የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 5/1 ገጽ 3-4
  • ከዚህ ሁሉ በስተጀርባ ያለው ማን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከዚህ ሁሉ በስተጀርባ ያለው ማን ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ይሖዋ ማን ነው?
    ይሖዋ ማን ነው?
  • ከአንድ ባዮኬሚስት ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ
    ንቁ!—2006
  • ማን ሊነግረን ይችላል?
    የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? እንዴትስ ልታገኘው ትችላለህ?
  • የተፈጥሮን ንድፍ ከማድነቅ ባሻገር ስለ ንድፍ አውጪው ተማር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 5/1 ገጽ 3-4

ከዚህ ሁሉ በስተጀርባ ያለው ማን ነው?

ኤንሪ ሙኦ የተባለው የ19ኛው መቶ ዘመን ፈረንሳዊ አሳሽ የካምቦዲያን ጥቅጥቅ ያለ ደን እየጣሰ ካቋረጠ በኋላ አንድን ቤተ መቅደስ ለመከላከል ተብሎ ወደ ተቆፈረ ሰፊ የውኃ ጉድጓድ ደረሰ። እሱ ከቆመበት በአንድ ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ ከ60 ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው አምስት የቤተ መቅደሱ ማማዎች ይታያሉ። ይህ ቤተ መቅደስ አንኮር ዋት ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በምድር ላይ ከሚገኙት ሃይማኖታዊ ቅርሶች ሁሉ ትልቁ ነበር። ሙኦ ቤተ መቅደሱን ያገኘው ቤተ መቅደሱ ለሰባት መቶ ዓመታት ያህል የተለያየ የአየር ሁኔታን ተቋቁሞ ካሳለፈ በኋላ ነበር።

ሙኦ እነዚያን በድንጋይ ሽበት የተሸፈኑ ሕንፃዎች ገና ሲመለከት የሰው እጅ ሥራ ውጤት መሆናቸውን እንደተገነዘበ ምንም ጥርጥር የለውም። “የማይክልአንጄሎን የመሰለ ችሎታ ባለው አንድ ጥንታዊ ሰው የተሠራው ይህ ቤተ መቅደስ ግሪክ ወይም ሮም ትተውልን ካለፉት ነገሮች ሁሉ የሚበልጥ ነው” ሲል ጽፏል። ለብዙ ምዕተ ዓመታት ማንም ዝር ሳይልባቸው ተትተው የነበረ ቢሆንም ከእነዚህ አስደናቂ ሕንፃዎች በስተጀርባ አንድ ንድፍ አውጪ መኖሩን በፍጹም አልተጠራጠረም።

ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት የተጻፈ ጥበብ ያለበት አንድ መጽሐፍ በዙሪያችን ያለው ዓለም የአንድ ንድፍ አውጪ የሥራ ውጤት መሆን እንዳለበት ለመግለጽ ተመሳሳይ የሆነ ማብራሪያ መጠቀሙ ትኩረት የሚስብ ነው። ዓለም በፍጥረት የተገኘ መሆን አለበት። ሐዋርያው ጳውሎስ “እያንዳንዱ ቤት በአንድ ሰው ተዘጋጅቶአልና፣ ሁሉን ያዘጋጀ ግን እግዚአብሔር ነው” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 3:​4) አንዳንዶች ‘የተፈጥሮና የሰው ሥራ የተለያየ ነው’ በማለት በዚህ ንጽጽር አይስማሙ ይሆናል። ይሁን እንጂ በዚህ የተቃውሞ ሐሳብ የሚስማሙት ሁሉም ሳይንቲስቶች አይደሉም። በሊሃይ ዩኒቨርሲቲ የባዮኬሚስትሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ማይክል ቤሄ “ባዮኬሚካላዊ አሠራሮች ግዑዝ ነገሮች አለመሆናቸውን” አምነው ከተቀበሉ በኋላ “ሕያው የሆኑ ባዮኬሚካላዊ አሠራሮች በከፍተኛ የማሰብ ችሎታ የተነደፉ ናቸውን?” ብለው ጠይቀዋል። ቀጥለውም ሳይንቲስቶች እንደ ጄነቲክ ምህንድስና የመሳሰሉ ዘዴዎችን በመጠቀም በሕያዋን ዘአካሎች ላይ መሠረታዊ ለውጦች ለማምጣት ንድፍ እያወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ግዑዝም ሆኑ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ንድፍ ሊወጣላቸውና በዚያ መሠረት ሊሠሩ ይችላሉ! ቤሄ በማጕያ መነጽር አማካኝነት ብቻ ሊታዩ በሚችሉት ሕይወት ያላቸው ሕዋሳት ላይ ምርምር የማድረግ ተግባራቸውን ለማከናወን እንዲችሉ አንዳቸው በሌላው ላይ ጥገኛ ስለሆኑ አስደናቂ ውስብስብ አሠራሮች ገልጸዋል። ታዲያ ምን መደምደሚያ ላይ ደረሱ? “ሕዋስን በመመርመር ሕይወትን ከሥር መሠረቱ ለማወቅ የተደረጉት የእነዚህ ጥረቶች ጥምረት ውጤት ሕዋስ በ‘ንድፍ!’ የተገኘ መሆኑን ጥርት ባለ ድምፅ ይናገራል።”

በተመሳሳይም የሥነ ኮስሞስና የፊዚክስ ምሁራን ዓለምንና ጠፈርን በጥንቃቄ ከመረመሩ በኋላ አንዳንድ አስደናቂ እውነታዎችን አግኝተዋል። ለምሳሌ ያህል ሁለንታዊ ቋሚ (universal constants) በሚባሉት ቁጥሮች ላይ እጅግ ትንሽ የሆነ ለውጥ ቢደረግ አጽናፈ ዓለም ሕይወት አልባ ይሆን ነበር።a የሥነ ኮስሞስ ምሁር የሆኑት ብራንደን ካርተር እነዚህን እውነታዎች አስገራሚ አጋጣሚዎች ብለዋቸዋል። ይሁን እንጂ ምስጢራዊና ውስብስብ ነገሮችን ብትመለከት ሌላው ቢቀር አንድ የሆነ አካል ከበስተጀርባቸው መኖር አለበት ብለህ አትጠረጥርም?

ከእነዚህ ውስብስብ አሠራሮችና በጥሩ ሁኔታ ከተቀነባበሩ “አጋጣሚዎች” በስተጀርባ አንድ ንድፍ አውጪ መኖሩ የተረጋገጠ ነው። እሱ ማን ነው? ፕሮፌሰር ቤሄ “ንድፍ አውጪውን በሳይንሳዊ ዘዴዎች ለማወቅ መሞከር እጅግ አስቸጋሪ” መሆኑን ካመኑ በኋላ ለጥያቄው መልስ እንዲሰጡ “ለፍልስፍናና ለሃይማኖታዊ ትምህርት” ትተውላቸዋል። አንተ በበኩልህ ጥያቄው ተገቢ አይደለም ብለህ ታስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ በጣም በምትፈልጋቸው ነገሮች የተሞላና በሚያምር ወረቀት የተጠቀለለ ስጦታ ቢደርስህ ማን እንደላከልህ ለማወቅ አትፈልግም?

በምሳሌያዊ አነጋገር እኛ እንዲህ ዓይነት እሽግ ተቀብለናል። በሕይወት እንድንኖርና እንድንደሰት በሚያስችሉን ግሩም ስጦታዎች የተሞላ ጥቅል ተሰጥቶናል። ያ ጥቅል ሕይወትን ጠብቆ ለማቆየት በሚረዱ ድንቅ ሥርዓቶች የተሞላችው ምድር ናት። እነዚህን ስጦታዎች ማን እንደሰጠን ማወቅ አይኖርብንምን?

ደስ የሚለው ነገር ላኪው አካል ከጥቅሉ ጋር አንድ ማስታወሻ አያይዞ ልኮልናል። ይህ “ማስታወሻ” ቀደም ሲል የተጠቀሰውና ጥንታዊ የጥበብ መጽሐፍ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በመክፈቻ ቃላቱ ላይ በሚያስደንቅ እንዲሁም ቀላልና ግልጽ በሆነ መንገድ ጥቅሉን የሰጠን ማን ስለመሆኑ ለተነሣው ጥያቄ መልስ ይሰጣል:- “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ።”​—⁠ዘፍጥረት 1:​1

በዚህ “ማስታወሻ” ላይ ፈጣሪ ስሙን ገልጿል:- “ሰማያትን የፈጠረ የዘረጋቸውም፣ ምድርንና በውስጥዋ ያለውን ያጸና፣ በእርስዋ ላይ ለሚኖሩ ሕዝብ እስትንፋስን . . . የሚሰጥ አምላክ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] እንዲህ ይላል።” (ኢሳይያስ 42:​5) አዎን፣ የአጽናፈ ዓለምን ንድፍ ያወጣና ወንድንና ሴትን በምድር ላይ የሠራ አምላክ ስሙ ይሖዋ ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ ማን ነው? ምን ዓይነት አምላክ ነው? በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎችስ እርሱን ማዳመጥ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?

[የግርጌ ማስታወሻ]

a “ኢተለዋዋጭ” የሚባሉት ቁጥሮች በየትኛውም የአጽናፈ ዓለም ክፍል ውስጥ የማይለዋወጡ ቁጥሮች ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ የብርሃን ፍጥነት እንዲሁም ስበት (gravity) ከመጠነቁስ (mass) ጋር ያለው ዝምድና እንደ ምሳሌ ሊጠቀሱ ይችላሉ።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንኮር ዋት የተገነባው በሰዎች ነው

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ስጦታ ሲመጣልህ ስጦታውን ማን እንደላከልህ ለማወቅ አትፈልግም?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ