እውነተኛ ትሕትና ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?
እውነተኛ ትሕትና በአምላክ ዘንድ ከፍተኛ ዋጋ አለው። ያዕቆብ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፣ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” በማለት ጽፏል። (ያዕቆብ 4:6) እዚህ ላይ ያዕቆብ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተገለጹ በርካታ ሐሳቦችን በተዘዋዋሪ መንገድ ጠቅለል አድርጎ መናገሩ ሊሆን ይችላል። “ይሖዋ ከፍ ያለ ነው፤ ይሁን እንጂ ትሑት የሆነውን ይመለከታል፤ ኩሩዎችን ግን ገና ከሩቅ ያውቃል።” “ከፍ ያለችውም የሰው ዓይን ትዋረዳለች፣ የሰዎችም ኩራት ትወድቃለች፣ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ብቻውን ከፍ ከፍ ይላል።” “በፌዘኞች እርሱ ያፌዛል፣ ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል።”—መዝሙር 138:6፤ ኢሳይያስ 2:11፤ ምሳሌ 3:34
ሐዋርያው ጴጥሮስም ትሑት መሆንን አበረታቷል። እንዲህ በማለት ጽፏል:- “እንዲሁም፣ ጐበዞች ሆይ፣ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፣ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፣ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።”—1 ጴጥሮስ 5:5
ክርስቶስ ያሳየው የትሕትና ምሳሌ
ትሑት መሆን ጥቅሙ ምንድን ነው? ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። እውነተኛ ክርስቲያን ሆኖ ለመገኘት ለሚጥር ሰው የዚህ ጥያቄ መልስ እጅግ ወሳኝ ነው። ትሑት መሆን ማለት ክርስቶስን መምሰል ማለት ነው። ኢየሱስ ከሰማይ ወደ ምድር መምጣትና ከመላእክት ያነሰ ተራ ሰው መሆን የሚጠይቅ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የሥራ ምድብ በመቀበል ትሕትናውን አሳይቷል። (ዕብራውያን 2:7) የአምላክ ልጅ ሆኖ ሳለ ሃይማኖታዊ ጠላቶቹ የከመሩበትን የውርደት መዓት በጽናት ተቋቁሟል። ቢፈልግ ለእርዳታ የመላእክት ጭፍራ መጥራት ይችል የነበረ ቢሆንም የደረሰበትን ፈተና በዝምታ ተቀብሏል።—ማቴዎስ 26:53
በመጨረሻም ኢየሱስ ተዋርዶ በመከራ እንጨት ላይ ቢሰቀልም እስከ መጨረሻ ለአባቱ ታማኝ ሆኗል። በመሆኑ ጳውሎስ ስለ እርሱ እንዲህ ብሎ ለመጻፍ ችሏል:- “በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን። እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፣ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፣ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፣ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።”—ፊልጵስዩስ 2:5-8
ታዲያ እኛስ እውነተኛ ትሕትና ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? አንዳንድ ሁኔታዎች ሲገጥሙን በኩራተኝነት መንፈስ ሳይሆን በትሕትና ልንወጣቸው የምንችለው እንዴት ነው?
ትሑት የሆነ ሰው ምላሽ የሚሰጥበት መንገድ
ትሑትና በሥራ ቦታም ሆነ በክርስቲያናዊ አገልግሎት እንዴት በሥራ እንደሚገለጽ እስቲ እንመርምር። አንድን ሥራ በተሳካ ሁኔታ ማከናወን ይቻል ዘንድ የበላይ ተመልካቾች፣ ሥራ አስኪያጆችና የበላይ ተቆጣጣሪዎች መኖራቸው አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ውሳኔ የሚያስተላልፍ አንድ ሰው የግድ መኖር አለበት። ለዚህ ሰው የሚኖርህ አመለካከት ምንድን ነው? “ለመሆኑ እርሱ ማን ሆነና ነው እንዲህ አድርግ ብሎ የሚነግረኝ? በዚህ ሥራ ላይ ከእርሱ ይልቅ እኔ ብዙ ዓመት አሳልፌአለሁ” ብለህ ታስባለህ? አዎን፣ ኩራተኛ ከሆንክ የበታች መሆን ያስቆጣሃል። በሌላው በኩል ደግሞ ትሑት የሆነ ሰው ‘ራሱን ዝቅ በማድረግ ሌሎች ሰዎች ከእሱ እንደሚሻሉ አድርጎ ይቆጥራል እንጂ ያለ እኔ ማን አለ በሚል ትምክሕት’ አንዳች ነገር አያደርግም።—ፊልጵስዩስ 2:3 የ1980 ትርጉም
በዕድሜ ከአንተ ከሚያንስ ሰው ወይም ከአንዲት ሴት አስተያየት ቢቀርብልህ እንዴት ይሰማሃል? ትሑት ከሆንክ ቢያንስ ጉዳዩን ታጤነዋለህ። ኩራተኛ ከሆንክ ግን ወዲያው ቅር ልትሰኝ ወይም አስተያየቱን ሳትቀበለው ልትቀር ትችላለህ። ማግኘት የምትፈልገው የኋላ ኋላ ውድቀት ላይ ሊጥልህ የሚችል ሽንገላ ወይም ማሞካሻ ነው ወይስ ሊገነባህ የሚችል ጠቃሚ የሆነ ምክር?—ምሳሌ 27:9፤ 29:5
የሚደርስብህን መከራ ፊት ለፊት ተጋፍጠህ መወጣት ትችላለህ? ትሕትና ልክ ኢዮብ እንዳደረገው አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንድትጋፈጣቸውና በጽናት እንድትወጣቸው ያስችልሃል። ኩራተኛ ከሆንክ ግን ከበድ ያሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎችም ሆኑ ቀላል ችግሮች ሲደርሱብህ ቶሎ ተስፋ ልትቆርጥ ወይም ልትመረር ትችላለህ።—ኢዮብ 1:22፤ 2:10፤ 27:2–5
ትሕትና አፍቃሪና ይቅር ባይ ነው
አንዳንድ ሰዎች “ይቅርታ። ተሳስቻለሁ። አንተ ትክክል ነበርክ” ብሎ መናገር ይከብዳቸዋል። ለምን? ምክንያቱም ከፍተኛ የኩራት መንፈስ ስላለባቸው ነው! ይሁን እንጂ ከልብ በመነጨ ስሜት ይቅርታ መጠየቅ ብዙውን ጊዜ በባልና ሚስት መካከል ለሚነሱ ግጭቶች እልባት አምጥቷል።
አንድ ሰው በሚያስቀይምህ ጊዜ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ነህ? ወይስ በኩራት መንፈስ ተነሳስተህ ቂም በመያዝ ጎድቶኛል የምትለውን ሰው ለበርካታ ቀናት ወይም ወራት ታኮርፋለህ? ነገር በሆድህ ይዘህ ብድር ለመመለስ ታደባለህ? አንዳንድ ሰዎች በቂም በቀል በተነሳሱ ሰዎች ተገድለዋል። ሌሎች ደግሞ ሆነ ብለው ስም የማጥፋት ዘመቻ ያካሂዳሉ። በተቃራኒው ግን ትሑት የሆነ ሰው አፍቃሪና ይቅር ባይ ነው። ለምን? ምክንያቱም ፍቅር በደልን አይቆጥርም። እስራኤላውያን የነበረባቸውን የኩራት መንፈስ ካስወገዱ ይሖዋ ይቅር ሊላቸው ዝግጁ ነበር። ትሑት የሆነ አንድ የኢየሱስ ተከታይ ሌላው ቀርቶ በተደጋጋሚ ጊዜም እንኳ ቢሆን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ነው!—ኢዩኤል 2:12-14፤ ማቴዎስ 18:21, 22፤ 1 ቆሮንቶስ 13:5
ትሑት የሆነ ሰው ‘ሌሎችን ለማክበር ቀዳሚ ይሆናል።’ (ሮሜ 12:10) ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን “ከራሳችሁ አስበልጣችሁ ሌሎችን አክብሩ” ይላል። ሌሎችን ታመሰግናለህ? እንዲሁም ችሎታዎቻቸውንና ተሰጥዖዎቻቸውን ታደንቃለህ? ወይስ በሰዎች ዘንድ ያላቸውን ጥሩ ስም ለማጉደፍ ሁልጊዜ አንድ ዓይነት ጉድለት ለማግኘት ትፈላልጋለህ? አዎን፣ ሌሎችን ከልብ በመነጨ ስሜት ማመስገን ትችላለህን? በዚህ ረገድ ችግር ካለብህ ምናልባት በራስ ያለመተማመን ስሜት ወይም ኩራት ይኖርብህ ይሆናል።
ኩሩ ሰው ትዕግሥት የለውም። ትሑት ሰው ግን ትዕግሥተኛና ቻይ ነው። አንተስ እንዴት ነህ? ጥሩ አያያዝ እንዳልተደረገልህ ሲሰማህ ወዲያው ቱግ ትላለህ? እንዲህ ዓይነቱ ጠባይ የቻይነት ተቃራኒ ነው። ትሑት ከሆንክ ስለ ራስህ ከመጠን በላይ አታስብም። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከመጠን በላይ ስለ ራሳቸው ባሰቡ ጊዜ የሆነውን ነገር አስታውስ። ከሁሉም የተሻለ ማን ስለመሆኑ በመካከላቸው የከረረ ክርክር ተነስቶ ነበር። ሁሉም ‘የማይጠቅሙ ባሪያዎች’ መሆናቸውን ዘንግተው ነበር!—ሉቃስ 17:10፤ 22:24፤ ማርቆስ 10:35-37, 41
ፈረንሳዊው ጸሐፊ ቮልቴር ስለ ትሕትና ሲናገር “ጭምት ልብ . . . የኩራት ማርከሻ” ነው በማለት ገልጿል። አዎን፣ ትሕትና ራስን ዝቅ ማድረግ ነው። ትሑት የሆነ ሰው አቅሙንና ቦታውን የሚያውቅ እንጂ ኩራተኛ አይደለም። ሰው አክባሪና ለሌሎች አሳቢ ነው።
ትሑት ለመሆን ጥረት ማድረግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ትሕትና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ባሕርይ ከመሆኑም በላይ መለኮታዊ መመሪያ እንድናገኝ ይረዳናል። ዳንኤል በይሖዋ ዘንድ ‘እጅግ የተወደደ’ እንዲሆን ያደረገውና ይሖዋም አንድ መልአክ ራእይ ይዞ ወደ እርሱ እንዲሄድ ያደረገበት አንዱ ምክንያት ትሑት በመሆኑ የተነሳ ነው! (ዳንኤል 9:23፤ 10:11, 19) ትሕትና ብዙ በረከቶች አሉት። የሚወዱህ እውነተኛ ወዳጆችን ያፈራልሃል። ከሁሉም በላይ ግን የይሖዋን በረከት ያስገኝልሃል። “ትሕትናና እግዚአብሔርን መፍራት ባለጠግነት ክብር ሕይወትም ነው።”—ምሳሌ 22:4
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በትሕትና ይቅርታ መጠየቅ ሕይወትን አስደሳች ያደርገዋል