“በባሕር ፍርሃት”
ማታ በጭለማ፣ 276 ሰዎች የጫነች አንዲት መርከብ በሜዲትራኒያን ባሕር ላይ ወደምትገኝ ደሴት ደረሰች። ለ14 ቀናት ያህል መርከበኞቹም ሆኑ መንገደኞቹ በማዕበል ሲናጥ በነበረው ባሕር ላይ ከመንገላታታቸው የተነሳ በጣም ደክሟቸዋል። ጎሕ ሲቀድ፣ የባሕር ወሽመጥ በመመልከታቸው መርከቧን ወደ ባሕሩ ዳርቻ ለማስጠጋት ሞከሩ። ሆኖም የመርከቡ ፊተኛ አካል ሊንቀሳቀስ በማይችል ሁኔታ ከመቀርቀሩም በላይ ሞገዱ የኋለኛውን ክፍል ሰባበረው። ተሳፋሪዎቹ በሙሉ መርከቧን ጥለው በዋና አሊያም ሳንቃዎች ወይም ሌሎች ዕቃዎች ላይ ተንጠላጥለው ወደ ማልታ የባሕር ዳርቻ ለመድረስ ቻሉ። ተሳፋሪዎቹ ብርክ ይዟቸውና ኃይላቸው ተሟጥጦ የሚገፋተረውን ማዕበል በትግል አልፈው ወጡ። ከመንገደኞቹ መካከል ለፍርድ እንዲቀርብ ወደ ሮም እየተወሰደ የነበረው ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ ይገኝበታል።—ሥራ 27:27-44
ጳውሎስ በባሕር ላይ ለሕይወት አስጊ የሆነ ሁኔታ ሲያጋጥመው ይህ በማልታ ደሴት ላይ የደረሰው የመርከብ መሰበር አደጋ የመጀመሪያው አልነበረም። ከጥቂት ዓመታት በፊት “መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረ፤ ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖርሁ” ሲል ጽፏል። አክሎም ‘በባሕር ላይ ሕይወቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች’ ገጥመውት እንደነበረ ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 11:25-27) ጳውሎስ ከአምላክ የተሰጠውን “የአሕዛብ ሐዋርያ” ሆኖ የማገልገል ድርሻውን መወጣት እንዲችል የባሕር ላይ ጉዞ ጠቅሞታል።—ሮሜ 11:13
ለመሆኑ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የባሕር ላይ ጉዞ ምን ያህል ስፋት ነበረው? ክርስትናን በማዳረስ ረገድ ምን ድርሻ አበርክቷል? ምን ያህልስ አስተማማኝ ነበር? ይጠቀሙባቸው የነበሩት መርከቦች ምን ዓይነት ነበሩ? በተጨማሪም መንገደኞች የሚስተናገዱት በምን መልኩ ነበር?
የባሕር ላይ ንግድ ለሮም የነበረው ጠቀሜታ
ሮማውያን የሜዲትራኒያን ባሕርን ማሬ ኖስትሩም ማለትም የእኛ ባሕር ብለው ይጠሩት ነበር። ሮም የባሕር መስመሮችን መቆጣጠሯ እጅግ አስፈላጊ የነበረው ለውትድርና ዓላማ ብቻ አልነበረም። አብዛኛዎቹ የሮም ግዛት ከተማዎች ወይ ወደቦች አሊያም የወደብ ተጠቃሚዎች ነበሩ። ለምሳሌ ያህል ሮም የምትጠቀምበት የባሕር ወደብ በአቅራቢያዋ ባለችው በኦስቲያ የሚገኝ ሲሆን ቆሮንቶስ ደግሞ በሊቆንየምና በክንክራኦስ ትጠቀም ነበር። እንዲሁም የሶሪያ አንጾኪያ በሴሌውቅያ ትገለገል ነበር። በእነዚህ ወደቦች መካከል የነበረው ጥሩ የባሕር መስመር ትስስር ቁልፍ በሆኑ ከተማዎች መካከል ፈጣን ግንኙነት እንዲኖር ከማስቻሉም በላይ የሮም ግዛቶችን ስኬታማ በሆነ መንገድ ለማስተዳደር ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
የሮም የምግብ አቅርቦትም በመርከብ ትራንስፖርት ኢንዱስትሪ ላይ የተመካ ነበር። ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጋ ሕዝብ የነበራት ሮም በዓመት ከ250,000 እስከ 400,000 ቶን የሚጠጋ ከፍተኛ የእህል ፍጆታ ነበራት። ይህን ያህል ብዛት ያለው እህል ይመጣ የነበረው ከየት ነው? ሰሜን አፍሪካ በዓመት ውስጥ ስምንቱን ወራት ለሮም የሚያስፈልገውን ምግብ ስታቀርብ ግብፅ ደግሞ ለተቀሩት አራት ወራት ለከተማዋ የሚያስፈልገውን እህል በበቂ መጠን እንደምታቀርብ ዳግማዊ ሄሮድስ አግሪጳ መናገሩን ፍላቪየስ ጆሴፈስ ጠቅሷል። ለዚህች ከተማ እህል በማቅረብ ሥራ ላይ የተሰማሩ በሺዎች የሚቆጠሩ መርከቦች ነበሩ።
የሮማውያኑን የተንደላቀቀ የኑሮ ዘይቤ ለማርካት ተስፋፍቶ የነበረው የባሕር ላይ ንግድ ማንኛውንም ዓይነት ሸቀጣ ሸቀጥ ያቀርብ ነበር። ማዕድን፣ ድንጋይና እብነ በረድ ከቆጵሮስ፣ ከግሪክና ከግብፅ የሚላክ ሲሆን ጣውላ ደግሞ ከሊባኖስ ይጋዝ ነበር። ወይን ከስሚርና፣ ለውዝ ከደማስቆ እንዲሁም ተምር ከጳለስጢና ይመጣ ነበር። ቅባቶችና ጎማ ከኪልቅያ፣ ሱፍ ከሚሊጢንና ከሎዶቅያ፣ ጨርቃ ጨርቅ ከሶርያና ከሊባኖስ፣ ሐምራዊ ጨርቅ ደግሞ ከጢሮስና ከሲዶን ይጫን ነበር። ማቅለሚያ ከቲያጥሮን፣ መስተዋት ደግሞ ከእስክንድሪያና ከሲዶን ይላክ ነበር። ሐር፣ ጥጥ፣ የዝሆን ጥርስና ቅመማ ቅመሞች ከቻይና እና ከሕንድ ይመጡ ነበር።
ጳውሎስ ተሳፍሮበት ስለነበረውና ማልታ ላይ ስለተሰባበረው መርከብ ምን የሚታወቅ ነገር አለ? መርከቡ እህል የጫነ ሲሆን ‘ወደ ኢጣሊያ የሚሄድ የእስክንድርያ መርከብ’ ነበር። (ሥራ 27:6፣ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) እህል ተሸካሚ መርከቦቹ የግሪካውያን፣ የፊንቃውያንና የሶርያውያን የግል ንብረቶች ሲሆኑ አመራር የሚያገኙትም ሆነ ዕቃዎች የሚሟሉላቸው በእነርሱ አማካኝነት ነበር። ሆኖም የሮም መንግሥት መርከቦቹን ይከራይ ነበር። ታሪክ ጸሐፊው ዊልያም ኤም ራምሴይ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “ከቀረጥ አሰባሰብ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ መንግሥት ራሱ ለዚህ ሰፊ አገልግሎት በሰው ኃይልና በመሣሪያ ረገድ የሚያስፈልገውን ግዙፍ መዋቅር ከማደራጀት ይልቅ ሥራውን በኮንትራት መልክ መስጠቱን ይበልጥ ቀላል ሆኖ አግኝቶታል።”
ጳውሎስ ወደ ሮም የሚያደርገውን ጉዞ ያጠናቀቀው “የዲዮስቆሮስ” ዓላማ ባለው የእስክንድርያ መርከብ ነበር። መርከቡ በኔፕልስ ባሕረ ሰላጤ በሚገኘው አብዛኛውን ጊዜ እህል የጫኑ መርከቦች ጭነታቸውን በሚያራግፉበት የፑቲዮሉስ ወደብ ቆመ። (ሥራ 28:11-13) ፑቲዮሉስ (በዘመናዊ አጠራሯ ፖዞውሊ ትባላለች) ላይ የተራገፈው ጭነት ወይ በየብስ አሊያም በጀልባዎች ተጭኖ በስተ ሰሜን በኩል ጥግ ጥጉን እስከ ታይበር ወንዝ ድረስ ይወሰድና ማዕከላዊ ሮም እንዲገባ ይደረጋል።
ጳውሎስና እርሱን የሚጠብቁት ወታደሮች በጭነት መርከብ የተጓዙት ለምን ነበር? ይህን ጥያቄ ለመመለስ በዚያ ዘመን መንገደኛ ሆኖ በባሕር ላይ መጓዝ ምን ይመስል እንደነበር ማወቅ ይኖርብናል።
በጭነት መርከብ የሚጓዙ መንገደኞች?
በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ የመንገደኞች መርከብ የሚባል ነገር አይታወቅም ነበር። መንገደኞች በንግድ መርከቦች የሚጠቀሙ ከመሆኑም በላይ የመንግሥት ሠራተኞችን፣ ምሁራንን፣ ሰባኪያንን፣ አስማተኞችን፣ አርቲስቶችን፣ አትሌቶችን፣ ነጋዴዎችን፣ ጎብኚዎችንና ተሳላሚዎችን ጨምሮ ማንኛውም ዓይነት ሰው በእነዚህ መርከቦች ተጉዞ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።
እርግጥ፣ በባሕር ዳርቻዎች አካባቢ መንገደኞችም ሆነ ዕቃ የሚያመላልሱ ትንንሽ ጀልባዎች ነበሩ። ጳውሎስ ከጢሮአዳ ‘ወደ መቄዶንያ ለመሻገር’ እንዲህ ዓይነት ጀልባ ተጠቅሞ ሊሆን ይችላል። እንዲያውም ከአንድ ጊዜ በላይ ወደ አቴና ሲሄድና ሲመለስ የተጓዘው በትንንሽ መርከቦች ሳይሆን አይቀርም። ጳውሎስ ከጊዜ በኋላ በትንሿ እስያ የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ በሚገኙ ደሴቶች አድርጎ ከጢሮአዳ ወደ ጳጥራ ባደረገውም ጉዞ ትንሽ ጀልባ ሳይጠቀም አይቀርም። (ሥራ 16:8-11፤ 17:14, 15፤ 20:1-6, 13-15፤ 21:1) በእንደነዚህ ዓይነቶቹ ትንንሽ ጀልባዎች መጠቀም ጊዜ ቢቆጥብም እንኳ ከየብስ ብዙ ርቀው መጓዝ አይችሉም ነበር። ስለዚህ ጳውሎስን ወደ ቆጵሮስና ከዚያም ወደ ጵንፍልያ ያደረሱት እንዲሁም ከኤፌሶን ወደ ቂሣርያ እና ከጳጥራ ወደ ጢሮስ የተጓዘባቸው መርከቦች በጣም ትልቅ እንደሚሆኑ ይገመታል። (ሥራ 13:4, 13፤ 18:21, 22፤ 21:1-3) ጳውሎስ ተሳፍሮበት የነበረውና ማልታ ላይ የመሰበር አደጋ የገጠመው መርከብም ትልቅ ከሚባሉት መካከል ሳይሆን አይቀርም። እንደነዚህ ዓይነቶቹ መርከቦች ምን ያህል ግዙፍ ነበሩ?
አንድ ምሁር ጽሑፎችን ዋቢ በማድረግ የሚከተለው መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል:- “በጥንታዊው ሥልጣኔ ሰዎች ይጠቀሙበት የነበረው በጣም አነስተኛ የሚባለው [መርከብ] ከ70 እስከ 80 ቶን ገደማ ይሆን ነበር። ቢያንስ በሔለናውያን ዘመን በጣም የተለመደው ባለ 130 ቶን ነበር። ምንም እንኳ ባለ 250 ቶኑ ለዓይን የተለመደ ቢሆንም ከመደበኛው መጠን እንደሚበልጥ የተረጋገጠ ነው። በሮም ዘመነ መንግሥት በንጉሠ ነገሥታዊው ግዛት የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ተስማሚ የሆኑት ባለ 340 ቶን መርከቦች ስለነበሩ በጣም ግዙፍ ነበሩ። የመጨረሻዎቹ ትላልቅ መርከቦች 1300 ቶን ይደርሱ የነበረ ሲሆን ከዚህ ትንሽ ከፍ የሚሉም የነበሩ ይመስላል።” በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ በተጻፈ መግለጫ መሠረት አይሲስ የተባለችው የእስክንድሪያዋ እህል ጫኝ መርከብ ከ55 ሜትር በላይ ርዝመት፣ ወደ 14 ሜትር የሚጠጋ ስፋትና ወደ 13 ሜትር ጥልቀት ያለው ዕቃ መጫኛ የነበራት ሲሆን ምናልባትም ከአንድ ሺህ ቶን በላይ እህልና በጥቂት መቶ የሚቆጠሩ መንገደኞች መጫን ትችል ነበር።
በእህል ጫኝ መርከብ የሚጓዙ መንገደኞች ይስተናገዱ የነበረው እንዴት ነው? የመርከቦቹ ተቀዳሚ ተግባር ጭነት ማመላለስ ስለሆነ መንገደኞች የሚታዩት በሁለተኛ ደረጃ ነበር። ከውኃ በስተቀር ምግብም ሆነ ሌሎች ግልጋሎቶች አይቀርብላቸውም። የሚተኙት ወለሉ ላይ ሲሆን ሁልጊዜ ማታ ተዘርግቶ ጠዋት የሚፈርስ ዳስ መሰል መጠለያ ይጠቀሙ የነበረ ይመስላል። ምንም እንኳ መንገደኞች ምግብ ለማብሰል ወጥ ቤቱን እንዲጠቀሙ ቢፈቀድላቸውም ድስትና መጥበሻን እንዲሁም የአልጋ ልብሶችን ጨምሮ ለማብሰያ፣ ለመመገቢያ፣ ለመታጠቢያና ለመኝታ የሚያስፈልጉ ነገሮችን በሙሉ ራሳቸው ማሟላት ነበረባቸው።
የባሕር ላይ ጉዞ —አስተማማኝነቱ ምን ያህል ነበር?
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ መርከበኞች ጉዞ የሚያደርጉት ኮምፓስን ጨምሮ ያለ ምንም መሣሪያ እርዳታ በዕይታ ብቻ ነበር። ስለዚህ ይበልጥ አስተማማኝ የሆነ ጉዞ የሚደረገው በጥቅሉ ከግንቦት ማብቂያ እስከ መስከረም አጋማሽ ድረስ የጠራ ዕይታ በሚኖርበት ወቅት ነበር። ከዚህ ጊዜ በፊትና በኋላ ባሉት ሁለት ወራት ውስጥም ቢሆን ነጋዴዎች መጓዝ ሊሞክሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ በክረምት ወቅት የሚኖረው ጭጋግና ደመና በአብዛኛው የመሬት ድንበር ምልክቶችን እንዲሁም ቀን ላይ ፀሐይን ማታ ደግሞ ከዋክብትን ይጋርድ ነበር። ከኅዳር 11 እስከ መጋቢት 10 ባለው ጊዜ ውስጥ በጣም አንገብጋቢ ወይም አስቸኳይ ጉዳይ ካልተፈጠረ በስተቀር የመርከብ ጉዞ የቆመ ያህል (በላቲን ማሬ ክሎውሰም) ነበር። በወቅቱ መገባደጃ ላይ ጉዞ የሚያደርጉ ሰዎች ክረምቱን በውጭ አገር ወደብ ላይ የማሳለፍ ኪሳራ ይገጥማቸዋል።—ሥራ 27:12፤ 28:11
የመርከብ ጉዞ አደገኛና በወቅቶች ላይ የተመካ ቢሆንም እንኳ በየብስ ላይ ከሚደረገው ጉዞ የተሻለ ጥቅም ያስገኝ ነበር? እንዴታ! የባሕር ጉዞ ጉልበት ከመቆጠቡም በላይ ርካሽና ፈጣንም ነበር። ተስማሚ ነፋስ ሲኖር አንድ መርከብ በቀን ወደ 150 ኪሎ ሜትር ገደማ መጓዝ ይችላል። በእግር ለሚደረግ ረጅም ጉዞ የተለመደው ፍጥነት ግን በቀን ከ25 እስከ 30 ኪሎ ሜትር ነበር።
የባሕር ጉዞ ፍጥነት ሙሉ በሙሉ በነፋስ ላይ የተመካ ነበር ማለት ይቻላል። ከግብፅ ወደ ኢጣሊያ የሚደረገው ጉዞ ተስማሚ በሆነ ወቅት እንኳ ፊት ለፊት ከሚመጣው ነፋስ ጋር የማያቋርጥ ግብግብ ማድረግ ይጠይቃል። በአመዛኙ የሚሠራበት አቋራጭ መስመር በሩድ ወይም በሙራ አሊያም በትንሿ እስያ በምትገኘው በሉቅያ ዳርቻ ላይ በሚገኝ ወደብ አድርጎ ያልፋል። በአንድ ወቅት አይሲስ የተባለችው እህል ጫኝ መርከብ ከእስክንድሪያ ከተነሳች ከ70 ቀናት በኋላ በማዕበል ተመትታና አቅጣጫዋን ስታ ፒሬቭስ ላይ ቆማ ነበር። ከበስተ ጀርባዋ ከሰሜን ምዕራብ የሚነፍስ ነፋስ ሲኖር ከኢጣሊያ የሚደረገው የመልስ ጉዞ ምናልባት ከ20 እስከ 25 ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ ሊጠናቀቅ ይችላል። በየብስ ላይ የሚደረገው ተመሳሳይ ጉዞ ግን ጥሩ የአየር ጠባይ እያለም መሄጃውም ሆነ መመለሻው ከ150 ቀናት በላይ ይፈጃል።
ምሥራቹ ከባሕር ማዶ ወደሚገኙ አገሮች ተዳረሰ
ጳውሎስ ተስማሚ ባልሆነ ወቅት ላይ የሚደረግ የባሕር ጉዞ አደገኛ መሆኑን እንደሚያውቅ በግልጽ መረዳት ይቻላል። እንዲያውም በመስከረም መገባደጃ ወይም በጥቅምት መግቢያ ላይ በመርከብ መጓዝ ተገቢ አለመሆኑን ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “እናንተ ሰዎች ሆይ፣ ይህ ጉዞ በጥፋትና በብዙ ጒዳት እንዲሆን አያለሁ፤ ጥፋቱም በገዛ ሕይወታችን ነው እንጂ በጭነቱና በመርከቡ ብቻ አይደለም።” (ሥራ 27:9, 10) ይሁን እንጂ ኃላፊ የነበረው የጦር መኮንን ምክሩን ችላ በማለቱ ማልታ ላይ የደረሰው የመርከብ አደጋ ሊከሰት ችሏል።
ጳውሎስ ሚስዮናዊ ተልዕኮውን እስካበቃበት ጊዜ ድረስ ቢያንስ አራት ጊዜ የመርከብ መሰበር አደጋ ደርሶበታል። (ሥራ 27:41-44፤ 2 ቆሮንቶስ 11:25) ሆኖም የቀድሞዎቹ የምሥራቹ ሰባኪዎች እንዲህ ዓይነቱ ክስተት ከመጠን በላይ ስጋት አሳድሮባቸው በመርከብ ከመሄድ አላገዳቸውም። የመንግሥቱን መልእክት ለማዳረስ በወቅቱ በነበሩት የመጓጓዣ ዘዴዎች በሙሉ በሚገባ ተጠቅመዋል። እንዲሁም የኢየሱስን መመሪያ በመታዘዝ በሁሉም ቦታ ምሥክርነት ተሰጥቷል። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ ሥራ 1:8) እነርሱ ባሳዩት ቅንዓት፣ የእነርሱን ምሳሌ የተከተሉ ሰዎች ባሳዩት እምነት እንዲሁም በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ አመራር አማካኝነት ምሥራቹ ሰዎች በሚኖሩባቸው ሩቅ የምድር ክፍሎች በሙሉ ሊዳረስ ችሏል።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.