የኢየሱስ ልደት እውነተኛው ታሪክ
በአገርህ ታሪክ ውስጥ በሰፊው ስለሚታወቅ አንድ ታላቅ ክንውን እስቲ አስብ። ይህ ክንውን ከአንድ በላይ በሆኑ ታሪክ ጸሐፊያን በሚገባ ተመዝግቦ ይገኛል። ሆኖም አንድ ሰው ይህ ክንውን ፈጽሞ እንዳልተፈጸመና እንዲያው ዝም ብሎ አፈ ታሪክ እንደሆነ ቢነግርህስ? እንዲያውም ነገሩን ይበልጥ ወደ ራስህ እናምጣውና አንድ ሰው ቤተሰቦችህ ስለ አያትህ ልደትና የቀድሞ ሕይወት የነገሩህ አብዛኛው ነገር ውሸት መሆኑን ቢነግርህስ? ይህን የነገረህ ሰው እንዲህ ብሎ ማሰቡ ራሱ ያናድድህ ይሆናል። መቼም እንዲህ ዓይነቱን አባባል እንዲሁ በደፈናው አምነህ እንደማትቀበለው የተረጋገጠ ነው!
ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ ያሉ ተቺዎች በማቴዎስና በሉቃስ ተመዝግበው የሚገኙትን ስለ ኢየሱስ ልደት የሚናገሩትን የወንጌል ዘገባዎች በአጠቃላይ አይቀበሉም። እነዚህ ዘገባዎች ፈጽሞ እንደሚቃረኑና ሊጣጣሙ እንደማይችሉ እንዲሁም ሁለቱም ዘገባዎች ፈጽሞ ከእውነት የራቁ የታሪክ ግድፈቶች መያዛቸውን ይናገራሉ። ይህ እውነት ሊሆን ይችላል? እንዲህ ዓይነት ትችቶችን ከመቀበል ይልቅ የወንጌል ዘገባዎችን እስቲ እኛ ራሳችን እንመርምራቸው። በምንመረምርበት ጊዜ ዛሬ ዘገባዎቹ ለእኛ የሚሆን ምን ትምህርት እንደያዙ እንመልከት።
ለመጻፍ የተነሳሱበት ዓላማ
ገና ከወዲሁ የእነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ዓላማ ማስታወሱ ጠቃሚ ነው። እነዚህ ዘገባዎች የሕይወት ታሪኮች ሳይሆኑ ወንጌሎች ናቸው። ይህን ልዩነት ማወቁ በጣም አስፈላጊ ነው። የሕይወት ታሪክ በሚሆንበት ጊዜ ጸሐፊው ግለሰቡ እንዴት ታዋቂ ሰው ለመሆን እንደበቃ ለመግለጽ በመጣር በመቶዎች የሚቆጠሩ ገጾች ይጽፍ ይሆናል። በመሆኑም አንዳንድ የሕይወት ታሪክ ጸሐፊዎች የግለሰቡን የዘር ሐረግ፣ ልደትና የልጅነት ሕይወት በዝርዝር ለማስፈር ሲሉ በርካታ ገጾችን ይጽፋሉ። የወንጌሎች ይዘት ግን ለየት ያለ ነው። ከአራቱ የወንጌል ዘገባዎች መካከል ስለ ኢየሱስ ልደትና የልጅነት ሕይወት የሚተርኩት የማቴዎስና የሉቃስ ወንጌሎች ብቻ ናቸው። ሆኖም ዓላማቸው ኢየሱስ በምን መልኩ ያን ዓይነት ሰው ሊሆን እንደቻለ ለመግለጽ አይደለም። ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ ይኖር እንደነበር ተከታዮቹ እንደሚያውቁ አትዘንጋ። (ዮሐንስ 8:23, 58) ስለዚህ ማቴዎስና ሉቃስ፣ ኢየሱስ ካደገ በኋላ ምን ዓይነት ሰው ሊሆን እንደቻለ ለመግለጽ ሲሉ ስለ ልጅነት ሕይወቱ በዝርዝር መጻፍ አላስፈለጋቸውም። ከዚህ ይልቅ ለሚጽፉት ወንጌል ዓላማ የሚስማሙ ክንውኖችን ብቻ ጽፈዋል።
ታዲያ ለመጻፍ የተነሳሱበት ዓላማ ምን ነበር? “ወንጌል” የሚለው ቃል “ምሥራች” የሚል ትርጉም አለው። ሁለቱም ሰዎች ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ ወይም ክርስቶስ መሆኑን፣ ለሰው ልጆች ኃጢአት ሲል መሞቱን እንዲሁም ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ ማረጉን የሚገልጽ ተመሳሳይ መልእክት ጽፈዋል። ይሁን እንጂ ሁለቱም ጸሐፊዎች ፈጽሞ የተለያየ ዓይነት አነሳስ ያላቸው ሲሆን የጻፉትም ለተለያዩ አንባብያን ነው። ቀረጥ ሰብሳቢው ማቴዎስ ዘገባውን በአመዛኙ አይሁዳዊ የሆኑ አንባብያንን እንዲማርክ አድርጎ ጽፎታል። ሐኪሙ ሉቃስ ደግሞ የጻፈው አንድ ዓይነት ከፍተኛ ስልጣን የነበረው ሰው ሳይሆን አይቀርም ለሚባለው ‘ለተከበረው ቴዎፍሎስ’ ሲሆን በዚያውም አይሁዳውያንንና አሕዛብን ለሚያካትት በርካታ አንባብያን ነው። (ሉቃስ 1:1-3) ሁለቱም ጸሐፊዎች በጣም ተስማሚ የሆኑ ክንውኖችን የመረጡ ሲሆን ይህንንም ያደረጉት በአእምሮአቸው የያዟቸውን አንባብያን ለማሳመን ሳይሆን አይቀርም። በመሆኑም የማቴዎስ ዘገባ ከኢየሱስ ጋር በተያያዘ ፍጻሜያቸውን ባገኙ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች በሚገኙ ትንቢቶች ላይ ያተኩራል። በአንጻሩ ደግሞ ሉቃስ አይሁዳውያን ያልሆኑ አንባቢዎች ሊያስተውሉት የሚችሉትን ዓይነተኛ የሆነ ታሪክ አዘል አቀራረብ ተከትሏል።
ሁለቱ ዘገባዎች የተለያዩ መሆናቸው ምንም አያስደንቅም። ይሁን እንጂ ተቺዎች እንደሚሉት ሁለቱ ዘገባዎች እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ አይደሉም። እንዲያውም ይበልጥ የተሟላ መልእክት ለማቅረብ በጥሩ ሁኔታ እርስ በርስ ይደጋገፋሉ።
የኢየሱስ ልደት በቤተ ልሔም
ማቴዎስም ሆነ ሉቃስ የኢየሱስን ልደት በተመለከተ ከድንግል መወለዱን የሚገልጽ አስደናቂ የሆነ ተአምር ጽፈዋል። ማቴዎስ በዚህ ተአምር አማካኝነት ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ኢሳይያስ የተናገረው አንድ ትንቢት ፍጻሜውን ማግኘቱን ገልጿል። (ኢሳይያስ 7:14፤ ማቴዎስ 1:22, 23) ሉቃስ፣ ቄሣር በደነገገው የሕዝብ ቆጠራ ምክንያት ዮሴፍና ማርያም ወደ ቤተ ልሔም ለመሄድ እንደተገደዱና ኢየሱስም በዚያ መወለዱን ገልጿል። (ገጽ 7 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) ኢየሱስ በቤተ ልሔም መወለዱ ከፍተኛ ትርጉም ያዘለ ነው። በመቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ነቢዩ ሚክያስ መሲሑ በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ከምትገኘው፣ ያን ያህል አስፈላጊ መስላ ከማትታየው ትንሽ ከተማ እንደሚወጣ ተንብዮ ነበር።—ሚክያስ 5:2
ኢየሱስ በተወለደበት ምሽት የነበረውን ሁኔታ የሚያሳዩ ምስሎች ይሠራሉ። ሆኖም ብዙውን ጊዜ በእነዚህ ምስሎች አማካኝነት ለመግለጽ የሚሞከረው ነገር ከእውነተኛው ታሪክ ፈጽሞ የተለየ ነው። ዮሴፍንና ማርያምን ወደ ቤተ ልሔም እንዲሄዱ ስላደረጋቸው የሕዝብ ቆጠራ የገለጸልን ታሪክ ጸሐፊው ሉቃስ በዚያች ከፍተኛ ትርጉም ባላት ምሽት ላይ እረኞቹ ከመንጎቻቸው ጋር በሜዳ ማደራቸውንም ጠቅሶልናል። እነዚህ ሁለት ሁኔታዎች ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተመራማሪዎች ኢየሱስ በታኅሣሥ ወር ሊወለድ አይችልም ወደሚል መደምደሚያ እንዲደርሱ አድርገዋቸዋል። ቄሣር ለማመፅ በቋፍ ላይ ያሉትን አይሁዳውያን ቅዝቃዜና ዝናብ ባለበት ወቅት ወደ ትውልድ ከተማቸው እንዲሄዱ ማስገደዱ ዓመፀኛ የሆኑትን ሰዎች ይበልጥ ሊያስቆጣ ስለሚችል ይህ የማይመስል መሆኑን ጠቅሰዋል። በእንዲህ ዓይነቱ አስቸጋሪ የአየር ጠባይ እረኞች ከመንጎቻቸው ጋር በሜዳ ማደራቸው ከዚያ በማይተናነስ ሁኔታ ሊሆን እንደማይችል የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ተናግረዋል።—ሉቃስ 2:8-14
ይሖዋ ስለ ልጁ ልደት ለማብሰር የመረጠው በወቅቱ ለነበሩት የተማሩና ተሰሚነት ላላቸው የሃይማኖት መሪዎች ሳይሆን በሜዳ ያድሩ ለነበሩት ምስኪን የቀን ሠራተኞች እንደነበር አስተውል። ጸሐፍትና ፈሪሳውያን፣ ወጥ ያልሆነ የሥራ ፕሮግራማቸው አንዳንድ ዝርዝር የቃሉን ሕጎች ከመከተል ወደ ኋላ ካስቀራቸው እረኞች ጋር ያላቸው ግንኙነት አናሳ እንደሚሆን መገመት ይቻላል። ሆኖም አምላክ ለእነዚህ ትሑትና ታማኝ የሆኑ ሰዎች ከፍተኛ ክብር አሳይቷቸዋል። የአምላክ ሕዝቦች ለብዙ ሺህ ዓመታት ሲጠባበቁ የኖሩት መሲሕ በቤተ ልሔም መወለዱን መላእክትን በመላክ አስታውቋቸዋል። ማርያምና ዮሴፍን የጎበኙትና በግርግም ተኝቶ የነበረውን የሚያሳሳ ሕፃን ከበው የተመለከቱት፣ የኢየሱስን ልደት በሚያሳዩ ምስሎች ላይ አብዛኛውን ጊዜ የሚታዩት “ሦስት ነገሥታት” ሳይሆኑ እነዚህ እረኞች ናቸው።—ሉቃስ 2:15-20
ይሖዋ በትሕትና እውነትን ለሚፈልጉ ሞገሱን ያሳያል
አምላክ እሱን ለሚወዱትና ዓላማዎቹ ሲፈጸሙ ለማየት በጣም ለሚጓጉ ሰዎች ሞገሱን ያሳያል። ይህ ጉዳይ በኢየሱስ ልደት ዙሪያ ባሉ ክስተቶች ላይ በተደጋጋሚ የተጠቀሰ ጉዳይ ነው። ልጁ ከተወለደ ከአንድ ወር ገደማ በኋላ ዮሴፍና ማርያም የሙሴን ሕግ በመታዘዝ ወደ ቤተ መቅደስ ይዘውት የሄዱ ሲሆን በዚያም “ሁለት ዋሊያ ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች” መሥዋዕት አድርገው አቅርበዋል። (ሉቃስ 2:22-24) እርግጥ ሕጉ አውራ በግ እንዲቀርብ ይጠይቅ ነበር፤ ሆኖም ሰዎቹ ችግረኞች ከሆኑ ብዙ ወጪ የማይጠይቀውን አማራጭ እንዲጠቀሙ ይፈቅድላቸዋል። (ዘሌዋውያን 12:1-8) እስቲ አስበው። የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ የሆነው ይሖዋ አምላክ በጣም የሚወደውን አንድያ ልጁን በሰብዓዊ ሁኔታዎች እንዲከባከብ የመረጠው ባለጠጋ ቤተሰብ ሳይሆን ድሃ ቤተሰብን ነው። ወላጅ ከሆንክ ከቁሳዊ ሃብት ወይም ከፍተኛ ግምት ከሚሰጠው ትምህርት ይልቅ ለልጆችህ ልትሰጠው የምትችለው ከሁሉ የላቀ ስጦታ ለመንፈሳዊ እሴቶች ቅድሚያ የሚሰጥ ቤተሰብ መገንባት መሆኑን ይህ ሁኔታ ጥሩ አድርጎ የሚያስገነዝብ መሆን ይኖርበታል።
በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያሉ ሌሎች ሁለት ታማኝ የሆኑ ትሑት አገልጋዮች የይሖዋን ሞገስ አግኝተዋል። አንደኛዋ የ84 ዓመት መበለት የሆነችው ሐና ስትሆን እስዋም “ከመቅደስ አትለይም ነበር።” (ሉቃስ 2:36, 37) ሌላው ደግሞ ታማኝ የሆነው አረጋዊው ስምዖን ነው። ሁለቱም ሰዎች አምላክ ከመሞታቸው በፊት ተስፋ የተደረገበትን መሲሕ የማየት መብት ስለሰጣቸው በጣም ተደስተው ነበር። ስምዖን ትንሹን ልጅ የሚመለከት ትንቢት ተናግሯል። ትንቢቱ ተስፋ ያዘለ ቢሆንም በመጠኑ ሐዘንም ተቀላቅሎበታል። ይህች ወጣት የሆነች እናት ማለትም ማርያም አንድ ቀን የምትወደው ልጅዋን በተመለከተ ሐዘን እንደሚደርስባት ተንብዮዋል።—ሉቃስ 2:25-35
አደጋ የተደቀነበት ልጅ
ስምዖን ይህ ምንም የማያውቅ ሕፃን የጥላቻ ዒላማ እንደሚሆን የሚያስገነዝብ አሳዛኝ ትንቢት ተናግሯል። ገና ሕፃን እያለም እንኳ ጥላቻው ጀምሮ ነበር። የማቴዎስ ዘገባ ይህ የሆነበትን ሁኔታ ይገልጻል። ብዙ ወራቶች ካለፉ በኋላ ዮሴፍ፣ ማርያምና ኢየሱስ በቤተ ልሔም በሚገኝ ቤት ውስጥ መኖር ጀምረዋል። በርካታ እንግዶች ሳይታሰብ መጥተው ጠይቀዋቸዋል። የኢየሱስን ልደት ያሳያሉ ተብለው የሚሠሩ ምስሎች ከሚያቀርቡት በተለየ መልኩ ማቴዎስ መጥተው የጠየቋቸው ሰዎች ምን ያህል እንደሆኑ የገለጸው ነገር የለም። እንዲሁም እንግዶቹን እንኳንስ “ሦስት ነገሥታት” ብሎ ሊጠራቸው ይቅርና “ጠቢባን” ብሎ እንኳ አልሰየማቸውም። ማንነታቸውን ለማመልከት የተጠቀመው “ኮከብ ቆጣሪዎች” የሚል ትርጉም ያለውን ማጂ የሚለውን የግሪክኛ ቃል ነው። ይህ ራሱ በቦታው አንድ መጥፎ ነገር በመጠንሰስ ላይ እንዳለ ለአንባቢው ፍንጭ ሊሰጠው ይገባል። ምክንያቱም ኮከብ ቆጠራ የአምላክ ቃል የሚያወግዘው ተግባር ከመሆኑም በላይ ታማኝ አይሁዶች ፈጽሞ የሚርቁት ነገር ነበር።—ዘዳግም 18:10–12፤ ኢሳይያስ 47:13, 14
እነዚህ ኮከብ ቆጣሪዎች በስተ ምሥራቅ የታየን አንድ ኮከብ ተከትለው ‘ለተወለደው የአይሁድ ንጉሥ’ ስጦታ ሊሰጡ መጡ። (ማቴዎስ 2:1, 2) ይሁን እንጂ ኮከቡ ወደ ቤተ ልሔም አልመራቸውም። ከዚህ ይልቅ በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ወደ ታላቁ ሄሮድስ አደረሳቸው። በዚያን ወቅት ሕፃኑን ኢየሱስን ለመጉዳት የሄሮድስን ያህል አቅሙም ሆነ ፍላጎቱ ያለው ሰው አልነበረም። ይህ እብሪተኛ የሆነ ነፍሰ ገዳይ ሥልጣኔን ይቀናቀኑኛል ብሎ ያሰባቸውን በርካታ ቅርብ የቤተሰቡን አባላት የገደለ ሰው ነው።a ወደፊት “የአይሁድ ንጉሥ” ስለሚሆነው ልጅ ልደት በመስማቱ ስለተረበሸ ኮከብ ቆጣሪዎቹ ልጁን ፈልገው እንዲያገኙ ወደ ቤተ ልሔም ላካቸው። ጉዟቸውን እንደጀመሩ አንድ እንግዳ ነገር ተከሰተ። ወደ ኢየሩሳሌም እንዲያቀኑ የመራቸው “ኮከብ” መንቀሳቀስ ጀመረ!—ማቴዎስ 2:1-9
ይህ ነገር በሰማይ ላይ የታየ እውነተኛ ብርሃን ይሁን ወይም እንዲሁ ራእይ ብቻ ስለመሆኑ የምናውቀው ነገር የለም። ሆኖም ይህ “ኮከብ” ከአምላክ የተላከ አለመሆኑን እናውቃለን። ኮከቡ መሰሪ በሆነ ሁኔታ ዝንፍ ሳይል እነዚህን ጣዖት አምላኪዎች ለአደጋ ወደተጋለጠውና ራሱን ማስጣል ወደማይችለው፣ የአንድ ድሃ አናጢና የሚስቱን ጥበቃ ብቻ ወደሚያገኘው ልጅ ወደ ኢየሱስ አደረሳቸው። አይወቁት እንጂ የሄሮድስ መጠቀሚያ የሆኑት እነዚህ ኮከብ ቆጣሪዎች ተበቃይ ወደሆነው ንጉሥ ሪፖርት ይዘው መመለሳቸው የማይቀር ነበር፤ ይህ ደግሞ ልጁን ለጥፋት ይዳርገዋል። ይሁን እንጂ አምላክ በሕልም አማካኝነት ጣልቃ በመግባት በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አደረጋቸው። ስለዚህ “ኮከቡ” መሲሑን ለመጉዳት የተቻለውን ሁሉ የሚያደርገው የአምላክ ጠላት የሆነው የሰይጣን መሣሪያ መሆን አለበት። የኢየሱስን ልደት ለማሳየት ተብለው በሚሠሩ ምስሎች ላይ ‘ኮከቡ’ እና ኮከብ ቆጣሪዎቹ ከአምላክ የተላኩ መልእክተኞች እንደሆኑ ተደርጎ መቅረቡ በጣም የሚያስገርም ነው!—ማቴዎስ 2:9-12
አሁንም ቢሆን ሰይጣን እጅ አልሰጠም። በዚህ ጉዳይ የእርሱ መሣሪያ የሆነው ንጉሥ ሄሮድስ በቤተ ልሔም የሚኖሩ ከሁለት ዓመት ዕድሜ በታች ያሉ ሕፃናት በሙሉ እንዲገደሉ አዘዘ። ሆኖም ሰይጣን ከይሖዋ ጋር በሚያደርገው ፍልሚያ ሊያሸንፍ አይችልም። ሌላው ቀርቶ አምላክ ምንም የማያውቁ ሕፃናት በጭካኔ እንደሚጨፈጨፉ እንኳ ከረጅም ጊዜ በፊት መገንዘቡን ማቴዎስ ጠቅሷል። ይሖዋ በመልአክ አማካኝነት ዮሴፍ ወደ ግብጽ እንዲሸሽ በማስጠንቀቅ ሰይጣንን በድጋሚ ተቋቁሞታል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ዮሴፍ ጥቂት የሆኑትን የቤተሰቡን አባላት ይዞ ወደ ናዝሬት እንደሄደና በዚያ መኖር እንደጀመረ ማቴዎስ ገልጿል። ኢየሱስ ከታናናሽ ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር ያደገው በዚህ ቦታ ነው።—ማቴዎስ 2:13-23፤ 13:55, 56
የክርስቶስ ልደት ለአንተ የያዘው ትርጉም
በኢየሱስ ልደትና በልጅነት ሕይወቱ ዙሪያ የተከናወኑትን ነገሮች በተመለከተ ያደረግከው ይህ አጭር ክለሳ ከዚህ ቀደም ከምታውቀው ለየት ያለ ሆኖብሃልን? ብዙዎች ለየት ያለ ይሆንባቸዋል። ምንም እንኳ አንዳንድ ሰዎች ወንጌሎቹ እርስ በርስ እንደሚቃረኑ አፋቸውን ሞልተው ቢናገሩም ብዙዎች ዘገባዎቹ በእርግጥ ስምምና ትክክል መሆናቸውን ሲገነዘቡ በጣም ይደነቃሉ። አንዳንዶቹ ሁኔታዎች በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የተተነበዩ መሆናቸውን ሲያውቁ ይገርማቸዋል። እንዲሁም በወንጌሎች ውስጥ የተዘገቡት አንዳንድ ጉልህ ክንውኖች ሲወርዱ ሲዋረዱ ከመጡት ስለ ኢየሱስ ልደት ከሚነገሩት ታሪኮችም ሆነ ሁኔታውን ለመግለጽ ሲባል ከሚቀርቡት ምስሎች ትልቅ ልዩነት እንዳላቸው ሲያውቁ ይደነቃሉ።
ሆኖም ከሁሉም በላይ ይበልጥ የሚያስገርመው አብዛኛው ባሕላዊ የገና በዓል አከባበሮች የወንጌል ትረካዎች የያዙዋቸውን ዐበይት ነጥቦች አለማካተታቸው ሳይሆን አይቀርም። ለምሳሌ ያህል ለኢየሱስ አባት ማለትም ለዮሴፍ ሳይሆን ለይሖዋ አምላክ እምብዛም ትኩረት አይሰጥም። ይሖዋ የሚወደውን ልጁን፣ ዮሴፍና ማርያም እንዲያሳድጉትና እንዲንከባከቡት በአደራ ሲሰጣቸው የተሰማውን ስሜት እስቲ ገምት። ልጁ ገና ሕፃን በነበረበት ጊዜ እንኳ ሳይቀር ሊገድለው የሚያሴር ጥላቻ የተሞላ ንጉሥ ባለበት ዓለም ውስጥ እንዲያድግ ሲፈቅድ በሰማይ የሚኖረው አባት የሚሰማውን ስቃይ ገምት! ይሖዋ ለሰው ልጆች ያለው ጥልቅ ፍቅር ይህን መሥዋዕት እንዲከፍል አነሳስቶታል።—ዮሐንስ 3:16
አብዛኛውን ጊዜ የገና ክብረ በዓሎች እውነተኛው ኢየሱስ እንዲረሳ እያደረጉ ነው። እንዲያውም ለደቀ መዛሙርቱ ስለተወለደበት ቀን አንስቶ እንኳ እንደሚያውቅ የሚገልጽ አንድም በጽሑፍ የሰፈረ ማስረጃ ካለመኖሩም በላይ ተከታዮቹ የልደት ቀኑን እንዳከበሩ የሚጠቁም ምንም ፍንጭ የለም።
ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲያከብሩ ያዘዘው የልደት ቀኑን ሳይሆን በዓለም ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ትርጉም ያዘለውን ክንውን ማለትም የሞተበትን ቀን ነው። (ሉቃስ 22:19, 20) ኢየሱስ በግርግም እንደተኛ አቅመ ቢስ ሕፃን ተደርጎ እንዲታወስ አይፈልግም። በአሁኑ ጊዜ እርሱ የሚገኘው በዚህ ሁኔታ አይደለም። ኢየሱስ ከተገደለ ከ60 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ ራሱን ለሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ የገለጠው ወደ ጦርነት በመገስገስ ላይ እንዳለ ንጉሥ አድርጎ ነው። (ራእይ 19:11–16) ኢየሱስ ዓለምን የሚለውጥ ንጉሥ ስለሆነ በዛሬው ጊዜ እሱን ማወቅ ያለብን የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ገዥ በመሆን በሚወስደው እርምጃ መሆን አለበት።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እንዲያውም አውግስጦስ ቄሣር የሄሮድስ ልጅ ከመሆን ይልቅ የሄሮድስ አሳማ መሆን እንደማያሰጋ ተናግሯል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
ሉቃስ ተሳስቷልን?
በናዝሬት ያደገውና አብዛኛውን ጊዜ የናዝሬቱ እየተባለ የሚጠራው ኢየሱስ 150 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ በምትገኘው በቤተ ልሔም እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሉቃስ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “በዚያም ወራት [ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት] ዓለሙ ሁሉ እንዲጻፍ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣች። ቄሬኔዎስ በሶርያ አገር ገዥ በነበረ ጊዜ ይህ የመጀመሪያ ጽሕፈት ሆነ። ሁሉም እያንዳንዱ ይጻፍ ዘንድ ወደ ከተማው ሄደ።”—ሉቃስ 1:1፤ 2:1–3
ተቺዎች ይህን ጥቅስ ስህተት እንደሆነ ይባስ ብሎም ፈጠራ እንደሆነ በመቁጠር በጣም ያወግዙታል። ይህ የሕዝብ ቆጠራ የተካሄደውና የቄሬኔዎስ የግዛት ዘመን የነበረው በ6 ወይም 7 እዘአ እንደሆነ ይገልጻሉ። አባባላቸው ትክክል ከሆነ፣ ማስረጃው ኢየሱስ በ2 ከዘአበ መወለዱን ስለሚያመለክት ይህ ጉዳይ በሉቃስ ዘገባ ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ ያሳድራል። ሆኖም እነዚህ ተቺዎች ሁለት ቁልፍ እውነታዎችን ችላ ብለዋል። በመጀመሪያ ደረጃ ሉቃስ ከአንድ በላይ ቆጠራ መካሄዱን ገልጿል። “ይህ የመጀመሪያ ጽሕፈት” ሲል የጠቀሰውን ልብ በል። ከጊዜ በኋላ ሌላ ምዝገባ መካሄዱን በሚገባ ያውቅ ነበር። (ሥራ 5:37) ከጊዜ በኋላ የተደረገው ይህ የሕዝብ ቆጠራ ታሪክ ጸሐፊው ጆሴፈስ ከገለጸው በ6 እዘአ ከተካሄደው ቆጠራ ጋር ተመሳሳይ ነው። በሁለተኛ ደረጃ የቄሬኔዎስ የግዛት ዘመን የኢየሱስን ልደት በድጋሚ ከተደረገው ቆጠራ ጋር እንድናያይዝ አያስገድደንም። ለምን? ማስረጃዎቹ እንደሚያሳዩት ቄሬኔዎስ በዚህ የኃላፊነት ሥልጣን ያገለገለው ሁለት ጊዜ በመሆኑ ምክንያት ነው። መጀመሪያ በሥልጣን የቆየበት ዘመን በ2 ከዘአበ ያለውን ጊዜ እንደሚያጠቃልል ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ተገንዝበዋል።
አንዳንድ ተቺዎች ሉቃስ፣ ኢየሱስ በቤተ ልሔም የሚወለድበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ይህን የሕዝብ ቆጠራ በመፍጠር እግረ መንገዱን የሚክያስ 5:2 ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ አድርጓል ይላሉ። እንዲህ ዓይነቱ አስተያየት ሉቃስ ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ታሪክ እንደፈጠረ ያስመስለዋል። ሆኖም የትኛውም ተቺ ቢሆን ይህ ዓይነቱን ክስ ወንጌሉንና የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን ከጻፈው ጠንቃቃ ታሪክ ጸሐፊ ጋር ሊያስታርቅ አይችልም።
የትኛውም ተቺ ማስረዳት የማይችለው ሌላም ነገር አለ፤ የሕዝብ ቆጠራው ራሱ አንድ ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ አድርጓል! በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ዳንኤል ‘በመንግሥቱ ክብር መካከል አስገባሪውን ስለሚያሳልፈው’ ገዥ ትንቢት ተናግሯል። ይህ ትንቢት አውግስጦስንና በእስራኤል ውስጥ የሕዝብ ቆጠራ እንዲካሄድ ያስተላለፈውን ትእዛዝ የሚመለከት ነውን? እንዲያውም ትንቢቱ በመቀጠል ይህን ገዢ ተክቶ በሚነሳው ንጉሥ የግዛት ዘመን መሲሑ ወይም “የቃል ኪዳኑ አለቃ” ‘እንደሚሰበር’ ተናግሯል። በእርግጥም ኢየሱስ ‘የተሰበረው’ ማለትም የተገደለው የአውግስጦስ ተተኪ በሆነው በጢባርዮስ የንግሥና ዘመን ነበር።—ዳንኤል 11:20–22
[ሥዕሎች]
አውግስጦስ ቄሣር (27 ከዘአበ-14 እዘአ)
ጢባርዮስ ቄሣር (14-37 እዘአ)
[ምንጮች]
Musée de Normandie, Caen, France
Photograph taken by courtesy of the British Museum
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ መልአክ ትሑት ለሆኑት እረኞች ስለ ክርስቶስ ልደት የሚገልጸውን ምስራች በማብሰር ሞገስ አሳይቷቸዋል