ‘ማኅበሩ’ በማለት ሲጠቅስ ቃሉ እንዲሁ አንድን ሕጋዊ ማኅበር ብቻ ሳይሆን ይህን ሕጋዊ ማኅበር ያቋቋሙት በማኅበሩ የሚጠቀሙትን የቅቡዓን ክርስቲያኖች አካል የሚያመለክት ነው። በመሆኑም መግለጫው ታማኝና ልባም ባሪያን የሚያመለክት ነው።”a (ማቴዎስ 24:45) በአጠቃላይ ምሥክሮቹ “ማኅበሩ” የሚለውን ስያሜ የተጠቀሙበት በዚህ መንገድ ነው። እርግጥ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ለሕጋዊ ማኅበሩ የሚሠራ ስያሜ አይደለም። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ዲሬክተሮች የሚመረጡ ሲሆን ‘የታማኙ ባሪያ’ አባላት ግን በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ የተቀቡ ምሥክሮች ናቸው።
4. (ሀ) ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች አለመግባባቶችን ለማስወገድ ሲሉ ምን ዓይነት መግለጫዎችን ይጠቀማሉ? (ለ) ስያሜዎችን በተመለከተ ሚዛናዊ መሆን የሚገባን ለምንድን ነው?
4 የይሖዋ ምሥክሮች አለመግባባቶች እንዳይፈጠሩ ስለሚፈልጉ ማንነታቸው ስለሚገልጹበት መንገድ ጥንቃቄ ለማድረግ ይሞክራሉ። ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች “ማኅበሩ እንዲህ በማለት ያስተምራል” ከማለት ይልቅ “መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል” ወይም “መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሎ እንደሚያስተምር ተረድቻለሁ” የሚሉትን የመሰሉ መግለጫዎችን መጠቀምን ይመርጡ ይሆናል። በዚህ መንገድ እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክር የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን አምኖ ለመቀበል በግሉ ያደረገው ውሳኔ ጎላ ብሎ እንዲታይ ከማድረጋቸውም ሌላ የይሖዋ ምሥክሮች እንደ አንዳንድ ሃይማኖታዊ ኑፋቄዎች ፈላጭ ቆራጭ መሪዎችን የሚከተሉ ናቸው የሚለውን የተሳሳተ መልእክት ከማስተላለፍ ይቆጠባሉ። እርግጥ የምንጠቀምባቸውን የስያሜ ቃላት በሚመለከት የተሰጠው ሐሳብ ትልቅ የመከራከሪያ ርዕስ ሊሆን አይገባም። የስያሜዎችም ዋና ዓላማ አለመግባባትን ማስቀረት ነው። ክርስቲያናዊ ሚዛናዊነት ያስፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘በቃል እንዳንጣላ’ ያሳስበናል። (2 ጢሞቴዎስ 2:14, 15) ቅዱሳን ጽሑፎችም ስለዚሁ መሠረታዊ ሥርዓት ይገልጻሉ:- “እናንተ ደግሞ የተገለጠውን ቃል በአንደበት ባትናገሩ ሰዎች የምትናገሩትን እንዴት አድርገው ያስተውሉታል?”—1 ቆሮንቶስ 14:9
የአምላክ መንፈስ ብዙ ሕግ የማውጣትን አስፈላጊነት ይቀንሳል
5. በ1 ቆሮንቶስ 10:23 ላይ የተጠቀሰውን ሐሳብ ልንረዳው የሚገባን እንዴት ነው?
5 ሐዋርያው ጳውሎስ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል፣ ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም” ብሏል። ጨምሮም “ሁሉ ተፈቅዶልኛል፣ ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም” ሲል ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 10:23) ጳውሎስ የአምላክ ቃል በግልጽ የሚያወግዛቸውን ነገሮች ማድረግ ተፈቅዷል ማለቱ እንዳልነበር ግልጽ ነው። ለጥንቱ የእስራኤል ብሔር ተሰጥተው ከነበሩት 600 የሚያክሉ ሕጎች አንጻር ሲታይ ግን ለክርስትና ሕይወት መመሪያ እንዲሆኑ የተሰጡት ቀጥተኛ ሕግጋት በጣም ጥቂት ናቸው። በመሆኑም ብዙ ነገሮች ለግለሰቡ ሕሊና የተተዉ ናቸው። ራሱን ለይሖዋ የወሰነ አንድ ሰው በአምላክ መንፈስ መመራት የሚያስገኘው ነፃነት ይኖረዋል። እውነትን የራሱ ያደረገ አንድ ክርስቲያን በመጽሐፍ ቅዱስ የሰለጠነ ሕሊናውን ይጠቀማል እንዲሁም አምላክ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በሚሰጠው አመራር ላይ ይደገፋል። ይህም ራሱን የወሰነ አንድ ክርስቲያን ለራሱም ሆነ ለሌሎች ‘የሚያንጸውንና’ ‘የሚጠቅመውን’ ነገር ለመለየት ይረዳዋል። የሚያደርጋቸው ውሳኔዎች ራሱን ከወሰነለት አምላክ ጋር ያለውን የግል ዝምድና እንደሚነኩበት ይገነዘባል።
6. እውነትን የራሳችን እንዳደረግን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
6 አንድ የይሖዋ ምሥክር በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ሲሰጥ እውነትን የራሱ እንዳደረገ ያሳያል። መጀመሪያ አካባቢ በሚጠናው ጽሑፍ ላይ ያለውን ሐሳብ እያነበበ ይመልስ ይሆናል። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ እድገት በማድረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን በራሱ አባባል ለማብራራት ብቃት ይኖረዋል። በዚህ መንገድ ሌሎች ያሉትን ነገር እንደማይደግምና የራሱን የማሰብ ችሎታ እያዳበረ እንዳለ ያሳያል። ነጥቦቹን በራሱ አባባል አሳክቶ ልብ በሚነካ መንገድ ትክክለኛ የእውነት ቃላትን መግለጽ መቻሉ ደስታ የሚያመጣለት ከመሆኑም ሌላ ነገሩን እንዳመነበት ያሳያል።—መክብብ 12:10፤ ከሮሜ 14:5 ጋር አወዳድር።
7. የይሖዋ አገልጋዮች በነፃነት ያደረጓቸው ውሳኔዎች ምንድን ናቸው?
7 የይሖዋ ምሥክሮችን ለሥራ የሚያንቀሳቅሳቸው ለአምላክና ለሌሎች ሰዎች ያላቸው ፍቅር ነው። (ማቴዎስ 22:36-40) እርስ በርሳቸው የክርስቶስን በመሰለ ፍቅር የተሳሰሩ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ኅብረት መሆናቸው አይካድም። (ቆላስይስ 3:14፤ 1 ጴጥሮስ 5:9) ይሁን እንጂ እያንዳንዳቸው የመምረጥ ነፃነት ያላቸው ፍጡራን እንደመሆናቸው መጠን የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለማወጅ፣ ከፖለቲካ ገለልተኛ ለመሆን፣ ከደም ለመራቅ፣ ከአንዳንድ የመዝናኛ ዓይነቶች ለመቆጠብ እንዲሁም ከመጽሐፍ ቅዱስ የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምተው ለመኖር የየግላቸውን ውሳኔ ያደርጋሉ። እነዚህ በሌላ ወገን የተጫኑባቸው ውሳኔዎች አይደሉም። እነዚህ ውሳኔዎች የይሖዋ ምሥክር ለመሆን የሚያስቡ ሰዎች በክርስትና ጎዳና ራሳቸውን ለአምላክ ወደ መወሰን ከመድረሳቸውም በፊት ያለሌላ ወገን አስገዳጅነት ለመከተል የሚመርጡት የሕይወት ጎዳና ክፍል ናቸው።
ተጠያቂ የሚሆኑት በአስተዳደር አካሉ ፊት ነውን?
8. መብራራት የሚያስፈልገው ጥያቄ የትኛው ነው?
8 እውነተኛ ክርስቲያኖች አምላክን የሚያገለግሉት ተገደው እንዳልሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። “ጌታ [“ይሖዋ፣” NW] ግን መንፈስ ነው፤ የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ” ይላል። (2 ቆሮንቶስ 3:17) ይሁን እንጂ ይህ አባባል “ታማኝና ልባም ባሪያ” እና እርሱን የሚወክል የአስተዳደር አካል አለ ከሚለው ሐቅ ጋር እንዴት ሊስማማ ይችላል?—ማቴዎስ 24:45-47
9, 10. (ሀ) የራስነት መሠረታዊ ሥርዓት በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚሠራው እንዴት ነው? (ለ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የራስነትን መሠረታዊ ሥርዓት መከተል ምን ይጠይቅ ነበር?
9 ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ቅዱስ ጽሑፉ ስለ ራስነት መሠረታዊ ሥርዓት የሚገልጸውን ነገር ማስታወስ ይኖርብናል። (1 ቆሮንቶስ 11:3) በኤፌሶን 5:21-24 ላይ ክርስቶስ ‘የጉባኤው ራስ’ እንደሆነና ጉባኤውም ‘እንደሚገዛለት’ ተገልጿል። የይሖዋ ምሥክሮች፣ የታማኝና ልባም ባሪያ አባላት የተውጣጡት ከኢየሱስ መንፈሳዊ ወንድሞች መሆኑን ያውቃሉ። (ዕብራውያን 2:10-13) ይህ የታመነ የባሪያ ክፍል የተሾመው ለአምላክ ሕዝቦች ‘በተገቢው ጊዜ መንፈሳዊ ምግብ’ እንዲያቀርብ ነው። ክርስቶስ በዚህ የመጨረሻ ዘመን ይህንን ባሪያ ‘ባለው ሁሉ ላይ ሾሞታል።’ በመሆኑም ይህ የባሪያ ክፍል ያለው ቦታ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሁሉ ሊያከብሩት ይገባል።
10 የራስነት ሥልጣን ዓላማው አንድነት እንዲሰፍን እንዲሁም ‘ሁሉም ነገር በአግባብና በሥርዓት’ እንዲካሄድ ማድረግ ነው። (1 ቆሮንቶስ 14:40) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይህንን ለማድረግ ሲባል ከታማኝና ልባም ባሪያ መካከል ጠቅላላውን ቡድን በመወከል ጥቂት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ተመርጠው ነበር። ይህ የመጀመሪያው መቶ ዘመን የአስተዳደር አካል በበላይነት ያከናወነው ሥራ የይሖዋ ሞገስና በረከት እንደነበረው ከዚያ በኋላ የተከናወኑት ነገሮች ያረጋግጣሉ። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ይህን ዝግጅት በደስታ ተቀብለውታል። አዎን፣ ይህን ዝግጅት በደስታ የደገፉ ከመሆኑም በላይ ላስገኛቸው ግሩም ውጤቶችም አመስጋኞች ነበሩ።—ሥራ 15:1-32
11. ዛሬ ላለው የአስተዳደር አካል ሊኖረን የሚገባው አመለካከት ምንድን ነው?
11 ይህን የመሰለው ዝግጅት ዛሬም ቢሆን ዋጋማነቱ በጉልህ ይታያል። በዛሬው ጊዜ ያለው የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አሥር ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ያቀፈ ሲሆን ሁሉም በክርስቲያናዊ አገልግሎት የአሥርተ ዓመታት ተሞክሮ ያካበቱ ናቸው። የመጀመሪያው መቶ ዘመን የአስተዳደር አካል ያደርግ እንደነበረው ሁሉ ለይሖዋ ምሥክሮች መንፈሳዊ መመሪያ ይሰጣል። (ሥራ 16:4) የይሖዋ ምሥክሮች እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች አምልኳቸውን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መመሪያ ለማግኘት ደስ እያላቸው በአስተዳደር አካል ውስጥ ወዳሉት የጎለመሱ ወንድሞች ይሄዳሉ። የአስተዳደር አካል አባላት እንደ ሌሎቹ ክርስቲያኖች ሁሉ የይሖዋና የክርስቶስ ባሪያዎች ቢሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይነግረናል:- “ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ፤ እነርሱ ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው፣ ይህንኑ በደስታ እንጂ በኃዘን እንዳያደርጉት፣ ይህ የማይጠቅማችሁ ነበርና፣ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ።”—ዕብራውያን 13:17
12. እያንዳንዱ ግለሰብ ክርስቲያን ተጠያቂ የሚሆነው በማን ፊት ነው?
12 ቅዱሳን ጽሑፎች ለአስተዳደር አካል እንዲህ ዓይነት የበላይነት ቦታ መስጠታቸው እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክር ስለሚያደርገው ነገር በአስተዳደር አካሉ ፊት ተጠያቂ ይሆናል ማለት ነውን? ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች ከጻፈው ሐሳብ እንደምንረዳው እንደዚያ ማለት አይደለም:- “በወንድምህ ላይ ስለ ምን ትፈርዳለህ? ወይስ አንተ ደግሞ ወንድምህን ስለ ምን ትንቃለህ? ሁላችን በክርስቶስ [“በአምላክ፣” NW] ፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለንና። . . . እንግዲያስ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን።”—ሮሜ 14:10-12
13. የይሖዋ ምሥክሮች የአገልግሎት እንቅስቃሴያቸውን ሪፖርት የሚያደርጉት ለምንድን ነው?
13 ይሁን እንጂ እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክር የአገልግሎት እንቅስቃሴውን ሪፖርት ያደርግ የለምን? አዎን ያደርጋል፣ ነገር ግን የዚህ ዓላማ እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክር ባለው መመሪያ መጽሐፍ ላይ በሚከተለው መልኩ ተቀምጧል:- “የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች የስብከቱ ሥራ ስላደረገው ዕድገት ሪፖርት የመስጠትና የመስማት ፍላጎት አሳይተዋል። (ማርቆስ 6:30) ሥራው ሲስፋፋ የስታቲስቲክ ሪፖርቶች ይጠናቀሩ ነበር፤ ከዚሁም ጋር በምሥራቹ ስብከት የሚካፈሉት ሰዎች ያጋጠሟቸው ጎላ ያሉ ተሞክሮዎች ይገለጹ ነበር። . . . (ሥራ 2:5-11, 41, 47፤ 6:7፤ 1:15፤ 4:4) . . . እነዚያ ታማኝ ክርስቲያን ሠራተኞች ምን እየተከናወነ እንዳለ የሚገልጹ ሪፖርቶች ሲሰሙ እንዴት ተበረታተው ይሆን! . . . በተመሳሳይም ዘመናዊው የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት ማቴዎስ 24:14 እስከ ምን ድረስ እንደ ተፈጸመ የሚገልጹ ትክክለኛ መዝገቦች ለመያዝ ይጥራል።”
14, 15. (ሀ) በ2 ቆሮንቶስ 1:24 ላይ ያለው ሐሳብ ለአስተዳደር አካል የሚሠራው እንዴት ነው? (ለ) እያንዳንዱ ክርስቲያን ውሳኔ የሚያደርገው ምንን መሠረት በማድረግ መሆን ይኖርበታል? ይህንንስ የሚያደርገው ምን በመገንዘብ ነው?
14 የአስተዳደር አካል ፍቅራዊ ዝግጅት ከመሆኑም ሌላ ልንመስለው የሚገባ የእምነት አብነት ነው። (ፊልጵስዩስ 3:17፤ ዕብራውያን 13:7) የክርስቶስን ምሳሌ በጥብቅ በመከተል “ለደስታችሁ ከእናንተ ጋር የምንሠራ ነን እንጂ፣ በእምነታችሁ በእናንተ ላይ የምንገዛ አይደለንም። በእምነታችሁ ቆማችኋልና” የሚሉትን የጳውሎስ ቃላት ያስተጋባሉ። (2 ቆሮንቶስ 1:24) የአስተዳደር አካል ያሉትን ሁኔታዎች በማስተዋል የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ሥራ ላይ ማዋል ያለውን ጠቀሜታ ጎላ አድርጎ ይገልጻል፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባር ላይ የሚውሉበትን መንገድ ይጠቁማል፣ ስውር አደጋዎችን ያስጠነቅቃል እንዲሁም ‘አብረው ለሚሠሩት’ አስፈላጊውን ማበረታቻ ይሰጣል። በዚህ መንገድ የተጣለበትን ክርስቲያኖችን የመመገብ ኃላፊነት ይወጣል፣ ደስታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ ይረዳቸዋል እንዲሁም ጸንተው እንዲቆሙ እምነታቸውን ይገነባል።—1 ቆሮንቶስ 4:1, 2፤ ቲቶ 1:7-9
15 አንድ የይሖዋ ምሥክር የአስተዳደር አካሉ ያቀረበውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክር ተከትሎ ውሳኔ ቢያደርግ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ባጠናበት ወቅት ይህን ማድረጉ ተገቢ እንደሆነ ያመነ በመሆኑ በገዛ ፈቃዱ የሚያደርገው ነገር ይሆናል። እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክር የሚያደርጋቸው ውሳኔዎች ራሱን ከወሰነለት አምላክ ጋር ያለውን የግል ዝምድና እንደሚነኩ ከልብ በመገንዘብ የአስተዳደር አካል የሚያቀርበውን ዋጋማ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ሥራ ላይ እንዲያውል የአምላክ ቃል ራሱ ግፊት ያሳድራል።—1 ተሰሎንቄ 2:13
ተማሪዎችና ወታደሮች
16. አኗኗርን የሚመለከቱት ውሳኔዎች ለእያንዳንዱ ግለሰብ የተተዉ ቢሆንም አንዳንዶች የሚወገዱት ለምንድን ነው?
16 ይሁን እንጂ በአኗኗሩ ረገድ ምን ማድረግ እንዳለበት የሚወስነው ራሱ ግለሰቡ ከሆነ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች የሚወገዱት ለምንድን ነው? ይህ ኃጢአት ሊያስወግደው ይገባል ብሎ በጭፍን የሚወስን ሰው አይኖርም። ከዚህ ይልቅ ግን የክርስቲያን ጉባኤ አባል የሆነ አንድ ሰው በአንደኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ አምስት ውስጥ የተዘረዘሩትን የመሰሉ ከባድ ኃጢአቶች ፈጽሞ ንስሐ ሳይገባ ከቀረ ቅዱሳን ጽሑፎች ግለሰቡ እንዲወገድ ያዝዛሉ። ከዚህ አንጻር አንድ ክርስቲያን ዝሙት በመፈጸሙ ምክንያት ሊወገድ ቢችልም ይህ እርምጃ የሚወሰደው አፍቃሪ የሆኑት እረኞች የሚሰጡትን መንፈሳዊ እርዳታ ለመቀበል አሻፈረኝ ካለ ብቻ ነው። (1 ቆሮንቶስ 5:1-5, 9-13) ከዚህም በላይ ይህንን ክርስቲያናዊ ልማድ የሚከተሉት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ አይደሉም። ዚ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪሊጅን እንዲህ ይላል:- “እያንዳንዱ ማኅበረሰብ የብዙኃኑን ደህንነት ስጋት ላይ ከሚጥሉ ሥርዓት አልባ አባላት ራሱን የመጠበቅ መብት አለው። ሃይማኖታዊ ወገኖች ብዙውን ጊዜ ይህን መብት የሚያስጠብቁት ግለሰቡ [በመገለሉ ምክንያት] የሚጣልበት እገዳ ከአምላክ ጋር ያለውን ግንኙነት ይነካበታል በሚል እምነት ነው።”
17, 18. (ሀ) በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ (ለ) በአንድ ወታደራዊ ተቋም ውስጥ የሚኖረውን መመሪያ እንደ ምሳሌ በመጠቀም የውገዳን ሥርዓት ተገቢነት እንዴት ማስረዳት ይቻላል?
17 የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ናቸው። (ኢያሱ 1:8፤ መዝሙር 1:2፤ ሥራ 17:11) የአስተዳደር አካል የሚያቀርበው መጽሐፍ ቅዱሳዊ የትምህርት መርሐ ግብር የትምህርት ቦርድ ከሚያወጣው ሥርዓተ ትምህርት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። የሚሰጠው ትምህርት ምንጭ የትምህርት ቦርዱ ባይሆንም ሥርዓተ ትምህርቱን ይነድፋል፣ የማስተማሪያ ዘዴዎቹ ምን መሆን እንዳለባቸው ይወስናል እንዲሁም አስፈላጊ መመሪያዎችን ያስተላልፋል። ከተቋሙ መስፈርቶች ጋር ተስማምቶ ለመሄድ አሻፈረኝ የሚል፣ ሌሎች ተማሪዎች ላይ ችግር የሚፈጥር ወይም በትምህርት ቤቱ ላይ ነቀፋ የሚያመጣ ተማሪ ካለ ከትምህርት ቤቱ ሊባረር ይችላል። የትምህርት ቤቱ ባለ ሥልጣናት ለመላው ተማሪ ጥቅም ሲሉ እርምጃ የመውሰድ ሥልጣን አላቸው።
18 የይሖዋ ምሥክሮች ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ‘መልካሙን የእምነት ገድል እንዲጋደሉ’ መመሪያ የተሰጣቸው የኢየሱስ ክርስቶስ ወታደሮችም ናቸው። (1 ጢሞቴዎስ 6:12፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:3) ለአንድ ክርስቲያን ወታደር የማይገባ ጠባይ ማንጸባረቅ መለኮታዊ ሞገስ ሊያሳጣ እንደሚችል የታወቀ ነው። እያንዳንዱ ግለሰብ የመምረጥ ነፃነት ያለው እንደመሆኑ መጠን አንድ ክርስቲያን ወታደር እንደ ምርጫው ውሳኔ ማድረግ ይችላል፤ ይሁን እንጂ ውሳኔው የሚያስከትለውን ውጤት መቀበል ይኖርበታል። ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል ገልጿል:- “የሚዘምተው ሁሉ ለጦር ያስከተተውን ደስ ያሰኝ ዘንድ ትዳር በሚገኝበት ንግድ ራሱን አያጠላልፍም። ደግሞም በጨዋታ የሚታገል ማንም ቢሆን፣ እንደሚገባ አድርጎ [“በደንቡ መሠረት፣” የ1980 ትርጉም] ባይታገል፣ የድሉን አክሊል አያገኝም።” (2 ጢሞቴዎስ 2:4, 5) በአስተዳደር አካሉ ውስጥ ያሉትን ጨምሮ ሁሉም የጎለመሱ ክርስቲያኖች ለዘላለም ሕይወት ሽልማት ይበቁ ዘንድ ‘ደንቡን’ በመጠበቅ ረገድ በሙሉ ልባቸው የመሪያቸውን የኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣን ይደግፋሉ።—ዮሐንስ 17:3፤ ራእይ 2:10
19. በክርስትና ጎዳና ራስን መወሰን ምን እንደሚመስል እውነታዎቹን ከመረምርን በኋላ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
19 እነዚህ እውነታዎች የይሖዋ ምሥክሮች የሰዎች ባሪያዎች ሳይሆኑ የአምላክ አገልጋዮች እንደሆኑ በግልጽ አያሳዩምን? በክርስቶስ አማካኝነት ነፃነት የተጎናጸፉ ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች እንደመሆናቸው መጠን በአምላክ ጉባኤ ውስጥ ከወንድሞቻቸው ጋር በአንድነት ሲያገለግሉ የአምላክ ቃልና መንፈሱ ሕይወታቸውን እንዲመራው ይፈቅዳሉ። (መዝሙር 133:1) ይህንን ሐቅ የሚያረጋግጡት ማስረጃዎች ምሥክሮቹ ብርታታቸውን ከማን እንዳገኙት የሚነሣውን ጥርጣሬ ሁሉ የሚያስወግድ ሊሆን ይገባል። ከመዝሙራዊው ጋር እንደሚከተለው በማለት ሊዘምሩ ይችላሉ:- “እግዚአብሔር ኃይሌና ጋሻዬ ነው፤ ልቤ በእርሱ ታመነ እኔም ተረዳሁ፤ ሥጋዬም ደስ ይለዋል፣ ፈቅጄም አመሰግነዋለሁ።”—መዝሙር 28:7
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በ1993 ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኀበር የተዘጋጀ።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበርና መሰል ሕጋዊ ማኅበራት የይሖዋ ምሥክሮችን የሚረዷቸው በምን መንገድ ነው?
◻ ክርስቲያኖች ከይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል ተግባር ተጠቃሚ የሚሆኑት እንዴት ነው?
◻ የይሖዋ ሕዝቦች የአገልግሎት እንቅስቃሴያቸውን ሪፖርት የሚያደርጉት ለምንድን ነው?
◻ አንድ ራሱን ለአምላክ የወሰነ ክርስቲያን መወገዱ ተገቢ የሚሆንባቸው ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጀመሪያው መቶ ዘመን የአስተዳደር አካል የመሠረተ ትምህርት አንድነት እንዲጠበቅ አድርጓል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በምድር ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በክርስቶስ በኩል በተገኘው አርነት ነፃ ወጥተዋል