“ባለ ሐር ፀጉሯ የሶርያ በረሃ እመቤት”
መልኳ የቀይ ዳማ፣ ጥርሷ እንደ በረዶ የነጣ፣ ዓይኖቿ ጥቁርና እንደ ኮከብ የሚያበሩ ናቸው። የተማረችና በቋንቋ ችሎታዋም የተካነች ነበረች። ይህቺ ተዋጊ ንግሥት በእውቀቷ ክሊዮፓትራን የምታስንቅ በውበቷም ቢሆን ከእርሷ የማትተናነስ እንደሆነች ይነገርላታል። በዘመኗ የነበሩትን የዓለም ኃያላን በድፍረት በመቋቋሟ በቅዱስ ጽሑፋዊ ድራማ ውስጥ ትንቢታዊ ሚና ሊኖራት ችሏል። ከሞተች ከረጅም ጊዜ በኋላ ደራሲያን በብዕራቸው አወድሰዋታል ሰዓሊያን በብሩሻቸው ውብ አድርገው ስለዋታል። አንድ የ19ኛው መቶ ዘመን ባለቅኔ “ባለ ሐር ፀጉሯ የሶርያ በረሃ እመቤት” ሲል ገልጿታል። ይህን ያህል አድናቆት የተቸራት ይህች ሴት የሶሪያዋ ከተማ የፓልሚራ ንግሥት ዘኖቢያ ናት።
ዘኖቢያ እንዲህ ገናና ስም ልታተርፍ የቻለችው እንዴት ነው? ሥልጣን ላይ እንድትወጣ ያስቻላት ፖለቲካዊ ሁኔታ ምን ነበር? ባሕርይዋንስ በሚመለከት ምን ማለት ይቻላል? ይህች ንግሥት የነበራት ትንቢታዊ ሚናስ ምንድን ነበር? በመጀመሪያ ግን ድራማው የሚከናወንበትን መልከዓ ምድራዊ መቼት ተመልከት።
በበረሃ ዳርቻ የምትገኝ ከተማ
የዘኖቢያ ከተማ የሆነችው ፓልሚራ ከደማስቆ በስተ ሰሜን ምሥራቅ 210 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የአንቲሊባነን ተራራ አልቆ አውላላ ሜዳ በሚጀምርበት የሶሪያ በረሃ ሰሜናዊ ዳርቻ ላይ የምትገኝ ከተማ ናት። ይህች የበረሃ ገነት የሆነች ከተማ የምትገኘው በምዕራብ ካለው የሜድትራኒያን ባሕርና በምሥራቅ ካለው የኤፍራጥስ ወንዝ መካከል ነው። ንጉሥ ሰሎሞን ተድሞር በሚል ስም የሚያውቃትና በሁለት ምክንያቶች የተነሣ ለመንግሥቱ ደህንነት በጣም ወሳኝ ድርሻ የነበራት ከተማ ነች። እነዚህም ምክንያቶች ለሰሜናዊው ድንበሩ መከታ የሆነች ወታደራዊ ቦታ በመሆኗና በመደዳ ከተቀመጡት ከተሞች መካከል ቁልፍ የሆነ ቦታ ያላት መሆኗ ናቸው። በመሆኑም ሰሎሞን “በምድረ በዳም ያለውን ተድሞር” ሠርቷል።—2 ዜና መዋዕል 8:4
ከንጉሥ ሰሎሞን ግዛት በኋላ ያለው የአንድ ሺህ ዓመት ታሪክ ስለ ተድሞር አንድም የሚናገረው ነገር የለም። ተድሞር የተባለችው ፓልሚራ ናት መባሉ ትክክል ከሆነ ገናና መሆን የጀመረችው ሶሪያ በ64 ከዘአበ የሮማ ግዛት የድንበር ከተማ ከሆነች በኋላ ነበር። ሪቻርድ ስቶንማን ፓልሚራ ኤንድ ኢትስ ኢምፓየር—ዘኖቢያስ ሪቮልት አጌይንስት ሮም በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “ፓልሚራ ለሮም ከሁለት አቅጣጫ ይኸውም ከኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ጠቀሜታ አንጻር እጅግ ቁልፍ ሚና ነበራት” ሲሉ ገልጸዋል። ይህች የዘንባባዎች ከተማ ሮምን ከሜሶጶጣሚያና ከምሥራቅ በሚያገናኘው ዋና የንግድ መስመር ላይ የምትገኝ ሲሆን የጥንቱ ዓለም የንግድ ዕቃዎች ማለትም ከኢስት ኢንዲስ የሚመጣው ቅመማ ቅመም፣ ከቻይና የሚመጣው ሐር እና ከፋርስ ማለትም ከታችኛው ሜሶጶጣሚያ እንዲሁም ከሜዲትራኒያን አገሮች የሚመጡ ሌሎችም ሸቀጣ ሸቀጦች የሚያልፉት በእርሷ በኩል ነበር። የሮም ሕልውና ከውጭ በሚገቡላት በእነዚህ እቃዎች ላይ የተመካ ነበር።
ከወታደራዊ ጠቀሜታ አንጻር ሲታይ ሶሪያ በሁለቱ ባላንጣ ኃይሎች ማለትም በሮምና በፋርስ መካከል ያለች ነፃ ቀጣና ነበረች። እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በነበሩት የመጀመሪያ 250 ዓመታት የኤፍራጥስ ወንዝ ሮምን ከምሥራቃዊ አጎራባቿ የሚለያት ወሰን ነበር። ፓልሚራ የምትገኘው ከበረሃው ባሻገር ከዱራ-ዩሮፖስ ከተማ በስተ ምዕራብ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ ነበር። ቁልፍ ቦታ የተቀመጠች መሆኗን በመገንዘብ እንደ ሃድሪያንና ቫለሪያን ያሉት የሮማ ንጉሠ ነገሥቶች ፓልሚራን ጎብኝተዋል። ሃድሪያን የከተማዋ የንድፍ ውበት እንዲጨምር ከማድረጉም ሌላ በልግስና ብዙ እርዳታ ሰጥቷል። አዲናተስ የተባለው የፓልሚራ ባላባት ማለትም የዘኖቢያ ባል በፋርስ ላይ ዘምቶ ድል ስለተቀዳጀና የሮማ ግዛት እስከ ሜሶጶጣሚያ ድረስ እንዲሰፋ ስላደረገ ቫለሪያን በ258 እዘአ የሮማ ቆንስላ አድርጎ አዲናተስን በመሾም ከፍተኛ ስልጣን ሰጥቶታል። ዘኖቢያ ባሏ ሥልጣን እንዲያገኝ በማድረግ ረገድ ትልቅ ድርሻ ነበራት። ታሪክ ጸሐፊው ኤድዋርድ ጊቦን “ለአዲናተስ ድል ትልቅ ሚና የተጫወተው የእርሷ [የዘኖቢያ] ወደር የለሽ ብልህነትና ጥንካሬ ነው” ሲሉ ጽፈዋል።
ከጊዜ በኋላ የፋርሱ ንጉሥ ሳፖር የሮማን የበላይነት ለመገዳደርና በቀድሞዎቹ የፋርስ ግዛቶች ሁሉ ላይ የበላይነቱን ለማረጋገጥ ቆርጦ ተነሣ። የማይደፈር ሠራዊት ይዞ በመዝመት በምዕራብ በኩል ገስግሶ የሮማ የጦር ይዞታ የነበሩትን ኒሲቢስንና ካሬይን (ሃራንን) በመቆጣጠር ሰሜናዊ ሶሪያንና ኪልቅያን ማውደሙን ተያያዘው። ንጉሠ ነገሥት ቫለሪያን ራሱ ሠራዊቱን በመምራት ወራሪዎቹን ለመመከት ዘምቶ የነበረ ቢሆንም ተሸንፎ በፋርሳውያን ተማረከ።
አዲናተስ ውድ ስጦታዎችንና የሰላም መልእክት ወደ ፋርስ አፄዎች መላኩ እንደሚያዋጣ ተሰምቶት ነበር። ንጉሥ ሳፖር ግን በትዕቢት፣ ስጦታዎቹ ኤፍራጥስ ወንዝ ውስጥ እንዲጣሉና አዲናተስ ራሱ እንደ ምርኮኛ ሆኖ ፊቱ መጥቶ እንዲለምነው አዘዘ። ለዚህ ምላሽ የፓልሚራ ሰዎች የበረሃ ዘላኖችንና የተረፈውን የሮማ ሠራዊት በማሰባሰብ ሠራዊት አቋቁመው ማፈግፈግ ጀምረው የነበሩትን ፋርሳውያን ያጣድፏቸው ገቡ። ዘመቻ ያደከመውና ከዘረፈው ዕቃ የተነሳ ሸክም የበዛበት የሳፖር ሠራዊት የበረሃዎቹን ተዋጊዎች ድንገተኛ ጥቃት መቋቋም ስላልቻለ ለመሸሽ ተገደደ።
በቫለሪያን እግር የተተካው ወንድ ልጁ ጋሌነስ አዲናተስ በሳፖር ላይ የተቀዳጀውን ድል በመመልከት ኮሬክተር ቶቲየስ ኦሪየንቲስ (የምሥራቅ ክፍል ሁሉ ገዥ) የሚል ማዕረግ ሰጠው። ከጊዜ በኋላ ራሱ አዲናተስ ለራሱ “የነገሥታት ንጉሥ” የሚል ማዕረግ ሰጥቷል።
ዘኖቢያ ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛት ለመመሥረት የነበራት ጉጉት
አዲናተስ እጅግ ገንኖ በነበረበት በ267 እዘአ አንድ የወንድሙ ልጅ ምናልባትም በቂም በቀል ተነሳስቶ ሳይሆን አይቀርም አዲናተስንና አልጋ ወራሹን ገደላቸው። ዘኖቢያ ወንድ ልጅዋ ገና ሕፃን ስለነበር የባሏን ሥልጣን ተረከበች። ውበትን የተላበሰችውና ትልቅ ምኞት እንዲሁም የአስተዳደር ብቃት ያላት፣ ከሟቹ ባሏ ጋር አብራ ትዘምት የነበረችውና በርካታ ቋንቋዎችን አቀላጥፋ የምትናገረው ዘኖቢያ የተገዥዎቿን ድጋፍና አክብሮት ማትረፍ ችላ ነበር። ይህ በበድዊን ጎሳዎች ዘንድ ቀላል ግምት የሚሰጠው ነገር አልነበረም። ዘኖቢያ ለትምህርት ፍቅር ስለነበራት ዙሪያዋን የተከበበችው በምሁራን ነበር። ከአማካሪዎቿ መካከል “አንዱ ሕያው ቤተ መጻሕፍትና ተንቀሳቃሽ ቤተ መዘክር” የሚል ስም ያተረፈው የፍልስፍና ምሁሩና ድንቅ ተናጋሪ የነበረው ካሲየስ ሎንጊነስ ነበር። ደራሲ ስቶንማን እንዳሉት:- “አዲናተስ ከሞተ በኋላ ባሉት አምስት ዓመታት ውስጥ . . . ዘኖቢያ የምሥራቅ እመቤት መሆኗን በሕዝቧ ልብ ውስጥ መትከል ችላ ነበር።”
በዘኖቢያ ግዛት በአንደኛው በኩል የነበረው እርሷና ባሏ ያሽመደመዱት ፋርስ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ እየተዳከመ የነበረው የሮም ግዛት ነበር። በዚያን ወቅት በሮም ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛት ስለነበረው ሁኔታ ሲገልጹ ታሪክ ጸሐፊው ጄ ኤም ሮበርትስ እንዲህ ብለዋል:- “ሦስተኛው መቶ ዘመን . . . ለሮም በምሥራቅም ሆነ በምዕራብ ድንበሯ በኩል የተመቸ ነገር አልገጠማትም፤ በውስጥ ደግሞ አዲስ የእርስ በርስ ጦርነትና የሥልጣን ሽኩቻ ተጀምሮ ነበር። ሃያ ሁለት ንጉሠ ነገሥታት (አስመሳዮችን ሳይጨምር) ተቀያይረዋል።” በሌላ በኩል ደግሞ የሶርያዋ እመቤት በግዛቷ እጅግ የተደላደለች ፍጹም አፄያዊ መንግሥት ሆና ነበር። “የሁለት ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛቶችን [የፋርስና ሮምን] የኃይል ሚዛን በመቆጣጠር ሁለቱንም የሚያንበረክክ ሦስተኛ ግዛት የማቋቋም ጉጉት ነበራት” ሲሉ ስቶንማን ተናግረዋል።
በ269 እዘአ የሮማን አገዛዝ የሚቀናቀን አስመሳይ መንግሥት በግብጽ በተነሣ ጊዜ ዘኖቢያ ንጉሣዊ ሥልጣኗን የምታሰፋበት አመቺ አጋጣሚ አገኘች። የዘኖቢያ ሠራዊት በፍጥነት ወደ ግብፅ በመዝመት ዓማፂዎቹን ደምስሶ አገሪቱን ተቆጣጠረ። ራሷን የግብጽ ንግሥት ብላ በመሰየም ስሟ ያለበት ሳንቲም አስቀረጸች። በዚህ ጊዜ የመንግሥቷ ግዛት ከአባይ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ሆነ። “የደቡብ ንጉሥ” ሆና በመጽሐፍ ቅዱሱ የዳንኤል ትንቢት ውስጥ የተጠቀሰችው በዚህ ወቅት ነበር። ምክንያቱም መንግሥቷ ከዳንኤል የትውልድ አገር በስተደቡብ ያለውን ቦታ ተቆጣጥሮ ነበር። (ዳንኤል 11:25, 26) ከዚህም ሌላ አብዛኛውን የትንሿን እስያ ክፍል ተቆጣጥራ ነበር።
ዘኖቢያ መዲናዋ የሆነችውን ፓልሚራን ከሮማውያኑ ዓለም ታላላቅ ከተሞች ጋር እስክትወዳደር ድረስ እጅግ አጠናክራትና አስውባት ነበር። የነዋሪዋ ብዛት 150,000 ደርሶ እንደነበር ይገመታል። የሚያማምሩ የሕዝብ ሕንፃዎች፣ ቤተ መቅደሶች፣ መናፈሻዎች፣ ዓምዶችና ሐውልቶች 21 ኪሎ ሜትር የሚያክል ዙሪያ መጠን ባለው ግንብ የተከበበችውን ከተማ ሞልተዋት ነበር። በዋናው አውራ ጎዳና ላይ እያንዳንዳቸው 15 ሜትር ርዝማኔ ያላቸው 1,500 የቆሮንቶስ ሰዎች የጥበብ ሥራ የሆኑ ዓምዶች ግራና ቀኝ ተሰልፈው ይታዩ ነበር። በከተማዋ ውስጥ በየቦታው የጀግኖችና የባለውለታ ባለጠጎች ሐውልትና የአንገት በላይ ምስል ይገኝ ነበር። በ271 እዘአ ዘኖቢያ የራሷንና የሟቹን ባሏን ምስል አቆመች። ፓልሚራ በበረሃው ዳርቻ እንደ አንድ ውድ ማዕድን ታብረቀርቅ ነበር።
በፓልሚራ ከሚገኙት እጅግ ድንቅ የሕንፃ ሥራዎች መካከል የፀሐይ ቤተ መቅደስ አንዱ ሲሆን በከተማይቱ ውስጥ ከሌሎቹ ሁሉ ጉልህ ሆኖ የሚታይ ሃይማኖታዊ ሥፍራ እንደነበር ምንም አያጠራጥርም። ዘኖቢያም ከፀሐይ አምላክ ጋር የተያያዘ አምልኮ እንደነበራት መገመት ይቻላል። ይሁን እንጂ በሦስተኛው መቶ ዘመን የነበረችው ሶርያ የብዙ ሃይማኖቶች ምድር ነበረች። በዘኖቢያ ግዛት ክርስቲያን ነን ባዮች፣ አይሁዶች፣ ኮከብ ቆጣሪዎችና ፀሐይንና ጨረቃን የሚያመልኩ ሰዎችም ነበሩ። በግዛቷ ስለነበረው የተለያየ ዓይነት አምልኮ ምን ይሰማት ነበር? ደራሲ ስቶንማን እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “አንድ ብልህ ገዥ ሕዝቡ ይበጀኛል የሚለውን ልማድ አይንቅም። . . . አማልክት አንድ ላይ ተሰባስበው ለፓልሚራ . . . እንደወገኑ ይታሰብ ነበር።” ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ዘኖቢያ ሁሉንም ዓይነት ሃይማኖታዊ አቋም የምታስተናግድ ነበረች። ነገር ግን ‘አማልክት በእርግጥ ለፓልሚራ ወግነው’ ነበርን? ፓልሚራና የዚች ከተማ ‘ብልህ መሪ’ ምን ይገጥማቸው ይሆን?
አንድ ንጉሠ ነገሥት በዘኖቢያ ላይ ‘ልቡን አነሣ’
በ270 እዘአ ኦሬሊየን የሮም ንጉሠ ነገሥት ሆነ። ጭፍሮቹ በተሳካ ሁኔታ በሰሜን የነበሩትን ኋላቀር ወገኖች መመከትና ቀጥተው መመለስ ችለው ነበር። በ271 እዘአ ደግሞ በዳንኤል ትንቢት ውስጥ የተገለጸውን ‘የሰሜን ንጉሥ’ በመወከል ኦሬሊየን በዘኖቢያ የሚወከለውን ‘የደቡብ ንጉሥ’ ለመውጋት ‘ኃይሉንም ልቡንም አነሣ።’ (ዳንኤል 11:25) ኦሬሊየን የተወሰነውን ሠራዊቱን በቀጥታ ወደ ግብጽ በመላክ ዋናውን ሠራዊቱን በትንሿ እስያ በኩል ወደ ምሥራቅ ላከ።
የደቡብ ንጉሥ ማለትም በዘኖቢያ የሚመራው አገዛዝ ዜብዳስና ዜባይ በተባሉ ሁለት ጄኔራሎች በመመራት “በታላቅና በብዙ ሠራዊት ሆኖ” ኦሬሊየንን ለመግጠም ተነሣ። (ዳንኤል 11:25) ነገር ግን ኦሬሊየን ግብጽን በቁጥጥሩ ሥር ካደረገ በኋላ ወደ ትንሿ እስያና ወደ ሶርያ መዝመት ጀመረ። ዘኖቢያ (ዛሬ ሆምስ በምትባለው) በኤመሳ ድል ተነስታ ወደ ፓልሚራ አፈገፈገች።
ኦሬሊየን ፓልሚራን በቁጥጥሩ ሥር ሲያውል ዘኖቢያ እርዳታ እንደምታገኝ በማሰብ ከወንድ ልጁዋ ጋር ወደ ፋርስ ሸሸች። ይሁን እንጂ ገና የኤፍራጥስን ወንዝ ሳትሻገር ሮማውያን ማረኳት። የፓልሚራ ሰዎች ከተማቸውን በ272 እዘአ ለወራሪዎች አስረከቡ። ኦሬሊየን የከተማዋን ነዋሪዎች አባብሎ በመያዝ ከፀሐይ ቤተ መቅደስ የተወሰዱ ጣዖታትን ጨምሮ ከፍተኛ መጠን ያለው የተለያየ ቁሳቁስ ዘርፎ ወደ ሮም አሻግሮ ነበር። የሮማው ንጉሠ ነገሥት ዘኖቢያን በሕይወት ካስመጣት በኋላ በ274 እዘአ በሮም ከተማ የተካሄደውን የድል ሰልፍ እንድታደምቅ አድርጓል። ቀሪ የሕይወት ዘመኗን የሮማ እመቤት ሆና አሳልፋለች።
የበረሃዋ ከተማ ተደመሰሰች
ኦሬሊየን ፓልሚራን ከተቆጣጠረ ከጥቂት ወራት በኋላ የፓልሚራ ሰዎች በዚያ አካባቢ የቀረውን ጠባቂ ጦር ጨፈጨፉት። የዚህ ዓመፅ ወሬ ኦሬሊየን ጆሮ በደረሰ ጊዜ ወታደሮቹ ወደ መጡበት እንዲመለሱ ትእዛዝ ሰጠ። በዚህ ጊዜ በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ የበቀል እርምጃ ወስደዋል። ከምሕረት የለሹ ጭፍጨፋ ያመለጡት በባርነት ተወሰዱ። ያች የተከበረች ከተማ ዳግም እንደማትጠገን ሆና ተበዘበዘች፣ ወደመች። ያች ሞቅ ደመቅ ያለች ከተማ ድሮ ወደነበረችበት ሁኔታዋ ማለትም ‘በምድረ በዳ እንደነበረችው ተድሞር’ ሆነች።
ዘኖቢያ ሮምን በተቋቋመች ጊዜ እርሷም ሆነች ንጉሠ ነገሥቱ ኦሬሊየን ባይታወቃቸውም ‘የደቡብ ንጉሥና’ ‘የሰሜን ንጉሥ’ በመሆን ከ800 ዓመታት በፊት የይሖዋ ነቢይ በዝርዝር በመዘገበው ትንቢት ውስጥ ያሉት ነገሮች በከፊል ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ አድርገዋል። (ዳንኤል ምዕራፍ 11) ዘኖቢያ በማራኪ ስብዕናዋ የብዙዎችን አድናቆት አትርፋለች። ይሁን እንጂ ከሁሉ ይበልጥ ጉልህ ሥፍራ የሚሰጠው በዳንኤል ትንቢት ውስጥ የተጠቀሰውን ፖለቲካዊ ኃይል በመወከል የተጫወተችው ሚና ነው። ግዛቷ ከአምስት ዓመት በላይ አልዘለቀም። የዘኖቢያ መንግሥት መዲና የነበረችው ፓልሚራ ዛሬ አንዲት ትንሽ መንደር ናት። ኃያል የነበረው የሮማ ንጉሠ ነገሥት ግዛትም ሳይቀር ጠፍቶ ዛሬ ላሉት መንግሥታት ቦታውን ለቅቋል። የእነዚህ ኃይላት የወደፊት ዕጣ ምን ይሆናል? የእነርሱም ዕጣ ፋንታ በእርግጠኝነት ፍጻሜውን በሚያገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ላይ የተመካ ነው።—ዳንኤል 2:44
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የዘኖቢያ ቅርስ
ንጉሠ ነገሥት ኦሬሊየን የፓልሚራዋን ንግሥት ዘኖቢያን ድል ካደረገ በኋላ ሲመለስ ለፀሐይ ቤተ መቅደስ ገነባ። በዚያም ውስጥ ከንግሥቲቱ ከተማ ያመጣውን የፀሐይ አምላክ ሐውልት አቆመበት። ሂስትሪ ቱዴይ የተባለው መጽሔት ተጨማሪ አስተያየት ሲሰጥ እንዲህ ብሏል:- “ኦሬሊየን ካደረጋቸው ነገሮች ሁሉ ይበልጥ ለረጅም ጊዜ የዘለቀው በ274 ዓ.ም. ያቋቋመውና በክረምቱ ወራት መግቢያ ላይ ፀሐይ በምትወጣበት በታኅሣሥ 25 የሚከበረው ዓመታዊ በዓል ሳይሆን አይቀርም። ንጉሠ ነገሥታዊ መንግሥቱ ክርስትናን በተቀበለ ጊዜ የክርስቶስ ልደት ወደዚህ ዕለት ተዛውሮ አዲሱ ሃይማኖት የጥንቱን በዓል ያፈቅሩ በነበሩ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ተደርጓል። ዛሬ [ሰዎች] የእኛኑ የገና በዓል የሚያከብሩት . . . ከንግሥተ ነገሥት ዘኖቢያ የተነሣ . . . መሆኑ የሚያስገርም ነው።”
[በገጽ 28, 29 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የሜዲትራኒያን ባሕር
ሶሪያ
አንጾኪያ
ኤመሳ (ሆምስ)
ፓልሚራ
ደማስቆ
ሜሶጶጣሚያ
ኤፍራጥስ
ካሬይ (ሃራን)
ኒሲቢስ
ዱራ- ዩሮፖስ
[ምንጭ]
Map: Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.
Colonnade: Michael Nicholson/Corbis
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኦሬሊየን እንደሆነ የሚገመተውን ምስል የያዘ የሮማ ሳንቲም
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በፓልሚራ የሚገኘው የፀሐይ ቤተ መቅደስ
[ምንጭ]
The Complete Encyclopedia of Illustration/J. G. Heck
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ንግሥት ዘኖቢያ ለወታደሮቿ ንግግር ስታደርግ
[ምንጭ]
Giovanni Battista Tiepolo, Queen Zenobia Addressing Her Soldiers, Samuel H. Kress Collection, Photograph © Board of Trustees, National Gallery of Art, Washington
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Detail of: Giovanni Battista Tiepolo, Queen Zenobia Addressing Her Soldiers, Samuel H. Kress Collection, Photograph © Board of Trustees, National Gallery of Art, Washington