የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 9/15 ገጽ 8-9
  • አንድ ኩሩ እንደራሴ ግዛቱን አጣ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አንድ ኩሩ እንደራሴ ግዛቱን አጣ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • እንደራሴ ወይስ ንጉሥ?
  • ከመጠን በላይ በራሱ የሚተማመን ኩሩ እንደራሴ
  • ዓለምን የለወጡ አራት ቃላት
    የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል!
  • ይህን ያውቁ ኖሯል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020
  • ዳንኤል ማን ነው?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
  • ዳንኤል—ክስ የቀረበበት መጽሐፍ
    የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል!
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 9/15 ገጽ 8-9

አንድ ኩሩ እንደራሴ ግዛቱን አጣ

“ንጉሡ ብልጣሶር ለሺህ መኳንንቶቹ ትልቅ ግብዣ አደረገ፣ በሺሁም ፊት የወይን ጠጅ ይጠጣ ነበር” ሲል ነቢዩ ዳንኤል ጽፏል። ይሁን እንጂ ግብዣው እየሞቀ ሲሄድ የንጉሡ “ፊት ተለወጠበት፣ አሳቡም አስቸገረው፣ የወገቡም ጅማቶች ተፈቱ፣ ጉልበቶቹም ተብረከረኩ።” ሌሊቱ ከመገባደዱ በፊት “የከለዳውያን ንጉሥ ብልጣሶር ተገደለ። ሜዶናዊውም ዳርዮስ መንግሥቱን ወሰደ።”​—⁠ዳንኤል 5:​1, 6, 30, 31

ብልጣሶር ማን ነበር? “የከለዳውያን ንጉሥ” ተብሎ ሊጠራ የቻለውስ እንዴት ነበር? በጥንቱ የባቢሎን ግዛት ውስጥ የነበረው ትክክለኛ የሥልጣን ቦታ ምን ነበር? ግዛቱን ያጣው እንዴት ነበር?

እንደራሴ ወይስ ንጉሥ?

ዳንኤል የብልጣሶር አባት ናቡከደነፆር መሆኑን ገልጿል። (ዳንኤል 5:​2, 11, 18, 22) ይሁን እንጂ ይህ ዝምድና ቀጥተኛ የሆነ የሥጋ ዝምድና አይደለም። በሬይመንድ ፒ ዶርቲ የተዘጋጀው ኔበኒደስ ኤንድ ቤልሼዘር የተባለው መጽሐፍ ናቡከደነፆር ለብልጣሶር በእናቱ በኒቶክሪስ በኩል አያቱ ሳይሆን እንደማይቀር ይናገራል። በተጨማሪም ናቡከደነፆር “አባት” የሆነው ከብልጣሶር በፊት ንጉሥ ስለነበረ ብቻ ሊሆን ይችላል። (ከዘፍጥረት 28:​10, 13 ጋር አወዳድር።) ያም ሆነ ይህ በ19ኛው መቶ ዘመን በደቡብ ኢራቅ የተገኙት በሞላላ ሸክላዎች ላይ የተቀረጹ ጽሑፎች ብልጣሶር የባቢሎኑ ንጉሥ የናቦኒደስ የበኩር ልጅ መሆኑን አመልክተዋል።

በዳንኤል ምዕራፍ 5 ላይ ያለው ዘገባ በ539 ከዘአበ ባቢሎን በወደቀችበት ምሽት በተከናወኑ ነገሮች ላይ ያተኮረ በመሆኑ ብልጣሶር ንጉሣዊ ሥልጣን ሊይዝ የቻለው እንዴት እንደሆነ አይናገርም። ይሁን እንጂ አርኪኦሎጂያዊ ምንጮች በናቦኒደስና በብልጣሶር መካከል ስላለው ዝምድና አንዳንድ ሐሳቦችን ይሰጣሉ። አርኪኦሎጂስትና የጥንት ሴማዊ ቋንቋዎች አጥኚ የሆኑት አለን ሚለርድ “ባቢሎናዊ ጽሑፎች ናቦኒደስ ለየት ያለ ባሕርይ የነበረው ገዥ መሆኑን ያሳያሉ” ሲሉ ተናግረዋል። ሚለርድ አክለውም:- “የባቢሎንን አማልክት ችላ ባይልም . . . በሌሎች ሁለት ከተማዎች ማለትም በኡርና በሃራን ለሚገኘው የጨረቃ አምላክ የተለየ ትኩረት ይሰጥ ነበር። ናቦኒደስ በንግሥና በቆየባቸው በርካታ ዓመታት እንኳ በባቢሎን አልኖረም፤ ከዚህ ይልቅ ራቅ ብላ በሰሜን አረቢያ በምትገኘው በቴይማ [ወይም፣ ቴማ] የባሕር ዳርቻ ይኖር ነበር።” ማስረጃዎቹ እንደሚያሳዩት ናቦኒደስ አብዛኛውን የንግሥና ዘመኑን ያሳለፈው ከዋና ከተማዋ ከባቢሎን ውጪ ነበር። እሱ በማይኖርበት ጊዜ የማስተዳደሩ ሥልጣን ለብልጣሶር ይሰጥ ነበር።

“በግጥም የተቀነባበረ የናቦኒደስ ታሪክ” ተብሎ የሚጠራ አንድ ሰነድ ብልጣሶር ስለነበረው ትክክለኛ የሥልጣን ቦታ ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጣል:- “[ናቦኒደስ] ‘ሠራዊቱን’ ለታላቅ ልጁ (ወንድ ልጁ)፣ ለበኩር ልጁ ሰጠ፤ በመላ አገሪቱ የሚገኘው ሠራዊት በእሱ (አመራር) ሥር እንዲሆኑ አደረገ። የንግሥና ሥልጣኑን (በሙሉ) በውክልና ሰጠው።” ይህም በመሆኑ ብልጣሶር እንደራሴ ነበር።

ይሁንና አንድ እንደራሴ እንደ ንጉሥ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል? በ1970ዎቹ በሰሜን ሶሪያ የተገኘ የአንድ ጥንታዊ ገዥ ሐውልት እንደሚያሳየው አንድ ገዥ ዝቅተኛ ሥልጣን እያለውም ቢሆን ንጉሥ ተብሎ የሚጠራበት ጊዜ ነበር። ሐውልቱ የጎዛን ገዥ ሐውልት ሲሆን በሶሪያና በአረማይክ ቋንቋ ጽሑፍ ተቀርጾበታል። በሶሪያ ቋንቋ የተቀረጸው ጽሑፍ ሰውዬውን የጎዛን ገዥ ብሎ ሲጠራው በአረማይክ ቋንቋ የተቀረጸው ጽሑፍ ግን ንጉሥ ብሎ ይጠራዋል። ስለዚህ ብልጣሶር በባቢሎን መንግሥታዊ ጽሑፎች ላይ አልጋ ወራሽ ተብሎ ሲጠራ በዳንኤል የአረማይክ ጽሑፍ ላይ ግን ንጉሥ መባሉ አዲስ ነገር አልነበረም።

በናቦኒደስና በብልጣሶር መካከል የነበረው የጥምር ገዥነት ዝግጅት የጥንቱ የባቢሎን መንግሥት እስካከተመበት ቀን ድረስ ዘልቋል። ባቢሎን በወደቀችበት ምሽት ብልጣሶር ዳንኤልን በመንግሥቱ ሁለተኛ ሳይሆን ሦስተኛ ገዥ አድርጎ እንደሚሾመው ነግሮት ነበር።​—⁠ዳንኤል 5:​16

ከመጠን በላይ በራሱ የሚተማመን ኩሩ እንደራሴ

በብልጣሶር ንግሥና ማክተሚያ ላይ የተከናወኑ ነገሮች መስፍኑ ከመጠን በላይ በራሱ የሚተማመንና ኩሩ እንደነበር ያሳያሉ። ናቦኒደስ ጥቅምት 5 ቀን 539 ከዘአበ የሥልጣን ዘመኑ ባከተመበት ወቅት በሜዶ ፋርስ ኃይሎች ተሸንፎ ቦርሲፓ በሚባል ቦታ ተሸሸገ። ባቢሎን ራሷ ተከብባ ነበር። ሆኖም ብልጣሶር ግዙፍ በሆኑ ቅጥሮች በተከበበችው ከተማ ውስጥ መሆኑ ደኅንነት እንዲሰማው ስላደረገው በዚያ ቀውጢ ምሽት “ለሺህ መኳንንቶቹ ትልቅ ግብዣ አደረገ።” በአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ይኖር የነበረው ግሪካዊ ታሪክ ጸሐፊ ሄሮደተስ በከተማው ውስጥ የነበሩ ሰዎች “በዚያን ጊዜ ይጨፍሩና ይዝናኑ ነበር” ሲል ተናግሯል።

ይሁንና ከባቢሎን ቅጥሮች ውጪ የሜዶ ፋርስ ሠራዊት በተጠንቀቅ ቆሞ ነበር። በቂሮስ አመራር ሥር በመሆን በከተማይቱ መሃል ለመሃል ያልፍ የነበረውን የኤፍራጥስ ወንዝ ውኃ አቅጣጫ ቀየሩ። ተዋጊዎቹ የውኃው መጠን በበቂ ሁኔታ እንደቀነሰ ወንዙ በሚያልፍበት ውስጥ ለመጓዝ ዝግጁ ነበሩ። ዳገቱን ይወጡና በወንዙ ዳርቻ በሚገኙትና ክፍት በነበሩት ከመዳብ የተሠሩ በሮች አልፈው ወደ ከተማይቱ ይገባሉ።

ብልጣሶር ከከተማይቱ ውጪ የሚካሄደውን እንቅስቃሴ ተመልክቶ ቢሆን ኖሮ የመዳብ በሮቹን በዘጋ፣ ጠንካራ ወታደሮቹን በወንዙ ዳርቻ በሚገኘው ቅጥር ላይ ባሰለፈና ጠላቶቹን ባጠመደ ነበር። ከዚህ ይልቅ በወይን መጠጥ ስሜት ተገፋፍቶ እብሪተኛው ብልጣሶር ከይሖዋ ቤተ መቅደስ የተወሰዱትን ዕቃዎች እንዲያመጡ አደረገ። ከዚያም እንግዶቹ፣ ሚስቶቹና ቁባቶቹ የባቢሎንን አማልክት እያወደሱ በድፍረት በዕቃዎቹ ጠጡ። በድንገት አንድ እጅ በተአምራዊ ሁኔታ ታየና በቤተ መንግሥቱ ግድግዳ ላይ መጻፍ ጀመረ። በፍርሃት የተዋጠው ብልጣሶር የመልእክቱ ትርጉም ምን እንደሆነ እንዲነግሩት ጠቢባኑን በሙሉ ጠራ። ይሁን እንጂ “ጽሕፈቱን ያነብቡ፣ ፍቺውንም ለንጉሡ ያሳውቁ ዘንድ አልቻሉም።” በመጨረሻም ዳንኤል “ወደ ንጉሡ ፊት ገባ።” ደፋር የነበረው የይሖዋ ነቢይ ባቢሎን በሜዶንና በፋርስ ሰዎች እጅ እንደምትወድቅ የሚተነብየውን የዚያን ተአምራዊ መልእክት ትርጉም በመለኮታዊ መንፈስ መሪነት ተናገረ።​—⁠ዳንኤል 5:​2–28

የሜዶንና የፋርስ ሰዎች ከተማዋን በቀላሉ ተቆጣጠሩ፤ ብልጣሶርም ያቺን ሌሊት በሕይወት አላሳለፈም። ብልጣሶር በመሞቱና ናቦኒደስ ለቂሮስ እጁን በመስጠቱ የጥንቱ የባቢሎን ግዛት አከተመ።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳንኤል በባቢሎን ግዛት ላይ የሚመጣውን የጥፋት መልእክት ተርጉሟል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ