የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 2/1 ገጽ 9-13
  • ታላቁ ሸክላ ሠሪና ሥራው

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ታላቁ ሸክላ ሠሪና ሥራው
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሸክላ ሠሪው ሥራውን ቀጥሏል
  • ምን ዓይነት ዕቃ ትሆኑ ይሆን?
  • ፈተናዎችን ለመቋቋም በሚያስችል መንገድ መቀረጽ
  • ልጆቻችንን መቅረጽ
  • ሁሉንም ለመቅረጽ የሚያስችል መንገድ
  • የይሖዋ ተግሣጽ እንዲቀርጻችሁ ፍቀዱ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2013
  • ይሖዋ እንደሚቀርጸን መገንዘባችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
  • በሸክላ ዕቃ ውስጥ ያለን ውድ ሀብት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • አዲስ የልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራም
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2007
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 2/1 ገጽ 9-13

ታላቁ ሸክላ ሠሪና ሥራው

“ለክብር የሚሆን . . . ለበጎም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ [ሁኑ]።”—⁠2 ጢሞቴዎስ 2:​21

1, 2. (ሀ) አምላክ ወንድንና ሴትን ሲፈጥር ያከናወነው ሥራ ዕጹብ ድንቅ ነው ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ታላቁ ሸክላ ሠሪ አዳምንና ሔዋንን የፈጠራቸው ለምን ዓላማ ነበር?

ይሖዋ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ሸክላ ሠሪ ነው። ታላቁ የፍጥረት ሥራው የመጀመሪያው ወላጃችን አዳም ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ፣” ማለትም “የሚተነፍስ ፍጡር” ሆነ። (ዘፍጥረት 2:​7፣ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) የመጀመሪያው ሰብዓዊ ፍጡር የአምላክን መለኮታዊ ጥበብ እንዲሁም ለእውነተኛ ጽድቅና ፍትሕ ያለውን ፍቅር የሚያሳይ በራሱ በአምላክ አምሳያ የተፈጠረ ፍጹም ፍጡር ነበር።

2 በተጨማሪም አምላክ ከአዳም አንድ የጎድን አጥንት ወስዶ ለወንድ ማሟያና ረዳት የምትሆን ሴት ሠራ። ሔዋን የነበራት እንከን የማይወጣለት ውበት በዛሬው ጊዜ ያሉትን እጅግ ውብ የሆኑ ሴቶች እንኳ ሳይቀር የሚያስንቅ ነበር። (ዘፍጥረት 2:​21–23) ከዚህም ሌላ የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት እንዲያከናውኑት የተሰጣቸውን ይህችን ምድር ገነት የማድረግ ሥራ ለመፈጸም የሚያስችል ፍጹም በሆነ መንገድ የተሠራ አካልና አእምሮ ተሰጥቷቸዋል። በተጨማሪም በዘፍጥረት 1:​28 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን የአምላክ ትእዛዝ ለመፈጸም የሚያስችል ኃይል ተሰጥቷቸው ነበር:- “ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።” ውሎ አድሮ ይህ ዓለም አቀፋዊ የአትክልት ሥፍራ “ፍጹም የአንድነት ማሰሪያ [NW]” በሆነው ፍቅር በተሳሰሩ በቢልዮን በሚቆጠሩ ደስተኛ ሰዎች እንዲሞላ የአምላክ ዓላማ ነበር።​—⁠ቆላስይስ 3:​14

3. የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የውርደት ዕቃዎች የሆኑት እንዴት ነው? ይህስ ምን ውጤት አስከትሏል?

3 የሚያሳዝነው ግን፣ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ታላቅ ሸክላ ሠሪ በሆነው በሉዓላዊው ፈጣሪ ሥልጣን ላይ ሆን ብለው ዓመፁ። በኢሳይያስ 29:​15, 16 ላይ የተገለጸውን ዓይነት እርምጃ ወሰዱ:- “ምክራቸውን ጥልቅ አድርገው ከእግዚአብሔር ለሚሰውሩ፣ ሥራቸውንም በጨለማ ውስጥ አድርገው:- ማን ያየናል? ወይስ ማን ያውቀናል? ለሚሉ ወዮላቸው! . . . እንደ ሸክላ ሠሪ ጭቃ የምትቆጠሩ አይደላችሁምን? በውኑ ሥራ ሠሪውን:- አልሠራኸኝም ይለዋልን? ወይስ የተደረገው አድራጊውን:- አታስተውልም ይለዋልን?” ያሻቸውን ለማድረግ መነሳታቸው መዓት አምጥቶባቸዋል፤ ለዘላለማዊ ሞት ዳርጓቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከእነሱ የመጣው መላው የሰው ዘር ኃጢአትና ሞት ወርሷል። (ሮሜ 5:​12, 18) የታላቁ ሸክላ ሠሪ ፍጥረት ውበት ክፉኛ ጎደፈ።

4. ለየትኛው ክብራማ ዓላማ ልናገለግል እንችላለን?

4 ይሁን እንጂ ኃጢአተኛ የሆንነው የአዳም ዘሮች አሁን ባለንበት የአለፍጽምና ሁኔታም እንኳ በመዝሙር 139:​14 ላይ በሚገኙት ቃላት ይሖዋን ማወደስ እንችላለን:- “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፣ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች።” ሆኖም የታላቁ ሸክላ ሠሪ የመጀመሪያ የእጅ ሥራ ክፉኛ መጉደፉ እጅግ ያሳዝናል!

ሸክላ ሠሪው ሥራውን ቀጥሏል

5. የታላቁ ሸክላ ሠሪ ችሎታ ለምን ዓላማ ይውላል?

5 የሚያስደስተው ግን፣ ፈጣሪያችን በሸክላ ሥራ ረገድ ያለው ችሎታ የመጀመሪያውን የሰው ዘር ፍጥረት በመቅረጽ ብቻ ተወስኖ የሚቀር አልነበረም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “ነገር ግን፣ አንተ ሰው ሆይ፣ ለእግዚአብሔር የምትመልስ ማን ነህ? ሥራ ሠሪውን:- ስለ ምን እንዲህ አድርገህ ሠራኸኝ ይለዋልን? ወይም ሸክላ ሠሪ ከአንዱ ጭቃ ክፍል አንዱን ዕቃ ለክብር አንዱንም ለውርደት ሊሠራ በጭቃ ላይ ሥልጣን የለውምን?”​—⁠ሮሜ 9:​20, 21

6, 7. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ብዙዎች ለውርደት መቀረጽ የሚመርጡት እንዴት ነው? (ለ) ጻድቃን ክብራማ ለሆነ አገልግሎት የሚቀረጹት እንዴት ነው?

6 አዎን፣ ከታላቁ ሸክላ ሠሪ ሥራዎች መካከል አንዳንዶቹ ለክብራማ አገልግሎት የሚውሉ ሆነው ሲቀረጹ አንዳንዶቹ ደግሞ ለውርደት የሚያገለግሉ ሆነው ይቀረጻሉ። ወደ ርኩሰት ማጥ ውስጥ ይበልጥ ጠልቆ እየገባ ካለው ዓለም ጋር መጓዝ የመረጡ ሁሉ ለጥፋት በሚለያቸው መንገድ ተቀርጸዋል። ክብራማው ንጉሥ ክርስቶስ ኢየሱስ ለፍርድ በሚመጣበት ጊዜ እነዚህ የውርደት ዕቃዎች ማቴዎስ 25:​46 በሚገልጸው መሠረት “ወደ ዘላለም ቅጣት” የሚሄዱትን ፍየል መሰል ልበ ደንዳና ሰዎች በሙሉ የሚያጠቃልሉ ይሆናሉ። ‘ክብራማ’ ለሆነ አገልግሎት የተቀረጹት በግ መሰል “ጻድቃን” ግን የ“ዘላለም ሕይወት” ያገኛሉ።

7 እነዚህ ጻድቃን በመለኮታዊ መንገድ ለመቀረጽ ራሳቸውን በትሕትና ያቀረቡ ናቸው። በአምላክ የሕይወት መንገድ መመላለስ ጀምረዋል። በ1 ጢሞቴዎስ 6:​17–19 ላይ የሚገኘውን “ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለጠግነት ተስፋ [አታድርጉ]” የሚለውን ምክር ተቀብለዋል። “እውነተኛውን ሕይወት ይይዙ ዘንድ፣ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ፣ መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ሥራ ሁሉ ባለ ጠጎች እንዲሆኑ፣ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ” የተሰጣቸውን ምክር ሠርተውበታል። በመለኮታዊ እውነት ከመቀረጻቸውም በላይ በአዳም ኃጢአት ያጡትን ነገር ሁሉ መልሶ ለማስገኘት “ራሱን ተመጣጣኝ ቤዛ” አድርጎ በሰጠው በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል ይሖዋ ባዘጋጀው ዝግጅት ላይ የማይናወጥ እምነት አሳድረዋል። (1 ጢሞቴዎስ 2:​6 NW) እንግዲያው ጳውሎስ “የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን [የተቀረጸውን] ሰው” እንድንለብስ ለሰጠው ምክር ራሳችንን በፈቃደኝነት ማስገዛታችን ምንኛ የተገባ ነው!​—⁠ቆላስይስ 3:​10

ምን ዓይነት ዕቃ ትሆኑ ይሆን?

8. (ሀ) አንድ ሰው ምን ዓይነት ዕቃ እንደሚሆን የሚወስነው ምንድን ነው? (ለ) አንድ ሰው በሚቀረጽበት ሁኔታ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት ሁለት ነገሮች ምንድን ናቸው?

8 አንድ ሰው ምን ዓይነት ዕቃ እንደሚሆን የሚወስነው ምንድን ነው? አመለካከቱና ምግባሩ ነው። እነዚህ ነገሮች መጀመሪያ የሚቀረጹት በልብ ፍላጎትና ዝንባሌ ነው። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “የሰው ልብ መንገዱን ያዘጋጃል፤ እግዚአብሔር ግን አካሄዱን ያቀናለታል።” (ምሳሌ 16:​9) በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በምንሰማቸውና በምናያቸው ነገሮች ማለትም በባልንጀሮቻችንና በሚገጥሙን ነገሮች ይቀረጻሉ። እንግዲያው የሚከተለውን ምክር መከተላችን በጣም አስፈላጊ ነው:- “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል።” (ምሳሌ 13:​20) ሁለተኛ ጴጥሮስ 1:​16 እንደሚያስጠነቅቀን “በብልሃት የተፈጠረውን ተረት” ወይም ደግሞ የኖክስ የሮማ ካቶሊክ ትርጉም እንደሚለው “የሰውን አፈ ታሪኮች” ከመከተል መራቅ ይኖርብናል። ይህም ብዙዎቹን የከሃዲዋን ሕዝበ ክርስትና ትምህርቶችና በዓላት ያካትታል።

9. ታላቁ ሸክላ ሠሪ እኛን ለሚቀርጽበት መንገድ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?

9 ስለዚህ አምላክ እኛ በምንሰጠው ምላሽ ላይ በመመርኮዝ ሊቀርጸን ይችላል። በትሕትና የሚከተለውን የዳዊት ጸሎት ለይሖዋ ልናቀርብ እንችላለን:- “አቤቱ፣ መርምረኝ ልቤንም እወቅ፤ ፍተነኝ መንገዴንም እወቅ፤ በደልንም በእኔ ውስጥ ብታገኝ እይ፤ የዘላለምንም መንገድ ምራኝ።” (መዝሙር 139:​23, 24) ይሖዋ የመንግሥቱ መልእክት እንዲሰበክ በማድረግ ላይ ነው። ልባችን ለምሥራቹና ለሌሎቹም አመራሮቹ አድናቆት የተሞላበት ምላሽ ሰጥቷል። በድርጅቱ አማካኝነት ምሥራቹን ከመስበክ ሥራ ጋር የተያያዙ የተለያዩ መብቶች ዘርግቶልናል። እነዚህን መብቶች አጥብቀን እንያዛቸው፤ እንዲሁም ከፍ አድርገን እንመልከታቸው።​—⁠ፊልጵስዩስ 1:​9–11

10. መንፈሳዊ ፕሮግራሞችን ለመከተል ጥረት ማድረግ ያለብን እንዴት ነው?

10 በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና ከቤተሰባችንም ጋር ሆነ ከጓደኞቻችን ጋር በምናደርገው ውይይት ቅዱሳን ጽሑፎችንና የአምላክን አገልግሎት መሠረት በማድረግ ለአምላክ ቃል ቋሚ የሆነ ትኩረት መስጠታችን በጣም አስፈላጊ ነው። በእያንዳንዱ የቤቴል ቤተሰብና የይሖዋ ምሥክሮች የሚስዮናውያን ቡድን በቁርስ ሰዓት በሚካሄደው የማለዳ አምልኮ ላይ ብዙውን ጊዜ በየሳምንቱ በፈረቃ አንዴ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንዴ ደግሞ በወቅቱ ከወጣው የዓመት መጽሐፍ ላይ አጠር ያለ ንባብ ይኖራል። የእናንተስ ቤተሰብ እንዲህ ዓይነት ዝግጅት ማድረግ ይችል ይሆን? ሁላችንም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ባለን ወዳጅነት፣ አንድ ላይ በምናደርጋቸው ስብሰባዎችና በተለይ ደግሞ በሳምንታዊው የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ በምናደርገው ተሳትፎ ምን ያህል ጥቅሞች እንደምናገኝ አስቡት!

ፈተናዎችን ለመቋቋም በሚያስችል መንገድ መቀረጽ

11, 12. (ሀ) በዕለታዊ ሕይወታችን የሚገጥሙንን ፈተናዎች በተመለከተ ያዕቆብ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) የኢዮብ ተሞክሮ የጸና አቋም እንድንጠብቅ የሚያበረታታን እንዴት ነው?

11 አምላክ በዕለታዊው ኑሯችን አንዳንድ ሁኔታዎች እንዲደርሱብን ይፈቅዳል፤ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ አስቸጋሪ ሊሆኑብን ይችላሉ። እነዚህን ሁኔታዎች ልንመለከታቸው የሚገባው እንዴት ነው? ያዕቆብ 4:​8 እንደሚመክረው ከመመረር ይልቅ ‘ወደ እሱ ስንቀርብ እሱም ወደ እኛ እንደሚቀርብ’ እርግጠኞች በመሆን በሙሉ ልባችን በእሱ ታምነን ወደ አምላክ እንቅረብ። አስቸጋሪ ሁኔታዎችንና ፈተናዎችን በጽናት መቋቋም እንደሚጠይቅብን የታወቀ ነው፤ ሆኖም አምላክ እነዚህ ነገሮች እንዲደርሱብን የሚፈቅደው በጥሩ ሁኔታ እንድንቀረጽ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ በመሆናቸው ነው። በመጨረሻ አስደሳች ውጤት ያስገኙልናል። ያዕቆብ 1:​2, 3 እንዲህ ሲል ያረጋግጥልናል:- “ወንድሞቼ ሆይ፣ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፣ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቊጠሩት።”

12 በተጨማሪም ያዕቆብ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ማንም ሲፈተን:- በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም። ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል።” (ያዕቆብ 1:​13, 14) የሚደርሱብን ፈተናዎች በርካታና የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ሆኖም በኢዮብ ሁኔታ ላይ እንደታየው ሁሉም በጥሩ ሁኔታ እንድንቀረጽ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ቅዱሳን ጽሑፎች በያዕቆብ 5:​11 ላይ የሚከተለውን ታላቅ ዋስትና ይሰጡናል:- “እነሆ፣ በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን እንላቸዋለን፤ ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል፣ ጌታም እንደ ፈጸመለት አይታችኋል፤ ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና።” በታላቁ ሸክላ ሠሪ እጅ ውስጥ ያለን ዕቃዎች እንደ መሆናችን መጠን መጨረሻ በምናገኘው ውጤት ላይ የኢዮብ ዓይነት እምነት በማሳደር ምንጊዜም የጸና አቋም ይዘን እንመላለስ!​—⁠ኢዮብ 2:​3, 9, 10፤ 27:​5፤ 31:​1–6፤ 42:​12–15

ልጆቻችንን መቅረጽ

13, 14. (ሀ) ወላጆች ልጆቻቸውን ከመቼ ጀምሮ መቅረጽ አለባቸው? ይህን የሚያደርጉትስ ምን ውጤት በመጠበቅ ነው? (ለ) የትኞቹን አስደሳች ውጤቶች ልትጠቅስ ትችላለህ?

13 ወላጆች ልጆቻቸውን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ በመቅረጽ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላሉ፤ እንዲህ በምናደርግበት ጊዜ ልጆቻችን የጸና አቋም ሊይዙ ይችላሉ! (2 ጢሞቴዎስ 3:​14, 15) ፈተናዎች ከባድ በሚሆኑበት ጊዜም እንኳ ይህ እውነት ሆኖ ተገኝቷል። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት በአንድ የአፍሪካ አገር ውስጥ ስደት እጅግ ተፋፍሞ በነበረበት ጊዜ እምነት የሚጣልበት አንድ ቤተሰብ በጓሮ በኩል በሚገኝ ክፍል ውስጥ አንድ የመጠበቂያ ግንብ ማተሚያ መሣሪያ በድብቅ አስቀምጦ ነበር። አንድ ቀን ወታደሮች ለብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ወጣቶችን ለማፈስ በየቤቱ ያስሱ ነበር። የዚህ ቤተሰብ አባላት የሆኑት ሁለት ወጣት ወንዶች ልጆች መደበቅ የሚችሉበት ጊዜ ነበራቸው፤ ሆኖም ወታደሮቹ እነሱን ሲፈልጉ የማተሚያ መሣሪያውን እንደሚያገኙት የታወቀ ነው። ይህ ደግሞ መላ ቤተሰቡን ለከባድ ሥቃይ ምናልባትም ለሞት ሊዳርግ ይችላል። ታዲያ ምን ማድረግ ይሻላል? ሁለቱ ወንዶች ልጆች ዮሐንስ 15:​13ን በመጥቀስ “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም” ሲሉ በድፍረት ተናገሩ። እናም ሳሎን ተቀምጠን እንጠብቃለን አሉ። ወታደሮቹ ሲያገኟቸው በጦር ሠራዊቱ ውስጥ ካላገለገላችሁ ብለው እንደሚያስገድዷቸውና ፈቃደኞች ሆነው ካልተገኙ ደግሞ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ እንደሚያሰቃዩአቸው አልፎ ተርፎም ሊገድሏቸው እንደሚችሉ ምንም ጥርጥር አልነበረውም። ሆኖም እነሱን ካገኙ ቤቱን የሚፈትሹበት ምክንያት ስለሌለ የማተሚያ መሣሪያውን አያገኙትም፣ የተቀሩት የቤተሰቡ አባላትም ለሥቃይ ከመዳረግ ይድናሉ። ይሁን እንጂ የተፈጸመው ሁኔታ ፈጽሞ ያልተጠበቀ ነበር። ወታደሮቹ ይህን ቤት አልፈው ሌሎቹን ቤቶች መፈተሽ ቀጠሉ! ለክብራማ አገልግሎት የተቀረጹት እነዚህ ሰብዓዊ ዕቃዎችም ሆኑ ማተሚያ መሣሪያው ተርፈው ወቅታዊ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ማተማቸውን ቀጠሉ። በአሁኑ ጊዜ ከሁለቱ ወንዶች ልጆች አንደኛውና እህቱ በቤቴል እያገለገሉ ነው፤ ይህ ወጣት አሁንም በዚያው አሮጌ የማተሚያ መሣሪያ በመሥራት ላይ ይገኛል።

14 ትንንሽ ልጆች እንዴት እንደሚጸልዩ ሊማሩ ይችላሉ። አምላክም ለጸሎታቸው መልስ ይሰጣል። እንዲህ ዓይነቱ አስደናቂ ገጠመኝ በሩዋንዳ የጅምላ ጭፍጨፋ ወቅት ተከስቶ ነበር። አንዲት የስድስት ዓመት ልጅና ወላጆቿ የእጅ ቦምብ በታጠቁ ዓማፂያን ሊገደሉ ሲሉ ልጅቷ ይሖዋ እሱን ማገልገላቸውን ይቀጥሉ ዘንድ እንዲያተርፋቸው ጮክ ብላ ከልቧ ጸለየች። ሊገድሏቸው የነበሩት ሰዎች “በዚህች ትንሽ ልጅ ምክንያት ነው የተውናችሁ” በማለት ምሕረት ሊያደርጉላቸው ችለዋል።​—⁠1 ጴጥሮስ 3:​12

15. ጳውሎስ ከየትኞቹ የሚበክሉ ተጽዕኖዎች መጠበቅ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል?

15 አብዛኞቹ ልጆቻችን ከላይ የተገለጹትን ዓይነት እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ላይገጥሟቸው ይችላል፤ ሆኖም በትምህርት ቤትና በዛሬው ጊዜ ባሉት ብልሹ ኅብረተሰቦች ውስጥ ብዙ ፈተናዎች ይገጥሟቸዋል:- ጸያፍ አነጋገር፣ ወሲባዊ ሥዕሎችና ጽሑፎች፣ ወራዳ መዝናኛና መጥፎ ልማዶችን ወደመፈጸም የሚመራ የእኩዮች ተጽዕኖ በብዙ ቦታዎች በእጅጉ የተስፋፉ ነገሮች ናቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ ከእነዚህ ተጽዕኖዎች እንድንጠበቅ በተደጋጋሚ አሳስቧል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 5:​6፤ 15:​33, 34፤ ኤፌሶን 5:​3–7

16. አንድ ሰው ለክብራማ አገልግሎት የሚውል ዕቃ መሆን የሚችለው እንዴት ነው?

16 ጳውሎስ “እኩሌቶቹም ለክብር፣ እኩሌቶቹም ለውርደት” ስለተቀመጡ ዕቃዎች ከተናገረ በኋላ እንዲህ አለ:- “እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ቢያነጻ፣ ለክብር የሚሆን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል።” ስለዚህ ወጣት ልጆቻችን ከክፉ ባልንጀርነት እንዲጠበቁ እናበረታታቸው። ‘ከክፉ የጒልማሳነት ምኞት በመሸሽ በንጹሕ ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን፣ እምነትን፣ ፍቅርንና ሰላምን አጥብቀው ይከተሉ።’ (2 ጢሞቴዎስ 2:​20–22) ‘እርስ በርስ ለመተናነጽ’ የሚያገለግል የቤተሰብ ፕሮግራም ወጣት ልጆቻችንን በመቅረጽ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ያበረክታል። (1 ተሰሎንቄ 5:​11፤ ምሳሌ 22:​6) በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብና ተስማሚ የሆኑትን የማኅበሩን ጽሑፎች በመጠቀም ማጥናት በጣም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

ሁሉንም ለመቅረጽ የሚያስችል መንገድ

17. ተግሣጽ የሚቀርጸን እንዴት ነው? የሚያስገኘው አስደሳች ውጤትስ ምንድን ነው?

17 ይሖዋ እኛን ለመቅረጽ በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት ምክር ይሰጠናል። እንዲህ ዓይነቱን አምላካዊ ምክር ከመቀበል ወደ ኋላ አትበሉ! ለዚህ ምክር ጥበብ የተሞላበት ምላሽ በመስጠት ይሖዋ ለክብራማ አገልግሎት ሊጠቀምባችሁ በሚችልበት መንገድ እንዲቀርፃችሁ ፍቀዱለት። ምሳሌ 3:​11, 12 የሚከተለውን ምክር ይሰጣል:- “ልጄ ሆይ፣ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ፣ በገሠጸህም ጊዜ አትመረር። እግዚአብሔር የወደደውን ይገሥጻልና፣ አባት የሚወድደውን ልጁን እንደሚገሥጽ።” በዕብራውያን 12:​6–11 ላይም ሌላ አባታዊ ምክር ሠፍሮ ይገኛል:- “ጌታ የሚወደውን ይቀጣዋልና . . . ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፣ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል።” እንዲህ ዓይነቱ ተግሣጽ የሚሰጥበት ዋነኛው መንገድ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል መሆን አለበት።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17

18. ንስሐን በተመለከተ ከሉቃስ ምዕራፍ 15 ምን ትምህርት እናገኛለን?

18 ይሖዋ መሐሪም ነው። (ዘጸአት 34:​6) በጣም ከባድ ኃጢአት የሠራ ሰው እንኳ ከልቡ ንስሐ ከገባ ይቅር ይለዋል። ዘመናዊ ‘አባካኞችም’ እንኳ ለክብራማ አገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎች ሆነው ሊቀረጹ ይችላሉ። (ሉቃስ 15:​22–24, 32) ኃጢአታችን የአባካኙን ልጅ ያህል የከፋ ላይሆን ይችላል። ሆኖም ለቅዱስ ጽሑፋዊው ምክር ትሕትና የተሞላበት ምላሽ መስጠታችን ዘወትር ለክብራማ አገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎች መሆን በምንችልበት መንገድ እንድንቀረጽ ይረዳናል።

19. ምንጊዜም በይሖዋ እጅ ውስጥ ክቡር ዕቃዎች ሆነን ማገልገል የምንችለው እንዴት ነው?

19 በመጀመሪያ እውነትን በተማርንበት ጊዜ ይሖዋ እንዲቀርጸን ፈቃደኞች መሆናችንን አሳይተናል። ዓለማዊ መንገዶችን ትተን አዲሱን ሰውነት መልበስ ከመጀመራችንም በላይ ራሳችንን ወስነን የተጠመቅን ክርስቲያኖች ሆነናል። ‘በቀድሞ አኗኗራችን ለብሰነው የነበረውን አሮጌ ሰውነት አታላይ ከሆኑት ምኞቶች ጋር አንድ ላይ አስወግደን በእውነተኛ ጽድቅና ታማኝነት እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውን አዲሱን ሰውነት በመልበስ’ በኤፌሶን 4:​20–24 ላይ የሚገኘውን ምክር ተከትለናል። ሁላችንም በግለሰብ ደረጃ ዘወትር ለክብራማ አገልግሎቱ የምንውል ዕቃዎች ሆነን በማገልገል ምንጊዜም በታላቁ ሸክላ ሠሪ በይሖዋ እጅ ውስጥ በቀላሉ የተፈለገውን ዓይነት ቅርጽ የምንይዝ ሆነን እንገኝ!

[ለክለሳ ያህል]

◻ ታላቁ ሸክላ ሠሪ ለምድራችን ያለው ዓላማ ምንድን ነው?

◻ ለክብራማ አገልግሎት ልትቀረጽ የምትችለው እንዴት ነው?

◻ ልጆቻችን በምን መንገድ ሊቀረጹ ይችላሉ?

◻ ተግሣጽን በተመለከተ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክብራማ ለሆነ አገልግሎት ለመቀረጽ ምቹ ነህን? ወይስ አይደለህም?

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆች ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ሊቀረጹ ይችላሉ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ