የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 4/15 ገጽ 9-14
  • እምነትና የወደፊት ዕጣህ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • እምነትና የወደፊት ዕጣህ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ያለፈው ጊዜ ምን ይመስል ነበር?
  • ሰብዓዊ መፍትሔ የለም
  • የይሖዋ ምሥክሮች የወደፊቱን ጊዜ የሚመለከቱት እንዴት ነው?
  • የሰብዓዊ አገዛዝ የወደፊት ዕጣ
  • ይሖዋ በሰጠው ተስፋ ላይ እምነታችሁን ጣሉ
  • ይሖዋ ዓላማውን እንደሚፈጽም ሙሉ እምነት ይኑራችሁ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ወደ ፊት ምን ይጠብቀኝ ይሆን?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች
  • የአምላክ ዓላማ በቅርቡ ይፈጸማል
    የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? እንዴትስ ልታገኘው ትችላለህ?
  • የአምላክ መንግሥት—አዲሱ የምድር አገዛዝ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 4/15 ገጽ 9-14

እምነትና የወደፊት ዕጣህ

“እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ . . . ነው።”​—⁠ዕብራውያን 11:​1

1. ብዙ ሰዎች የወደፊቱ ጊዜ ምን ዓይነት እንዲሆን ይፈልጋሉ?

ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ ትፈልጋላችሁ? አብዛኞቹ ሰዎች ይፈልጋሉ። የወደፊቱ ሕይወታቸው ከፍርሃት ነፃ የሆነና ሰላም የሰፈነበት እንዲሆንላቸው፣ እንዲሁም የተደላደለ ኑሮ፣ ፍሬያማና አርኪ ሥራ፣ ጥሩ ጤንነትና ረዥም ዕድሜ እንዲኖራቸው ይመኛሉ። በታሪክ ውስጥ ያለፈ እያንዳንዱ ትውልድ እነዚህን ነገሮች ይፈልግ እንደነበረ ምንም አያጠራጥርም። በተለይ ደግሞ ዛሬ በችግር በተሞላ በዚህ ዓለም ውስጥ እንዲህ ያለው ሁኔታ ከምንጊዜውም በበለጠ መጠን ተፈላጊ ነው።

2. አንድ ባለ ሥልጣን ስለ ወደፊቱ ጊዜ የነበራቸውን አመለካከት የገለጹት እንዴት ነበር?

2 የሰው ልጅ ወደ 21ኛው መቶ ዘመን እየቀረበ ባለበት በአሁኑ ጊዜ የወደፊቱ ጊዜ ምን እንደሚመስል ለማወቅ የሚያስችል አንድ ዓይነት መንገድ ይኖር ይሆን? አንደኛው መንገድ ፓትሪክ ሄንሪ የተባሉት አሜሪካዊ ባለ ሥልጣን ከ200 ዓመት በፊት የተናገሩት ነው። “የወደፊቱን ጊዜ ለመመዘን ያለፈውን ጊዜ ከመመልከት የተሻለ ዘዴ አይኖርም” ብለዋል። በዚህ አመለካከት መሠረት የሰብዓዊው ቤተሰብ የወደፊት ዕጣ ሰው ከዚህ ቀደም ካደረጋቸው ነገሮች በስፋት ለማወቅ ይቻላል ማለት ነው። ብዙዎችም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ።

ያለፈው ጊዜ ምን ይመስል ነበር?

3. ስለ ወደፊቱ ጊዜ የታሪክ ዘገባ ምን ያመለክታል?

3 የወደፊቱ ጊዜ ያለፈው ነጸብራቅ ከሆነ ብሩሕ ተስፋ እንዲኖራችሁ የሚያስችል ምክንያት አለ? ባለፉት የታሪክ ዘመናት በየተራ ለተነሱት ትውልዶች የወደፊቱ ጊዜ እየተሻሻለላቸው መጥቷል? በፍጹም አልተሻሻለም። የሰው ልጆች ባለፉት በሺህ የሚቆጠሩ ዘመናት የተለያዩ ነገሮችን በተስፋ የተጠባበቁ ከመሆኑም በላይ በአንዳንድ አገሮች ቁሳዊ እድገት የተደረገ ቢሆንም፤ የሰው ልጅ ታሪክ በጭቆና፣ በወንጀል፣ በዓመፅ፣ በጦርነትና በድህነት የተሞላ መሆኑ አልቀረም። ይህ ዓለም ስንኩል የሆኑት የሰዎች መንግሥታት ያመጡበት የተለያዩ መከራዎች ሲፈራረቁበት ኖሯል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው” በማለት በትክክል ይናገራል።​—⁠መክብብ 8:​9 NW

4, 5. (ሀ) በ20ኛው መቶ ዘመን መባቻ ላይ የነበሩ ሰዎች የተሻለ ዓለም ይመጣል ብለው ተስፋ ያደረጉት ለምን ነበር? (ለ) ስለ ወደፊቱ ጊዜ የነበራቸው ተስፋ ምን ሆነ?

4 ከዚህም በላይ ያለፈው አስከፊ የሰው ልጅ ታሪክ በመጠኑና በአውዳሚነቱ እየሰፋ መምጣት ብቻ ሳይሆን እየተደጋገመ መከሰቱ አልቀረም። ይህ 20ኛው መቶ ዘመን ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ይሆናል። የሰው ልጅ ባለፈው ጊዜ ከፈጸማቸው ስህተቶች ትምህርት ለማግኘትና ስህተቶቹን ለማስወገድ ችሏል? በዚህ መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ ረዘም ላለ ጊዜ ሰላም ሰፍኖ ስለነበረና በኢንዱስትሪ፣ በሳይንስና በትምህርት መስክ መሻሻል ስለታየ ሰዎች የተሻለ ዓለም እንደሚመጣ ተስፋ አድርገው ነበር። አንድ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር በ1900ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ “ሰዎች በጣም የሰለጠኑ ስለሚሆኑ” ወደፊት ጦርነት ሊኖር አይችልም ተብሎ ታምኖ ነበር ሲሉ ተናግረዋል። አንድ የብሪታንያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር በዚያን ዘመን የነበሩ ሰዎች ስለነበራቸው አመለካከት ሲናገሩ “ሁሉም ነገር ከቀን ወደ ቀን እየተሻሻለ ይሄዳል የሚል ተስፋ ነበር። የተወለድኩበት ዓለም ይህን ይመስል ነበር” ካሉ በኋላ “በ1914 በድንገት፣ በአንድ ጀንበር ይህ ሁሉ ተስፋ መከነ” ብለዋል።

5 ብዙ ሰዎች የተሻለ ጊዜ ይመጣል የሚል ተስፋ የነበራቸው ቢሆንም አዲሱ መቶ ዘመን ገና ከመጀመሩ ዓለም እስከዚያ ጊዜ ድረስ ታይቶ በማያውቅ እልቂት፣ ማለትም በአንደኛው የዓለም ጦርነት ተዋጠች። ሁኔታው ምን ይመስል እንደነበር ለማየት እንድትችል በ1916 በፈረንሳይ ውስጥ በሚገኘው የሶም ወንዝ አጠገብ የብሪታንያ ወታደሮች በጀርመን ግንባር ላይ ጥቃት በሰነዘሩበት ጊዜ የደረሰውን ነገር ተመልከት። በሰዓታት ጊዜ ውስጥ ብሪታንያ 20,000 ሰዎችን በሞት ስታጣ በጀርመን በኩልም ብዙዎች ተገደሉ። ይህ ለአራት ዓመታት የቆየው የጅምላ ጭፍጨፋ አሥር ሚልዮን የሚያክሉ ወታደሮችንና ሌሎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት አረገፈ። ብዙ ወንዶች በመሞታቸው የተነሣ የፈረንሳይ ሕዝብ ብዛት አሽቆልቁሎ ነበር። የየአገሩ ኢኮኖሚ መንኮታኮት በ1930ዎቹ ዓመታት በመላው ዓለም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት አስከተለ። አንዳንዶች ዓለም ያበደችው አንደኛው የዓለም ጦርነት የጀመረ ዕለት ነው ማለታቸው ብዙም የሚያስደንቅ አይደለም!

6. ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተሻለ ኑሮ ተገኝቷልን?

6 ያ ትውልድ ተስፋ ያደረገው የወደፊት ጊዜ ይህ ነበርን? በፍጹም አልነበረም። ተስፋቸው ሁሉ ከንቱ ሆኖ ቀረ። ይህ ሁሉ ደርሶም የተሻለ ሁኔታ ሊመጣ አልቻለም። አንደኛው የዓለም ጦርነት ከተካሄደ ከ21 ዓመት በኋላ በ1939 ከዚህ እጅግ የከፋ ሰው ሠራሽ እልቂት፣ ማለትም ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተከሰተ። ይህ ጦርነት 50 ሚልዮን የሚያክሉ ወንዶችን፣ ሴቶችንና ሕፃናትን አርግፏል። ከፍተኛ የቦምብ ድብደባዎች ታላላቅ ከተሞችን አመድ አደረጉ። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በተደረገ አንድ ውጊያ ላይ በጥቂት ሰዓቶች ውስጥ የተገደሉት በሺህ የሚቆጠሩ ወታደሮች ሲሆኑ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ግን በሴኮንዶች ውስጥ የ100,000 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፉት ሁለት የአቶም ቦምቦች ብቻ ነበሩ። በናዚ ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ በሚልዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ በሚገባ በታቀደ መንገድ የተፈጸመው ግድያ ደግሞ ከዚህ ይበልጥ የከፋ ነው።

7. የዚህ ምዕተ ዓመት አጠቃላይ ገጽታ ምንድን ነው?

7 በርካታ የሆኑ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በብሔራት መካከል የተደረጉትን ጦርነቶች፣ የእርስ በርስ ግጭቶችንና መንግሥታት በራሳቸው ዜጎች ላይ የፈጸሙትን ግድያ አንድ ላይ ብንደምር በዚህ መቶ ዘመን የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 200 ሚልዮን ይደርሳል። እንዲያውም አንድ የመረጃ ምንጭ 360 ሚልዮን እንደሚደርስ ገልጿል። በዚህ ምክንያት የደረሰውን ሰቆቃ፣ ሥቃይና መከራ፣ የፈሰሰውን እንባ፣ የጠፋውን ሕይወት፣ እስቲ ለአንድ አፍታ አስቡ! ከዚህም በላይ በየቀኑ በአማካይ 40,000 ሰዎች ከድህነት ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ይሞታሉ። ከሚሞቱት ውስጥ አብዛኞቹ ሕፃናት ናቸው። የዚህ ቁጥር ሦስት እጥፍ የሚሆኑት ደግሞ በየቀኑ በውርጃ ይገደላሉ። በተጨማሪም አንድ ቢልዮን የሚሆኑ ሰዎች እጅግ ድሃ በመሆናቸው መደበኛ የቀን ሥራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን በቂ ምግብ አያገኙም። እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አስቀድሞ በተናገረው መሠረት በዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ‘የመጨረሻ ዘመን’ ላይ እንደምንኖር የሚያረጋግጡ ናቸው።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5, 13፤ ማቴዎስ 24:​3-12፤ ሉቃስ 21:​10, 11፤ ራእይ 6:​3-8

ሰብዓዊ መፍትሔ የለም

8. ሰብዓዊ መሪዎች የዓለምን ችግሮች ለመፍታት የማይችሉት ለምንድን ነው?

8 ሃያኛው መቶ ዘመን ወደማለቂያው በተቃረበበት በአሁኑ ጊዜ እነዚህን ተሞክሮዎች ባለፉት መቶ ዘመናት በተፈጸሙት ላይ መደመር እንችላለን። ታዲያ ታሪክ ምን ያስገነዝበናል? ሰብዓዊ መሪዎች የዓለምን ችግሮች በሙሉ ፈጽሞ ፈትተው እንደማያውቁ፣ በአሁኑ ጊዜም በመፍታት ላይ እንዳልሆኑና ወደፊትም ቢሆን ሊፈቷቸው እንደማይችሉ ያስገነዝበናል። ሰብዓዊ መሪዎች ምንም ያህል በቀና ልብ ቢነሳሱ የምንፈልገውን ዓይነት የወደፊት ጊዜ ሊያመጡልን አይችሉም። ደግሞም ሥልጣን ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች ይህን ያህል የቀና ልብ ያላቸው አይደሉም። አብዛኞቹ ሥልጣንና ማዕረግ የሚፈልጉት የራስ ወዳድነት ምኞታቸውን ለማራመድና የግል ሀብታቸውን ለማካበት እንጂ ለሌሎች ጥቅም አስበው አይደለም።

9. ሳይንስ የሰው ልጆችን ችግር ለመፍታት ያለውን ችሎታ እንድንጠራጠር የሚያደርገን ምንድን ነው?

9 ከሳይንስስ መፍትሔ ማግኘት ይቻል ይሆን? ያለፈውን ጊዜ ከመረመርን መፍትሔ ማግኘት እንደማይቻል እንረዳለን። የመንግሥት ሳይንቲስቶች እጅግ አውዳሚ የሆኑ ኬሚካላዊ፣ ባዮሎጂያዊና ሌሎች ዓይነት መሣሪያዎችን ለመፈልሰፍ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ አፍስሰዋል። በጣም ድሃ የሆኑትን አገሮች ጨምሮ ብሔራት በአጠቃላይ በየዓመቱ ለጦር መሣሪያ ብቻ 700 ቢልዮን ዶላር ያወጣሉ! በተጨማሪም ‘ሳይንሳዊ እድገት’ ለአየር፣ ለምድር፣ ለውኃና ለምግብ መበከል ምክንያት ለሆኑት ኬሚካሎች በከፊል አስተዋጽኦ አድርጓል።

10. ትምህርትም ቢሆን የተሻለ የወደፊት ጊዜ ሊያመጣ የማይችለው ለምንድን ነው?

10 የዓለም የትምህርት ተቋሞችስ ከፍተኛ የሆኑ የሥነ ምግባር ሥርዓቶችን፣ ለሌሎች ማሰብንና ለጎረቤት ፍቅር የማሳየትን ባሕርይ በማስተማር የተሻለ የወደፊት ጊዜ ለመገንባት አስተዋጽኦ ያደርጉ ይሆን? አያደርጉም። ምክንያቱም እነርሱ የሚያተኩሩት የተለያዩ ሞያዎችን በማስፋፋትና ብዙ ገንዘብ በማግኘት ላይ ነው። በተማሪዎቻቸው ውስጥ የሚቀርጹት የፉክክር እንጂ የትብብር መንፈስ አይደለም። ትምህርት ቤቶች ስለ ሥነ ምግባር ከማስተማር ይልቅ በአሥራዎቹ ዕድሜ ለሚገኙ ወጣቶች እርግዝናና ለአባለ ዘር በሽታዎች መስፋፋት ምክንያት የሆነውን ወሲባዊ ልቅነት በዝምታ ይመለከታሉ።

11. የንግድ ድርጅቶች ያስመዘገቡት ታሪክ በወደፊቱ ጊዜ ላይ የጥርጣሬ ጥላ የሚያጠላበት ለምንድን ነው?

11 ትላልቆቹ የዓለም የንግድ ድርጅቶች በድንገት አስተሳሰባቸውን ለውጠው ምድራችንን ከመበከል ይልቅ ጥሩ እንክብካቤ ሊያደርጉላት ይጀምሩ ይሆን? ትርፍ ብቻ የሚያጋብሱባቸውን ምርቶች ትተው እውነተኛ ጠቀሜታ ያላቸውን ምርቶች በማምረት ለሌሎች ፍቅር እንዳላቸው ያሳዩ ይሆን? ይህ የማይመስል ነገር ነው። የሰዎችን አእምሮ፣ በተለይም የወጣቶችን አእምሮ በመበከል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉትን በዓመፅና በብልግና የተሞሉ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ማዘጋጀታቸውን ያቆሙ ይሆን? በዚህም ረገድ ያለፈው ጊዜ የሚያበረታታ ተስፋ አይሰጠንም። ምክንያቱም ቴሌቪዥን በአብዛኛው የብልሹ ምግባር፣ የብልግናና የዓመፅ ማስተላለፊያ ቦይ ሆኗል።

12. ሕመምንና ሞትን በተመለከተ የሰው ልጅ ያለበት ሁኔታ ምንድን ነው?

12 በዚህ ሁሉ ላይ፣ ዶክተሮች ምንም ያህል ልባዊ ጥረት ቢያደርጉ በሽታንና ሞትን ድል ለማድረግ አይችሉም። ለምሳሌ ያህል በአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ የሕክምናው ኅብረተሰብ የስፓኒሽ ኢንፍሉዌንዛን መቆጣጠር ተስኖት ነበር። በመላው ዓለም የ20 ሚልዮን ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። በዛሬው ጊዜም የልብ በሽታ፣ ካንሰርና ሌሎች ቀሳፊ በሽታዎች በጣም ተስፋፍተዋል። የሕክምናው ዓለም ዘመን አመጣሹን የኤድስ ወረርሽኝ መቆጣጠር ተስኖታል። እንዲያውም በኅዳር 1997 የታተመ አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘገባ የኤድስ ቫይረስ ቀደም ሲል ከተገመተው በእጥፍ የተስፋፋ መሆኑን ገልጿል። እስካሁን ድረስ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በኤድስ ሞተዋል። ይህ ዘገባ ከመውጣቱ በፊት በነበረው ዓመት ሦስት ሚልዮን የሚያክሉ ተጨማሪ ሰዎች በኤድስ ቫይረስ ተለክፈዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች የወደፊቱን ጊዜ የሚመለከቱት እንዴት ነው?

13, 14. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች የወደፊቱን ጊዜ የሚመለከቱት እንዴት ነው? (ለ) የሰው ልጆች የተሻለ ጊዜ ማምጣት የማይችሉት ለምንድን ነው?

13 ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች የሰው ልጅ ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ብሩህ ተስፋ እንዳለው ያምናሉ! ሆኖም ይህ የተሻለ ጊዜ በሰው ልጆች ጥረት ይመጣል ብለው አይጠብቁም። ከዚህ ይልቅ ፈጣሪ በሆነው በይሖዋ አምላክ ላይ ትምክህታቸውን ይጥላሉ። እርሱ የወደፊቱ ጊዜ ምን ዓይነት እንደሚሆን አስረግጦ ያውቃል። በጣም አስደናቂ ጊዜ ይሆናል! በተጨማሪም የሰው ልጆች እንዲህ ያለውን ብሩህ ጊዜ ሊያመጡ እንደማይችሉ ያውቃል። ሰዎችን የፈጠረው እሱ በመሆኑ አቅማቸውንና ችሎታቸውን ከማንም ይበልጥ ያውቃል። አምላክ የሰው ልጆችን ሲፈጥር መለኮታዊ መመሪያ ሳያስፈልጋቸው ራሳቸውን በተሳካ ሁኔታ እንዲያስተዳድሩ የሚያስችል ችሎታ እንዳልሰጣቸው ቃሉ ይነግረናል። አምላክ ከእሱ አመራር ውጪ የሆነው የሰው አገዛዝ ለረጅም ጊዜ እንዲቆይ መፍቀዱ ሰዎች ይህ ችሎታ እንደሌላቸው በማያዳግም ሁኔታ አረጋግጧል። አንድ ጸሐፊ “የሰው ልጅ አእምሮ አለ የሚባለውን የአገዛዝ ዓይነት የሞከረ ቢሆንም ሊሳካለት ግን አልቻለም” በማለት የእምነት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

14 በኤርምያስ 10:​23 ላይ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የነቢዩ ቃል “አቤቱ፣ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም” ይላል። በተጨማሪም መዝሙር 146:​3 “ማዳን በማይችሉ በሰው ልጆችና በአለቆች አትታመኑ” ይላል። እንዲያውም ሮሜ 5:​12 እንደሚናገረው ስንወለድ ጀምሮ ፍጽምና የጎደለን በመሆናችን የአምላክ ቃል በራሳችን እንኳን ቢሆን እንዳንታመን ያስጠነቅቀናል። ኤርምያስ 17:​9 “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኮለኛ እጅግም ክፉ ነው” ይላል። ምሳሌ 28:​26 “በገዛ ልቡ የሚታመን ሰው ሰነፍ ነው፤ በጥበብ የሚሄድ ግን ይድናል” በማለት ግልጽ ማስጠንቀቂያ የሚሰጠው በዚህ ምክንያት ነው።

15. መመሪያ ሊሆነን የሚችል ጥበብ ከየት ማግኘት እንችላለን?

15 ታዲያ ይህን ጥበብ ከየት ማግኘት እንችላለን? “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው። ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነው።” (ምሳሌ 9:​10) ከዚህ አስፈሪ ጊዜ መርቶ ሊያወጣን የሚችል ጥበብ ያለው ፈጣሪያችን ይሖዋ ብቻ ነው። እሱ ደግሞ ጥበቡን የሚሰጠን መመሪያችን እንዲሆኑ ብሎ ባስጻፋቸው ቅዱሳን ጽሑፎች አማካኝነት ነው።​—⁠ምሳሌ 2:​1-9፤ 3:​1-6፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17

የሰብዓዊ አገዛዝ የወደፊት ዕጣ

16. የወደፊቱን ጊዜ የወሰነው ማን ነው?

16 ታዲያ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የአምላክ ቃል ምን ይነግረናል? የወደፊቱ ጊዜ የሰው ልጆች ባለፉት ዘመናት ካደረጓቸው ነገሮች ጋር በምንም መንገድ እንደማይመሳሰል ያረጋግጥልናል። ስለዚህ የፓትሪክ ሄንሪ አስተያየት ስህተት ነው ማለት ይቻላል። የዚህች ምድርም ሆነ በምድር ላይ የሚኖር የእያንዳንዱ ሰው የወደፊት ዕጣ የሚወሰነው በሰው ልጆች ሳይሆን በይሖዋ አምላክ ነው። በምድር ላይ የሚፈጸመው የአምላክ ፈቃድ እንጂ የማንም ሰው ወይም የየትኛውም የዚህ ዓለም ብሔር ፈቃድ አይደለም። “በሰው ልብ ብዙ አሳብ አለ፤ የእግዚአብሔር ምክር ግን እርሱ ይጸናል።”​—⁠ምሳሌ 19:​21

17, 18. አምላክ ስለ ዘመናችን ያለው ፈቃድ ምንድን ነው?

17 እንግዲያው አምላክ ለዘመናችን ያለው ፈቃድ ምንድን ነው? ይህን በብልግና የተሞላ መጥፎ የነገሮች ሥርዓት የማጥፋት ዓላማ አለው። ለበርካታ መቶ ዘመናት ተንሰራፍቶ የኖረው የሰው ልጆች ክፉ አገዛዝ አምላክ ባዘጋጀው አገዛዝ በቅርቡ ይተካል። በዳንኤል 2:​44 ላይ የሚገኘው ትንቢት እንዲህ ይላል:- “በእነዚያም ነገሥታት ዘመን [በዛሬው ጊዜ ባሉት ማለት ነው] የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት [በሰማይ] ያስነሣል፤ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፤ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች።” መንግሥቱ ሰዎች ሊያደርጉ የማይችሉትን ነገር ማለትም የሰይጣን ዲያብሎስን አጋንንታዊ ተጽእኖም ያስወግዳል። ሰይጣን ይህን ዓለም መምራቱ ለዘላለም ያከትማል።​—⁠ሮሜ 16:​20፤ 2 ቆሮንቶስ 4:​4፤ 1 ዮሐንስ 5:​19

18 ይህ ሰማያዊ መንግሥት ሁሉንም ዓይነት የሰው አገዛዝ ጠራርጎ እንደሚያጠፋ ልብ በሉ። ከዚያ በኋላ የሰው ልጆችን የማስተዳደሩ ሥራ በምድር ላይ ለሚኖሩ ሰዎች ዳግመኛ አይሰጥም። የሰማያዊው መንግሥት አባላት የሚሆኑት የአምላክ ሰማያዊ ወኪሎች የምድርን ጉዳዮች በሙሉ በመቆጣጠር ለሰው ልጆች የሚበጀውን ሁሉ ያደርጋሉ። (ራእይ 5:​10፤ 20:​4-6) በምድር ላይ የሚኖሩት ታማኝ ሰዎች የአምላክ መንግሥት ከሚሰጣቸው አመራር ጋር ሙሉ በሙሉ ይተባበራሉ። ኢየሱስ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” በማለት እንድንጸልይ ሲያስተምር ይህን አገዛዝ ማመልከቱ ነው።​—⁠ማቴዎስ 6:​10

19, 20. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ የመንግሥቱን ዝግጅት የሚገልጸው እንዴት ነው? (ለ) አገዛዙ ለሰው ልጆች ምን ያደርግላቸዋል?

19 የይሖዋ ምሥክሮች እምነታቸውን የጣሉት በአምላክ መንግሥት ላይ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ “ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን” በማለት በጻፈ ጊዜ “አዲስ ሰማይ” ብሎ የጠቀሰው ይህን መንግሥት ነው። (2 ጴጥሮስ 3:​13) “አዲሱ ምድር” ደግሞ በአዲሱ ሰማይ ማለትም በአምላክ መንግሥት የሚተዳደረው አዲስ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ነው። ለሐዋርያው ዮሐንስ በተገለጠው ራእይ ላይ አምላክ ይህን ዝግጅት ገልጿል:- “አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፣ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና . . . [አምላክ] እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።”​—⁠ራእይ 21:​1, 4

20 አዲሱ ምድር ጽድቅ የሚኖርበት እንደሚሆን ልብ በሉ። ጻድቅ ያልሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሙሉ አምላክ በአርማጌዶን በሚወስደው እርምጃ ፈጽመው ይወገዳሉ። (ራእይ 16:​14, 16) በምሳሌ 2:​21, 22 ላይ የሚገኘው ትንቢት እንዲህ በማለት ገልጾታል:- “ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና፣ ፍጹማንም በእርስዋ ይኖራሉና፤ ኀጥኣን ግን ከምድር ይጠፋሉ፣ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ።” መዝሙር 37:​9 ደግሞ “ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ” የሚል የተስፋ ቃል ይሰጠናል። ታዲያ እንዲህ ባለው አዲስ ዓለም ውስጥ መኖር አትፈልግም?

ይሖዋ በሰጠው ተስፋ ላይ እምነታችሁን ጣሉ

21. ይሖዋ በሰጠን ተስፋ ላይ እምነት መጣል የምንችለው ለምንድን ነው?

21 ይሖዋ በሰጠው ተስፋ ላይ እምነት መጣል እንችላለን? ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል የተናገረውን ልብ በሉ:- “እኔ አምላክ ነኝና፣ ሌላም የለምና የቀድሞውን የጥንቱን ነገር አስቡ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም። በመጀመሪያ መጨረሻውን፣ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ፤ ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴንም ሁሉ እፈጽማለሁ እላለሁ።” የቁጥር 11 የመጨረሻ ክፍል “ተናግሬአለሁ እፈጽምማለሁ፤ አስቤአለሁ አደርግማለሁ” ይላል። (ኢሳይያስ 46:​9-11) አዎን፣ እነዚህ ተስፋዎች የተፈጸሙ ያክል በይሖዋና በተስፋ ቃሉ ላይ መታመን እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይገልጸዋል:- “እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፣ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ . . . ነው።”​—⁠ዕብራውያን 11:​1

22. ይሖዋ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም ልንተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?

22 ትሑታን የሆኑ ሰዎች አምላክ እነዚህን የተስፋ ቃሎች እንደሚፈጽም ስለሚያውቁ ይህን የመሰለውን እምነት ያሳያሉ። ለምሳሌ ያህል መዝሙር 37:​29 ላይ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ” የሚል እናነባለን። ታዲያ ይህን ማመን እንችላለን? አዎን፣ ማመን እንችላለን። ምክንያቱም ዕብራውያን 6:​18 ‘እግዚአብሔር ሊዋሽ አይችልም’ ይላል። አምላክ ምድርን ለትሑታን ሊሰጥ የሚችለው በእርግጥ እሱ የምድር ባለቤት ስለሆነ ነውን? ራእይ 4:​11 ስለ እርሱ ሲናገር “አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና” ይላል። በዚህም ምክንያት መዝሙር 24:​1 “ምድርና ሞላዋ ለእግዚአብሔር ናት” ይላል። በእርግጥም ምድርን የፈጠረው ይሖዋ ነው፤ ባለቤትዋም እርሱ ነው፤ በእርሱ ላይ እምነት ላላቸው ሰዎችም ይሰጣታል። የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት በዚህ ላይ ያለንን ትምክህት ለመገንባት ይሖዋ ባለፉት ጊዜያት ለነበሩትም ሆነ በጊዜያችን ላሉት ሕዝቦቹ የሰጣቸውን ተስፋዎች የፈጸመላቸው እንዴት እንደሆነና ወደፊትም ሌሎች ተስፋዎቹን እንዲሁ እንደሚፈጽም ሙሉ በሙሉ የምንተማመንበትን ምክንያት ይገልጻል።

ለክለሳ የሚሆኑ ነጥቦች

◻ በታሪክ ዘመናት በሙሉ የሰው ልጆች ተስፋ ያደረጓቸው ነገሮች ምን ሆነዋል?

◻ የተሻለ የወደፊት ጊዜ ያመጣሉ ብለን በሰዎች መታመን የሌለብን ለምንድን ነው?

◻ አምላክ ለወደፊቱ ጊዜ ያለው ፈቃድ ምንድን ነው?

◻ አምላክ ተስፋዎቹን እንደሚፈጽም ልንተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው አካሄዱን ለማቅናት አይችልም” በማለት በትክክል ይናገራል። ​—⁠ኤርምያስ 10:​23 NW

[ምንጭ]

ቦምብ:- U.S. National Archives photo; በረሃብ የተጎዱ ልጆች:- WHO/OXFAM; ስደተኞች:- UN PHOTO 186763/J. Isaac; ሙሶሎኒና ሂትለር:- U.S. National Archives photo

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ