‘የማያሳፍር ሠራተኛ’ ለመሆን መጣር
አንድሬ ሶፓ እንደተናገረው
የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተባብሶ ይህ ነው የማይባል ታላቅ እልቂትና ተስፋ መቁረጥ አስከትሎ አበቃ። በኖርዌይ ናርቪክ አቅራቢያ በሚገኘው የጀርመን ባሕር ኃይል ውስጥ ምልክት ሰጪ ሆኜ አገለግል ስለነበር የሰው ልጅ ለሰው ልጅ አውሬ ሲሆንበት በዓይኔ በብረቱ አይቻለሁ። አንድ ቀን ሌሊት በገደላማ የባሕር ወሽመጥ ውስጥ ሆኜ እጅግ ማራኪ የሆነውን የሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ጎህ ስመለከት ስለ ሕይወት በጥልቀት ለማሰብ ተገደድኩ። እንዲህ ያሉ ነገሮችን የፈጠረ አምላክ በጦርነት ለሚፈጸመው የእብደት ተግባር በኃላፊነት ሊጠየቅ እንደማይችል እርግጠኛ ነበርኩ።
የተወለድኩት በቼክ ድንበር አቅራቢያ በምትገኝ ላሶት በምትባል (በአሁኑ ጊዜ በፖላንድ የምትገኝ) አንዲት ትንሽ መንደር ውስጥ በ1923 ሲሆን ያደግሁት በአንድ ደሀ የገበሬ ቤተሰብ ውስጥ ነበር። ወላጆቼ የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታዮች ሲሆኑ ሃይማኖት በሕይወታችን ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ነበረው። ይሁን እንጂ ሃይማኖቴን መጠራጠር የጀመርኩት ገና ድሮ ነበር። በመንደራችን የሚኖሩ ሦስት የፕሮቴስታንት ቤተሰቦች የነበሩ ሲሆን እነዚህን ሰዎች የካቶሊኩ ማኅበረሰብ በጣም ያገላቸው ነበር። ለምን እንደሚያገሏቸው ጨርሶ ሊገባኝ አልቻለም። በትምህርት ቤት በጥያቄና መልስ መልክ የተዘጋጀ የሃይማኖት ትምህርት እንማር ነበር። ሆኖም አንድ ቀን ቄሱን ስለ ሥላሴ እንዲያብራሩልኝ ስጠይቃቸው ያገኘሁት መልስ በከዘራ አሥር ምት መቅመስ ነበር። ያም ሆኖ ግን በቤተ ክርስቲያን ላይ የነበረኝን ጥርጣሬ ያባባሰው በ17 ዓመቴ የተፈጸመ ነገር ነበር። በአንድ ወር ልዩነት ውስጥ የእናቴ ወላጆች ሞቱ። እናቴ ደግሞ የሁለቱንም የቀብር ሥነ ሥርዓት በቤተ ክርስቲያን ለማስፈጸም የሚያስችላት በቂ ገንዘብ አልነበራትም። ስለዚህ ቆየት ብላ ልትከፍላቸው ትችል እንደሆነ ቄሱን ጠየቀቻቸው። “ወላጆችሽ አንዳንድ እቃዎች አሏቸው፤ ለምን እነሱን ሸጠሽ ገንዘቡን ለቀብር ማስፈጸሚያ አትጠቀሚበትም?” ሲሉ መለሱላት።
ይህ ከመሆኑ ከጥቂት ዓመታት በፊት ሂትለር በ1933 ሥልጣን ከጨበጠ በኋላ በፖላንድ ቋንቋ እንዳንናገር ተከልክለን ነበር፤ የግድ ጀርመንኛ መናገር ነበረብን። ጀርመንኛ ለመናገር አሻፈረን ያሉ ወይም ጀርመንኛ መማር ያልቻሉ ቀስ በቀስ ከአካባቢው ተሰወሩ፤ አንድ በአንድ እየተለቀሙ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ እንደተጨመሩ ከጊዜ በኋላ ሰማን። ሌላው ቀርቶ የመንደራችን ስም ተቀይሮ ግሩንፍሊስ የሚባል የጀርመን ስም ተሰጣት። አሥራ አራት ዓመት ሲሞላኝ ትምህርት አቆምኩ፤ የሂትለር ወጣቶች ድርጅት አባል ስላልሆንኩ ሥራ ማግኘት ተቸግሬ ነበር። ይሁንና በመጨረሻ ተለማማጅ ቀጥቃጭ ሆኜ ተቀጠርኩ። ጦርነቱ ከጀመረ በኋላ ለሂትለርና ለጀርመን ሠራዊት በቤተ ክርስቲያን ጸሎት ይቀርብ ነበር። በሌላኛው ወገን ያለው ሠራዊት ድል እንዲያደርግ ተመሳሳይ የሆነ ጸሎት ይቀርብ ይሆን እያልኩ አስብ ነበር።
በጀርመን ባሕር ኃይል ውስጥ ማገልገል
በታኅሣሥ 1941 በጀርመን ባሕር ኃይል ውስጥ ለማገልገል ተቀጠርኩና በ1942 መጀመሪያ ላይ በአንዲት ቃኚ መርከብ ላይ እንድሠራ ወደ ኖርዌይ የባሕር ጠረፍ ተላክሁ። ወታደሮች፣ የጦር መሣሪያ ወይም ጭነት የሚያጓጉዙ በትሮንዴምና በኦስሎ መካከል የሚያልፉ መርከቦችን እንድናጅብ ተመድበን ነበር። በባሕር ላይ ሳለን ሁለት መርከበኞች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለ ተተነበየው የዓለም መጨረሻ ሲያወሩ ሰማሁ። በግልጽ ለመናገር ቢፈሩም ወላጆቻቸው የይሖዋ ምሥክሮች እንደነበሩ ሆኖም የእነሱን አርአያ እንዳልተከተሉ ነገሩኝ። ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የሰማሁት በዚህ ጊዜ ነበር።
ጦርነቱ ሲያበቃ የብሪታንያ ወታደሮች ካሰሩን በኋላ ወደ ጀርመን ተመልሰን እንድንሄድ ለአሜሪካ ወታደሮች አሳልፈው ሰጡን። በዚያን ጊዜ በሶቪየት ክልል ውስጥ የምንኖረው ሁሉ በከሰል ማውጫዎች ውስጥ እንድንሠራ በሰሜን ፈረንሳይ በሊዬቨ ወደሚገኘው የእስር ቤት ካምፕ ተላክን። ይህ የሆነው በነሐሴ 1945 ነበር። ከፈረንሳውያን ጠባቂዎቻችን ውስጥ አንዱን ሃይማኖቱ ምን እንደሆነ እንደጠየቅሁት ትዝ ይለኛል። “ካቶሊክ” ሲል መለሰልኝ። እኔም ካቶሊክ ስለሆንኩ ታዲያ እኔና አንተ በምን ተደራርሰን ነው ጠላት የሆነው? ስል ጠየቅሁት። “ምንም መመራመር አያስፈልግም። ሁኔታው ይኸው ነው” ሲል መለሰ። ለእኔ ተመሳሳይ ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች መዋጋታቸውና መገዳደላቸው ግራ የሚያጋባ ነበር።
በከሰል ማዕድን ማውጫ ውስጥ የፈነጠቀ የብርሃን ጭላንጭል
በአካባቢው ከሚገኙ ማዕድን አውጪዎች ጋር ባሳለፍኩት የመጀመሪያ ቀን ላይ አንድ ኤቨንዝ ኤምዮት የሚባል ሰው ከያዘው ሳንድዊች አካፈለኝ። ከዩናይትድ ስቴትስ ኦሃዮ የመጣ ሲሆን ለብዙ ዓመታት በፈረንሳይ ኖሯል። ጦርነት የማይኖርበት ዓለም እንደሚመጣ ነገረኝ። የደግነት ባሕርይው አስገረመኝ። እኔ ጀርመናዊ እሱ አሜሪካዊ ቢሆንም ለእኔ ምንም የጠላትነት ስሜት አልነበረውም። ከዚያ በኋላ የተገናኘነው በ1948 መጀመሪያ ላይ ሲሆን በዚህ ጊዜ “የሰላሙ መስፍን” የሚል ርዕስ ያለው ቡክሌት ሰጠኝ። በመጨረሻ ጦርነትን የሚጠላ ሩኅሩኅ አምላክ መኖሩን አወቅሁ። የሰሜናዊ ንፍቀ ክበብን ጎህ እየተመለከትኩ አስብ የነበረው እንዲህ ስላለው አምላክ ነበር። ይህን የሚያስተምረውን ሃይማኖት ለማግኘት ቆረጥኩ። ሆኖም ኤቨንዝ ይሠራ የነበረው በሌላ የማዕድን ማውጫ ቦታ ስለነበረ ላገኘው አልቻልኩም። በእስር ቤት ካምፕ ውስጥ ወደሚገኙት የተለያዩ የሃይማኖት ቡድኖች በመሄድ ስለ ቡክሌቱ የሚያውቁት ነገር እንዳለ ብጠይቅም ማንንም አላገኘሁም።
በመጨረሻ በሚያዝያ 1948 ከእስር ቤት ካምፑ ተለቀቅሁና ነፃ ሠራተኛ ሆንኩ። በሚቀጥለው ቀን እሁድ በመንገድ ላይ የቃጭል ድምፅ ስሰማ ተገረምሁ። ኤቨንዝን ሳየው በጣም ተደሰትኩ! ከአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቡድን ጋር በመሆን የአንድን የሕዝብ ንግግር ርዕስ የሚያስተዋውቅ ከፊትና ከኋላ በትከሻ ላይ የሚንጠለጠል ማስታወቂያ አንግቶ ነበር። ቃጭሏን ያቃጭል የነበረው ሞርሶ ለርዎ የተባለ ምሥክር ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በፈረንሳይ የሚገኘው ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል ነው። በእምነቱ ምክንያት በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ሥቃይ ከደረሰበት ዮዜፍ ኩልቼክ ከሚባል ጀርመንኛ ተናጋሪ ከሆነ ፖላንዳዊ ጋር ተዋወቅሁ። ያን ቀን ምሽት ወደሚደረገው ስብሰባ እንድመጣ ጋበዘኝ። በዚያ የሚነገረው አብዛኛው ነገር አልገባኝም፤ ሆኖም ተሰብሳቢዎቹ በሙሉ እጃቸውን ሲያወጡ አጠገቤ የነበረውን ሰው ለምን እጃቸውን እንዳወጡ ጠየቅሁት። “በሚቀጥለው ሳምንት ደንከርክ ሄደው መስበክ የሚችሉ ናቸው።” “እኔም መምጣት እችላለሁ?” ስል ጠየቅሁት። “አዎን፣ ትችላለህ!” ሲል መለሰልኝ። ስለዚህ በቀጣዩ እሁድ ከቤት ወደ ቤት መስበክ ጀመርኩ። አዎንታዊ ምላሽ ይሰጥ የነበረው ሁሉም ሰው ባይሆንም እኔ ግን ደስ ብሎኝ ነበር፤ አዘውትሬም በስብከቱ ሥራ መካፈል ጀመርኩ።
ቁጣዬን መቆጣጠር ተማርኩ
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ምሥክሮቹ ነፃ የተለቀቁ የጀርመን እስረኞች በሚኖሩበት ካምፕ ውስጥ መስበክ ጀመሩ። ይህ ለእኔ ቀላል አልነበረም፤ ምክንያቱም በዚያ የነበሩ ሰዎች ቁጠኛ መሆኔን ያውቁ ነበር። አንድ ሰው በቁም ነገር አላዳምጠኝ ካለ “ብትጠነቀቅ ይሻልሃል፤ ካለበለዚያ ችግር ይፈጠራል” እያልኩ አስፈራራው ነበር። ሌላው ቀርቶ በአንድ ወቅት በማዕድን ማውጫ ውስጥ በምሠራበት ጊዜ አንድ ሰው በይሖዋ በማሾፉ በቡጢ ነርቼዋለሁ።
ይሁን እንጂ ከይሖዋ እርዳታ ጋር ባሕርዬን ለመለወጥ ችያለሁ። አንድ ቀን በእነዚህ የማደሪያ ሰፈሮች ውስጥ እያገለገልን ሳለ ብዙ መጠጥ ጠጥተው የነበሩ ሰዎች አንዳንድ ምሥክሮችን እያስቸገሯቸው ነበር። አብሬያቸው የነበርኩት ወንድሞች ግልፍተኛ መሆኔን ስለሚያውቁ በነገሩ ውስጥ እጄን እንዳላስገባ ሊከለክሉኝ ሞከሩ፤ ሆኖም ከሰዎቹ መካከል አንዱ እየዛተና ጃኬቱን እያወለቀ ወደ እኔ መጣ። ከቢስክሌቴ ላይ ወረድኩና ቢስክሌቴን እንዲይዝ ሰጥቼው እጄን ኪሴ ከተትሁ። በድርጊቴ በጣም በመገረሙ የምለውን ፀጥ ብሎ አዳመጠኝ። ወደ ቤቱ እንዲሄድና እንዲተኛ ከዚያም ሕዝብ ንግግሩን ለማዳመጥ እንዲመጣ ነገርሁት። ሰውየው ልክ በ9:00 ሰዓት በዚያ ተገኝቶ ነበር! ውሎ አድሮ 20 የሚሆኑ የቀድሞ እስረኞች መልእክቱን ተቀብለዋል። እኔም በመስከረም 1948 ተጠመቅሁ።
በሥራ የተጣበበ ሆኖም የሚያረካ ፕሮግራም
የምንሰብክባቸው ክልሎች የማዘጋጀትና የሕዝብ ንግግር ለማቅረብ የምንችልባቸው ቦታዎች ፈልጎ የማግኘት ኃላፊነት ተሰጥቶኝ ነበር። ይህን ለማድረግ በትንሿ የሞተር ቢስክሌት ወደ 50 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ርቀት ከተጓዝኩ በኋላ በማዕድን ማውጫ ውስጥ የምሽት ተረኛ ሆኜ እሠራለሁ። ከዚያም በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በአውቶቡስ ተሳፍረን ወደ ክልሉ እንሄድና ሁለት ወይም አራት አስፋፊዎች ከአንድ ተናጋሪ ጋር ወርደው ወደ ክልሉ ይገባሉ። በትላልቅ ከተሞች ተስማሚ ቦታ ስናገኝ የአገልግሎት ቦርሳዎቻችንን እንደራርብና ለተናጋሪው እንደ አትራኖስ ሆኖ እንዲያገለግል እናደርጋለን። አብዛኛውን ጊዜ በትከሻ ላይ ከፊትና ከኋላ በሚንጠለጠሉ ማስተዋወቂያዎች በመጠቀም የሕዝብ ንግግሩን ጭብጥ በማስተዋወቅ ሰዎችን እንጋብዝ ነበር።
በሬም ከምትገኘው ምሥክር ከዣኔት ሾፉር ጋር የተገናኘነው በ1951 ነበር። ልክ እንደተያየን ተዋደድን፤ ከአንድ ዓመት በኋላ በግንቦት 17, 1952 ተጋባን። በዱዌ አቅራቢያ በምትገኝ ፔከንኩር ወደምትባል አንዲት የማዕድን ማውጫ መንደር ተዛወርን። ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የጤና እክል ያጋጥመኝ ጀመር። በማዕድን ማውጫ ውስጥ በመሥራቴ ምክንያት ሲሊኮሲስ የሚባል የመተንፈሻ አካል ሕመም ይዞኝ ነበረ፤ ሆኖም ሌላ ዓይነት ሥራ ለማግኘት አልቻልኩም። ስለዚህ በ1955 በጀርመን ኑረምበርግ በተካሄደው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ሳለን፣ በራይን በምትገኝ ኬል በምትባል ትንሽ የኢንዱስትሪ መንደር ያለውን አነስተኛ ጉባኤ እንድንረዳ ስንጠየቅ ወደዚያ ለመዛወር ነፃ ነበርን። በዚያ ወቅት በጉባኤው ውስጥ 45 አስፋፊዎች ብቻ ነበሩ። ከዚህ ጉባኤ ጋር ባገለገልንባቸው በቀጣዮቹ ሰባት ዓመታት ውስጥ የአስፋፊዎቹ ቁጥር ወደ 95 አድጓል።
ተጨማሪ የአገልግሎት መብቶች
ጉባኤው በሚገባ እንደተደራጀ ስላየን በፈረንሳይ ውስጥ በልዩ አቅኚነት ለማገልገል ለማኅበሩ ጥያቄ አቀረብን። በጣም የሚገርመው በፓሪስ እንድናገለግል ተመደብን። በዚያ ያሳለፍናቸው ስምንት ወራት በደስታ የተሞሉ ነበሩ። ዣኔትና እኔ በአንድ ላይ 42 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች የመምራት መብት አግኝተን ነበር። አምስቱ እዚያው እያለን የተጠመቁ ሲሆን 11ዱ ደግሞ ከጊዜ በኋላ እውነትን ተቀብለዋል።
እንኖር የነበረው ተማሪዎች በሚገኙበት የፓሪስ ክፍል በመሆኑ በሶርቦን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከሚሠሩ ፕሮፌሰሮች ጋር ብዙ ጊዜ እንገናኝ ነበር። የእምነት ፈውስ ያደርግ የነበረ አንድ ጡረታ የወጣ የፍልስፍና ፕሮፌሰር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክር ሆኗል። አንድ ቀን ከኢየሱሳውያን አስተማሪዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት ካለው ከአንድ የሲቪል መሃንዲስ ጋር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት ማድረግ ጀመርን። ከሰዓት በኋላ በዘጠኝ ሰዓት ወደ አፓርታማችን መጥቶ ከምሽቱ በአራት ሰዓት ሄደ። የሚያስገርመው ነገር ከአንድ ሰዓት ተኩል በኋላ ተመልሶ በራችንን አንኳኳ። ከአንድ ኢየሱሳዊ ጋር ቢነጋገርም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ያቀረበለትን ጥያቄዎች ሊመልስለት አልቻለም ነበር። ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ላይ ወደ ቤቱ ቢሄድም በአንድ ሰዓት ላይ ተመልሶ መጣ። ከጊዜ በኋላ እሱም የይሖዋ ምሥክር ሆኗል። ሰዎች ለእውነት ያላቸው ይህን የመሰለው ጥማት ለእኔና ለባለቤቴ ትልቅ ማበረታቻ ሆኖልናል።
በፓሪስ ካገለገልን በኋላ በምሥራቅ ፈረንሳይ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተጋበዝኩ። ፈረንሳይኛና ጀርመንኛ ተናጋሪ ጉባኤዎችን መጎብኘትና ወንድሞችን ማበረታታት በጣም አስደሳች ነበር። በሎሬይን የሚገኘውን የሮምባስ ጉባኤ ስጎበኝ ከስታኒስዋስ አምብሮሽቻክ ጋር ተገናኘሁ። በጦርነቱ ጊዜ በአንድ የኅብረ ብሔሩ ባሕር ሰርጓጅ መርከብ ላይ ያገለገለና በኖርዌይ ውኃዎች ላይ በተካሄዱ ውጊያዎች የተካፈለ ፖላንዳዊ ነበረ። በአንድ ባሕር ላይ ብንሆንም ለውጊያ የተሰለፍነው በተቃራኒ ወገን ነበር። አሁን ግን አምላካችንን ይሖዋን በማገልገል በአንድነት የምንሠራ ወንድማማቾች ነን። በሌላ ወቅት በፓሪስ በተካሄደ በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ አንድ የማውቀው ሰው ተመለከትሁ። በሰሜን ፈረንሳይ በታሰርኩበት ጊዜ የካምፑ አዛዥ የነበረ ሰው ነው። በስብሰባው ላይ በአንድነት ለመሥራት በመቻላችን ምን ያህል ተደስተን ነበር! የአምላክ ቃል ቀደም ሲል ጠላቶች የነበሩ ሰዎችን ወንድማማቾችና የሚቀራረቡ ወዳጆች እንዲሆኑ የማድረግ ኃይል አለው!
የሚያሳዝነው ለ14 ዓመታት ያክል በተጓዥነት ሥራ ካሳለፍኩ በኋላ ጤንነቴ እየተቃወሰ በመምጣቱ ለማቆም ተገደድኩ። ይሁን እንጂ እኔም ሆንኩ ባለቤቴ አቅማችን በፈቀደ መጠን ይሖዋን በተሻለ ሁኔታ ማገልገላችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርገን ነበር። ስለዚህ በምሥራቅ ፈረንሳይ ሙልሃውስ በሚባል መንደር መኖሪያ ቤትና ሥራ ስላገኘን አቅኚዎች (ሙሉ ጊዜ አገልጋዮች) ሆንን።
ባሳለፍኳቸው ዓመታት ሌላው ትልቅ ደስታ የሰጠኝ ነገር በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ላይ መካፈሌ ነው። በ1985 ለምሥራቅ ፈረንሳይ አንድ የግንባታ ቡድን እንዳደራጅ ተጠይቄ ነበር። ችሎታ ያላቸውን ባለሙያዎች በመጠቀምና ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን በማሰልጠን ከ80 የሚበልጡ አዳራሾችን ለይሖዋ አምልኮ ብቁ እንዲሆኑ በመሥራት ወይም በማደስ ሥራ ለመካፈል የበቃ ቡድን ለማደራጀት ችለን ነበር። እንዲሁም በ1993 በደቡብ አሜሪካ በምትገኘው በፍሬንች ጊያና አንድ የትልቅ ስብሰባ አዳራሽና አምስት የመንግሥት አዳራሾች ግንባታ ሥራ ተካፋይ ለመሆን በመቻሌ ተደስቼ ነበር!
ፈተናዎች ቢኖሩም ወደፊት መግፋት
በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች በመካፈል ባሳለፍኳቸው ባለፉት 50 ዓመታት ሕይወቴ በሚያስደስቱ ነገሮችና በአገልግሎት መብቶች የተሞላ ነበር በማለት በእርግጠኝነት ለመናገር እችላለሁ። የሚያሳዝነው ለ43 ዓመታት አብሬያት የኖርኩት ውዷ ባለቤቴ በታኅሣሥ 1995 ሞተች። አሁንም ገና ኃዘኔ ባይወጣልኝም ይሖዋ ጥንካሬ ይሰጠኛል፤ መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼም ሥቃዬን የሚያቃልል ፍቅርና ድጋፍ ሰጥተውኛል።
በ1963 በጀርመን ሚዩኒክ በተካሄደ አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ አንድ ቅቡዕ ወንድም የተናገራቸውን ቃላት አሁንም አስታውሳለሁ። እንዲህ አለኝ:- “አንድሬ ወደ ግራም ወደ ቀኝም አትመልከት። በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ የነበሩ ወንድሞች ብዙ ፈተናዎችን አሳልፈዋል። አሁን ሥራውን መቀጠሉ የእኛ ፈንታ ነው። ስለ ራሳችን ማዘን የለብንም። ስለዚህ ወደፊት ግፋ!” ይህን ቃል ፈጽሞ አልረሳውም። በአሁኑ ጊዜ በጤና ማጣትና በዕድሜ መግፋት ምክንያት ብዙ ለመሥራት ባልችልም በዕብራውያን 6:10 ላይ የሚገኙት ቃላት የማያቋርጥ የመጽናናት ምንጭ ሆነውልኛል:- “እግዚአብሔር ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና።” አዎን፣ በይሖዋ አገልግሎት መካፈል አንድ ሰው ሊያገኘው የሚችለው ከሁሉ የሚበልጥ መብት ነው። ላለፉት 50 ዓመታት የነበረኝና አሁንም ቢሆን ያለኝ ግብ ‘የማያሳፍር ሠራተኛ’ መሆን ነው።—2 ጢሞቴዎስ 2:15
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኖርዌይ ገደላማ የባሕር ወሽመጥ ውስጥ እጠቀምበት የነበረው መርከብ ይህን የሚመስል ነበር
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሰሜን ፈረንሳይ በቢስክሌት መስበክ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የተደራረቡ ቦርሳዎች ለሕዝብ ንግግር ተናጋሪው እንደ አትራኖስ ሆነው አገልግለዋል
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1952 ከባለቤቴ ከዣኔት ጋር ስንጋባ