በ80 ዓመት ዕድሜ የመኖሪያ ሥፍራ መቀየር
ግዊንደሊን ማቲውስ እንደተናገረችው
ሰማንያ ዓመት ሲሞላኝ፣ ባለቤቴና እኔ ጓዛችንን ሁሉ በተከራየነው ከባድ መኪና ላይ ጭነን ከእንግሊዝ ወደ ስፔይን ለመሄድ ተነሳን። ስፓንኛ መናገር አንችልም፤ የምንሄድበት ቦታ ደግሞ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ቱሪስቶች ከሚያዘወትሩበት ቦታ ርቆ ወደሚገኘው ወደ ደቡብ ምዕራብ ስፔይን ነበር። አብዛኞቹ ወዳጆቻችን ሐሳባችን ባይዋጥላቸውም እኔ ግን አብርሃም ዑርን ለቅቆ ሲሄድ ዕድሜው 75 ዓመት እንደነበር በማስታወስ ራሴን አጽናና ነበር።
ስፔይን ከደረስንበት ከሚያዝያ 1992 ወዲህ ያሳለፍናቸው ዓመታት በሕይወታችን ውስጥ እጅግ የሚክሱ ጊዜያት ሆነውልናል። ወደዚያ የተዛወርንበትን ምክንያት ከመግለጼ በፊት ግን በይሖዋ አገልግሎት ያሳለፍነው ሕይወት ይህን ትልቅ ውሳኔ እንድናደርግ የመራን እንዴት እንደሆነ ልንገራችሁ።
የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሕይወታችንን ለወጠው
ያደግሁት በእንግሊዝ በደቡባዊ ምዕራብ ለንደን በሚገኝ ሃይማኖተኛ ቤተሰብ ውስጥ ነው። እናቴ መንፈሳዊ ፍላጎቷን ለማርካት ከአንዱ የአምልኮ ስፍራ ወደሌላው በምትሄድበት ጊዜ እኔንና እህቴንም ትወስደን ነበር። በሳንባ ነቀርሣ በሽታ ክፉኛ ይሠቃይ የነበረው አባቴ አብሮን አይሄድም ነበር። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ በጣም ይወድ የነበረ ከመሆኑም በላይ ደስ የሚሉ ጥቅሶችን ባገኘ ቁጥር ያሰምርባቸው ነበር። እጅግ ውድ ከሆኑት ቅርሶቼ መካከል አንዱ አባቴ በጣም ይወደው የነበረውና ብዙ ከማገልገሉ የተነሣ ያረጀው መጽሐፍ ቅዱስ ነው።
በ1925 የ14 ዓመት ልጅ ሳለሁ በዌስት ሃም ከተማ አዳራሽ ተገኝተን ለሕዝብ የሚሰጠውን ንግግር እንድናዳምጥ የሚጋብዝ ትራክት በበራችን ስር ተቀምጦ አገኘን። እናቴና አንዲት ጎረቤታችን ስብሰባው ላይ ተገኝተው ንግግሩን ለማዳመጥ በመወሰናቸው እህቴንና እኔን ይዘውን ሄዱ። “በአሁኑ ጊዜ በሕይወት የሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደፊት ፈጽሞ አይሞቱም” የሚለው ንግግር በእናቴ ልብ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንዲዘራ አደረገ።
ከጥቂት ወራት በኋላ አባቴ በ38 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። የእሱ መሞት እጅግ አስደንጋጭ ከመሆኑም በላይ ቅስማችንን የሰበረና ችግር ላይ የጣለን ነበር። በከተማው በሚገኘው የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን በተካሄደው የመታሰቢያ ቅዳሴ ላይ ቄሱ፣ የአባባ ነፍስ በሰማይ ነች ብሎ ሲናገር ስትሰማ እናቴ ደነገጠች። ከመጽሐፍ ቅዱስ ባገኘችው እውቀት አማካኝነት ሙታን በመቃብር ውስጥ ተኝተው እንዳሉ ታውቅ የነበረ ከመሆኑም በላይ ወደፊት አንድ ቀን አባቴ በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር በትንሣኤ ይነሣል የሚል ጠንካራ እምነት ነበራት። (መዝሙር 37:9-11, 29፤ 146:3, 4፤ መክብብ 9:5፤ ሥራ 24:15፤ ራእይ 21:3, 4) የአምላክን ቃል ከሚያስተምሩ ሰዎች ጋር መሰብሰብ እንደሚኖርባት አሳማኝ ማስረጃዎች በማግኘቷ ከዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር ማለትም በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለው ከሚጠሩት ጋር ለመሰብሰብ ወሰነች።
ለመጓጓዣ የሚሆን ገንዘብ ስላልነበረን በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ከቤታችን ተነሥተን በየሳምንቱ ለሁለት ሰዓታት ያህል በእግራችን እንጓዝ ነበር። ወደ ቤት ስንመለስ ደግሞ ሌላ ሁለት ሰዓት እንጓዛለን። ይሁን እንጂ እነዚያን ስብሰባዎች እጅግ አድርገን እናደንቃቸው ስለነበር የታወቀው የለንደን ጭጋግ ከተማዋን በሸፈናት ጊዜ እንኳ ሳይቀር አንድም ስብሰባ አምልጦን አያውቅም። እናቴ ወዲያውኑ ሕይወቷን ለይሖዋ ለመወሰንና ለመጠመቅ ወሰነች፤ እኔ ደግሞ በ1927 ተጠመቅሁ።
የኤኮኖሚ ችግር ቢኖርብንም እናቴ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ የመስጠትን አስፈላጊነት ሁልጊዜ ታስተምረኝ ነበር። ማቴዎስ 6:33 ከምትወዳቸው ጥቅሶች መካከል አንዱ ነበር። በእርግጥም ‘መንግሥቱን ታስቀድም’ ነበር። በ1935 በካንሰር ድንገት ተቀጠፈች እንጂ ወደ ፈረንሳይ ተዛውረው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ለሚፈልጉ ሰዎች ለቀረበው ጥሪ ምላሽ ለመስጠት በዝግጅት ላይ ነበረች።
የሚያበረታቱን ምሳሌዎች
በእነዚያ ቀደምት ጊዜያት በለንደን በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ አንዳንድ ተሰብሳቢዎች የራሳቸውን ሐሳብ ለመግለጽ ሲሉ ጠብና ጭቅጭቅ እንዲነሳ ያደርጉ ነበር። ሆኖም እናቴ ብዙ ነገር ከተማርንበት ከይሖዋ ድርጅት መውጣት ታማኝነትን ማጉደል እንደሆነ ሁልጊዜ ትናገር ነበር። በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ ያደርግልን የነበረው ጉብኝት በታማኝነት ማገልገላችንን እንድንቀጥል ብርታት ሰጥቶናል።
ወንድም ራዘርፎርድ ደግና የሚቀረብ ሰው እንደነበረ አስታውሳለሁ። ገና በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ ከለንደን ጉባኤ ጋር አብሮ ሽርሽር ሄዶ ነበር። ካሜራ ይዤ አየኝና ዓይን አፋር ወጣት መሆኔን ተገንዝቦ ፎቶ ላነሳው እፈልግ እንደሆነ ጠየቀኝ። ይህ ፎቶ ግራፍ ልዩ ማስታወሻ ሆኖናል።
ከጊዜ በኋላ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ባላቸው ወንድሞችና ታዋቂ በሆኑ የዓለም ሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት እንድገነዘብ ያደረገኝ አንድ ሁኔታ አጋጥሞኝ ነበር። በአንድ ትልቅ የለንደን መዝናኛ አዳራሽ ውስጥ በአስተናጋጅነት እሠራ በነበረበት ጊዜ ፍራንትስ ቮን ፓፐን የተባለው የሂትለር መልእክተኛ ምሳ ተጋብዞ ነበር። የታጠቀውን ሳንጃ አውልቆ ለመመገብ ፈቃደኛ ስላልነበረ ሳንጃው አደናቀፈኝና የያዝኩት ሾርባ ተደፋ። ሰውየው ይህ የግዴለሽነት ድርጊት የተፈጸመው በጀርመን ቢሆን ኖሮ በጥይት ይገድለኝ እንደነበረ በንዴት ተናገረ። ከዚያ በኋላ ተመግቦ እስኪጨርስ ድረስ አጠገቡ ድርሽ አላልኩም!
በ1931 በአሌክሳንድራ ፓላስ ታሪካዊ የሆነ የአውራጃ ስብሰባ ተደርጎ ነበር፤ በዚህ ስብሰባ ላይ ወንድም ራዘርፎርድ ንግግር ሲሰጥ አዳመጥኩ። የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን አዲስ ስም በደስታ የተቀበልነውም በዚህ ስብሰባ ላይ ነበር። (ኢሳይያስ 43:10, 12) ከሁለት ዓመት በኋላ በ1933 አቅኚ በመሆን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መሳተፍ ጀመርኩ። ከእነዚያ ዓመታት የማስታውሰው ሌላ ነገር ከጊዜ በኋላ ሚስዮናውያን በመሆን ራቅ ወዳሉ የምድር ክፍሎች ከሄዱ በርካታ ጎበዝ ወጣቶች ጋር ጓደኛ ለመሆን መቻሌን ነው። ከእነዚህ መካከል ክላውድ ጉድማን፣ ሃሮልድ ኪንግ፣ ጆን ኩክና ኤድዊን ስኪነር ይገኙበታል። የእነዚህ ታማኝ ወንድሞች ምሳሌነት በውጪ አገር የማገልገል ፍላጎት እንዲኖረኝ አድርጓል።
በኢስት አንግሊያ አቅኚ ሆኖ ማገልገል
አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል የተመደብኩት በኢስት አንግሊያ (ምሥራቃዊ እንግሊዝ) ውስጥ ሲሆን በዚያ ለመስበክ ደግሞ ግለትና ቅንዓት ይጠይቅ ነበር። ሰፊውን ክልላችንን ለመሸፈን ስንል ከከተማ ወደ ከተማና ከመንደር ወደ መንደር በብስክሌት እየተጓዝን በተከራየነው ቤት ውስጥ እንቆይ ነበር። በአካባቢው ጉባኤ የሚባል ነገር ስላልነበር እኔና የአገልግሎት ጓደኛዬ አብረን ሆነን መደበኛ በሆኑት ሳምንታዊ ስብሰባዎች የሚወሰዱትን ሁሉንም ክፍሎች እንወያይ ነበር። በአገልግሎታችን የአምላክን ዓላማዎች የሚገልጹ በመቶ የሚቆጠሩ መጻሕፍትንና ቡክሌቶችን አበርክተናል።
በከተማው ከሚገኘው የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ቄስ ጋር ያደረግነው ውይይት የማይረሳ ነበር። ብዙውን ጊዜ በአንድ አካባቢ ምሥራቹን ስንሰብክ ችግር ይፈጥሩብናል ብለን ስለምናስብ በአካባቢው የአንግሊካን ቄስ ቤት ካለ የምናኳኳው መጨረሻ ላይ ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ መንደር ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ሁሉ እዚህ ስላሉት ቄስ ጥሩነት ይናገሩ ነበር። የታመሙትን ይጠይቃሉ፣ ማንበብ ለሚወዱ መጻሕፍትን ያውሳሉ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን ለማብራራት ሲሉ በየቤቱ ይሄዳሉ።
እንደተባለውም ቤታቸው በሄድን ጊዜ ጥሩ አቀባበል አደረጉልን፤ እንዲሁም በርካታ መጻሕፍት ወሰዱ። ከዚህም በላይ በመንደሩ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ሰው መጽሐፎቻችንን ለመውሰድ ፍላጎት ኖሮት ገንዘብ ለመክፈል ካልቻለ እሳቸው ክፍያውን እንደሚሸፍኑ አረጋገጡልን። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ያጋጠሟቸው ዘግናኝ ተሞክሮዎች በቤተ ክርስቲያናቸው ውስጥ ሰላምንና መልካም ፈቃድን ለማስፋፋት ቆርጠው እንዲነሡ እንዳደረጋቸው ነገሩን። ከመሄዳችን በፊት መረቁን፤ የያዝነውን ጥሩ ሥራ መሥራታችንን እንድንቀጥልም አበረታቱን። ስንለያይ የተናገሯቸው ቃላት በዘኁልቁ 6:24 ላይ የሚገኙት “እግዚአብሔር ይባርክህ፣ ይጠብቅህም” የሚሉት ነበሩ።
አቅኚ ሆኜ ማገልገል በጀመርኩ በሁለተኛ ዓመቴ ላይ እናቴ ሞተች። በመሆኑም ወደ ለንደን ስመለስ ገንዘብም ሆነ ቤተሰብ አልነበረኝም። አንዲት ደግ ስኮትላንዳዊት እህት ቤቷ አስጠግታኝ በእናቴ ሞት ምክንያት ከተሰማኝ ኃዘን እንድጽናና በመርዳት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድቀጥል አበረታታችኝ። በመሆኑም ጁሊያ ፌይርፋክስ ከምትባል አዲስ የአገልግሎት ጓደኛ ጋር ወደ ኢስት አንግሊያ ተመልስኩ። አንድ ያረጀ መኪና ጠግነን ግማሽ ተንቀሳቃሽ ቤት አደረግነው። ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለማንቀሳቀስ በትራክተር ወይም በጭነት መኪና እንጠቀም ነበር። እንደ ቤት ሆኖ የሚያገለግል አነስተኛ መኪና ካላቸው አልበርትና ኢቴል አቦት ከሚባሉ በዕድሜ የገፉ ባልና ሚስት ጋር በመሆን መስበካችንን ቀጠልን። አልበርትና ኢቴል እንደ ወላጆች ሆነውኝ ነበር።
በካምብሪጅሻየር በአቅኚነት በማገለግልበት ጊዜ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር በማለፍ ለይሖዋ ያለውን የጸና አቋም ካስመሰከረውና ጎበዝ ክርስቲያን ከነበረው ከጆን ማቲውስ ጋር ተዋወቅሁ። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከጀመረ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በ1940 ተጋባን።
የጦርነት ወቅትና ቤተሰብ
ገና እንደተጋባን አንዲት ትንሽ ማድቤት የምታክል እንደ ቤት ሆና የምታገለግል መኪና ቤታችን ነበረች። አገልግሎታችንን ለማከናወን ከቦታ ወደ ቦታ የምንዘዋወርበት አስተማማኝ ሞተር ብስክሌት ነበረን። ከተጋባን ከአንድ ዓመት በኋላ ጆን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረተው አቋሙ ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ በአንድ እርሻ ውስጥ በሞያተኛነት እንዲሠራ ተፈረደበት። (ኢሳይያስ 2:4) በእርግጥ ይህ አቅኚነታችንን እንድናቆም ቢያደርገንም እኔ እርጉዝ ስለነበርኩና በጆን ላይ የተላለፈው ፍርድ በኢኮኖሚ ራሳችንን ለመርዳት ያስችለን ስለነበር አጋጣሚው ጥሩ ነበር።
በጦርነቱ ዓመታት አስቸጋሪ ነገሮች ቢኖሩም እንኳ ይደረጉ የነበሩት ልዩ ስብሰባዎች በጣም ያስደስቱን ነበር። በ1941 ጆንና እኔ በሞተርብስክሌታችን ተሳፍረን 300 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው ወደ ማንቸስተር ሄድን። በዚህ ጊዜ የመጀመሪያውን ልጃችንን ነፍሰ ጡር ነበርኩ። በመንገዳችን ላይ በርካታ በቦምብ የተደበደቡ መንደሮችን አልፈን የሄድን ሲሆን በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ስብሰባው ይካሄድ ይሆን እያልን እናስብ ነበር። በመሃል ማንቸስተር የሚገኘው የነፃ ገበያ አዳራሽ ከእንግሊዝ የተለያዩ ክፍሎች በመጡ ምሥክሮች ጢም ብሎ ከመሙላቱም በላይ የስብሰባው ሙሉ ፕሮግራም ቀርቧል።
የአውራጃ ስብሰባው የመጨረሻ ተናጋሪ በንግግሩ ማጠቃለያ ላይ አካባቢው በቦምብ ሊደበደብ ስለሚችል ተሰብሳቢዎቹ በፍጥነት ቦታውን ለቅቀው መሄድ እንዳለባቸው ተናገረ። በእርግጥም ማስጠንቀቂያው በተገቢው ጊዜ የተሰጠ ነበረ። ከአዳራሹ ብዙም ሳንርቅ የማስጠንቀቂያ ደውልና የአየር መቃወሚያ መሣሪያ ተኩስ ሰማን። ወደኋላችን መለስ ብለን ስንመለከት በደርዘን የሚቆጠሩ አውሮፕላኖች በከተማው ማዕከል ላይ ቦምቦችን እየጣሉ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በፊት ተሰብስበንበት የነበረው አዳራሽ ሙሉ በሙሉ ወድሞ በእሳትና በጭስ መካከል ከርቀት ይታየን ነበር! ደስ የሚለው ነገር ከክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መካከል አንድም አልተገደለም።
ልጆቻችንን በምናሳድግበት ጊዜ አቅኚ ሆነን ለማገልገል አልቻልንም። ይሁን እንጂ ማረፊያ ለሌላቸው ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና አቅኚዎች ቤታችን ክፍት ነበር። በአንድ ወቅት ስድስት የሚሆኑ አቅኚዎች ለጥቂት ወራት በቤታችን ቆይታ አድርገዋል። በ1961 ልጃችን ዩኒስ ገና በ15 ዓመቷ የአቅኚነት አገልግሎት ለመጀመር እንድትመርጥ ያደረጋት አንዱ ምክንያት እንዲህ ካሉ ወንድሞች ጋር መወዳጀታችን እንደነበረ ምንም አያጠራጥርም። የሚያሳዝነው ግን ልጃችን ዴቪድ ባደገ ጊዜ ይሖዋን በማገልገል አልቀጠለም፤ እንዲሁም ሊንዳ የምትባለው ሌላዋ ሴት ልጃችን በጦርነቱ ጊዜ በአሳዛኝ ሁኔታ ሞተች።
ወደ ስፔይን ለመዛወር ያደረግነው ውሳኔ
የእናቴ ምሳሌነትና ማበረታቻ ሚስዮናዊ ሆኖ የማገልገልን ፍላጎት በውስጤ ተክሎ የነበረ ሲሆን ይህን ግብ ፈጽሞ ዘንግቼው አላውቅም። ስለዚህ ዩኒስ በ1973 እንግሊዝን ለቅቃ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ወደ ስፔይን ስትሄድ ተደስተን ነበር። እርግጥ ከእኛ ተለይታ በመሄዷ ቅር ቢለንም በውጪ አገር ለማገልገል በመፈለጓ ግን ኩራት ተሰምቶን ነበር።
በእነዚህ ዓመታት ዩኒስን እየሄድን ጠይቀናታል። እግረ መንገዳችንንም ስፔይንን በደንብ ለማወቅ ቻልን። እንዲያውም ጆንና እኔ ከተመደበችባቸው የተለያዩ ቦታዎች ውስጥ በአራቱ ተገኝተን ጠይቀናታል። ዓመታት እያለፉ በሄዱ ቁጥር ግን ጉልበታችን እየተዳከመ ሄደ። ጆን በአንድ ወቅት በመውደቁ ምክንያት ጤንነቱ በጣም ተጎድቶ ነበር። እኔ ደግሞ የልብና የታይሮይድ ችግሮች አሉብኝ። ከዚህም በላይ ሁለታችንም የአንጓ ብግነት በሽታ (አርትራይተስ) አለብን። የዩኒስ እርዳታ በጣም ቢያስፈልገንም ለእኛ ስትል ግን አገልግሎቷን እንድትተው አልፈለግንም።
ያሉንን አማራጮች ከዩኒስ ጋር ተወያየን፤ መመሪያም ለማግኘት ጸለይን። ወደ ቤት መጥታ ልትረዳን ፈቃደኛ ብትሆንም ጆንና እኔ ከእሷ ጋር ለመኖር ወደ ስፔይን መሄዱ የተሻለ መፍትሔ ሆኖ ስላገኘነው ወደ ስፔይን ለመሄድ ወሰንን። እኔ ሚስዮናዊ መሆን ካልቻልኩ ሌላው ቢቀር ሴት ልጄና ሁለቱ አቅኚ ጓደኞቿ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲቀጥሉ ልደግፋቸው እችላለሁ። በዚያን ጊዜ ጆንና እኔ ለ15 ዓመታት ያክል ከዩኒስ ጋር በአቅኚነት ያገለገሉትን ኑሪያንና አናን እንደ ራሳችን ሴት ልጆች አድርገን እናያቸው ነበር። እነሱም ተመድበው በሚሄዱበት በየትኛውም ቦታ አብረናቸው በመኖራችን ደስተኞች ነበሩ።
ያንን ውሳኔ ካደረግን ከስድስት የሚበልጡ ዓመታት አልፈዋል። በሽታችን አልተባባሰም እንዲሁም ሕይወታችን ይበልጥ አስደሳች ሆኖልናል። አሁንም ቢሆን ስፓንኛ በደንብ መናገር አልችልም። ይሁን እንጂ ይህ ከመስበክ አያግደኝም። ጆንና እኔ በደቡብ ምዕራብ ስፔይን በኤክስትሪማዱራ የሚገኘው ትንሽ ጉባኤ ውስጥ ስንሰበሰብ ባይተዋርነት ተሰምቶን አያውቅም።
በስፔይን መኖሬ ስለ መንግሥቱ ስብከት ሥራ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ብዙ ነገር አስተምሮኛል። ኢየሱስ ክርስቶስ “እርሻውም ዓለም ነው” ብሎ ሲናገር ምን ማለቱ እንደነበር አሁን ይበልጥ ለማስተዋል ችያለሁ።—ማቴዎስ 13:38
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አቅኚነት በ1930ዎቹ