ቤተሰብን ለመንከባከብ ያለውን ኃላፊነት መሸከም
“አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቈጡአቸው።” (ኤፌሶን 6:4) ሐዋርያው ጳውሎስ በእነዚህ በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፉ ቃላት አማካኝነት ቤተሰብን የመንከባከብ ኃላፊነት በአባትየው ጫንቃ ላይ እንደሚወድቅ በግልጽ አስቀምጦታል።
በአብዛኞቹ ቤተሰቦች ውስጥ አባትየው ልጆቹን የሚንከባከበው ብቻውን አይደለም። የልጆቹ እናት የሆነችው ሚስቱ ሸክሙን ከባልዋ ጋር በደስታ ትጋራለች። ከዚህም የተነሳ ንጉሥ ሰሎሞን እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ልጄ ሆይ፣ የአባትህን ምክር ስማ፣ የእናትህንም ሕግ አትተው።”—ምሳሌ 1:8
ቁሳዊ እና መንፈሳዊ እንክብካቤ
ልጆቻቸውን የሚያፈቅሩ ወላጆች ሆን ብለው ችላ አይሏቸውም። ክርስቲያኖች እንደዚያ ቢያደርጉ እምነታቸውን የመካድ ያህል ይቆጠርባቸዋል። እንዲህ የምንለው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ከጻፋቸው ከሚከተሉት ቃላት በመነሳት ነው:- “ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፣ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው።” (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ክርስቲያኖች ልጆችን “በጌታ ምክርና በተግሣጽ” ማሳደግ ቁሳዊ ነገሮችን ከማሟላት እጅግ የላቀ ነገር እንደሚጠይቅ ይገነዘባሉ።
እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት በሞአብ ሜዳ ሰፍረው በነበሩበት ጊዜ ሙሴ ለእስራኤል ሕዝብ የሰጠውን ጥብቅ ምክር ተመልከት። በዚያ ቦታ የአምላክን ሕግ በድጋሚ ከነገራቸው በኋላ “እንግዲህ እነዚህን ቃሎች በልባችሁና በነፍሳችሁ አኑሩ” በማለት መመሪያ ሰጣቸው። (ዘዳግም 11:18) ከዚህ ቀደም በሙሉ ልባቸው፣ ነፍሳቸውና ኃይላቸው ይሖዋን መውደድ እንደሚኖርባቸው ከገለጸ በኋላ “እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ” በማለት አሳስቧቸው ነበር። (ዘዳግም 6:5, 6) እስራኤላውያን ወላጆች የአምላክ ሕግ ቃሎች ልባቸው ውስጥ ጠልቆ እንዲገባ መፍቀዳቸው በጣም አስፈላጊ ነበር። ልባቸው በመንፈሳዊ አድናቆት ከተሞላ ሙሴ ቀጥሎ የተናገራቸውን ቃላት ውጤታማ በሆነ መንገድ መፈጸም ይችላሉ:- “[የአምላክን ሕግ ቃሎች] ለልጆችህም አስተምረው [“በልጆችህ አእምሮ ውስጥ ቅረጸው፣” NW]፣ በቤትህም ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም፣ ስትነሣም ተጫወተው [“ንገረው፣” NW]።”—ዘዳግም 6:7፤ 11:19፤ ከማቴዎስ 12:34, 35 ጋር አወዳድር።
አባቶች እነዚህን ቃሎች በልጆቻቸው አእምሮ ውስጥ “መቅረጽ” እና ለልጆቻቸው “መንገር” ይጠበቅባቸው እንደነበር ልብ በሉ። “መቅረጽ” የሚለውን ቃል ሚርያም ዌብስተርስ ኮሊጂየት ዲክሽነሪ “ሳያሰልሱ በመደጋገም ወይም በመምከር ማስተማርና አእምሮ ላይ መትከል” በማለት ይፈታዋል። በየዕለቱ ማለዳ፣ ቀንና ማታ ወላጆች ስለ አምላክ ቃል የሚናገሩ ከሆነ ልጆቻቸው ከፍተኛ ትምህርት ያገኛሉ። ወጣቶች ወላጆቻቸው ለአምላክ ሕግ ፍቅር እንዳላቸው በሚያዩበት ጊዜ እነርሱም ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንዲመሰርቱ ተጽዕኖ ያሳድርባቸው ነበር። (ዘዳግም 6:24, 25) ሙሴ ‘ቤታቸው በሚሆኑበት ጊዜ’ ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩ በተለይ አባቶችን ማዘዙ ትኩረት የሚስብ ነው። በዚህ መልኩ ማስተማር ለቤተሰብ እንክብካቤ የሚደረግበት አንዱ ክፍል ነበር። በዛሬውስ ጊዜ ሁኔታው ምን ይመስላል?
“በቤትህም ስትቀመጥ”
ጃነት የተባለች አራት ልጆች ያሏት አንዲት ክርስቲያን እናት “ቀላል አይደለም” በማለት ትገልጻለች።a ባለቤቷ ፖል “ጽናት ይጠይቅባችኋል” በማለት በአባባሏ ይስማማል። ፖልና ጃነት እንደ አብዛኞቹ ሌሎች የይሖዋ ምሥክር ወላጆች ሁሉ ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ ከልጆቻቸው ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ጥረት ያደርጋሉ። “ሁልጊዜ ሰኞ ማታ በተወሰነ ሰዓት ላይ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግ እንጥራለን፤ ሆኖም አልፎ አልፎ የማይሳካበት ጊዜ አለ” ሲል ፖል ሳይሸሽግ ተናግሯል። በጉባኤው ውስጥ የተሾመ ሽማግሌ እንደመሆኑ መጠን አንዳንድ ጊዜ አጣዳፊ በሆኑ ጉዳዮች ምክንያት ይጠራል። የመጀመሪያዎቹ ሁለት ልጆቹ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ናቸው። በስብከቱ ሥራ ሰዎችን ለማግኘት በምሽት ማገልገሉን ውጤታማ ሆኖ አግኝተውታል። ከዚህ የተነሳ የቤተሰብ ጥናት የሚያደርጉበትን ሰዓት አንድ ላይ ሆነው አስተካክለዋል። “አንዳንድ ጊዜ ጥናታችንን የምናደርገው ወዲያው እራት በልተን እንደጨረስን ነው” ሲል ፖል ይገልጻል።
ምንም እንኳ ወላጆች የቤተሰብ ጥናት የሚያደርጉበትን ጊዜ እንደ አስፈላጊነቱ በጥበብ ቢቀያይሩም ጥናቱ ሳይቋረጥ እንዲደረግ ይጥራሉ። “ጥናት የምናደርግበትን ሰዓት የግድ መቀየር ካስፈለገ ሁላችንም በስንት ሰዓት ላይ እንደሚደረግ ማወቅ እንድንችል አባባ አዲሱን የጥናት ጊዜ ማቀዝቀዣው መዝጊያ ላይ ይለጥፍልናል” በማለት ሴት ልጁ ክላር ትናገራለች።
ቋሚ ለሆነ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አንድ ላይ መገናኘቱ የቤተሰቡ አባል የሆኑት ወጣት ልጆች ጭንቀቶቻቸውንና ችግሮቻቸውን ለወላጆቻቸው እንዲያካፍሉ ጥሩ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። እንዲህ ዓይነቱ ጥናት ጥሩ ውጤት የሚያስገኘው ልጆቹ ለሚቀርቡት ጥያቄዎች ከሚጠናው መጽሐፍ በቀጥታ በማንበብ ብቻ እንዲመልሱ የማይገደዱ ከሆነ ነው። የሁለት ወንዶች ልጆች አባት የሆነው ማርቲን “የቤተሰብ ጥናታችን ውይይት የምናደርግበት መድረክ ነው” በማለት ይገልጻል። “በሳምንት አንድ ጊዜ ቅዱስ ጽሑፋዊ በሆነ ትምህርት ላይ ለመወያየት አብራችሁ ስትገናኙ ቤተሰባችሁ በምን ዓይነት መንፈሳዊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ እንድታውቁ ያደርጋችኋል” ሲል ሐሳብ ይሰጣል። “በውይይቱ ወቅት ብዙ የተለያዩ ነገሮች ይነሳሉ። በትምህርት ቤት ምን ሁኔታዎች እንዳሉ የማወቅ አጋጣሚ ይኖራችኋል። ከዚህ ይበልጥ ጠቃሚ የሆነው ልጆቻችሁ ምን ዓይነት አመለካከት እያዳበሩ እንዳሉ ለመረዳት ትችላላችሁ።” ባለቤቱ ሳንድራ በዚህ ሐሳብ ከመስማማቷም በላይ ከቤተሰብ ጥናቱ ከፍተኛ ጥቅም እያገኘች እንዳለች ይሰማታል። “ባለቤቴ ጥናቱን በሚመራበት ጊዜ ልጆቹ የሚጠይቃቸውን ጥያቄዎች እንዴት እንደሚመልሱ በማዳመጥ ስለ እነሱ ብዙ ማወቅ እችላለሁ” በማለት ትናገራለች። ከዚያም ልጆቹን ሊጠቅም በሚችል መንገድ ሐሳብ ትሰጣለች። በጥናቱ ላይ ንቁ ተሳትፎ ስለምታደርግ ጥናቱ ይበልጥ አስደሳች ሆኖላታል። አዎን፣ የቤተሰብ ጥናት የሚደረግባቸው ጊዜያት ወላጆች የልጆቻቸውን አስተሳሰብ በጥልቅ እንዲረዱ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል።—ምሳሌ 16:23፤ 20:5
ራሳችሁን ከሁኔታዎች ጋር የምታስማሙና ጽኑ ሁኑ
የቤተሰብ ጥናት በምታደርጉበት ጊዜ አንደኛው ልጅ ደስ ብሎት በንቃት ሲከታተል ሌላኛው ደግሞ በትኩረት እንዲከታተልና ከቤተሰብ ጥናቱ ጥቅም እንዲያገኝ ትንሽ ማባበል አስፈላጊ ሆኖ ታገኙት ይሆናል። አንዲት ክርስቲያን እናት እንዲህ ስትል ሐሳብ ሰጥታለች:- “የቤተሰብ ሕይወት እንደዚህ ነው! ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ታውቃላችሁ። ስለዚህ የቤተሰብ ጥናቱን ሳታቋርጡ በምታደርጉበት ጊዜ ይሖዋ ይረዳችኋል፤ ውጤትም ታገኙበታላችሁ።”
የአንድ ልጅ በትኩረት የመከታተል ችሎታ እንደ ዕድሜው መጠን በጣም ሊለያይ ይችላል። አስተዋይ የሆነ ወላጅ ይህን ግምት ውስጥ ያስገባል። አንድ ባልና ሚስት ዕድሜያቸው ከ6 እስከ 20ዎቹ ባለው መካከል ያሉ አምስት ልጆች አሏቸው። አባታቸው ማይክል እንዲህ ይላል:- “ጥያቄዎቹን እንዲመልስ በመጀመሪያ እድሉን ለትንሹ ልጅ ስጡ። ከዚያም ትልልቆቹ ልጆች ዝርዝር ሐሳቦችን እንዲናገሩና የተዘጋጁዋቸውን ተጨማሪ ነጥቦች እንዲያክሉ አድርጉ።” ወላጆች በዚህ መንገድ ልጆቻቸውን በማስተዋል መያዛቸው ለሌሎች አሳቢነት የማሳየትን አስፈላጊነት ለማስተማር ያስችላቸዋል። “አንደኛው ልጅ ነጥቡን ይረዳ ይሆናል፤ ሌላኛው ግን ነጥቡ እስኪገባው ድረስ ተጨማሪ ማብራሪያ ይፈልግ ይሆናል” ሲል ማርቲን ይገልጻል። “የጥናቱ ክፍለ ጊዜ ክርስቲያናዊ ትዕግስትና ሌሎች የመንፈስ ፍሬዎች እንዳሳይ ስልጠና የማገኝበት ዝግጅት ሆኖ አግኝቸዋለሁ።”—ገላትያ 5:22, 23፤ ፊልጵስዩስ 2:4
ልጆቻችሁ ካላቸው የተለያየ ዓይነት ችሎታና የእድገት ደረጃ ጋር ራሳችሁን ለማስማማት ዝግጁ ሁኑ። በአሁኑ ጊዜ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙት ሳይመንና ማርክ ልጆች በነበሩበት ጊዜ እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተባለውን መጽሐፍ ከወላጆቻቸው ጋር ማጥናታቸው በጣም አስደሳች ሆኖ አግኝተውት ነበር። “አባታችን የተለያዩ ክፍሎችን በተውኔት መልክ እንድናሳይ ያደርግ ነበር” በማለት ያስታውሳሉ። አባታቸው ከልጆቹ ጋር ሆኖ ስለ ደጉ ሳምራዊ የሚናገረውን ምሳሌ በተግባር ለማሳየት በእጁና በጉልበቱ በእንብርክክ መሄዱን ያስታውሳል። (ሉቃስ 10:30-35) “አቀራረቡ እውነታውን የሚያንጸባርቅና በጣም የሚያስቅ ነበር።”
ብዙ ልጆች ዘወትር በሚደረግ የቤተሰብ ጥናት አይደሰቱ ይሆናል። ታዲያ ይህ በታቀደው ጊዜ ጥናቱን ከማድረግ ወላጆችን ሊያግዳቸው ይገባልን? በፍጹም። ምሳሌ 22:15 “ስንፍና በሕፃን ልብ ታስሮአል” በማለት ይገልጻል። አንዲት ነጠላ እናት የጥናቱ ክፍለ ጊዜ በተለያዩ ምክንያቶች ብዙ ጊዜ ሲስተጓጎል የቤተሰብ ጥናቱን የመምራት ብቃት እንደሌላት ተሰማት። ሆኖም በጽናት ቀጠለች። ባሁኑ ወቅት፣ በጽናት ቋሚ የሆነ የቤተሰብ ጥናት በመምራት ያሳየቻቸውን ፍቅርና አሳቢነት ልጆችዋ ከፍ አድርገው ከመመልከታቸውም በላይ ለእሷ ጥልቅ አክብሮት አላቸው።
“አባት” የሌላቸውን ልጆች መርዳት
ክርስቲያን ሽማግሌዎች ‘በእነሱ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ እንዲጠብቁ’ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። (1 ጴጥሮስ 5:2, 3) አልፎ አልፎ በጉባኤያቸው ውስጥ ያሉትን ቤተሰቦች መጎብኘታቸው ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶቻቸውን የሚወጡትን ወላጆች ለማመስገን አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። የነጠላ ወላጆችን ልጆች የማስተማሩ ኃላፊነት የሚወድቀው በማን ጫንቃ ላይ ነው? ልጆቹን የማስተማሩ ኃላፊነት የወላጅ መሆኑን በፍጹም አትዘንጉ።
ሽማግሌዎች የሌለውን ወላጅ ለመተካት በመሞከር ድርሻውን የሚሸከሙ ከሆነ ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን የሚያስጥሳቸው ነገር እንዳያደርጉ ክርስቲያናዊ ማስተዋል ይረዳቸዋል። ምንም እንኳ ሁለት ወንድሞች ነጠላ ወላጅ የሆነችን ክርስቲያን እህት መጎብኘት ቢችሉም የቤተሰብ ጥናት ዝግጅቱን ለመደገፍ ብለው አንዳንድ ዝግጅቶች ሲያደርጉ ምንጊዜም ጠንቃቃ መሆን አለባቸው። አልፎ አልፎ የራሱ የሽማግሌው ቤተሰብ በሚያደርገው የቤተሰብ ጥናት ላይ እንዲገኙ ልጆቹን መጋበዙ (ነጠላ ወላጁንም ጭምር) ገንቢና ተግባራዊ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ይሖዋ በሰማይ ያለ ታላቅ አባታችን መሆኑን በፍጹም አትርሱ። ምንም እንኳ እናትየው ብቻዋን ሆና ከልጆቹ ጋር ጥናቱን ብትመራም እሷን ለመምራትና ለመርዳት ይሖዋ እንደሚገኝ አያጠራጥርም።
አንድ ልጅ ጥሩ መንፈሳዊ አመለካከት ኖሮት ወላጆቹ ግን ለመንፈሳዊ ኃላፊነቶታቸው ቸልተኞች ቢሆኑስ ምን ማድረግ ይቻላል? ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች በጭራሽ ተስፋ መቁረጥ የለባቸውም። መዝሙራዊው “ድሀ ራሱን ለአንተ [ለይሖዋ አምላክ] ይተዋል፣ ለድሀ አደግም ረዳቱ አንተ ነህ” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 10:14) በመሆኑም በጉባኤ ውስጥ ያሉ አፍቃሪ ሽማግሌዎች ወላጆች ልጆቻቸውን ለማሳደግ በሚያደርጉት ጥረት ማበረታቻ ለመስጠት የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። ሽማግሌዎቹ ቤተሰቡ አንድ ላይ እንዲወያይ ሐሳብ ሊያቀርቡና በዚያም ተገኝተው እንዴት አንድ ላይ ሊያጠኑ እንደሚችሉ ለማሳየት አንዳንድ ተግባራዊ ሐሳቦችን ሊሰጡ ይችላሉ። እርግጥ፣ የወላጁን ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነት ከጫንቃው ላይ ያወርዱለታል ማለት አይደለም።
ወላጆቻቸው እውነትን ያልተቀበሉ ልጆች የበለጠ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ወላጆቻቸው የሚፈቅዱ ከሆነ በቤተሰብ ጥናታችሁ ላይ እንዲገኙ ማድረጋችሁ ጠቃሚ ሆኖ ሊገኝ ይችላል። ባሁኑ ጊዜ የራሱ ቤተሰብ ያለው ሮበርት ገና የሦስት ዓመት ልጅ እያለ ከቤተሰቦቹ ጋር በክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ ይገኝ ነበር። ወላጆቹ ከክርስቲያን ጉባኤ ከቀሩ በኋላ እንኳ ስለእነዚያ ስብሰባዎች አስደሳች የሆኑ ትዝታዎች አሉት። የአሥር ዓመት ልጅ ሳለ የይሖዋ ምሥክር ከሆነ አንድ ልጅ ጋር ተገናኘና ወደ ስብሰባዎች ይወስደው ጀመር። የዚህ ልጅ ወላጆች ሮበርትን በመንፈሳዊ አሳዳጊ እንደሌለው ልጅ በመቁጠር በደስታ ተንከባከቡት፤ መጽሐፍ ቅዱስንም አስጠኑት። ከዚህ ፍቅራዊ እንክብካቤ የተነሳ ፈጣን እድገት ያደረገ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በጉባኤው ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ የማገልገል መብት አግኝቷል።
ወላጆች ልጆቻቸው የሚያደርጉትን እድገት ቢቃወሙ እንኳ ልጆቹ ያለ ደጋፊ አይቀሩም። ምንጊዜም ታማኝ ሰማያዊ አባት የሆነው ይሖዋ አለ። “እግዚአብሔር በቅዱስ ቦታው ለድሀ አደጎች አባት . . . ነው” በማለት መዝሙር 68:5 ይገልጻል። በመንፈሳዊ አባት የሌላቸው ልጆች እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ በጸሎት መቅረብ እንደሚችሉ ያውቃሉ፤ ይሖዋም ይደግፋቸዋል። (መዝሙር 55:22፤ 146:9) እንደ እናት የሆነው የይሖዋ ድርጅት በጽሑፎችና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ከ85,000 በላይ የሚሆኑ ክርስቲያን ጉባኤዎች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች አማካኝነት አርኪ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ በማቅረብ ኃላፊነቱን በትጋት ያሟላል። ስለዚህ ይሖዋ አባታችንና እናት መሰል ድርጅቱ በሚያቀርቡት መንፈሳዊ እርዳታ ‘አባት የሌላቸው’ እንኳ ሳይቀሩ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ደስታ ሊያገኙ ይችላሉ።
ከልጆቻቸው ጋር በመሆን በቋሚነት የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚያደርጉ ክርስቲያን ወላጆች ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። ልጆቻቸውን በይሖዋ መንገድ በጽናት የሚያሰለጥኑ ነጠላ ወላጆች ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸውና ለሚያደርጉት ጥረት ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። (ምሳሌ 22:6) በመንፈሳዊ አባት ለሌላቸው ልጆች አሳቢነት የሚያሳዩ ሁሉ እንዲህ ማድረጋቸው በሰማይ የሚኖረውን ይሖዋ አባታችንን እንደሚያስደስተው ያውቃሉ። አንድ ቤተሰብ በመንፈሳዊ የሚያስፈልገውን ማሟላት ከባድ ኃላፊነት ነው። ሆኖም ‘ሳትዝሉ ከቀጠላችሁ በጊዜው ስለምታጭዱ መልካም ሥራን ለመሥራት አትታክቱ።’—ገላትያ 6:9
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቤተሰብ ጥናት ልጆች የሚያሳስቧቸውን ነገሮች ለወላጆቻቸው እንዲነግሩ ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Harper’s