ሕይወታችሁን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት
አባትየው በካንሰር በሽታ የአልጋ ቁራኛ ሆኖ ሞቱን እየተጠባበቀ ነው። ወንድ ልጁ በአባቱ የእንጨት ሥራ ክፍል ውስጥ ሆኖ አባቱ ይገለገልባቸው የነበሩትን መሣሪያዎች በየቦታቸው ይሰትራል። መሣሪያዎቹን አንድ በአንድ ባነሳ ቁጥር አባቱ በመሣሪያዎቹ ተጠቅሞ ይሠራቸው የነበሩትን ግሩም ዕቃዎች ያስታውሳል። የእንጨት ሥራው የሚካሄድበት ክፍል የሚገኘው ከመኖሪያ ቤታቸው አጠቀብ ቢሆንም አባቱ ወደዚህ ክፍል ገብቶ በደንብ የተካነባቸውን መሣሪያዎች ዳግመኛ እንደማያነሳቸው ያውቃል። እነዚያ ጊዜያት አልፈዋል።
ልጁ መክብብ 9:10 ላይ የሚገኘውን “አንተ በምትሄድበት በሲኦል [በመቃብር] ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ” የሚለውን ጥቅስ አስታወሰ። ይህን ጥቅስ በሚገባ ያውቀዋል። ሞት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የማይደረግበት ሁኔታ መሆኑን የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለሌሎች ሲያስተምር ይህን ጥቅስ ብዙ ጊዜ ተጠቅሞበታል። ሰሎሞን ምንም ማድረግ የማንችልበት ጊዜ ስለሚመጣ የቻልነውን ያክል በሕይወታችን ሙሉ በሙሉ መጠቀምና በሕይወት ዘመናችን ተደስተን መኖር እንዳለብን የተናገረው አሳማኝ ነጥብ ልቡን ነካው።
በደስታ ኑሩ
ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን በመላው የመክብብ መጽሐፍ ውስጥ አንባቢዎቹ በሕይወታቸው ተደስተው እንዲኖሩ ማሳሰቢያ ሰጥቷል። ለምሳሌ ያህል ምዕራፍ 3 እንዲህ ይላል:- “ሰው ደስ ከሚለውና በሕይወቱ ሳለ መልካምን ነገር ከሚያደርግ በቀር መልካም ነገር እንደሌለ አወቅሁ። ደግሞም ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው።”—መክብብ 3:12, 13
ሰሎሞን ይህን ሐሳብ ዳግመኛ እንዲጽፍ አምላክ በመንፈሱ አነሳስቶታል:- “እነሆ፣ እኔ ያየሁት መልካምና የተዋበ ነገር ሰው እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፣ ከፀሐይ በታችም በሚደክምበት ድካም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ ነው፤ ይህ እድል ፈንታው ነውና።”—መክብብ 5:18
በተመሳሳይም ወጣቶችን “አንተ ጎበዝ፣ በጉብዝናህ ደስ ይበልህ፣ በጉብዝናህም ወራት ልብህን ደስ ይበለው፣ በልብህም መንገድ ዓይኖችህም በሚያዩት ሂድ” በማለት ያሳስባል። (መክብብ 11:9) የወጣትነትን ጥንካሬና ጉልበት ሙሉ በሙሉ መጠቀም ምንኛ መልካም ነው!—ምሳሌ 20:29
“ፈጣሪህን አስብ”
እርግጥ ነው፣ ሰሎሞን ለልባችንና ለዓይናችን ማራኪ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ መከታተሉ ጥበብ እንደሆነ መናገሩ አልነበረም። (ከ1 ዮሐንስ 2:16 ጋር አወዳድር።) ቀጥሎ የጻፈው ሐሳብ ጉዳዩን ግልጽ ያደርገዋል:- “ዳሩ ግን ስለዚህ ነገር ሁሉ [ምኞቶችህን ለማርካት ስትል ታሳድደው ስለነበረው ነገር] እግዚአብሔር ወደ ፍርድ እንዲያመጣህ እወቅ።” (መክብብ 11:9) በየትኛውም የዕድሜ ክልል ላይ እንገኝ አምላክ ሕይወታችንን እንዴት እንደተጠቀምንበት እንደሚመለከትና ያንኑ መሠረት በማድረግ ፍርድ እንደሚሰጠን ማስታወስ ይኖርብናል።
በራሳችን ሕይወት ላይ ብቻ ያተኮረ ኑሮ መምራት እንደምንችልና ለአምላክ የምንሰጠውን አገልግሎት ወደ መጨረሻዎቹ የሕይወት ዘመናችን ማስተላለፍ እንደምንችል ማሰቡ ምንኛ ጥበብ የጎደለው ነው! ሕይወታችን በየትኛውም ጊዜ በድንገት ሊቀጭ ይችላል። እንዲህ ያለው ሁኔታ ባይደርስብን እንኳ በሽምግልና ዘመን አምላክን ማገልገል ቀላል አይሆንም። ሰሎሞን ይህን ሐቅ በመገንዘብ “የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ፤ ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ” በማለት ጽፏል።—መክብብ 12:1
ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ብዙ ችግሮች ያስከትላል። ሰሎሞን ዕድሜ መግፋት የሚያስከትላቸውን መዘዞች ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ቀጥሎ ገልጿል። እጆች ይንቀጠቀጣሉ፣ እግሮች ይደክማሉ እንዲሁም ጥርሶች ይረግፋሉ። የራስ ፀጉር ይሸብታል ብሎም ይረግፋል። በዕድሜ የገፋ ሰው ትንሽ ኮሽታ ሲሰማ በቀላሉ ስለሚያነቃው የወፍ ድምፅ እንኳ ሊያባንነው ይችላል። የስሜት ሕዋሳት የሆኑት የማየት፣ የመስማት፣ የመዳሰስ፣ የማሽተትና የመቅመስ ችሎታዎች ይዳከማሉ። የደከመው ሰውነቱ ካሁን ካሁን በመንገድ ላይ እወድቃለሁ ብሎ እንዲፈራና በሌሎች ነገሮችም ‘እንዲሸበር’ ያደርገዋል። በመጨረሻም ይሞታል።—መክብብ 12:2-7
የሽምግልና ዘመን በተለይ በወጣትነታቸው ጊዜ ‘ታላቁ ፈጣሪያቸውን ለማያስቡ’ ሰዎች አስከፊ ጊዜ ይሆንባቸዋል። ሕይወታቸውን በከንቱ ያጠፉ በመሆናቸው እንደነዚህ ያሉት ሰዎች በቀሪዎቹ የሕይወት ዘመናቸው ‘ደስታ አይኖራቸውም።’ ሲከተሉት የነበረው አምላካዊ ያልሆነ የአኗኗር ዘይቤም በሽምግልና ዘመናቸው ተጨማሪ ችግርና ሥቃይ ሊያስከትልባቸው ይችላል። (ምሳሌ 5:3-11) የሚያሳዝነው እንደነዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች ከሞት በስተቀር ወደፊት የሚታያቸው ምንም ነገር የለም።
በሽምግልና ዘመን ተደስቶ መኖር
ይህ ማለት ግን በዕድሜ የገፉ ሰዎች በሕይወታቸው ደስታ ማግኘት አይችሉም ማለት አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ብዙ ዘመናትና ረጅም ዕድሜ” ከአምላክ በረከት ጋር ተያይዘው ተገልጸዋል። (ምሳሌ 3:1, 2) ይሖዋ ወዳጁ ለነበረው ለአብርሃም:- “አንተ ግን . . . በመልካም ሽምግልና ትቀበራለህ” ብሎታል። (ዘፍጥረት 15:15) አብርሃም በመሸምገሉ ምክንያት ጉስቁልና የደረሰበት ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ያዋለውን ያለፈውን የሕይወት ዘመኑን ወደ ኋላ መለስ ብሎ በመመልከት በመጨረሻ የሕይወት ዘመኑ ሰላምና የመንፈስ እርጋታ አግኝቷል። በተጨማሪም “መሠረት ያላትን . . . ከተማ” ማለትም የአምላክን መንግሥት አሻግሮ በእምነት ተመልክቷል። (ዕብራውያን 11:10) በዚህ መንገድ ‘ብዙ ዘመናት ጠግቦ’ ሞተ።—ዘፍጥረት 25:8
በመሆኑም ሰሎሞን “ሰው ብዙ ዘመን በሕይወት ቢኖር በሁሉም ደስ ይበለው” በማለት አጥብቆ አሳስቧል። (መክብብ 11:8) ወጣቶችም ሆንን በዕድሜ የገፋን እውነተኛ ደስታ ከአምላክ ጋር በሚኖረን ዝምድና ላይ የተመካ ነው።
በእንጨት ሥራ ክፍል ውስጥ የነበረው ወጣት የመጨረሻውን የአባቱን መሣሪያ ቦታው ካስቀመጠ በኋላ ስለ እነዚህ ነገሮች አሰበ። ሕይወታቸውን በተሻለ መንገድ ለመጠቀም ይደክሙ የነበሩ ሆኖም ከፈጣሪያቸው ጋር ዝምድና ባለመመሥረታቸው ምክንያት ደስታ የራቃቸውን የሚያውቃቸውን ሰዎች አንድ በአንድ አሰበ። ሰሎሞን አንድ ሰው በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ደስ እንዲለው ማበረታቻ ከሰጠ በኋላ “የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ እንስማ፤ ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፤ እግዚአብሔርን ፍራ፣ ትእዛዙንም ጠብቅ” በሚሉት ቃላት ሁኔታውን ማጠቃለሉ ምንኛ የተገባ ነው!—መክብብ 12:13