“ይሖዋ” ወይስ “ያህዌህ”?
“ድቅል፣” “ክልስ ቃል፣” “ባዕድ ስያሜ።” መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበትን ዕብራይስጥ የሚያጠኑ ምሁራን እንዲህ ያሉ የተጋነኑ ቃላትን እንዲጠቀሙ ያደረጋቸው ምንድን ነው? አከራካሪው ጉዳይ በእንግሊዝኛ “ጀሆቫ” የሚለው የአምላክ ስም አጠራር ትክክለኛ ነው ወይስ አይደለም የሚል ነው። ይህ ጉዳይ ከአንድ መቶ ለሚበልጡ ዓመታት ሲያወዛግብ ቆይቷል። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ አብዛኞቹ ምሁራን ሁለት ክፍለ ቃል ያለውን “ያህዌህ” የሚለውን ስም ወደ መጠቀም ያዘነበሉ ይመስላሉ። ይሁንና “ጀሆቫ” የሚለው አጠራር በእርግጥ “ባዕድ ስያሜ” ነው?
የውዝግቡ መነሾ
ስሙን ለሰው ልጆች የነገረው ራሱ አምላክ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘጸአት 3:15) ቅዱስ ጽሑፋዊው ማስረጃ እንደሚያሳየው የጥንት የአምላክ አገልጋዮች ስሙን በስፋት ይጠቀሙበት ነበር። (ዘፍጥረት 12:8፤ ሩት 2:4) የአምላክ ስም በሌሎች ሕዝቦችም ዘንድ የታወቀ ነበር። (ኢያሱ 2:9) በተለይ ይህ የሆነው አይሁዶች ከባቢሎን ግዞት ከተመለሱ በኋላ ከብዙ አገር ሕዝቦች ጋር ግንኙነት ፈጥረው ስለነበር ነው። (መዝሙር 96:2–10፤ ኢሳይያስ 12:4፤ ሚልክያስ 1:11) ዚ ኢንተርፕሬተርስ ዲክሺነሪ ኦቭ ዘ ባይብል እንዲህ ይላል:- “አይሁዳውያን ከግዞት ከተመለሱ በኋላ ባሉት ዘመናት ብዙ ቁጥር ያላቸው የባዕድ አገር ሰዎች በአይሁዳውያን ሃይማኖት ተስበው እንደነበር የሚያሳይ በርካታ ማስረጃ አለ።” ይሁን እንጂ በአንደኛው መቶ ዘመን እዘአ የአምላክን ስም በሚመለከት አጉል እምነት እየዳበረ መጣ። በመጨረሻም የአይሁድ ብሔር በአምላክ ስም በግልጽ መጠቀሙን ከማቆሙም በላይ አንዳንዶች እንዲያውም ስሙ እንዳይጠራ መከልከል ጀመሩ። ከዚህ የተነሣ ትክክለኛ አጠራሩ ጠፋ፤ ግን ትክክለኛ አጠራሩ ጨርሶ አይታወቅም ማለት ነው?
በስም ውስጥ ምን ሊገኝ ይችላል?
በዕብራይስጥ ቋንቋ የአምላክ ስም ሲጻፍ יהוה ነው። ከቀኝ ወደ ግራ የሚነበቡት እነዚህ አራት ፊደላት በተለምዶ ቴትራግራማተን ተብለው ይጠራሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ በርካታ የሰውና የቦታ ስሞች የመለኮታዊውን ስም አኅጽሮተ ቃል ይዘዋል። ታዲያ እነዚህ የተጸውኦ ስሞች የአምላክ ስም እንዴት ይጠራ እንደነበር የሚሰጡን ፍንጭ ይኖር ይሆን?
በዩናይትድ ስቴትስ፣ ዋሺንግተን ዲሲ የሚገኘው የዌስሊ ቲኦሎጂካል ሴሚናሪ የክብር ፕሮፌሰር የሆኑት ጆርጅ ቡካነን እንደሚሉት ከሆነ መልሱ አዎን፣ ይኖራል የሚል ነው። ፕሮፌሰር ቡካነን እንዲህ ሲሉ አብራርተዋል:- “በጥንት ዘመን ወላጆች አብዛኛውን ጊዜ ለልጆቻቸው ስም የሚያወጡት በአማልክቶቻቸው ስም ነበር። ይህ ማለት ደግሞ የልጆቻቸውን ስም የሚጠሩት የአምላካቸውን ስም በሚጠሩበት መንገድ ነው ማለት ነው። ቴትራግራማተን በሰዎች ስሞች ውስጥ ተጠቅሶ ይገኝ የነበረ ሲሆን ሰዎቹ ሁልጊዜ ይጠቀሙ የነበረው የመካከለኛውን አናባቢ ነበር።”
የአምላክ ስም አጭር አጠራር የሚገኝባቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ጥቂት የተጸውኦ ስሞች ምሳሌዎችን ተመልከት። ፕሮፌሰር ቡካነን በዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ዮህኔታን ወይም የሆህኔታን ተብሎ የተጻፈው ዮናታን የሚለው ስም “ያሆ ወይም ያሆዋህ ሰጠ” የሚል ትርጉም እንዳለው ይናገራሉ። የነቢዩ ኤልያስ ስም በዕብራይስጥ ኤላይያህ ወይም ኤላይያሁ ነው። እንደ ፕሮፌሰር ቡካነን አባባል ስሙ “አምላኬ ያሁ ወይም ያሁዋህ ነው” የሚል ትርጉም አለው። በተመሳሳይም ኢዮሣፍጥ የሚለው ስም በዕብራይስጥ ዬሆህሻፋት ሲሆን ትርጉሙም “ያሆ ፈረደ” ነው።
“ያህዌህ” እንደሚለው ያለ የቴትራግራማተን የሁለት ክፍለ ቃላት አጠራር ኦ የምትባለው አናባቢ ፊደል የአምላክ ስም ክፍል እንዳትሆን ያደርጋል። ሆኖም መለኮታዊው ስም የሚገኝባቸው በደርዘን የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ስሞች በረዥሙም ሆነ በአጭሩ በሚጻፉበት ጊዜ ይህ በመካከል የሚገባው አናባቢ ድምፅ የሚገኝ ሲሆን ጀሆኔታን እና ጆኔታን የሚለውን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። ይህም በመሆኑ ፕሮፌሰር ቡካነን መለኮታዊውን ስም አስመልክተው እንዲህ ብለዋል:- “ኡ ወይም ኦ የሚለው አናባቢ በምንም መንገድ አይቀርም ነበር። ቃሉ አንዳንድ ጊዜ ‘ያ’ ተብሎ በአጭሩ ቢጠራም ‘ያዌህ’ ተብሎ ግን አያውቅም። . . . ቴትራግራማተን በአንድ ክፍለ ቃል ሲነበብ ‘ያህ’ ወይም ‘ዮ’ ነው። በሦስት ክፍለ ቃላት በሚነበብበት ጊዜ ደግሞ ‘ያሆዋህ’ ወይም ‘ያሁዋህ’ መባል አለበት። በሁለት ክፍለ ቃላት ሊጠራ የሚችልበት አጋጣሚ ከተፈጠረ ደግሞ ‘ያሆ’ ይሆን ነበር።”—ቢብሊካል አርኬኦሎጂ ሪቪው
እነዚህ ትንታኔዎች ጌዜኒዩስ የተባለው የ19ኛው መቶ ዘመን የዕብራይስጥ ምሁር ሂብሩ ኤንድ ካለዲ ሌክሲከን ቱ ዚ ኦልድ ቴስታመንት ስክሪፕቸርስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ያሰፈሩትን ሐሳብ ለመረዳት ያስችሉናል:- “[የአምላክ ስም] ትክክለኛ አጠራር יְהוָֹה [ዬሆዋህ] ነበር የሚሉት ክፍሎች ለአባባላቸው ምንም መሠረት የላቸውም ማለት አይቻልም። ብዙ የተጸውኦ ስሞች የሚጀምሩባቸው יְהוֹ [ዬሆ] እና יוֹ [ዮ] የሚሉት በአጭሩ የተጻፉ ክፍለ ቃላት ይበልጥ አጥጋቢ በሆነ ሁኔታ ሊብራሩ የሚችሉት የአምላክ ስም በዚህ መንገድ ሲጠራ ነው።”
ይሁንና ኤቨረት ፎክስ በቅርብ ጊዜ ባወጡት ዘ ፋይቭ ቡክስ ኦቭ ሞሰስ በተባለው የትርጉም ሥራቸው መቅድም ላይ እንዲህ ብለዋል:- “‘ትክክለኛ’ የሚባለውን [የአምላክን] የዕብራይስጥ ስም አጠራር መልሶ ለማግኘት ሲባል ጥንትም ሆነ ዛሬ የተደረጉ ሙከራዎች ስኬታማ ሊሆኑ አልቻሉም፤ አልፎ አልፎ የሚሰማው ‘ይሖዋ’ (በእንግሊዝኛ ‘ጀሆቫ’) የሚለውም ሆነ በምሁራን ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው ‘ያህዌህ’ የሚለው አጠራር ትክክለኛነት ሙሉ በሙሉ ሊረጋገጥ አይችልም።”
ምሁራዊው እሰጥ አገባ እንደሚቀጥል ምንም አያጠራጥርም። አይሁዳውያን የእውነተኛውን አምላክ ስም መጥራት ያቆሙት ማሶሬቶች አናባቢን የሚጠቁሙ ምልክቶችን መጠቀም ከመጀመራቸው በፊት ነበር። ይህም በመሆኑ የሐወሐ (יהוה) ለሚሉት ተነባቢዎች የገቡት አናባቢዎች የትኞቹ እንደሆኑ በግልጽ ለማወቅ አይቻልም። ይሁንና ትክክለኛው አጠራራቸው ያልጠፋው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰው የሚገኙ የታዋቂ ሰዎች ስሞች ስለ አምላክ ስም ጥንታዊ አጠራር ጉልህ ፍንጭ ይሰጡናል። ከዚህ የተነሣ ቢያንስ የተወሰኑ ምሁራን “ይሖዋ” (በእንግሊዝኛ “ጀሆቫ”) የሚለው አጠራር “ባዕድ ስያሜ” አለመሆኑን ይስማማሉ።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ጀሆቫ” በሰፊው የሚታወቅ የአምላክ ስም አጠራር ሆኖ ቆይቷል