የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 1/15 ገጽ 15-20
  • ታማኝ እጆችን እያነሣችሁ ጸልዩ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ታማኝ እጆችን እያነሣችሁ ጸልዩ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ከመጸለያችሁ በፊት በጥሞና አስቡ
  • አምላክን በታላቅ አክብሮት መቅረብ
  • በትሕትና መንፈስ ጸልዩ
  • ከልባችሁ ጸልዩ
  • ምስጋናንና ውዳሴን አትዘንጉ
  • ለመጸለይ ፈጽሞ ሐፍረት አይሰማችሁ
  • በጸሎት ተጽናኑ
  • ታማኞች በጸሎት ይጸናሉ
  • የምታቀርበው ጸሎት ስለ አንተ ምን ይገልጻል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • ሳናቋርጥ መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • ከአምላክ ጋር መቀራረብ የምትችለው እንዴት ነው?
    ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት
  • በጸሎት አማካኝነት ከአምላክ ጋር ያለህን ዝምድና አጠናክር
    ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 1/15 ገጽ 15-20

ታማኝ እጆችን እያነሣችሁ ጸልዩ

“ወንዶች በስፍራ ሁሉ አለ ቁጣና አለ ክፉ አሳብ [“አለ ክርክር፣” NW] የተቀደሱትን [“ታማኞቹን፣” NW] እጆች እያነሡ እንዲጸልዩ እፈቅዳለሁ።”​—⁠1 ጢሞቴዎስ 2:​8

1, 2. (ሀ) የይሖዋ ሕዝቦችን በተመለከተ በሚቀርበው ጸሎት ረገድ 1 ጢሞቴዎስ 2:​8 የሚሠራው እንዴት ነው? (ለ) ከዚህ ቀጥሎ የምንመረምረው ነገር ምንድን ነው?

ይሖዋ ሕዝቦቹ ለእሱም ሆነ አንዳቸው ለሌላው ታማኞች እንዲሆኑ ይፈልጋል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሎ በጻፈ ጊዜ ታማኝነትን ከጸሎት ጋር አያይዞ ገልጿል:- “ወንዶች በስፍራ ሁሉ አለ ቊጣና አለ ክፉ አሳብ [“አለ ክርክር፣” NW] የተቀደሱትን [“ታማኞቹን፣” NW] እጆች እያነሡ እንዲጸልዩ እፈቅዳለሁ።” (1 ጢሞቴዎስ 2:​8) ጳውሎስ ክርስቲያኖች በአንድነት በሚሰበሰቡበት “ስፍራ ሁሉ” በሕዝብ ፊት ስለሚቀርበው ጸሎት መናገሩ ይመስላል። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የአምላክን ሕዝቦች ወክለው የሚጸልዩት እነማን ነበሩ? በአምላክ ፊት ያሉባቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታዎች በሙሉ በሚገባ ያሟሉ ቅዱሳን፣ ጻድቃንና ጥልቅ አክብሮት ያላቸው ሰዎች ብቻ ነበሩ። (መክብብ 12:​13, 14) መንፈሳዊም ሆነ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናቸውን መጠበቅ እንዲሁም በማያጠያይቅ መንገድ ለይሖዋ አምላክ ያደሩ መሆን ነበረባቸው።

2 በተለይ የጉባኤ ሽማግሌዎች ‘ታማኝ እጆችን በማንሣት መጸለይ’ አለባቸው። በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት የሚያቀርቡት ልባዊ ጸሎት ለአምላክ ያላቸውን ታማኝነት የሚያንጸባርቅ ከመሆኑም በላይ ክርክርንና ቁጣን ለማስወገድ ይረዳቸዋል። እርግጥ ነው፣ ክርስቲያን ጉባኤን ወክሎ በሕዝብ ፊት የመጸለይ መብት የሚሰጠው ማንኛውም ወንድ የማይቆጣ፣ ሌሎችን በክፉ ዓይን የማይመለከት እንዲሁም በይሖዋና በድርጅቱ ላይ የክህደት ድርጊት የማይፈጽም መሆን ይኖርበታል። (ያዕቆብ 1:​19, 20) ሌሎችን ወክለው በሕዝብ ፊት የመጸለይ መብት የሚያገኙ ወንዶች ሊከተሏቸው የሚገቡ ምን ተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መምሪያዎች አሉ? በግልም ሆነ በቤተሰብ ደረጃ ስንጸልይ ተግባራዊ ልናደርጋቸው የሚገቡ አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችስ የትኞቹ ናቸው?

ከመጸለያችሁ በፊት በጥሞና አስቡ

3, 4. (ሀ) በሕዝብ ፊት ከመጸለያችን በፊት በጥሞና ማሰባችን ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ቅዱሳን ጽሑፎች የጸሎትን ርዝማኔ በተመለከተ ምን የሚያመለክቱት ነገር አለ?

3 በሕዝብ ፊት እንድንጸልይ ከተጠየቅን ስለምንጸልየው ነገር በጥቂቱም ቢሆን አስቀድመን ማሰባችን እንደማይቀር የታወቀ ነው። እንዲህ ማድረጋችን ጸሎታችን ያልተንዛዛና ምንም መጨበጫ የሌለው ከመሆን ይልቅ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንዲሆን ይረዳናል። እርግጥ፣ በግል ስንጸልይም ድምፃችንን ከፍ አድርገን መጸለይ እንችላለን። በግል የምናቀርበውን ጸሎት የፈለግነውን ያህል ልናስረዝመው እንችላለን። ኢየሱስ 12 ሐዋርያቱን ከመምረጡ በፊት ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልይ አድሯል። ይሁን እንጂ የሞቱን መታሰቢያ በዓል ባቋቋመበት ጊዜ ለቂጣውና ለወይኑ ያቀረባቸው ጸሎቶች አጠር ያሉ ሳይሆኑ አይቀሩም። (ማርቆስ 14:​22–24፤ ሉቃስ 6:​12–16) ኢየሱስ ያቀረባቸው አጫጭር ጸሎቶችም በአምላክ ዘንድ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት እንደነበራቸው እናውቃለን።

4 ለምሳሌ ያህል በማዕድ ፊት የቀረበን አንድ ቤተሰብ በጸሎት የመወከል መብት ተሰጠን እንበል። እንዲህ ዓይነቱ ጸሎት አጠር ያለ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም በጸሎቱ ላይ ምንም ጠቀስን ምን ለምግቡ ያለንን የአመስጋኝነት መንፈስ የሚገልጽ ቃል መካተት ይኖርበታል። በአንድ ክርስቲያናዊ ስብሰባ መክፈቻ ወይም መደምደሚያ ላይ በሕዝብ ፊት የምንጸልይ ከሆነ ብዙ ነጥቦችን ያካተተ ረጅም ጸሎት ማቅረብ አያስፈልገንም። ኢየሱስ ‘ለማመካኘት ሲሉ ጸሎታቸውን የሚያስረዝሙትን’ ጻፎች አውግዟቸዋል። (ሉቃስ 20:​46, 47) ፈሪሃ አምላክ ያለው ሰው እንዲህ ማድረግ የለበትም። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ በሕዝብ ፊት ረዘም ያለ ጸሎት ማቅረብ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል በአንድ ትልቅ ስብሰባ መደምደሚያ ላይ እንዲጸልይ የተጋበዘ አንድ ሽማግሌ ስለሚጸልየው ነገር አስቀድሞ በጥሞና ማሰብ ያለበት ከመሆኑም በተጨማሪ የተወሰኑ ነጥቦችን መጥቀስ ይፈልግ ይሆናል። ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ ጸሎትም እንኳ ከልክ በላይ መርዘም የለበትም።

አምላክን በታላቅ አክብሮት መቅረብ

5. (ሀ) በሕዝብ ፊት በምንጸልይበት ጊዜ በአእምሯችን ልንይዘው የሚገባው ነገር ምንድን ነው? (ለ) በረጋ መንፈስና በአክብሮት መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?

5 በሕዝብ ፊት በምንጸልይበት ጊዜ ጸሎታችንን የምናቀርበው ለሰብዓዊ ፍጡራን እንዳልሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። ከዚህ ይልቅ ሉዓላዊውን ጌታ ይሖዋን የምንለምን ኃጢአተኛ ፍጥረታት ነን። (መዝሙር 8:​3–5, 9፤ 73:​28) ስለዚህ በምንናገረው ነገርና በአነጋገራችን እንዳናሳዝነው አክብሮታዊ ፍርሃት ማሳየት አለብን። (ምሳሌ 1:​7) መዝሙራዊው ዳዊት “እኔ ግን በምሕረትህ ብዛት ወደ ቤትህ እገባለሁ፤ አንተን በመፍራት ወደ ቅድስናህ መቅደስ እሰግዳለሁ” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 5:​7) እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ካለን በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ በሕዝብ ፊት እንድንጸልይ በምንጠየቅበት ጊዜ ሐሳባችንን የምንገልጸው እንዴት ነው? በአንድ ሰብዓዊ ንጉሥ ፊት በምንናገርበት ጊዜ በአክብሮትና በረጋ መንፈስ እንደምንናገር የታወቀ ነው። የምንጸልየው “የዘላለም ንጉሥ [NW]” ለሆነው ለይሖዋ እንደመሆኑ መጠን ጸሎታችን ይበልጥ አክብሮት የሚንጸባረቅበት መሆን አይገባውምን? (ራእይ 15:​3) ስለዚህ በምንጸልይበት ጊዜ “እንደምን አደርክ፣ ይሖዋ፣” “ፍቅራዊ ሰላምታችን ይድረስህ፣” ወይም ደግሞ “መልካም ቀን” የሚሉትን የመሰሉ አነጋገሮች አንጠቀምም። የአምላክ አንድያ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ሰማያዊ አባቱን በዚህ መንገድ አነጋግሮ እንደማያውቅ ቅዱሳን ጽሑፎች ያሳያሉ።

6. ‘ወደ ጸጋው ዙፋን በምንቀርብበት’ ጊዜ ምን ነገር በአእምሯችን መያዝ አለብን?

6 ጳውሎስ “ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት [“የመናገር ነፃነት ተሰምቶን፣” NW] እንቅረብ” ሲል ተናግሯል። (ዕብራውያን 4:​16) ኃጢአተኞች ብንሆንም እንኳ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት የምናምን በመሆኑ ይሖዋን “የመናገር ነፃነት ተሰምቶን” ልንቀርበው እንችላለን። (ሥራ 10:​42, 43፤ 20:​20, 21) ሆኖም “የመናገር ነፃነት” ሊሰማን ይገባል ሲባል የባጥ የቆጡን ሁሉ እናወራለታለን ወይም ደግሞ አክብሮት የጎደለው ነገር እንናገራለን ማለት አይደለም። በሕዝብ ፊት የምናቀርባቸው ጸሎቶች አምላክን የሚያስደስቱ እንዲሆኑ ከተፈለገ ተገቢውን አክብሮት በሚያንጸባርቅና በረጋ መንፈስ መቅረብ አለባቸው፤ በተጨማሪም ማስታወቂያ ለመን​ገር፣ ግለሰቦችን ለመምከር ወይም ደግሞ አድማጮችን ለመገሰጽ ልንጠቀምባቸው አይገባም።

በትሕትና መንፈስ ጸልዩ

7. ሰሎሞን የይሖዋ ቤተ መቅደስ ለአምላክ አገልግሎት በተወሰነበት ሥነ ሥርዓት ላይ ሲጸልይ ትሕትና ያሳየው እንዴት ነው?

7 በሕዝብ ፊትም ሆነ በግላችን በምንጸልይበት ጊዜ ጸሎቶቻችን የትሕትናን ዝንባሌ የሚያንጸባርቁ መሆን እንዳለባቸው የሚያመለክተውን አስፈላጊ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓት በአእምሯችን ልንይዝ ይገባል። (2 ዜና መዋዕል 7:​13, 14) ንጉሥ ሰሎሞን በኢየሩሳሌም የተሠራው የይሖዋ ቤተ መቅደስ ለይሖዋ አገልግሎት በተወሰነበት ሥነ ሥርዓት በሕዝብ ፊት ባቀረበው ጸሎት ላይ ትሕትና አሳይቷል። ሰሎሞን በምድር ላይ ከተገነቡት እጹብ ድንቅ ሕንፃዎች መካከል አንዱን ገንብቶ መጨረሱ ነበር። ሆኖም በትሕትና እንዲህ ሲል ጸልዮአል:- “እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፣ ሰማይ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ይልቁንስ እኔ የሠራሁት ቤት እንዴት ያንስ!”​—⁠1 ነገሥት 8:​27

8. በሕዝብ ፊት ስንጸልይ ትሕትና ማሳየት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

8 ሌሎችን ወክለን በሕዝብ ፊት በምንጸልይበት ጊዜ ልክ እንደ ሰሎሞን ትሑቶች መሆን አለብን። የግብዝነት መንፈስ በሚያንጸባርቅ መንገድ መጸለይ ባይኖርብንም እንኳ የድምፃችን ቃና ትሕትናችንን ሊያሳይ ይችላል። ትሕትና የተሞላበት ጸሎት በተራቀቀ አማርኛ ወይም ደግሞ በተጋነኑ ቃላት የሚቀርብ አይደለም። የሰዎችን ትኩረት የሚስበው ጸሎቱን ወደሚያቀርበው ሰው ሳይሆን ጸሎቱ ወደሚቀርብለት አካል ነው። (ማቴዎስ 6:​5) በተጨማሪም ትሕትና በጸሎታችን ውስጥ በምንናገራቸው ነገሮችም ላይ ይንጸባረቃል። በትሕትና የም​ንጸልይ ከሆነ አምላክ አንዳንድ ነገሮችን እኛ በፈለግነው መንገድ እንዲያከናውን እንደምንጠይቅ በሚያሳይ መንገድ አንጸልይም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ከቅዱስ ፈቃዱ ጋር የሚስማማ እርምጃ እንዲወስድ እንለምነዋለን። መዝሙራዊው “አቤቱ፣ እባክህ፣ አሁን አድን፤ አቤቱ፣ እባክህ፣ አሁን አቅና” ብሎ በተማጸነ ጊዜ ትክክለኛውን አመለካከት በሚገባ አሳይቷል።​—⁠መዝሙር 118:​25፤ ሉቃስ 18:​9–14

ከልባችሁ ጸልዩ

9. ኢየሱስ በማቴዎስ 6:​7 ላይ ምን ግሩም ምክር ሰጥቷል? ይህን ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለውስ እንዴት ነው?

9 በሕዝብ ፊትም ሆነ በግል የምንጸልያቸው ጸሎቶች አምላክን እንዲያስደስቱ ከተፈለገ ከልብ የመነጩ መሆን አለባቸው። እንደዚያ ከሆነ እየተናገርነው ስላለነው ነገር ምንም ሳናስብ ነጋ ጠባ በዘልማድ አንጸልይም። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል:- “አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደ እነርሱ በከንቱ አትድገሙ።” በሌላ አነጋገር ኢየሱስ “ባዶ ቃላት አትደርድሩ፤ ትርጉም የለሽ ድግግሞሽ አስወግዱ” ብሏል።​—⁠ማቴዎስ 6:​7፤ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ

10. ስለ አንድ ነገር ከአንድ ጊዜ በላይ መጸለይ ተገቢ የሚሆነው ለምንድን ነው?

10 እርግጥ ስለ አንድ ጉዳይ በተደጋጋሚ መጸለይ ሊያስፈልገን ይችላል። ይህ ስህተት አይ​ደለም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ “ሳታቋርጡ ለምኑ፣ ይሰጣችሁማል፤ ሳታቋርጡ ፈልጉ፣ ታገኙማላችሁ፤ ሳታ​ቋርጡ መዝጊያን አንኳኩ፣ ይከፈትላችሁማል” ሲል አጥብቆ አሳስቧል። (ማቴዎስ 7:​7 NW) ምናልባት ይሖዋ በአካባቢው ያለውን የስብከት ሥራ እየባረከው በመሆኑ አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ያስፈልግ ይሆናል። (ኢሳይያስ 60:​22) በግል ስንጸልይም ሆነ በይሖዋ ሕዝቦች ስብሰባዎች ላይ በሕዝብ ፊት በምንጸልይበት ጊዜ አዘውትረን ይህን ነገር መጥቀሳችን ተገቢ ነው። እንዲህ ማድረጋችን ‘ትርጉም የለሽ ድግግሞሽ አበዛን’ ማለት አይደለም።

ምስጋናንና ውዳሴን አትዘንጉ

11. ፊልጵስዩስ 4:​6, 7 በግልም ሆነ በሕዝብ ፊት በምናቀርበው ጸሎት ረገድ የሚሠራው እንዴት ነው?

11 ብዙ ሰዎች የሚጸልዩት የሆነ ነገር ለመለመን ብቻ ነው፤ ሆኖም ለይሖዋ አምላክ ያለን ፍቅር በግልም ሆነ በሕዝብ ፊት በምንጸልይበት ጊዜ እንድናመሰግነውና እንድናወድሰው ሊገፋፋን ይገባል። ጳውሎስ “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል” ሲል ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 4:​6, 7) አዎን፣ ከምልጃና ከልመና በተጨማሪ ለመንፈሳዊና ለሥጋዊ በረከቱ ይሖዋን ማመስገን አለብን። (ምሳሌ 10:​22) መዝሙራዊው “ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት ሠዋ፣ ለልዑልም ስእለትህን ስጥ” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 50:​14) በተጨማሪም በዜማ የቀረበው የዳዊት ጸሎት የሚከተሉትን ልብ የሚነኩ ቃላት የያዘ ነው:- “የእግዚአብሔርን ስም በዝማሬ አመሰግናለሁ፣ በምስጋናም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ።” (መዝሙር 69:​30) በሕዝብ ፊትም ሆነ በግል በምንጸልይበት ጊዜ እንዲህ ማድረግ አይኖርብንምን?

12. መዝሙር 100:​4, 5 በዛሬው ጊዜ እየተፈጸመ ያለው እንዴት ነው? ከዚህ ጋር በተያያዘ አምላክን ስለ ምን ነገር ልናመሰግነውና ልናወድሰው እንችላለን?

12 መዝሙራዊው አምላክን በተመለከተ እንዲህ ሲል ዘምሯል:- “ወደ ደጆቹ በመገዛት፣ ወደ አደባባዮቹም በምስጋና ግቡ፤ አመስግኑት፣ ስሙንም ባርኩ፤ እግዚአብሔር ቸር፣ ምሕረቱም ለዘላለም፣ እውነቱም ለልጅ ልጅ ነውና።” (መዝሙር 100:​4, 5) በዛሬው ጊዜ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች ወደ ይሖዋ መቅደስ አደባባዮች እየገቡ በመሆኑ ይሖዋን ልናወድሰውና ልናመሰግነው እንችላለን። ስለ ጉባኤያችሁ የመንግሥት አዳራሽ አምላክን ታመሰግነዋለህን? አምላክን ከሚወዱ ሰዎች ጋር አዘውትረህ በመንግሥት አዳራሹ በመሰብሰብ አድናቆትህን ታሳያለህን? በስብሰባውም ላይ ለአፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን የሚቀርቡትን የውዳሴና የምስጋና መዝሙሮች ድምፅህን ከፍ አድርገህ ከልብህ ትዘምራለህን?

ለመጸለይ ፈጽሞ ሐፍረት አይሰማችሁ

13. በጥፋተኝነት ስሜት የተነሳ ምንም ዋጋ እንደሌለን ሆኖ በሚሰማን ጊዜ እንኳ ይሖዋን መለመን እንዳለብን የሚያሳየው የትኛው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌ ነው?

13 በጥፋተኝነት ስሜት የተነሳ ምንም ዋጋ እንደሌለን ሆኖ በሚሰማን ጊዜም እንኳ ወደ አምላክ ዞር ብለን ልባዊ ምልጃ ማቅረብ አለብን። አይሁዶች ባዕድ ሚስቶችን በማግባት ኃጢአት በሠሩ ጊዜ ዕዝራ ተንበርክኮ ታማኝ እጆቹን ወደ አምላክ ዘረጋና በትሕትና እንዲህ ሲል ጸለየ:- “አምላኬ ሆይ፣ ኃጢአታችን በራሳችን ላይ በዝቶአልና፣ በደላችንም ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ ብሎአልና አምላኬ ሆይ፣ ፊቴን ወደ አንተ አነሣ ዘንድ አፍራለሁ፣ እፈራማለሁ። ከአባቶቻችን ዘመን ጀምረን እስከ ዛሬ ድረስ እጅግ በድለናል፤ . . . ስለ ክፉ ሥራችንና ስለ ታላቁ በደላችን ካገኘን ነገር ሁሉ በኋላ፣ አንተ አምላካችን እንደ ኃጢአታችን ብዛት አልቀሠፍኸንም ነገር ግን ቅሬታን ሰጠኸን። በውኑ ተመልሰን ትእዛዝህን እናፈርስ ዘንድ፣ ርኩስ ሥራን ከሚሠሩ ከእነዚህም አሕዛብ ጋር እንገባ ዘንድ ይገባናልን? አንተስ ቅሬታ የሌለንና የማናመልጥ እስክንሆን ድረስ እንድታጠፋን አትቆጣምን? አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ፣ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ዛሬም እንደ ሆነው እኛ አምልጠን ቀርተናል፤ እነሆ በፊትህ በበደላችን አለን፤ ስለዚህ በፊትህ ሊቆም የሚችል የለም።”​—⁠ዕዝራ 9:​1–15፤ ዘዳግም 7:​3, 4

14. በዕዝራ ዘመን እንደታየው የአምላክን ምሕረት ለማግኘት የሚያስፈልገው ነገር ምንድን ነው?

14 የአምላክን ይቅርታ ለማግኘት ለእሱ ከመናዘዝም በተጨማሪ መጸጸትና “ለንስሐ የሚገባ ፍሬ” ማፍራት ያስፈልጋል። (ሉቃስ 3:​8፤ ኢዮብ 42:​1–6፤ ኢሳይያስ 66:​2) በዕዝራ ዘመን የንስሐ ዝንባሌ ባዕድ የሆኑትን ሚስቶች በማሰናበት የተፈጸመውን ስህተት ለማስተካከል በተደረገ ጥረት የታገዘ ነበር። (ዕዝራ 10:​44፤ ከ2 ቆሮንቶስ 7:​8–13 ጋር አወዳድር።) የሠራነውን ከባድ ኃጢአት አምላክ ይቅር እንዲለን ከፈለግን ትሕትና በተሞላበት መንገድ በጸሎት ከተናዘዝን በኋላ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ እናፍራ። በተጨማሪም የንስሐ መንፈስና የሠራነውን ስህተት ለማስተካከል ያለን ፍላጎት የክርስቲያን ሽማግሌዎችን መንፈሳዊ እርዳታ እንድንሻ ይገፋፋናል።​—⁠ያዕቆብ 5:​13–15

በጸሎት ተጽናኑ

15. የሐና ተሞክሮ በጸሎት ልንጽናና እንደምንችል የሚያሳየው እንዴት ነው?

15 ልባችን በሆነ ምክንያት በሐዘን ሲዋጥ በጸሎት አማካኝነት ልንጽናና እንችላለን። (መዝሙር 51:​17፤ ምሳሌ 15:​13) ታማኟ ሐና በዚህ መንገድ ተጽናንታለች። ትኖር የነበረው በእስራኤል ምድር ብዙ ልጆች መውለድ የተለመደ በነበረበት ዘመን ቢሆንም አንድም ልጅ አልወለደችም ነበር። ባልዋ ሕልቃና ከሌላኛዋ ሚስቱ ከፍናና ወንዶችና ሴቶች ልጆች ወልዶ ነበር። ሐና መካን በመሆኗ ፍናና ትሳለቅባት ነበር። ሐና ከልቧ በመጸለይ አምላክ ወንድ ልጅ በመስጠት ከባረካት ‘ዕድሜውን ሙሉ ለይሖዋ እንደምትሰጠው’ ቃል ገባች። በጸሎቷና በሊቀ ካህናቱ በዔሊ ቃላት በመጽናናቷ ‘ሐዘንዋን አቆመች።’ ወንድ ልጅ ወለደችና ሳሙኤል ብላ ጠራችው። ከጊዜ በኋላ በይሖዋ ቤተ መቅደስ እንዲያገለግል ሰጠችው። (1 ሳሙኤል 1:​9–28) አምላክ ላሳያት ደግነት አመስጋኝ በመሆን ባቀረበችው የምስጋና ጸሎት ይሖዋ አቻ የማይገኝለት እንደሆነ በመግለጽ አወድሳዋለች። (1 ሳሙኤል 2:​1–10) ልክ እንደ ሐና እኛም አምላክ ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ መንገድ ለሚቀርብለት ጥያቄ ሁሉ መልስ እንደሚሰጥ በመተማመን በጸሎት ልንጽናና እንችላለን። ሸክማችንን የሚያስወግድልን ወይም ደግሞ እንድንችለው የሚረዳን በመሆኑ ልባችንን ካፈሰስንለት በኋላ ‘ሐዘንተኛ መስለን መታየት የለብንም።’​—⁠መዝሙር 55:​22

16. በያዕቆብ ሁኔታ እንደታየው በምንፈራበት ወይም በምንጨነቅበት ጊዜ መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?

16 አንድ ሁኔታ ፍርሃት፣ የልብ ሐዘን ወይም ደግሞ ጭንቀት ከፈጠረብን በጸሎት ለመጽናናት ወደ ይሖዋ ዞር ከማለት ወደ ኋላ አንበል። (መዝሙር 55:​1–4) ያዕቆብ ተለይቶት ከነበረው ወንድሙ ከዔሳው ጋር ሊገናኝ ሲል በጣም ፈርቶ ነበር። ሆኖም ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጸለየ:- “የአባቴ የአብርሃም አምላክ ሆይ፣ የአባቴም የይስሐቅ አምላክ ሆይ:- ወደ ምድርህ ወደ ተወለድህበትም ስፍራ ተመለስ፣ በጎነትንም አደርግልሃለሁ ያልኸኝ እግዚአብሔር ሆይ፤ ለባሪያህ ከሠራኸው ከምሕረትህና ከእውነትህም ሁሉ ትንሽ ስንኳ የማይገባኝ ነኝ፤ በትሬን ብቻ ይዤ ይህን ዮርዳኖስን ተሻግሬ ነበርና፣ አሁን ግን የሁለት ክፍል ሠራዊት ሆንሁ። ከወንድሜ ከዔሳው እጅ አድነኝ፤ መጥቶ እንዳያጠፋኝ፣ እናቶችንም ከልጆች ጋር እንዳያጠፋ እኔ እፈራዋለሁና። አንተም:- በእርግጥ መልካም አደርግልሃለሁ፣ ዘርህንም ከብዛቱ የተነሣ እንደማይቆጠር እንደ ባሕር አሸዋ አደርጋለሁ ብለህ ነበር።” (ዘፍጥረት 32:​9–12) ዔሳው ያዕቆብንም ሆነ አብረውት የነበሩትን ሰዎች አልነካም። በመሆኑም ይሖዋ በወቅቱ ለያዕቆብ ‘መልካም አድርጎለታል።’

17. ከባድ ፈተና በሚደርስብን ጊዜ ጸሎት ከመዝሙር 119:​52 ጋር በሚስማማ መንገድ ሊያጽናናን የሚችለው እንዴት ነው?

17 ምልጃ በምናቀርብበት ጊዜ በአምላክ ቃል ውስጥ የተነገሩትን ነገሮች በማስታወስ ልንጽናና እንችላለን። በረጅሙ መዝሙር ላይ በዜማ የተቀናበረ አንድ ግሩም ጸሎት ይገኛል። መዝሙሩን የዘመረው መስፍኑ ሕዝቅያስ ሳይሆን አይቀርም:- “ከጥንት የነበረውን ፍርድህን አሰብሁ፣ አቤቱ፣ ተጽናናሁም።” (መዝሙር 119:​52) ከባድ ፈተና በሚደርስብን ጊዜ ትሕትና በሞላበት መንገድ መጸለያችን ሰማያዊ አባታችንን እያስደሰትን እንዳለን እንዲሰማን የሚያደርግ ጎዳና እንድንከተል ሊረዳን የሚችል የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ወይም ሕግ እንድናስታውስ ሊያደርገን ይችላል።

ታማኞች በጸሎት ይጸናሉ

18. ‘ታማኝ ሁሉ ወደ አምላክ ይጸልያል’ ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

18 ለይሖዋ አምላክ ታማኝ የሆኑ ሁሉ ‘በጸሎት ይጸናሉ።’ (ሮሜ 12:​12) ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ኃጢአት ከሠራ በኋላ የተቀናበረ ሊሆን ይችላል ተብሎ በሚገመተው በ32ኛው መዝሙር ላይ ይቅርታ ባለመጠየቁ የተሰማውን ሥቃይ እንዲሁም ንስሐ መግባቱና ለአምላክ መናዘዙ ያስገኘለትን እፎይታ ገልጿል። ዳዊት በመቀጠል እንዲህ ሲል ዘምሯል:- “ስለዚህ [ከልባቸው ንስሐ የሚገቡ ሁሉ የይሖዋን ምሕረት የሚያገኙ በመሆኑ] ቅዱስ [“ታማኝ፣” NW] ሁሉ በምቹ ጊዜ ወደ አንተ ይለምናል።”​—⁠መዝሙር 32:​6

19. ታማኝ እጆችን በማንሣት መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?

19 ከይሖዋ አምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ከፍ አድርገን የምንመለከት ከሆነ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት እንዲምረን እንጸልያለን። ምሕረትና ወቅታዊ እርዳታ ለማግኘት የመናገር ነፃነት ተሰምቶን ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት ልንቀርብ እንችላለን። (ዕብራውያን 4:​16) ሆኖም የምንጸልይባቸው ሌሎች ብዙ ምክንያቶች አሉ! እንግዲያው ከልብ በመነጩ የውዳሴና የምስጋና ቃላት ‘ሳናቋርጥ እንጸልይ።’ (1 ተሰሎንቄ 5:​17) ታማኝ እጆችን በማንሳት ቀን ከሌት እንጸልይ።

[ምን ብለህ ትመልሳለህ?]

◻ በሕዝብ ፊት ከመጸለያችን በፊት በጥሞና ማሰባችን ምን ጥቅም አለው?

◻ በረጋ መንፈስና አክብሮት በተሞላበት መንገድ መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?

◻ ስንጸልይ ምን ዓይነት መንፈስ ማንጸባረቅ አለብን?

◻ ስንጸልይ ምስጋናንና ውዳሴን መዘንጋት የሌለብን ለምንድን ነው?

◻ መጽሐፍ ቅዱስ በጸሎት ልንጽናና እንደምንችል የሚያሳየው እንዴት ነው?

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ንጉሥ ሰሎሞን የይሖዋ ቤተ መቅደስ ለአምላክ አገልግሎት በተወሰነበት ሥነ ሥርዓት ላይ በሕዝብ ፊት ሲጸልይ ትሕትና አሳይቷል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልክ እንደ ሐና አንተም በጸሎት ልትጽናና ትችላለህ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ