እርስ በርስ መተማመን የጠፋው ለምንድን ነው?
‘ዛሬ ማንን ማመን ይቻላል?’ ሁኔታዎቹ ተስፋ ያስቆረጧቸው አንዳንድ ሰዎች ይህን ጥያቄ ሲያነሡ ሰምተህ ይሆናል። ወይም አንተ ራስህ በሕይወትህ ውስጥ ካጋጠሙህ ነገሮች የተነሣ ስሜትህ ተረብሾ እንደዚያ ብለህ ጠይቀህ ይሆናል።
በዓለም ዙሪያ በተቋማትም ሆነ በሌሎች ሰዎች መታመን አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱ አሌ የማይባል ሐቅ ነው። ብዙውን ጊዜ ደግሞ በሌሎች መታመን አስቸጋሪ የሚሆነው ያለ ምክንያት አይደለም። አብዛኞቹ የፖለቲካ ሰዎች ከመመረጣቸው በፊት የገቡትን ቃል ሙሉ በሙሉ ይፈጽማሉ ብሎ ከልቡ የሚጠብቅ ሰው ይኖራል? በ1990 በጀርመን በሚገኙ 1,000 ተማሪዎች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው 16.5 በመቶ የሚሆኑት ተማሪዎች የፖለቲካ ሰዎች ለዓለም ችግሮች መፍትሔ እንደሚያመጡ ሲተማመኑ ሁለት እጥፍ ብዛት ያላቸው ተማሪዎች ግን ከፍተኛ ጥርጣሬ እንዳላቸው ገልጸዋል። እንዲሁም አብዛኞቹ የፖለቲካ ሰዎች ችግሮችን ለመፍታት ባላቸው ችሎታም ሆነ ይህን ለማድረግ ባላቸው ፈቃደኝነት ላይ እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል።
ሽቱትጋርተ ናክሪክተን የተባለው ጋዜጣ እንደሚከተለው በማለት ቅሬታውን አሰምቷል:- “በጣም ብዙ ፖለቲከኞች የሚያስቀድሙት የራሳቸውን ፍላጎት ሲሆን ከዚያ በኋላ ምናልባት መራጮቻቸው ስለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ያስቡ ይሆናል።” በሌሎች አገሮች የሚገኙ ሰዎችም በዚህ አባባል ይስማማሉ። ዘ ዩሮፒየን የተባለው ጋዜጣ አንድን አገር በተመለከተ እንዲህ ብሏል:- “ወጣቶች የፖለቲካ ሰዎችን የሚያብጠለጥሉት ከመሬት ተነሥተው አይደለም። በዕድሜ የገፉትም ቢሆኑ በወጣቶቹ ሐሳብ ይስማማሉ።” ጋዜጣው ‘መራጩ ሕዝብ ሁልጊዜ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከሥልጣን እንዳወረደ’ ነው ሲል ገልጿል። በመቀጠልም “[በዚህች አገር] ከሚገኙ ወጣቶች ጋር ጥቂት ጊዜ ያሳለፈ ማንኛውም ሰው ወጣቶቹ በማን መታመን እንደሚችሉ ግራ ተጋብተው እንደሚዋልሉ ወዲያውኑ ማስተዋል ይችላል” ብሏል። ሆኖም አንድ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት የሕዝብን አመኔታ ካላተረፈ ሊያከናውነው የሚችለው ነገር በጣም ውስን ነው። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆን ኤፍ ኬነዲ በአንድ ወቅት “ለስኬታማ መስተዳድር መሠረቱ የሕዝብ አመኔታ ነው” ብለው ነበር።
በንግዱ ዓለምም ቢሆን ድንገተኛ ኢኮኖሚያዊ ክስረቶች መከሰታቸውና በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀብት ለማካበት ያስችላሉ የተባለላቸው ውጥኖች መክሸፋቸው ብዙዎች እንዲያመነቱ አድርጓል። በጥቅምት 1997 የዓለም የአክሲዮን ገበያዎች ከፍተኛ የዋጋ መዋዠቅ ባጋጠማቸው ጊዜ አንድ ጋዜጣ “እንግዳ የሆነና አንዳንድ ጊዜም መሠረት የሌለው ጥርጣሬ” እንዲሁም “ተላላፊ የሆነ በሌሎች ያለመታመን ስሜት” መኖሩን ተናግሮ ነበር። በተጨማሪም ጋዜጣው “[በእስያ በሚገኝ አንድ አገር] ውስጥ በሌሎች የመታመኑ ነገር በመጥፋቱ መንግሥት በሥልጣን ላይ መቆየቱ ራሱ . . . ያሰጋል” ብሏል። ከዚያም በማጠቃለያው ላይ “ኢኮኖሚያዊ ውጥኖች በመተማመን ስሜት ላይ የተመኩ መሆናቸውን” ገልጿል።
ሃይማኖትም ቢሆን ሌሎች እንዲታመኑበት ማድረግ እየተሳነው መጥቷል። በጀርመን የሚታተመው ክሪስት ኢን ደ ጋጌንቫርት የተባለው ሃይማኖታዊ መጽሔት “ሕዝቡ በቤተ ክርስቲያን ላይ ያለው አመኔታ በከፍተኛ ሁኔታ እየተመናመነ ነው” ሲል በቁጭት ስሜት አስተያየቱን ሰጥቷል። ከ1986 እስከ 1992 ባሉት ዓመታት ውስጥ በቤተ ክርስቲያን ላይ ጠንካራ ወይም የተወሰነ መጠን ያለው እምነት የነበራቸው ጀርመናውያን ቁጥር ከ40 ወደ 33 በመቶ ዝቅ ብሏል። እንዲያውም በቀድሞዋ ምሥራቅ ጀርመን ቁጥሩ ከ20 በመቶ በታች ዝቅ ብሏል። በሌላ አነጋገር በቤተ ክርስቲያን ላይ ጥቂት እምነት ያላቸው ወይም ጭራሹኑ ምንም እምነት የሌላቸው ሰዎች ቁጥር በቀድሞው ምዕራብ ጀርመን ከ56 በመቶ ወደ 66 በመቶ ሲጨምር በቀድሞው ምሥራቅ ጀርመን ደግሞ ወደ 71 በመቶ ከፍ ብሏል።
ከሦስቱ የሰብዓዊው ኅብረተሰብ አምዶች ማለትም ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚና ከሃይማኖት ውጭ በሚገኙ መስኮችም በሌሎች የመታመኑ ጉዳይ እንደተመናመነ ይታያል። ሌላው ምሳሌ የሕግ አፈጻጸም ነው። በወንጀለኛ መቅጫ ሕጎች ውስጥ የሚገኙ ማምለጫ ቀዳዳዎች፣ ሕግን በትክክል በማስፈጸም ረገድ የሚገጥሙት ችግሮችና አጠያያቂ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች ሰዎች ያላቸውን እምነት በእጅጉ አናግተዋል። ታይም የተባለው መጽሔት “ነዋሪውም ሆነ ፖሊስ አደገኛ ወንጀለኞችን በተደጋጋሚ እየፈታ በሚለቅ የአሠራር ሥርዓት ላይ ያላቸው እምነት ተሟጧል” ብሏል። ሌላው ቀርቶ ፖሊሶች ምግባረ ብልሹና ጭካኔ ያለበት ድርጊት በመፈጸማቸው የሚቀርቡት ክሶች ሰዎች በፖሊሶች ላይ ያላቸው አመኔታ እንዲያሽቆለቁል አድርጓል።
የዓለም አቀፉን ፖለቲካ ያየንም እንደሆነ የሰላም ውይይቶች መቋረጥና የተኩስ አቁም ስምምነቶች መጣስ መተማመን መጥፋቱን ይጠቁማሉ። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር የሆኑት ቢል ሪቻርድሰን በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም እንዳይሰፍን ጋሬጣ የሆነው ነገር “መተማመን መጥፋቱ” መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ወደ ሰዎች የግል ሁኔታ ስንመጣ ደግሞ ሰው በተፈጥሮው ችግር ሲገጥመው እርዳታና ማጽናኛ ለማግኘት ጠጋ የሚለው ወደ ቅርብ ዘመዶቹና ጓደኞቹ ቢሆንም ብዙ ሰዎች የቅርብ ዘመዶቻቸውንና ወዳጆቻቸውንም አያምኗቸውም። ሁኔታው ዕብራዊው ነቢይ ሚክያስ ከገለጸው ጋር በእጅጉ የሚመሳሰል ነው:- “ባልንጀራን አትመኑ፣ በወዳጅም አትታመኑ፤ የአፍህን ደጅ በብብትህ ከምትተኛው ጠብቅ።”—ሚክያስ 7:5
የዘመኑ ምልክት
ጀርመናዊው የስነ ልቦና ባለ ሙያ አርተር ፊሸር በቅርቡ እንዲህ ሲሉ ተደምጠዋል:- “የማኅበረሰቡ እድገትም ሆነ የግለሰቦች ሁኔታ ወደፊት የተሻለ ይሆናል የሚለው እምነት በሁሉም መስክ በእጅጉ አሽቆልቁሏል። ወጣቶች ማኅበራዊ ተቋሞች ይረዱናል የሚል እምነት የላቸውም። በፖለቲካም ይሁን በሃይማኖት ወይም በሌላ በማንኛውም ድርጅት ላይ ያላቸው እምነት ተሟጧል።” ማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚያጠኑት ኡልሪክ ቤክ ዘመናት ያስቆጠሩ መመሪያዎችን፣ ተቋማትንና ኤክስፐርቶችን “የመጠራጠር ባህል” እንደተፈጠረ ገልጸዋል።
እንዲህ ዓይነቱ ባህል ሰዎች ራሳቸውን እንዲያገሉ፣ ሁሉንም ዓይነት መመሪያ ለመቀበል አሻፈረኝ እንዲሉ፣ በራሳቸው መስፈርቶች እንዲመሩና ከማንም ምክር ወይም መመሪያ ሳይቀበሉ የራሳቸውን ውሳኔ እንዲያደርጉ ገፋፍቷቸዋል። አንዳንዶች ከእንግዲህ ላምነው አልችልም ካሉት ሰው ጋር ባላቸው ግንኙነት ከመጠን በላይ ተጠራጣሪና አንዳንዴም አሳቢነት የጎደላቸው ሆነው ይገኛሉ። ይህ ዓይነቱ አመለካከት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጾ የሚገኘው ዓይነት ጤናማ ያልሆነ መንፈስ እንዲሰፍን ያደርጋል:- “በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን [ይመጣል]። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል።” (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ ምሳሌ 18:1) በእርግጥም በዛሬው ጊዜ ሌሎችን ማመን አስቸጋሪ መሆኑ የዘመኑ ምልክት ማለትም “በመጨረሻው ቀን” እንደምንገኝ የሚያሳይ ምልክት ነው።
ሌሎችን ማመን አስቸጋሪ በሆነበትና ከላይ እንደተጠቀሱት ያሉ ሰዎች በተጨናነቁበት ዓለም ውስጥ ከሕይወት ሙሉ ደስታ ማግኘት አይቻልም። ይሁን እንጂ ሁኔታዎች ይለወጣሉ ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነውን? በጊዜያችን ያለው መተማመን የጠፋበት ሁኔታ ማስተካከል ይቻል ይሆን? የሚቻል ከሆነስ እንዴትና መቼ?