ሕሊናህን ልታምነው ትችላለህ?
አብዛኛውን ጊዜ ኮምፓስ አስተማማኝ የሆነ መሣሪያ ነው። በምድር መግነጢሳዊ መስክ እየተመራ መግነጢሳዊው ቀስት ምንጊዜም ወደ ሰሜን ያመለክታል። በዚህም የተነሳ መንገደኞች የሚታይ ምልክት በማይኖርበት ጊዜ በኮምፓስ እየተመሩ አቅጣጫቸውን ሳይስቱ ሙሉ በሙሉ ተማምነው መጓዝ ይችላሉ። ይሁን እንጂ አንድ መግነጢሳዊ ዕቃ ኮምፓሱ አጠገብ ቢቀመጥስ? ቀስቱ ወደ ሰሜን ከማመልከት ይልቅ ወደ መግነጢሱ ይዞራል። በዚህ ጊዜ አስተማማኝ መመሪያ ሆኖ ሊያገለግል አይችልም።
በሰብዓዊው ሕሊና ላይም ተመሳሳይ ነገር ሊደርስ ይችላል። ፈጣሪ ይህን ችሎታ በውስጣችን የተከለው አስተማማኝ መመሪያ ሆኖ እንዲያገለግለን ነው። በአምላክ አምሳል የተፈጠርን እንደመሆናችን መጠን ውሳኔ ለማድረግ ስንፈልግ ሕሊናችን ያለማቋረጥ ትክክለኛ ወደ ሆነ አቅጣጫ ሊያመለክተን ይገባል። አምላክ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር መስፈርቶች እንድናንጸባርቅ ሊገፋፋን ይገባል። (ዘፍጥረት 1:27) ብዙውን ጊዜም እንዲህ ያደርጋል። ለምሳሌ ያህል ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ ሲጽፍ አምላክ የገለጠውን ሕግ የማያውቁ አንዳንድ ሰዎች እንኳ “በተፈጥሮአቸው ሕግ የሚያዝዘውን ነገር ይፈጽማሉ” ብሏል። ለምን? ምክንያቱም ‘ሕሊናቸው ስለሚመሰክርባቸው ነው።’—ሮሜ 2:14, 15 የ1980 ትርጉም
ሆኖም ሕሊና ምላሽ መስጠት በሚያስፈልገው ጊዜ ሁሉ ምላሽ ይሰጣል ማለት አይደለም። በሰብዓዊ አለፍጽምና ምክንያት ስህተት እንደሆነ የምናውቀውን ነገር ማድረጉ ይቀናናል። “በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፣ ነገር ግን በብልቶቼ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ” በማለት ጳውሎስ ሳይሸሽግ ተናግሯል። (ሮሜ 7:22, 23) ለተሳሳቱ ዝንባሌዎች በተደጋጋሚ የምንሸነፍ ከሆነ ቀስ በቀስ ሕሊናችን ይደነዝዝና ውሎ አድሮ እንዲህ የመሰለው ተግባር ስህተት መሆኑን ከናካቴው መናገሩን ያቆማል።
ይሁን እንጂ ፍጹም ባንሆንም እንኳ ሕሊናችንን አምላክ ካወጣቸው መስፈርቶች ጋር ማስማማት እንችላለን። እንዲያውም እንዲህ ማድረጋችን እጅግ አስፈላጊ ነው። ንጹሕና በተገቢ መንገድ የሰለጠነ ሕሊና ከአምላክ ጋር ሞቅ ያለ የግል ዝምድና እንድንመሠርት የሚረዳን ከመሆኑም በላይ ለደህንነታችንም የግድ አስፈላጊ ነው። (ዕብራውያን 10:22፤ 1 ጴጥሮስ 1:15, 16) ከዚህም በላይ ጥሩ ሕሊና በሕይወታችን ውስጥ ጥበብ የሞላባቸው ውሳኔዎች እንድናደርግ ይረዳናል። ይህም ሰላምና ደስታ እንድናገኝ ይረዳናል። መዝሙራዊው እንዲህ ያለ ሕሊና ስላለው ሰው ሲናገር “የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው፣ በእርምጃውም አይሰናከልም” ብሏል።—መዝሙር 37:31
ሕሊናን ማሰልጠን
ሕሊናን ማሰልጠን ዝርዝር ሕግጋት ከመሸምደድና ከእነርሱ ጋር ተጣብቆ ከመኖር የበለጠ ነገር ማድረግን ይጠይቃል። በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ፈሪሳውያን ያደርጉ የነበረው ይህንኑ ነበር። እነዚህ ሃይማኖታዊ መሪዎች ሕጉን ያውቁ የነበረ ከመሆኑም በላይ ሕዝቡ ሕጉን እንዳይጥስ ለመርዳት በሚል ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ ወግ አዳብረው ነበር። በዚህም የተነሳ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በሰንበት ቀን እሸት ቀጥፈው ሲበሉ በተመለከቱ ጊዜ ቁጣቸው ነድዶ ነበር። እንዲሁም ኢየሱስ እጁ የሰለለችበትን ሰው በሰንበት ቀን በፈወሰ ጊዜ ክፉኛ ተፈታትነውት ነበር። (ማቴዎስ 12:1, 2, 9, 10) በፈሪሳውያን ወግ መሠረት እነዚህ ድርጊቶች አራተኛውን ትእዛዝ የሚጻረሩ ነበሩ።—ዘጸአት 20:8-11
ፈሪሳውያን ሕጉን በጥንቃቄ አጥንተው እንደነበር ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ሕሊናቸው ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር የሚስማማ ነበርን? በጭራሽ! እንዲያውም የሰንበትን ደንብ ተጻርሯል ብለው ከተቹት በኋላ ወዲያውኑ ኢየሱስን “እንዴት አድርገው እንደሚያጠፉት” ተማከሩ። (ማቴዎስ 12:14) እነዚህ ራሳቸውን የሚያመጻድቁ የሃይማኖት መሪዎች በሰንበት ቀን እሸት ቀጥፎ መብላትንና መፈወስን በጥብቅ እንደተቃወሙ ልብ በሉ፤ ኢየሱስን ለመግደል ሲያሴሩ ግን ሕሊናቸው ቅንጣት ታክል አልቆረቆራቸውም!
የካህናት አለቆችም ተመሳሳይ የሆነ የተጣመመ አስተሳሰብ ነበራቸው። እነዚህ ብልሹ ሰዎች ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጣቸው ከቤተ መቅደሱ ግምጃ ቤት አውጥተው ለይሁዳ 30 ብር ሲሰጡ ሕሊናቸው ፈጽሞ አልወቀሳቸውም። ይሁን እንጂ ይሁዳ ባልተጠበቀ ሁኔታ ገንዘቡን መልሶ አምጥቶ ወደ ቤተ መቅደሱ በወረወረ ጊዜ የካህናት አለቆቹ ሕሊናቸው አስጨነቃቸው። “የደም ዋጋ ነውና [ሳንቲሞቹን] ወደ መባ ልንጨምረው አልተፈቀደም አሉ።” (ማቴዎስ 27:3-6) የካህናት አለቆቹ ይሁዳ አሁን ይዞት የመጣው ገንዘብ ርኩስ በመሆኑ እንዳስጨነቃቸው ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። (ከዘዳግም 23:18 ጋር አወዳድር።) ሆኖም እነዚሁ ሰዎች የአምላክን ልጅ አሳልፎ እንዲሰጣቸው ገንዘብ መስጠታቸው ግን ስህተት ሆኖ አልታያቸውም!
ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር ስምም መሆን
ሕሊናን ማሰልጠን ማለት አእምሮን በተለያዩ ደንቦች ከመሙላት የበለጠ ነገርን እንደሚጠይቅ ከላይ ያሉት ምሳሌዎች ያሳያሉ። እርግጥ የአምላክን ሕግጋት ማወቁ የግድ አስፈላጊ ነው፤ ለመዳን ከፈለግንም ሕጎቹን መታዘዝ ይኖርብናል። (መዝሙር 19:7-11) ይሁን እንጂ የአምላክን ሕግጋት ከማጥናታችን በተጨማሪ ልባችን ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር እንዲስማማ ማድረግ ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ “ዓይኖችህ ግን አስተማሪህን ያያሉ፣ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ ብትል ጆሮችህ በኋላህ:- መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ የሚለውን ቃል ይሰማሉ” በማለት በኢሳይያስ በኩል ያስነገረው ትንቢት በሥራ ላይ ሲውል ለመመልከት እንችላለን።—ኢሳይያስ 30:20, 21፤ 48:17
ይህ ማለት ግን ውሳኔ የሚጠይቅ አንድ ከባድ ጉዳይ በሚገጥመን ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለብን የሚነግረን ድምፅ ቃል በቃል እንሰማለን ማለት አይደለም። ሆኖም አስተሳሰባችን አምላክ ለነገሮች ካለው አስተሳሰብ ጋር በሚስማማበት ጊዜ ሕሊናችን እርሱን የሚያስደስተውን ውሳኔ እንድናደርግ ሊገፋፋን በሚችልበት ሁኔታ ላይ ሊገኝ ይችላል።—ምሳሌ 27:11
በ18ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ይኖር የነበረውን የዮሴፍን ምሳሌ እንመልከት። የጶጢፋራ ሚስት ከእርሷ ጋር ዝሙት እንዲፈጽም ስትወተውተው ዮሴፍ “እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ?” በማለት ተቃውሞውን ገልጿል። (ዘፍጥረት 39:9) በዮሴፍ ዘመን አምላክ ዝሙትን የሚያወግዝ በጽሑፍ የሰፈረ ሕግ አላወጣም ነበር። ከዚህም በላይ ዮሴፍ ይኖር የነበረው የቤተሰብ ምክር ወይም የእምነት አባቶች የሚሰጡትን መመሪያ በቀላሉ ሊያገኝ በማይችልበት በግብፅ አገር ነበር። ታዲያ ዮሴፍ የደረሰበትን ፈተና ሊቋቋም የቻለው እንዴት ነው? በአጭር አነጋገር የሰለጠነ ሕሊና ስለነበረው ነው። ዮሴፍ ባልና ሚስት “አንድ ሥጋ” ናቸው የሚለውን የአምላክ አመለካከት በውስጡ አዳብሮ ነበር። (ዘፍጥረት 2:24) በዚህም የተነሳ የሌላን ሰው ሚስት መውሰድ ስህተት እንደሆነ ተገንዝቧል። ዮሴፍ በዚህ ጉዳይ ላይ የነበረው አመለካከት አምላክ ካለው አመለካከት ጋር የሚስማማ ነበር። ዝሙት የሥነ ምግባር አቋሙን የሚያስጥስ ድርጊት ነበር።
በዛሬው ጊዜ ዮሴፍን የመሰሉ ጥቂት ሰዎች አሉ። የፆታ ብልግና በሰፊው ተዛምቶ ይገኛል፤ ብዙዎች በፈጣሪያቸው፣ በራሳቸው አልፎ ተርፎም በትዳር ጓደኛቸው ዘንድ ንጹሕ ሥነ ምግባር ይዘው የመኖር ግዴታ እንዳለባቸው ጨርሶ አይታያቸውም። ሁኔታው በኤርምያስ መጽሐፍ ውስጥ ከተገለጸው ጋር በእጅጉ የሚመሳሰል ነው:- “ማናቸውም:- ምን አድርጌአለሁ? ብሎ ከክፋቱ ንስሐ የገባ የለም፤ ወደ ሰልፍም እንደሚሮጥ ፈረስ እያንዳንዱ በየመንገዱ ይሄዳል።” (ኤርምያስ 8:6) ስለዚህ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በአሁኑ ጊዜ ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር ተስማምተን መኖራችን በጣም አስፈላጊ ነው። እንዲህ ማድረግ እንድንችል የሚረዱን ግሩም ዝግጅቶች አሉ።
ሕሊናን ለማሰልጠን የሚያስችል እርዳታ
“የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ” በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች “ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር” ይጠቅማሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት መልካሙንና ክፉውን ለመለየት የሚያስችለውንና መጽሐፍ ቅዱስ “የማስተዋል ችሎታ” ብሎ የሚጠራውን ነገር ለማዳበር ይረዳናል። (ዕብራውያን 5:14 NW) አምላክ ለሚወዳቸው ነገሮች ፍቅር እንድናዳብርና የሚጠላቸውን ነገሮች እንድንጸየፍ ያስችለናል።—መዝሙር 97:10፤ 139:21
መጽሐፍ ቅዱስን የምናጠናበት ዓላማ እንዲሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ እውቀት ለማግኘት ሳይሆን የእውነትን ቃል መንፈስና የሚያስገኘውን ተግባራዊ ጠቀሜታ ለመረዳት ብለን መሆን ይኖርበታል። መጠበቂያ ግንብ በመስከረም 1, 1976 እትሙ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ቅዱሳን ጽሑፎችን ስናጠና የአምላክን ፍትሕ፣ ፍቅርና ጽድቅ ለመገንዘብ መጣርና ልክ የመብላትና የመጠጣት ያክል የሕይወታችን ክፍል እንዲሆኑ በልባችን ውስጥ ሰርጸው እንዲገቡ ማድረግ አለብን። ትክክልና ስህተት የሆኑ ነገሮችን ለይተን በማወቅ ሥነ ምግባራዊ ኃላፊነት ይበልጥ በተሟላ መንገድ እንዲሰማን ለማድረግ መጣር ይኖርብናል። ከዚህም በላይ ሕሊናችን ሕግ ሰጪና ፈራጅ በሆነው አምላክ ዘንድ ተጠያቂ መሆኑን በሚገባ እንዲገነዘብ ማድረግ ይኖርብናል። (ኢሳ. 33:22) ስለዚህ ስለ አምላክ ትምህርት በምንቀስምበት ጊዜ በሁሉም የኑሮ ዘርፎች እርሱን ለመምሰል ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።”
“የክርስቶስን አስተሳሰብ” መያዝ
ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችን “የክርስቶስን አስተሳሰብ” እንድንይዝ ማለትም ኢየሱስ ያሳየውን የታዛዥነትና የትህትና ባህርይ እንድናሳይ ይረዳናል። (1 ቆሮንቶስ 2:16 NW) የአባቱን ፈቃድ ማድረግ ደስታ የሚሰጠው ነገር እንጂ እንዲሁ በነሲብ የሚፈጽመው ልማዳዊ ድርጊት አልነበረም። ያሳይ የነበረውን ዝንባሌ መዝሙራዊው ዳዊት አስቀድሞ በትንቢት ገልጾት ነበር። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ለማድረግ ወደድሁ፣ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው።”a—መዝሙር 40:8
ሕሊናን ለማሰልጠን “የክርስቶስን አስተሳሰብ” መኮረጅ እጅግ አስፈላጊ ነው። ኢየሱስ ፍጹም ሰው ሆኖ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሰብዓዊ አቅም የሚፈቅደውን ያህል ሙሉ በሙሉ የአባቱን ባሕርያትና ጠባይ አንጸባርቋል። በዚህም የተነሳ “እኔን ያየ አብን አይቶአል” ብሎ ለመናገር ችሏል። (ዮሐንስ 14:9) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ማንኛውም ሁኔታ ሲገጥመው አባቱ እንዲያደርግ የሚፈልግበትን ነገር ያደርግ ነበር። ስለዚህ የኢየሱስን የሕይወት ታሪክ በምናጠናበት ጊዜ የይሖዋ አምላክን ማንነት በሚገባ እንገነዘባለን።
ይሖዋ ‘መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽ፣ ቸርነቱ የበዛ’ እንደሆነ እናነባለን። (ዘጸአት 34:6) ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር በነበረው ግንኙነት እነዚህን ባሕርያት በተደጋጋሚ ጊዜያት አንጸባርቋል። ከመሃከላቸው ማን ታላቅ እንደሚሆን በተደጋጋሚ ጊዜያት ሲከራከሩ ኢየሱስ በትዕግሥት “ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፣ ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን” በማለት በቃልና በምሳሌ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 20:26, 27) የኢየሱስን የሕይወት ታሪክ በመመርመር ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር መስማማት እንደምንችል የሚያሳዩ ሌሎች ብዙ ምሳሌዎችም አሉ።
ስለ ኢየሱስ ይበልጥ እያወቅን በሄድን መጠን የሰማዩ አባታችንን ይሖዋን ለመምሰል ይበልጥ የታጠቅን እንሆናለን። (ኤፌሶን 5:1, 2) ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር ስምም የሆነ ሕሊና በትክክለኛው አቅጣጫ ይመራናል። ይሖዋ በእርሱ ላይ ለሚታመኑ ሁሉ “አስተምርሃለሁ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ ዓይኖቼን በአንተ ላይ አጠናለሁ” በማለት ቃል ገብቷል።—መዝሙር 32:8
የሰለጠነ ሕሊና የሚያስገኘው ጥቅም
ሙሴ ፍጹም ያልሆነው ሰብዓዊ ሰው በራስ የመመራት ዝንባሌ ያለው መሆኑን በመገንዘቡ “የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ ይጠብቁና ያደርጉ ዘንድ ልጆቻችሁን እንድታዝዙበት ዛሬ የምመሰክርላችሁን ቃል ሁሉ በልባችሁ አኑሩት” በማለት እስራኤላውያንን አስጠንቅቋል። (ዘዳግም 32:46) እኛም ብንሆን የአምላክን ሕግ በልባችን ላይ መቅረጽ አለብን። እንዲህ ካደረግን ሕሊናችን እርምጃችንን ለመምራት የተሻለ ብቃት ስለሚኖረው ትክክል የሆኑ ውሳኔዎችንም እንድናደርግ ይረዳናል።
እርግጥ ነው ጠንቃቆች መሆን ይገባናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እንዲህ ይላል:- “ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፤ ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው።” (ምሳሌ 14:12) ይህ ሁኔታ በተደጋጋሚ የሚከሰተው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኮለኛ እጅግም ክፉ ነው፤ ማንስ ያውቀዋል?” በማለት ምክንያቱን ይገልጻል። (ኤርምያስ 17:9) ስለዚህ ሁላችንም ምሳሌ 3:5, 6 ላይ የሚገኘውን “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል” የሚለውን ምክር መከተላችን የተገባ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን በጻፈው ደብዳቤ በ40ኛው መዝሙር ላይ የሚገኙት ቃላት በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ተፈጻሚነት እንዳላቸው አመልክቷል።—ዕብራውያን 10:5-10
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመጽሐፍ ቅዱስ የሰለጠነ ሕሊና ልክ እንደ ኮምፓስ ትክክለኛውን አቅጣጫ ሊያመለክተን ይችላል
[ምንጭ]
ኮምፓስ:- Courtesy, Peabody Essex Museum, Salem, Mass.