የይሖዋን ፈቃድ ፈጽመዋል
ኢየሱስ ከልጆች ጋር ጊዜ አሳለፈ
የኢየሱስ የሦስት ዓመት ተኩል አገልግሎት ወደ ማለቂያው ተቃርቧል። በቅርቡ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድና በዚያም ስቃይና ሞት ይጠብቀዋል። ለደቀ መዛሙርቱ “የሰው ልጅ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጣል፣ ይገድሉትማል” ብሎ ነግሯቸው ስለነበር ከፊቱ የሚጠብቀውን አሳምሮ ያውቃል።—ማርቆስ 9:31
ኢየሱስ የቀረችውን እያንዳንዷን ቀን፣ ሰዓትና ደቂቃ በአግባቡ ሊጠቀምባት እንደሚፈልግ የታወቀ ነው። ደቀ መዛሙርቱ አሁንም እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ኢየሱስ የትሕትናን አስፈላጊነትና ከፊታቸው ያለውን የመሰናከል አደጋ በተመለከተ በድጋሚ ጠንከር ያለ ምክር እንደሚያስፈልጋቸው ተገንዝቧል። (ማርቆስ 9:35–37, 42–48) ከዚህም በተጨማሪ ጋብቻን፣ ፍቺንና ነጠላነትን በተመለከተ መመሪያ ያስፈልጋቸዋል። (ማቴዎስ 19:3–12) ኢየሱስ በቅርቡ እንደሚገደል ስለሚያውቅ አስፈላጊ የሆነውን ነገር አጠር አድርጎና በጥድፊያ ስሜት ለደቀ መዛሙርቱ እንደነገራቸው ምንም ጥርጥር የለውም። የጊዜ ጉዳይ አንገብጋቢ ነበር። የወቅቱ ሁኔታ ይህ በመሆኑ ኢየሱስ ቀጥሎ ያደረገው ነገር ከፍተኛ ቁም ነገር ነበረው ማለት ነው።
ኢየሱስ ልጆችን እጁን ዘርግቶ ተቀበላቸው
የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ “እንዲዳስሳቸውም ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ” ይላል። ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሲመለከቱ ወዲያውኑ ተቃውሞ አሰሙ። ኢየሱስ በጣም ትልቅ ሰው ስለሆነ ወይም ጊዜው በጣም የተጣበበ በመሆኑ ስለ ልጆች ግድ አይኖረውም ብለው አስበው ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ በእነሱ ላይ ሲቆጣ ደቀ መዛሙርቱ ምን ያህል እንደተገረሙ ገምት! “ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉ አትከልክሉአቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ናትና” ሲል ነገራቸው። በመቀጠልም ኢየሱስ እንዲህ ሲል ተናገረ:- “እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም።”—ማርቆስ 10:13–15
ኢየሱስ ልጆች አስደናቂ ባሕርያት እንዳሏቸው ተመልክቷል። ልጆች መጠያየቅ ይወዳሉ፤ የተነገራቸውን ያምናሉ። ወላጆቻቸው የሚነግሯቸውን ይቀበላሉ፤ እንዲሁም በሌሎች ልጆች ፊት ስለ እነሱ ይከራከራሉ። የአምላክን መንግሥት ለመውረስ የሚፈልጉ ሁሉ እሺ ባይና ገራም ባሕሪያቸውን ሊኮርጁ ይገባል። ኢየሱስ እንደተናገረው “የእግዚአብሔር መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ናት።”—ከማቴዎስ 18:1–5 ጋር አወዳድር።
ይሁን እንጂ ኢየሱስ ልጆችን ወደ እርሱ ያቀረበው ምሳሌ ለመናገር እንዲጠቀምባቸው ብሎ አይደለም። ኢየሱስ ከእነሱ ጋር መሆን ከልብ ያስደስተው እንደነበር ዘገባው ግልጽ ያደርገዋል። ማርቆስ፣ ኢየሱስ “አቀፋቸውም እጁንም ጭኖ ባረካቸው” በማለት ጽፏል። (ማርቆስ 10:16) ኢየሱስ ልጆቹን ‘እንዳቀፋቸው’ የሚናገረውን ፍቅራዊ መግለጫ ያከለው የማርቆስ ዘገባ ብቻ ነው።a ይህም በመሆኑ ኢየሱስ ልጆቻቸውን “እንዲዳስሳቸው” ብቻ ብለው ያመጧቸው ወላጆች ከጠበቁት በላይ አድርጓል።
ኢየሱስ በልጆቹ ላይ ‘እጁን መጫኑ’ ምን ትርጉም ነበረው? እዚህ ላይ እንደ ጥምቀት ያለ አንድ ዓይነት ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት መካሄዱን አያመለክትም። ምንም እንኳ በአንዳንድ ሁኔታዎች እጅ መጫን ሹመት መስጠትን ቢያመለክትም በሌሎች ሁኔታዎች ደግሞ መባረክን ብቻ ያመለክታል። (ዘፍጥረት 48:14፤ ሥራ 6:6) ይህም በመሆኑ ኢየሱስ እጁን ሲጭንባቸው ልጆቹን መባረኩ ብቻ ሊሆን ይችላል።
ያም ሆነ ይህ ማርቆስ አጽንኦት ለመስጠት “ባረካቸው” (ካቲዮሎጂኦ) የሚለውን ጠንከር ያለ ቃል ተጠቅሟል። ይህ አባባል ኢየሱስ እነዚህን ልጆች ከልብ በመነጨ ፍቅራዊ ስሜት መባረኩን ይጠቁማል። ከዚህ በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ልጆችን ጊዜውን የሚሻሙበት ሸክም አድርጎ አልተመለከታቸውም።
ለእኛ የሚሆን ትምህርት
ኢየሱስ ከልጆችም ሆነ ከአዋቂዎች ጋር የነበረው ግንኙነት የሚያሸማቅቅ ወይም ዝቅ የሚያደርግ አልነበረም። አንድ የማጣቀሻ ጽሑፍ እንዳለው “በቀላሉ ፈካ ብሎና በደስታ ስሜት ስቆ መሆን አለበት።” በተለያየ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች ከእርሱ ጋር ሲሆኑ አለመሸማቀቃቸው ምንም አያስገርምም። ኢየሱስ በተወልን ምሳሌ ላይ ስናሰላስል ‘ሌሎች የምቀረብ ሆኜ ያገኙኛል?’ ‘ሌሎች ስለሚያከናውኑት ሥራና ስለሚያሳስቧቸው ጉዳዮች ደንታ ቢስ እስክሆን ድረስ በራሴ ጉዳዮች የተጠመድኩ ነኝ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን። ለሰዎች ልባዊ ትኩረት የመስጠትን ዝንባሌ መኮትኮታችን ኢየሱስ እንዳደረገው ሌሎችን ለመርዳት ያነሳሳናል። ሌሎች የምናሳያቸውን ልባዊ ትኩረት በመገንዘብ ወደ እኛ ይሳባሉ።—ምሳሌ 11:25
የማርቆስ ዘገባ እንደሚያሳየው ኢየሱስ ከልጆች ጋር መሆን ያስደስተው ነበር። ከምሳሌዎቹ በአንዱ ላይ ስለ እነሱ ጨዋታ ጠቅሶ ስለተናገረ ጊዜ ወስዶ ሲጫወቱ ተመልክቷቸው መሆን አለበት። (ማቴዎስ 11:16–19) ምናልባትም ኢየሱስ ከባረካቸው ልጆች መካከል አንዳንዶቹ በዕድሜ ትንንሽ ከመሆናቸው የተነሳ የእሱን ማንነትና ያስተማራቸውን ነገሮች አልተገነዘቡ ይሆናል። ሆኖም እንዲህ መሆኑ ጊዜውን እንዳባከነ ሆኖ እንዲሰማው አላደረገም። ልጆችን ይወድ ስለነበር ጊዜ ወስዶ ያነጋግራቸው ነበር። ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት አግኝቶ ያነጋገራቸው ብዙ ልጆች ከጊዜ በኋላ የእሱ ደቀ መዛሙርት በመሆን ላሳያቸው ፍቅር ምላሽ ሳይሰጡ አይቀርም።
ኢየሱስ ወሳኝ በሆኑት የሕይወቱ የመጨረሻ ሳምንታት ከልጆች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ከቻለ እኛም ፕሮግራማችን የተጣበበ ቢሆን እንኳ ከእነሱ ጋር የምናሳልፈው ጊዜ ማግኘት እንደምንችል የተረጋገጠ ነው። አባት የሌላቸው ልጆች ለመሳሰሉ ለየት ያለ ችግር ላለባቸው ይበልጥ ትኩረት መስጠት አለብን። በእርግጥም ሁሉም ልጆች ትኩረት ሲሰጣቸው በስሜትና በመንፈስ ቶሎ ያድጋሉ። ይሖዋ የቻልነውን ያህል ፍቅርና ድጋፍ እንድንሰጣቸው ይፈልጋል።—መዝሙር 10:14
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “በክንዱ ተሸከማቸው” ይላል።