ያለንበትን ጊዜ በንቃት እየተከታተልክ ነውን?
ለአደጋ ንቁ መሆንና አለመሆን የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነው። ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት በሁለት የእሳተ ገሞራ ደሴቶች ላይ የደረሰውን ነገር መጥቀስ ይቻላል።
ግንቦት 8, 1902 የካረቢያን ደሴት በሆነችው በማርቲኒክ የፐሌ ተራራ እሳተ ገሞራ ፈነዳ፤ ይህም በ20ኛው መቶ ዘመን ከፈነዱት እሳተ ገሞራዎች ሁሉ እጅግ ኃይለኛ ነበር። በእሳተ ገሞራው ግርጌ በምትገኘው በሴይንት ፒየር ከተማ ከሚገኙት 30,000 ነዋሪዎች መካከል በሕይወት የተረፈ የለም ለማለት ይቻላል።
ሰኔ 1991 ደግሞ በክፍለ ዘመኑ ከደረሱት ፍንዳታዎች ሁሉ እጅግ ከፍተኛ ሳይሆን አይቀርም የተባለለት የፒነቱቦ ተራራ ፈነዳ። ፍንዳታው የደረሰው በፊሊፒንስ በጣም ብዙ ሕዝብ በሚኖርበት አካባቢ ሲሆን 900 የሚሆኑ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ይሁን እንጂ በዚህ ወቅት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ሊተርፍ ችሏል፤ ለዚህም አስተዋጽዖ ያደረጉት የሚከተሉት ሁለት ነገሮች ናቸው:- (1) ለአደጋው ንቁ መሆንና (2) ከተሰጡት ማስጠንቀቂያዎች ጋር የሚስማማ እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ መሆን።
ተገቢ እርምጃ መወሰዱ የብዙዎችን ሕይወት አድኗል
የፒነቱቦ ተራራ በሚያዝያ 1991 ሊፈነዳ እንደተቃረበ ምልክት ማሳየት የጀመረው በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት ያህል ዋልጌ (dormant) ሆኖ ከቆየ በኋላ ነበር። ከተራራው ጫፍ እንፋሎትና ሰልፈር ዳይኦክሳይድ የተባለ ኬሚካል እያፈተለከ መውጣት ጀመረ። የአካባቢው ነዋሪዎች ተከታታይ የመሬት ርዕደቶች የተሰማቸው ሲሆን የከፋ ነገር መምጣቱን የሚያመለክተው ጠጣር የሆነ ትፍ ቅላጭ ድንጋይ (lava) ከተራራው አናት ላይ መውጣት ጀመረ። የፊሊፒንስ የእሳተ ገሞራና የርዕደ ምድር ጥናት ተቋም ሳይንቲስቶች በቅርብ ይከታተሉት ስለነበረ በአቅራቢያው በሚገኙ ከተማዎችና መንደሮች የሚኖሩ 35,000 ሰዎችን ማስወጣቱ ጥበብ እንደሚሆን ባለ ሥልጣናትን አሳመኑ።
ሰዎች ያለ አንድ ምክንያት ቤታቸውን ለቅቀው ለመሰደድ እንደሚያመነቱ የታወቀ ቢሆንም የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ የሚያደርሰውን ጥፋት በግልጽ የሚያሳይ አንድ የቪዲዮ ፊልም በማቅረብ ሰዎች ቸልተኞች ከመሆን ይልቅ እርምጃ እንዲወስዱ ቅስቀሳ ተደርጓል። ሕዝቡ ከአካባቢው የለቀቀው በተገቢው ጊዜ ነበር። ከሁለት ቀናት በኋላ አንድ ከፍተኛ የሆነ ፍንዳታ 8 ኩቢክ ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው አመድ ወደ ከባቢ አየር ረጨ። ከጊዜ በኋላ ጭቃፍሶች (mudflows or lahars) በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድለዋል። ሆኖም ሰዎች አደጋውን በንቃት እንዲጠባበቁ በመደረጋቸውና ከማስጠንቀቂያዎቹ ጋር ተስማሚ የሆነ እርምጃ በመውሰዳቸው ብዙዎች ምናልባትም በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሊተርፉ ችለዋል።
ሰው ሠራሽ ከሆነ ጥፋት ማምለጥ
በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖችም ቤት ንብረታቸውን ትተው ለመሄድ ወይም ላለመሄድ መወሰን ግድ ሆኖባቸው ነበር። በ66 እዘአ ከዚያች ከተማ መሸሻቸው ሌሎች ነዋሪዎችና በ70 እዘአ የማለፍን በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው የነበሩ በሺህ የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ከደረሰባቸው ጥፋት ሊድኑ ችለዋል። የሮማ ሠራዊት ምንም ማምለጫ እንዳይኖር ባደረገበት ወቅት በዚያች ዙሪያዋን በግንብ በታጠረች ከተማ ውስጥ የማለፍ በዓልን ለማክበር ከአንድ ሚልዮን የሚበልጥ ሕዝብ ይገኝ ነበር። ረሃብ፣ የሥልጣን ሽኩቻዎችና ከሮማውያኑ የሚሰነዘረው የማያባራ ጥቃት ከአንድ ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ለሞት ዳርጓል።
አይሁዳውያን በሮም ላይ ያስነሡት ዓመፅ እንዲያከትም ያደረገው ታላቅ ጥፋት የደረሰው እንዲሁ በድንገት አልነበረም። በርካታ አሥርተ ዓመታት ቀደም ብሎ ኢየሱስ ክርስቶስ ኢየሩሳሌም እንደምትከበብ ተናግሮ ነበር። እንዲህ አለ:- “ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ። የዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፣ በመካከልዋም ያሉ ከእርስዋ ፈቀቅ ይበሉ፣ በገጠር ያሉም ወደ እርስዋ አይግቡ።” (ሉቃስ 21:20, 21) እነዚህ መመሪያዎች ግልጽ ነበሩ፤ የኢየሱስ ተከታዮችም በቁም ነገር ተመልክተዋቸዋል።
በአራተኛው መቶ ዘመን ይኖር የነበረው ታሪክ ጸሐፊ የቂሣርያው ዩሴቢየስ እንደዘገበው በመላው ይሁዳ የሚገኙ ክርስቲያኖች በኢየሱስ ማስጠንቀቂያ መሠረት እርምጃ ወስደዋል። ሮማውያኑ በ66 እዘአ ያደረጉትን የመጀመሪያ ከበባ ትተው በሄዱ ጊዜ ብዙ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ሮማ ውስጥ በፍርጊያ ክፍለ ሃገር በምትገኘው የአሕዛብ ከተማ በፔላ ለመኖር ሄዱ። ስለ ጊዜያቸው ሁኔታ ንቁ በመሆንና የኢየሱስን ማስጠንቀቂያ ሰምተው እርምጃ በመውሰድ “በታሪክ ዘመናት በሙሉ በአሰቃቂነቱ አቻ አልተገኘለትም” ከተባለለት ከበባ ሊያመልጡ ችለዋል።
ዛሬም በተመሳሳይ ንቁ መሆን ያስፈልጋል። አሁንም ቁርጥ ያለ እርምጃ መውሰድ ግድ ነው። የሚቀጥለው ርዕስ እንዲህ ማድረግ አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ያብራራል።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Godo-Foto, West Stock