የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
እያንዳንዱን አጋጣሚ መጠቀም
የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማር ሥራቸው በዓለም ዙሪያ ይታወቃሉ። ከዚህም በተጨማሪ ለኅብረተሰቡ ጥቅም የሚያስገኙ ሌሎች ፕሮግራሞችንም ያካሂዳሉ። ከኢኳዶር የተገኙት ቀጥሎ ያሉት ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ይህ ሕዝባዊ አገልግሎት ጥሩ ምላሽ አግኝቷል።
◻ የአንድ ትልቅ የብርጭቆ ፋብሪካ የአስተዳደር ቢሮ ለሠራተኞቹ በቤተሰብ ዕሴቶች ላይ ትምህርት እንዲሰጥ የሚያስችል ዝግጅት ለማስተባበር ፈለገ። የሠራተኞች ጉዳይ አስፈጻሚ ቢሮ ዲሬክተር በዚህ ጉዳይ ላይ ትምህርት እንዲሰጡ ለበርካታ የካቶሊክ ቄሶች ግብዣ ቢያቀርቡም ምንም ምላሽ ሳያገኙ ቀሩ። አንድ ቄስ፣ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ትምህርት ለመስጠት ብቃት ያላቸው ቄሶች በጣም ጥቂት በመሆናቸው ማንም ሊገኝ እንደማይችል ለዲሬክተሩ ነገሩ። በዚያ ድርጅት ውስጥ የምትሠራ አንዲት እህት ይህን ስትሰማ፣ አብዛኛውን ጊዜ የንግድ ክልሎችን የሚሸፍን አንድ ወንድም ወደ ፋብሪካው መጥቶ እንዲያነጋግራቸው ዝግጅት አደረገች።
በሚቀጥለው ቀን የይሖዋ ምሥክሩ ትምህርቱን ለመስጠት ለሠራተኞች ጉዳይ ዲሬክተር ሐሳብ አቀረበ። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ከሚያሳትማቸው የተለያዩ ጽሑፎች ርዕሶችን መርጦ አሳያቸው። ዲሬክተሩ በጉዳዩ ተደነቁ። ለውይይት የሚሆኑ ሦስት ርዕሶችን ማለትም ማኅበራዊ ግንኙነት፣ ግብረገብነት በሥራ ቦታ እና ግብረገብነት በቤተሰብ መካከል የሚሉትን መረጡ። ከዚያም ትምህርቱ ለሠራተኞቹ በሙሉ የሚቀርብበት ዝግጅት ተደረገ።
ሠራተኞቹ ሠላሳ ሠላሳ በመሆን በሰባት ቡድን ከተከፋፈሉ በኋላ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሦስት ወንድሞች ትምህርቱን አቀረቡ። ምን ውጤት ተገኘ? በርካታ ቁጥር ያላቸው ሠራተኞች ቤታቸው መጥተው እንዲያነጋግሯቸው የጠየቁ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ 216 ጽሑፎችም ተበርክተዋል። የአስተዳደር ቢሮው በጉዳዩ በጣም ከመደነቁ የተነሳ ምሥክሮቹ ሌላ ተከታታይ ንግግሮች ማዘጋጀት ይችሉ እንደሆነ ጠየቀ።
◻ ኢኳዶር፣ በትምህርት ቤት የሃይማኖት ትምህርት እንዲሰጥ የሚፈቅድ ሕግ በቅርቡ አጽድቃለች። አንዲት ሚስዮናዊ እህት ወደ አንዲት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪዎች ተቆጣጣሪ በመሄድ አዲሱን ሕግ በምን መልኩ በሥራ ላይ እንዳዋሉት ጠየቀቻት። በማርያም አምልኮ ላይ የተመሠረተ አንድ ፕሮግራም ለመጀመር ሙከራ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም በተግባር ሳይውል መቅረቱን ተቆጣጣሪዋ ገለጸችላት። ይህ ዓይነቱ አምልኮ ካቶሊክ ላልሆኑ ልጆች ችግር ሊፈጥር እንደሚችል እህት ሐሳብ ባቀረበች ጊዜ ተቆጣጣሪዋ በሐሳቡ ተስማማች። “ሆኖም እኛ የአንድን ሰው ሃይማኖት የማይነካ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰደ የስነ ምግባር ትምህርት የምንሰጥበት ፕሮግራም አለን” በማለት ሚስዮናዊቷ እህት ገለጸች። የተማሪዎች ተቆጣጣሪዋ “ከነገ ወዲያ መምጣት ትችያለሽ?” ብላ ጠየቀች። ሚስዮናዊቷ እህት ታላቁን አስተማሪ ማዳመጥ የተባለውን መጽሐፍ ካሳየቻት በኋላ፣ “ሰላማዊ የሆኑ ሰዎች ደስተኞች ናቸው” በሚለው ምዕራፍ ላይ የቀረበው ትምህርት እንዲሰጥ ተወሰነ።
ሚስዮናዊቷ እህት ተመልሳ ሄደችና ተቆጣጣሪዋ በተገኘችበት በተለያዩ ሰባት ክፍሎች ውስጥ ትምህርት በመስጠት ሦስት ሰዓት አሳለፈች። የአምስተኛ ክፍል ተማሪዎችን አስተምራ ስትጨርስ ከተማሪዎቹ አንዱ “እባክዎ ሄደው ስድስተኛ ክፍሎችንም ያስተምሩዋቸው። ሁልጊዜ ይመቱናል፣ እንዲሁም ነገር ይፈልጉናል!” አላት። አንዲት አስተማሪ ደግሞ “ጠብ፣ ሰፊ ጊዜ ወስደን ልንወያይበት የሚገባ በጣም አስፈላጊ ርዕስ ነው” በማለት ሐሳብ አቀረበች።
ወደ ትምህርት ቤቱ እየመጣች ታዛዥነት እና መዋሸት በሚሉ ጭብጦች ላይ ትምህርት እንድትሰጥ ዝግጅት ተደረገ። እስካሁን አጥጋቢ ውጤቶች ተገኝተዋል። ተማሪዎቹ ሚስዮናዊቷን መንገድ ላይ ሲያገኝዋት ሰላምታ ለመስጠት ሮጠው ከመምጣታቸውም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች ይጠይቋታል። ሌሎቹ ደግሞ በኩራት ከወላጆቻቸው ጋር ያስተዋውቋታል። ከዚህም በተጨማሪ ከተማሪዎቹ መካከል ከሁለቱ ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀምሯል።