አሰቃቂ ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት አገኘሁ
ኢቫ ዩሴፍሶን እንደተናገረችው
ለክርስቲያናዊ አገልግሎት ከመሰማራታችን በፊት ሃንጋሪ ውስጥ በቡዳፔስት አውራጃ በምትገኘው በዩፔሽት ጥቂት ሆነን አጭር ስብሰባ ለማድረግ ተገናኝተን ነበር። ጊዜው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመጀመሩ ትንሽ ቀደም ብሎ በ1939 ሲሆን ሃንጋሪ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች የስብከት ሥራ ታግዶ ነበር። በዚያን ወቅት በግልጽ መጽሐፍ ቅዱስን ሲያስተምሩ የተገኙ አብዛኛውን ጊዜ ይታሰሩ ነበር።
በዚህ ሥራ ስሳተፍ የመጀመሪያ ጊዜዬ ስለሆነ በመጠኑ እንደተጨነቅሁና እንደፈራሁ ያስታውቅብኝ ነበር። አንድ በዕድሜ ሸምገል ያለ ክርስቲያን ወንድም ተመለከተኝና “ኢቫ በፍጹም መፍራት የለብሽም። ይሖዋን ማገልገል አንድ ሰው ሊያገኘው ከሚችለው መብት ሁሉ የላቀ ነው” አለኝ። እነዚህ አሳቢነት የተሞላባቸውና ብርታት የሚሰጡ ቃላት ብዙ አሰቃቂ ፈተናዎችን ችዬ በጽናት እንድቋቋም ረድተውኛል።
አይሁዳዊ ቤተሰብ
አምስት ልጆች ባሉበት በአንድ አይሁዳዊ ቤተሰብ ውስጥ የመጀመሪያ ልጅ ነበርኩ። እናቴ የአይሁድ እምነት ምንም ስላላረካት ሌሎች ሃይማኖቶችን ትመረምር ጀመር። እንደ እሷ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በመፈለግ ላይ ከነበረችው ከሌላዋ አይሁዳዊት ሴት ከኤርዜቤት ስሌዚንገር ጋር የተገናኘችው በዚህ ምክንያት ነበር። ኤርዜቤት እናቴን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር አገናኘቻት። በዚህም አማካኝነት እኔም ለመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጥልቅ ፍላጎት አደረብኝ። ብዙም ሳልቆይ የተማርኩትን ነገር ለሌሎች ማካፈል ጀመርኩ።
በ1941 የበጋ ወቅት 18 ዓመት ከሆነኝ በኋላ ራሴን ለይሖዋ አምላክ መወሰኔን በዳኑብ ወንዝ በጥምቀት አሳየሁ። በተመሳሳይ ጊዜ እናቴም ተጠመቀች፤ አባቴ ግን አዲሱን የክርስትና እምነታችንን አልተቀበለም ነበር። ወዲያው እንደተጠመቅሁ አቅኚ ለመሆን ማለትም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመሳተፍ ዕቅድ አወጣሁ። ብስክሌት ያስፈልገኝ ስለነበር በአንድ ትልቅ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ቤተ ሙከራ ውስጥ ተቀጥሬ መሥራት ጀመርኩ።
የመጀመሪያዎቹ ፈተናዎች
ሃንጋሪ በናዚዎች ቁጥጥር ስር ወደቀች፤ የምሠራበት ፋብሪካም በጀርመኖች አስተዳደር ሥር ሆነ። አንድ ቀን ሠራተኞቹ ሁሉ በፋብሪካው ባለሥልጣኖች ፊት ቀርበው ለናዚዎች ታማኝ ለመሆን ቃለ መሐላ እንዲገቡ ተጠሩ። ይህን አለማድረግ አስከፊ መዘዞች እንደሚያስከትል ተነገረን። ሂትለርን እንድናወድስ በተጠየቅንበት በዚህ ክብረ በዓል ላይ በአክብሮት ተነስቼ ብቆምም እንድንፈጽም የተጠየቅነውን ድርጊት ግን አልፈጸምኩም ነበር። የዚያኑ ዕለት ወደ ቢሮ ተጠርቼ ደሞዜ ከተሰጠኝ በኋላ ከሥራ ተባረርኩ። ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ ስለነበር አቅኚ ለመሆን የነበረኝን ዕቅድ እንዴት እንደማሳካ ግራ ገባኝ። ሆኖም በሚቀጥለው ቀን የተሻለ ደሞዝ ያለው አዲስ ሥራ አገኘሁ።
አሁን፣ አቅኚ ለመሆን ያለኝ ፍላጎት ሊሳካ ይችላል። አቅኚ የሆኑ በርካታ የአገልግሎት ጓደኞች ነበሩኝ፤ የመጨረሻዋ ጓደኛዬ ዩሊሽካ ኦስተሎሽ ነበረች። የምናበረክተው ምንም ጽሑፍ ስላልነበረን ለአገልግሎት የምንጠቀመው በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነበር። ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በምናገኝበት ጊዜ ተመላልሶ መጠየቅ እናደርግላቸውና ጽሑፎች እናውሳቸው ነበር።
እኔና ዩሊሽካ እናገለግልበት የነበረውን ክልል በተደጋጋሚ መቀየር ነበረብን። እንዲህ የምናደርግበት ምክንያት አንድ ቄስ ‘የእሱን በጎች’ እያነጋገርን መሆናችንን ሲያውቅ የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው ካነጋገሯቸው ለእሱ ወይም ለፖሊስ እንዲናገሩ በቤተ ክርስቲያኑ ማሳሰቢያ ይሰጣቸው ስለነበረ ነው። እኛን የሚወዱን ሰዎች እንዲህ ዓይነት ማሳሰቢያ መሰጠቱን በሚነግሩን ጊዜ ወደ ሌላ ክልል እንሄድ ነበር።
አንድ ቀን እኔና ዩሊሽካ ፍላጎት ያለው አንድ ወጣት አነጋገርን። ተመልሰን መጥተን አንድ የሚያነበውን ጽሑፍ ለማዋስ ተቀጣጠርን። ሆኖም ተመልሰን ስንሄድ በቦታው ፖሊሶች ነበሩ። ተያዝንና በዱንአቬች ወደሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ተወሰድን። እኛን ለመያዝ ልጁን እንደ ወጥመድ ተጠቀሙበት። ፖሊስ ጣቢያው ስንደርስ አንድ ቄስ በቦታው ነበር፣ እሱም በጉዳዩ እንዳለበት አወቅን።
ከሁሉ የከፋው ፈተና
ፖሊስ ጣቢያ ከገባሁ በኋላ ፀጉሬን ሙልጭ አድርገው ላጩኝ፤ ከዚያም ወደ አሥራ ሁለት በሚጠጉ ፖሊሶች ፊት እርቃኔን አስቆሙኝ። በሃንጋሪ ያለው መሪያችን ማን እንደሆነ ለማወቅ በጥያቄዎች መረመሩኝ። ከኢየሱስ ክርስቶስ በስተቀር ማንም መሪ እንደሌለን ገለጽኩላቸው። ያለአንዳች ርህራሄ በፖሊስ ዱላ ደበደቡኝ ሆኖም ክርስቲያን ወንድሞቼን አሳልፌ አልሰጠሁም።
ከዚያም እግሮቼን አንድ ላይ ጠፍረውና እጆቼን ወደ ላይ አድርገው አሰሩኝ። ቀጥሎም ከአንደኛው ፖሊስ በስተቀር የተቀሩት ሁሉ እየተፈራረቁ አስገድደው ደፈሩኝ። ክፉኛ ጠፍረው አስረውኝ ስለነበረ ከሦስት ዓመታት በኋላ እንኳ በእጅ አንጓዎቼ ላይ የታሰርኩበት ምልክት ነበር። በጣም ተጎድቼ ስለነበር ከባድ የሆኑት ቁስሎቼ በመጠኑ እስኪሽሩ ድረስ ለሁለት ሳምንታት ምድር ቤት ውስጥ አቆዩኝ።
ፋታ ያገኘሁበት ጊዜ
ከጊዜ በኋላ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ወደነበሩበት በናጅኮኒዞ ወደሚገኝ እስር ቤት ተወሰድኩ። ምንም እንኳ ከእስር ባልለቀቅም በአንፃራዊ ሁኔታ አስደሳች የሆኑ ሁለት ዓመታት አለፉ። በድብቅ ስብሰባዎቻችንን በሙሉ ከማድረጋችንም በላይ ከሞላ ጎደል በጉባኤ መልክ እንቀሳቀስ ነበር። መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመስከር የሚያስችሉ ብዙ አጋጣሚዎችም ነበሩን። ለእኔና ለእናቴ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ያስተዋወቀችንን የኤርዜቤት ስሌዚንገር የሥጋ እህት ኦልጋ ስሌዚንገርን ያገኘኋት በዚህ እስር ቤት ውስጥ ነበር።
በሃንጋሪ የነበሩት ናዚዎች በ1944 ሃንጋርያውያን አይሁዶችን ለመደምሰስ ቆርጠው ነበር። ተቆጣጥረዋቸው በነበሩ ሌሎች ቦታዎችም አይሁዳውያንን በዘዴ ይገድሏቸው ነበር። አንድ ቀን እኔና ኦልጋን ፈልገው መጡ። በከብት ባቡር ፉርጎዎች አጎሩንና ቼኮዝሎቫኪያን አቋርጠን በጣም አድካሚ ከሆነ ጉዞ በኋላ በደቡባዊ ፖላንድ ወደሚገኘው የሞት ካምፕ ወደሆነው ኦሽዊትዝ ደረስን።
ከኦሽዊትዝ በሕይወት መትረፍ
ከኦልጋ ጋር በምሆንበት ጊዜ ስጋት አይሰማኝም ነበር። ሌላው ቀርቶ ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ስር ሆና እንኳ ተጫዋች ነች። ኦሽዊትዝ ስንደርስ አዲስ ከመጡት ውስጥ፣ ለሥራ ብቁ የሆኑትንና ያልሆኑትን የመለየት ኃላፊነት ወዳለው ዶክተር ሜንጌለ ወደሚባለው መጥፎ ሰው ፊት ቀረብን። ብቁ ያልሆኑት የመርዝ ጢስ ወዳለበት ክፍል ይላኩ ነበር። የእኛ ተራ በደረሰ ጊዜ ሜንጌለ ኦልጋን “ስንት ዓመትሽ ነው?” ብሎ ጠየቃት።
በቀልድ መልክ ዓይኖችዋን እያቁለጨለጨች በድፍረት “20” በማለት መለሰች። እንደ እውነቱ ከሆነ ዕድሜዋ የዚያ እጥፍ ነበር። ሆኖም ሜንጌለ በነገሩ ሳቀና በቀኝ በኩል እንድትሆን ነገራት። በዚህ መንገድ በሕይወት ለመትረፍ ቻለች።
በኦሽዊትዝ የነበሩ ሁሉም እስረኞች የእስር ቤት ልብሳቸው ላይ ምልክት ይደረግባቸው ነበር፤ ለአይሁዶች የዳዊት ኮከብ ሲሆን ለይሖዋ ምሥክሮች ደግሞ የወይን ጠጅ ቀለም ያለው ባለሦስት ማዕዘን ምልክት ነበር። በልብሶቻችን ላይ የዳዊትን ኮከብ ሊሰፉልን ሲሉ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንንና የወይን ጠጅ ቀለም ያለውን ባለሦስት ማዕዘን ምልክት እንደምንፈልግ ገለጽንላቸው። እንደዚህ ያልነው በአይሁዳዊነታችን ስላፈርን ሳይሆን የይሖዋ ምሥክሮች ስለሆንን ነው። የአይሁዶችን አርማ እንድንቀበል በድብደባ ለማስገደድ ሞክረው ነበር። ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን እስኪቀበሉ ድረስ በአቋማችን ጸናን።
ከጊዜ በኋላ የሦስት ዓመት ታናሽ እህቴ ከሆነችው ኤልቪረ ጋር ተገናኘሁ። ሰባት አባላት ካሉት ቤተሰባችን ውስጥ ማንም ሳይቀር ወደ ኦሽዊትዝ ተወስደን ነበር። ለሥራ ብቁ ሆነን ተቀባይነት ያገኘነው እኔና ኤልቪረ ብቻ ነበርን። አባቴ፣ እናቴና ሦስት ወንድሞቼና እህቶቼ የመርዝ ጭስ ባለበት ክፍል ውስጥ ተከተው ሞቱ። በዚያን ጊዜ ኤልቪረ የይሖዋ ምሥክር ስላልነበረች ካምፑ ውስጥ በአንድ ዓይነት የእስረኞች ክፍል አልነበርንም። በሕይወት ተርፋ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ከሄደች በኋላ በፒትስበርግ ፔንሲልቫኒያ የይሖዋ ምሥክር ሆነች። በመጨረሻም በ1973 እዚያው አረፈች።
ከሌሎች ካምፖችም በሕይወት መትረፍ
በ1944/45 የክረምት ወራት ሩሲያውያን ወደ ኦሽዊትዝ እየተጠጉ ስለነበር ጀርመኖች ካምፑን ለቀው ለመሄድ ወሰኑ። በዚህ ምክንያት የጀርመን ሰሜናዊ ክፍል ወደ ሆነው በርገንቤልዘን ተዛወርን። ወዲያው እዚያ እንደደረስን እኔና ኦልጋ ወደ ብራውንሽቪክ ተላክን። እዚህ የተላክነው የኅብረ ብሔሩ ጦር ከፍተኛ የቦንብ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ የነበረውን ፍርስራሽ በማጽዳት እንድንረዳ ተፈልጎ ነበር። እኔና ኦልጋ በጉዳዩ ላይ ተወያየን። በዚህ ሥራ መሳተፋችን ገለልተኝነታችንን ሊያጎድፍ ይችል ወይም አይችል እንደሆነ ስላላወቅን ሁለታችንም ላለመሥራት ወሰንን።
ውሳኔያችን በጣም አናደዳቸው። በአለንጋ ከተገረፍን በኋላ ወደሚረሽኑት ወታደሮች ተወሰድን። በጉዳዩ ላይ በድጋሚ እንድናስብበት አንድ ደቂቃ እንደሚሰጠንና አስተሳሰባችንን ካልቀየርን ግን እንደምንገደል ተነገረን። ውሳኔያችንን ስለማንቀይር በጉዳዩ ላይ ለማሰብ ምንም ጊዜ እንዲኖረን እንደማንፈልግ ነገርናቸው። ሆኖም የካምፑ አዛዥ በቦታው ስላልነበረና የሞት ቅጣት እንዲፈጸም ትእዛዝ ማስተላለፍ የሚችለው እሱ ብቻ በመሆኑ የምንገደልበት ጊዜ መዘግየት ነበረበት።
እስከዚያ ድረስ ቀኑን ሙሉ በካምፑ ግቢ ውስጥ እንድንቆም ተገደድን። ሁለት የታጠቁ ወታደሮች በየሁለት ሰዓቱ እየተቀያየሩ ይጠብቁን ነበር። ምንም ምግብ አልተሰጠንም፣ ጊዜው የካቲት ወር በመሆኑም ብርዱ አንሰፍስፎን ነበር። በዚህ መንገድ ለአንድ ሳምንት ተቀጣን፤ ሆኖም አዛዡ አልተመለሰም። በዚህ ምክንያት በአንድ የጭነት መኪና ላይ አሳፍረው ወደ በርገንበልዘን መለሱን። እንዲህ ይሆናል ብለን አልጠበቅንም ነበር።
በዚህ ጊዜ እኔና ኦልጋ በአስጊ ሁኔታ ላይ እንገኝ ነበር። ፀጉሬ በአብዛኛው ከመመለጡም በላይ ከፍተኛ ትኩሳት ነበረኝ። ትንሽ እንኳ መሥራት የምችለው በብዙ ሥቃይ ነበር። በየቀኑ የሚሰጠን ቀጭን የጎመን ሾርባና ትንሽ የዳቦ ቁራሽ ምንም አይጠቅመንም ነበር። ሆኖም መሥራት የማይችሉ ሁሉ ስለሚገደሉ የግድ መሥራት ነበረብን። ወጥቤት ውስጥ አብረውኝ ይሠሩ የነበሩት ጀርመናውያን እህቶች ጥቂት እረፍት እንዳገኝ ይረዱኝ ነበር። እህቶች ቁጥጥር የሚያደርጉት ጠባቂዎች በመምጣት ላይ እንዳሉ ሲያዩ በትጋት እየሠራሁ ያለሁ እንድመስል በሥራ ቦታዬ ላይ ቆሜ እንድገኝ አስቀድመው ምልክት ይሰጡኝ ነበር።
አንድ ቀን ኦልጋ ወደ ሥራ ቦታዋ ለመሄድ የሚያስችላት አቅም አጣች፤ ከዚያ በኋላ አላየናትም። በካምፖች ውስጥ ባሳለፍኳቸው በእነዚያ አስቸጋሪ ወራት ከፍተኛ እገዛ ታደርግልኝ የነበረችውን ደፋር ጓደኛዬንና አጋሬን አጣሁ። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅቡዕ ተከታይ እንደመሆንዋ መጠን ሰማያዊ ሽልማቷን ወዲያውኑ አግኝታ መሆን አለበት።—ራእይ 14:13
ከእስር ከተለቀኩ በኋላ ያሳለፍኩት ሕይወት
ግንቦት 1945 ጦርነቱ አክትሞ ነፃነት ሲገኝ በጣም ደክሜ ስለነበር በመጨረሻ ያንገላቱን የነበሩት ሰዎች ቀንበር ቢሰባበርም መደሰት አልቻልኩም፤ ነፃ የወጡትን ሰዎች ለመቀበል ፈቃደኛ ወደ ሆኑ አገሮች በሚወስዱት መኪናዎች ላይ መሳፈርም አልቻልኩም ነበር። እስካገግም ድረስ ለሦስት ወራት በአንድ ሆስፒታል ውስጥ ቆየሁ። ከዚያ በኋላ አዲስ መኖሪያዬ ወደ ሆነው ስዊድን ተወሰድኩ። ወዲያውኑ ከክርስቲያን ወንድሞቼና እህቶቼ ጋር ተገናኘሁ፤ በመጨረሻም ውድ ሃብት የሆነውን የመስክ አገልግሎት ተያያዝኩት።
ለዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ ካገለገለው ከሌናርት ዩሴፍሶን ጋር በ1949 ተጋባን። እሱም ቢሆን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለእምነቱ ሲል ጽኑ አቋም በመውሰዱ ታስሮ ነበር። ከተጋባን በኋላ በመስከረም 1, 1949 አብረን አቅኚነት ጀመርንና ቦራስ በሚባል ከተማ እንድናገለግል ተመደብን። በዚያ ባገለገልንባቸው የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በየሳምንቱ ያለማቋረጥ አሥር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ፍላጎት ላላቸው ሰዎች እንመራ ነበር። በዘጠኝ ዓመታት ጊዜ ውስጥ በቦራስ የነበረው አንድ ጉባኤ ወደ ሦስት ከፍ ሲል በማየታችን ተደስተናል። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ አምስት ጉባኤዎች አሉ።
በ1950 አንዲት ሴት ልጅ ከዚያም ከሁለት ዓመት በኋላ አንድ ወንድ ልጅ ስለወለድን አቅኚ ሆኜ ብዙ መቀጠል አልቻልኩም። ይህም በመሆኑ የ16 ዓመት ልጅ እያለሁ ያ በሃንጋሪ የነበረ ውድ ወንድም “ይሖዋን ማገልገል አንድ ሰው ሊያገኘው ከሚችለው መብት ሁሉ የላቀ ነው” ሲል ያስተማረኝን ክቡር እውነት ለልጆቻችን የማስተማር አስደሳች መብት አግኝቻለሁ።
ያሳለፍኩትን ሕይወት መለስ ብዬ ስመለከት ሐዋርያው ያዕቆብ ስለ ኢዮብ ጽናት ሲያስታውሰን “ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነው” ብሎ የጻፈውን ሐቅ ከራሴ ተሞክሮ አስተውያለሁ። (ያዕቆብ 5:11) ምንም እንኳ አሰቃቂ ፈተናዎች የደረሱብኝ ቢሆንም ይሖዋን የሚያመልኩ ሁለት ልጆች፣ የእነሱ የትዳር ጓደኞችና ስድስት የልጅ ልጆች በማግኘቴ በእጅጉ ተባርኬአለሁ። ከዚህም በተጨማሪ እጅግ በርካታ የሆኑ መንፈሳዊ ልጆችና የልጅ ልጆች አሉኝ፤ ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ አቅኚዎችና ሚስዮናውያን ሆነው እያገለገሉ ናቸው። አሁን የምጠባበቀው ታላቅ ተስፋ በሞት አንቀላፍተው ያሉትን ወዳጆቼን ማግኘትና ከመታሰቢያ መቃብራቸው ሲነሱ እጄን ዘርግቼ መቀበል ነው።—ዮሐንስ 5:28, 29
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በስዊድን ሳገለግል
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባለቤቴ ጋር