የይሖዋን ፈቃድ ፈጽመዋል
ታላቁ ሰው ትሕትና የሚጠይቅ አገልግሎት ሰጠ
ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር የሚያሳልፋቸው የመጨረሻዎቹ ሰዓታት በጣም ውድ እንደሆኑ ያውቅ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሊያዝና ከዚህ በፊት ደርሶበት በማያውቅ ሁኔታ እምነቱ ሊፈተን ነው። ኢየሱስ ከፊቱ ታላቅ በረከት እንደሚጠብቀውም ያውቃል። በቅርቡ በአምላክ ቀኝ የመቀመጥ ክብር የሚጎናጸፍ ሲሆን ‘በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ ከስምም ሁሉ በላይ ያለው ስም’ ይሰጠዋል።—ፊልጵስዩስ 2:9, 10
ሆኖም ኢየሱስ ከፊቱ የሚጠብቀው ሞት ያሳደረበት ጭንቀትም ሆነ ለሚያገኘው ሽልማት ያለው ከፍተኛ ጉጉት ሐዋርያቱ ለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ትኩረት እንዳይሰጥ እንቅፋት አልሆነበትም። ኢየሱስ “እስከ መጨረሻ ወደዳቸው” ሲል ዮሐንስ ከጊዜ በኋላ በወንጌሉ ላይ ዘግቧል። (ዮሐንስ 13:1) ኢየሱስ ፍጹም ሰው ሆኖ ባሳለፋቸው በእነዚህ ወሳኝ የሆኑ የመጨረሻ ሰዓታት ለሐዋርያቱ አንድ በጣም አስፈላጊ ትምህርት አስተማራቸው።
ስለ ትሕትና የተሰጠ ትምህርት
ሐዋርያቱ ከኢየሱስ ጋር ሆነው የማለፍን በዓል ለማክበር በኢየሩሳሌም በአንድ ደርብ ላይ ባለ ክፍል ውስጥ ነበሩ። ከዚህ ቀደም ከመካከላቸው ማን ታላቅ እንደሆነ እርስ በርስ ሲከራከሩ ኢየሱስ ሰምቷቸው ነበር። (ማቴዎስ 18:1፤ ማርቆስ 9:33, 34) በዚህ ጉዳይ ላይ ከእነርሱ ጋር ተወያይቶና አመለካከታቸውን ለማስተካከልም ጥረት አድርጎ ነበር። (ሉቃስ 9:46) አሁን ግን ኢየሱስ ለየት ያለ ዘዴ በመጠቀም ትምህርቱን ጎላ አድርጎ አቀረበ። ስለ ትሕትና በቃል መንገር ብቻ ሳይሆን በተግባርም ሊያሳያቸው ፈለገ።
ኢየሱስ “ከእራት ተነሣ ልብሱንም አኖረ” ሲል ዮሐንስ ጽፏል። “ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፣ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበት ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ።”—ዮሐንስ 13:4, 5
ጥንት በመካከለኛው ምሥራቅ በሞቃታማ የአየር ጠባይ ወቅት አቧራማ በሆኑት መንገዶች ላይ በእግር ሲጓዙ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚያደርጉት ነጠላ ጫማ ነበር። ወደ አንድ ተራ ሰው ቤት በሚገቡበት ጊዜ የቤቱ ባለቤት በሰላምታ ይቀበላቸውና እግራቸውን የሚታጠቡበት ጎድጓዳ ዕቃና ውኃ ያቀርብላቸው ነበር። የሀብታም ሰው ቤት ከሆነ ደግሞ እግር የሚያጥብ አገልጋይ ይኖራል።—መሳፍንት 19:21፤ 1 ሳሙኤል 25:40-42
በደርብ ላይ ባለው ክፍል ውስጥ ግን ኢየሱስና ሐዋርያቱ የማንም እንግዶች አልነበሩም። እግራቸውን የሚታጠቡበት ዕቃና ውኃ የሚያቀርብላቸው አስተናጋጅም ሆነ እግራቸውን የሚያጥባቸው አገልጋይ አልነበረም። ኢየሱስ እግራቸውን ለማጠብ ሲነሳ ሐዋርያቱ አፍረው የሚገቡበት ጠፋቸው። ከመካከላቸው ታላቅ የነበረው ሰው ትልቅ ትሕትና የሚጠይቅ ሥራ አከናወነ!
ጴጥሮስ መጀመሪያ ላይ ኢየሱስ እግሩን ሊያጥበው ሲል እምቢ አለ። ሆኖም ኢየሱስ “ካላጠብሁህ፣ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም” አለው። ኢየሱስ የሁሉንም ሐዋርያት እግር አጥቦ ከጨረሰ በኋላ እንዲህ አላቸው:- “ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ። እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፣ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና።”—ዮሐንስ 13:6-15
ኢየሱስ ይህን ያደረገው እግር የማጠብ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ለመደንገግ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሐዋርያቱ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ወንድሞቻቸውን ለማገልገል የትሕትናና የፈቃደኝነት መንፈስ እንዲያዳብሩ እየረዳቸው ነበር። በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ሐዋርያቱ ኢየሱስ ይህን ያደረገበት ዓላማ ገብቷቸዋል። ከበርካታ ዓመታት በኋላ የግርዘት ጥያቄ ሲነሳ የተፈጸመውን ነገር ተመልከት። ምንም እንኳ ስብሰባው ላይ ‘ብዙ ክርክር’ የተካሄደ ቢሆንም በዚያ የተገኙት ሁሉ ጥሩ ሥርዓት ከመያዛቸውም በላይ አንዳቸው ሌላውን በአክብሮት አዳምጠዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሐዋርያት በቦታው ተገኝተው ስለነበር እኛ እንደምንገምተው ስብሰባውን የመራው ከእነርሱ አንዱ ሳይሆን ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ይመስላል። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ በዝርዝር የሰፈረው ይህ ጉዳይ ትህትና በማሳየት ረገድ ሐዋርያቱ ከፍተኛ መሻሻል ማድረጋቸውን ያሳያል።—ሥራ 15:6-29
እኛ ከዚህ የምናገኘው ትምህርት
ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ትህትናን በተመለከተ ከባድ ትምህርት ሰጥቷል። በእርግጥም፣ ክርስቲያኖች በጣም ተፈላጊ እንደሆኑና ሌሎች ሁልጊዜ እነሱን ሊያገለግሏቸው እንደሚገባ አድርገው ማሰብም ሆነ የላቀ ክርብና ቦታ እንዲሰጣቸው መፈለግ አይኖርባቸውም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ የተወላቸውን ምሳሌ መከተል ይኖርባቸዋል፤ እርሱ “ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።” (ማቴዎስ 20:28) አዎን፣ የኢየሱስ ተከታዮች አንዳቸው ለሌላው እጅግ ትሕትና የሚጠይቅ ነገርም እንኳ ለማከናወን ፈቃደኛ መሆን አለባቸው።
ጴጥሮስ “ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፣ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፣ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ብሎ የጻፈበት ጥሩ ምክንያት ነበረው። (1 ጴጥሮስ 5:5) “ታጠቁ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል የመጣው ብትን ጨርቅ ማሸረጥን ከሚያመለክተው “የአንድ አገልጋይ ሽርጥ” የሚል ትርጉም ካለው ቃል ነው። እዚህ ላይ ጴጥሮስ ጠቅሶ የተናገረው ኢየሱስ ወገቡን በማበሻ ታጥቆ የሐዋርያቱን እግር ስለማጠቡ ሊሆን ይችላልን? በእርግጠኝነት እንደዚህ ብሎ መናገር አይቻልም። ያም ሆነ ይህ ኢየሱስ ያከናወነው ትህትና የሚጠይቅ አገልግሎት በጴጥሮስ ልብ ውስጥ የማይፋቅ አሻራ እንደተወ ሁሉ በሁሉም የክርስቶስ ተከታዮች ልብ ውስጥ ተመሳሳይ ነገር ማከናወን አለበት።—ቆላስይስ 3:12-14