የይሖዋ ድርጅት በአገልግሎታችሁ ይደግፋችኋል
“የዘላለም ወንጌል ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ መካከል ሲበር አየሁ።”—ራእይ 14:6
1. የይሖዋ ምሥክሮች ምን ፈተና ገጥሟቸዋል? ፈተናውን ሊወጡ የቻሉትስ እንዴት ነው?
የይሖዋ ሰማያዊ ድርጅት ክርስቲያናዊ አገልግሎትን በመደገፍ ረገድ የሚጫወተውን ሚና መገንዘባችን ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? የይሖዋ ምሥክሮች የይሖዋ ሰማያዊ ሠራዊት ድጋፍ ባይኖራቸው ኖሮ ጥላቻ በሞላበት ዓለም ውስጥ የአምላክን መንግሥት ምሥራች የመስበኩን ሥራ ማከናወን ይችሉ ነበርን? ምሥክሮቹ ጽንፈኛ ብሔረተኝነት፣ አምባገነን የፖለቲካ ሥርዓት፣ የዓለም ጦርነትና ሌሎች የተለያዩ ችግሮች በተፈራረቁበት መቶ ዘመን ሁሉ ይህን የስብከት ሥራ አከናውነዋል። የይሖዋ እርዳታ ባይኖር ኖሮ ምሥክሮቹ በዓለም ዙሪያ የሚሰነዘርባቸውን መሠረተ ቢስ ጥላቻና አድልዎ እንዲሁም አብዛኛውን ጊዜ የሚያጋጥማቸውን ከባድ ስደት መቋቋም ይችሉ ነበርን?—መዝሙር 34:7
ዓለም አቀፍ ተቃውሞ ቢኖርም መጽናት
2. በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበሩትና ዛሬ ባሉት እውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ?
2 በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ሃይማኖታዊም ሆኑ ፖለቲካዊ ጠላቶች የይሖዋን ሥራ ለማገድ ወይም ለማደናቀፍ ሲሉ በሕግም ሆነ በሌላ መንገድ የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል። ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ተሰድደዋል፣ በሐሰት ተወንጅለዋል፣ የሐሰት ወሬ ተነዝቶባቸዋል፣ ያለ ስማቸው ስም ተሰጥቷቸዋል አልፎ ተርፎም ብዙዎች ተገድለዋል። ብዙውን ጊዜ ይህን የሚቆሰቁሱት የታላቂቱ ባቢሎን ቀሳውስት ናቸው። ለመጀመሪያዎቹ መቶ ዘመን ክርስቲያኖች እንደተባለው ሁሉ ዛሬም “ስለዚህ ወገን በየስፍራው ሁሉ እንዲቃወሙ በእኛ ዘንድ ታውቆአልና” ሊባል ይችላል። በኢየሱስ ዘመን የነበሩት የአይሁድ ካህናት ያለ የሌለ ኃይላቸውን ተጠቅመው አገልግሎቱን ለመግታት እንደሞከሩ ሁሉ ዛሬም ያሉት ቀሳውስትና ከሃዲዎች ከፖለቲካ ውሽሞቻቸው ጋር በማበር የይሖዋ ሕዝቦች የሚያካሂዱትን ትምህርት ሰጪ የምሥክርነት ሥራ ለማፈን ሞክረዋል።—ሥራ 28:22፤ ማቴዎስ 26:59, 65-67
3. ሄንሪካ ዙር ካሳየችው ጽኑ አቋም ምን ልንማር እንችላለን?
3 ለምሳሌ ያህል መጋቢት 1, 1946 በፖላንድ የተፈጸመውን ሁኔታ ተመልከት። ከኬልም አቅራቢያ የምትኖረው ሄንሪካ ዙር የተባለች የ15 ዓመት ልጃገረድ ከአንድ ወንድም ጋር ሆና በአቅራቢያቸው በሚገኝ መንደር ውስጥ ያሉትን ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ለመጠየቅ ትሄዳለች። ናሮዶቭ ሽዊ ሲ ዝበሮይኔ (ብሔራዊ የጦር ሠራዊት) የተባለው የካቶሊክ ወታደራዊ ጓድ አባል የሆኑ ሰዎች ይይዟቸዋል። ወንድምን ክፉኛ ቢደበድቡትም በሕይወት ይተርፋል። ሄንሪካ ግን ከሞት አላመለጠችም። እንደ ካቶሊኮች እንድታማትብ ለማስገደድ ለብዙ ሰዓታት ከባድ ሥቃይ አደረሱባት። ከሚያሰቃዩአት ሰዎች መካከል አንዱ “በልብሽ የፈለግሽውን እመኚ፣ አሁን ግን ዝም ብለሽ አማትቢ። አለዚያ የሚጠብቅሽ ጥይት ነው!” ብሏት ነበር። ሄንሪካ የጸና አቋሟን አላልታለችን? በፍጹም። እነዚህ ሃይማኖታዊ ሰዎች ሄንሪካን ወደ ጫካ እየጎተቱ ወስደው በጥይት በመግደል የፈሪ በትራቸውን ሰነዘሩ። ሆኖም ድል ያደረገችው እርሷ ነበረች! ጽኑ አቋሟን ሊያስለውጧት አልቻሉም።a—ሮሜ 8:35-39
4. ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ወገኖች የስብከቱን ሥራ ለማፈን የሞከሩት እንዴት ነው?
4 በዚህ ዘመን ያሉት የአምላክ አገልጋዮች ከአንድ መቶ ለሚበልጡ ዓመታት ሲንገላቱና የሚያዋርድ ድርጊት ሲፈጸምባቸው ቆይተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች፣ የሰይጣን ዋነኛ መሣሪያ ከሆኑት ሃይማኖቶች መካከል ስላልሆኑና መሆንም ስለማይፈልጉ የተዛባ አመለካከት ያላቸው ተቺዎችና አክራሪ ተቃዋሚዎች ለሚሰነዝሩት ጥቃት የተጋለጡ ሆነዋል። ከፖለቲካዊ ወገኖች ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት ተሰንዝሮባቸዋል። ብዙ ምሥክሮች ለእምነታቸው ሲሉ ሕይወታቸውን ሰውተዋል። ዴሞክራት የሚባሉት ወገኖች እንኳ ሳይቀሩ የምሥራቹን ስብከት ሥራ ለማገድ ሙከራ አድርገዋል። በ1917 አካባቢ በካናዳና በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) በቀሳውስት አቀነባባሪነት መንግሥትን ተጻርረዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ የነበሩት ወንድሞች በስህተት ታስረው የነበረ ቢሆንም በኋላ ከክሱ ነፃ ሆነዋል።—ራእይ 11:7-9፤ 12:17
5. ለይሖዋ አገልጋዮች የማበረታቻ ምንጭ የሆኑት የትኞቹ ቃላት ናቸው?
5 የክርስቶስ ወንድሞችና ከእነርሱ ጎን በታማኝነት የቆሙት ጓደኞቻቸው የሚሠሩትን የምሥክርነት ሥራ ለማስቆም ሰይጣን የተለያዩ ዘዴዎችን ሞክሯል። ይሁንና ብዙ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ዛቻ፣ ማስፈራሪያ፣ ድብደባ፣ እስር ቤትና ማጎሪያ ካምፕ መጣል፣ ሌላው ቀርቶ ሞትም ቢሆን የይሖዋ ምሥክሮችን ዝም አላሰኛቸውም። በታሪክ ዘመናት ሁሉ የታየውም ነገር ይኸው ነው። “ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ” የሚሉት የኤልሳዕ ቃላት ማበረታቻ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ይህን ያለበት አንዱ ምክንያት የታመኑ መላእክት ከዲያብሎስ ጭፍሮች በቁጥር ስለሚበልጡ ነው!—2 ነገሥት 6:16፤ ሥራ 5:27-32, 41, 42
ይሖዋ በቅንዓት የሚከናወነውን ስብከት ይባርካል
6, 7. (ሀ) ቀደም ባሉት ዓመታት ምሥራቹን ለመስበክ ምን ጥረቶች ተደርገዋል? (ለ) ከ1943 ወዲህ ምን ጠቃሚ ለውጥ ተካሂዷል?
6 የይሖዋ ምሥክሮች መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት የሚያከናውኑትን ታላቅ የምሥክርነት ሥራ ለማስፋትና ለማፋጠን በ20ኛው መቶ ዘመን ብዙ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተጠቅመዋል። በ1914 የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት የነበረው ፓስተር ራስል የስላይድ ፊልሞችንና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በሸክላ ከተቀረጸ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር ጋር በማቀናጀት ስምንት ሰዓት የሚፈጀውንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መልእክት ያለውን “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” አዘጋጅቶ ነበር። በወቅቱ በብዙ አገሮች የነበሩ ተመልካቾችን አስገርሟል። በ1930ዎቹና በ1940ዎቹ ደግሞ ተንቀሳቃሽ የሸክላ ማጫዎቻዎችን በመጠቀም የማኅበሩ ሁለተኛ ፕሬዚዳንት የነበረው ወንድም ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ የሰጣቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግሮች እያሰሙ ከቤት ወደ ቤት በማገልገላቸው በሰፊው ይታወቁ ነበር።
7 የማኅበሩ ሦስተኛ ፕሬዚዳንት በነበረው በናታን ኤች ኖር መሪነት በ1943 አንድ ትልቅ እርምጃ ተወሰደ። ይህም በየጉባኤው ያሉ አገልጋዮች የሚሰለጥኑበት ትምህርት ቤት እንዲጀመር የሚያደርግ ውሳኔ ነበር። ምሥክሮች ከዚህ በኋላ ያለ ሸክላ ቅጂዎች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መስበክንና ማስተማርን ይሰለጥናሉ። ከዚህ ጊዜ ወዲህ ሚስዮናውያን፣ የሙሉ ጊዜ አቅኚ አገልጋዮች፣ የጉባኤ ሽማግሌዎች እንዲሁም በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ በኃላፊነት ቦታ የሚሠሩ የበላይ ተመልካቾች የሚሰለጥኑባቸው ትምህርት ቤቶች ተቋቁመዋል። ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል?
8. በ1943 ምሥክሮቹ ትልቅ እምነት ያሳዩት እንዴት ነው?
8 ሁለተኛ የዓለም ጦርነት እየተካሄደ ባለበት በ1943 የይሖዋ ምሥክሮች የነበሩት በ54 አገሮች ውስጥ ሲሆን ቁጥራቸውም 129,000 ብቻ ነበር። ይሁንና መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ማቴዎስ 24:14 ፍጻሜውን እንደሚያገኝ እምነት ነበራቸው፤ ቁርጥ ያለ አቋምም ይዘው ነበር። የዚህን ብልሹ የነገሮች ሥርዓት ጥፋት ከሚያበስሩት ተከታታይ ክስተቶች በፊት ይሖዋ በጣም አስፈላጊ የሆነው የማስጠንቀቂያ መልእክት እንዲታወጅ እንደሚያደርግ ጠንካራ እምነት ነበራቸው። (ማቴዎስ 24:21፤ ራእይ 16:16፤ 19:11-16, 19-21፤ 20:1-3) ድካማቸው ፍሬ አስገኝቷልን?
9. የምሥክሮቹ ሥራ እየጎለበት መሄዱን የሚያሳየው ምንድን ነው?
9 ዛሬ እያንዳንዳቸው ከ100,000 በላይ አስፋፊዎች ያሏቸው ቢያንስ 13 አገሮች አሉ። ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሰፊ ተቀባይነት ያገኘችባቸው አገሮች ናቸው። ይሁን እንጂ ሁኔታው ምን እንደሚመስል ተመልከቱ። ብራዚል 450,000 የምሥራቹ አስፋፊዎች ሲኖሯት በ1997 በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ የተገኙት ሰዎች ከ1,200,000 በላይ ናቸው። ሌላዋ ምሳሌ ደግሞ ሜክሲኮ ስትሆን በዚህች አገር ወደ 500,000 የሚጠጉ ምሥክሮች ይገኛሉ። የመታሰቢያው በዓል ሲከበር ከ1,600,000 በላይ ሰዎች ተገኝተዋል። ሌሎቹ ካቶሊካዊ አገሮች ደግሞ ኢጣልያ (225,000 የሚያክሉ ምሥክሮች)፣ ፈረንሳይ (ወደ 125,000 የሚጠጉ)፣ ስፔይን (ከ105,000 በላይ) እና አርጀንቲና (ከ115,000 የሚበልጡ) ናቸው። የፕሮቴስታንት፣ የካቶሊክና የአይሁድ እምነት ተከታዮች በሚበዙባት በዩናይትድ ስቴትስ 975,000 የሚያክሉ ምሥክሮች ሲኖሩ ከ2,000,000 በላይ ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ ተገኝተዋል። በእርግጥም እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ምሥጢራዊ ትምህርቶቿን እርግፍ አድርገው ትተው የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ከታላቂቱ ባቢሎን በመውጣት ለመረዳት ቀላልና እርግጠኛ የሆነውን የ“አዲስ ሰማይና ምድር” ተስፋ ለመቀበል እየጎረፉ ነው።—2 ጴጥሮስ 3:13፤ ኢሳይያስ 2:3, 4፤ 65:17፤ ራእይ 18:4, 5፤ 21:1-4
እንደ ሰዎች ሁኔታ ለውጥ ማድረግ
10. በአንዳንድ አካባቢዎች ያሉት ሁኔታዎች የተለወጡት እንዴት ነው?
10 በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል ወደ ይሖዋ የመጡት ብዙዎቹ ሰዎች የተገኙት ከቤት ወደ ቤት ነው። (ዮሐንስ 3:16፤ ሥራ 20:20) ይሁን እንጂ ሌሎች ዘዴዎችም ነበሩ። ዛሬ ሁኔታዎች ተለውጠዋል። የኢኮኖሚ ሁኔታው ብዙ ሴቶች ከቤታቸው ውጭ እንዲሠሩ የሚያስገድድ ሆኗል። ብዙውን ጊዜ በሳምንቱ መሀል ቤታቸው የሚገኙ ሰዎች በጣም ጥቂት ናቸው። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች ከዚህ ሁኔታ ጋር የሚስማማ ለውጥ አድርገዋል። እንደ ኢየሱስና እንደ መጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ሰዎች በሚገኙበት ጊዜና ቦታ የስብከት ሥራቸውን ያከናውናሉ።—ማቴዎስ 5:1, 2፤ 9:35፤ ማርቆስ 6:34፤ 10:1፤ ሥራ 2:14፤ 17:16, 17
11. የይሖዋ ምሥክሮች ዛሬ በየትኞቹ መስኮች እየሰበኩ ነው? ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል?
11 የይሖዋ ምሥክሮች ውይይት ለመጀመር ቀዳሚዎች በመሆን በመኪና ማቆሚያ ሥፍራዎች፣ በገበያ አዳራሾች፣ በፋብሪካዎች፣ በቢሮዎችና በንግድ ክልሎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በፖሊስ ጣቢያዎች፣ በጋዝ ማደያዎች፣ በሆቴሎችና በምግብ ቤቶች እንዲሁም በጎዳናዎች ላይ በጥበብ ለሰዎች ይመሠክራሉ። ሰዎች ሊገኙ በሚችሉባቸው ቦታዎች ሁሉ ይመሠክራሉ። ሰዎች ቤታቸው በሚገኙባቸው ጊዜያት ደግሞ ወደ ቤታቸው ሄደው ከማነጋገር ወደኋላ አይሉም። ይህ ከሁኔታው ጋር የሚስማማና ተግባራዊ የሆነ ዘዴ ብዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለማሠራጨት አስችሏል። በግ መሰል የሆኑ ሰዎች እየተገኙና አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እየተጀመሩ ነው። ከአምስት ሚልዮን ተኩል የሚበልጡት ፈቃደኛ አገልጋዮች በሰው ዘር ታሪክ ታይቶ በማያውቅ መጠን ከፍተኛ የማስተማር ሥራ እያከናወኑ ነው! ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ የመሆን መብት አግኝተሃልን?—2 ቆሮንቶስ 2:14-17፤ 3:5, 6
የይሖዋ ምሥክሮችን እንዲሰብኩ የሚያነሳሳቸው ምንድን ነው?
12. (ሀ) ይሖዋ ሕዝቦቹን እያስተማረ ያለው እንዴት ነው? (ለ) ይህስ ትምህርት ምን ውጤት አለው?
12 በዚህ ሁሉ ሰማያዊው ድርጅት ያለው ድርሻ ምንድን ነው? ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናግሯል:- “ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፣ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል።” (ኢሳይያስ 54:13) ይሖዋ ይህን አንድነት ያለውን ምድር አቀፍ የወንድማማች ማኅበር በምድራዊ ድርጅቱ በኩል በመንግሥት አዳራሾች በሚደረጉ ስብሰባዎች፣ በአውራጃ እንዲሁም በልዩና በወረዳ ስብሰባዎች ላይ እያስተማረ ነው። ይህም አንድነትና ሰላም ያስገኛል። የይሖዋ ትምህርት፣ በዚህ በሚከፋፍልና እርስ በርሱ በተለያየ ዓለም ውስጥ በየትኛውም ቦታ ቢኖሩ እርስ በርስ መፋቀርን እንዲሁም ጎረቤታቸውን መጥላትን ሳይሆን እንደ ራሳቸው መውደድን የተማሩ ልዩ ሕዝቦች አፍርቷል።—ማቴዎስ 22:36-40
13. የስብከቱ ሥራ የመላእክት ድጋፍ እንዳለው እንዴት እናውቃለን?
13 ሰዎች ለመልእክታቸው ግዴለሽ ቢሆኑም ወይም ስደት ቢደርስባቸውም የይሖዋ ምሥክሮች መስበካቸውን እንዲቀጥሉ የሚገፋፋቸው ፍቅር ነው። (1 ቆሮንቶስ 13:1-8) በራእይ 14:6 ላይ እንደተጠቀሰው ሕይወት አድን ሥራቸው የሚመራው ከሰማይ እንደሆነ ያውቃሉ። በመላእክታዊ መመሪያ እየታወጀ ያለው መልእክት ምንድን ነው? “የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት፤ ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውኃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት።” የመንግሥቱ ምሥራች ስብከት የይሖዋን ስም ከፍ ከፍ የሚያደርግ ነው። ሰዎች ለፍጡራንና ጭፍን ለሆነው የዝግመተ ለውጥ ትምህርት ሳይሆን ፈጣሪ ለሆነው አምላክ ክብር እንዲሰጡ ጥሪ እየቀረበላቸው ነው። የስብከቱ ሥራ ይህን ያህል አጣዳፊ የሆነውስ ለምንድን ነው? የፍርዱ ሰዓት ማለትም በታላቂቱ ባቢሎንና የሚታየው የሰይጣን የነገሮች ሥርዓት ክፍል በሆኑት ሌሎች ወገኖች ሁሉ ላይ የቅጣት እርምጃ የሚወሰድበት ጊዜ ስለደረሰ ነው።—ራእይ 14:7፤ 18:8-10
14. በዚህ ታላቅ የማስተማር ዘመቻ እነማን ጭምር ይካፈላሉ?
14 ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች ሁሉ ከዚህ የስብከት ሥራ ነፃ አይደሉም። መንፈሳዊ ሽማግሌዎች ከጉባኤው ጋር በመስበክ ረገድ ቀዳሚ ሆነው ይገኛሉ። ሥልጠና ያገኙ አቅኚዎች በዚህ ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠምደዋል። የመንግሥቱ መልእክት ቀናተኛ አስፋፊዎችም በወር ውስጥ መስበክ የሚችሉት ሰዓት ጥቂትም ሆነ ብዙ መልእክቱን በሁሉም የምድር ማዕዘን እያዳረሱ ነው።—ማቴዎስ 28:19, 20፤ ዕብራውያን 13:7, 17
15. የይሖዋ ምሥክሮች ስብከት ተጽእኖ እንዳሳደረ የሚጠቁመው ነገር ምንድን ነው?
15 ይህ ሁሉ ጥረት በዓለም ላይ ያሳደረው ተጽእኖ አለ? ስለ ይሖዋ ምሥክሮች በቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና በዜና አምዶች ላይ ተደጋግሞ መነገሩ ራሱ ሥራው ተጽዕኖ እንዳሳደረ የሚያሳይ ቀላል ማስረጃ ነው። ብዙውን ጊዜ ይህ እያንዳንዱን ሰው ለማግኘት የምናደርገውን ያላሰለሰ ጥረትና ያለንን ቁርጠኝነት ጎላ አድርጎ የሚያሳይ ነው። እርግጥ ነው አብዛኞቹ ሰዎች መልእክቱንና መልእክተኞቹን ለመቀበል አሻፈረኝ ቢሉም የምናሳየው ቅንዓትና ደጋግመን መሄዳችን ትልቅ ውጤት ይኖረዋል!
የምሥክርነቱን ሥራ ለማጠናቀቅ የምናሳየው ቅንዓት
16. በቀረው አጭር ጊዜ ውስጥ ልናሳየው የሚገባን ዝንባሌ ምን ዓይነት ነው?
16 ይህ የነገሮች ሥርዓት ምን ያህል ጊዜ እንደቀረው አናውቅም። ደግሞም ይሖዋን ለማገልገል ያነሳሳን ውስጣዊ ዝንባሌ ንጹሕ ከሆነ ይህ ሥርዓት ምን ያህል ጊዜ እንደቀረው ማወቅ አያስፈልገንም። (ማቴዎስ 24:36፤ 1 ቆሮንቶስ 13:1-3) ይሁን እንጂ የይሖዋ ፍቅር ኃይልና ፍትሕ እንዲገለጥ ምሥራቹ “አስቀድሞ” ሊሰበክ እንደሚገባው እናውቃለን። (ማርቆስ 13:10) በመሆኑም የዚህን ክፉ የሆነ፣ ፍትሕ የጎደለውና ዓመፀኛ ዓለም ፍጻሜ ስንጠባበቅ ምንም ያህል ዓመት ቢያልፍ እንደ ሁኔታችን ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን በቅንዓት መመላለስ ይኖርብናል። ዕድሜያችን እየገፋ ሄዶ ወይም ደግሞ ጤና አጥተን ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ዛሬም ቢሆን ወጣት ሳለን ወይም ሙሉ ጤና እያለን ይሖዋን ባገለገልንበት ቅንዓት ልናገለግለው እንችላለን። ምናልባት ካሁን ቀደም እናደርገው የነበረውን ያህል በአገልግሎት ብዙ ሰዓት ማሳለፍ አንችል ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ለይሖዋ የምናቀርበውን የውዳሴ መሥዋዕት ጥራት መጠበቅ እንደምንችል የተረጋገጠ ነው።—ዕብራውያን 13:15
17. ሁላችንንም ሊጠቅም የሚችል አንድ አበረታች ተሞክሮ ተናገር።
17 እንግዲያውስ ወጣቶችም ሆንን በዕድሜ የገፋን በቅንዓት ተነሳስተን ለምናገኛቸው ሁሉ ስለ አዲሱ ዓለም የሚገልጸውን አስደሳች የሆነ መልእክት እናካፍል። በአውስትራሊያ እንዳለችው የሰባት ዓመት አይናፋር ልጅ እንሁን። ይህች ልጅ ከእናቷ ጋር ወደ አንድ የገበያ አዳራሽ ትሄዳለች። ሁሉም ሰው መስበኩ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ በመንግሥት አዳራሽ ሰምታ ስለነበር በቦርሳዋ ሁለት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ብሮሹሮች ያዘች። እናቷ ዕቃዎች ለመግዛት ባንኮኒው አካባቢ እያለች ትንሿ ልጅ ከአጠገቧ ጥፍት ብላ ሄደች። እናቷ ስትፈልጋት ለአንዲት ሴት ብሮሹር እያበረከተች አየቻት! ልጅዋ ሴትዮዋን እንደረበሸቻት በማሰብ እናትየው ይቅርታ ለመጠየቅ ሄደች። ይሁን እንጂ ሴትዮዋ ብሮሹሩን አመስግና ወስዳ ነበር። ከሴትዮዋ ከተለዩ በኋላ ልጅቷ የማታውቀውን ሰው ቀርባ ለማነጋገር እንዴት ድፍረት እንዳገኘች እናቷ ጠየቀቻት። “አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት አልኩና ሄድኩ” ስትል መለሰችላት።
18. የሚደነቅ መንፈስ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
18 በተለይ ለማናውቃቸው ሰዎች ወይም ለባለ ሥልጣኖች ምሥራቹን ለማድረስ ሁላችንም የዚህች አውስትራሊያዊት ልጅ ዓይነት መንፈስ ሊኖረን ይገባል። አንቀበልም እንዳይሉን እንፈራ ይሆናል። ኢየሱስ ምን እንዳለ እናስታውስ:- “እንዴት ወይም ምን እንድትመልሱ ወይም እንድትናገሩ አትጨነቁ፤ መንፈስ ቅዱስ በዚያች ሰዓት ልትናገሩት የሚገባችሁን ያስተምራችኋልና።”—ሉቃስ 12:11, 12
19. ስለ አገልግሎትህ ምን ይሰማሃል?
19 የምሥራቹን ይዘህ ወደ ሰዎች በደግነት ስትቀርብ የአምላክ መንፈስ እንደሚረዳህ እምነት ይኑርህ። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ዛሬ ታይተው ነገ በሚጠፉ ወንዶችና ሴቶች ይታመናሉ። እኛ የምንታመነው በይሖዋና በእርሱ ሰማያዊ ድርጅት ማለትም ለዘላለም ሕያዋን ሆነው በሚኖሩት በክርስቶስ ኢየሱስ፣ በቅዱሳን መላእክቱ እንዲሁም ትንሣኤ ባገኙት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ነው! እንግዲያው አንድ ነገር አስታውሱ:- “ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉ”!—2 ነገሥት 6:16
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ተጨማሪ ምሳሌዎች ለማግኘት የ1994 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ገጽ 217-20ን ተመልከት።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ የይሖዋ ሕዝቦች ፈተናዎችን እንዲቋቋሙ የአምላክ ሰማያዊ ድርጅት ምን ሚና ተጫውቷል?
◻ በ20ኛው መቶ ዘመን በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ጥቃት የሰነዘሩት ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ወገኖች የትኞቹ ናቸው?
◻ የይሖዋ ምሥክሮች አገልግሎታቸውን ካለው ሁኔታ ጋር በሚስማማ መንገድ እያከናወኑ ያሉት እንዴት ነው?
◻ እንድትሰብክ የሚያነሳሳህ ነገር ምንድን ነው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሄንሪካ ዙር
[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ጃፓን
ማርቲኒክ
ዩናይትድ ስቴትስ
ኬንያ
ዩናይትድ ስቴትስ
የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎች በሚገኙባቸው ቦታዎችና ወቅቶች ሁሉ ይሰብካሉ
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዚህ መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ የሸክላ ማጫወቻዎች የመንግሥቱን መልእክት ለማሠራጨት አገልግለዋል