ምድር የተፈጠረችው ለምንድን ነው?
ልትመረምረው የሚገባ አንድ ጥያቄ አለ:- ውቧ ፕላኔታችን የተፈጠረችው ለምድርና በምድር ላይ ለሚኖሩት የሰው ልጆች ዓላማ ባለው አስተዋይ በሆነ ፈጣሪ አማካኝነት ነውን? ለዚህ ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ማግኘትህ ፕላኔታችን ወደፊት ምን እንደሚጠብቃት ማወቅ እንድትችል ሊረዳህ ይችላል።
ስለ አጽናፈ ዓለምና ስለ ምድራችን በጥልቀት ያጠኑ ብዙ ሳይንቲስቶች አንድ ፈጣሪ እንዳለ ማለትም ከዚህ የፍጥረት ሥራ በስተጀርባ አንድ አምላክ እንዳለ የሚጠቁሙ ማስረጃዎች ተመልክተዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ የሰጡትን አስተያየት ተመልከት:-
ፕሮፌሰር ፖል ዴቪስ ዘ ማይንድ ኦቭ ጎድ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ጽኑ የሆኑ፣ በሚገባ የተደራጁና የተወሳሰቡ መዋቅሮች ያሉት ሥርዓታማውና በደንብ የተቀናጀው አጽናፈ ዓለም እጅግ ልዩ የሆኑ ሕጎችና ሁኔታዎች የሚጠይቅ ነው።”
ፕሮፌሰር ዴቪስ የአስትሮፊዚክስ ጠበብትና ሌሎች ሳይንቲስቶች የገጠሟቸውን በርካታ “ተመሳሳይ ገጠመኞች” ከዘረዘሩ በኋላ እንዲህ ሲሉ አክለው ተናግረዋል:- “እነዚህን “ተመሳሳይ ገጠመኞች” በአንድነት ስንመለከት እንደምናውቀው ሕይወት በፊዚክስ ሕጎችና ተፈጥሮ ለተለያዩ የእኑስ መጠነቁስ (particle masses)፣ የኃይል መጠንና እነዚህን ለመሳሰሉት ነገሮች በሚጠቀምባቸው ትክክለኛ ስሌቶች ላይ በሚያጋጥሙ ድንገተኛ አደጋዎች በቀላሉ ሊነካ እንደሚችል የሚያሳዩ ትልቅ ማስረጃ ይሆኑናል። . . . እኛ በአምላክ ቦታ ሆነን የአንድን ማሽን የተለያዩ ቁልፎች እያዞርን የእነዚህን ነገሮች ስሌት ለማስተካከል ብንሞክር ሁሉም ቁልፎች ማለት ይቻላል፣ አጽናፈ ዓለምን ሕይወት አልባ እንደሚያደርጉት መጥቀሱ ብቻ ይበቃል። በአንዳንድ ሁኔታዎች አጽናፈ ዓለምን ለሕይወት ተስማሚ ለማድረግ ቁልፎቹን ፍጹም በሆነ መንገድ በጥንቃቄ ማስተካከል የሚጠይቅ ይመስላል። . . . ባሉት ሁኔታዎች ላይ በጣም ጥቃቅን የሆኑ ለውጦች ማድረጉ ብቻ እንኳ አጽናፈ ዓለምን ከእይታ ውጪ ሊያደርገው የሚችል መሆኑ ጥልቅ ትርጉም ያለው ሐቅ ነው።”
ከላይ የተገለጹት ግኝቶች ለብዙዎች የሚጠቁሙት ነገር ምድራችንም ሆነች የተቀረው አጽናፈ ዓለም ዓላማ ባለው ፈጣሪ የተፈጠሩ መሆናቸውን ነው። ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ ይህ ፈጣሪ መጀመሪያውኑ ምድርን የፈጠረበትን ምክንያት ማወቅ ይኖርብናል። በተጨማሪም የምንችል ከሆነ፣ ለምድር ያለው ዓላማ ምን እንደሆነ ማወቅ አለብን። በእነዚህ ነገሮች መካከል ባለው ዝምድና ረገድ አንድ እንግዳ የሆነ ነገር ብቅ ይላል። ምንም እንኳ አምላክ የለም የሚለው እምነት በጣም የተስፋፋ ቢሆንም አንድ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ያለው ፈጣሪ አለ የሚል እምነት ያላቸው በርካታ ሰዎች አሉ። አብዛኞቹ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት አጽናፈ ዓለሙን የፈጠረ ሁሉን ቻይ አምላክ እንዳለ ይናገራሉ። ሆኖም ከእነዚህ ሃይማኖቶች መካከል በአምላክ ዓላማ መሠረት የምድር የወደፊት ዕጣ ምን እንደሆነ በሙሉ ትምክህትና እምነት የሚናገር የለም ማለት ይቻላል።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ከፈጣሪ የተገኘ ነው ተብሎ ሰፊ ተቀባይነት ያገኘውን የመረጃ ምንጭ መመልከቱ ተገቢ ነው። ይህ ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። የምድርን የወደፊት ዕጣ አስመልክቶ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጹት ቀላልና ግልጽ ሐሳቦች መካከል አንዱ በመክብብ 1:4 ላይ የሚገኘው ነው። እንዲህ እናነባለን:- “ትውልድ ይሄዳል፣ ትውልድም ይመጣል፤ ምድር ግን ለዘላለም ነው።” መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ አምላክ ምድርን የፈጠረው ለምን እንደሆነ ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ይገልጻል። በተጨማሪም በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከፀሐይ ትክክለኛ ርቀት ኖሯት ለሕይወት ተስማሚ ሆና በምታገለግልበት ተገቢ ቦታ ላይ እንዳስቀመጣት ያመለክታል። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ጥንታዊውን ነቢይ ኢሳይያስን እንዲህ ብሎ እንዲጽፍ በመንፈሱ አነሳስቶታል:- “ሰማያትን የፈጠረ እግዚአብሔር፣ እርሱም ምድርን የሠራና ያደረገ ያጸናትም፣ መኖሪያም ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን ያልፈጠራት አምላክ፣ እንዲህ ይላል:- እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም።”—ኢሳይያስ 45:18
ሆኖም በምድር ላይ ያለውን ሕይወት ሁሉ ሊያጠፋ ስለሚችለው የሰው ልጅ ስለሠራው ነገርስ ምን ማለት ይቻላል? የሰው ልጅ በፕላኔታችን ላይ ያለውን ሕይወት በሙሉ ከማጥፋቱ በፊት አምላክ ተወዳዳሪ በሌለው ጥበቡ አማካኝነት እጁን ጣልቃ እንደሚያስገባ ተናግሯል። የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ መጽሐፍ በሆነው በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን የሚከተለውን የሚያጽናና ቃል ተመልከት:- “አሕዛብም ተቈጡ፣ ቊጣህም መጣ፣ በሙታንም ትፈርድ ዘንድ ዘመን መጣ፣ ለባሪያዎችህም ለነቢያትና ለቅዱሳን ስምህንም ለሚፈሩት ለታናናሾችና ለታላላቆችም ዋጋቸውን ትሰጥ ዘንድ፣ ምድርንም የሚያጠፉትን ታጠፋ ዘንድ ዘመን መጣ።”—ራእይ 11:18
በአንድ ወቅት አንድ አስትሮኖት ምድርን ሲዞር በሕዋው ውስጥ ያለች እንቁ ብሎ ገልጿታል። ይሖዋ ይህችን ምድር ሲፈጥር የመጀመሪያ ዓላማው ምን እንደነበረ ገልጾልናል። ምድር በበቂ ሁኔታ በሰላምና በስምምነት በሚኖሩ የሰው ልጆች ማለትም ወንዶችና ሴቶች የተሞላች ዓለም አቀፍ ገነት እንድትሆን ዓላማ ነበረው። የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ጥንዶች ልጆች እንዲወልዱ በማድረግ ፕላኔቷ ቀስ በቀስ በሰዎች እንድትሞላ ዝግጅት አደረገ። ይሖዋ የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት ተድላና ደስታ እንዲያገኙ ሲል አንዱን አነስተኛ የምድር ክፍል ገነት አደረገው። የሰብዓዊ ቤተሰብ ዝርያዎች በብዙ ዓመታትና መቶ ዘመናት ሂደት እየተባዙ ሲሄዱ የኤደን የአትክልት ሥፍራ ዘፍጥረት 1:28 ፍጻሜውን እስኪያገኝ ድረስ ቀስ በቀስ እየሰፋ ይሄድ ነበር:- “እግዚአብሔርም . . . አላቸው:- ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም።”
በአሁኑ ጊዜ ምድርም ሆነች በውስጧ ያሉት ነዋሪዎች ያሉበት አሳዛኝ ሁኔታ አምላክ ለምድር ያወጣው የመጀመሪያ ዓላማ ተለውጧል እንድንል ያደርገናልን? ወይም ደግሞ ዓላማውን በመለወጥ በሰው ልጆች ሥርዓት አልበኝነት የተነሳ ፕላኔቷ ሙሉ በሙሉ ከጠፋች በኋላ ሁሉን ነገር እንደ አዲስ ለመጀመር ወስኗልን? በፍጹም፣ ከእነዚህ ሁኔታዎች መካከል የትኛውም ትክክል እንዳልሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ዓላማ ሁሉ ውሎ አድሮ ፍጻሜውን እንደሚያገኝና የሚያደርገው ቁርጥ ውሳኔ ሁሉ በማንም ሰው አልፎ ተርፎም በየትኛውም ያልተጠበቀ ክስተት ሊጨናገፍ እንደማይችል ይገልጽልናል። የሚከተለውን ማረጋገጫ ሰጥቶናል:- “ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም።”—ኢሳይያስ 55:11
የአምላክ ዓላማ ለጊዜው ተስተጓጎለ እንጂ አልተለወጠም
አዳምና ሔዋን ስህተት ሠርተው ከኤደን የአትክልት ሥፍራ ከተባረሩ በኋላ አምላክ ምድርን ገነት ለማድረግ ያለው ዓላማ ያለ እነርሱ እንደሚፈጸም ግልጽ ሆነ። ይሁን እንጂ ይሖዋ የእነርሱ ዘር የመጀመሪያ ዓላማውን እንደሚያስፈጽም በዚያው ጊዜና ቦታ ገልጾ ነበር። እርግጥ ነው፣ ይህ ረጅም ጊዜ አልፎ ተርፎም ብዙ መቶ ዘመናት የሚወስድ ነው፤ ሆኖም አዳምና ሔዋን በፍጽምና ደረጃ መኖራቸውን ቀጥለው ቢሆን ኖሮ እንኳ ይህን የመጀመሪያ ዓላማ ለመፈጸም ምን ያህል ጊዜ ሊወስድ ይችል እንደነበረ የሚጠቁም ነገር የለም። ከአሁኑ ጊዜ አንስቶ ከሺህ ዓመት ብዙም በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ በክርስቶስ ኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት ማብቂያ ላይ የኤደን ገነታዊ ሁኔታዎች በመላው ምድር ላይ ይስፋፋሉ፤ ፕላኔቷ ምድርም የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት ዝርያዎች በሆኑ ሰላማዊና ደስተኛ ሰዎች ትሞላለች። በእርግጥም ይሖዋ እንከን የማይወጣለት ዓላማ አውጪ እንደሆነ ለዘላለም ይረጋገጣል!
አምላክ ከረጅም ጊዜ በፊት በመንፈሱ አነሳሽነት ያስነገራቸው አስደሳች ትንቢቶች በዚያን ጊዜ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ። እንደ ኢሳይያስ 11:6-9 ያሉት ጥቅሶች ታላቅ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ:- “ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር ይቀመጣል፣ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፤ ጥጃና የአንበሳ ደቦል ፍሪዳም በአንድነት ያርፋሉ፤ ታናሽም ልጅ ይመራቸዋል። ላምና ድብ አብረው ይሰማራሉ፣ ግልገሎቻቸውም በአንድነት ያርፋሉ፤ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል። የሚጠባውም ሕፃን በእባብ ጉድጓድ ላይ ይጫወታል፣ ጡት የጣለውም ሕፃን በእፉኝት ቤት ላይ እጁን ይጭናል። በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጎዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና።”
የጤና ችግርና ለሞት የሚያደርስ ከባድ ሕመም እንዲሁም ሞት ራሱ ጊዜ ያለፈባቸው ነገሮች ይሆናሉ። በመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ከሚገኙት ከእነዚህ ቃላት ይበልጥ ይህን በግልጽ የሚያሳይ ቃል ሊኖር ይችላልን? “የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።”—ራእይ 21:3, 4
አዎ፣ ውቧ ፕላኔቷ ምድራችን ጸንታ እንደምትኖር ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን። ይህ ክፉ ሥርዓት ምድርን ከሚያጠፉ ልማዶቹ ጋር ተጠራርጎ ሲጠፋ በሕይወት ለመትረፍ እንድትበቃ እንመኛለን። አምላክ የሚያመጣው ንጹሕ አዲስ ዓለም በጣም ቀርቧል። በዚያን ጊዜ የምንወዳቸው በርካታ ሰዎች በትንሣኤ ተአምር አማካኝነት ከሞት ይነሳሉ። (ዮሐንስ 5:28, 29) አዎ፣ ምድራችን ጸንታ ትኖራለች፤ እኛም በውስጧ እየተደሰትን መኖር እንችላለን።