የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 4/15 ገጽ 5-8
  • የወደፊቱ ዕጣህ ምን ይሆን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የወደፊቱ ዕጣህ ምን ይሆን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የወደፊቱ ጊዜ አስቀድሞ ተጽፏል
  • አምላክ አስቀድሞ ሁሉንም ነገር ያውቃል?
  • ሁለቱ የሰው ዘር የወደፊት ዕጣዎች
  • የወደፊቱ ዕጣህ አስቀድሞ ተወስኗል?
    ንቁ!—2009
  • ዕድል ተወስኗል የሚለው እምነት ከአምላክ ፍቅር ጋር ሊስማማ ይችላልን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ጥሩ ሰዎች መጥፎ ነገሮች ይደርሱባቸዋል—ለምን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2014
  • ይሖዋ “የመጨረሻውን ከመጀመሪያው” ይናገራል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 4/15 ገጽ 5-8

የወደፊቱ ዕጣህ ምን ይሆን?

አምላክ ሁሉን አዋቂ ማለትም ያለፈውን፣ የአሁኑንና የወደፊቱን የሚያውቅ ከሆነ ሁሉም ነገሮች አምላክ ባቀደላቸው ጊዜ እንዲፈጸሙ ዕድላቸው የተወሰነ አይደለምን? አምላክ የእያንዳንዱን ሰው የሕይወት ሒደትና የመጨረሻ ዕጣ አስቀድሞ የሚያውቅና የሚወስን ከሆነ የሕይወት ሒደታችንን ማለትም የወደፊት ዕጣችንን የመምረጥ ነፃነት አለን ለማለት ይቻላል?

እነዚህ ጥያቄዎች ለዘመናት ሲያከራክሩ ኖረዋል። እሰጥ አገባው አሁንም ዋና ዋና ሃይማኖቶችን ከፋፍሎ ይገኛል። አምላክ የወደፊቱን ጊዜ አስቀድሞ የማየት ችሎታው ከሰብዓዊ የምርጫ ነፃነት ጋር ሊጣጣም ይችላልን? መልሶቹን ለማግኘት ትኩረታችንን ማዞር ያለብን ወዴት ነው?

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አምላክ በቃል አቀባዮቹ በነቢያት ባጻፈው ቃሉ አማካኝነት ከሰው ልጅ ጋር ግንኙነት ያደርግ ነበር በሚለው ሐሳብ ይስማማሉ። ለምሳሌ ያህል ታውራ (ቶራህ፣ ሕጉ ወይም አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት)፣ ዛቡር (መዝሙራት) እንዲሁም ኢንጂል (ወንጌል፣ ግሪክኛ የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች ወይም “አዲስ ኪዳን”) እና ለእስራኤል ነቢያት የተገለጡትን ጨምሮ ራእዮች ከአምላክ እንደሚመጡ ቁራን ይናገራል።

በክርስቲያን የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት . . . ይጠቅማል” የሚል እናነባለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:​16) የምናገኘው ማንኛውም መመሪያ ወይም ትምህርት ሙሉ በሙሉ ከራሱ ከአምላክ የመጣ መሆን አለበት። ታዲያ ቀደም ሲል የነበሩ የአምላክ ነቢያት የጻፏቸውን ጽሑፎች መመርመራችን ጥበብ አይሆንምን? ስለ ወደፊት ዕጣችን ምን ገልጸዋል?

የወደፊቱ ጊዜ አስቀድሞ ተጽፏል

ቅዱሳን ጽሑፎችን ያነበበ ማንኛውም ሰው እነዚህ ጽሑፎች ቃል በቃል በመቶ የሚቆጠሩ ትንቢቶችን ያቀፉ መሆናቸውን ሊያውቅ ይችላል። የጥንቷ ባቢሎን መውደቅ፣ የኢየሩሳሌም መልሶ መገንባት (ከስድስተኛው እስከ አምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ) እንዲሁም የሜዶ ፋርስና የግሪክ ጥንታዊ ነገሥታት መነሣትና መውደቅ የሚናገሩ ታሪካዊ ክንውኖች ሁሉ በዝርዝር የተተነበዩ ነበሩ። (ኢሳይያስ 13:​17-19፤ 44:​24–45:​1፤ ዳንኤል 8:​1-7, 20-22) ወደፊት የሚሆነውን ነገር አስቀድሞ የማየትም ሆነ የመወሰን ኃይል ያለው አምላክ ብቻ ስለሆነ የእነዚህ ትንቢቶች መፈጸም ቅዱሳን ጽሑፎች የአምላክ ቃል መሆናቸውን ከሚያሳዩት ጠንካራ ማስረጃዎች መካከል አንዳንዶቹ ናቸው። በዚህ አነጋገር ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስቀድሞ የተጻፈውን ነገር መዝግበው ይዘዋል ማለት ነው።

አምላክ ራሱ እንዲህ ብሏል:- “እኔ አምላክ ነኝና፣ ሌላም የለምና የቀድሞውን የጥንቱን ነገር አስቡ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም። በመጀመሪያ መጨረሻውን፣ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ፤ ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴንም ሁሉ እፈጽማለሁ እላለሁ። . . . ተናግሬአለሁ እፈጽምማለሁ፤ አስቤአለሁ አደርግማለሁ።” (ኢሳይያስ 46:​9-11፤ 55:​10, 11) አምላክ ለጥንቶቹ ነቢያት ራሱን ያስተዋወቀው ይሖዋ በሚለው ስም ሲሆን ይህም ቃል በቃል ሲተረጎም “እንዲሆን ያደርጋል” ማለት ነው።a (ዘፍጥረት 12:​7, 8 NW፤ ዘጸአት 3:​13-15 NW፤ መዝሙር 83:​18 NW) አምላክ ቃሉን የሚፈጽምና ዓላማውን ሁልጊዜ ከግቡ የሚያደርስ እንደሆነ አድርጎ ራሱን ገልጧል።

ስለዚህ አምላክ አስቀድሞ በማወቅ ኃይሉ ተጠቅሞ ዓላማዎቹን ከግብ ያደርሳል። ክፉዎችን ከሚመጣባቸው ፍርድ ለማስጠንቀቅና ለአገልጋዮቹ ደግሞ የመዳን ተስፋ ለመስጠት ይህን ችሎታውን ብዙ ጊዜ ተጠቅሞበታል። ይሁን እንጂ አምላክ ይህን ኃይሉን ያለ ገደብ ይጠቀምበታል? አምላክ አስቀድሞ በማወቅ ችሎታው ላለመጠቀም የመረጠባቸው ነገሮች ስለ መኖራቸው በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተገልጾ የሚገኝ ማረጋገጫ ይኖር ይሆን?

አምላክ አስቀድሞ ሁሉንም ነገር ያውቃል?

ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚለውን እምነት ደግፈው የሚቀርቡ የመከራከሪያ ነጥቦች የተመሠረቱት አምላክ ሁሉንም ነገር አስቀድሞ የማወቅና ወደፊት የሚከሰቱ ነገሮችን የመወሰን የማይገሰስ ኃይል ስላለው እያንዳንዱ ግለሰብ ወደፊት የሚያደርጋቸውን ነገሮች ጨምሮ ሁሉንም ነገር አስቀድሞ ማወቅ አለበት በሚለው አስተሳሰብ ላይ ነው። ይሁን እንጂ ይህ አስተሳሰብ ተቀባይነት አለውን? አምላክ በቅዱሳን ጽሑፎቹ ውስጥ ያጻፈው ነገር የሚያመለክተው የዚህን ተቃራኒ ነው።

ለምሳሌ ያህል አምላክ ልጁን ይስሐቅን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብለት በመጠየቅ “እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው” በማለት ቅዱሳን ጽሑፎች ይናገራሉ። አብርሃም ይስሐቅን ሊሠዋ ሲል አምላክ አስቆመውና “አንድ ልጅህን ለእኔ አልከለከልህምና እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደሆንህ አሁን አውቄአለሁ” አለው። (ዘፍጥረት 22:​1-12፤ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) አምላክ፣ አብርሃም ይህን ትእዛዝ እንደሚታዘዝ አስቀድሞ የሚያውቅ ቢሆን ኖሮ እንዲህ ብሎ ይናገር ነበር? ፈተናውስ ሐቀኛ ይሆን ነበር?

ከዚህም በላይ የጥንት ነቢያት አምላክ በተደጋጋሚ ጊዜያት አንድን ነገር በማድረጉ ምክንያት ወይም ለማድረግ በማሰቡ ምክንያት “ጸጸት እንደተሰማው” ዘግበዋል። ለምሳሌ ያህል አምላክ “ሳኦል[ን] . . . ስላነገሥሁት ተጸጸትሁ [ናቻም ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የተወሰደ]” ብሏል። (1 ሳሙኤል 15:​11, 35፤ ከኤርምያስ 18:​7-10ና ከዮናስ 3:​10 ጋር አወዳድር።) አምላክ ፍጹም ነው። ስለሆነም ሳኦል የእስራኤል የመጀመሪያው ንጉሥ እንዲሆን አምላክ በመምረጡ ስህተት መሥራቱን እነዚህ ጥቅሶች አያመለክቱም። ከዚህ ይልቅ ሳኦል ታማኝነቱን በማጉደሉና ታዛዥ ባለመሆኑ ምክንያት አምላክ ማዘኑን የሚገልጹ መሆን አለባቸው። አምላክ የሳኦልን ድርጊቶች አስቀድሞ የሚያውቅ ቢሆን ኖሮ እንዲህ ብሎ ስለ ራሱ መናገሩ ትርጉም የለሽ ይሆን ነበር።

ይኸው ሐረግ እጅግ ጥንታዊ በሆኑት ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተጠቅሶ የሚገኝ ሲሆን ስለ ኖኅ ዘመን ሲናገር እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፣ በልቡም አዘነ። እግዚአብሔርም:- የፈጠርሁትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ፣ . . . ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቼአለሁና አለ።” (ዘፍጥረት 6:​6, 7) እዚህ ላይም የሰው ድርጊቶች አስቀድመው በአምላክ የተወሰኑ አለመሆናቸውን ለማየት ይቻላል። አምላክ የተጸጸተው፣ ያዘነውና ስሜቱ የተጎዳው የእርሱ ሥራዎች ስህተት ስለነበረባቸው ሳይሆን የሰው ክፋት በመበራከቱ ምክንያት ነው። ፈጣሪ ከኖኅና ከቤተሰቡ በስተቀር ሁሉንም የሰው ልጅ ማጥፋቱ አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘው ተጸጽቷል። አምላክ “ኃጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል።​—⁠ሕዝቅኤል 33:​11፤ ከዘዳግም 32:​4, 5 ጋር አወዳድር።

ስለዚህ አምላክ አዳም ወደ ኃጢአት እንደሚወድቅና ይህ ድርጊቱ በሰብዓዊው ቤተሰብ ላይ አስከፊ ውጤት እንደሚኖረው አስቀድሞ ያውቅ ነበር፤ እንዲህ እንዲሆንም የወሰነው ራሱ ነው ማለት ነውን? እስከ አሁን የተመለከትነው ነገር ይህ እውነት ሊሆን እንደማይችል ያሳያል። ከዚህም በላይ አምላክ ይህን ሁሉ ነገር አስቀድሞ የሚያውቅ ቢሆን ኖሮ አዳምን በፈጠረበት ጊዜ የኃጢአት ጠንሳሽ ይሆን ነበር፤ እንዲሁም ሆን ብሎ የሰው ልጆች ክፋትና መከራ እንዲደርስባቸው በማድረጉ ተጠያቂ ይሆን ነበር። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይህ አምላክ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ስለ ራሱ ከጠቀሰው ነገር ጋር በፍጹም አይጣጣምም። እሱ የፍቅርና የፍትሕ አምላክ ስለሆነ ክፋትን ይጠላል።​—⁠መዝሙር 33:​5፤ ምሳሌ 15:​9፤ 1 ዮሐንስ 4:​8

ሁለቱ የሰው ዘር የወደፊት ዕጣዎች

ቅዱሳን ጽሑፎች አምላክ በግለሰብ ደረጃ የወደፊት ዕጣችንን አስቀድሞ የወሰነ መሆኑን አይገልጹም። ከዚህ ይልቅ አምላክ የሰው ዘር ሁለት የወደፊት ዕጣዎች እንዳሉት አስቀድሞ መናገሩን ይገልጻሉ። አምላክ ለእያንዳንዱ ሰው የወደፊት ዕጣው የትኛው ሊሆን እንደሚችል የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶታል። ነቢዩ ሙሴ ከረጅም ጊዜ በፊት ለእስራኤላውያን እንዲህ ብሏል:- “በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን በረከትንና መርገምን [አስቀምጫለሁ]፤ . . . እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ፤ . . . እርሱ ሕይወትህ የዘመንህም ርዝመት ነውና አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድደው ትጠባበቀውም ቃሉንም ትሰማ ዘንድ ምረጥ።” (ዘዳግም 30:​19, 20 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) የአምላክ ነቢይ የነበረው ኢየሱስ እንዲህ ሲል አስቀድሞ አስጠንቅቋል:- “በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፣ መንገዱም ትልቅ ነውና፣ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፣ መንገዱም የቀጠነ ነውና፣ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።” (ማቴዎስ 7:​13, 14) ሁለት መንገዶች፣ ሁለት ዕጣዎች። የወደፊት ዕጣችን በራሳችን ድርጊቶች ላይ የተመካ ነው። አምላክን መታዘዝ ሕይወት ማለት ሲሆን እሱን አለመታዘዝ ደግሞ ሞት ማለት ነው።​—⁠ሮሜ 6:​23

አምላክ “በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል።” ምክንያቱም “ቀን ቀጥሮአልና፣ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው።” (ሥራ 17:​30, 31) በኖኅ ዘመን የነበረው አብዛኛው የሰው ዘር አምላክን ላለመታዘዝ በመምረጡ እንደጠፋ ሁሉ በዛሬው ጊዜ የሚገኘው ብዙሃኑ ኅብረተሰብ የአምላክን ትእዛዛት አያከብርም። ሆኖም አምላክ ማን መጥፋት እንዳለበት ወይም ማን መዳን እንዳለበት አስቀድሞ አልወሰነም። እንዲያውም አምላክ “ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ” እንደሚፈልግ የአምላክ ቃል ይናገራል። (2 ጴጥሮስ 3:​9) ሌላው ቀርቶ እጅግ ክፉ የነበሩ ሰዎች በአምላክ ፊት ተቀባይነት ለማግኘት ሲሉ ንስሐ ሊገቡ፣ ታዛዦች ሊሆኑና አስፈላጊ የሆኑ ለውጦችን ሊያደርጉ ይችላሉ።​—⁠ኢሳይያስ 1:​18-20፤ 55:​6, 7፤ ሕዝቅኤል 33:​14-16፤ ሮሜ 2:​4-8

አምላክ ታዛዥ ለሆኑ ሰዎች በሙሉ ከክፋት፣ ከዓመፅና ከጦርነት በጸዳችና ሰላም በሚሰፍንባት ገነት ውስጥ ከረሃብ፣ ከስቃይ፣ ከሕመምና ከሞት ነፃ የሆነ ዘላለማዊ ሕይወት ሊሰጣቸው ቃል ገብቷል። (መዝሙር 37:​9-11፤ 46:​9፤ ኢሳይያስ 2:​4፤ 11:​6-9፤ 25:​6-8፤ 35:​5, 6፤ ራእይ 21:​4) ሙታንም እንኳ ትንሣኤ አግኝተው አምላክን የማገልገል አጋጣሚ ይሰጣቸዋል።​—⁠ዳንኤል 12:​2፤ ዮሐንስ 5:​28, 29

“ቅንነትን ጠብቅ፣ ጽድቅንም እይ፤ ለሰላም ሰው ቅሬታ አለውና። በደለኞች በአንድነት ይጠፋሉ፤ የኃጢአተኞች ቅሬታ ይጠፋል” በማለት አምላክ ይናገራል። (መዝሙር 37:​37, 38) የወደፊት ዕጣህ ምን ይሆን? ሁሉም ነገር የተመካው በአንተ ላይ ነው። የዚህ መጽሔት አሳታሚዎች የወደፊት ሕይወትህ አስደሳችና ሰላም የሰፈነበት እንዲሆን የሚያስችልህን ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት ደስተኞች ናቸው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ይሖዋ የሚለው ስም በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከ7,000 ጊዜ በላይ ተጠቅሶ ይገኛል፤ በኅዳር 1, 1993 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ከሁሉ የሚበልጠውን ስም ምሥጢር መግለጥ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አምላክ የወደፊቱን ጊዜ አስቀድሞ በማወቅ ችሎታው ተጠቅሞ ዓላማዎቹን ከግብ ያደርሳል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አምላክ አብርሃም ልጁን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ እንደሚሆን አስቀድሞ የሚያውቅ ቢሆን ኖሮ ፈተናው ሐቀኛ ይሆን ነበርን?

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ “ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ” ይፈልጋል። 2 ጴጥሮስ 3:​9

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ