በኮምኒስት እገዳ ሥር ያሳለፍኳቸው ከ40 የሚበልጡ ዓመታት
ሚከኤል ቨሲለቪች ሰቪትስኪ እንደተናገረው
የሚያዝያ 1, 1956 መጠበቂያ ግንብ በሚያዝያ 1, 7 እና 8, 1951 የይሖዋ ምሥክሮችን “የመመንጠር ከፍተኛ ዘመቻ” እንደተካሄደ ዘግቧል። መጠበቂያ ግንቡ “እነዚህ ቀናት በሩሲያ በሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ዘንድ ምንጊዜም የማይረሱ ናቸው” ሲል ገልጿል። “በእነዚህ ሦስት ቀናት በምዕራብ ዩክሬይን፣ በኋይት ሩሲያ [ቤላሩስ]፣ በቤሳራቢያ፣ በሞልዳቪያ፣ በላትቪያ፣ በሊቱዋኒያ እና በኢስቶኒያ የሚገኙ ከሰባት ሺህ የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ወንድ ሴት ሳይባል ባጠቃላይ . . . በጋሪ ተጭነው ወደ ባቡር ጣቢያዎች ከተወሰዱ በኋላ በከብት ማጓጓዣ ፉርጎዎች ተጭነው ወደ ሩቅ ቦታ ተወሰዱ።”
ሚያዝያ 8, 1951 ባለቤቴ፣ ገና ስምንት ወር የሆነው ልጄ፣ ወላጆቼ፣ ታናሽ ወንድሜና ሌሎች ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች በዩክሬይን በተርኖፕልና በአካባቢው ከሚገኘው ቤታቸው ተለቃቅመው ተወሰዱ። በከብት ማጓጓዣ ፉርጎዎች ከተጫኑ በኋላ ለሁለት ሳምንታት ያህል ተጓዙ። በመጨረሻም ከባይካል ሐይቅ በስተ ምዕራብ ባለው በደን በተሸፈነው ሳይቤርያ ክልል (መለስተኛው አርክቲክ ጫካ) ሲደርሱ አራገፏቸው።
እኔ አብሬ ያልተጋዝኩት ለምን ነበር? በወቅቱ የት እንደነበርኩና ከዚያ በኋላ በሁላችንም ላይ ምን እንደደረሰ ከመናገሬ በፊት እንዴት የይሖዋ ምሥክር ልሆን እንደቻልኩ ልንገራችሁ።
የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ደረሰን
መስከረም 1947 እኔ ገና የ15 ዓመት ልጅ ሳለሁ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ከተርኖፕል ወደ 50 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ በምትገኝ ስላቪያቲን በምትባል ትንሽ መንደር ወደሚገኘው ቤታችን መጥተው አነጋገሩን። እኔና እናቴ እነዚህን ሁለት ወጣቶች (አንደኛዋ ማሪያ ትባላለች) ቁጭ ብለን ስናዳምጥ ነገሩ እንዲሁ ሌላ ሃይማኖት አለመሆኑን ተገነዘብኩ። ስለ እምነታቸው ያብራሩልን ከመሆኑም በላይ መጽሐፍ ቅዱስን አስመልክቶ የነበሩንን ጥያቄዎች ግልጽ በሆነ መንገድ መለሱልን።
መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን አምን ነበር፤ ሆኖም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚደረገው ነገር ላይ ግን ቅሬታ ነበረኝ። አያቴ እንዲህ ይል ነበር:- “ቄሶች እሳታማ ሲኦል ውስጥ ገብታችሁ ትሰቃያላችሁ እያሉ ሰዎችን ያስፈራራሉ፤ እነርሱ ራሳቸው ግን ምንም ነገር አይፈሩም። ሥራቸው ምስኪኖችን መዝረፍና ማታለል ነው።” በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጀመሪያ መንደራችን ውስጥ በሚኖሩ ፖላንዳውያን ላይ ጥቃት መፈጸሙና ንብረታቸው መቃጠሉ ትዝ ይለኛል። በጣም የሚያሳዝነው ጥቃቱን ያቀነባበሩት የግሪክ ካቶሊክ ቄሶች ናቸው። በኋላም በደርዘን የሚቆጠሩ የግድያ ሰለባዎችን በመመልከቴ ይህ ዓይነቱ ጭካኔ የተፈጸመበትን ምክንያት ለማወቅ ጉጉት አደረብኝ።
ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ እያጠናሁ ስሄድ ምክንያቱ ይገባኝ ጀመር። እሳታማ ሲኦል አለመኖሩን እንዲሁም ሰይጣን ዲያብሎስ ጦርነትና ደም መፋሰስ ለማዛመት በሐሰት ሃይማኖት እንደሚጠቀም የሚገልጸውን እውነት ጨምሮ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ተረዳሁ። የግል ጥናት በማደርግበት ወቅት አልፎ አልፎ ጥናቴን ቆም አደርግና እየተማርኩ ስላለሁት ነገር ለይሖዋ ልባዊ የምስጋና ጸሎት አቀርባለሁ። እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ለታናሽ ወንድሜ ለስታክ አካፍለው ጀመር፤ እሱም እውነትን በመቀበሉ በጣም ተደሰትኩ።
የተማርኩትን በሥራ ላይ ማዋል
በሕይወቴ ውስጥ ለውጥ ማድረግና ወዲያው ሲጋራ ማጨስ ማቆም እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን አንድ ላይ ለማጥናት አዘውትሮ ከሌሎች ጋር መሰብሰብ አስፈላጊ መሆኑን አስተዋልኩ። ለዚህ ስል ስብሰባዎቹ በድብቅ የሚደረጉበት ቦታ ለመድረስ ጫካ አቋርጬ ወደ 10 ኪሎ ሜትር ገደማ በእግር መጓዝ ነበረብኝ። አንዳንድ ጊዜ ስብሰባው ላይ መገኘት የሚችሉት ጥቂት ሴቶች ብቻ ይሆናሉ። በዚህ ጊዜ ምንም እንኳ ገና ያልተጠመቅሁ ብሆንም ስብሰባውን እንድመራ ይጠይቁኝ ነበር።
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ይዞ መገኘት በጣም አደገኛ ነበር፤ እስከ 25 ዓመት የሚደርስ እስራት ሊያስከትል ይችላል። እንደዚህም ሆኖ የራሴ ቤተ መጻሕፍት እንዲኖረኝ እመኝ ነበር። አንድ ጎረቤታችን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያጠና ነበር። ሆኖም ካደረበት ፍርሃት የተነሳ ጥናቱን ከማቋረጡም በላይ ጽሑፎቹን ጓሮው ቆፍሮ ቀብሯቸው ነበር። ሰውየው መጻሕፍቱንና መጽሔቶቹን በሙሉ ከቀበረበት አውጥቶ ለእኔ ለመስጠት በመስማማቱ ይሖዋን በጣም አመሰገንኩ! ሰዎች በማይጠረጥሩበት ቦታ ማለትም በአባቴ የንብ ቀፎዎች ውስጥ ደበቅኋቸው።
ሐምሌ 1949 ሕይወቴን ለይሖዋ ከወሰንኩ በኋላ ውሳኔዬን በውኃ ጥምቀት አሳየሁ። ይህ ቀን በሕይወቴ በጣም የተደሰትኩበት ነበር። በምሥጢር የተካሄደውን የጥምቀት ሥነ ሥርዓት ያከናወነው ወንድም እውነተኛ ክርስቲያን መሆን ቀላል አለመሆኑንና ከፊታችን ብዙ ፈተና እንደሚጠብቀን ጎላ አድርጎ ገለጸልን። ብዙም ሳይቆይ የተናገራቸው ቃላት እውነት መሆናቸውን ተገነዘብኩ! ሆኖም የተጠመቀ ምሥክር ሆኜ የምመራው ሕይወት አስደሳች ጅምርም ነበረው። ከተጠመቅሁ ከሁለት ወራት በኋላ ለእኔና ለእናቴ እውነትን ከነገሩን አንዷን ማለትም ማሪያን አገባሁ።
ለመጀመሪያ ጊዜ ያጋጠመኝ ድንገተኛ ፈተና
ሚያዝያ 16, 1950 ላይ ፖድጌትሲ ከምትባለው ትንሽ ከተማ ወደ ቤት እየተመለስኩ ሳለ ወታደሮች ድንገት አጋጠሙኝና ወደ ጥናት ቡድናችን ይዤ ስሄድ የነበሩትን አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ስላገኙብኝ ታሰርኩ። በእስር ባሳለፍኳቸው የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት በዱላ ከመደብደቤም በላይ መብላትም ሆነ መተኛት ተከልክዬ ነበር። በተጨማሪም እጆቼን ወደ ላይ ዘርግቼ አንድ መቶ ጊዜ ቁጭ ብድግ እንድል ታዘዝኩ። በጣም ስለደከመኝ መጨረስ አልቻልኩም። ከዚህ በኋላ ቀዝቃዛ በሆነና እርጥበት ባለው ምድር ቤት ውስጥ ለ24 ሰዓት ያክል ተዘጋብኝ።
እንዲህ አድርገው ያንገላቱኝ ጽናቴን ለማዳከምና በቀላሉ መረጃ እንዳወጣ ለማድረግ አስበው ነበር። “ጽሑፎቹን ከየት ነው ያመጣሃቸው? ለማንስ ነበር ይዘህ የምትሄደው?” ሲሉ አፋጠጡኝ። አንዳችም ነገር ለመንገር ፈቃደኛ አልሆንኩም። ከዚያም ለፍርድ የምቀርብበት የሕጉ ክፍል ተነበበልኝ። ሕጉ ፀረ-ሶቪዬት የሆነ ጽሑፍ ማሰራጨትም ሆነ ይዞ መገኘት በሞት አሊያም በ25 ዓመት እስራት ያስቀጣል ይላል።
“የትኛውን ቅጣት ትመርጣለህ?” ሲሉ ጠየቁኝ።
“አንዳቸውንም አልመርጥም፤ ሆኖም በይሖዋና እርሱ በሚሰጠኝ ድጋፍ ስለምታመን እርሱ የፈቀደውን ማንኛውንም ነገር እቀበላለሁ” ስል መለስኩ።
ከሰባት ቀናት በኋላ በነፃ መለቀቄ ፈጽሞ ያልጠበኩት ነገር ነበር። ይህ ተሞክሮ ይሖዋ “አልለቅህም ከቶም አልተውህም” ሲል የገባው ቃል ምን ያህል እውነት እንደሆነ እንዳስተውል ረድቶኛል።—ዕብራውያን 13:5
ቤት በተመለስኩበት ወቅት በጣም ታምሜ ነበር፤ ሆኖም አባባ አሳከመኝና በጥቂት ጊዜ ውስጥ አገገምኩ። ምንም እንኳ አባቴ የተቀረነው የቤተሰቡ አባላት የያዝነውን ሃይማኖታዊ እምነት ባይከተልም አምልኮታችንን ይደግፍ ነበር።
እስራትና ግዞት
ከተወሰኑ ወራት በኋላ በሶቪዬት ጦር ሠራዊት ውስጥ እንዳገለግል ተመለመልኩ። ሕሊናዬ ስለማይፈቅድልኝ በውትድርና ማገልገል እንደማልችል ገለጽኩላቸው። (ኢሳይያስ 2:4) የሆነ ሆኖ በየካቲት 1951 የአራት ዓመት እስራት ተፈርዶብኝ በተርኖፕል ወደሚገኝ እስር ቤት ተላክሁ። ከጊዜ በኋላ ወደ 120 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ ወደሚገኝ ለቪፍ ወደሚባል ትልቅ ከተማ ተዛወርኩ። እዚያ በእስር ቤት ሳለሁ ብዙ ምሥክሮች ወደ ሳይቤርያ መወሰዳቸውን ሰማሁ።
በ1951 የበጋ ወራት ጥቂቶቻችንን ከሳይቤርያም አልፎ ወደ ሩቅ ምሥራቅ ጠረፍ ጣሉን። በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 11 የጊዜ ሰቅ (time zones) አቋርጠን ወደ 11,000 ኪሎ ሜትር ገደማ ተጓዝን! ወደ አንድ አገር ስንደርስ ለመጀመሪያ ጊዜ ገላችንን እንድንታጠብ የተፈቀደልን ከሁለት ሳምንት በላይ በባቡር ከተጓዝን በኋላ ነበር። ቦታው በሳይቤርያ፣ ኖቮሰቢርስክ የሚገኝ አንድ ትልቅ የሕዝብ ገላ መታጠቢያ ነበር።
እዚያ በጣም ብዙ እስረኞች በተሰበሰቡበት መሃል አንድ ሰው ድምፁን ከፍ አድርጎ “እዚህ ካላችሁት የኢዮናዳብ ቤተሰብ ማን ነው?” ሲል ሰማሁት። በወቅቱ “ኢዮናዳብ” የሚለው ቃል በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸውን ሰዎች ለማመልከት ይሠራበት ነበር። (2 ነገሥት 10:15-17፤ መዝሙር 37:11, 29) ወዲያውኑ ብዙ እስረኞች የይሖዋ ምሥክር መሆናቸውን አሳወቁ። እርስ በርስ ሰላምታ የተለዋወጥነው በከፍተኛ ደስታ ነበር!
በእስር ቤት የነበረው መንፈሳዊ እንቅስቃሴ
በኖቮሰቢርስክ እያለን፣ መውረጃችን ላይ ስንደርስ እርስ በርሳችን የምንተዋወቅበት ኮድ አውጥተን ነበር። ሁላችንም ከቭላዲቮስቶክ ብዙም በማይርቀው በጃፓን ባሕር ላይ በሚገኝ አንድ እስር ቤት ካምፕ ውስጥ ተጨመርን። እዚያ መጽሐፍ ቅዱስ የምናጠናባቸውን መደበኛ ስብሰባዎች አደራጀን። የረጅም ጊዜ እስራት ከተፈረደባቸው ከእነዚህ ጎልማሳና በዕድሜ የበሰሉ ወንድሞች ጋር መሆኔ በእርግጥ በመንፈሳዊ እንድጠነክር ረድቶኛል። ከመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶች የሚያስታውሷቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ተዛማጅ ነጥቦች በመጠቀም በየተራ ስብሰባዎቻችንን ይመሩልን ነበር።
ጥያቄዎች ይጠየቁና ወንድሞች ይመልሱ ነበር። አብዛኞቻችን ባዶ ከሆኑ የሲሚንቶ ከረጢቶች ቁርጥራጭ ወረቀቶች እናዘጋጅና የሚሰጡትን መልሶች እነርሱ ላይ እንጽፍ ነበር። ማስታወሻዎቹን አጠራቅመን አንድ ላይ እንጠርዛቸውና የግል ቤተ መጻሕፍት አድርገን እንጠቀምባቸዋለን። ከሁለት ወራት በኋላ ረጅም እስራት ተፈርዶባቸው የነበሩት ከሳይቤርያ ርቀው በስተ ሰሜን ወደሚገኙ ካምፖች ተላኩ። በዕድሜ አነስ የምንል ሦስት ወንድሞች ደግሞ በአቅራቢያው ወዳለ ከጃፓን 650 ኪሎ ሜትር በማይሞላ ርቀት ላይ ወደሚገኘው የነኮትከ ከተማ ተዛወርን። በዚያም ሁለት ዓመት በእስር አሳለፍኩ።
አልፎ አልፎ የመጠበቂያ ግንብ ቅጂ ይደርሰን ነበር። መጽሔቱ ለብዙ ወራት መንፈሳዊ ምግብ ሆኖ ያገለግለናል። ከጊዜ በኋላ ደብዳቤዎችም ይደርሱን ጀመር። (በወቅቱ በግዞት ከሚገኙት) ቤተሰቦቼ የተላከልኝ የመጀመሪያ ደብዳቤ ሲደርሰኝ አለቀስሁ። ደብዳቤው፣ መግቢያው ላይ የተጠቀሰው መጠበቂያ ግንብ እንደዘገበው የይሖዋ ምሥክሮች መኖሪያ ቤቶች ከተከበቡ በኋላ አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ ሁለት ሰዓት ብቻ እንደተሰጣቸው የሚገልጽ ነበር።
ከቤተሰቤ ተቀላቀልኩ
ተፈርዶብኝ ከነበረው የአራት ዓመት እስራት ውስጥ ሁለቱን ካጠናቀቅሁ በኋላ ታኅሣሥ 1952 ተፈታሁ። ከዩክሬይን ተወስደው በሳይቤርያ ቱሉን አቅራቢያ በምትገኘው በትንሿ የጋዳለይ መንደር እንዲኖሩ ከተደረጉት ቤተሰቦቼ ጋር ተቀላቀልኩ። እርግጥ ነው፣ ከቤተሰቤ ጋር እንደገና አብሬ መሆን መቻሌ ያስደስታል፤ በዚህ ጊዜ ወንዱ ልጄ ኢቫን ሦስት ዓመት ሊሆነው ትንሽ ሲቀረው ሴቷ ልጄ አና ደግሞ ሁለት ዓመት ሊሞላት ተቃርባ ነበር። ሆኖም ያገኘሁት ነፃነት አንጻራዊ ነበር። የአካባቢው ባለሥልጣኖች ፓስፖርቴን የነጠቁኝ ሲሆን የቅርብ ክትትል ይደረግብኝም ነበር። ከሦስት ኪሎ ሜትር በላይ ከቤቴ ርቄ መሄድ አልችልም። ከጊዜ በኋላ በቱሉን ወደሚገኘው ገበያ በፈረስ እንድሄድ ተፈቀደልኝ። በዚያ ከሚገኙ ምሥክሮች ጋር በዘዴ እገናኝ ነበር።
በዚህ ጊዜ አና እና ናዲያ የሚባሉ ሁለት ሴቶች ልጆችና ኢቫንና ኮልያ የሚባሉ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩን። በ1958 ቫሎድያ የሚባል ወንድ ልጅ ወለድን። ከዚያም በ1961 ጋሊያ የምትባል ሴት ልጅ ወለድን።
የኬ ጂ ቢ አባላት (የቀድሞው መንግሥት የደኅንነት ድርጅት) ብዙ ጊዜ እየያዙ በጥያቄ ይመረምሩኝ ነበር። ዓላማቸው ጉባኤውን የሚመለከት መረጃ እንዳወጣ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን ከእነርሱ ጋር ይተባበራል የሚል ጥርጣሬ በወንድሞች ላይ ለማሳደርም ነበር። በመሆኑም ወደ አንድ ጥሩ ምግብ ቤት ይወስዱኝና ከእነርሱ ጋር እየተጫወትኩ እንዳለሁ ፎቶ ለማንሳት ይሞክራሉ። ሆኖም ዓላማቸው ስለገባኝ ኮስተር ብዬ ለመታየት ጥረት አደርግ ነበር። ተይዤ በተለቀቅሁ ቁጥር የሆነውን ሁኔታ ሁሉ ለወንድሞች እነግራቸዋለሁ። በመሆኑም ወንድሞች ታማኝነቴን ተጠራጥረው አያውቁም።
ካምፕ ውስጥ ካሉት ጋር የሚደረግ ግንኙነት
ባለፉት ዓመታት በመቶዎች የሚቆጠሩ ምሥክሮች እየተያዙ እስር ቤት ካምፖች ውስጥ ተጥለዋል። በዚህ ወቅት በእስር ላይ ለሚገኙ ወንድሞቻችን ጽሑፎች በመላክ ከእነርሱ ጋር የማያቋርጥ ግንኙነት እናደርግ ነበር። ይህን እናደርግ የነበረው እንዴት ነው? ወንድሞች ወይም እህቶች ከአንድ ካምፕ ተለቅቀው ሲወጡ፣ ምንም እንኳ ጥብቅ ቁጥጥር ቢኖርም ካምፑ ውስጥ ለቀሩት ወንድሞች ጽሑፍ በድብቅ ማስገባት የሚቻልባቸውን መንገዶች ይነግሩን ነበር። ለአሥር ዓመታት ያህል በእነዚህ ካምፖች ውስጥ ለሚገኙ ወንድሞቻችን ከፖላንድና ከሌሎች አገሮች ያገኘናቸውን የመጽሔትና የመጽሐፍ ቅጂዎች መላክ ችለናል።
ብዙ ክርስቲያን እህቶቻችን የክብሪት ሳጥን በምታክል ትንሽ ነገር ውስጥ አንድ ሙሉ መጽሔት መደበቅ እንዲቻል ሳይሰለቹ በጥቃቅን ፊደላት ጽሑፎች በመገልበጥ ረጅም ሰዓታት ያሳልፉ ነበር! በ1991 በእገዳ ሥር መሆናችን አክትሞ ማራኪ የሆኑ ባለ ሙሉ ቀለም መጽሔቶች ማግኘት ስንጀምር ከእነዚህ እህቶች አንዷ “በቃ ከእንግዲህ እኛን የሚያስታውሰን የለም” ስትል ተናገረች። አባባሏ ትክክል አልነበረም። ምንም እንኳ ሰዎች ሊረሱት ቢችሉም ይሖዋ እነዚህን የመሳሰሉ ታማኝ አገልጋዮች ያከናወኑትን ሥራ ፈጽሞ አይረሳም!—ዕብራውያን 6:10
የመኖሪያ ቦታ መቀየርና አሳዛኝ ገጠመኞች
በ1967 ማብቂያ ላይ በኢርኩትስክ የሚገኘው የወንድሜ ቤት ተፈትሾ ፊልምና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ተገኙበት። ጥፋተኛ ነህ በሚል ተወንጅሎ የሦስት ዓመት እስራት ተፈረደበት። ሆኖም በእኛ ቤት ላይ በተደረገው አሰሳ ምንም ነገር ሳይገኝ ቀረ። ይህም ሆኖ ባለሥልጣኖቹ የእኛም እጅ እንዳለበት እርግጠኞች ነበሩ፤ በመሆኑም ቤተሰባችን አካባቢውን ለቅቆ እንዲሄድ ተገደደ። ወደ 5,000 ኪሎ ሜትር ገደማ በስተ ምዕራብ ተጉዘን ካውካሰስ ውስጥ ወደምትገኘው የኔቪነሚስክ ከተማ ተዛወርን። በዚያ መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት መስጠታችንን ተያያዝነው።
በሰኔ 1969 ትምህርት ቤት ለእረፍት በተዘጋ በመጀመሪያው ቀን አሳዛኝ ነገር ተከሰተ። አሥራ ሁለት ዓመት የሆነው ልጃችን ኮልያ ከፍተኛ ቮልቴጅ ካለው የኤሌትሪክ ትራንስፎርመር አጠገብ ኳስ ሊያመጣ ሲል ኤሌትሪክ ያዘው። ከ70 በመቶ በላይ በሚሆነው የሰውነቱ ክፍል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደረሰበት። ሆስፒታል ውስጥ እያለ ወደ እኔ ዞር አለና “እንደገና አብረን ወደ ደሴቱ መሄድ የምንችል ይመስልሃል?” ሲል ጠየቀኝ። (ለሽርሽር እንሄድበት ስለነበረው ደሴት መናገሩ ነበር።) “አዎን፣ ኮልያ እንደገና ወደ ደሴቱ እንሄዳለን። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሕይወት መልሶ ሲያስነሳህ በእርግጥ ወደዚያ እንሄዳለን” አልኩት። በከፊል ሕሊናውን ስቶ እያለ እንኳ ከጉባኤው ኦርኬስትራ ጋር ሆኖ በራሱ ትራንፔት መጫወት ያስደስተው የነበረውን በጣም የሚወደውን የመንግሥቱን መዝሙር ይዘምር ነበር። ከሦስት ቀን በኋላ በትንሣኤ ተስፋ ላይ የነበረውን ትምክህት እንደያዘ ሞተ።
በቀጣዩ ዓመት 20 ዓመት የሆነው ልጃችን ኢቫን ለውትድርና አገልግሎት ተመለመለ። የውትድርና አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ሦስት ዓመት በእስር አሳለፈ። በ1971 የውትድርና አገልግሎት እንድሰጥ ተመለመልኩና ፈቃደኛ ባለመሆኔ በድጋሚ እንደምታሰር ዛቱብኝ። ጉዳዩ ለወራት ተጓተተ። በመሃሉ ሚስቴ በካንሰር በሽታ በመያዝዋ ከፍተኛ ክትትል አስፈለጋት። በዚህ ምክንያት የእኔ የክስ ፋይል ተዘጋ። ማሪያ በ1972 ሞተች። እስከ ዕለተ ሞቷ ድረስ ለይሖዋ ታማኝ መሆኗን ያረጋገጠች የምተማመንባት የትዳር ጓደኛዬ ነበረች።
ቤተሰባችን በየአገሩ ተበታተነ
በ1973 ኒናን አገባሁ። ምሥክር በመሆኗ ምክንያት አባቷ በ1960 ከቤት አባርሯት ነበር። ካምፕ ውስጥ ላሉት መጽሔት በመገልበጥ በትጋት ይሠሩ ከነበሩት እህቶች መካከል አንዷ ስትሆን ቀናተኛ አገልጋይም ነበረች። ልጆቼም እርሷን በጣም ወደዷት።
ባለሥልጣኖቹ በኔቪነሚስክ የምናደርገው እንቅስቃሴ ስለረበሻቸው ከተማውን ለቅቀን እንድንሄድ አስገደዱን። በዚህ ምክንያት በ1975 እኔ፣ ሚስቴና ሴቶች ልጆቼ ጆርጂያ ውስጥ ወደሚገኘው የደቡባዊ ካውካሰስ ክልል ተዛወርን። በዚሁ ጊዜ ወንዶች ልጆቼ ኢቫንና ቫሎድያ በካዛክስታን ምዕራባዊ ጠረፍ ወደሚገኘው ወደ ጃምቡል ተዛወሩ።
ጆርጂያ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ገና መጀመሩ ነበር። በጥቁር ባሕር ዳርቻ ላይ በሚገኙት በጋግራ እና በሱኩሚ እንዲሁም በአቅራቢያቸው መደበኛ ባልሆነ መንገድ እንሰብክ ነበር። በመሆኑም ከአንድ ዓመት በኋላ ከተራራ በሚወርድ ወንዝ ውስጥ 10 አዲስ ምሥክሮች ተጠመቁ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ባለሥልጣኖቹ አካባቢውን ለቅቀን እንድንወጣ አስገደዱንና ወደ ምሥራቃዊ ጆርጂያ ተዛወርን። በዚያ በግ መሰል ሰዎችን ለማግኘት ያላሰለሰ ጥረት አደረግን፤ ይሖዋም ባረከን።
በትንንሽ ቡድኖች እየሆንን እንሰበሰብ ነበር። እኛ የጆርጂያ ቋንቋ ስለማንችልና አንዳንድ ጆርጂያውያን ደግሞ ሩሲያኛ በደንብ መናገር ስለማይችሉ የቋንቋ ጉዳይ ችግር ፈጥሮብን ነበር። መጀመሪያ ላይ ሩሲያውያንን ብቻ ነበር የምናስጠናው። ሆኖም በጆርጂያ ቋንቋ የሚካሄደው የስብከትና የማስተማር እንቅስቃሴ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕድገት ያሳየ ሲሆን አሁን ጆርጂያ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች አሉ።
በ1979 አሠሪዬ፣ ኬ ጂ ቢ ባሳደረበት ተጽእኖ የተነሳ ካሁን በኋላ በአገሩ ውስጥ እንድቀመጥ እንደማይፈቀድልኝ ነገረኝ። ሴቷ ልጄ ናዲያ የመኪና አደጋ የደረሰባትና ከነልጅዋ የሞተችው በዚሁ ጊዜ ነበር። ከአንድ ዓመት በፊት እናቴ፣ አባቴንና ወንድሜን ትታ ለይሖዋ ያላትን ታማኝነት እንደጠበቀች በኔቪነሚስክ ሞተች። ስለዚህ ወደዚያ ለመመለስ ወሰንን።
ጽናት የሚያስገኛቸው በረከቶች
በኔቪነሚስክ በድብቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማዘጋጀታችንን ቀጠልን። አንድ ወቅት በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ ባለሥልጣኖቹ ጠርተው ሲያነጋግሩኝ፣ በሕልሜ መጽሔቶቻችንን ስደብቅ እንዳየሁ ነገርኳቸው። ይህን ስነግራቸው ሳቁ። እየወጣሁ ሳለ ከእነርሱ አንዱ “ካሁን በኋላ ጽሑፎችህን ስለመደበቅ ከማለም እንድትገላገል እመኝልሃለሁ” አለኝ። በመጨረሻም “በቅርቡ ጽሑፎቹ መጽሐፍ መደርደሪያህ ላይ የሚቀመጡበት እንዲሁም አንተና ሚስትህ መጽሐፍ ቅዱሳችሁን አንግባችሁ እጅ ለእጅ ተያይዛችሁ ወደ ስብሰባዎች የምትሄዱበት ጊዜ ይመጣል” አለኝ።
በ1989 ሴቷ ልጄ አና ገና በ38 ዓመቷ አንጎልዋ ውስጥ በተከሰተ አኒይሪዝም በሚባል በሽታ መሞቷ ጥልቅ ሐዘን ላይ ጣለኝ። በዚያው ዓመት በነሐሴ ወር በኔቪነሚክስ የሚኖሩ ምሥክሮች በፖላንድ፣ ዋርሶ በሚደረግ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ባቡር ተከራይተው ሄዱ። ከሶቪዬት ኅብረት የሄዱትን በሺዎች የሚቆጠሩ ጨምሮ ስብሰባው ላይ 60,366 ሰዎች ተገኝተው ነበር። በእርግጥ ሕልም የምናይ ነበር የመሰለን! ሁለት ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ መጋቢት 27, 1991 ሞስኮ ውስጥ ለይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ድርጅት ሕጋዊ እውቅና ባስገኘው ታሪካዊ ሰነድ ላይ ከፈረሙትና በሶቪዬት ኅብረት ለረጅም ጊዜ የጉባኤ ሽማግሌ ከሆኑት ከአምስቱ አንዱ የመሆን መብት አግኝቼ ነበር!
በሕይወት ያሉት ልጆቼ ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል ላይ መሆናቸው ያስደስተኛል። እንዲሁም አናን፣ ናዲያንና ልጅዋንም ሆነ ኮልያን እንደገና ማግኘት የምችልበት የአምላክ አዲስ ዓለም የሚመጣበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ። ኮልያ በትንሣኤ ሲነሳ ከብዙ ዓመታት በፊት አብረን ጊዜ እናሳልፍበት ወደነበረው ደሴት ልወስደው የገባሁትን ቃል እጠብቃለሁ።
ያ እስኪፈጸም ድረስ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በዚህ ሰፊ አገር ላይ ፈጣን እድገት ማድረጉን ማየት ምንኛ አስደሳች ነው! በእርግጥ ባሳለፍኩት ሕይወት ረክቻለሁ። ይሖዋ ከምሥክሮቹ አንዱ እንድሆን ስላስቻለኝም አመሰግነዋለሁ። “እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ ቅመሱ እዩም፤ በእርሱ የሚታመን ሰው ምስጉን ነው” የሚለውን የመዝሙር 34:8ን እውነተኛነት አምኜ ተቀብያለሁ።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቱሉን ከቤተሰቦቼ ጋር በተቀላቀልኩበት ዓመት
[በገጽ 26 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ከላይ:- በሳይቤርያ ቱሉን ከሚገኘው ቤታችን ደጃፍ ላይ አባቴና ልጆቼ
ከላይ በስተቀኝ:- በመኪና አደጋ የሞቱት ሴት ልጄ ናዲያና ልጅዋ
በስተ ቀኝ:- ቤተሰቡ በ1968 የተነሳው ፎቶግራፍ