ከንጉሠ ነገሥት አምልኮ ወደ እውነተኛው አምልኮ
ኢሳሙ ሱጊውራ እንደተናገረው
ምንም እንኳ ጃፓን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት እየተሸነፈች እንዳለች በ1945 ግልጽ እየሆነ ቢመጣም እኛ ግን ካሚካዚ (“መለኮታዊ ነፋስ”) እንደሚነፍስና ጠላትን ድል እንደሚነሣልን እርግጠኞች ነበርን። ካሚካዚ የሚለው ቃል በጃፓን ጠረፍ ላይ ሰፍሮ የነበረውን አብዛኛውን ወራሪ የሞንጎልያ የባሕር ኃይል ሠራዊት ሁለት ጊዜ ጠራርጎ ያጠፋውንና አካባቢውን ለቅቆ እንዲሄዱ ያስገደደውን በ1274 እና በ1281 ተከስቶ የነበረውን ማዕበል የሚያመለክት ነው።
በመሆኑም ንጉሠ ነገሥት ሂሮሂቶ በነሐሴ 15, 1945 ጃፓን ለኅብረ ብሔሩ ኃይል እጅ መስጠቷን ሲያስታውቁ ለእሳቸው ያደሩ የነበሩ አንድ መቶ ሚልዮን ሰዎች ተስፋቸው ሁሉ ጨለመ። ያኔ ገና ተማሪ ብሆንም እንደ ሌሎቹ ሁሉ የእኔም ተስፋ ጨልሞ ነበር። ‘ሕያው አምላክ ንጉሠ ነገሥቱ ካልሆኑ ታዲያ ማን ሊሆን ይችላል?’ እያልኩ አስብ ነበር። ‘መታመን ያለብኝ በማን ነው?’
እርግጥ ጃፓን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መሸነፏ እኔም ሆንኩ በሺህ የሚቆጠሩ ሌሎች ጃፓናውያን ስለ እውነተኛው አምላክ ስለ ይሖዋ እንድንማር መንገድ ከፍቶልናል። ማድረግ ስለነበሩብኝ ለውጦች ከመተረኬ በፊት ስለ ሃይማኖታዊ አስተዳደጌ ጥቂት ልንገራችሁ።
ቀደምት ሃይማኖታዊ ተጽእኖዎች
የተወለድኩት በናጎያ ከተማ ሰኔ 16, 1932 ሲሆን ከአራት ወንድ ልጆች መካከል እኔ የመጨረሻ ልጅ ነኝ። አባቴ የከተማው ቀያሽ ሆኖ ይሠራ ነበር። እናቴ ቴንሪኪዮ የሚባል የሺንቶ ሃይማኖት ቡድን አጥባቂ ተከታይ ነበረች፤ ታላቅ ወንድሜ ደግሞ የቴንሪኪዮ አስተማሪ ለመሆን የሚያስችለውን ሃይማኖታዊ ሥልጠና ተከታትሏል። በተለይ እኔና እናቴ በጣም እንቀራረብ ስለነበረ ለአምልኮ ወደሚሰበሰቡበት ቦታ ትወስደኝ ነበር።
ራሴን ጎንበስ አድርጌ መጸለይ እንዳለብኝ ተምሬ ነበር። የቴንሪኪዮ ሃይማኖት ቴንሪ ኦ ኖ ሚኮቶ በሚባል ፈጣሪና በሌሎች አሥር ትናንሽ አማልክት ማመንን ያስተምራል። አባላቶቹ የእምነት ፈውስ ያከናውኑ የነበረ ሲሆን ሌሎችን መርዳትና እምነታቸውን ማስፋፋት ጉልህ ሥፍራ የሚሰጧቸው ነገሮች ነበሩ።
ልጅ እንደ መሆኔ መጠን ሁሉን ነገር የማወቅ ጉጉት ነበረኝ። በምሽት ሰማይ ላይ የሚታዩት ጨረቃና ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ከዋክብት ያስደንቁኝ ነበር፤ እንዲሁም ጠፈር ከሰማይ ምን ያህል ርቆ እንደሚገኝ አስብ ነበር። በጓሯችን በሚገኝ አነስተኛ ቦታ ላይ የተከልኳቸው ደበርጃን እና ኪያር ሲበቅሉ ማየት እጅግ ያስደስተኝ ነበር። ተፈጥሮን መመልከት በአምላክ ላይ ያለኝን እምነት አጠንክሮልኛል።
የጦርነቱ ዓመታት
በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያሳለፍኳቸው ከ1939 እስከ 1945 ያሉት ዓመታት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተካሄደባቸው ዓመታት ነበሩ። ንጉሠ ነገሥቱን ማምለክ የሺንቶ ሃይማኖት አቢይ ክፍል ሲሆን በትምህርት ቤት በሚሰጠን ትምህርት ውስጥ ጠበቅ ተደርጎ ይገለጽ ነበር። ብሔራዊና ወታደራዊ ስሜት የሚንጸባረቅበት የግብረገብ ሥልጠናን የሚያካትት ሹሺን የሚባል ትምህርት ይሰጠን ነበር። ባንዲራ የመስቀል ሥነ ሥርዓቶች፣ ብሔራዊ መዝሙር መዘመር፣ ንጉሠ ነገሥታዊ የትምህርት ድንጋጌዎችን ማጥናትና የንጉሠ ነገሥቱን ፎቶ ግራፍ መሳለም በትምህርት ቤት የምናከናውናቸው የተለመዱ ተግባራት ነበሩ።
በተጨማሪም በአካባቢው ወደሚገኘው የሺንቶ ቤተ መቅደስ በመሄድ ንጉሣዊው ሠራዊት ድል እንዲቀዳጅ አምላክን እንለምን ነበር። ሁለቱ ወንድሞቼ በሠራዊቱ ውስጥ ያገለግሉ ነበር። በትምህርት ቤት በተማርኩት ብሔራዊ ስሜት በሚንጸባረቅበት ሃይማኖታዊ ትምህርት ምክንያት የጃፓን ሠራዊት ስላገኘው ስኬት ስሰማ እደሰት ነበር።
ናጎያ የጃፓን የአውሮፕላን ኢንዱስትሪ ማዕከል በመሆኗ ለዩናይትድ ስቴትስ አየር ኃይል ከባድ ድብደባ ዋነኛ ዒላማ ነበረች። በቀኑ ክፍለ ጊዜ ቢ-29 የሚባሉት እጅግ ግዙፍ የሆኑ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች በ9,000 ሜትር ከፍታ በከተማዋ ላይ በሰልፍ በመብረር ፋብሪካ በሚገኝባቸው አካባቢዎች ቦምቦችን ያዘንቡ ነበር። ምሽት ላይ እነዚህ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች እስከ 1,300 ሜትር ዝቅ ብለው ሲበሩ በባውዛ መብራቶች መመልከት ይቻል ነበር። ተደጋጋሚ የአየር ድብደባዎች ተቀጣጣይ ከሆኑ ቦምቦች ጋር ተዳምረው የመኖሪያ አካባቢዎችን በእሳት አጋዩአቸው። ጦርነቱ ከተጀመረ ከዘጠኝ ወራት ወዲህ በናጎያ ብቻ 54 የአየር ድብደባዎች የተደረጉ ሲሆን ለብዙ ሥቃይና ከ7,700 ለሚበልጡ ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆነዋል።
በዚህ ጊዜ ደግሞ የጦር መርከቦች በባሕር ጠረፍ ላይ የሚገኙ አሥር ከተሞችን በቦምብ መደብደብ ጀምረው ነበር፤ የዩናይትድ ስቴትስ ኃይሎች በቶክዮ አቅራቢያ ሊሰፍሩ ይችላሉ የሚል ወሬ በሰዎች ዘንድ እየተናፈሰ ነበር። ሴቶችና ወጣት ወንዶች አገሪቱን እንዲጠብቁ ከቀርቀሃ በሚሠራ ጦር እንዴት መዋጋት እንደሚችሉ ሥልጠና ይሰጣቸው ነበር። መፈክራችን “ኢቺዮኩ ሶጊዮኩሳይ” የሚል ሲሆን “እጅ ከመስጠት ይልቅ 100 ሚልዮን ሰዎች ቢያልቁ ይሻላል” የሚል ትርጉም አለው።
ነሐሴ 7, 1945 አንድ ጋዜጣ “አዲስ ዓይነት ቦምብ በሂሮሺማ ላይ ተጣለ” የሚል ርዕሰ ዜና ይዞ ወጣ። ከሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ ሌላ ተመሳሳይ ቦምብ በናጋሳኪ ላይ ተጣለ። እነዚህ የአቶም ቦምቦች ሲሆኑ ከጊዜ በኋላ እንደሰማነው ደግሞ ቦምቦቹ በአጠቃላይ ከ300,000 የሚበልጡ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፈዋል። ከዚያም ነሐሴ 15 ከእንጨት በተሠሩ ጠመንጃዎች የሚሰጠውን የሰልፍ ስልጠና ስናጠናቅቅ ጃፓን እጅ መስጠቷን ያስታወቁበትን የንጉሠ ነገሥቱን ንግግር አዳመጥን። ድል እናደርጋለን የሚል ጠንካራ እምነት የነበረን በመሆኑ መሸነፋችንን ስንሰማ እጅግ አዘንን!
አዲስ ተስፋ ለመለመ
የአሜሪካ ሠራዊት አገሪቱን መቆጣጠር ሲጀምር ዩናይትድ ስቴትስ በጦርነቱ ማሸነፏን ቀስ በቀስ አምነን ተቀበልን። በጃፓን ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ከመደረጉም በላይ የአምልኮ ነፃነትን የሚፈቅድ አዲስ ሕገ መንግሥት ተረቅቆ ወጣ። የኑሮው ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነበር፤ የምግብ እጥረት ነበር፤ አባቴ በተመጣጠነ ምግብ እጦት በ1946 ሞተ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በምማርበት ትምህርት ቤት ውስጥ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት መሰጠት ተጀመረ፤ እንዲሁም ኤን ኤች ኬ በሚል ምህጻረ ቃል የሚታወቀው የሬዲዮ ጣቢያ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ንግግር ፕሮግራም ማቅረብ ጀመረ። ይህን ተወዳጅ ፕሮግራም የመማሪያ መጽሐፍ በእጄ ይዤ ለአምስት ዓመታት ያህል በየቀኑ ተከታትያለሁ። ይህ ደግሞ አንድ ቀን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እሄዳለሁ የሚል ፍላጎት በውስጤ እንዲያድር አደረገ። በሺንቶና በቡዲስት ሃይማኖቶች ስለተበሳጨሁ ስለ አምላክ የሚናገረው እውነት ምናልባት በምዕራባውያን ሃይማኖቶች ውስጥ ይገኝ ይሆናል ብዬ ማሰብ ጀመርኩ።
በ1951 በሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ሚስዮናዊ ከሆነችው ከግሬስ ግሪጎሪ ጋር ተገናኘሁ። በናጎያ ባቡር ጣቢያ ፊት ለፊት ቆማ በእንግሊዝኛ የታተመ የመጠበቂያ ግንብ ቅጂና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕስ ያለው አንድ በጃፓንኛ የተጻፈ ቡክሌት ታበረክት ነበር። እንዲህ ያለውን ሥራ ለመሥራት ባሳየችው ትሕትና ስሜቴ ተነካ። ሁለቱንም ጽሑፎች ወሰድኩና መጽሐፍ ቅዱስ እንዳጠና ያቀረበችልኝን ግብዣ ምንም ሳላቅማማ ተቀበልሁ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግ ከጥቂት ቀናት በኋላ ወደ ቤቷ ለመምጣት ቃል ገባሁ።
ባቡር ተሳፍሬ ወንበር ከያዝኩ በኋላ መጠበቂያ ግንቡን ማንበብ እንደጀመርሁ በመግቢያው ርዕስ ላይ የሚገኘው “ይሖዋ” የሚለው የመጀመሪያ ቃል ቀልቤን ሳበው። ይህን ስም ከዚህ በፊት በፍጹም አይቼው አላውቅም። በያዝኳት ትንሽ እንግሊዝኛ-ጃፓንኛ መዝገበ ቃላት ውስጥ ቃሉ ይገኛል ብዬ አልጠበቅኩም ነበር፤ ሆኖም ቃሉን በያዝኳት መዝገበ ቃላት ውስጥ አገኘሁት! “ይሖዋ . . . በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው አምላክ።” አሁን የክርስትና እምነት አምላክ ስለሆነው ማወቅ ጀመርኩ!
የሚስዮናውያኑን ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ስጎበኝ በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ናታን ኤች ኖር ከጥቂት ሳምንታት በኋላ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር የሚያቀርብ መሆኑን አወቅሁ። ከጸሐፊው ከሚልተን ሄንሼል ጋር በመሆን ጃፓንን በመጎብኘት ላይ የነበረ ሲሆን ወደ ናጎያም ይመጣ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቴ ውስን የነበረ ቢሆንም በንግግሩ እንዲሁም ከሚስዮናውያንና ከሌሎች ተሰብሳቢዎች ጋር በመተዋወቄ በጣም ተደስቼ ነበር።
በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ከግሬስ ጋር ባረግሁት ጥናት ስለ ይሖዋ፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ስለ ቤዛው፣ ስለ ሰይጣን ዲያብሎስ፣ ስለ አርማጌዶንና ስለ ገነቲቱ ምድር የሚናገረውን መሠረታዊ እውነት ተማርሁ። የመንግሥቱ ምሥራች በትክክል እኔ ስፈልገው የነበረው ዓይነት መልእክት ነው። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት የጀመርኩት ማጥናት እንደጀመርኩ ነበር። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ የሚታየው ወዳጃዊ ስሜት ያስደስተኝ ነበረ፤ ሚስዮናውያኑ ከጃፓናውያኑ ጋር በነፃነት ተቀላቅለው በታታሚ (ከደረቅ ሣር በተሠራ ምንጣፍ) ላይ አብረውን ይቀመጡ ነበር።
በጥቅምት 1951 በጃፓን የተደረገው የመጀመሪያው የወረዳ ስብሰባ በኦሳካ ከተማ በናካኖሺማ የሕዝብ አዳራሽ ተካሄደ። በመላው ጃፓን ከ300 የሚያንሱ ምሥክሮች ይገኙ የነበረ ቢሆንም ወደ 50 የሚጠጉ ሚስዮናውያንን ጨምሮ 300 የሚሆኑ ሰዎች በስብሰባው ላይ ተገኙ። እንዲያውም እኔ በፕሮግራሙ ላይ አንድ አጭር ክፍል ነበረኝ። ባየሁትና በሰማሁት ነገር ልቤ በጣም ተነክቶ ስለነበር ይሖዋን በሕይወት ዘመኔ በሙሉ ለማገልገል በልቤ ወሰንኩ። በሚቀጥለው ቀን በአቅራቢያው በሚገኝ ሙቅ ውኃ ባለው የሕዝብ መታጠቢያ ቤት ውስጥ ተጠመቅሁ።
በአቅኚነት አገልግሎት ያገኘሁት ደስታ
የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ማለትም አቅኚ የመሆን ፍላጎት የነበረኝ ቢሆንም ቤተሰቤን የመርዳት ግዴታም እንዳለብኝ ሆኖ ይሰማኝ ነበር። እንደምንም ደፍሬ ለአለቃዬ ፍላጎቴን ስነግረው “አንተን የሚያስደስትህ ከሆነ ልተባበርህ ፈቃደኛ ነኝ” ሲለኝ ተገረምኩ። በሳምንት ሁለት ቀን ብቻ እየሠራሁ እናቴን በቤት ወጪዎቿ ለመደጎም ችዬ ነበር። ልክ ከወጥመድ ነፃ እንደተለቀቀች ወፍ ነበር የሆንኩት።
ሁኔታዎች እየተሻሻሉ ሲመጡ በነሐሴ 1, 1954 አቅኚ በመሆን ከናጎያ ባቡር ጣቢያ በስተ ጀርባ፣ ከግሬስ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ከተገናኘሁበት ቦታ የጥቂት ደቂቃዎች ርቀት ላይ በሚገኝ ክልል ማገልገል ጀመርኩ። ከበርካታ ወራት በኋላ በኪዩሹ ምዕራባዊ ደሴት ላይ በምትገኝ ቤፑ በምትባል ከተማ ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ። ጹቶሙ ሚኡራ አብሮኝ እንዲያገለግል ተመድቦ ነበር።a በዚያን ወቅት በመላው ደሴት ላይ አንድም የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ አልነበረም። አሁን ግን በ22 ወረዳዎች የተከፋፈሉ በመቶ የሚቆጠሩ ጉባኤዎች ይገኛሉ!
የአዲሱ ዓለም ቅምሻ
ወንድም ኖር በሚያዝያ 1956 ጃፓንን በድጋሚ በጎበኘ ጊዜ ከእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ጥቂት አንቀጾችን ጮክ ብዬ እንዳነብብ ጠየቀኝ። ለምን እንዳነብብ እንደጠየቀኝ አልነገረኝም፤ ሆኖም ከጥቂት ወራት በኋላ በጊልያድ የሚስዮናውያን ትምህርት ቤት 29ኛውን ክፍል እንድከታተል የሚጋብዝ ደብዳቤ ደረሰኝ። ስለዚህ በዚያው ዓመት ኅዳር ላይ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የመሄድ የረጅም ጊዜ ሕልሜን እውን የሚያደርግ አስደሳች ጉዞ ጀመርኩ። ሰፊ ከሆነው የብሩክሊን ቤቴል ቤተሰብ ጋር ለሁለት ወራት ያህል መቆየቴና መሥራቴ በሚታየው የይሖዋ ድርጅት ላይ ያለኝን እምነት አጠንክሮልኛል።
የካቲት 1957 ወንድም ኖር ሦስት ተማሪዎችን በኒው ዮርክ ሰሜናዊ ክልል በሳውዝ ላንሲንግ ወደሚገኘው የጊልያድ ትምህርት ቤት በመኪና ወሰደን። በጊልያድ ትምህርት ቤት ቆይታ ባደረግሁባቸው በቀጣዮቹ አምስት ወራት ውስጥ ከይሖዋ ቃል በመማርና ከመሰል ተማሪዎች ጋር ደስ በሚሉ ቦታዎች በመኖር ያሳለፍኩት ጊዜ የምድራዊቷ ገነት ቅምሻ ነበር። ከ103 ተማሪዎች መካከል እኔን ጨምሮ አሥር የምንሆነው በጃፓን እንድናገለግል ተመደብን።
የአገልግሎት ምድቦቼን ማድነቅ
ጥቅምት 1957 ወደ ጃፓን ስመለስ በዚያ የነበሩት ምሥክሮች ብዛት ወደ 860 ይጠጋ ነበር። የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ በተጓዥነት ሥራ እንዳገለግል ተመደብኩ፤ ከዚያ በፊት ግን ለጥቂት ቀናት በናጎያ ከአድሪያን ቶምሰን ለሥራው የሚያስፈልገውን ሥልጠና ወሰድኩ። የእኔ ወረዳ ከፉጂ ተራራ አቅራቢያ ከሚገኘው ከሺሚዙ አንስቶ እስከ ሺኮኩ ደሴት የሚገኘውን ቦታ የሚሸፍንና እንደ ኪዮቶ፣ ኦሳካ፣ ኮቤና ሂሮሺማ የመሳሰሉ ትላልቅ ከተሞችን የሚያጠቃልል ነበር።
በ1961 የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ። ይህ ደግሞ ከበረዷማው የሆካይዶ ደሴት ሰሜናዊ ክፍል አንስቶ ከፊል ሞቃታማ ወደሆነው የኦኪናዋ ደሴት የሚደርስና በታይዋን አቅራቢያ ወደሚገኙት ወደ ኢሺጋኪ ደሴቶች ሳይቀር አልፎ የሚሄድ ወደ 3,000 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ርቀት የሚሸፍን ነበር።
ከዚያም በ1963 በብሩክሊን ቤቴል በሚገኘው የጊልያድ ትምህርት ቤት አሥር ወራት የሚፈጅ ስልጠና እንድወስድ ተጋበዝኩ። ኮርሱ በሚሰጥበት ጊዜ ወንድም ኖር ለተሰጠን የሥራ ምድብ ተገቢ አመለካከት ሊኖረን እንደሚገባ ጠበቅ አድርጎ ገልጾ ነበር። መጸዳጃ ቤት ማጽዳትም ሆነ ቢሮ ውስጥ መሥራት እኩል ተፈላጊ እንደሆነ ገልጾ ነበር። የመጸዳጃ ቤቶቹ ንጹህ ባይሆኑ ኖሮ መላው የቤቴል ቤተሰብና የሚሠሩት ሥራ ይጎዳ ነበር ብሏል። ከጊዜ በኋላ ጃፓን በሚገኘው ቤቴል ከነበረኝ ሥራ አንዱ የመጸዳጃ ቤቶችን ማጽዳት ስለነበር ይህን ምክር አስታውሳለሁ።
ወደ ጃፓን ከተመለስኩ በኋላ እንደገና የተጓዥነት ሥራ እንድሠራ ተመደብኩ። ከሁለት ዓመታት በኋላ በ1966 በማትሱዌ ከተማ ልዩ አቅኚ ሆና ታገለግል የነበረችውን ጁንኮ ኢዋሳኪን አገባሁ። በወቅቱ የጃፓን ቅርንጫፍ የበላይ ተመልካች የነበረው ሎይድ ባሪ አስደሳች የጋብቻ ንግግር አደረገልን። ከዚያም ጁንኮ አብራኝ የተጓዥነት ሥራ መሥራት ጀመረች።
በ1968 ቶኪዮ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የትርጉም ሥራ እንድሠራ በመጠራቴ የሥራ ምድባችን ተቀየረ። የመኖሪያ ክፍሎች እጥረት ስለነበረ ከቶኪዮ ሱሚዳ ሰፈር እየተመላለስኩ እሠራ የነበረ ሲሆን ጁንኮ ደግሞ በአካባቢው በሚገኘው ጉባኤ ልዩ አቅኚ ሆና ታገለግል ነበር። በዚህ ጊዜ ሰፊ የሆኑ የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃዎች ያስፈልጉ ነበር። ስለዚህ በ1970 በኑማዙ፣ ከፉጂ ተራራ ብዙም በማይርቅ ቦታ ላይ የሚገኝ መሬት ተገዛ። በዚያም ለፋብሪካና ለመኖሪያነት የሚያገለግል ባለ ሦስት ፎቅ ሕንፃ ተሠራ። ግንባታው ከመጀመሩ በፊት በቦታው ላይ የሚገኙ በርካታ ቤቶች ለጉባኤ የበላይ ተመልካቾች ሥልጠና የሚሰጥባቸው የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ሆነው አገልግለዋል። በዚህ ትምህርት ቤት የማስተማር መብት አግኝቼ የነበረ ሲሆን ጁንኮ ደግሞ ለተማሪዎቹ ምግብ ታዘጋጅ ነበር። በመቶ ለሚቆጠሩ ክርስቲያን ወንዶች ለአገልግሎቱ የሚሆን ልዩ ሥልጠና ሲሰጥ መመልከቱ እጅግ የሚያስደስት ነበር።
አንድ ቀን ከቀትር በኋላ አንድ አስቸኳይ ቴሌግራም ደረሰኝ። እናቴ ሆስፒታል ገብታ የነበረ ሲሆን በሕይወት መቀጠሏም አጠራጣሪ ነበር። ወደ ናጎያ በሚሄድ ፈጣን ባቡር ተሳፍሬ ሆስፒታሉ ደረስኩ። እናቴ ምንም አትሰማም ነበር፤ ሆኖም በአልጋዋ አጠገብ ሆኜ ሌሊቱን አሳለፍኩ። እናቴ ሊነጋጋ ሲል ሞተች። ወደ ኑማዙ በመመለስ ላይ እያለሁ እናቴ በሕይወቷ ውስጥ ያሳለፈችውን ችግርና ለእኔ የነበራትን ፍቅር ሳስብ እምባዬን መቆጣጠር ተስኖኝ ነበር። የይሖዋ ፈቃድ ከሆነ በትንሣኤ እንደገና አገኛት ይሆናል።
ቁጥራችን በመጨመሩ በኑማዙ የነበረው ሕንፃ ሊበቃን አልቻለም። ስለዚህ በኢቢና ከተማ 7 ሄክታር የሚሆን መሬት ተገዛና በ1978 አዲስ የቅርንጫፍ ሕንፃዎች ግንባታ ተጀመረ። በአሁኑ ጊዜ በዚህ መሬት ላይ የሚገኘው ክፍት ቦታ በሙሉ ለፋብሪካና ለመኖሪያነት የሚያገለግሉ ሕንፃዎችና ከ2,800 ሰዎች በላይ ማስቀመጥ የሚችል አንድ የትልቅ ስብሰባ አዳራሽ ተሠርቶባቸዋል። በቅርቡ የተጨመሩት ሁለት ባለ 13 ፎቅ የመኖሪያ ሕንፃዎች እንዲሁም ባለ 5 ፎቅ የመኪና ማቆሚያና የጥገና አገልግሎት መስጪያ ሕንፃ በዚህ ዓመት መግቢያ ላይ ተሠርተው ተጠናቅቀዋል። የቤቴል ቤተሰባችን በአሁኑ ጊዜ ወደ 530 የሚጠጋ ቢሆንም እነዚህ ሰፋፊ ሕንፃዎች 900 የሚሆኑ ሰዎችን ማስተናገድ ይችላሉ።
ለደስታ የሚሆኑ ብዙ ምክንያቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ሲፈጸም፣ አዎን፣ ‘የሁሉም ታናሽ ብርቱ ሕዝብ ሲሆን’ መመልከት እጅግ የሚያስደስት ነው። (ኢሳይያስ 60:22) በ1951 ከወንድሞቼ አንዱ “በጃፓን ውስጥ ስንት የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ?” ብሎ እንደጠየቀኝ አስታውሳለሁ።
“ወደ 260 ይጠጋሉ” ብዬ መለስኩለት።
“በቃ እነዚህ ብቻ ናቸው?” በማለት በሚያንኳስስ የድምፅ ቃና ጠየቀኝ።
‘በዚህች የሺንቶ-ቡድሃ አገር ይሖዋ ምን ያህል ሰዎችን ወደ አምልኮ ቤቱ እንደሚሰበስብ ጊዜ ያሳያል’ ብዬ እንዳሰብኩ ትዝ ይለኛል። ይሖዋም መልሱን ሰጥቷል! ዛሬ በጃፓን ውስጥ በስብከቱ ሥራ ያልተሸፈነ አንድም የአገልግሎት ክልል አይገኝም፤ እንዲሁም የእውነተኛ አምላኪዎች ቁጥር አድጎ በ3,800 ጉባኤዎች ውስጥ ከ222,000 በላይ ደርሷል!
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፍኳቸው ያለፉት 44 ዓመታት በጣም የሚያስደስቱ ነበሩ። ከእነዚህም ውስጥ 32ቱን ዓመታት ያሳለፍኩት ከውዷ ባለቤቴ ጋር ነው። በቤቴል ውስጥ በትርጉም ክፍል ለ25 ዓመታት አገልግያለሁ። በተጨማሪም በመስከረም 1979 በጃፓን የይሖዋ ምሥክሮች የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል እንድሆን ግብዣ ቀርቦልኛል።
ቅን ልብ ያላቸውንና ሰላም ወዳድ የሆኑ ሰዎችን ወደ ይሖዋ አምልኮ እንዲመጡ በመርዳቱ ሥራ አነስተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ መብትም በረከትም ነው። ብዙዎች እኔ እንዳደረግሁት ለንጉሠ ነገሥቱ ማደርን ትተው ብቸኛውን እውነተኛ አምላክ ይሖዋን ማምለክ ጀምረዋል። አሁንም ቢሆን ብዙ ሰዎች ከድል አድራጊው ከይሖዋ ጎን እንዲሰለፉና ሰላም በሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ውስጥ ፍጻሜ የሌለው ሕይወት እንዲያገኙ የመርዳት ልባዊ ምኞት አለኝ።—ራእይ 22:17
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አባቱ በአንድ የጃፓን እስር ቤት ውስጥ ሆኖ በ1945 በሂሮሺማ ላይ ከፈነዳው የአቶም ቦምብ በሕይወት የተረፈ የታመነ ምሥክር ነው። የጥቅምት 8, 1994 ንቁ! ገጽ 11–15 ተመልከት።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በትምህርት ቤት የሚሰጠን ትምህርት በንጉሠ ነገሥት አምልኮ ላይ ያተኮረ ነበር
[ምንጭ]
The Mainichi Newspapers
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኒው ዮርክ ከወንድም ፍራንዝ ጋር
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባለቤቴ ከጁንኮ ጋር
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በትርጉም ክፍል በሥራ ላይ እያለሁ