ትዳርን የተሳካ ለማድረግ ቁልፉ ምንድን ነው?
ዋና ከመማርህ በፊት ዘለህ ውኃ ውስጥ ለመግባት ትፈልጋለህ? እንዲህ ያለው የሞኝነት ድርጊት ጉዳት የሚያስከትል ከመሆንም አልፎ ሕይወት ሊያሳጣ ይችላል። ሆኖም ትዳር የሚያስከትላቸውን ኃላፊነቶች መወጣት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ አስቀድመው ሳያገናዝቡ ወደ ትዳር ዓለም ዘው ብለው የሚገቡ ስንቶቹ እንደሆኑ እስቲ አስብ።
ኢየሱስ “ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደሚያ የሚበቃ ያለው እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ ኪሳራውን የማይቆጥር ማን ነው?” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 14:28) ግንብ መገንባትን በተመለከተ የተነገረው ይህ ምክር ትዳር መመሥረትን በተመለከተም ይሠራል። ትዳር መመሥረት የሚፈልጉ ሁሉ ትዳር የሚጠይቅባቸውን ነገሮች ማሟላት ይችሉ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ አስቀድመው ኪሳራቸውን ማስላት ይኖርባቸዋል።
ስለ ጋብቻ ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘት
ደስታንም ሆነ ሐዘንን የሚጋራ የትዳር ጓደኛ ማግኘት በእርግጥም በረከት ነው። ጋብቻ በብቸኝነት ወይም በተስፋ መቁረጥ ምክንያት የሚከሰተውን የባዶነት ስሜት ሊያስቀር ይችላል። እንደ ማፍቀር፣ ተጓዳኝ ማግኘትና መቀራረብ ያሉትን ከፍተኛ የሆኑ ተፈጥሯዊ ፍላጎቶቻችንን ሊያረካልን ይችላል። አምላክ አዳምን ከፈጠረ በኋላ “ሰው ብቻውን መኖሩ መልካም አይደለም፤ ስለዚህ ተስማሚና ረዳት ጓደኛ እፈጥርለታለሁ” ሲል የተናገረው ያለ ምክንያት አይደለም።—ዘፍጥረት 2:18 የ1980 ትርጉም፤ 24:67፤ 1 ቆሮንቶስ 7:9
አዎን፣ ማግባት ለአንዳንድ ችግሮች መፍትሄ ሊያስገኝ ይችላል። ይሁን እንጂ እንግዳ የሆኑ ሌሎች ችግሮችንም ያመጣል። ለምን? ምክንያቱም ጋብቻ ምናልባት አቻ የሆኑ ሆኖም ፍጹም አንድ ዓይነት ሊሆኑ የማይችሉ የተለያየ ባሕርያት ያላቸው የሁለት ሰዎች ጥምረት ነው። ሌላው ቀርቶ አቻ ናቸው በተባለላቸው በሁለት የትዳር ጓደኛሞች መካከል እንኳን አልፎ አልፎ አለመግባባት ሊፈጠር ይችላል። ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ “ያገቡ በሥጋቸው ላይ መከራ ይሆንባቸዋል” ወይም ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል እንዳስቀመጠው “በሥጋ የሕይወት ዘመናቸው ሕመምና ሐዘን ይገጥማቸዋል” በማለት ጽፏል።—1 ቆሮንቶስ 7:28
ጳውሎስ ጋብቻን በተመለከተ አፍራሽ አመለካከት ነበረው ማለት ነውን? በፍጹም! ለማግባት የሚያስቡ ሰዎች እውነታውን እንዲቀበሉ አጥብቆ መምከሩ ብቻ ነው። አንድን ሰው በማፍቀር የሚገኘው የደስታ ስሜት ከሰርጉ ቀን በኋላ ባሉት ወራትና ዓመታት ለሚኖረው የጋብቻ ሕይወት ትክክለኛ መመዘኛ አይደለም። እያንዳንዱ ጋብቻ የራሱ የሆነ ተፈታታኝ ሁኔታዎችና ችግሮች አሉት። አሁን ጥያቄው እነዚህ ችግሮች ወደፊት ይከሰታሉ ወይም አይከሰቱም የሚል ሳይሆን በሚከሰቱበት ጊዜ መወጣት የሚቻለው እንዴት ነው የሚል ነው።
ችግሮች፣ አንድ ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር እውነተኛነት ማረጋገጥ የሚችሉበት አጋጣሚ ይከፍቱላቸዋል። በምሳሌ ለማስረዳት:- ወደብ ላይ የቆመ አንድ የመጓጓዣ መርከብ ጠንካራ ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ አስተማማኝ መሆኑ የሚረጋገጠው በባሕር ላይ በሚያደርገው ጉዞ ምናልባትም አንድን ከባድ ማዕበል ተቋቁሞ ሲያልፍ ነው። በተመሳሳይም የአንድ ጋብቻ ሰንሰለት ጥንካሬ የሚለካው ፍቅር ባየለበት ሰላማዊ ወቅት ላይ አይደለም። ጥንካሬው የሚፈተነው ባልና ሚስቱ እንደ ማዕበል ያሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁመው ሲያልፉ ነው።
ይህን ለማድረግ አንድ ወንድ ‘በሚስቱ ይጣበቃል’ ከዚያም “ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ከሚለው አምላክ ካወጣው ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ የተጋቡ ባልና ሚስት በቃል ኪዳን መተሣሠር ይኖርባቸዋል። (ዘፍጥረት 2:24) ብዙዎች በቃል ኪዳን መታሠር የሚለው ሐሳብ ያስፈራቸዋል። ይሁንና ከልብ የሚዋደዱ ሁለት ሰዎች አንድ ላይ ለመኖር በቃል ኪዳን መተሣሠራቸው ምክንያታዊ ነው። በቃል ኪዳን መተሣሠር ትዳርን ክብራማ ያደርገዋል። ድንገተኛ የሆነ ምንም ነገር ይከሰት ባልና ሚስቱ አንዳቸው ሌላውን የሚደግፉ ለመሆናቸው አስተማማኝ መሠረት ይሰጣል።a በዚህ መንገድ በቃል ኪዳን ለመታሠር ዝግጁ ካልሆንክ ትዳር ለመመሥረትም ዝግጁ አይደለህም ማለት ነው። (ከመክብብ 5:4, 5 ጋር አወዳድር።) ያገቡም ቢሆኑ በቃል ኪዳን መታሠር ዘላቂ ለሆነ ጋብቻ ወሳኝ መሆኑን በተመለከተ ያላቸውን አድናቆት ማሳደግ ይኖርባቸዋል።
ራስን ማወቅ
የትዳር ጓደኛህ እንድትሆን የምትፈልጋት ሴት እንዲኖራት የምትፈልገውን ባሕርያት በዝርዝር ማስቀመጥ እንደምትችል ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ለትዳር የበኩልህን አስተዋጽዖ ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ለመገንዘብ መጀመሪያ ራስህን ማወቁ ይበልጥ አስቸጋሪ ነው። የጋብቻ መሃላ ከመፈጸሙ በፊትም ሆነ በኋላ ራስን መመርመሩ እጅግ አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ።
• ከትዳር ጓደኛዬ ጋር ዕድሜ ልክ በቃል ኪዳን ለመታሠር ፈቃደኛ ነኝን?—ማቴዎስ 19:6
በነቢዩ ሚልክያስ ዘመን በርካታ ባሎች ወጣት ሴቶችን ለማግባት ብለው ሳይሆን አይቀርም የቀድሞ ሚስቶቻቸውን ትተው ሄደው ነበር። ይሖዋ መሠዊያው ባሎቻቸው በተዉአቸው ሚስቶች እንባ እንደተሞላ በመናገር ሚስቶቻቸውን ‘የሚያታልሉ’ ወንዶችን አውግዟል።—ሚልክያስ 2:13-16
• ለማግባት የማስብ ከሆነ የፆታ ስሜት የሚያይልበትንና ትክክለኛ ውሳኔ እንዳላደርግ ተጽዕኖ ሊያሳድርብኝ የሚችለውን የወጣትነት ዕድሜን አልፌአለሁን?—1 ቆሮንቶስ 7:36
በሃያ ሁለት ዓመቷ ያገባችው ኒክ “በልጅነት ማግባት በጣም አደገኛ ነው” በማለት ትናገራለች። እንዲህ በማለት የማስጠንቀቂያ ምክር ትሰጣለች:- “ከአሥራዎቹ እድሜ ክልል መገባደጃ ጀምሮ እስከ ሃያዎቹ አጋማሽ ብሎም እስከ ሃያዎቹ መገባደጃ ድረስ ስሜቶቻችሁ፣ ግቦቻችሁና ፍላጎቶቻችሁ መለዋወጣቸውን ይቀጥላሉ።” እርግጥ ነው አንድ ሰው ለማግባት መድረሱ የሚለካው በዕድሜ ብቻ አይደለም። ሆኖም የፆታ ስሜት ገና የሚጀምርበትንና በተለይ ደግሞ በጣም የሚያይልበትን አፍላ የወጣትነት ዕድሜ ሳያልፉ ማግባት አስተሳሰብን ሊያዛባና ወደፊት ሊመጡ የሚችሉ ችግሮች እንዳይታዩ ሊጋርድ ይችላል።
• የምመሠርተው ትዳር የተሳካ ይሆን ዘንድ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ምን ምን ባሕርያት አሉኝ?—ገላትያ 5:22, 23
ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች ሲጽፍ “ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ” ብሏል። (ቆላስይስ 3:12) ማግባት ለሚያስቡም ሆነ ላገቡ ይህ ምክር በጣም አስፈላጊ ነው።
• አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚፈጠሩበት ጊዜ የትዳር ጓደኛዬን ለመደገፍ የሚያስችል ጉልምስና አለኝን?—ገላትያ 6:2
“ችግሮች በሚነሱበት ጊዜያት” ይላሉ አንድ ሐኪም “ብዙውን ጊዜ የሚታየው ዝንባሌ በትዳር ጓደኛ ላይ ማሳበብ ነው። አንገብጋቢው ጉዳይ ጥፋተኛው ማን መሆኑ አይደለም። ከዚያ ይልቅ የጋብቻ ትስስርን ይበልጥ ለማጠንከር ባልና ሚስት ተግባብተው መሥራት የሚችሉት እንዴት ነው የሚለው ጉዳይ ነው።” ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን የተናገራቸው ቃላት ለተጋቡ ወንድና ሴት የሚሠሩ ናቸው። “አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል። ቢወድቁ አንዱ ሁለተኛውን ያነሣዋልና፤ አንዱ ብቻውን ሆኖ በወደቀ ጊዜ ግን የሚያነሣው ሁለተኛ የለውምና ወዮለት” ሲል ጽፏል።—መክብብ 4:9, 10
• በአብዛኛው ደስተኛና ብሩህ አመለካከት ያለኝ ነኝ ወይስ በትንሽ በትልቁ የሚከፋኝና አፍራሽ አስተሳሰብ የተጠናወተኝ ነኝ?—ምሳሌ 15:15
አፍራሽ አስተሳሰብ የተጠናወተው ሰው እያንዳንዱ ቀን መጥፎ እንደሆነ አድርጎ ይመለከታል። ትዳር እንዲህ ያለውን አመለካከት በተዓምራዊ ሁኔታ አይለውጠውም! በአብዛኛው ነቃፊ ወይም አፍራሽ አመለካከት ያላቸው ነጠላ ወንድ ወይም ነጠላ ሴት ካገቡም በኋላ ይህንኑ የነቃፊነትና የተስፋ ቢስነት ባሕርይ ይዘው ይኖራሉ። እንዲህ ያለው አፍራሽ አመለካከት በትዳር ውስጥ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።—ከምሳሌ 21:9 ጋር አወዳድር።
• የሚያበሳጭ ነገር ሲገጥመኝ መንፈሴን እቆጣጠራለሁ ወይስ ቶሎ በቁጣ እገነፍላለሁ?—ገላትያ 5:19, 20
ክርስቲያኖች ‘ለቁጣ የዘገዩ’ እንዲሆኑ ታዝዘዋል። (ያዕቆብ 1:19) ከማግባታቸው በፊትም ሆነ ካገቡ በኋላ አንድ ወንድ ወይም አንዲት ሴት “ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ” በሚለው ምክር መሠረት ለመመላለስ የሚያስችል ችሎታ ማዳበር ይኖርባቸዋል።—ኤፌሶን 4:26
የወደፊት የትዳር ጓደኛን ማወቅ
“ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል” በማለት የምሳሌ መጽሐፍ ይናገራል። (ምሳሌ 14:15) ይህ ምሳሌ የትዳር ጓደኛን በመምረጥ ረገድም በትክክል ይሠራል። አንድ ወንድ ወይም አንዲት ሴት በሕይወት ዘመናቸው ከሚያደርጓቸው ትልልቅ ውሳኔዎች መካከል አንዱ የትዳር ጓደኛ መምረጥ ነው። ሆኖም ብዙ ሰዎች የሚያገቡትን ሰው ለመምረጥ ከሚያጠፉት ጊዜ ይልቅ የሚገዙትን መኪና ወይም የሚማሩበትን ትምህርት ቤት ለመምረጥ የሚያጠፉት ጊዜ ይበልጣል።
በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ይዘው እንዲያገለግሉ አደራ የሚሰጣቸው ሁሉ ‘የሚበቁ ስለ መሆናቸው አስቀድመው ይፈተናሉ።’ (1 ጢሞቴዎስ 3:10) ለማግባት የምታስብ ከሆነ ሌላኛው ወገን ‘ይበቃ’ እንደሆነና እንዳልሆነ መፈተን እንደምትፈልግ የታወቀ ነው። ለምሳሌ ቀጥለው የተዘረዘሩትን ጥያቄዎች መርምር። ምንም እንኳ ጥያቄዎቹ ወንዶችን ለመመዘን በሚያስችል መንገድ የቀረቡ ቢሆኑም ብዙዎቹ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለሴቶችም ይሠራሉ። እንዲሁም ቀደም ብለው ያገቡም ቢሆኑ እነዚህን ነጥቦች በመመርመር ጥቅም ሊያገኙ ይችላሉ።
• በሰዎች ዘንድ ያተረፈው ስም ምን ዓይነት ነው?—ፊልጵስዩስ 2:19-22
ምሳሌ 31:23 ‘በአገር ሽማግሌዎች መካከል በሸንጎ በተቀመጠ ጊዜ በበር የታወቀ ስለሆነ’ አንድ ባል ይናገራል። የከተማው ሽማግሌዎች በከተማው መግቢያ በር ይቀመጡ የነበረው የፍርድ ጉዳዮችን ለማየት ነበር። ይህ የሚያመለክተው ደግሞ ሰውዬው የሕዝብ አመኔታ ያተረፈ መሆኑን ነው። ሌሎች ሰዎች ስለ አንድ ግለሰብ የሚኖራቸው ግምት ሰውዬው ምን ዓይነት ስም እንዳተረፈ የሚጠቁመው ነገር ይኖራል። በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚገኝ ሰው ከሆነ ደግሞ በሥሩ ያሉት ሰዎች እንዴት አንደሚመለከቱት ለማወቅ ሞክሪ። ይህም ወደፊት ሚስቱ በምትሆኚበት ጊዜ እንዴት እንደምትመለከችው ከወዲሁ ሊጠቁም ይችላል።—ከ1 ሳሙኤል 25:3, 23-25 ጋር አወዳድር።
• ምን ዓይነት ሥነ ምግባር ያለው ነው?
አምላካዊ ጥበብ “በመጀመሪያ ንጽሕት ናት።” (ያዕቆብ 3:17) የትዳር ጓደኛ ይሆነኛል ብለሽ ያሰብሽው ሰው እርሱና አንቺ በአምላክ ፊት ከሚኖራችሁ አቋም ይልቅ ይበልጥ የሚጨነቀው ስለ ራሱ የፆታ ፍላጎት ነው? አሁን በአምላክ የሥነ ምግባር አቋም ለመመላለስ ጥረት የማያደርግ ከሆነ ከተጋባችሁ በኋላ ይህን ጥረት ያደርጋል ብሎ ለማመን ምን ዋስትና ይኖራል?—ዘፍጥረት 39:7-12
• ባገባው በምን ዓይነት ሁኔታ ይይዘኛል?—ኤፌሶን 5:28, 29
የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ በሚስቱ ‘ስለሚታመን’ ባል ይናገራል። ከዚያም በላይ “ያመሰግናታል።” (ምሳሌ 31:11, 28) ተገቢ ባልሆነ መንገድ አይቀናም ወይም ከልክ በላይ ከሌሎች አይጠብቅም። ያዕቆብ ላይኛይቱ ጥበብ “ሰላማዊ፣ ምክንያታዊ . . . ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት” እንደሆነች ጽፏል።—ያዕቆብ 3:17 NW
• ከቤተሰቡ አባላት ጋር ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል?—ዘጸአት 20:12
ወላጆችን ማክበር ለትንንሽ ልጆች ብቻ የተሰጠ ትእዛዝ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “የወለደህን አባትህን ስማ፣ እናትህም ባረጀች ጊዜ አትናቃት” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 23:22) ዶክተር ደብልዩ ሃይ ሚሰልዲን እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “ለመጋባት በዝግጅት ላይ ያሉት ሙሽራውና ሙሽሪት አልፎ አልፎ አንዱ የሌላውን ቤተሰብ ጎራ ብለው ቢጎበኙና እጮኛቸው ከወላጆቹ ጋር ያለውን ግንኙነት ቢመለከቱ በትዳር ውስጥ ብቅ የሚሉ በርካታ ችግሮችንና ያለመጣጣም ሁኔታዎችን ማስወገድ በቻሉ ነበር። ወላጆቹን የሚመለከትበት መንገድ የትዳር ጓደኛውን እንዴት እንደሚመለከት የሚጠቁም ይሆናል። ስለዚህ አንድ ሰው እንዲህ ብሎ መጠየቅ አለበት:- ‘ወላጆቹን በሚይዝበት መንገድ እንዲይዘኝ እፈልጋለሁ?’ ወላጆቹ እርሱን የሚይዙበት መንገድ ራሱን እንዴት አድርጎ እንደሚይዝና በጫጉላነት ከምታሳልፉት ጊዜ በኋላ እንዴት አድርገሽ እንድትይዢው እንደሚፈልግ ጥሩ አድርጎ የሚጠቁም ይሆናል።”
• ቶሎ የመቆጣት ወይም የመሳደብ ባሕርይ ይታይበታልን?
መጽሐፍ ቅዱስ “መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ” በማለት ይመክራል። (ኤፌሶን 4:31) ጳውሎስ “ምርመራን በቃልም መዋጋትን” ስለሚናፍቁና “ቅንዓትና ክርክር ስድብም ክፉ አሳብም እርስ በርስ መናደድም” ስለሞላባቸው ሰዎች በመናገር ጢሞቴዎስን አስጠንቅቆታል።—1 ጢሞቴዎስ 6:4, 5
ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ በጉባኤ ውስጥ ለኃላፊነት ብቁ የሆነ ሰው “የማይማታ” ወይም በግሪክኛው በኩረ ጽሑፍ ደግሞ “ቡጢ የማይሰነዝር” መሆን እንዳለበት ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 3:3፣ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ።) ሰዎችን በአካልም ሆነ በቃል የሚማታ መሆን የለበትም። ትንሽ ሲቆጣ መደባደብ የሚቀናው ሰው ተስማሚ የትዳር ጓደኛ አይደለም።
• ግቦቹ ምንድን ናቸው?
አንዳንዶች ባለጠግነትን ሲያሳድዱ ሊቀር የማይችለውን መዘዝ ያጭዳሉ። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) ሌሎች ደግሞ በሕይወታቸው ውስጥ ምንም ግብ ሳይኖራቸው ዝም ብለው በመዋለል ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ። (ምሳሌ 6:6-11) ይሁን እንጂ ለአምላክ የማደር ባሕርይ ያለው ሰው “እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን” በማለት ቁርጥ ያለ አቋም የወሰደውን የኢያሱን ምሳሌ ይከተላል።—ኢያሱ 24:15
በረከቶችና ኃላፊነቶች
ጋብቻ መለኮታዊ ተቋም ነው። የፈቀደውም ሆነ ያቋቋመው ይሖዋ አምላክ ነው። (ዘፍጥረት 2:22-24) እርሱ ጋብቻን የመሠረተበት ዓላማ አንዱ ለሌላው ረዳት መሆን ይችል ዘንድ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል ሊበጠስ የማይችል ለሁልጊዜው የሚኖር ትስስር እንዲኖር ለማድረግ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ሲውሉ አንድ ባልና ሚስት መላ ሕይወታቸው ደስታ የሰፈነበት ይሆናል ብለው ሊጠባበቁ ይችላሉ።—መክብብ 9:7-9
ሆኖም ‘አስጨናቂ በሆነ ዘመን ውስጥ’ እንደምንኖር መዘንጋት የለበትም። በዚህ ዘመን የሚኖሩ ሰዎች ‘ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ’ እንደሚሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ተንብዮአል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-4) እነዚህ ጠባዮች በትዳር ላይ ይህ ነው የማይባል ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። ስለዚህ ለማግባት የሚያስቡ ሁሉ ወጪያቸውን በጥንቃቄ ማስላት ይኖርባቸዋል። ያገቡም ቢሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን መለኮታዊ መመሪያ በመማርና በሥራ ላይ በማዋል የጋብቻ ትስስራቸውን ይበልጥ ለማጠንከር መጣራቸውን መቀጠል ይኖርባቸዋል።
አዎን፣ ለማግባት የሚያስቡ ሁሉ ከሠርጋቸው ቀን በኋላ ያለውን ጊዜ አሻግረው ቢመለከቱ የተሻለ ነው። እንዲሁም ሁሉም ስለማግባት ማሰብ ብቻ ሳይሆን የትዳር ሕይወት ምን እንደሚመስልም ማሰብ ይኖርባቸዋል። በፍቅር ስሜት ዝም ብሎ ከመነዳት ይልቅ እውነታውን ግምት ውስጥ ማስገባት ትችል ዘንድ መመሪያ እንዲሰጥህ ይሖዋን ጠይቅ። እንዲህ ካደረግህ የተሳካ ትዳር ለመመሥረት ያለህ አጋጣሚ ሰፊ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a መጽሐፍ ቅዱስ ተፋትቶ እንደገና ለማግባት የሚያስችለው ምክንያት አንድ ብቻ እንደሆነ ይናገራል። ይህም ከጋብቻ ውጭ የፆታ ግንኙነት ከተደረገ ማለትም “ዝሙት” ከተፈጸመ ብቻ ነው።—ማቴዎስ 19:9
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“እስከ ዛሬ ካነበብኩት ሁሉ የሚልቅ ስለ ፍቅር የተሰጠ መግለጫ”
ዶክተር ኬቭን ሊመን “በእርግጥ ፍቅር እንደያዘህ ማወቅ የምትችለው አንዴት ነው?” ሲሉ ጽፈዋል። “ስለ ፍቅር የተሟላ መግለጫ የሚሰጥ አንድ ጥንታዊ መጽሐፍ አለ። መጽሐፉ ከተጻፈ ወደ ሁለት ሺህ ዓመት ገደማ ሆኖታል። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን እስከ ዛሬ ካነበብኩት ሁሉ የሚልቅ ስለ ፍቅር የተሰጠ መግለጫ የሚገኘው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ነው።”
ዶክተር ሊመን እየጠቀሱ ያሉት ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በ1 ቆሮንቶስ 13:4-8 ላይ ያሰፈራቸውን ቃላት ነው።
“ፍቅር ይታገሣል፣ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፣ አይታበይም፤ የማይገባውን አያደርግም፣ የራሱንም አይፈልግም፣ አይበሳጭም፣ በደልን አይቆጥርም፤ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም፤ ሁሉን ይታገሣል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ በሁሉ ይጸናል።”
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ስሜት አታላይ ሊሆን ይችላል
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ትኖር የነበረችው ሱላማጢሷ ሴት ስሜታዊ ፍቅር ያለውን የማታለል ኃይል በሚገባ የተገነዘበች ትመስላለች። ኃያሉ ንጉሥ ሰሎሞን ሊያግባባት በሞከረ ጊዜ ለሴት ጓደኞቿ “ፍቅር ራሱ ፈቅዶ እስኪነሣ ድረስ ቀስቅሳችሁ እንዳታስነሡት” በማለት ነግራቸዋለች። (መኃልየ መኃልይ 2:7 የ1980 ትርጉም) ይህች ብልህ ወጣት ጓደኞቿ ስሜቷ እንዲያሸንፋት የሚያደርግ ተጽዕኖ እንዲያደርሱባት አልፈለገችም። ይህ ምክር ዛሬም ለማግባት ለሚያስቡ ሁሉ ተግባራዊ ጠቀሜታ አለው። ስሜታችሁ ወደፈለገው አቅጣጫ እንዳይነዳችሁ ልጓም አብጁለት። ለማግባት የምታስብ ከሆነ ምክንያትህ አንድን ሰው ስለወደድክ እንጂ ለማግባት ሐሳቡ ስላለህ ብቻ መሆን የለበትም።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከተጋቡ ረዥም ጊዜያት ያስቆጠሩም ቢሆኑ የጋብቻ ትስስራቸውን ማጠናከር ይችላሉ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወላጆቹን በምን መንገድ ይይዛል?