አመስጋኝ ነህን?
በምዕራብ አፍሪካ በሚገኝ በአንድ የሚስዮናውያን ቤት ቴዲ የተባለ አንድ ውሻ ይኖር ነበር። አንድ ሰው አንድ ቁራጭ ስጋ ወርወር ሲያደርግለት ቴዲ ሳያጣጥምና ሳያላምጥ ስጋውን በቅጽበት ይሰለቅጠዋል። ኃይለኛ በሆነው የሃሩር ፀሐይ እያለከለከ ዳግመኛ የሚወረወርለትን ስጋ በጉጉት ይጠባበቃል። ሥጋው ሲያልቅ ዞሮ መንገዱን ይቀጥላል።
ቴዲ ለተደረገለት ነገር ቅንጣት ታክል እንኳ አያመሰግንም። ደግሞም ውሻ እንደመሆኑ መጠን ማንም ከእሱ ምስጋና አይጠብቅም።
አብዛኛውን ጊዜ ከእንስሳት ይልቅ ከሰዎች አመስጋኝነትን እንጠብቃለን። ብዙውን ጊዜ ግን ሰዎች እንደምንጠብቀው አመስጋኞች ስለማይሆኑ ቅር እንሰኛለን። ብዙ ሰዎች ተፈጥሮ የሰጠቻቸውን ሁሉ አፈፍ አድርገው ይወስዱና ተጨማሪ ደግሞ ይፈልጋሉ። ይህም ቢሆን የሚያስደንቅ አይደለም። በመጨረሻው ዘመን ሰዎች የማያመሰግኑ እንደሚሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ ተናግሯል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1, 2
ይሁን እንጂ የአምላክ አገልጋዮች ከዚህ የተለየ መንፈስ ያሳያሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደ እርሱ ላሉት አማኞች “የምታመሰግኑም ሁኑ” በማለት የሰጠውን ምክር ይከተላሉ።—ቆላስይስ 3:15
ይሖዋ አመስጋኝ ነው
አመስጋኝ በመሆን ረገድ ይሖዋ ፍጹም ምሳሌ ነው። ታማኝ አገልጋዮቹን እንዴት እንደሚመለከታቸው ልብ በል። ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ተገፋፍቶ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች እንዲህ በማለት ጽፏል:- “እግዚአብሔር፣ ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው፣ ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለም።”—ዕብራውያን 6:10
ይሖዋ ለታመኑ አገልጋዮቹ አድናቆት እንዳለው የሚያሳዩ በርካታ ምሳሌዎች አሉ። የሆዱን ፍሬ በማብዛት አብርሃምን በመባረኩ ዘሮቹ “እንደ ሰማይ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ” ለመሆን በቅተዋል። (ዘፍጥረት 22:17) ኢዮብ በመከራ ሥር ሆኖ ላሳየው ታማኝነት ይሖዋ ሀብቱን በመመለስ ብቻ ሳይሆን “ሁለት እጥፍ አድርጎ” በመስጠት ለእርሱ ያለውን አድናቆት አሳይቷል። (ኢዮብ 42:10) ይሖዋ ላለፉት ሺህ ዓመታት ከሰዎች ጋር የነበረው ግንኙነት የሚከተለውን አባባል እውነተኝነት የሚያረጋግጥ ነው:- “እግዚአብሔር ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉና።”—2 ዜና መዋዕል 16:9
ፈቃዱን ለማድረግ ለሚፈልጉት ሁሉ አድናቆት ማሳየትና ለጥረታቸው ወሮታ መክፈል የአምላክ ባሕርይ ዋነኛ ገጽታ ነው። ይህን ጉዳይ መገንዘብ ለክርስትና እምነት ወሳኝ ነው። ጳውሎስ “ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ . . . ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና” በማለት ጽፏል።—ዕብራውያን 11:6
ይሖዋ ከመጠን በላይ ጥብቅና ስህተት የሚለቃቅም ቢሆን ኖሮ ማናችንም በፊቱ መቆም አንችልም ነበር። መዝሙራዊው ከረዥም ጊዜ በፊት ይህን ጉዳይ በመገንዘብ “አቤቱ፣ ኃጢአትንስ ብትጠባበቅ፣ አቤቱ፣ ማን ይቆማል?” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 130:3) ይሖዋ ምንም አድናቆት የሌለው ስህተት ለቃቃሚ አምላክ አይደለም። አገልጋዮቹን ከፍ አድርጎ ይመለከታቸዋል፤ ደግሞም አመስጋኝም ነው።
ከልቡ አድናቂ የሆነው ኢየሱስ
ኢየሱስ ክርስቶስ ሌሎች በእምነት ለሚያደርጓቸው ነገሮች አመስጋኝ መሆኑን በማሳየት የሰማይ አባቱን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። በአንድ ወቅት በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ምን ነገር ተከስቶ እንደነበር ተመልከት:- “ዓይኑንም አንሥቶ መባቸውን በመዝገብ የሚጥሉ ባለ ጠጎችን አየ። አንዲትም ድሀ መበለት ሁለት ሳንቲም በዚያ ስትጥል አየና:- እውነት እላችኋለሁ፣ ይህች ደሀ መበለት ከሁሉ ይልቅ አብልጣ ጣለች፤ እነዚህ ሁሉ ከትርፋቸው ወደ እግዚአብሔር መዝገብ ጥለዋልና፤ ይህች ግን ከጉድለትዋ የነበራትን ትዳርዋን ሁሉ ጣለች አለ።”—ሉቃስ 21:1-4
ከገንዘብ አንጻር ከታየ በተለይ ደግሞ ባለጠጋ የሆኑ ሰዎች ከሰጡት መዋጮ ጋር ሲወዳደር ይህ መዋጮ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። በዚያ የነበሩ አብዛኞቹ ሰዎች መኖሯን እንኳ ያስተዋሉ አይመስልም። ኢየሱስ ግን ተመልክቷታል። ያለችበትን ሁኔታ በሚገባ ተገንዝቧል። ኢየሱስ አይቶ አደነቃት።
በሌላ ወቅት ደግሞ ማርያም የምትባል አንዲት ሀብታም ሴት ያደረገችው ነገር ነበር። ኢየሱስ ለማዕድ ተቀምጦ ሳለ በጣም ውድ የሆነ ሽቶ አምጥታ በኢየሱስ እግርና ራስ ላይ አፈሰሰችው። አንዳንዶች ሽቶው ተሽጦ ገንዘቡ ድሆችን ለመርዳት ሊውል ይገባል የሚል ምክንያት በማቅረብ ያደረገችውን ቸርነት ክፉኛ ተቃወሙ። ታዲያ ኢየሱስ ምን ምላሽ ሰጠ? “ተዉአት፤ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? መልካም ሥራ ሠርታልኛለች። እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ፣ እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ ሊሆን ይነገራል” አለ።—ማርቆስ 14:3-6, 9፤ ዮሐንስ 12:3
ኢየሱስ ውድ የሆነው ሽቶ ለሌላ አገልግሎት ሳይውል በመቅረቱ ሃዘን አልገባውም። ማርያም በፍቅርና በእምነት ተገፋፍታ ላደረገችው ደግነት አድናቆቱን ገልጿል። የፈጸመችው ይህ ተግባር ማስታወሻ እንዲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቧል። እነዚህና ሌሎች ታሪኮች ኢየሱስ ከልቡ የሚያደንቅ ሰው እንደነበረ ያሳያሉ።
አንተም የአምላክ አገልጋይ ከሆንክ ንጹሑን አምልኮ ለማስፋፋት የምታደርገውን ጥረት ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ከልባቸው እንደሚያደንቁት እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ። ይህን ማወቃችን ወደ እነርሱ እንድንቀርብና የእነርሱን ምሳሌ በመኮረጅ አመስጋኞች እንድንሆን ያነሳሳናል።
ከሳሹ ሰይጣን
አሁን ደግሞ ፈጽሞ ማመስገን የሚባል ነገር የማያውቀውን ሰይጣን ዲያብሎስን እንመልከት። ሰይጣን በአምላክ ላይ እንዲያምፅ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ የአድናቆት ማጣት ነው።
ሰይጣን በራሱ ባለመርካቱ ምክንያት ያዳበረውን የከሳሽነት መንፈስ ወደ ሌሎችም ማጋባት ጀመረ። በኤደን ገነት የደረሰውን ነገር ተመልከት። ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ፈጥሮ ገነት በሆነ የአትክልት ሥፍራ ካስቀመጣቸው በኋላ ‘ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላላችሁ’ አላቸው። ሆኖም አንድ ዕገዳ ተጥሎባቸው ነበር። አምላክ እንዲህ አለ:- “መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።”—ዘፍጥረት 2:16, 17
ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ሰይጣን የይሖዋን ተአማኒነት ጥያቄ ላይ ጣለ። ሰይጣን ራሱ እንዳመፀ ሁሉ ሔዋንም በይሖዋ ላይ እንድታምፅና ይሖዋ ላደረገላት ነገር ሁሉ ውለታ ቢስ እንድትሆን ለማድረግ ፈለገ። “በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዟልን?” ሲል ጠየቃት። (ዘፍጥረት 3:1) ይህ የሰይጣን አባባል ሔዋን ዓይኗ እንዲከፈትና እንደ አምላክ እንድትሆን ሊያደርጋት የሚችል ውድ ነገር እንደተነፈገች ሆኖ እንዲሰማት የሚያደርግ አንድምታ ያለው ነው። ሔዋን ለይሖዋ የተትረፈረፈ በረከት አመስጋኝ ከመሆን ይልቅ እንዳትበላ የተከለከለችውን ለመብላት መጎምጀት ጀመረች።—ዘፍጥረት 3:5, 6
ይህ እርምጃዋ የሚያስከትለው መዘዝ ግልጽ ነበር። ምንም እንኳ “የሕያዋን ሁሉ እናት” የሚል ትርጉም ያለው ሔዋን የሚል ስም ተሰጥቷት የነበረ ቢሆንም በሌላ መልኩ የሟቾች ሁሉ እናት ሆነች። ሁሉም ሰው ከአዳም ሞት የሚያስከትል ኃጢአት ወረሰ።—ዘፍጥረት 3:20፤ ሮሜ 5:12
አምላክንና ክርስቶስን ኮርጅ
እስቲ በሰይጣንና በኢየሱስ መካከል ያለውን ልዩነት እንመልከት። ሰይጣን “በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ” ተብሎ ተጠርቷል። (ራእይ 12:10) ኢየሱስ “ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።”—ዕብራውያን 7:25
ሰይጣን የአምላክን አገልጋዮች ይከስሳል። ኢየሱስ ግን ጥረታቸውን ያደንቃል እንዲሁም ስለ እነርሱ ያማልዳል። ክርስቲያኖች አንዳቸው የሌላውን መልካም ጎን ለመመልከትና ለማድነቅ በመጣር ክርስቶስን መኮረጅ አለባቸው። እንዲህ በማድረግ አድናቂ በመሆን በኩል ከፍተኛ ምሳሌ ለሚሆነን ለይሖዋ አምላክ አመስጋኝ መሆናቸውን ያሳያሉ።—1 ቆሮንቶስ 11:1
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ማርያም ላከናወነችው መልካም ተግባር አድናቆቱን ገልጿል